ከውህደቱ ጀርባ – ማስረሻ ባደንጋ (አባስ)

ማስረሻ ባደንጋ (አባስ)

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመንደር ወሬ ሆኖ የከረመውና እስከአሁንም መጨረሻው ያለየለት ዋና ጉዳይ ሆኖ የሰነበተው ከወደ ኤርትራ የሚሰማው የሁለት ብረት ያነሱ ኃይሎች ውህደት ነው፡፡ ይህ ውህደት ከጅምሩ ግልፅነት የጎደለውና ብዙዎችን ግራ በማጋባቱ ለብዙ ትችቶች የተመቸና የተዳረገ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጋራ ጉዳይ ተባብሮ አለመስራትና ያለውን አቅም አንድ አድርጎ ፖለቲካዊውም ሆነ ወታደራዊ ትግልን ማድረግ አለመቻል አሁን አሁን ላለንበት (በተለይ ለተቃዋሚው ጎራ) ትርምስና ለውጤት መብቃት አለመቻል ዋና ሰበብ ነው፡፡ ከሰሞኑ ከወደ ኤርትራ የሚሰማውም ይህንን ችግር ተገንዝበናል በሚሉት ሁለት ሃይሎች መሃል ውህደታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ሊገቡ የሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ እየሰሩ መሆናቸውን እየሰማን ነው፡፡ ለዚህ ውሳኔ የበቁት ማለትም ዕድሜ ጠገቡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አርበኞች ግንባር እና የ“ግንቦት7 ንቅናቄ” ከምንም በፊት ተበታትኖ ከመታገል ሃይልና አቅምን አሰባስቦ ለመታገል መሞከራቸው ለብዙ ተመሳሳይ ችግር ላለባቸው ምሳሌ በመሆናቸው አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል፡፡

ሰላማዊ ትግል አያዋጣም ብለውና ብረት አንስተው ኤርትራ የከተሙ ኃይሎች እድሜያቸው ሲሰላ በቀላሉ ወደ አስራ አራት መሙላቱ ነው፡፡ ከእነዚህ ሃይሎች ውስጥ ኤርትራ በመግባት ቀዳሚ የሆነውና ለዴምህት (ትህዴን)ና ሌሎች ኃይሎች መፈጠር ዋና ምክንያት የሆነው ሰሞኑን ተወሃዱ ከሚባሉት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ነው፡፡ ይህ ሃይል ኤርትራ ገባ ከተባለለት ግዜ ጀምሮ ምን አልባት ከላይ ለመጥቀስ እደተሞከረው ለሌሎች ኃይሎች መፈጠር ሰበብ ከመሆን የዘለለ ይህ ነው የሚባል ተግባር ፈፅሞ ስለመኖሩ ያረጋገጠ ድርጅት አይደለም፡፡ ይህንን ለማድረግ እንደዋና ምክንያት ሊጠቀሱ ከሚችሉት መሃል፤ አመራሩን ከመሾምና ከመሻር አልፎ በሁሉም ነገሮች ላይ ውሳኔ አሳላፊ የሆነው የሻእቢያ ከልክ ያለፈ ጣልቃ ገብነት፤ ኢ.ህ.አ.ግ ለትጥቅ ትግል ያሰባሰባቸው በርካታ አባላቱ በአገርቤት በተለይ በትውልድ ቦታቸው በዝርፊያና በደመኝነት የተነሳ ከህግ ሸሽተው ጫካ የነበሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት መሆኑ፤ ከዚህ ቀደም ኢ.ህ.አ.ግን ሲመሩ የነበሩና ጥሩ ደረጃ ያደርሱታል ተብለው ይታሰቡ አመራሮች በሻእቢያ ተፅእኖ ጥለው ለመውጣት መገደዳቸውና አንዳንዶቹም እስከ አሁንም ድረስ ለእስራት መዳረጋቸው፤ በኋላ የተተኩ አመራሮች ግንባሩን ይዘው ለማታገል የሚችሉ በሳልና ብቁ አለመሆናቸው፤ ኢህአግ ከመሰረቱ ታጋዮቹን በስነ- ምግባር አንፆ ለመያዝ ባለመቻሉና አንዳንዴም የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ሲገባ ሃገርቤት ውስጥ በተለይም ግንባሩ ብዙ ድጋፍ ሊያገኝባቸው ይችላል ተብሎ በሚታሰቡ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፅሙት ግድያ፤ ዝርፊና አፍኖ ይዞ ወደ ኤርትራ መሄድ የተነሳ ግንባሩ ከፍሽቶች ስብስብ በዘለለ መታየት አለመቻሉን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሌላኛው የዚሁ ውህደት አካል የሆነውና ምርጫ 97ን ተከትሎ የተፈጠረውና ከምስረታው ጀምሮ በአሜሪካና አውሮፓ ብቻ እንቅስቃሴው ተገድቦ የነበረው የግንቦት7 ንቅናቄ ነው፡፡ ንቅናቄውን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በጠንካራና ደካማ ጎኖቹ ዙሪያ ብዙ የተባለ በመሆኑ ወደዚህ መመለስ አያሻም፡፡ ተያያዥ ነገሮችን ለመጥቀስ ያህል ግን ንቅናቄው ልክ እንደ ሌሎቹ ኃይሎች ሰላማዊ ትግልን በመተው አካሂደዋለሁ ላለው የትግል ስልት “ሁለገብ ትግል” የሚል ስም መጠሪያ ሰጥቶ ያየን ቢሆንም በዲያስፖራው አካባቢ ድጋፍ ሊያስገኝለት ከመቻሉ ውጪ ምንም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አድርጎ አንዱን እንኳን ሊያሳካበት ያልቻለባቸውን አመታትን አሳልፏል፡፡ ይህ ንቅናቄ በዲያስፖራው አካባቢ ከሌሎቹ የተሻለ ድጋፍና አቅምን ያገኘ ቢሆንም ለተከታታይ ዓመታት ሊታይ በሚችል መልኩ በፕሮግራሙ ላይ ከነደፋቸው ተግባራት አንዱንም ማሳካት ባለመቻሉና የሚጠበቅበትን መንገድ ለመጓዝ ስለተሳነው የነበሩትን ድጋፎች ከማጣት ባለፈ ለተለያዩ ፖለቲካዊ ኪሳራዎች ተዳርጎም አይተናል፡፡ ንቅናቄው ትግሉን አንድ ደረጃ ማሻገር በሚል መልኩ “የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል” የሚል ክንፍ አቛቁሞ በደጋፊውና በአባላቱ ዘንድ ደስታን የፈጠረና ለንቅናቄው ይደረግለት የነበረን የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ያነቃቃ እንዲሁም ተስፋን የሰጠ ጉዳይ ነበር፤ በዚያው ልክም ከጅምሩ በህዝባዊ ሃይሉ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ የተሸፋፈነ ነገር የታየበት በመሆኑ እንዲሁም ሻእቢያን ብቻ አምኖና ብዙ ዙሪያ ገቡን ያስተዋለ ውሳኔ አይደለም በሚሉ የተለያዩ ግለሰቦችና ማህበራት ትችትና ወቀሳ ደርሶበታል፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዋናው አላማ ውህደቱን የተመለከተ በመሆኑና ወደ ሌላ ርዕስ እንዳይጎትተኝ በመስጋት ወደ ጉዳዩ ልለፍ፡፡

ውህደቱን በተመለከተ ስንነጋገር ውህደቱ ሊያስገኛቸው የሚችሉ ጠቃሚ ነገሮችን ማንሳቱ ያስፈልጋል፡፡ ውህደቱን ተከትለው ሊመጡ ከሚችሉ በጎ ጎኖች መሃል፤ በሁለቱ ተዋሃጅ ሃይሎች ውስጥ በተናጠል የነበረውን አቅም በጋራ እዲጠቀሙ የሚረዳ ነው፤ ይህንን መነሳሳት ያዩ የተለያዩ ደጋፊዎችን ማስገኘት ከመቻሉ ሌላ በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፋቸውን ያቆሙና ተቀዛቅዘው የነበሩ ደጋፊዎችን መመለስና ማነሳሳት የሚችል ነው፡፡ እነዚህ ተዋሃጅ ሃይሎች ከዚህ ቀደም ሲከተሏቸው የነበሩትና ለውጤት እዳይበቁ ያደረጓቸውን የትግል መንገዶች ደግሞ በመፈተሽ ከውህደቱ በኋላ ያስኬደናል ብለው የሚወስዱት አዲስ የትግል መንገዶችን ያመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ፤ በተጨማሪም ልክ እንደነሱ የትጥቅ ትግል አማራጭ አድርገው የያዙ ሃይሎችም ደፍረው ወደ ውህደት እንዲመጡ መንገድ የሚከፍትም ነው፡፡

በተጨማሪም ውህደቱን ስናነሳ ካየናቸው መልካምና ጠቃሚ ነገሮች ጎንለጎን ያሉ ችግሮችን ማንሳቱ ምልከታችንን ሚዛናዊ ከማድረጉ ያለፈ አንዳንድ ነገሮችን ለመጠቆምና በግልፅ ውይይት ለማድረግ ይረዳልና የተወሰኑትን እናንሳ፡፡ ይህን ውህደት የተመለከተ ወሬ ገና ከመነሻው መነገር የጀመረው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄን ጨምሮ የሶስት ተዋሃጆችን መግለጫና መሃተማቸውን ይዞ በመጣ ፅሁፍ ነው፡፡ ኋላም በተለያዩ ሚዲያዎችና ድህረ-ገፆች ስለ ሶስቱ ኃይሎች ውህደት በተደጋጋሚ በሚነገርበት ተመሳሳይ ሰዓት ውስጥ ሲዊዲን ሀገር የሚኖሩትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ መስራችና ሊቀመንበር ኮ/ል አለበል ድርጅታቸው ተገዶ ሊዋሃድ እንደሆነና አመራሮቹም በሻእቢያ እስርቤት እንደሚገኙ የሚናገር ተከታታይ መግለጫውን በድርጅታቸው ስም ሲያወጡ ታይተዋል፡፡ ብዙም ሳይቆይ የተዋሃጆችን ቁጥር ሁለት መሆኑን በእነዚያው ሚዲያዎችና ከውህደቱ በሚወጡ ዜናዎች ይነገር ጀመር፡፡ ይህ መሆኑና የአንዱ ድርጅት እንዲገለል ያደረገው ምክንያት ግልፅ መልስ ሳይሰጥበት ማለፍ ከጅምሩ ጥርጣሬን ይዞ የመጣና ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ኤርትራ ውስጥ ያሉሃይሎች በሚታዩበት የጥርጣሬ መንፅር እንዲታይ ያደረገ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ ተዋሃጆቹ ወደ ውህደቱ የመጡበትና ከውህደቱ በፊት የነበሩበትን ሁኔታ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይልም ሆነ የግንቦት7 ንቅናቄ መስራችና አድራጊ ፈጣሪ የነበረው አቶ አንዳርጋቸው በግንባር ቀደምትነት ኤርትራ ውስጥ በተሞከረ የውስጥ ለውስጥ ስራዎች በቦታው የነበሩ ኃይሎችን ከማስኮረፉ ባለፈ ህልውናቸውን አደጋ ውስጥ ሊከት በሚችል መልኩ ግንቦት7 ከሻእቢ ጋር ግንኙነትን ፈጥሮ እደነበረ በቦታው የነበርንና የተለያዩ ሚዲያዎችን የተከታተልን አስረጅ መሆን እንችላለን፡፡ የነበረውን ግጭት ለማስታወስ ያህል አንዳርጋቸው ከሻእቢያ ጋር በተለይም ከኮ/ል ፍፁም ጋር በነበረው ቅርበት ሌሎች ኤርትራ የነበሩ ኃይሎችን በማንነታቸው፤ በአካዳሚክና የትምህርት ደረጃቸው ወዘተ የተለያየ ስም ይሰጣቸው የነበረና ስማቸውን ያስጠፋ ስለነበረ ይህ ነገር በዛኛው ወገን በመታወቁ በወቅቱ ኤርትራ ውስጥ የነበሩ የሁለቱም ወገን አባሎቻቸው መሳሪያ ያልታጠቁ ስለነበረ እንጂ እሰከ መጠፋፋት የሚያስችል መፈላለግ ውስጥ ገብተው ታይተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የአርበኞች ሊቀመንበር መአዛው ጌጡ በሻእቢያ በተቀነባበረ ሴራ በደረሰበት የመኪና አደጋ በወቅቱ የአንዳርጋቸው ደስታውን የገለፀበት መንገድ ህዝባዊ ሃይሉ ውስጥ በቦታው በነበርን አባላት ውስጥ ግርምትን ፈጥሮ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ አንዳርጋቸው የመን ላይ በወያኔ እጅ ወደቀ ተብሎ ሲነገር በተመሳሳይ መልኩ የአርበኞችና የአዴሃን ታጣቂዎች ደስታቸው ወደር እንዳልነበረው ይታወቃል፡፡

በዚህ ሁኔታ ከሌሎች ጋር በመነጋገር ግንቦት7ን በጠላትነት በመፈረጅ ተሰብስበው አቛም ከያዙትና በተናጠል የተለያየ መግለጫዎችን ሲያወጡ ከነበሩት እንዱና ቀዳሚው የኢትዮጵ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዋናው ነበር፡፡ የግንቦት7ንና የአርበኞች ግንባር ቀደምት ግንኙነት በቅርበት ለሚያውቅ ሰው ለውህደት ከመብቃታቸው በፊት ያለውን ችግር በምን መልኩ ፈተውት ለዚህ እንደበቁ የሚያሳይ ነገር በግልፅ አለመኖሩ “ውህደቱ በሁለቱም ኃይሎች ፍቃደኝነት ብቻ የሚካሄድ ነው?” የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ እዲያነሳ ያደርገዋል፡፡

ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ የግንቦት7 ንቅናቄ ለውህደቱ ወደ ኤርትራ የላካቸው ግለሰቦችና አመራሮች በምን መልኩ ከንቅናቄው የተወከሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ነገር የሌለ መሆኑና፤ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ አባላቱን በተመለከተ ሃሳባቸውን የሚናገሩበት ምንም አይነት ዲሞከራሲያዊ መድረክ ሳይዘጋጅ የተገባበት ውህደት መሆኑ፤ ቢያንስ ለሌላ ጉዳይ ሲጠሩ አቤት ማለት የማይደክማቸው በየከተማው ያሉ አባላትን እንኳን በዚህ ጉዳይ የጠራ ነገር እንዲኖራቸው ያልተሞከረ መሆኑ ነው ይህ ከሆነ ግንቦት7 ወደ ውህደቱ ይዞት የመጣው ችግር ነው ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን መጀመሪም ሲፈራ የነበረው ግንቦት7 ጠፋ እንዳይባልና ሻእቢያ እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዳይጠየቅ በውህደቱ ስም የሚስራው ሽወዳ መምሰሉ ግድ ነው ፡፡
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የተለያዩ ድርጅቶችን ሲመሩና በሻእቢያ ባለመወደዳቸው ምክንያት ወደ ሻእቢያ ወህኒ ከወረዱት መሃከል አንዱ የሆነውና በብዙዎቹ የሚወደደው የግንባሩ ሊቀመንበር ኮ/ል ታደሰ ሙሉነህ ጉዳይን ሳያነሱና እንደተራ እቃ በመረሳት ሻእቢያ ይመቹኛል ብሎ ካስቀመጣቸው አመራሮች ጋር ብቻ ስምምነት ላይ መድረስ ምንአልባት ያለ አማራጭ ተገደው የሚዋሃዱት በረሃ ያሉ ታጋዮችን ሊያካትት ይችል ይሆናል እንጂ በዚህ ጉዳይ ዘወትር ጥያቄ የሚያነሱ የብዙ ሰዎችን እምነት ከወዲሁ የሚሸረሽር ነው፡፡
በግልፅ እውነት ላይ የተመሰረተ ውህደት ብቻ ኃይል ነው፤ ያለበለዚያ ቀድሞም በተናጠል የነበረን አቅምን ይዞ የሚሄድ አደጋን ያዘለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s