• Conversation started Wednesday
 • Brhanu Tekleyared Ze Ethiopia
  Brhanu Tekleyared Ze Ethiopia

  በሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ቅዳሜ ከሰአት በኋላ የሚደረገው የወጣቶች ውይይት ላይ በአቶ ታምራት ታረቀኝ የቀረበ ፅሁፍ ውይይቱ ቅዳሜ በ 21/03/06 9.00 ይቀጥላል

  ለውጤታማ ትብብር ካለፈው መማር

  መግቢያ፣

  የመተባበርን አስፈለጊነትና ጠቀሜታን የማይረዳ የለም፡፡ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ፣ድር ቢያብር አንበሳ ያስር፤ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሀምሳ ሰው ጌጡ ነው ወዘተ የሚሉት አባባሎች የመተባበርን ጠቀሜታ የሚገልጹ ናቸው፡ ፖለቲከኞቹ የግል ፍላጎትና ስሜታቸውን በመግራት የሐገርን ጉዳይ አስቀድመው፣ ከሥልጣን በላይ ትውልድ ተሻጋሪ ለውጥን አልመው፣ ሲሆን ተዋህደው አንድ ሁለት በመሆን ካልተቻለም ተደጋግፈውና ተባብረው እንዲታገሉ በተለያየ መንገድ ጥያቄ ቀርቧል፣ ጩኸት ተሰምቷል ለማስገደድም ተሞክሯል፡፡ (በተለይ በውጪ ባሉ ኢትዮጵያዉያን) የፓርቲ መሪዎቹም ጥያቄውን ለማለዘብና ግፊቱን ለማስተንፈስ እንዲያም ሲል ጊዜያዊ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማትረፍና የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት የይስሙላ መተባበር ሲፈጥሩ፤ የእውነት እየመሰለ እሰየው ተብሎ ተጨብጭቦላቸው፣ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ ነው ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው በጉጉት ሲታዩ ተባበርን ያሉበት መግለጫ ቀለም ሳይደርቅ መለያየታቸውን ሲያረዱን ኖረዋል፡፡ በመሆኑም ወይ አንድ ሁለት ጠንካራ ፓርቲ ሳይኖረን፣ ወይ ጠንካራ የፓርቲዎች ትብብር ሳይኖረን ወደ ምርጫ 2007 እየተቃረብን ነው፡፡

  በዛሬው የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚተውኑት አብዛኛዎቹ ያለፉበትና የአስተሳሰቡ ምርኮኛ የሆኑበት በፖለቲካ መደራጀት የተጀመረበት የደርግ ዘመን ነው፡፡ ሁሉም የማሌ ርዕዩተ ዓለም አራማጅ ነን እያሉ ነገር ግን ተባብሮ መታገላቸው ቢቀር ተከባብረው መቆም ተስኖአቸው እስከ መገዳደል በደረሰ እኩይ ተግባር ርስ በርስ ሲጠቃቁ ሥልጣን ለያዘው ኃይል ጥቃት ራሳቸውን ከማጋለጥ አልፈው ለአገዛዙ ዘመን መራዘም ምክንያት መሆናቸው የትናንት ክንውን ነውና ሊረሳ አይችልም፡፡የመጣው ከሄደው ያልተሻለ ለመሆኑም አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የሀሳብ ልዩነትን በውይይት ለመፍታት ሳይሆን በጉልበት ለማስወገድ የማይሆን ሙከራ ማድረግ፣ ተማምኖ ከመጓዝ ጥሎ ማለፍ መጫወት፣ከዴሞክራሲዊ አሰራር ይልቅ በሴራ ፖለቲካ መካን የትናንቱ አሉታዊ ውርስ ነው፡፡

  ፕ/ር መረራ ጉዲና የተቀዋሚዎችን መተባበር ያለመቻል ሲገልጹ {የተቀዋሚ ፓርቲዎች ችግር የራሳቸው የውስጥ ችግር ነው፡፡ ያፓርቲዎቹ መሪዎች በቀላሉ የመከፋፈል ወጥመድ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ባለመተማመን በሀሜት ይወድቃሉ፡ የሚያገኙትን ትርፍ እንኳን ሳያውቁ ወደ መከፋፈል ወጥመድ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መስራት አልተቻላቸውም} ብለው ነበር፡፡ ( እንቢልታ ጋዜጣ ቅጽ 1 ቁ27) ከተሞከሩ መተባበሮች የአብዛኛዎቹ ሊቀመንበር የነበሩት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ መድረክ ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ ባቀረቡት ባለ ሀያ ገጽ የጥናት ጽሁፍ «ህብረት የሚፈጥሩ ድርጅቶች ከአባል ድርጅቶች ያላቸውን የፖለቲካ መስመር ልዩነትንና አንድነት በተገቢው ባለማወቅና ከዚህም ድክመት የተነሳ የሰፋ የፖለቲካ አቋም ልዩነት የሌላቸው ድርጅቶች በተለያዩ ስሞች አየተጠሩ በአንድ ህብረት ውስጥ አባል ሲሆኑ ይስተዋል ነበር፡፡ይህ ሁኔታ ለከፍተኛ የጊዜና የሪሶርስ ብክነት ሲዳርግና አባላትንና ደጋፊውንም ግራ ሲያጋባ እንደኖረ ይታወቃል፣ከዚህም የተነሳ ትግሉም ተገቢውን ድጋፍ ከህዝቡ እንዳያገኝ ጥርጣሬን ሲያሰፋ ቆይቷል ይላሉ፡፡ አክለውም ህብረት የሚፈጥሩ ድርጅቶች ብቃታቸው አናሳ በመሆኑ የተፈጠሩ ህብረቶች ዓላማቸውን ሳያከናውኑ ይቀራሉ፡፡ በተለይም በአደረጃጀትም ሆነ በአባላት ረገድ ይህ ነው የሚባል ብቃት የሌላቸውና በአንድ ሁለት ግለሰብ መሪዎች አማካኝነት ብቻ ድርጅት ነኝ የሚሉትን ሁሉ በአባልነት ይዞ ለመጓዝ መሞከር ለውጤት እንደማያበቃ …ይገልጻሉ፡፡

  ይህ የፖለተከኞቹ ተግባር ምንም ለውጥ ሳያሳይ እነሆ  ባለፉት ዓመታት እየተሞከሩ ለውጤት ያለበቁ መተባበሮችን የምንቃኘው የመተባበር ጥያቄው የሚነሳበት ወይንም ሥራው የሚጀመርበት ወቅትና ሁሉም የከሸፉባቸው ምክንያቶች ተመሳሳይነት፣ ሁሉም ወይንም አብዛኛዎቹ መተባበሮች ውስጥ የሚታዮት የተወሰኑ ሰዎች መሆን፣ ትንሽም ቢሆን ውጤት ያሳዩት የተከተሉት የተለየ መንገድ ወዘተ እነዚህን ለይተን ትኩረት አዎንታዊውንና አሉታዊውን ተግባር በመለየት ችግሩን ማወቅ የመፍትሄው ግማሽ አካል ነው እንደሚባለው ውጤታማ ህብረት እንዴት ማምጣት እንደምንችል መፍትሄ ለመፈለግ ስለሚበጅ ነው፡፡

  ኢማሌዲህ

  ፓርቲዎች በህግ እውቅና አግኝተው መንቀሳቀስ በጀመሩበት ዘመነ ደርግ አምስት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ማራክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት ኢማሌድህ የሚባል ህብረት መሰረቱ፡፡ የህብረቱ አባል የነበሩት ማርክሲስት ሌኒኒስት ሪቮሉሽን ድርጅት (ማሌሪድ)፣የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት)፣አብዮታዊ ሰደድ፣ወዝ ሊግ፣የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ሁሉም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ቢሆኑም ህብረት የመሰረቱበትን ዓላማ ማሳካት ተስኖአቸው ተበታተኑ፣ በፓርቲዎች ህብረት አንድ ጠንካራ የማሌ ፓርቲ መመስረት አልተቻለም ተብሎ በጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ማእከልነት ኢሰፓአኮ ይመሰረታል ተባለ፣ተግባራዊም ሆነና ከኢሰፓ ሌላ ፓርቲ፣ ከመንግሥቱ ሌላ መሪ ማሰብ የማይቻልበት ስርዓት ተፈጠረ፡፡ ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው እየተባለ፣ አብዮት ልጆቿን ትበላለች መፈክር እየተስተጋባ፣ ቀይና ነጭ የሚል ስም የተሰጠው ሽብር ነግሶ አንድ ትውልድ ተላለቀ፣ በእርስ በርስ ጦርነት ሀገር ታምሶ 17 የስቃይ ዓመታት ታለፈ፡፡ በጊዜው ከነበሩት ፓርቲዎች የአንዱ የወዝ ሊግ መሪ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ይድረስ ለባለታሪኩ በተሰኘው መጽሐፋቸው { በሕዝባችን ፊት ተሰባስበን ችግሮቻችንን ለመፈታት ችሎታው ያልነበረን የኢትዮጵያ ልጆች የኮ/ል መንግሥቱ የግድያ ጉሮኖ ውስጥ ለመጨረሻ ግዜ ተገናኘን፡፡ሁላችንም በተዘዋዋሪ መንገድና ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ሲበዛ ለድርጅት ሲያንስ ለግል የሥልጣን ሽኩቻ ስንባላ ለዚያው ተመሳሳይ ዓላማ የቆሙት ኮ/ል መንግሥቱ በአሸናፊነት ሊበሉን በአንድ ቦታ አሰባሰቡን ፡፡ክቡር በሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ካደረስነው በደል አንጻር ከዚህ የበለጠ ምን የታሪክ ፍርድ ይኖራል፡፡} በማለት ራሳቸውን ነጻ ሳያደርጉ በቁጭት የገለጹት በወቅቱ የነበረውን የፖለቲከኞች ተግባር በግልጽ የሚያሳይ ነው፡ የዛሬውንም የሚገልጽ ነው፡፡የዚህ መሰል ድርጊት በምርጫ 97 ማግስትም ተፈጽሟል፡፡

  በእነዛ ዓመታት ለተፈጸመው አቶ አሰፋ ጫቦ ደጋግመው ይገልጹት እንደነበረው ደረጃው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር በወቅቱ የነበረ ማንም ነጻ ሊሆን አይችልምና የድርሻ የድርሻ ተጠያቂነቱን ወስዶ ስለወደፊቱ ተቻችሎ ተከባብሮና ተባብሮ ለመስራት ከመዘጋጀት ይልቅ ሁሉም ራሱን ነጻ በማድረግ ሌላኛውን ወገን መወንጀልን በመምረጡ ፖለቲካችንን ጤና የራቀው የፖለቲከኞቹን ግንኙነት በጥርጣሬ የተሞላ ይጥሎ ማለፍ ጨዋታና የሴራ ፖለቲካ እንዲሆን አድርጎት ከዛሬ ደርሷል፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ይዞ ጊዜያዊ የሽግግር ፓርላማ ሲያቋቁም ዜጎች ፓርቲ እየመሰረቱ የፓርላማ አባል እንዲሆኑ በፈቀደበትና በጎሳ መደራጀትን ባበረታተታበት ወቅት የተመሰሩቱ ፓርቲዎች ህብረት መፍጠር የጀመሩት ወዲያው ነበር፡፡

  የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኀብረት

  ፣ ይህ ኀብረት የሽግግሩ ፓርላማ አባል የነበሩ ወደ 15 የሚጠጉ በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ጎሳዎች ስም የተደራጁ ፓርቲዎች የፈጠሩት ህብረት ሲሆን ሊቀመንበሩ የሀድያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ ሌሎች የአመራር አባላት ብዙም የሚታዩም የሚታወቁም አልነበረም፡፡ ደኢኅዴህ ራሱ ህብረት ሆኖ የብዙዎች ህብረቶች አባል እየሆነ እስከ መድረክ ድረስ ዘልቆ ከሌላኛው የፕ/ር በየነ ፓርቲ (ሶሻል ሞከራሲ) ጋር ተዋሀደ ተብሎ የከሰመ ነው፡፡

  የጋራ ፖለቲካ መድረክ (ጋፖመ)፣

  በጀነራል ጃገማ ኬሎ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ(ኢብአፓ) በአቶ ኤፍሬም ዘሚካኤል ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እንቅሰቃሴ ቡድን( ኢዳግ) እና ደቡብ ህብረትን በአባልነት ይዞ የተመሰረተ ራሱ ኀብረት ሆኖ የህብረቶች አባል ከመሆን የዘለለ በግሉ ይሄ ነው የሚባል ብዙም እንቅስቃሴ ሳይታይበት መፍረሱም ሆነ መክሰሙ በይፋ ሳይነገር የውኃ ሽታ የሆነ ህብረት ነው፡፡

  የአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት፣

  በ1985ዓምበሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ፓርቲዎችን፣ኀብረቶችን፣የሙያ ማኀበራትንና ግለሰቦችን በአባልነት ይዞ የተመሰረተ ሲሆን ደቡብ ህብረት አባል ፣ፕ/ር በየነ ሊቀመንበር ሆኑ፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤትን የመሰረተው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ነዋሪነታቸው በውጪ ሀገር የነበረ ፖለቲከኞች ወደ ሀገር ቤት መጥተው አንዳንዶቹ ከቦሌ አውሮፕላና ማረፊያ ወደ እስር ቤት ሲወሰዱ ይህን የሰሙ ከመንገድ ተመለሱ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከውጪ መጥተው የታሰሩትን አስፈትተው መሄድ ቻሉ፡፡ አቶ አበራ የማነአብ ለበርካታ አመታት በአስር ለመቆየት በቁ፡፡ ብዙ የተባለለትና ተስፋ የተጣለበት አማራጭ ኃይሎች ብዙም ርቀት ሳይጓዝ አባላቱ ተለይተውት ደቡብ ኅብረት፣ኢዲዩ፣ኢዳግ፣ ብዴህ፣የአገው ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ድርጅት፣የየም ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ብቻ ቀሩ፡፡ ደቡብ ህብረት በአማራጭ ኃይሎች ውስጥ አንደም አስራ አምስትም የመሆኑ ጉዳይ አለመግባባት ፈጥሮ ህብረቱ ሊኖረው የሚገባው አንድ ድምጽ ብቻ ነው መባሉን ፕ/ር በየነ ሊቀበሉ ባለመቻላቸው ስድስቱ ፓርቲዎች ተስማምተው ዶ/ር በየነን በማንሳት የኢዳግ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ክፍሌ ጥግነህነ የአማራጭ ሊቀመንበር አድርገው መረጡ፡፡ አማራጭ የሚጠቀምበት ቢሮም የኢዳግ ስለነበረ ፕ/ር በየነ እንዳይገቡ በመደረጉ አማራጭና ደቡብ ህብረት በአንድ መሪ በአንድ ቢሮ ተጠቃለሉ፡፡ ጉዳዩ በአቤቱታ የቀረበለት ምርጫ ቦርድ እኔ በአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት ሊቀመንበርነት የማውቀው ፕ/ር በየነን ነው በማለቱ፡ አማራጭ ማለት ደቡብ ህብረት ሆነ፡፡ ከውጤቱ መስዋዕትነቱ የላቀው ም/ቤት መቼ፣ እንዴትና ለምን እንደከሰመም ሳይታወቅ ወይንም በይፋ ሳይገለጽ የውኃ ሽታ ሆነ፡፡

  የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ኅብረት፣(ኢተፖድህ)

  ይህ ህብረት በፈረንሳይ ፓሪስ የተመሰረተ ሲሆን ፓሪስ አንድ እና ፓሪስ ሁለት የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡ የሽግግሩ ፓርላማ አባል የነበሩ ፓርቲዎች ፓሪስ አንድ ጉባኤ ላይ ተካፍለው ሲመለሱ የፈጸሙትን ተግባር እንዲያወግዙ ተጠይቀው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከፓርላማ ተባረሩ፡፡ ደቡብ ህብረት የኢተፖድህ አባል ሲሆን ፕ/ር በየነም የሀገር ውስጥ መሪነቱን ይዘው ነበርና ከትምህርት ምኒስቴር ም/ል ምኒስትርነት የተነሱት ፓርቲያቸው ከሽግግሩ ፓርላማ በተሰናበተበት ግዜ ነው፡፡ ኢተፖድህ በውጪ ሀገር የተመሰረተና በሀገር ውስጥ አባላት የነበሩት ቢሆንም ይሄ ነው የሚባል ብዙ ተግባር ሳያከናወን ወይንም ሳይታይለት መፍረሱም በይፋ ሳይነገር ከሰመ፡፡

  የኢዴፓና የኢዳግ ውህደት፣

  የኢዳግ አመራሮች ከጋራ ፖለቲካ መድረክ እስከ አማራጭ ያደረጉት መተባበር ውጤት ባለማምጣቱ ኢዴፓ ገና እንደተመሰረተ ነበር የውህደት ጥያቄ አንስተው ግንኙነት የተጀመረው፡፡ኢዴፓ የተመሰረተው ምርጫ 92 ስድስት ወራት ሲቀሩት ስለነበረና ፓርቲው በምርጫው ለመወዳደር በመወሰኑ የውህደቱን ጉዳይ ለማከናወን ግዜ አልነበረም፡፡ ምርጫው አልፎ ጥቅምት 93 በተካሄደው የኢዴፓ ጉባኤ የተመረጠው አመራር ወዲያውኑ ከኢዳግ ጋር የውህደት ንግግር ጀመረ፡፡ የኢዳግ አመራሮች ለውህደት ተብሎ ለስራ የተነሳሳውን አዲሱን አመራር መበወዝ፣ በህዝብ ውስጥ መታወቅ የጀመረውንም የፓርቲውን ሰም መለወጥ አንፈልግም፣ እኛ ዓላማችን በውህደት ጥንካሬ ፈጥሮ ትግሉን አንድ ርምጅ ወደ ፊት ማስኬድ ነው፣ የሚል አቋም በመያዝ ለፓርቲዎች ውህደት እንቅፋት የሆነውን የሥልጣን ክፍፍልና የፓርቲ ስም ጉዳይ እልባት ሰጡት፡፡ ቀድሞ ከነበሩባቸው ትብብሮች ጋር ሁሉ ያላቸውን ግንኙነትም በመሰረዝ የተሳካ ውህደት ለማድረግ ተቻለ፡፡ በዚህም ቀላል የማይባል ጥንካሬ ለመፍጠር ተቻለ፡፡

  የምክክር መድረክ፣

  በኢተፖድህ ድጋፍ ሰጪነትና በኦብኮ አስተባባሪነት ስድስት ፓርቲዎች (ኦብኮ፣ መአህድ፤ ኢዲዮ፤ ብዴህ፤የም፣¬) በ1992 በኢየሩሳሌም ሆቴል ተሰብስበው የምክክር መድረክ መሰረቱ፣በዚህ ስብሰባ ላይ ያልተጋበዙት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እኛ እያለን ኦብኮ እንዴት አስተባባሪ ይሆናል በሚል ተሰብሳቢዎቹ ከሆቴሉ ሳይወጡ የተቃውሞ መግለጫ አወጡ፡፡ በዚህም ከጅምሩ እንካሰላንቲያ የገጠመው ምክክር መድረክ በ1993 የአዲስ አበባ የወረዳና የቀበሌ ምርጫ በጋራ ለመወዳደር ሙከራ ቢያደርግም የተሳካ ስራ መስራት አልቻለም፡ ይሄ መድረክ ያገናኛቸው መዐህድና ኢዴፓ ግን አንድ የምርጫ ምልክት መርጠው በጋራ መወዳደር በመቻላቸው የምርጫውን ሂደት ነብስ ስለዘሩበት የተደናገጠው ኢህአዴግ የተለመደውንና የሚታወቅበትን ተግባር በመፈጸሙ ፓርቲዎቹ በጋራ የወረዳውን ምርጫ አውግዘው በሳምንቱ ይደረግ ከነበረው የቀበሌ ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ፡፡ የምክክር መድረኩም እድሜ በዚሁ አበቃ፡፡

  ትዴኢ፣

  የተገለጸው የምክክር መድረክ ተልእኮው ሲያበቃ በመድረኩ አማካኝነት ይገናኙ የነበሩት የተወሰኑ የፓርቲ አመራሮች ለምን እንበታተናለን በማለት ግንኙነታቸውን ቀጠሉ፡፡ የመድረኩ አባል ያልነበሩትና መተባበር በሚባልበት ቦታ ሁሉ የማይጠፉት ፕ/ር በየነ ተቀላቀሉ፡፡ ይህ ሂደት ቀጥሎ መአህድ ኢዴፓ ኦብኮ እና ዶ/ር በየነ (በአማራጭ ይሁን በደቡብ ህብረት ስላልታወቀ ነው) ግንኙነቱን አንድ ደረጃ ለማሳደግ የጋራ መግባቢያ ሰነድ አዘጋጁ፡፡ (ሰነዱን የጻፉት የኢዴፓው ቀመንበር ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ ነበሩ፡) ሰነዱ ከመጽደቁ በፊት በአንድ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከመዐህድ፣ኦብኮ አማራጭ ኃይሎችና ኢዴፓ የተሰጠ የሚል መግለጫ ተዘጋጀና ፓርቲዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ለየፓርቲዎቹ ተላከ፡፡ ኢዴፓ ረቂቁን በሥራ አስፈጻሚው ተመልክቶ ማስተካካያ ካደረገ በኋላ በፕ/ር በየነ የአማራጭ ሊቀመንበርነት ላይ ጥያቄ እየተነሳ ባለበት ወቅት አማራጭን የመግለጫው አንዱ ባለቤት ማድረግ እንዴት ይሆናል? ፕ/ር በየነንስ የተቀበልናቸው በአማራጭ ነው በደቡብ ህብረት? ለዚህ ማብራሪያ እንፈልጋለን በማለት ጠየቀ፡፡ ሶስቱ ፓርቲዎች ለጥያቄው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ኢዴፓ እኔ ትልቅ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ነኝ፣ ከጎሳ ፓርቲዎች ጋር አልሰራም፣ አይመጥነኝም ብሏል በማለት ጥያቄውን ወደ ጎን በመግፋት መግለጫውን በሶስቱ ስም አወጡት፡፡ ቀጥለውም በጋራ የተዘጋጀው ሰነድ ላይ አንድ በጎሳ የተደራጁትን የሚመለከት አንቀጽ ብቻ በመጨመር ተፈራርመው ትብብር ለዴሞክራሲ በኢትዮጵያን (ትዴኢ) መሰረትን ብለው መግልጫ አወጡ፡፡ ፕሮፓጋንዳውም 3 ለ1 ቀጠለ፡፡ ምርጫ 97 እየተቃረበ ባለበት ወቅት የፓርቲዎች ጉዳይ ይህ መሆኑ ያሳሰባቸው ዜጎች ሽምግልና ጀመሩ፡፡ ሽምግልናው እስከ ህዳር 95 ቀጥሎ ውጤት ባለመገኘቱ ሽማግሌዎቹ ተስፋ ቆርጠው ማቆማቸው ተሰማ፡፡

  ኢዴኃኀ፣

  ዋንኛ ተዋናዩ ኢህአፓ ነው ተብሎ የተነገረለትና በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶችን ያሰባሰበ ህብረት የመሰረተው ጉባኤ ላይ ከሀገር ቤት የስብሰባው ተሳታፊ የሆኑት ትዴኤን የመሰረቱት ሶስቱ ፓርቲዎችና የተገፋው ኢዴፓ ብቻ ነበሩ፡፡ ፕ/ር በየነና ፕ/ር መረራ በዙር የሀገር ቤቱን ሊቀመንበርነት ሲይዙ ኢዴፓ የጸኃፊነት ቦታ ደረሰው፡፡ በትዴኤ ሰረገላ አብረው አሜሪካ የሄዱት ኢ/ር ኃይሉም ሆነ መዐህድ አንድም ቦታ ሳያገኙ ቀሩ፡፡ በዚህ የተከፋው መኢአድ የጉባኤው ሰነድ ለአባል ድርጅቶች አለመድረሱን ምንያት በማድረግ ልዑካኑ ገና ወደ ሀገር ቤት ሳይመለሱ ተቃውሞውን አሰማ፣ በዚህም አመሰራረቱ እንዳይሆን እንዳይሆን የነበረው ኢዴኃኀ ከጅምሩ ችግር ገጠመው፡፡ ህብረቱ እንደምንም እየተንገታገተ ምርጫ 97 ደርሶ በምርጫው መሳተፍ አለመሳተፍ በሚል ሰፊ ውዝግብ ውስጥ ገባ፡፡ ከውጤት በኋላ ደግሞ ፓርላማ መገባት የለበትም የሚለውን የህብረቱን ውሳኔ ሁለቱ የሀገር ቤት ተተካኪ ሊቀመንበሮች ባለመቀበላቸው የውስጡና የውጪው አመራር ተለያዩ፡፡ ነገር ግን እነማንን ይዘው እንደሆነ ባይታወቅም ፕ/ር በየነ የኢዴኃኀ ሊቀመንበር ተብለው የመድረክ አባል ለመሆን በቅተው ነበር፡፡ ኋላ ግን እንዴትና በምን ምክንያት እንደሆነ ሳይታወቅ በደኢህዴህ ተተክቶ ከመድረኩ የተሰወረ ህብረት ነው፡፡

  የኢዴፓና ኢዲዩ ውህደት፣

  የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኀብረት ፓርቲ (ኢዴህ.ኢዲዩ) መሪው ልዑል ራሰ መንገሻ ስዩም ነዋሪነታቸው በውጪ ሆኖ ሀገር ወስጥ ላለው ቢሮ ኪራይና ለጽ/ቤት ሰራኞች ደመወዝ የሚችሉት ርሳቸው ነበሩ፡፡ በሚመሰረቱ ኀብረቶች ውስጥ አባል ከመሆን ባለፈ በግሉ የሚያሳየው ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ በዚህ የተሰላቹት መሪው የኢዴፓ መሪዎች አሜሪካን በሚሄዱበት ወቅት ምክክር ሲያደርጉ ቆይተው ብዙም ባላወያየ መንገድ ውህደት ተፈጽሞ የሁለቱን ስም በማጣመር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አነድነት ፓርነት (ኢዴአፓ)-በሚል መጠሪያ ወህደት ተፈጠረ ተብሎ ታወጀ፡፡ መሪው ልዑል መንገሻ ስዩም የበላይ ጠባቂ ቢባሉም ደመወዝ የሚከፈሏቸውን ሰድስት ያህል የፓርቲው ቋሚ ሰራተኞች ለኢዴፓ አስረክበው ወደ መኖሪያቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡ ከዛ በኋላ ዘወር ብለውም አላዩት፡፡ ብዙም ሳይቆይ የኢዲዩ ሰዎች ውህደቱን አፍርሰናል ብለው መግለጫ ሰጡ፡፡ ዛሬም ድረስ ፓርቲ እየተባሉ የፓርቲዎች የጋራ መድረክ አባል ሆነው አሉ፡፡ እንደውም ኢፍዴኃግ የሚባል አራት ፓርቲዎች አባል የሆኑበት ግንባር መስርተናል ይላሉ፡፡

  የመኢአድና የኢዴአፓ የውህደት ሙከራ፣

  የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች ለኢዴኃኀ መስራች ጉባኤ አሜሪካ በተገኙበት ወቅት በዛው ነዋሪ የሆኑ የሁለቱም ፓርቲዎች ደጋፊዎች ለውህደት እንደ ችግር ሆኖ ሲነሳ የነበረው መአህድ በጎሳ ላይ የተደራጀ የመሆኑ ጉዳይ አሁን ወደ መኢአድነት ሲቀየር እልባት አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ፕሮግራማችሁ ተመሳሳይ፣ ዓላማና አደራጃጀታችሁ አንድ ሆኖ ሳለ ተለያይታችሁ የምትጓዙት፣ እኛንም በሁለት አቅጣጫ እንድንረዳ የምታስቸግሩን ለምንድን ነው? ከዚህ በኋላ ተዋህዳችሁ አንድ ካልሆናችሁ አንረዳም በማለት የማግባባትም የማስገደድም ስራ ሰሩ፡፡ በእነርሱ አገናኝነትም አመራሮቹ አንድ ሀሳብ ላይ ደረሱና ለየፓርቲዎቻቸው የሥራ አስፈጻሚ በፋክስ ማስታወሻ ላኩ፡፡ ይሄው መነሻ ሆኖ ሶስት ሶስት አባላት ያሉት የውህደት አመቻች ኮሚቴ ተቋቁሞ በፍጹም መግባባት ፕሮግራምና ደንብ አዋህዶ ከጨረሰ በኋላ እዚህ ግባ በማይባል በግለሰቦች የሥልጣን ፍቅር ከሽፎ ህዝብ በተስፋ የጠበቀው ውህደት ሳይሳካ ቀረ፡፡ ከውህደቱ አለመሳካት በላይ አንዱ ሌላኛውን ተጠያቂ ለማድረግ ሲባል ይነዛ የነበረው ፕሮፓጋንዳ እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡

  ኢዴአፓና መድህን፣

  መሰረቱ በውጪ ሀገር የነበረውና በኮ/ል ጎሹ ወልዴ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ መድህን ዴሞክራሲዊ ፓርቲ በያዘው መንገድ መቀጠል በሚሉና የአመጽ ትግል የምንለው አላወጣም ትግላችን ሰላማዊ የትግል ቦታችን ሀገር ቤት ከሕዝቡ መሀል መሆን አለበት በሚሉ ወገኖች ለሁለት ተከፍለ፡፡ ሰለማዊውን መንገድ የመረጠው ወገን ከኢዴፓ ጋር ለውህደት መነጋገር አንደጀመረ የመኢአድና የኢዴአፓ የውህደት ድርደር በመቅደሙ ሶስተኛ ሆኖ ለመግባት አስቦም ስላልተሳካ የሁለቱን ድርድር በቅርበት በመከታተል ውህደቱ ከተሳካ ከውህዱ ፓርቲ ጋር ውህደት ለመፈጸም ወሰነ፡፡ የመአህድ ኢዴአፓ ውህደት ሲከሽፍም መድህን በነገሩ ማዘኑን ለሁለቱ ፓርቲዎች ገልጾ ተወካይ ወደ ሀገርቤት በመላክ በአጭር ግዜ ፕሮግራምና ደንብ የማዋሀድ ስራ ተሰርቶ እስከ ምርጫ 97 ፍጻሜ ድረስ ስያሜውም የሁለቱንም ፓርቲዎች ስም ይዞ ኢዴአፓ መድህን እንዲባል ስምምነት ተደርሶ ውህድ ተፈጸመ፡፡ኢዴአፓ መድህን ቅንጅት ሆኖ ሲከስም የምርጫ 97 ወላፈን ያልነካቸው ኢዴፓ ብለው ቀጠሉ

  መኢአድና ብዴህ

  የትግሉ መጀመሪያም መጨረሻም በአዲስ አበባ ከተማ በ1985 ዓም ያካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የሆነው ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት(ብዴህ) የሚፈጠሩ ህብረቶች አባል እየሆነ ከቆየ በኋላ ተመናምኖ በምርጫ 97 ዋዜማ የቀሩት ጥቂት ሰዎች በውል ባልታወቀና ባልተነገረ መንገድ መኢአድ ወስጥ ገቡ፡፡ የምርጫ 97 ውጤት አይሆኑ ሲሆን ደግሞ ከመኢአድ አባላት ጥቂት ሰዎችን ይዘው በመውጣት ብርሀን ለኢትዮጵያ የተሰኘ ፓርቲ መሰረቱ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ደግሞ መኢአድ በገቡበት መንገድ አንድነት ወስጥ ገቡ፡፡

  ቅንጅት፣

  ትዴኤን በመሰረቱት መኢአድ፣ኦብኮ፣ፕ/ር በየነና በተገፋው ኢዴፓ መካከል የተጀመረውን የ3ለ1 መወጋገዝ ለማስቆምና እርቅ ለመፍጠር ሙከራ አድርገው ያልተሳካላቸው ሽማግሌዎች የመአህድና ኢዴአፓ ውህደት ድርድር ከጫፍ ደርሶ አለመሳካቱና ይህንኑ ተከትሎ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ መወነጃጀል መጀመሩና ይህ የሆነው ደግሞ ምርጫ 97 እየተቃረበ ባላበት ወቅት መሆኑ አሳስቦአቸው እንደገና ሸምግልና ሞከሩ፡፡ ነገር ግን በየፓርቲዎቻቸው ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን በሽምግልና አስታርቆ በምርጫ 97 ጠንካራ ተወዳዳሪ ፓርቲ ማድረሰ እንደማይቻል አረጋገጡ፡፡ ምርጫ 97 ደግሞ እንደ ቀደሙት ምርጫዎች ፓርቲዎች ለመወዳደር ብቻ የሚገቡበት ሳይሆን ለውጤት የሚፎካከሩበት መሆን አለበት የሚል እምነት አሳደሩ፡፡ መፍትሄም ብለው ዓላማው ፓርቲዎችን አቀራርቦ አንድ ጠንካራ ተፎካካሪ ቅንጅት መፍጠር የሆነ ቀስተደመና ኢትዮጵያ ማህበራዊ ንቅናቄ የተሰኘ ፓርቲ መሰረቱ፡፡ አደረጃጀታቸው ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ክፍት የሆነ መቀመጫቸውን በሀገር ቤት ያደረጉ የሚል መስፈርት አውጥተው ይህን የሚያሟሉ አራት ፓርቲዎች መርጠው ቅንጅት ተመሰረተ፡፡ የምርጫው ውጤት ሞት፣ ስደት፣እስራት አካል መጉደል፣ትዳር መፈናቀል፣ ወዘተ አስከተለ፡፡ ከዚህ አሳዛኝ ክንውን በኃላ 21 ወራት ታስረው የተፈቱት መሪዎች ቅንጅትን ሲመሰርቱ ለፈጸሙት ስምምነት፣ ከእስር ሲወጡ ለገቡት ቃል ከምንም በላይ የመረጥናቸው ለቤተ መንግሥት እንጂ ለቃሊቲ ወህኒ ቤት አይደለም በማለት መሪዎቻችን ይፈቱ እያለ 21 ወራት ያለመታከት ለጮኸውና በአመቸው መንገድ ሁሉ ለታገለው በውስጥም በውጪም ለሚኖረው ዜጋ መስዋእትነት አክብሮት ሰጥተው የግል ችግራቸውንና የሥልጣን ጥማቸውን ወደ ጎን በማለት አንድ ሆነው ትግሉን ሊያስቀጥሉ ሲገባቸው የጨው ዘር ሆኑ፡፡ ከመበታተናቸው በላይ መወነጃጀል መዘላለፋቸው በእጅጉ አሳፋሪና ህዝቡን ተስፋ ያስቆረጠ ነበር፡፡

  ኢፍዴኃግ፣

  ፓርቲዎች እንደመሰረቱት ቢነገርም አባላቱ በተናጠልም ሆነ ግንባር የሚባለው በተግባር ቀርቶ በስም ብዙም የሚታወቁ አይደሉም፡፡ በምናራመደው መድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት ፓርቲዎች በተናጠልም ሆነ ግንባርና ህብረት በመፍጠር መንቀሳቀስ ችለዋል ለሚለው ፕሮፓጋንዳ ግን ይነሰም ይብዛም የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ አባል ሆነው እየጠቀሙ ነው፡፡

  መድረክ

  ምርጫ 2002 ሲቃረብ ወደ አመካይ ስፍራ መምጣት በሚል የአቶ ስዬ ስትራቴጂ አራት ፓርቲዎችና ሁለት ግለሰቦች የምክክር መድረክ የሚባል ህብረት መሰረቱ፣ አንድነት እንደተመሰረተም ጥያቄው ቀርቦለት እያጠናው እያለ ሊቀመንበሩ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመታሰሯ አመራሩን የያዙት ሰዎች አንድነትን ያለበቂ ጥናትና ዝግጅት የመድረክ አባል አደረጉት፣ የመድረክ አባላት ዓላማና አደረጃጀታቸው የተዘበራረቀ አንዴ ስምንት ፓርቲዎች ሌላ ግዜ ስድስት ፓርቲዎች ሲሆኑ ከመታየታቸው በላይ በአንድ ሰው የሚመሩ ሶስት ፓርቲዎቸ እየተፈራረቁ አባል ሲሆኑም ተስተውሏል፡፡ ምስረታው ላይ ፕ/ር በየነ አባል የሆኑት በኢዴኃኀ ነበር ቆየት ብሎ ኢዴኃኀ በደኢህዴህ ተቀየረ ሶሻል ዴሞክራሲ የሚባለው ፓርቲያቸውም አባል ሆነ፡፡ የኢዮጵያ ዴሞክራሲዊ አንድነት ንቅናቄ የሚባለው ብዙም የማይታወቅ ፓርቲና የሶማሌ ዴሞክራሲዊ ኃይሎቸ ቅንጅት የተባለው ነጠላ ፓር ይሁን የፓርቲዎች ተምረት በውል የማይታወቅ ፓርቲ ከመድረክ መውጣታቸውን አወጁ፡፡ ከሶስት ኣመት በኋላ ደግሞ ሁለቱበኦሮሞ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ሲሆኑ የፕ/.ር በየነ ሁለት ፓርቲዎችም ተዋሀዱ፡፡ በዚህ አወንታዊና የሚደገፍ ርምጃ አማካኝነት አሁን የመድረክ አባላት አራት ፓርቲዎች ማለትም አንድነት ፣አረና እና ሁለቱ በውህደት የተፈጠሩ ፓርቲዎች ናቸው፡፡

  ነገር ግን የአንድነት የመድረክ አባልነት አይጥሉት አያንጠለጥሉት ሆኗል፡፡ መድረክም መጠናከር እንደተሳነው ሲታይ አራት ዓመታት በከንቱ ባክነዋል ለማለት ያስደፍራል፡፡

  33ቱ፣

  ለመገናኘታቸው ምክንያት የሆነው ምርጫ 2005 የከተማና የአካባቢ ምርጫ ሲሆን አብዛኛዎቹ ስማቸውም ሆነ መሪያቸው በውል የማይታወቅ ነው፡፡ ዋና ዋና የሚባሉት መኢአድ አንድነት ሰማያዊና መድረክ( አንድነት የመድረክ አባል ሲሆን ሰላሳ ሶስቱ ውስጥ ደግሞ ሁለቱም አባል መሆናቸው የአደረጃጀት መመሰቃቀልን ያሳያል) አባል ነበሩ፡፡ ምርጫ ቦርድ የግዜ ሰሌዳ አውጥቶ አጽድቁልኝ ያለበትን የምርጫ 2005 ሂደት በጋራ መቃወማቸው፣ሁሉም በምርጫው ላለመሳተፍ መወሰናቸውና በምርጫው ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ለማድረግ መብቃታቸው በበጎ ጎን የሚጠቀስ ሲሆን ልንተባበር ነው ቅንጅት ልንፈጥር ነው ወዘተ የሚለው ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የዘለለ አልፈየደም አይፈይድምም፡፡ በተለይ ደግሞ ከ10 ያላነሱ ከስብስቡ ወጥተው ሳለ 33 የሚለውን ቁጥር መጠሪያ አድርጎ መጠቀም ከተግባር ይልቅ ፕሮፓጋንዳ፣ ከብቃት ይልቅ የቁጥር ጨዋታ የተቀዋሚው ስራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

  አስሩ፣

  ይሄ ደግሞ በምርጫ 2007 ዋዜማ የተሰማ ነው፡፡ እነማን እንደሆኑ ያልታወቁ፣ለምን ዓላማ እስከምን ድረስ እንደሚተባበሩ ያልተገለጸ ከመሆኑ አንጻር ዛሬም እንደትናንቱ ተባብረናል ከሚል ፕሮፓጋንዳ ተጠቃሚ መሆንን ያለመ ይመስላል፡፡ የ33ቱም የ10ም አጋፋሪ ሆነው የሚታዩትና ፉክክር የገጠሙ የሚመስሉት አንድነትና መኢአድ ደግሞ ለብቻችው ለውህደት እየተነጋገርን ነው ሲሉ መስማት ጀምረናል፡፡

  አንድነትና መኢአድ፣

  ሁለቱም ፓርቲዎች የ33ቱ አባል ከመሆን በላይ በስብስቡ ውስጥ የበላይነት ለመያዝ የሚታገሉ መሆናቸው ከድርጊት ከንግግራቸው በግልጽ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድነት የመድረክ አባል ሆኖ በይፋ ለመውጣት ለመቀጠል ተቸግሮ የሚገኝ ሲሆን መኢአድ ደግሞ የአስሩ ስብስብ አባል ከመሆኑም በላይ የአንበሳውን ድርሻ ለመያዝ እየተጣጣረ ነው፡፡ በዚህ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ለውህደት እየተነጋገርን ነው ማለት ይዘዋል፡፡ ለጊዜው ሆኖ ለማየት ያብቃን ማለት ይበቃል፡፡

  ውጤታማ መተባበር እንዴት?

  ተባብሮ መስራት ከተቻለም ከቅንጅት እስከ ውህደት ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊነቱ ተቃውሞ የማይነሳበት የዘወትር የህብረተሰቡ ጥያቄ ነው፡፡ ቅንነቱ፣ከራስ በላይ ማሰቡ፣ለፍሬው ተጠቃሚነት ሳይሆን ትግሉ ለሚጠይቀው መስዋዕትነት ራስን ማዘጋጀት ካለ ተግባራዊ ማድረግ የማይቻልም አይደለም፡፡ ነገር ግን ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ሀያ አመት ሙሉ ከጅምር አልፎ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ተባበሩ የሚለው ጥያቄም ሆነ ካልተባበርን ከፊት ለፊታችን ያለውን ተራራ መግፋት አንችልም የሚለው የፕሮፓጋንዳ ዋይታ ዛሬም አለ፣ ይሁን እንጂ ጥያቄውን የሚያቀርቡት ሶስተኛ ወገኖችም ሆኑ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የእንተባበርን ነጋሪት የሚጎስሙት ፖለቲከኞች መተባበሩ እንዴት፣ በምን ደረጃ በእነማን መካከል ወዘተ ሊፈጸም እንደሚችል በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ ተአማኒና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አቅጣጫ አያመላክቱም፡፡

  ጉዳዩ ደግሞ አንድ ሁለት ፓርቲዎች ተጠናክረው እንዳይወጡ ወይንም ከምር የታሰበበት መተባበር እንዳይኖር እያደረገ በመሆኑ በተለይ ደግሞ ከምርጫ 2007 ጊዜ መቃረብ አንጻር ፈጣን መፍትሄ የሚያሻው ጥያቄ ነው፡፡ በምርጫ ዋዜማ ምኒልክን ቤተ መንግሥትን አሸጋግረው እያዩ ካልተባበርን ምርጫውን አናሸንፍም በሚል የሚታሰብ መተባበር፣ከፊታችን ያለውን ተራራ ተጋግዘን እንናደው ቀሪው እዛ ሲደረስ ይታሰብበታል ተብሎ የሚጀመር ግብ አልባ አብሮ መስራት፣እስከ ዛሬ ከተመለከትናቸው የተለየ ውጤት አያስገኝም፡፡ምክንያቱ ደግሞ ገልጽ ነው፣መተባበሩ የተፈለገው ተደጋግፎ ጠንካራ ኃይል ሆኖ ለመውጣት ሳይሆን አንዱ በአንዱ ላይ በመደገፍ፣ ደካማው በጠንካራው ላይ በመንጠላጠል ስልጣን ማግኘትን ያለመ ስለሚሆን ህብረትም ይባል ውህደት ድርድር ሲካሄድ ሁሉም በልቡ የሚያስብና የሚያቅደው ሰለ መተባበሩ ውጤታማነት ሳይሆን የመተባበሩን መሰላል ተጠቅሞ ስለሚያገኘው ስልጣን በመሆኑ ጅምሩ አይሰምርም፣ እንደምንም ጥርስ ተነክሶ ይሉኝታ ተፈርቶና የህብረተሰቡ ቁጣ ታስቦ እስከ ደምጽ መስጫው እለት አብሮ መዝለቅ ቢቻል እንኳን በሚገኘው ውጤት ጸብ ይነሳል፡፡የመድረክ አንድ ወንበር ያስነሳውን ውዝግብ ማስታወስ ብቻ ይበቃል፡፡

  ስያሜው ምንም ይሁን ምን የመተባበሩ ዓላማ በምርጫ ለውጥ ለማምጣትና አስተማማኝ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሰረት ለመጣል የሚያስችል ጠንካራ ተፎካካሪ ኃይል መሆንን ያለመ ሳይሆን ራስን ለሥልጣን ማብቃትን መነሻ ያደረገ ሲሆን ሁሉም በአደባባይ ከሚናገረው በተቃራኒ ጥረቱ ለየግሉ ፍላጎት መሳካት ይሆናል፡፡ ቅንጅት፣ ግንባርም እንበለው ውህደት ደግሞ ሥልጣን ናፋቂዎችን ሁሉ ለሚፈልጉት ሥልጣን ሊያበቃ ስለማይችል ነገሩ ሁሉ አንድ ርምጃ ሳይሄድ ይሰነካከላል፡በአዋጅ የተነገረው መተባበር በመወነጃጀልና በመዘላለፍ ይፈርሳል፣አልያም የውኃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ ፖለቲከኞቻችን ከትናንት የማይማሩ፣ በደረሰባቸው የማይቆጩ፣ ባደረሱት የማይጸጸቱ በመሆናቸውም የመተባበርን ዜማ እያዜሙ አለመተባበርን በተግባር እያሳዩ እነሆ ምርጫ 2007 ዋዜማ ደርሰዋል፡፡

  ሕዝቡ ለውጥ ናፍቋል፣ አገዛዙ ከፍቷል ተፎካካሪው ባለበት ይረግጣል ፣ታዲያ ምን ይበጃል!! መተባበር በግለሰቦች ፍላጎት ላይ የሚንጠለጠል ሳይሆን በፓርቲዎቹ መካከል የሚፈጸም መሆን አለበት ለዚህ ደግሞ ፓርቲዎች ብሄራዊ መግባባት፣ እርቅ፣ ውይይት፣ እያሉ ራሳቸው በውስጣቸውና እርስ በርሳቸው ያልፈጸሙትን ኢህአዴግን መጠየቁን አቁመው በመካከላቸው መቀራረብና መደጋገፍ ሊያመጣ የሚችል መተማመን ላይ የሚያደርሳቸው ውይይት ቀዳሚ ሥራቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ከአብዛኛዎቹ የፓርቲ መሪዎች የአሮጌው አስተሳሰብ ምርኮኝነትና ከሚፈለገው አስተማማኝ የዴሞክራሲ መሰረት አንጻር ወደ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ቅድመ ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ 

  1. መነጽሩን ወደ ራስ ማዞር፣ የሌላኛውን ህጸጽ በአደባባይ አጉልተውና ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለመናገር የሚደፍሩትን ግማሽ ወኔ ተጠቅመው ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ውይይት በየቤታቸው በማካሄድ የመጡበትን መንገድ መለስ ብለው በመቃኘት ድክመት ጥንካሬያቸውን መፈተሽ፣

  2. የሀሳብ ልዩነትን ማክበር፣ ሀ–በአንድ ፕሮግራም ማመንና በአንድ መተዳደሪያ ደንብ መገዛት እንጂ ሁሉም አባል አንድ አይነት አስተሳሰብ እንዲኖረው እይጠበቅምና እስከ ዛሬ የቆየው የተለየ ሀሳብ ያላቸውን የመፈረጅና በአሉባልታ ለማዳከም የመጣር በሽታ ተወግዶ፣የሀሳብ ልዩነት ለመሻሻል ያለው ጠቀሜታም ግንዛቤ አግኝቶ የሚከበርበትና የሚዳብርበት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ባሕል መፍጠር፣ ለ-ከመነሻው የተለያዩ ፓርቲዎች መመስረታቸው አንድ የማያደርጉዋቸው ነገሮች በመኖራቸው ነውና በደፈናው ተባብረን እንስራ ከማለት፣ አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ ከመግባት፣ በጥላቻ ስሜት ከመተያየት ወጥቶ የተለያዩ ፓርቲዎች ለመሆን ያበቃቸውን የፕሮግራም የመርህ የመሪዎች ፍላጎት ወዘተ በቅጡ መመርመር ፣ልዩነትን እያጠበቡ አንድነትን ማስፋት፣ መሰረታዊ በሆኑ ልዩነቶቸ ላይ ላለመግባባት ተግባብቶ በመከባበር ለመቀጠል የሚያስችል ስምምነት መፍጠር፡፡

  3. ተከታይ ሳይሆን አባል ማብዛት፣አቤት፡ ወዴት፡ እሺ፡ እያለ ለአመራሮቹ የሚሰግድ ተከታይ ሳይሆን ፕሮግራሙን ተረድቶ ለተፈጻሚነቱ ለመታገል የቆረጠ፣ የመተዳደሪያ ደንቡን አውቆ ለመገዛት የወሰነ አባል ነው የሚያስፈልገው፡፡ ይህ አይነቱ አባል የሰጡትን ሁሉ እንደወረደ የሚቀበል፣ የነገሩትን ሁሉ ትክክል የሚል፣ የአመራሮች ተከታይ ሳይሆን ለምን? ማን? መቼ? ወዘተ እያለ የሚጠይቅ የባለቤትነት ስሜት ያለው ስለሚሆን ለፓርቲ እድገት ብሎም ለሚፈለገው አብሮነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡

  4. ምክር ቤትን ማጠናከር፣ እጅ የሚያወጣና የሚያጨበጭብ ሳይሆን ሀሳብ የሚያፈልቅ ተከራክሮ የሚወስን፣ግለሰብ መሪዎችንም ሆነ ሥራ አስፈጻሚውን የሚሞግት ምክር ቤት ማቋቋም፡፡

  እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ከተቻለ ስምና የምርጫ ቦርድ የምዝገባ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ካለው ስብስብነት ወደ ፓርቲነት ማደግ ተቻለ ማለት ነው፡፡ ለመተባበር የሚደረገው ውይይትም በመሪ ግለሰቦች ፈቃድና ፍላጎት በእነርሱው ስሜት የሚደረግ ከመሆን ወጥቶ ፓርቲ ከፓርቲ ይሆናል፡፡ በግለሰቦች መካከል የሚደረግ ውይይት ታሳቢ የሚያደርገው ሥልጣንን ሲሆን በፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት መነሻውም ሆነ መድረሻው ሀገራዊ ጥቅምን ታሳቢ የሚያደርግ በመሆኑ ሁለተኛው የተሻለ ውጤት ይኖረዋል፡፡

  በፓርቲ መካከል ውይይት ሲባል ተወክለው የሚነጋገሩት ግለሰቦች መሆናቸውን በመዘንጋት አይደለም፡፡ፓርቲው ለውይይት ለሚወክላቸው ሰዎች መመሪያ ሰጥቶ የሚልክ፣ ሂደቱንም በቅርብ የሚከታተል፣ በየደረጃውም ሪፖርት እየዳመጠ የሚወስን በመሆኑ መሪ ግለሰቦች በራሳቸው ፍላጎትና መንገድ መሄድ የሚችሉበት ልቅነት ስለማይኖር ነው፡፡ አጀንዳውም እንተባበር ሳይሆን አስተማማኝ የዴሞክራሲ መሰረት ለማኖር 20 ዓመት ሙሉ ለምን አቃተን? አሁንስ እንዴትና በምን ሁኔታ ብንስራ ገቢራዊ ልናደርገው እንችላለን? የሚል ሆኖ ተባብሮ መቆም፣ ግንባር መፍጠር፣ ውህደት መመስረት፣ወዘተ የሚለው ከውይይቱ ውጤት የሚገኝ መሆን አለበት፡፡

  ይህ ሲባል አለ ምክንያት አይደለም፣ አጀንዳው መተባበር ሲሆን ሁሉም የራሳቸውን ቦታ ወስነው ያንን ለማግኘት የሚያስችላቸውን ስልት ቀይሰው የሚፈልጉትን የማያገኙ ከሆነም ግንኙነቱን የሚያፈርሱበትን ስልት አቅደው ፓርቲያቸውን በጋሻነት ለመተቀም ተዘጋጀተው የሚቀርቡ በመሆኑ ነው፡፡ ግለሰብ መሪዎች ፓርቲ ሆነው በሚወስኑበትና እጅ የሚያወጡ ሰዎች ብቻ በተሰባሰቡበት ወይንም በበዙበት ስመ ምክር ቤት እያስወሰኑ የሚሰሩበት ሂደት ካልተለወጠ ወደ ውይይት መምጣት አይቻልም፣ በጥረትና በግፊት ወይይት ቢጀመርም መሪዎቹ የሚገናኙት በጥሎ ማለፍ ጨዋታ አሸናፊ ሆነው ስለሚወጡበት እያሰቡ በመሆኑ በግልጽ ከልብ በአጀንዳዎች ላይ መነጋገር አይቻላቸውም፡፡ በፊት ለፊት ከሚናገሩት የማስመሰያ ቃል በሰተጀርባ በሚያካሂዱት የሽምቅ ውጊያ ውይይቱ ይደናቀፋል፣ ነገሩ ሁሉ በጥርጣሬ ተጠባብቆ የመኖር የአይጥና የድመት ፍጥጫ አይነት ይሆናል፡፡ ስብስቦች ወደ ፓርቲነት ካደጉ የግለሰቦች የጥሎ ማለፍ ጨዋታም ሆነ በፓርቲ ስም ተከልለው የፓርቲ ጥቅም እያሉ የፓርቲ ካባ ለብሰው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያካሂዱት የሽምቅ ውጊያ ሊቀጥል ስለማይችል ለውይይት በር ይከፈታል፡ ለአብሮነት መሰረት ይጥላል፣ መተማመንን ያጠናክራል፡ ደረጃ በደረጃም ህብረት ግንባር ውህደት ለመፍጠር ያስችላል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ አፄ ምኒልክ የሞቱበትን አንድ መቶኛ ዓመት በዓል ሊያከብር ነው።

ሰማያዊ ፓርቲ አፄ ምኒልክ የሞቱበትን አንድ መቶኛ ዓመት በዓል እንደሚያከብር የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት አስታውቋል። አፄ ምኒልክ የሞቱበት ዕለት ታህሳስ 3 ቀን በመሆኑ ዕለቱን የፓናል ውይይት፣ ጉብኝትና ኤግዚቪሽኖች በማዘጋጀት በአሉን በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ለማክበር እየተዘጋጁ መሆኑን አስታውቋል።  በዕለቱ በተመሳሳይ ቀን ያለፉት ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ አብረው የሚታሰቡ መሆኑን የፓርቲው አስታውቋል። ፓርቲው ወደፊትም “የታላቋ ኢትዮጵያ ቀን” በሚል በየሶስት ወሩ ቋሚ ፕሮግራም እንደሚያዘጋጅ ጨምሮ አስታውቋል። አፄ ምኒልክ እና ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የሚዘከሩበት ቀን የዚሁ የታላቋ ኢትዮጵያ ቋሚ ፕሮግራም አካል መሆኑንም አመልክቷል።  አፄ ምኒልክንም ሆኑ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴን መዘከር ያስፈለገው የሀገሪቱን አንድነት ጠብቀው ከማቆየት ባሻገር በሀገሪቱ ዘመናዊነት፣ ቴክኖሎጂ መስፋፋትና እድገት ፈርቀዳጅ በመሆናቸው እንዲሁም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች በነጮች ላይ ድል እንዲጎናፀፍ ያደረጉ ገናና መሪዎች በመሆናቸው ነው ብሏል።

ብርሃኑ ተ/ያሬድ

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ