የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም!!!! ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም!!!! ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም!!!!
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
የብሔራዊ ደህንነት መረጃ እና የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የጋራ ኃይል አድርጎ ራሱን የሚጠራ አካል የዜጎችንና የተቋማትን ሕገ-መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በመጣስ ጥፋተኝነታቸው በፍርድ ቤት ሳይወሰን ወንጀለኛ ሲያደርጋቸውና ስማቸውን ሲያጎድፍ ማየት እየተለመደ የመጣ ተደጋጋሚ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ተቋማት ተውጣጥቶም ይሁን ተቀናጅቶ የሚሰራ አካል በተደጋጋሚ ጊዜ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬአቸዋለሁ የሚላቸውን ሁሉ በመክሰስ ወደ እስር ቤት እንዲወርዱ እያደረገ ጉዳያቸው የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳያገኝ እንደፈለገ በሚቆጣጠረው ወይም በሚያዘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት አማካኝነት የፈለገውን ዓይነት ፍረጃና ሥም ማጥፋት ሲያካሒድባቸው ቆይቷል፡፡

ይህ ራሱን ከሕግ በላይ የሰቀለ አካል ያለምንም ገደብ ከሚሰራቸው ተግባራት እንዲታቀብ በሕግ የሚያስቆመው በመጥፋቱ እስካሁን የፈፀማቸውን የማንአለብኝነት ተግባራት እንደጥፋት ሳይሆን እንደ መልካም ሥራ ቆጥሯቸው በተመሳሳይ የሥም ማጥፋትና የፍረጃ ተግባሩ እንዲገፋበት አድርጎታል፡፡ በዚሁም መሰረት ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው የዘጋቢ ፊልም ፕሮፓጋንዳ አሸባሪ ያላቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች አድርሰውታል ያለውን ጥፋት በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ፓርቲያችንን በዚሁ ዘገባ ከተጠቀሱት “አሸባሪ” ድርጅቶች ጋር በማገናኘት ስም ለማጉደፍና ለማስፈራራት የተደረገውን መፍጨርጨር አይተናል፣ ሰምተናል፣ ተገርመናል በመጨረሻም አዝነናል፡፡

በዘጋቢ ፊልሙ የቀረቡ ፓርቲያችንን የማይመለከቱ ጉዳዮችን ትተን ከፓርቲያችን ጋር በማገናኘት የተጠቀሰው “ኢሳት” የተባለ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገለትና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ የመገናኛ ብዙሃን እንዳንጠቀም የማስጠንቀቂያ ዛቻ ተላልፎልናል፡፡ ይህ አስፈራሪ አካል ራሱን ሕግ አውጭና ሕግ ተርጓሚ በማድረግ የፈለገውን አካል ለመፈረጅ፣ ለመክሰስና ለመፍረድ ሥልጣኑን ከየት እንዳገኘ የማይታወቅ ሲሆን የዚህች ሐገር ዜጎችም ሃሳባችንን የምንገልፅበትንና የማንገልፅበትን የመገናኛ ብዙሃን

እየመረጠልንና እየወሰነልን ይገኛል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ ዓይነቱን የእብሪት መልዕክት ከተራ ርካሽ ፕሮፓጋንዳነት የማያልፍ የሕግና የዲሞክራሲያዊ መብት ገደብን ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው ብሎ ያምናል፡፡

የገዥው ቡድን ሰዎች ሀሳብን በሃሳብ ማሸነፍ እንደማይችሉ ስለሚያውቁት የቀራቸው አማራጭ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሃሳባቸውን የሚያሰራጩባቸውን መንገዶች መዝጋት ብቻ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን ማንም አካል በሕግም ሆነ በሞራል ተጠያቂ የሚሆነው የሚያስተላልፈው መልዕክት ይዘት የሌሎችን ዲሞክራሲያዊና ሞራላዊ መብት የሚጋፋ መሆን አለመሆኑ እንጂ ገዥው ቡድን በጠላው ወይም በወደደው የመገናኛ ብዙሃን መልዕክቱን ማስተላለፍ አይደለም፡፡ መልዕክትን የገዥው ቡድን ሰዎች በጠሉት የመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፍ በራሱ ወንጀለኛ ወይም ሽብርተኛ ለማድረግ የሚያበቃ ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት የለም፡፡ ማንም መልዕክት የሚያስተላልፍ አካል የሚያሰራጨው ሃሳብ የሌሎችን ዲሞክራሲያዊና ሞራላዊ መብት የሚጋፋ ከሆነ መልዕክቱ የተላለፈበት መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ይሁን ሌላ ህጋዊ የተባለ የመገናኛ ብዙሃን መሆኑ ብቻ መልዕክት አስተላላፊውን አካል ከተጠያቂነት ሊያድን እንደማይችልም ለማንም የተሰወረ ይሆናል የሚል እምነት የለንም፡፡

በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ መልዕክቱን የሚያስተላልፍበትን መገናኛ ብዙሃን ማንም አካል እንዲመርጥለት ወይም እንዲወስንለት የማይፈልግ መሆኑን ግልፅ እያደረገ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ማንም ሰው በመረጠው መንገድ ሃሳቡን የማስተላለፍ መብቱን በመጠቀም በኢሳትም ሆነ እድሉን ካገኘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቋሙንና እምነቱን ማስተላለፍ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጥ ይወዳል፡፡ በዚሁ አጋጣሚም የፓርቲያችንን መልካም ስም በሃሰት ለማጉደፍ የተሰነዘሩ ቃላትን በቀላሉ የማንመለከታቸው መሆኑን ሕግ ባለበት ሐገር ራስን ከሕግ በላይ በማስቀመጥ ማንንም አካል መፈረጅና ስም ማጉደፍ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን የዘጋቢ ፊልሙ ባለቤቶች እንዲያውቁትና ወደፊትም ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈፀም እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡

ጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s