የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ አስተባባሪዎች ታሰሩ

የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ አስተባባሪዎች ታሰሩ

የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ አስተባባሪዎች ታሰሩ በጎንደር ከተማ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ሰማያዊ ፓርቲ ለሱዳን የሚሰጠውን መሬት በመቃወም እሁድ ጥር 25 ለማድረግ ያቀደውን ሰልፍ እያደናቀፉ ነው፡፡ የፓርቲው ሰልፍ አስተባባሪዎች ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ለማሳወቅ ወደ ከንቲባው ጽ/ቤት በሄዱበት ወቅት ከቢሮ ቢሮ ሲያጉላሉዋቸው ከቆዩ በኋላ በፖሊስ መያዛቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፓርቲው ላቀደው ሰልፍ ዝግጅት ወደ ጎንደር ያቀናው የሰማያዊ ፓርቲ የአደረጃጀት ኃላፊ ኢንጅነር ጌታነህ ባልቻ፤ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን የፓርቲው የዞን ሰብሰቢ የሆነው አቶ አግባው ሰጠኝን በፖሊስ መያዛቸው ታውቋል፡፡ ወከባው የሚጠበቅ መሆኑን የገለጹት የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፤ ጎንደርና አካባቢው እንዲሁም ከዋናው ጽህፈት ቤት የሚገኙት የፓርቲው አደረጃጀቶች በወከባው ሳይደናገጡ ሰልፉን ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገረ ኢትዮጵያ

ነገረ ኢትዮጵያ

ሰማያዊ ፓርቲ በቅርቡ ነገረ ኢትዮጵያ የተሰኘች የህዝብ ልሳን የሆነች ጋዜጣ ለማሳተም ዝግጂት እያደረገ የነበረ ሲሆን ዝግጂቱን አጠናቆ ወደ ማተሚያ ቤት ከገባ በኋላ ግን ከፍተኛ የሆነ ስልታዊ ማደናቀፍ እየደረሰበት በመሆኑና ለጊዜው ማሳተም ባለመቻሉ ሰሞኑን በድረ-ገፅ መልቀቅ የምንጀምር መሆኑን እናስታውቃለን አርብ ይጠብቋት

የመከላከያ መኮንኖች በአዲስ አበባ ፖሊስ የመምሪያ ሃላፊ ተደርገው ተመደቡ::

የመከላከያ መኮንኖች በአዲስ አበባ ፖሊስ የመምሪያ ሃላፊ ተደርገው ተመደቡ::

የመከላከያ መኮንኖች በአዲስ አበባ ፖሊስ የመምሪያ ሃላፊ ተደርገው ተመደቡ::
የአዲስ አበባ ፖሊስ ከጨዋታ ውጭ እንደሚደረግ ምንም ጥርጥር የለውም ::
በአዲስ አበባ ለጤና አገልግሎት የተሰሩ ክሊኒኮች ወደ እስር ቤትነት ተቀየሩ ::

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስሩ ክፍለ ከተሞች የመከላከያ መኮንኖች ተዛውረው መመደባቸውን ታማኝ የቅርብ ምንጮች ገለፁ። የሕወሐት አባላት የሆኑትና ከመቶ አለቃ እስከ ሻለቃ ደረጃ ያላቸው የመከላከያ መኮንኖች የአዲስ አበባን ፖሊስ በበላይነት እንዲቆጣጠሩ በአስሩም ክፍለ ከቶሞች የመምሪያ ሃላፊ ተደርገው መሾማቸውን ምንጮቹ አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ በሚገኙ ወረዳዎች “ኮሚኒቲ ፖሊስ” በሚል አዳዲስ የፌደራል ፖሊሶች እንደመተደቡ ምንጮቹ አያይዘው ገለፀዋል። በአዲስ አበባ ፖሊስ ሃይል እምነት ያጣው ገዢው ፓርቲ ሕወሐት/ኢህአዴግ ታማኝ በሚላቸው መኮንኖችና የፌደራል ፖሊሶች እየተካና አፈናውን እያጠናከረ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቹ አክለውም አሁን በተጀመረው የክልሉን ፖሊስ የማፍረስ ተግባር በቅርብ ጊዜ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከጨዋታ ውጭ እንደሚደረግ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።

ገዢው ፓርቲ ራሱ በደነገገው ሕገ-መንግስት ላይ ፖሊስ ፀጥታውን እንደሚቆጣጠር እንዲሁም መከላከያ ገለልተኛ ሆኖ የአገሩን ሉአላዊነት እንደሚጠብቅና ከማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት ነፃ ሆኖ እንደሚቆም አዋጁ የሚገልፅ ቢሆንም ነገር ግን ራሱ ላወጣው ሕገ መንግስት ተገዢ መሆን እንዳልቻለ የሕወሐት መኮንኖች ከመከላከያ ተዛውረው የአዲስ አበባን ፖሊስ በበላይነት እንዲመሩና እንዲቆጣጠሩ መመደባቸው የህግ ጥሰት እያካሄደ እንደሆነ በቂ ማስረጃ ነው ብለዋል ምንጮቹ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ለጤና አገልግሎት የተሰሩ ክሊኒኮች ወደ እስር ቤትነት እየተቀየሩ መሆኑን ምንጮች አጋልጠዋል። በአዲስ አበባ የካና አራዳ ክፍለ ከተሞች “ኬርና ፕላን” በተባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች የተሰሩት ጤና ጣቢያዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያነት ተቀይረው እስረኞች እየታሰሩባቸው መሆኑን አረጋግጠዋል። በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 06/07 ቤላ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ቀበሌ 11 እንዲሁም ጃንሜዳ ቀበሌ 05 የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች በከፊል እንደሚጠቀሱ ያስታወቁት ምንጮቹ በተጠቀሱት ቦታዎች እስረኞች በብዛት ታስረው እንደሚገኙ አያይዘው ገልፀዋል።

የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም!!!! ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም!!!! ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም!!!!
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
የብሔራዊ ደህንነት መረጃ እና የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የጋራ ኃይል አድርጎ ራሱን የሚጠራ አካል የዜጎችንና የተቋማትን ሕገ-መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በመጣስ ጥፋተኝነታቸው በፍርድ ቤት ሳይወሰን ወንጀለኛ ሲያደርጋቸውና ስማቸውን ሲያጎድፍ ማየት እየተለመደ የመጣ ተደጋጋሚ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ተቋማት ተውጣጥቶም ይሁን ተቀናጅቶ የሚሰራ አካል በተደጋጋሚ ጊዜ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬአቸዋለሁ የሚላቸውን ሁሉ በመክሰስ ወደ እስር ቤት እንዲወርዱ እያደረገ ጉዳያቸው የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳያገኝ እንደፈለገ በሚቆጣጠረው ወይም በሚያዘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት አማካኝነት የፈለገውን ዓይነት ፍረጃና ሥም ማጥፋት ሲያካሒድባቸው ቆይቷል፡፡

ይህ ራሱን ከሕግ በላይ የሰቀለ አካል ያለምንም ገደብ ከሚሰራቸው ተግባራት እንዲታቀብ በሕግ የሚያስቆመው በመጥፋቱ እስካሁን የፈፀማቸውን የማንአለብኝነት ተግባራት እንደጥፋት ሳይሆን እንደ መልካም ሥራ ቆጥሯቸው በተመሳሳይ የሥም ማጥፋትና የፍረጃ ተግባሩ እንዲገፋበት አድርጎታል፡፡ በዚሁም መሰረት ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው የዘጋቢ ፊልም ፕሮፓጋንዳ አሸባሪ ያላቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች አድርሰውታል ያለውን ጥፋት በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ፓርቲያችንን በዚሁ ዘገባ ከተጠቀሱት “አሸባሪ” ድርጅቶች ጋር በማገናኘት ስም ለማጉደፍና ለማስፈራራት የተደረገውን መፍጨርጨር አይተናል፣ ሰምተናል፣ ተገርመናል በመጨረሻም አዝነናል፡፡

በዘጋቢ ፊልሙ የቀረቡ ፓርቲያችንን የማይመለከቱ ጉዳዮችን ትተን ከፓርቲያችን ጋር በማገናኘት የተጠቀሰው “ኢሳት” የተባለ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገለትና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ የመገናኛ ብዙሃን እንዳንጠቀም የማስጠንቀቂያ ዛቻ ተላልፎልናል፡፡ ይህ አስፈራሪ አካል ራሱን ሕግ አውጭና ሕግ ተርጓሚ በማድረግ የፈለገውን አካል ለመፈረጅ፣ ለመክሰስና ለመፍረድ ሥልጣኑን ከየት እንዳገኘ የማይታወቅ ሲሆን የዚህች ሐገር ዜጎችም ሃሳባችንን የምንገልፅበትንና የማንገልፅበትን የመገናኛ ብዙሃን

እየመረጠልንና እየወሰነልን ይገኛል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ ዓይነቱን የእብሪት መልዕክት ከተራ ርካሽ ፕሮፓጋንዳነት የማያልፍ የሕግና የዲሞክራሲያዊ መብት ገደብን ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው ብሎ ያምናል፡፡

የገዥው ቡድን ሰዎች ሀሳብን በሃሳብ ማሸነፍ እንደማይችሉ ስለሚያውቁት የቀራቸው አማራጭ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሃሳባቸውን የሚያሰራጩባቸውን መንገዶች መዝጋት ብቻ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን ማንም አካል በሕግም ሆነ በሞራል ተጠያቂ የሚሆነው የሚያስተላልፈው መልዕክት ይዘት የሌሎችን ዲሞክራሲያዊና ሞራላዊ መብት የሚጋፋ መሆን አለመሆኑ እንጂ ገዥው ቡድን በጠላው ወይም በወደደው የመገናኛ ብዙሃን መልዕክቱን ማስተላለፍ አይደለም፡፡ መልዕክትን የገዥው ቡድን ሰዎች በጠሉት የመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፍ በራሱ ወንጀለኛ ወይም ሽብርተኛ ለማድረግ የሚያበቃ ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት የለም፡፡ ማንም መልዕክት የሚያስተላልፍ አካል የሚያሰራጨው ሃሳብ የሌሎችን ዲሞክራሲያዊና ሞራላዊ መብት የሚጋፋ ከሆነ መልዕክቱ የተላለፈበት መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ይሁን ሌላ ህጋዊ የተባለ የመገናኛ ብዙሃን መሆኑ ብቻ መልዕክት አስተላላፊውን አካል ከተጠያቂነት ሊያድን እንደማይችልም ለማንም የተሰወረ ይሆናል የሚል እምነት የለንም፡፡

በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ መልዕክቱን የሚያስተላልፍበትን መገናኛ ብዙሃን ማንም አካል እንዲመርጥለት ወይም እንዲወስንለት የማይፈልግ መሆኑን ግልፅ እያደረገ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ማንም ሰው በመረጠው መንገድ ሃሳቡን የማስተላለፍ መብቱን በመጠቀም በኢሳትም ሆነ እድሉን ካገኘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቋሙንና እምነቱን ማስተላለፍ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጥ ይወዳል፡፡ በዚሁ አጋጣሚም የፓርቲያችንን መልካም ስም በሃሰት ለማጉደፍ የተሰነዘሩ ቃላትን በቀላሉ የማንመለከታቸው መሆኑን ሕግ ባለበት ሐገር ራስን ከሕግ በላይ በማስቀመጥ ማንንም አካል መፈረጅና ስም ማጉደፍ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን የዘጋቢ ፊልሙ ባለቤቶች እንዲያውቁትና ወደፊትም ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈፀም እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡

ጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ