ይቅርታ መጠየቅ ታላቅነት፣ ይቅር ባይነት ደግሞ ጀግንነት ነው! -በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

በመንግሥት ታግዳ ከኅትመት ውጪ የሆነችው ‹‹የአዲስ ጉዳይ መጽሔት›› ዓምደኛ የሆኑት አቶ ሰለሞን ተሰማ ባለፈው ሳምንት በዚሁ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ባስነበቡን ጽሑፍ የዚሁ ጋዜጣ ም/ዋና  አዘጋጅ አቶ ፋኑኤል ክንፉን፣ አቶ ዳንኤል ብርሃነንና የአዲስ ጉዳይ መጽሔት አንባቢዎችንና ወዳጆችን በይፋ/በአደባባይ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ባልተረጋገጠ ወሬ በሐሜት የጎዷቸውን በተለይም አቶ ፋኑኤልንና አቶ ዳንኤልን ከታላቅ አክብሮት ጋር በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸውን አስነብበውናል፡፡

አቶ ሰለሞን ይህን ማድረጋቸውም አንድም ከእምነታቸው አስተምህሮ፣ ከሕሊና ፍርድ፣ ከሞራል ጥያቄና ለወደፊትም ታሪካችንን ከነትሩፋቱና ከነጠባሳው ለሚወርሱት ልጆቻችን ኩራትና ተምሳሌት ለመሆን በማሰብም ጭምር እንደሆነ በትሕትና ገልጸውልናል፡፡ ይህ በእውነትም ይበል የሚያሰኝ ታላቅ፣ የተቀደሰ በጎና ሰው ከሆነ ሰው የሚጠበቅ ሰናይ ምግባር ነው፡፡

አቶ ሰለሞን ተሰማ ባልተጨበጠ መረጃ፣ በሐሰት ወሬና በሐሜት ላይ ተመርኩዘው በመንግሥት በታገደችው በተወዳጇ አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ፡-‹‹የአዲስ ዘመን አሮጌ ወሬዎች፣ (ንኩ ጋዜጣ እና ንኩዎቹ ጋዜጠኞች!)›› በሚል ርዕስ ባስነበቡበት ጽሑፋቸው ያስቀየሟቸውን፣ ክብራቸውንና ሰብእናቸውን የጎዷቸውን ሰዎች በይፋ ይቅርታ በመጠየቃቸውም በግሌ ላመሰግናቸው፣ ላከብራቸው እወዳለኹ፡፡

ይህ የእርሳቸው የተቀደሰ፣ መልካምና በጎ ምግባርም በመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነት ባሉ፣ በፖለቲከኞቻችን፣ በአርቲስቶቻችን፣ በታዋቂ ሰዎችና በግለሰቦች ላይ ያለ ምንም ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ስማቸውን፣ ክብራቸውንና ስብእናቸውን በሚነካና በሚያዋርዱ መልኩ የሌሎችን ስም ለሚያብጠለጥሉ፣ ለሚያጎድፉ ሰዎች፣ ሐሜትና አሉባልታን ለሚነዙና ለሚጽፉ መጽሔቶችና ጋዜጦች፣ የመገናኛ ብዙኃን ጥሩ ማሳሰቢያና መልካም ምክርም ጭምር እንደሆነ አስባለሁ፡፡

አቶ ሰለሞን ስሕተታቸውን አምነው በይፋ፣ በአደባባይ ይቅርታ መጠየቃቸው ትልቅነታቸውንና አስተዋይነታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ይኸው በአብዛኞቻችን ዘንድ እምብዛም ያተለመደው የአቶ ሰለሞን ዕርምጃ ከዕርቅና ከይቅር ባይነት ይልቅ ቂም በቀል፣ ክፋትና ጥላቻ ልክ የባህል ያህል ለነገሠብን ለእኛና ለማኅበረሰባችን ጥሩ የማንቂያ ደወልና ጥሩ ትምህርት ሰጪ ምግባር ይመስለኛል፡፡

ዛሬ፣ ዛሬ በሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎች፣ በመንግሥት ባለ ሥልጣናትና ፖለቲከኞች፣ በአለቆችና የበታች ሠራተኞች፣ በንግድ ሸሪኮችና ወዳጆች፣ በባለ ትዳሮች፣ በቤተሰቦችና በወላጆች መካከልና እንዲሁም በአጠቃላይ በእለት ተእለት ማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን ይቅር ባይነት በመብራት የምንፈልገው ውድ ዕንቁ ከሆነብን ሰነባብቷል፡፡ ከይቅርታ፣ ከዕርቅ ይልቅ ቂምኝነት፣ ጥላቻና በቀል የብዙዎቻችን መለያና መታወቂያ ሆኗል፡፡ በርካታዎችም በውስጣቸው ባዘሉትና እሹሩሩ እያሉት ባለው ቂም የተነሳ ውስጣቸው የበቀል እሳት የሚነድባቸው የክፋት፣ የጥፋት መሣሪያ እየሆኑ ነው፡፡

ደመናው ሲዳምን ይወረዛል ገደል፣

ይዘገያል እንጂ መች ይረሳል በደል፡፡

እነርሱ በሬ ሲያርዱ እኛ ጥጃ እንረድ፣

ቢሆንም ባይሆንም እጃችን ደም ይልመድ፡፡

በሚሉ ጥላቻችንና ክፋትን፣ ቂምንና በቀልን በሚሰብኩ፣ በሚያበረታቱና በደም ስራችን ሳይቀር እንዲዋሃዱ የሚያደርጉ ግጥሞችን፣ ሽለላዎችን፣ ቀረርቶዎችንና ፉከራዎችን ሲሰማ ኖሮ፣ ሲሰማ ላደገ ለእንደኛ ዓይነቱ ማኅበረሰብ ይቅርታ መጠየቅ፣ ይቅርታ ማድረግም ሆነ ዕርቅ ብሎ ነገር ጨርሶ የሚታሰብ፣ የሚሞከር ነገር አይደለም፡፡ እናም በአብዛኛው የታሪካችን ገጽ በጥላቻ፣ በእርስ በርስ እልቂትና በመበላላት፣ በቂምና በበቀል፣ በደም የተዥጎረጎረ፣ የደመቀ ነው፡፡

ስለሆነም ይቅርታን የሚሰብኩ፣ የሰላምና የዕርቅ ሰዎችን ታላቅና ጀግና የሚያደርግ ባህላችን እጅጉን የደበዘዘ ነው፡፡ ከዛ ይልቅ በአብዛኛው ቂምን በልቡ አርግዞ የወፈጀውን ያህል ጊዜ ፈጅቶም ቢሆን አድብቶና ጠብቆ ሌላውን የሚበቀለውን፣ የትናንትና በደልንና ጥፋትን በደም ካሣ የሚያወራርደውን ሰው ጀግና ብሎ ለመሾምና ለመሸለም የሚተጋና የሚያተጋ ባህልና ታሪክ ነው ያለን፡፡

ግና ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅርታ ማድረግ ታላቅነት፣ ጀግንነት ነው፡፡ አቶ ሰለሞን ይህን ለብዙዎቻችን ተራራ የመውጣት ያህል የሚከብደንን ይቅርታ የመጠየቅን ጉዳይ በአደባባይ ለማድረግ በመፍቃደቸው ሊመሰገኑ ሊከበሩ ይገባቸዋል፡፡ በመሠረቱም የትኛውም የዓለማችን ሃይማኖቶች ትእዛዝና አስተምህሮም ኾነ በዓለማዊው ወይም በዘመናዊው ዓለም ዕውቀት ይቅር ባይነት/ይቅርታ ማድረግ ቅዱስና በእጅጉ የሚበረታታ መልካም ነገር እንደኾነ ነው አስረግጠው የሚነግሩን፡፡

ታላላቅ በሆኑት በክርስትናም ኾነ በእስልምና ሃይማኖቶች አስተምህሮ ዘንድም ይቅር ባይነት፡- አፍቃሪ፣ ቸር፣ ርኁርኁርና አዛኝ ከኾነው ከፈጣሪ ዘንድ ከተቀበልነው ገደብ የለሽ ይቅርታና ምሕረት ለሌሎችም ወዳጅና ጠላት ሳንልና ሳንለይ፣ ሳንሰስት የምናካፍለውና የምንከፍለው የፍቅር ዕዳችን እንደኾነ ነው አብዝተው፣ አስፍተውና አምልተው የሚናገሩት፣ የሚያስተምሩት፡፡

ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባሻገርም በጤና ሳይንስና እና በሥነ ልቦና ጥናት ረገድም ይቅር ባይነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያመለክታሉ፡፡ የባለሙያዎች ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ነገሮችን በይቅርታ ማለፍ መቻል የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ግንኑነታችንን ጤናማና ሚዛናዊ እንዲሆን ከማድረግም ባሻገር ከተለያዩ የጤና እክሎችና በሽታዎች እንደሚታደገንና፣ እንዲሁም ሕይወትን በፍቅርና በተስፋ፣ በደስታና በሰላም ለመኖር የሚያስችለንን ኃይል በሕይወታችን እንደሚጨምርልን ያስረዳሉ፡፡

ጄኒ ሴፈር የተባሉ ምሁር What We Forget about Forgiveness በሚል ርዕስ ‹‹ሳይኮሎጂ ቱዴይ›› መጽሔት ላይ በ2014 እትም ላይ ይቅርታን በተመለከ ባስነበቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው በአሜሪካና በአውሮፓ አገራት ካለፉት ዐሥር ወይም ዐሥራ አምስት ዓመታት ጀምሮ የይቅርታ ጉዳይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ፖለቲከኞች ድረስ ዐቢይ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው ጽፈዋል፡፡

ሴፈር በዚህ ጹሑፋቸው በአሜሪካንም ሆነ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በሚገኙ ታላላቅ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የይቅርታ/የዕርቅ የጥናትና የምርምር ማዕከሎችን በስፋት ማቋቋማቸውን ያትታሉ፡፡ እኚህ ምሁር በአሜሪካ አገር በዊስኮንሲን ሜዲሰን ዩኒቨርሲቲና የስታንፎርድ ዓለም አቀፍ የይቅርታ/የዕርቅ ፕሮጀክት፣ በሕክምና ሳይንስ፣ በሥነ-አእምሮ፣ በሥነ-ልቦና እና በማኅበረሰብ ሳይንስ ጥናቶች ረገድ እየወጡ ያሉ ጥናቶች ጠቅሰው እንዳስነበቡት፡-

የሌሎችን በደል ይቅር የሚሉ፣ ይቅርታ ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የተሻለና ጤናማ ሊባል የሚችል ማኅበራዊ ግንኙነት እንዳላቸውና አካላዊና አእምሮአዊ ጤንነታቸው መልካም እንደሚሆን አስነብበዋል፡፡ በተቃራኒው ሆነ ብለውም ሆነ ሳያውቁ ሌሎች ሰዎች ባደረጉባቸው በደል የተነሳ የሚብሰለሰሉ፣ በውስጣቸው ቂም የሚይዙና ለመበቀል ምቹ ጊዜን የሚጠባበቁ፣ ይቅርታ ለመጠይቅም ሆነ ይቅርታ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በአብዛኛው ለድብርት፣ ለጭንቀት፣ ለደም ግፊት፣ ከፍተኛ ለሆነ ሥነ ልቦናዊ ቀውስና የጤና እክል እንደሚዳረጉ ጨምረው አስነብበዋል፡፡

ሴፈር በዚህ ጽሑፋቸው የይቅርታና የዕርቅ ፕሮጀክቶች የዘር ማጥፋት ዘመቻ፣ እርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭትና እልቂት በተካሄደባቸው እንደ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሴራሊዮን፣ ካምቦዲያ፣ ደቡብ አፍሪካ ባሉ አገራትም ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ማምጣታቸውን አትተው ጽፈዋል፡፡

በተለይ በአፓርታይድ አገዛዝ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ለደረሰው ዘግናኝ የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻ፣ ጭፍጨፋ፣ ግድያና ሥቃይ በይቅርታ ጀግናው በማንዴላና በአቡነ ዴዝሞን ቱቱ መሪነት በደቡብ አፍሪካ የተቋቋመው South African Truth and Reconciliation Commissionበሚሊዮን የሚቆጠሩ ቂምን ያረገዙ ደቡብ አፍሪካውያን የበቀልና የእልቂት ሰይፍ ወደ ሰገባው እንዲመለስ በማድረግ በቋፍ ላይ የነበረችውንና በጥፋት መንገድ የቆመችውን ያችን አገር ወደ ሰላምና ዕርቅ መንገድ በማምጣት ታላቅ የሆነ ታሪካዊ ሚናን መጫወታቸውን ሁላችንም አንዘነጋውም፡፡

በመጨረሻም በእርግጥም ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅርታ ማድረግ በቁሳዊውም/በዘመናዊው ሆነ በመንፈሳዊው ዓለምም እጅግ ታላቅና የተወደደ ቅዱስ ምግባር መሆኑን ላሰምርበት እወዳለኹ፡፡ ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍም፡- ‹‹እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባባሉ፡፡ የወንድሞቻችሁን ኃጢአት ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁም የእናንተን በደል ይቅር ይላችኋል፡፡›› ‹‹መባህን ከማቅረብህ በፊት አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ›› ሲል ይናገራል፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ጸንቶ ከቆመባቸው ታላላቅ ዓምዶችም መካከልም ፍቅር፣ ምሕረትና ይቅርታ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ፈጣሪ አምላክም ከፍጡሩ ወይም ከሰው ልጆች ጋር ያለው ግንኙነትም ፍቅርን፣ ምሕረትንና ይቅርታን የተሞላ ወይም መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ስለሆነም እኛ የሰው ልጆች ከፈጣሪ ጋር ሊኖረን የሚገባው ግንኙነት የሚወሰነውም ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ፍቅር ደግሞ የሚታገሥ፣ የሌሎችን በደል ማይቆጥር፣ ይቅር ባይ፣ ታጋሽና እውነተኛ ነው፡፡ ሌሎችን ስንወድ፣ ከልብ ስናፈቅር የዛሬ በደላቸውን፣ ስሕተታቸውን  ሳይሆን የትናትና መልካምነታቸውና ወዳጅነታቸው ትዝ እያለን በደላቸውን ሳንቆጥር ይቅር እያልናቸውና እያፈቀርናቸው አብረናቸው በይቅርታ ለመኖር የሚያስችለንን ኃይል፣ ጉልበትና ጸጋ እናገኛለን፡፡

ትናንትና በሆነው የመበላላት፣ እርስ በርስ እልቂት አስቀያሚ የሕዝባችን ታሪክ የተነሣ፣ በዘርና በቋንቋ ተከፋፍለው በጎሪጥ ለሚተያዩ፣ ሊፈርሱ አንድ ሐሙስ የቀራቸውን በቋፍ ላይ ያሉ ትዳሮችን፣ ሊበተኑ ያሉ ልጆችን፣ በበደልና በቂም የደፈረሱ፣ የተበላሹ የፍቅር ወዳጅነቶችን፣ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶቻችንን ለመታደግ ይቅርታ፣ ሰላም፣ ዕርቅን ማውረድ ዋንኛውና ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡

አበው ‹‹ከታረቁ አይቀር ከልብ፣ ከታጠቡ አይቀር እስከ ክንድ››፣ ‹‹ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት›› እንዲሉ በዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን ኦርቶዶክሳውያን አባቶች፣ አገልጋዮችና ምእመናን እየጾምነው ባለነው በዚህ በታላቁ በዐቢይ ጾምም ቂምን ትቶ፣ ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ከልብ የሆነ ይቅርታ ማድረግ ጾማችንን ተቀባይነት ያለውና ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ብድራት ወይም ዋጋ የሚያስገኝንልን ቅዱስ ተግባር እንደሆነ ማስታወስ እፈልጋለኹ፡፡

በተጨማሪም አላስፈላጊ ከሆኑ የጤና እክሎች ድብርት፣ ጭንቀት፣ የደም ግፊት፣ ከማይፈለጉ ሥነ ልቦናዊ ቀውሶችና ውጥረቶችም ለመዳንም ይቅርታ ማድረግምም ሆነ ይቅርታ መጠየቅ መፍትሔ መሆኑን ሁላችንም ልብ ልንል ይገባናል፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ታላቅነት/ትልቅነት፣ ይቅር ባይነት ደግሞ ጀግንነት ነውና!! ለሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ የፍቅርና የይቅርታ የጾም ወራት እንዲሆን በመመኘት ልሰናበት!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s