በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንጂ የስሜት ፖለቲካ አያዋጣንም – ናኦሚን በጋሻው

ከ250 አመታት በፊት ፣ 13 ኮሎኒዎች፣ ተብለው የሚታወቁት የአሜሪካ ግዛቶች በእንግሊዝ ሥር ነበሩ። አሜሪካኖቹ የግብር ጫና ስለበዛባቸው ለነጻነት መታገል ጀመሩ። በአሜሪካኖች እና በእንግሊዞች መካከል ጦርነት ተጀመረ። የአሜሪካኖች መሪ ጀነራል ጆርጅ ዋሺንግተን ነበሩ። እንግሊዞች ብዙ ጦር አሰልፈው ያመጹ አሜሪካዉያንን ለማስገበር ተንቀሳቀሱ። በኑዮርክ አሜሪካኖች ትልቅ ሽንፈት ደረሰባቸው። የእንግሊዝን ጦር መቋቋም አልቻሉም። ጆርጅ ዋሽንግተን፣ በሌሊትና በጉም ወደ 9 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮች ወደ ኋላ እንዲመለሱ አደረጉ። እነዚያ ወታደሮች ባይሸሹና ወደ ኃላ ባይመለሱ ኖር፣ ምናልባትም አሁን የምናውቃት አሜሪካ ላትኖር ትችል ነበር። ያ የሸሸው ጦር ፣ እንደገና የበለጠ ተጠናክሮ፣ በቂ ዝግጅት አድርጎ፣ ተጨማሪ የሰው ኃይል አካቶ፣ ተመልሶ በእንግሊዞች ላይ ጥቃት በማድረስ እንግሊዞችን ሽንፈት አከናነበ። አሜሪክ ነጻ ወጣች።

ጆር ዋሺንገትን ፣ በጊዜያዊ ሽሽት፣ « ስሜ ይጠፋል። ክብሬ ይነካል። ፈሪ እባለለሁ» ብለው በጦርነቱ እንደሚሸነፉ እያወቁ ወታደሮቻቸውን  አላስጨረሱም። አንድ የጦር መሪ፣ ደፋርና ጀግና ሕይወቱንም አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆን እንዳለበትም  በሳል፣ አስተዋይ፣ ለወታደሮቹ ሕይወት የሚጠነቀቅ፣ ስትራቴጂክ ፣ የነገውን የሚመለከት መሆንን ይኖርበታል።

የሰላማዊ ትግልም ከወትድርና ትግል በብዙም አይለይም። የሰላማዊ ትግል መሪዎችም ፣ እንደ ጦር ጀነራሎች ሃላፊነት አለባቸው። አንድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ አስቀድሞ ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ሊያስገኝ የሚልቸውን ዉጤት መመርመር ይኖርባቸዋል።

በአገራችን ኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴው የተለያዩ ስትራቴጂዎች ባላቸው ድርጅቶች በሁለት መስመር እየተደረገ ነው። አንደኛው በነሰማያዊ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲሆን ሌላው ደግሞ በነአንድነት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ሁለቱም አላማቸውና ግባቸው አንድ ነው። ሁለቱም ትንታግ፣ ትንታግ የሆኑ፣ አገራቸውን የሚወዱ ለሕዝባቸው ሕይወታቸዉን አሳልፈው የሰጡ የዘመናችን የሰላማዊ አርበኞች ያሏቸው ናቸው።

በኢንጂነር ይልቃል የሚመራው የሰማያዊ ፓርቲ፣ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ አምስት ጊዜ ከፖሊሶች ጋር ግብግብ ፈጠሮ አባላቶቹን አሳስሯል፣ አስደብድቧል። ( የግራዚያኒ ኃዉልትን በመቃወም፣ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ሳይሆን ጃን ሜዳ ሰለፍ አድርጉ ሲባል «አይ መስቀል አደባባይ ነው የምናደርገው በሚል፣ በሳዉዲ አረቢያ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ግፍን በመቃወም፣ ህዳር ሶስት ከ9ኙ ፓርቲዎች ጋር በቤል ሄር ሕዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ሲሞከርና በቅርቡ በመስቀል አደባባይ የአዳር ሰልፍ ለማድረግ ተሞክሮ የነበረ ጊዜ)  እነዚህ ሰለፎችን ሲጠሩ የተጣሰ ሕግ የለም። የሰልፎቹም አላማ ጥሩ አላማ ነበር። ሆኖም ግጭት ሳይፈጠር አላማዉን ማሳካት አይቻልም ነበር  ወይ ?

ሰማያዊ ሶስት ሰልፎችን ያለ ምንም ችግር ሰላማዊ በሆነ መንገድ አጠናቋል። ( ሰኔ 2005 ዓ.ም  የተደረገውና ወደ 70 ሺህ ሰው የወጣበት ሰልፍ፣ ሚያዚያ 19 በጃን ሜዳ በተደረገዉን ሶስት መቶ ሰው ብቻ በተገኘበት ሰልፍ፣ በጎንደርም አንዴ በተደረገና አንድ መቶ የሚሆኑ የተገኘበት ሰልፍ )

የአንድነት ፓርቲን ከተመለከትን፣  ባለፉት ሁለት አመት ዉስጥ 12 ሰላማዊ ሰልፎች አድርጓል። ( መስከረም 19 እና ሚያዚያ 26 ከመቶ ሺህ በላይ ሰው የተገኘበት የአዲስ አበባ ሰልፎች፣ የባህር ዳር፣ የደሴና የአዳማ አሥር ሺዎች የተገኙበት ሁለት ሁለት ሰልፎች፣ የደብረ ማርቆስ፣ የጎንደር፣ የአርባ ምንጭ፣ የጂንካ፣ የፍቼ፣ የጊዶሌ ሰላማዊ ሰልፎች)  ። አንድነት ባደረጋቸው ሰልፎች ሁሉ ምንም አይነት ከፖሊስ ጋር ግብግብ አልተከሰተም። በሰልፎቹ ቀናት የተደበደበ፣ የታሰረ ሰው አልነበረም።

ኢሕአዴግ አፋኝና አምባገነን መሆኑ ይታወቃል። ወደድንም ጠላንም የራሱ የሆነ ጥንካሬ አለው። ኢሕአዴጎች ሲያስሩ፣ ሲገድሉ፣ ሲያፍሱ ፣  ትንሽ እንኳን ሰብእና የማይሰማቸው ሰዎች ናቸው። እነርሱን ፊት ለፊት በምንጋፈጥበት ጊዜ ፣ የነርሱን ዱላ የምንቋቋምበት ትከሻ ሊኖረን ይገባል። አለበለዚያ በቀላሉ በአንድ ምት መሬት ላይ መዘረራችን አይቀሬ ነው።

የሰማያዊ ፓርቲ ከላይ እንደጠቀስኩት የተለያዩ ኮንፍሮቴሽኖች ከኢሕአዴግ ጋር ሲያደርግ፣ ኮንፍሮቴሽኖችን በራሳቸው አልጠላቸውም። ሆኖም አቅም ሳናጎለብት የሚደረግን ኮንፍሮቴሽን ግን የብስለት ማነስን የሚያሳይ ነው። የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ እንግዲህ ያለኝ አንዱ ትልቅ ችግር ይሄ ነው። አመራሮቹ፣ ለአባላቶቻቸው የመቆርቆር ነገር አይታይባቸው። አባላቶቻቸው ፣ ቆራጦችና ጀግኖች ናቸው። ሆኖም በመሪዎቻቸው ጥበብ የለሽ ፣ ግብታዊና ግትር አመራር፣ አላስፈላጊ መስዋእትነት እንዲከፍሉ፣ እንዲደበደቡ፣ እንዲታሰሩ እየተደረገ ነው።

በኢሕአፓ ጊዜ የወጣቶችን ግለት ሁላችንም የምናውቀው ነው። ያኔ የነበሩ ወጣቶች ኢሕአፓን ደገፈው በስሜት፣ በሞራል ነበር ሲታገሉ የነበሩት። ብዙዎች ከአዉሮፓና ከአሜሪካ ተመልሰው ለሕዝባችን እና ለአገራችን ብለው ደረታቸው ለመስጠት የተዘጋጁ ነበሩ። ሆኖም የኢሕአፓ ብስለት የጎደለው አመራር ብዙ ወጣቶችን አስጨረሰ። አሁንም በሰማያዊ ተመሳሳይ ነገር ነው እያየን ያልነው። ለትግል የተነሳሱ ወጣቶችን ወደ ማይሆን አቅጣጫ እየመሯቸው ነው። ይህ መቆም አለበት።

በጣም የሚይሳዝነው ደግሞ በተለይም በዉጭ አገር ያሉ፣ እንደ ኢሳት፣ ከረንት አፌር ያሉ አንዳንድ ወገኖች፣ ይሀን አይነት ሃላፊነት የማይሰማው፣ በስሜት እንጂ በእወቅት ላይ ያልተመስረተ እንቅስቃሴን እንደ ትልቅ ጀብዱ  ማነፈሳቸው ነው።

ለምሳሌ የሚከተለውን የኢሳት ዘገባ ያዳምጡ። በ”እረ ጎራው” ሙዚቃ እያጀቡ፣ “አይውቁንም እኛን አያወቁንም” የሚል ዜማ እያሰሙ፣ “ያ ሆ” እየተባለ፣ እያጋነኑ የሰማያዊን ሰልፍ ሲዘግቡ ነዉ የነበሩት። እንደዉም ይሄን ዘገባ ሲያቀርቡ “ለሥራ ብለን አባል አንሆንም” የሚሉ፣ አንድነት በጠራዉና በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ በተገኘበት የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ የተገኙ ሰልፈኞችን፣ የሚሰሙበትን የኦዲዮ ክሊፕ ፣ ከሰማያዊ ሰልፍ ጋር በማግናኘትም አሰምተዉንም ነበር። በነጋታዉ ግን ምንም ሆነ ? ምንም ።በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶች ታሰሩ፣ ተደበደቡ። ፉከራው ሁሉ ዝግጅት ሳይደረግ፣ ሕዝብ በሚገባ ሳይደራጅ፣ በስሜት ብቻ መሆኑ ተረጋገጠ።

ከላይ እንደጠቀስኩት የሰማያዊ አመራሮች ቢያንስ አምስት ጊዜ ከፖሊሶች ጋር ግብግብ ፈጥረዋል። ይህ የሚፈጥሩት ግብግብ ፣ የድርጅት መሪዎችን ተክለ ሰዉነት ከመገንባት ዉጭ ለትግሉ፣ ለህዝቡ ምን ጥቅም እንዳስገኘ መጠየቅ መቻል ነበረበት። እነ ኢሳቶች ግን ያንን ማድረግ አልቻሉም።ዘጠኙ ፓርቲዎች ቆርጠዋል። መንግስትህ አድፍጧል። ነገ የሚሆነው ይሆናል።

ኮንፍሮንቴሽን ከአምባገነኖች ጋር ለማድረግ በምናነሳብት ጊዜ ህዝቡን ከጎናችን ማሰለፍ የግድ ነው። የሰላማዊ ትግል ሰራዊት ሕዝብ ነው። ሕዝብን ማደራጀቱ፣ ማስተማሩ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ሥራ መሆን አለበት። ሕዝብ ከተደራጀና ከተነሳ አምባገነኖች እድሜ አይኖራቸውም። የአንድነት ፓርቲ እያደረገ ያለው እንግዲህ ይሄንኑ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቷ ሕዝቡ ለለዉጥ፣ ለነጻነት እንዲነሳ እየሰራ ነው።

ከፖሊሶች ጋር ግብግብ ከመፍጠር ዉጭ፣ ሰማያዊዎች ያደረጉትን በሙሉ፣  በአሥር እጥፍ አንድነቶች እያደረጉት ነው። ኢሳት ስለሰማያዊ ሰልፍ ሰልፍ በዘገበ ጊዜ፣  በቅርቡም የሚሊዮኖች ድምጽ ለፍትሃዊ ምርጫ በሚል በአዲስ አበባና በክልል ባሉ ትላልቅ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚጠሩ ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይናግራሉ። «ኢሕአዴግ እንዲህ ነው  ..በሩ ተዘጋ ..» ብሎ ማማረር ብቻ ሳይሆን ፣ የተዘጋዉን እያስከፈቱ፣ ባሉት ትናንሽ ቀዳዳዎች ሕዝቡን ለማስተማርና ለማንቃት እየሰሩ ናቸው። ለምሳሌ አገዛዙ ጋዜጦቻቸዉን ብርሃንና ሰላም እና ሌሎች የግል ማተሚያ ቤቶች እንዳያትሙ ቢከለከሉም፣ አንድነቶች የራሳቸው የማተሚያ ማሽን ገዝተው፣ ኤልፓ መብራት አለቅም ሲል ደግሞ፣ ጄኔሬተርም ጨምረው፣ ይኸው ጋዜጦችን እያተሙ ወደ ሕዝቡ እየደረሱ ነው። ፍኖተ ነጻነት ከምትባለዋ ታዋቂ ጋዜጣ በተጨማሪ፣ የሚሊዮች ድምጽ የምትባል ሁለተኛ ጋዜጣ ለማሰራጨትም አንድነት ተዘጋጅቷል።

የአንድነት ፓርቲ በፊታችን 2007 በሚደረገው ምርጫ ፣ ሕዝቡን ለማደራጀትና ለማንቀሳቀስ በሚደረገው ትግል፣ በፖለቲካ ፕሮግራም ተመሳሳይነት ካላቸው ሌሎች ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል።በመሆኑም የሰማያዊ ፓርቲ አቋሙን እና ስትራቴጂዉችን በመመርመር፣ ከአንድነት ጋር፣ መፎካከር ሳይሆን፣  አብሮ ለመስራት እንዲዘጋጅ ጥሪ አቀርባለሁ። የሰማያዊ አመራሮች ከአንድነት ጋር መስራት እንደ አለርጂክ እንደሚሆንባቸው ቢታወቅም፣ ከዚህ የግለኝነት በሽታ ተላቀው፣ ከግል ዝናቸውና ክብር ይልቅ የአገርን እና የሕዝብን ጥቅም እንዲያስቀድሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ። በአንድ ላይ ከተባበርን፣ በሰሜት ሳይሆን በእወቀት ላይ የተመሰረተ ትግል ካደረግን፣ ሃብታሙ አያሌዉን ልጥቀስና “እመኑኝ፤ ደርግም ወድቋል። ወያኔም ይወድቃል”።

ሰማያዊን የምንደግፍ ካለን ደግሞ ጭፍን ደጋፊ ከመሆን ወጥተን መሰረታዊ ጥያቄዎች በመጠየቅ የሰማያዊ አመራሮችን ተጠያቂ ማድረግ ይኖርብናል። ከዚህ በፊት እነ ኃይሉ ሻዉልን እንደዚሁ ዙፋን ላይ በማውጣታችን ፣ ብዙ ስህተቶች ሲሰሩ ዝም በማለታችን፣  ይኸው የትላንቱ ትልቁና ጠንካራው የፕሬሮፌሰር አስራት ወልደየስ ድርጅት፣  አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ አድርገነዋል። በድርጅቶች ዉስጥ አምባገነነ ባህሪ ያላቸውን ግለሰቦች በጭራሽ ልንታገስ አይገባም። የሰማያዊ አመራሮች ከአንድነት ጋር አብረው ለመስራት ባለመፈለጋቸው፣  እያገዙ ያለው አገዛዙን መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል እንጂ ከአሁን ለአሁን ከፖሊስ ጋር ስልተጋጩ፣ ለጊዜ የጥቂት ቀናት ስሜታዊ ደስታ ስለሰጡን፣ ልንክባቸው አይገባም።

የተቀረው፣ ከዳር ሆኖ የሚመለከተው ኢትዮጵያዊ፣  “2007 ለለዉጥ” በሚል መርህ የአንድነት ፓርቲ እየመራ ያለውን ሕዝባዊ ትግል እንዲቀላቀልና እንዲያግዝ ጥሪ አቀርባለሁ። ይህ ሕዝባዊ ትግል ሊሳካ የሚችለው በሚሎዮኖች የምንቆጠር  ትግሉን ስንቀላቀል ብቻ ነው። በስሜት መጋለብ ካቆምን፣ ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታ ከሁሉም ማእዘናት ካገናዘብን፣ በአካባቢያችን ከሚናፈሱ ጨለምተኛ የሽንፈትና የጥላቻ አስተሳሰብ ደመና ወጣ ካልን፣  እርግጠኛ ነኝ በእወቅትና ሕዝብን በማደራጃት ላይ ያተኮረውን በአንድነት እየተመራ ያለውን የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ አካል እንደምንሆን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s