እግዚኦ! መጥኔ ለእኛ ፖለቲካ፡- ስለ ኢትዮጵያችን ሰላም፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ እውነት በአንድነት ድምፃችን ይሰማ! አብዝተን እንጩኽ …!

በፍቅር ለይኩን – fikirbefikir@gmail.com

ከሰሞኑ በእናት ምድር፣ እማማ ኢትዮጵያ መልካም ነገር እየታየ፣ እየተሰማ፣ እየተነገረ ያለ አይመስልም፡፡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የፖለቲካው ትግል ዛሬም መንገዱን እንደ ትናንቱ በደም ለመመረቅ በተጠንቀቅ ቆሞ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ከደርግ ሥርዓት መውደቅ በኋላም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ዘንድ ጉልህ የሆነ መቀራረብና የፖለቲካ መሳሳብ ልዩነት ያልታየበት ይኸው የአገራችን ፖለቲካ ምኅዳር ቀውስ የአንድ ተጨማሪ ትውልድን ማለፍ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡

እናም በእናት ምድር ሰማይ ላይ አንዳንች መዓትን ያረገዘ የሚመስል የጥፋት፣ የእልቂት ደመና እያንዣበበ ነው፡፡ ይኸው ምርጫ የሚሉት ነገር በደጅም አይደል፤ እዚህም እዚያም ቤት ጩኸት በርክቷል፡፡ መወነጃጀሉ፣ መወራረፉ፣ በነገር ጅራፍ መገራረፉ፣ መዠላለጡ አይሏል፣ በርትቷል፡፡ አዲስ የብሔራዊ መግባባት መንፈስና የዲሞክራሲያዊ አንድነት መንፈስን የተላበሰ ከመንደር፣ ከወንዝ የሚያልፍ አገራዊ አስተሳሰብን ለመውለድም ሆነ ለማዋለዱ ምጡ በርትቶብናል፣ ወይንም አልተቻለንም!!

እናም ይኸው ዛሬም እማማ ኢትዮጵያችን ደጋግሞ የጎበኛት የፖለቲካችን ሾተላይ ዳግመኛ አዲስ ተስፋን፣ አዲስ ሕይወትን እንዳትገላገል በደም የቀላ ሰይፉን እያወዛወዘ ሊጎበኛት በደጅ አድብቶአል፡፡ ይኸውን ምርጫንና የምርጫን ወሬ ተከትሎ ብዙዎችም ደስ የሚል ነገር እየሸተታቸው አይደለም፡፡ በፊታቸው ላይ የሚነበበው እውነት የሚነግረን ሐቅም ምን ያህል ምጣቸውና ጭንቀታቸው እንደበረታ ነው፡፡ እናም ብዙዎች ከሚያዩትና እየሰሙት ካለው ውጥረት የተነሣ እ-ግ-ዚ-ኦ የኢትዮጵያ አምላክ ምድርህን አደራህን እያሉ ጠዋት ማታ ተማጽኖአቸውን፣ ጩኸታቸውን አጠንክረዋል፡፡

ከዚኹ ከግንቦቱ ምርጫ ጋር ተያይዞም ባለፈው እለተ ሰንበት ሰልፍ እንወጣለን፣ ለመብታችን እንጮኻለን ባሉና አይ ሰልፋችሁ ከመንግሥት ዘንድ ፈቃድና እውቅና የለውም በሚሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ፍጥጫና ግጭት የወገን ደም ፈሷል፡፡ መቼም የተናደደ፣ የተቆጣ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ በሰላም ይመለሳል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም፤ ሊያውም በአፍሪካ ምድር ከአፍሪካም- በኢትዮጵያችን!! የዚህ ግፍ ቀማሽ የሆኑ ወገኖችና ይህን አሳዛኝ ትዕይንት በዓይናቸው አይተው የታዘቡ ዘንድሮማ አንላቀቅም ይለይናል ወደሚል ምሬት፣ ብሶትና ዛቻ የተሸጋገረውን ብርቱ ቁጣቸውን ሲያዘንቡት፣ ሲያሰሙ ነበር፤ አሁንም እያሰሙ ነው፡፡

በሩቅ ያሉና ወሬውን በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሰሙና ያዩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ደግሞ፣ በባዕድ ምድር አገራቸውና የሕዝባቸው ናፍቆትና ስስት በብርቱ ውስጣቸውን እያረሰው፣ እየማሰውና እየገመሰው ቁጣቸው ገንፍሎ፣ ብሶታቸው ድንበር ጥሶ በሶሻል ሚዲያው በኩል በገዢው ፓርቲ፣ በመንግሥት ላይ ርግማኑን፣ ትችቱን፣ መዓቱን እያዘነቡት፣ እያወረዱት ነው፡፡

ይባስኑ ትናንትና ደግሞ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ አበው ቀድሞውኑ ገለልተኝነቱ በጥያቄ ውስጥ የወደቀው ምርጫ ቦርድ በአንድነትና በመኢአድ ፓርቲ አመራሮች ላይ በሰጠናችሁ የጊዜ ገደብ መስማማት፣ መግባባት አልተቻላችሁም እናም ሕጋዊ አይደላችሁም በሚል እገዳን አስተላልፏል፡፡ ይህ አንዳንዶች እንደሚሉት ይጠበቅ የነበረው የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ትግሉን በይበልጥ ለማፋፋም ቃል ኪዳናቸውን እንዲያጠብቁ የሚያደርግ እንጂ ከትግላቸው አንዲት ጋት ፈቀቅ የማያደርጋቸው እንደሆነ እየተናገሩ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ፍጥጫ ደግሞ አንድ የሚነግረን ሐቅ አለ፡፡

ይኸውም የሰላሙ አማራጭ እየተገፋ፣ የሰላሙ መንገድ በእሾኽ እየታጠረ፣ አስጨናቂና ውጥረት እየነገሠበት መንገድ የመሆኑ ነገር የበርካቶችን ወኔ እየተፈታተነ ያለ ወደመሆን እየተሸጋገረ ነው፡፡ እናም ከመቼውም ጊዜ በላይ የጥፋቱ መንገድ አይቀሬነቱን የሚያረዱ ምልክቶች በእናት ምድር የፖለቲካ ሰማይ ላይ፣ በእውነትም የግንቦቱ ምርጫ የምጡ ጣር ጅማሬ ቀድሞ መታየት መጀመሩን እያረዱን ነው፡፡

በረጅም ታሪክ ዘመኗ ይህች የሕዝቦቿን ዕንባና ደምን በገፍ የጠገበች እናት ምድር ኢትዮጵያችን ዛሬም የአብራኳን ክፋይ የልጆቿን ዕንባና ደም ተጥታ፣ በግፍ ተግታ የኀዘን ከል ለብሳ ወዮ እያለች ብሶቷ፣ ጩኸቷ፣ እሪታዋ ሰማይ ሰማያትን ሰንጥቆ እየተሰማ ያለ ይመስለኛል- የፍትሕ፣ የእውነት፣ የፍርድ ያለህ እያለ!! በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ዛሬም በእናት ምድር ኢትዮጵያችን ከእውነት ጋር የሚቆሙ፣ ለድሃ አደጉና ለተበደሉ የሚፈርዱ፣ ለእውነትና ለፍትሕ በእውነት የሚቆሙ አገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፓርቲዎችና የፖለቲካ መሪዎች ድምፃቸው ገና ድል ነስቶ የወጣ አይመስልም፡፡

ቆም ብለን የተያያዝነው የዚህ ጉዞአችን ፍፃሜ ሲታሰብ ልብ ይደክማል፣ አእምሮአችን ታውኮና ኀዘናችን ክፉኛ በርትቶ ወዮ ለነጋችን ያሰኛል፡፡ እንዴት ዛሬም ተዋዶና ተከባብሮ መግባባት፣ መነጋገር ያቅተናል፡፡ እንዴትስ ከትናንትና መማር ተስኖን ዛሬም የትናንትናውን ክፉ ታሪክ ለመድገም እንፈልጋለን፡፡ ትናንትና በእኛ ዕርዳታ፣ በእኛ ውትወታ፣ በእኛ አደራዳሪነት ነጻነታቸውን የተጎናጸፉ የአፍሪካ አገራት ዛሬ ፖለቲካቸው ዘምኖ፣ ኢኮኖሚያቸው ዳብሮ ወደፊት ሲገሠግሡ እኛ ምን አዚም ቢጫነን፣ ቢወርድብን ነው ጉዞአችን እንዲህ እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ የሆነበት ምክንያት፡፡

መቼስ ይሆን ልዩነታችንን በጦር አውረድ ከመፍታት የጥላቻ፣ የግትርነትና የጠላትነት ፖለቲካ አባዜ የምንወጣው፡፡ በፓርቲ፣ በዘር፣ በጎሳ የተቧደኑ ሰዎች ዛሬም ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎራ ለይተው ጦር አውርድ እያሉ በምድሪቱ ላይ ሌላ እልቂትን ሌላ መዓትን እየጠሩ፣ እየጋበዙ ያሉ ነው የሚመስሉት፡፡ እንዴት የሞት አማልክት በምድሪቱ ላይ ተጠራርተው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የከተሙበት የመሰለው ያ የ1997ቱ ድኅረ ምርጫ ያወረደብን ዘግናኝ እልቂትና መዓት ተዘነጋን፡፡

እንዲያ ያከበርነውና የጓጓንለትን ያህል ውርደትን የተከናነብንበት ያ 97ቱ ድኅረ ምርጫ የሚረሳ ነውን፣ እነዛ ሮጠው ያልጠገቡ ጨቅላ ሕፃናት እንኳን ሣይቀሩ የኢሕአዴግ መንግሥት ባሰማራቸው በአልሞ ተኳሾች በጠራራ ፀሐይ ጭንቅላታቸው በጥይት አረር እየተገመሰ፣ እየተበረቀሰ ደማቸው እንደ ውሻ ደም በአደባባይ ላይ በከንቱ የፈሰሰበት- ያ የጨለማ፣ የጽልመት የ97ቱ ድኅረ ምርጫ ቀውስና ዘግናኝ እልቂት እንዴት ተብሎ፣ እንዴትስ ተደርጎ ይረሳናል፣ ተረሳን፡፡

እነዛ ችግር ከስውነት ተራ ያወጣቸው፣ ድህነት በራሳቸው ላይ ጎጆውን የቀለሰባቸው የሚመስሉ፣ መከራ ጀርባቸውን ያጎበጣቸው እናቶች፣ በራብ የሰረጎደ አጀንታቸውን በመቀነታቸውን አስረው ለሟችና ለገዳይ ልጆቻቸው ያፈሰሱት እንባቸው፣ እንደ ራሄል እንባ የምስኪን እናቶች እንባ የእማማ ኢትዮጵያን ሰማይ ያደፈረሰበት ያ የወዮታ ዘመን፣ ወደ አርያም፣ ወደ ፈጣሪ ኤሎሄ፣ እ-ግ-ዚ-ኦ… የአንተ ያለህ! የፍትሕ ያለህ! የሚለው እንባቸው፣ ሰቆቃቸው፣ ሰቀቀናቸውስ እንዴት ይዘነጋል፡፡

የሕዝባቸው እልቂት ነፍሳቸውና አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ የተሰማቸው፣ የእናት ኢትዮጵያ እንባና ሰቆቃ እረፍት የነሣቸው በባዕድ ምድር የሚኖሩ ወገኖቻችን በጨካኞች ዱላና ጥይት አንጎላቸው የተዘረገፈ፣ አካላቸው የተገመሰ የሟች ወገኖቻችንን ዘግናኝ ምስል ይዘው በአሜሪካና በአውሮፓ አገራት ኤምባሲዎች ደጅ- ይህን እልቂት፣ ይህን እብደት፣ ዘግናኝ መዓት ጣልቃ ገብተው ያስቆሙ ዘንድ ከእንባና ከብርቱ ጩኸት ጋር ብሶታቸውን ያሰሙ የወገኖቻችን እንባ፣ ለቅሶና ጩኸትስ እንዴት ይረሳል፡፡

ይህን ክፉ የታሪክ ጠባሳን የተሸከምን፣ ቁስላችን በሚገባ ያልሻረ፣ እንባችንም ገና በቅጡ ያልታበሰ ሕዝቦች ዛሬም በምርጫ ሰበብ በምድሪቱ ላይ፣ የትናንትናውን ዓይነት እልቂትና መዓት ለመድገም የጦር አውርድ ወሬን የሚያሰሙ ድምፆች እዚህም እዛም ጎልተው እየተሰሙ ነው፡፡ የሕዝብን ብሶት፣ የሕዝብን ጩኸት ለመስማት የዝኆን ጆሮ ይስጠኝ ያለ የሚመስለው መንግሥትም ስለ ሰላም ሲል በጠረጴዛ ዙሪያ በእርጋታ ተነጋግሮ ልዩነቶችንና ችግሮችን ከማስወገድ ይልቅ የኃይሉን መንገድ የሙጥኝ ብሏል፡፡ እናም በማንኛውም ኹኔታ ሕዝብ አደባባይ ድረስ ዘልቆ የመንግሥትን ቁጣ እስከቀሰቀሰ ድረስ ምላሹ ያው እየሆነ መምጣቱ ዛሬም በግልጽ በአደባባይ እየተደገመ ነው፡፡ ዱላ፣ ድብደባ፣ ጥይት፣ ግዞት፣ ስደት፡፡

በሌላም በኩል ለውጥ፣ ለውጥ አሁኑኑ በሚሉ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድም እየታዘብነው ያለው እውነታ አንድ የሚነግረን ሐቅ አለ፡፡ ይኸውም አሁንም በአገራችን ኢትዮጵያ የሰለጠነና ሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ስልት በአንደበት እንጂ በተግባር ገና መሬት እንዳልረገጠ ነው፡፡ በመንግሥት በተቃራኒው የቆሙትና ራሳቸውን ተቃዋሚ ብለው የሚጠሩ ሰዎች ስብስብ ልብ ውስጥም ያለውን የጥላቻ መንፈስ ስንመለከትም ውጤቱ ያው እንደለመድነው የመጠፋፋትና የመበላላት ፖለቲካው አባዜ ዛሬም በብዙዎች ልብ ውስጥ ዙፋኑን እንዳይነቃነቅ አድርጎ ተክሎ እንዳለ መታዘብ የምንችል ይመስለኛል፡፡

ከሕዝብ ጋር ለመነጋገር የሰላሙን በር ያጠበበው መንግሥት የሰላሙን መንገድ ባጠበበው ቁጥር አይቀሬ የሆነውን የጥፋት መንገድ እየመረጠ እንዳለ ለአፍታ ያህል እንኳን ሊያስበው ቢችል መልካም ነበር፡፡ ‹‹የምን እርቅ፣ እርቅ ነው የምትሉት በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም የተጣላ የለም፡፡›› በሚል የፖለቲካ ስላቅን ልማድ ያደረገው መንግሥት ስለ ብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ እንዲነሳበትና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መነጋገርን ዛሬም የሚፈልገው፣ የሚመርጠው መንገድ አይመስልም፡፡

የእርስ በርስ ጦርነት ዘግናኝ እልቂት፣ ራብ፣ ድርቅ፣ ስደት፣ ሞት፣ ግፍና መከራ እየተፈራረቀ ጀርባውን ክፉኛ ያጎበጠው ሕዝባችን ከአሁን ወዲህ ጦርንና የጦርን ወሬ መስማት አይፈልግም፡፡ መንግሥት ሕዝቡን የሚወድ፣ የሚያከብር ከሆነ የሕዝቡን የልብ ትርታ፣ የውስጡን ጩኸትና ብሶት ሊያዳምጥ ይገባዋል፡፡ በፊታችን የሚጠብቀን የግንቦቱ ምርጫም ሰላማዊና ተቀባይነት ያለው እንዲሆንም እርስ በርስ በቅንነትና በበጎነት መንፈስ ልንነጋገር የሚያስችለንን መድረክ በመፍጠር ረገድ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ሊንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች ሰላም፣ ፍትሕና እውነት ድል ነስቶ የሚወጣበትን ሥራ ለመሥራት በቃልም በተግባርም ቃል ኪዳናቸውን ማደስ ያለባቸው ወሳኝ ጊዜ ላይ እየደረስን ነው፡፡ ስለሆነም ስለ ሰላም፣ ስለ ብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ አባቶች ጠንክረው ድምፃቸውን ቢያሰሙ መልካም ነው፡፡ በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል መግባባትና ዕርቅ እንዲወርድ በርትተው ይሥሩ፡፡ ይህን በጊዜው ማድረግ ካልተቻለ ወይም ካልተቻለን ግን በአገራችን እየነፈሰ፣ ሽው እያለ ያለው ንፋስ እምብዛም ሰላም ሰላም የሚሸት አይደለምና አብዝተን ልንፈራ፣ አብዝተን ልንጮኽ ግድ ይለናል፡፡

በዘር፣ በጎሳ ፖለቲካ ጉዳይ እርስ በርሱ የተቃቃረ፣ ትናንትና በሆነው ክፉ የመበላላትና የእልቂት ታሪክ ብሶትና ቁጭት ልብ ልቡን እየበላው በሆዱ ያረገዘውን ቂም ለመገላገል አመቺ ጊዜን የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር በበረከቱባት ኢትዮጵያችን በምርጫ ሰበብ የሚከሰተው ግርግር ሊፈጥር፣ ሊያስነሳ የሚችለውን ኹከትና ግጭት ከወዲሁ አስልተን በጥንቃቄ ልናስብበት የሚገባ የቤት ሥራችን እየሆነ ነው፡፡ በእርግጥም ይህን ሥጋታችንን፣ ፍርሃታችንን የሚያባብሰው፣ በፊታችን የተደቀነው የግንቦቱ አገር አቀፍ ምርጫ ጉዳይ ከወዲሁ እንቅፋቱና ኹከቱ፣ ጭንቀቱና ውጥረቱ በርትቶበት እንዳለ እያየን ነው፡፡

እናም የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች፣ አገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች- ሁላችን አገራችን የምንወድ፣ ሕዝባችንን የምናፈቅርና ለወገኖቻችን የምንቆረቆር ሁሉ የሠጋነውና የፈራነው ነገር እንዳያገኘን፣ የፊታችን የግንቦቱ ምርጫ በእውነትም ምርጫ እንዲሆን፣ በኢትዮጵያችን ምድር ሰላም አብዝቶ እንዲሰፍን፣ ስለ ሰላም ዘብ የሚቆሙ የሰላም ጠበቃዎች፣ የሰላም ሐዋርያዎች ከፍ ከፍ እንዲሉ ሁላችንም አብዝተን እንጩኽ፣ ድምፃችንን ደጋግመን እናሰማ- ስለ ኢትዮጵያችን ሰላም፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ እውነት!!

ሰላም! ሻሎም!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s