ማን ያውራ የነበረ …በአፈወርቅ በደዊ ለጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ የተሰጠ ምላሽ

ማን ያውራ የነበረ …በአፈወርቅ በደዊ ለጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ የተሰጠ ምላሽ

ማን ያውራ የነበረ …

(ይህንን አጭር ፅሑፍ ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ መለዮ አልባው ምሁር ብሎ ለሰየማት ፅኁፉ መረጃ ትሆን ዘንድ ለሰንደቅ ጋዜጣ ልኬው የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ጋዜጣው ላይ አልታተመም፡፡)

አበው ሲተርቱ “ማን ያውራ የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” ይላሉ፡፡ እኔም ዛሬ ይህንን አባባል በመጠቀም በባለፈው እሮብ ታህሳስ 09 ቀን 2006 ዓ.ም በሰንደቅ ጋዜጣ 9ኛ አመት ቁጥር 432 እትም ላይ ያነበብኩት ፅሑፍ በእለቱ በቦታው ፕሮግራሙን ሲያስተባብሩ ከነበሩ ወጣቶች መካከል ስለነበርኩ ጋዜጣው መረጃው በአግባቡ አለመጠቀሙን ተገንዝቤያለው፡፡

በቅድሚያ በዚህ አጋጣሚ ፀሐፊውን ወይም የጽሑፉን ባለቤት ለማድነቅ እና ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ ይህንንም የምልበት ዋነኛው ምክኒያት ጸሐፊው በተለያዩ ጊዜያት የሚፅፋቸው እና ለአንባቢያን የሚያቀርባቸውን አስተማሪ እና መረጃ ሰጪ ጽሁፎች ሙያዊ ብቃቱ የሚያሳዩ ለመሆኑ ምስክር ስለሆኑ ከዚህ በተጨማሪም እውነትን ለህዝብ ለማድረስ ጥረት የሚያደርግ ጋዜጠኛ ማግኘት ከባድ በሆነበት በዚህ ወቅት እንደዚህ አይነቱን ሙያዊ ብቃት ያለው ጋዜጠኛ ሲገኝ ማመስገንም ሆነ ማበረታታትም ተገቢ ነው፡፡ ዛሬ የሃገራችን ችግር የሆኑት ጋዜጠኞች ሳይሆኑ የጋዜጠኝነት ለምድ የለበሱ እና ጃንጥላ የተጠለሉ ፕሮፖጋንዲስቶች ናቸው ብዬ በግሌ ስለማምን ይህንን ወጣት ስራውን በአግባቡ ለመስራት የሚያደርገውን ጥረት በድጋሜ ለማድነቅ እወዳለሁ፡፡

ይህንን ካልኩ ዘንዳ ከሰው ስህተት ከብረት ደግሞ ዝገት ስለማይታጣ ከዚህ ከማከብረው እና ከማደንቀው ጋዜጠኛ በግሌ ስህተት ነው ብዬ የማምነው ነገር ስላገኘው ለጋዜጣውም ሆነ ለጋዜጠኛው ካለኝ መውደድ እና ክብር የተነሳ በአደባባይ እውነታውን ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡

እንደሚታወቀው ሰማያዊ ፓርቲ የአጤ ምኒልክን 100ኛ የሙት አመት ምክኒያት በማድረግ ከታህሳስ 03 እስከ 06 ቀን 2006 ዓ.ም በፓርቲው ጽ/ቤት ደማቅ ፕሮግራም ማዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ለቀናት የቆየ ደማቅ እና ልዩ ፕሮግራም ለማሳረጊያ ይሆን ዘንድ እሁድ ታህሳስ 06 ቀን 2006 ዓ.ም የፓናል ውይይት አዘጋጅቷል፡፡ በዚህም የፓናል ውይይት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲገኙ በኤሌክትሮኒ ሚዲያ ጥሪ የተላለፈላቸው ሲሆን የጽሑፍ አቅራቢዎች እና የክብር እንግዶች በጸሁፍ ጥሪ ተላልፎላቸዋል፡፡ ከነዚህም የክብር እንግዶች መካከል ጋዜጠኞች መረጃን ለህዝቡ የሚያደርሱ የህዝብ ጆሮ እንደመሆናቸው ፓርቲው የአክብሮት ጥሪውን አስተላልፎላቸዋል፡፡

ሁሉም እንግዶች ቦታቸውን እንደያዙ የእለቱ ጽሑፍ አቅራቢዎች ማለትም ዶ/ር ዳንኤል አጥናፉ፣ አቶ ታዲዎስ ታንቱ እና ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የተዘጋጀላቸውን ቦታ ከያዙ በኋላ ፕሮግራሙ እንደታሰበው የታዳሚውን ቀልብ እንደያዘ ቀጠለ፡፡

በአቀራረብ ቅድመ ሁኔታው መሰረት ዶ/ር ዳንኤል አጥናፉ ስለ አጤ ምኒልክ ህይወት እና አስተዳደር አቅርበው እንደጨረሱ አቶ ታዲዎስ ታንቱ ስለ አድዋ ድል የታዳሚውን ቀልብ የሳበ ጽሑፋቸውን አቅርበው በማጠቃለል ላይ ባሉበት ወቅት የመጨረሻው ተናጋሪ የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው እኔ ወደቆምኩበት አቅጣጫ በመምጣት እንድ መልዕክት በጆሮዬ ሹክ አሉኝ፡፡ ያስተላለፉልኝ መልዕክት አጭርና “የሰንደቅ ጋዜጠኛ ድምጼን እንዲቀርጽ ስለማልፈልግ መቅረጫውን ያንሳልኝ” የሚል ነበር፡፡

ይህንንም ተናግረው ወደ መቀመጫቸው ተመለሱ፡፡ እኔም ወዲያውኑ የፓርቲውን ህዝብ ግንኙነት እና የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊዎችን ከዝግጅቱ ውስጥ ጠርቼ የዶ/ሩን ጥያቄ ነገርኳቸው፡፡ ከዚያም ጋዜጠኛውን ስለጉዳዩ ለማዋየት በምንነጋገርበት ወቅት የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ከጋዜጠኛው ጋር ቀረቤታ እና የግል ጓደኝነት ስለነበራቸው በቀላሉ መልዕክቱን ሊነግረው እና ሊያማክረው እንደሚችል ገልጦ ወደ መቀመጫው አመራ፡፡

የህዝብ ግንኙነቱ ከተቀመጠበት መቀመጫ አጠገብ ተቀምጦ ወደ ነበረው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙልጌታ ጠጋ ብሎ ጉዳዩን አስረዳው፡፡ ጋዜጠኛውም በዝምታ ተዋጠ፡፡ በዚህ ወቅት አቶ ታዲዎስ ጽሑፋቸውን አጠናቀው የድምፅ ማጉያውን ለዶ/ር ዳኛቸው አቀብለው ስለነበር የሌላ ጋዜጣ ሪፖርተር መቅረጸ ድምፁን ለማስቀመጥ ሲሄድ ማይኩን ጨብጠው የነበሩት ዶ/ር ዳኛቸው “የሰንደቅ ነው? የሰንደቅ ጋዜጣ ከሆነ አንሱልኝ” በማለት ተናገሩ፡፡ ይህ ሲሆን ቁጭ ብሎ በአንክሮ ሲከታተል የነበረው ጋዜጠኛ ዘሪሁን መቅረፀ ድምፁ እንዲያቀብሉት ጠይቆ እርሱ እንዳለው በፊት ለፊት ለማውጣት ሲሞክር የፓርቲው ም/ሊ/መንበር አቶ ስለሺ እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወጣት ብርሃኑ ይዘውት ለማነጋገር ቢሞክሩም ወጣቱ ጋዜጠኛ “ባካችሁ ደበረኝ… ደግሞ በነገር ሊሸነቁጠኝ ይችላል” በማለት እንቢታውን ገልጦ ዝግጅቱን አቋርጦ ወጣ፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግን ጋዜጠኛው ባለመደበት፣ ከእርሱ በማይጠበቅ እና የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ከሚፈቅደው ውጪ መረጃውን በአግባቡ ሳይጠቀም ፓርቲውን ለመውቀስ መሞከሩ በግሌ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይህንንም ለማስረዳት ጸሐፊው ከተጠቀመባቸውን አረፍተ ነገሮች የተወሰኑትን በመውሰድ በአክብሮት ለመተቸት እሞክራለሁ፡፡

ጸሃፊው በጽሑፉ አንቀጽ አምስት ላይ “…ፓርቲው እንዲዘግብለት የጋበዘውን ሚዲያ አቅራቢው ‹‹አስወጡልኝ›› ሲል ለመገዳደር አለመሞከሩ በእጅጉ ገርሞኛል…” የሚል አረፍተ ነገር ተጠቅሞ ፓርቲውን ይወቅሳል፡፡ እዚህ ጋር ማንሳት እና መገንዘብ ያለብን ዶ/ሩ ፈጽሞ አስወጡልኝ አላሉም፡፡ ቢሉም በግሌ ተቀባይነት የለውም፡፡

በአስወጡልኝ እና ድምፄን አትቅረፁ መካከል ያለው ልዩነት ምን እንደሆነ መንገር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ እንደ እኔም ሆነ እንደ ፓርቲ ባልደረቦቼ እምነት ከአንድ ሚዲያ ጋር ግለሰብን ፈጽሞ ለውድድር እንደማናቀርብ አምናለሁ፡፡ ሚዲያ ማለት ህዝብ ማለት ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው ደግሞ የህዝቡ አንድ አካል የሆኑ ግለሰብ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው በወቅቱ የመወያያ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ ያደረግነው ከጀርባቸው በተሰለፈው ህዝብ ቁጥር ወይም ደጋፊ ሳይሆን ባላቸው እውቀት መሰረት ነው፡፡

ጸሐፊው ሲቀጥልም በአንቀጽ 12 ላይ “…‹‹ቀዳሚ ሚና ለወጣቱ›› የሚለው ሰማያዊ ፓርቲም የቂም በቀለኞች መነሃሪያ መሆኑ አደናጋሪ ጭምር ነው፡፡…” በማለት ግንዛቤውን ያስቀምጣል፡፡ እዚህ ላይ ምንም አይነት ተጨባጭ መረጃ ሳይኖረው ይህንን ለማለት መድፈሩ እርሱ ከተደናገረው በላይ እኔን አደናግሮኛል፡፡ ጋዜጠኛው ከአንድ ግለሰብ ጋር ባለው ቅሬታ እና ችግር ወደ ተሳሳተ ጅምላ ፍረጃ እና ማጠቃለያ (Hasty generalization) መግባቱ ከሌሎችም ጋር እያቀያየመው ጠላት ከማብዛት የዘለለ ምንም እርባና የለውም፡፡

በዚሁ ጽሑፍ ውስጥም “…‹‹ምሁሩን›› ማረጋጋት ሲገባ ‹‹መቅረፀ ድምጽህን አንሳ›› ነበር የተባለው፡፡ …” የሚል አረፍተ ነገር ይገኛል፡፡ ይህ ሃሳብ ፈጽሞ ጋዜጠኛው በቦታው ላይ መኖሩን ሁሉ አይኔን እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡ ይህንንም ያልኩበት ዋነኛ ምክኒያት ሃሳቡ ፈጽሞ በወቅቱ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ፣ እውነታውን ያላገናዘበ እና ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በወቅቱ ቦታው ላይ ስለነበርኩ “መቅረፀ-ድምፅህን አንሳ” የሚል ቃል ከማንኛውም የፓርቲ አመራርም ሆነ አባል ያልተሰነዘረ ለመሆኑ እማኝ መሆኔን ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡

ውድ አንባቢያን በጽሑፉ መደምደሚያ አከባቢ እጅግ በጣም ያዘንኩበት ብቻ ሳይሆን ያፈርኩበት “…ሰማያዊ ፓርቲ ውለታ ቢስ ነው” የሚል አረፍተ ነገር ታገኛላችሁ፡፡ እውነት ጋዜጣው ስለፓርቲዎች ወይም ስለ ፖለቲካ ሲጽፍ ውለታ እየዋለ ነው ብሎ ያምናል? እኔ በግሌ ጋዜጣውን እስከማውቀው ድረስ ስራውን እየሰራ ነው፡፡ ስራ መስራት እና ውለታ ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው፡፡ እንኳን በሽያጭ ለህዝብ የሚደርስ ጋዜጣ ይቅርና ያለምንም ክፍያ በየሳምንቱ በተጋባዥነት በፓርቲያችን ጽ/ቤት እየተገኙ ወጣቶቻችንን የሚያስተምሩልን ምሁራን ሳይቀር ውለታ ዋልንላቸው ሊሉን አይገባም፡፡ ምክኒያቱም በፓርቲያችን እምነት እነዚህ ምሁራን የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ነው፡፡

ለሰማያዊ ፓርቲ ስትሉ ከሚታተምበት ወረቀት እና ቀለም ዋጋ በላይ የማያወጣ እና ህዝብ ጋር መድረስ የማይችል መረጃ ለህዝብ አድርሳችሁ ከሆነ ውለታ ሳይሆን ወንጀል ነው የሰራችሁት፡፡ ጋዜጠኛ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለእናንተ መንገር ለቀባሪ አረዱት ነው፡፡ በዚህች ሃገር ጋዜጠኝነት የተዛባ ትርጓሜ ስላለው እንደ ሰርግ በጥሪ ካርድ አክብሮ ካልተጠራ ስለማይመጡ እንጂ የባል እና ሚስት ጸብን እንኳን ሳይቀር መረጃን አነፍንፎ የሚያድን ጋዜጠኛ ባለበት ሃገር ለጋዜጠኛ የጥሪ ወረቀት አስፈላጊ አይደለም፡፡ የቤት ስራውን የሰራ እና የዜግነት ግዴታውን የተወጣ ሁላ ወለታን በቁና ሰፍሮ እንዳስረከበ የሚጠይቅ ከሆነ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡

በመጨረሻም የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር የሚዲያ አፈና ተከሂዷል የሚያስብል ምንም አይነት ነገር የለም፡፡ ያለ መቅረፀ-ድምፅ ጋዜጠኝነት የለም የሚል አንድምታ ያለው ይመስላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ቀድሞ መቅረጸ-ድምፅ በሌለበት ጊዜ ጋዜጠኝነት የለም ማለት ነው፡፡ የጋዜጠኝነት መብት ሲጣስ እንዴት እንደሆነ አታውቅም እንዳልል በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እያየህ ነው ያደከው፡፡ እንዳይፅፍ እጁ የተሰበረበት ጀግና ጋዜጠኛ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ጀግናው እስክንድር ግን እጄ ተሰበረ ብሎ መረጃን ለህዝብ ከማድረስ ተግባሩ አልተቆጠበም፡፡ ፅሑፌን ከማብቃቴ በፊት አንድ ጥያቄ ለጋዜጠኛው ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ እውነት ለሃገሬ ዜጎች የሚጠቅማቸው መረጃ የቱ ነው፡፡ የታላቁ ጀግና አጤ ምኒሊክ 100ኛ የሙት አመት ወይስ ያንተ የመቅረፀ-ድምፅ ‹‹አንሳ›› ተባልኩ መረጃ? ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረድ ብያለሁ…ሚዲያ ማለት ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ማለት ደግሞ የግለሰቦች ጥርቅም ነው፡፡ ህዝብን ሳያከብር ግለሰብን የሚያከብር ሊኖር አይችልም ካለም ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ በመጨረሻም የሃሳብ ልዩነት ለማስተናገድ የምታደርጉትን ጥረት ሳላመሰግን አላልፍም፡፡

ረጅም እድሜ፣ ጥንካሬ እና ሃላፊነት ለኢትዮጵያ ፕሬስ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s