ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ እጣ ክፍሏ አይደለም ይሆን?

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በትክክል የማይተረጉም ወይም የማይገልፅ እና የአለምን ነባራዊ ሁኔታ ከማንነቱ አንፃር ማየት የማይችል ህዝብ ለራሱ የሚጠቅመውን ገንቢ የሆነ ተግባራትን ሊፈፅም አይችልም፡ ምክንያቱም የስነ ልቦና ባርነት ያድርበታልና፡፡

በ1960ዎቹ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የታገለው ትውልድ ቆራጥ ትውልድ ነበር፡፡ ነገር ግን መብትን ማስከበር፣ ነፃነትን መጎናፀፍ፣ ብልፅግና ማስፈን ወዘተ የሚል መርሆዎችን ይዞ ይነሳ እንጂ የተመኛቸውን እነዚህን ለውጦች ለማምጣት የሚያስችል የእውቀት የባህልና የስብእና ብቃት አለኝ ብሎ በጥሞና ራሱን አለመመርመሩ ነበር ችግሩ፡፡ በዚያ ዘመን ለውጥን አመጣለሁ ብሎ ለትግል የተነሳው ኢትዮጵያዊ ምሁር የነፃ አውጪነት ሚና ሲጫወት ለዚህ የሚመጥን ብቃት እንዳለው በሚገባ አላሰበበትም::

ሀገራዊ ታሪካችንንም ሆነ ፖለቲካዊ እውነታዎችን በግልፅ ፍርጥርጥ አድርገን የመናገር ችግር አለብን፡፡ አንድን የፖለቲካ ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለን አንስተን ስንወያይ እውነታውን ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ ነን የሚለው መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እኔ መሰረታዊ ችግር ነው የምለው ይህንን ነው፡፡ በምድረ ኢትዮጵያ ስለዲሞክራሲ ሲነገር፣ ሲደሶከር፣ ሲዘመርና ሲተነተን ከአራት አስርት አመታት በላይ መቆጠሩ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን የተነገረውንና የታወቀውን ያህል የዲሞክራሲ ዘር ተዘርቶ ፍሬ ሲያፈራ አልታየም፡፡ ወይም ሊታይ አልቻለም፡፡ የዲሞክራሲ መርህ የተቀበሉ አብዛኛው የአለም ሐገራት ወደላቀ እድገት ብልጽግና እና የተሟላ ሰላም ተሸጋግረው ብሔራዊ እና ሀገራዊ ልእልናቸውን ለተምሳሌትነት ባበቁበት ዘመን እኛ ኢትዮጵያውያን ለዲሞክራሲ ባይተዋር ሆነን መገኘታችን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ስለዲሞክራሲ እያነበብን የምንብከነከንበት፣ ዲሞክራሲን ለማለም እንጂ ለመኖር ያልታደልን ህዝብ ለመሆን ተገደናል፡፡ በአጭሩ የዲሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የምንጠላለፍበት፣ ተጠላልፈንም የምንወድቅበት ሆኗል ብንል ስህተት አይሆንም፡፡

በዲሞክራሲ ሰበብ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከአርባ አመታት በላይ በተዘፈቅንበት ችግር ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ከነዚህ በርካታ ችግሮች መሀል ዋናው የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ በቀደምትነት እያቀነቀነ ለለውጥ የተነሳው ትውልድ (1960ዎቹ) ህይወት ተቀጥፏል፣ ሰበቡ ባመጣው ጦስ ምክንያት ምትክ የማይገኝላቸው ወጣቶች አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖችም ለሞት እና ለእስር ተዳርገዋል፤ አካላቸው መንፈሳቸውም እንዲኮላሽ ሆኗል፣ ቤተሰብ ተበትኗል….ወዘተ፡፡ በዚህም የተነሳ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና ውስጥ የማይሽር ቁስል እንደማህተም ተቀርጾ ሊኖር ግድ ሆኗል፡፡ ትውልዱ በዲሞክራሲ ስም የደረሰበት ግፍና በደል ሁሉ አንገት ደፊ ሆኖ ለመኖር እስከመወሰን ደርሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ እንዲህም ይሁን እንዲያ የዲሞክራሲን ስርዓት ለዚች ሀገር ለማስፈን የታገሉና የሚታገሉ አልጠፉም ፡፡ ግን ምን ያደርጋል? በየዘመናቱ ለሀገራዊ ራዕይ የተዋጣለት ስኬት ያስገኛል የተባለው ዲሞክራሲ ከተራ ቃልነት በዘለለ ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያስገኝ ይኸው እንዳለን አለን፡፡ ለምን?

እኛ ኢትዮጵያውን የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ስላልገባን? ወይስ ሊገባን የማይችል ስለሆነ? ወይም የዲሞክራሲን መሰረታዊ ሃቆች በቃል ብቻ የምናነበንበው ሌሎች ያሉትን እንደበቀቀን ደግመን የመናገር ልማድ ስለተፀናወተን? ወይስ ሌላ ያላየነውና ያልለየነው ምክንያት ይኖር ይሆን?… ወዘተ ብለን መጠየቅና ራሳችንን መመርመር ግድ የሚለን ይመስለኛል፡፡

በኢትዮጵያችን ለዘመናት የናፈቅነው ዲሞክራሲ እውን ሆኖ ህዝቦችዋ በሰላም እና በመተሳሰብ በጋራ አብረን እንኖር ዘንድ መልካም ምኞቴ ነዉ፡፡

dagnachew-tegegn.fw

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s