ግብጽ የዓባይን ወንዝ የመጠቀም ታሪካዊ መብቴ የምትለውን የቅኝ ግዛቱን ውል ወያኔን አስፈረመች! – ሠዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን አርጋው

Amsalu

ያሉን ታሪካዊ መዛግብት እንደሚያመላክቱት የዐባይ ወንዝ ከግብጽ ጋር በነበረን ግንኙነት ለውዝግብ ምክንያት መሆን የጀመረው ከሽህ ዓመታት ወዲህ እንደሆን ያስረዳሉ፡፡ እንዲያ እንዲያ እያለ መጥቶ በዐፄ ምኒልክ ዳግማዊ ዘመን እንግሊዝ ግብጽንና ሱዳንን ቅኝ ትገዛ በነበረበት ወቅት ለምትገዛው አካባቢ የዐባይን ወንዝ የውኃ ምንጭነት አስተማማኝ ለማድረግ በማሰብ የሀገራችን መንግሥት ሁለንተናዊ አቅም በዘመነ መሳፍንት የገጠመውን ስብራትና መዳከምን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የዐፄ ምኒልክ ዳግማዊን መንግሥት በመጫን እ.ኤ.አ. 1902ዓ.ም. አሳሪ ውል ለማስፈረም ጥረት አድርጋ ነበር፡፡ ይህ ውል እጅግ አወዛጋቢና በቀጥታም ከውጫሌው ውል ጋር ተመሳሳይ ይዘትና ቅኝት ያለው የተጭበረበረ ሰነድ ነው፡፡ የውሉ አንቀጽ የሚከተለውን ይል ነበር፡-

“His Majesty the Emperor Menilik II, King of Kings of Ethiopia, engages himself towards the Government of His Britannic Majesty not to construct or allow to be constructed any work across the Blue Nile, Lake Tana, or the Sobat, which would arrest the flow of their waters except in agreement with His Britannic Majesty’s Government and the Government of Sudan” “ከብሪታኒያ መንግሥትና ከሱዳን መንግሥት ጋር ከሚደረግ ስምምነት ውጭ በዐባይ በጣናና በባሮ ላይ ምንም ዐይነት ውኃውን ሊያቅብ የሚችል ግንባታ ላይደረግ” የሚል ነው፡፡ አማርኛው የውሉ ቅጅ የሚለው ደግሞ “የዐባይን ወንዝ ተፈጥሯዊ የፍሰት አቅጣጫ በመቀየር ወደሌላ አቅጣጫ እንዲፈስ ላይደረግ” የሚል ሆኖ ከእንግሊዝኛው ጋር ፍጹም የተራራቀ ትርጉም ያለው ነው፡፡

ይህ የቅኝ ግዛት ውል ሊሠራ የማይችልባቸው አራት ዐበይት ምክንያች አሉ እነሱም፡-

  1. ውሉ ከአንድ በሕግና ሥነ-ሥርዓት እተዳደራለሁ ከሚል መንግሥት ፍጹም በማይጠበቅና ሥነምግባር በጎደለው መልኩ በማጭበርበር በማታለል በማወናበድ የተሞላ በመሆኑ በሕግ ፊት እንኳን ተቀባይነት ኖሮት ገዥ ሊሆን ይቅርና ለማጭበርበር ለማታለል ለማወናበድ የሞከረውን አካል ፊርማና ማኅተም ያረፈባቸውን የእንግሊዝኛውንና የአማርኛውን ትርጉም በማናበብ ከሰነዱ መረዳት እንደሚቻለውና በግልጽ እንደሚያረጋግጠው ለማጭበርበር ለማታለል ለማወናበድ የሞከው አካል እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ወንጀል ለመፈጸም በመሞከሩ ቅጣት የሚጠብቀው በመሆኑና የተጭበረበረ ሰነድ በሕግ ፊት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ፡፡
  2. ይህ ውል ሲፈረም በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ማለትም በውሉ ላይ የተጠቀሰችው ሀገር ሱዳን ለዘለዓለም የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት እንደሆነች እንደምትኖር ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ በመሆኑና ይህ ሁኔታ ግን ዛሬ ላይ የሌለ የተሻረ የፈረሰ የተንኮታኮተ በመሆኑ ዛሬ ላይ ባለ መብት ነኝ የምትለዋ እንግሊዝ በቦታው የወሳኝነት ሥልጣን የሌላት በመሆኑ፡፡
  3. እንግሊዞች ሊያደርት የሞከሩት ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ከፍትሐዊነት የወጣ በመሆኑ፡፡
  4. በአማርኛው የውሉ ቅጅ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው “የዐባይን ወንዝ ተፈጥሯዊ የፍሰት አቅጣጫ በመቀየር ወደሌላ አቅጣጫ እንዲፈስ ላይደረግ” ይላል እንጅ በእንግሊዝኛው ላይ እንደሰፈረው “ከብሪታኒያ መንግሥትና ከሱዳን መንግሥት ጋር ከሚደረግ ስምምነት ውጭ በዐባይ በጣናና በባሮ ላይ ምንም ዐይነት ውኃውን ሊያቅብ የሚችል ግንባታ ላይደረግ” የሚል ባለመሆኑ፡፡ በእነዚህ አራት ዐበይት ምክንያቶች እ.ኤ.አ. 1902ዓ.ም. ከእንግሊዝ መንግሥትና ሱዳንን ይገዛ ከነበረው አሥተዳደሯ ጋር የተደረገው የተጭበረበረ የስምምነት ሰነድ ተቀባይነት አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ለነገሩ እነሱም ይሄንን በመረዳት ይመስላል ሲጨንቃቸው ካልሆነ በስተቀር ብዙም ሲጠቅሱት አይሰሙም፡፡

ይህ ውል ግብጽን የሚያካትት አልነበረም፡፡ ግብጽ ደግሞ በበኩሏ የዐባይ ወንዝ ባለመብት ነኝ ለማለት “ግብጽ የዐባይ ስጦታ ናት ወይም ዐባይ የግብጽ ስጦታ ነው፣ ዐባይን የመጠቀም ታሪካዊ መብት አለን” ይላሉ፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነና ታሪካዊ መብቱንና ዐባይንም በስጦታ ማን መቸ እንደሰጣቸው ተናገሩ ሲባሉ ግን ሊገልጽት የሚችሉት የሚጨበጥ ነገር የላቸውም፡፡ ከጭንቀታቸው የተነሣ ሀገራችን ዐባይን በተመለከተ እንዳትገዳደር ጥያቄ እንዳታነሣ ለመከላከል ያመነጩት ባዶና መሠረት የሌለው ቃል ነው፡፡ ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ሄሮዱቶስ ነው፡፡ ይሄንን ያለበት ምክንያትም ግብጽን በጎበኘበት ጊዜ የሥልጣኔዋ መሠረት የሕይወቷ እስትንፋስ ዐባይ መሆኑን በመረዳቱ እንደፈላስፋነቱ ይሄንን ሁኔታ በአጭር ቃል ልግለጸው ሲል የጠቀሰው ቃል ነው፡፡ ግብጾችም ከዚያ በኋላ ይህችን ቃል ይዘው ልክ እግዚአብሔር እንደተናገረው እያስመሰሉ ቋሚ መፈክር አድርገው ይዘውታል፡፡ ዐባይ ወደ ግብጽ የሚፈሰው የግብጽ ስጦታ ስለሆነ ሳይሆን ውኃ ቁልቁል መፍሰስ ተፈጥሯዊ ባሕርይው ስለሆነ ነው፡፡ ይህ አባባላቸው ትክክል ሊሆን ይችል የነበረው ዐባይን የፍሰት አቅጣጫውን አስቀይረነው ወዳስቀየርነው አቅጣጫ ፍሰስ ስንለው ወደ ግብጽ ካልሆነ አልፈስም የሚል ቢሆን ኖሮ ነበር፡፡

ግብጽ ከዚህ ተጨባጭነት ከሌለው ቅዠት ነክ አባባል በተጨማሪ ሀገራችን ዐባይን ገድባ ውኃውን እንዳትጠቀም ለማድረግ ከተቻለ ሀገሪቱን እስላማዊ አድርጎ በእስላማዊ ቃልኪዳን ማሰርና ለእነሱ ታማኝ እንድትሆን ማድረግ፡፡ ካልተቻለ ደግሞ ኢትዮጵያን ያልተረጋጋችና አንድነቷ ያልተጠበቀ አድርጎ አዳክሞ የማስቀረት ስልት (ስትራቴጂ) ነበር ዕድሜ ልካቸውን ሲጠቀሙብን የኖሩት፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግብጽና ሱዳን ከሀገራችን ውኃ እንዳያጡ እስካሁን ሲጠቀሙት የኖሩት ስልት የሚያዋጣና ተቀባይነት ያለውም አልነበረም ሕገ ወጥ ወንጀልና በሕግ ፊትም የሚያስጠይቃቸው ነው፡፡ ይህ ሕዝብ የሰቆቃና የመከራ ኑሮ እንዲገፋ ምክንያት ሆነዋልና ዋጋም ያስከፍላቸዋል፡፡ ግብጽና ሱዳን እኛን እየተማጸኑ እየለመኑ እየተለማመጡ ውኃ ከማግኘት ባለፈ እስከዛሬ ሲያደርጉት ከነበረው ግፈኛ ስልትና ድርጊታቸው አንዱንም እንኳ በእኛ ላይ እንዲያደርጉ እኛንም እንዲጫኑ እንዲያስገድዱ የሚደግፍ በዓለማ አቀፋዊው የመንግሥታቱ ድርጅት ማኅበርም ሆነ በሌላ የዓለም ሀገራት በአስገዳጅ መልኩ እንዲተዳደሩበት በተደነገገ ሕግ ምንም ዓይነት መብትና ሥልጣን የላቸውም ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ እንደ ግብጽና ሱዳን ሁሉ ሆድ የባሳቸው የተፋሰሶች የታሕታይ ሀገራት በመሰባሰብ የዓለም ሀገራት እንዲተዳደሩበት በመፈለግ “የወሰን ተሸጋሪ ወንዞችና የተፋሰስ ሀገራት የመተዳደሪያ ደንብ” ወይም ሕግ ብለው ማንም ሥልጣኑን ሳይሰጣቸው በራሳቸው ተነሣሽነት ያወጡት አንድ ሰነድ አለ፡፡ ይሁንና ይሄ በዓለም ሀገራትም ሆነ በመንግሥታቱ ድርጅት ተቀባይነት አግኝቶ እየተሠራበት ያለ ሕግ ባለመሆኑ ማንም በዚህ ሕግ የመተዳደር ግዴታ የለበትም ኖሮበትም አያውቅም ወደፊትም ይኖርበታል ብየ አላስብም፡፡ ምክንያቱም በተላያዩ አህጉራት ያሉ የላዕላይ ተፋሰስ ሀገራት ነገሩን መበተሳሰብ መፍታትን ይመርጣሉ እንጅ በአንዳች ዓይነት አሳሪ ወል ወይም ሕግ መታሰርና በዚያም ላይ መፈረም ፈጽሞ የሚፈልጉ ባለመሆናቸው ነው፡፡ እነኝህ ሀገራት በዚህ ጉዳይ ላይ የጸና አቋም ነው ያላቸው፡፡ እንግዲህ ያለው ዓለማቀፋዊ ሁኔታ እንዲህ በሆነበት ማለትም እንደሌሎቹ ሁሉ በፈቃደኝነት በመተሳሰብ ካልሆነ በስተቀር አስገዳጅ ሕግና ደንብ በሌለበት ሁኔታ ነው ወያኔ አሳሪና 100% ከዐባይ ውኃ ሀገራችን እንዳትጠቀም የሚያስር ውል ሊፈርም የቻለው፡፡

ሰሞኑን ሱዳን ውስጥ እንደተፈረመ ተደርጎ የተወራ ነገር ግን በሰነዱ ራስጌ ላይ የተጠቀሰው ቀን እንደሚያሳየው ተፈረመ ከተባለበት ሃያ ቀናት በፊት እንደተፈረመ በሚገልጠው ውል ላይ ግብጽ ሱዳንና ወያኔ የዐባይን ግድብና የዐባይን ውኃ በተመለከተ እንደተፈራረሙ ሰምታቹሀል፡፡ እስካሁን እንዳየሁት በዚህ በተፈረመው ውል ወያኔ ምን ያህል በዚህች ሀገር ላይ ዛሬም የሀገር ክህደት እንደፈጸመ፣ ሀገሪቱ ምን ያህል እንደተጎዳችና ልትጎዳም መሆኗን፣ ሉዓላዊነቷ መደፈሩን፣ ብሔራዊ ጥቅሟን መነጠቋን፣ መቀመጫዋ ላይ ተጨማሪ ፈንጅ መቅበሩን የተረዳን የገባል አልመሰለኝም፡፡

እኔ በግሌ የዐባይ ግድብ ግንባታ ሥራ ሲጀምር ከባድ ሥጋት ከጣለብኝና ግድቡ በወያኔ እጅ መገደቡን እንዳልወደው እንዳልቀበለው ካደረጉኝ ታች አምና በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ ከጠቀስኳቸው ስድስት ነጥቦች አንዱ ግብጽና ሱዳን ከባድ ተቃውሞ ማንሣታቸው ስለማይቀርና በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ግፊትና ጫና ወደ ድርድር መገባቱ ስለማይቀር ድርድር ከተደረገ ደግሞ ወያኔ በዓለማችን በተለያዩ አህጉራት እንዳሉት የላዕላይ ተፋሰስ ሀገራት ጠንካራ አቋም ይዞ በብልህነት በጥሩ የዲፕሎማቲክ (የአቅንኦተ ግንኙነት) ብቃትና ችሎታ የሀገራችንን ጥቅም የማስጠበቅ ሞራላዊ (ቅስማዊ) ፖለቲካዊ (እምነተ-አሥተዳደራዊ) ኢኮኖሚያዊ (ምጣኔ ሀብታዊ) ጥንካሬ አቅም ጽናትና ቁርጠኝነት የሌለው ከመሆኑ አንጻር እንደለመደው የቡድኑን ጥቅም በማስቀደም የሀገራችንን ጥቅም አሳልፎ ይሰጥብንና የሀገር ክህደት ይፈጽምብናል፣ የሀገሪቱን ጥቅም መቆመሪያ ያደርገዋል፣ ሀገሪቱን ለትውልድ የሚተላለፍ ችግር ላይ ይጥላታል የሚለው ሥጋቴ ከፍተኛ ስለሆነ ነበረ፡፡

“የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳ” ሆነና ነገሩ ምንጊዜም ምንም ነገር ቢሆን ከራሱ ጥቅም አንጻር ብቻ እንጅ ከሀገርና ሕዝብ ጥቅም አንጻር ወይም ሀገርና ሕዝብ ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግርና አደጋ ከመከላከል አንጻር ዐይቶ የማያውቀው ማየትም የማይፈልገው የሀገር ጥቅምን የማስቀደምም የሞራል (የቅስም) አቅም ወኔ ብቃትና ቁርጠኝነት ጨርሶ የሌለው የጥፋት ቡድን ወያኔ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ሉዓላዊነቷንም ጭምር ባስደፈረ መልኩ ታሪካዊ ክህደት በመፈጸም ውል ተፈራረመ፡፡ በዚህ ውል መፈረም የግብጽና ሱዳን ደስታ ገደብ አልነበረውም፡፡ እውነት እውነት መስሎም ሊታያቸው ካለመቻሉ የተነሣ ውሉ የሰጣቸውን ጥቅም ያህል መደሰት ጮቤ መርገጥ አቅቷቸዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ የተፈረመው ውል ግብጽና ሱዳን እ.ኤ.አ. 1959ዓ.ም. የዐባይን ውኃ ክፍፍል ባደረጉበት ጊዜ ለግብጽ 55.5 ቢሊየን (ብልፍ) ለሱዳን ደግሞ 18.5 ቢሊየን (ብልፍ) ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመከፋፈል ያደረጉትን ውል ባከበረ በጠበቀ በተስማማ መልኩ የዐባይ ውኃ ሙሉ በሙሉ 100% ባለመብትና ባለቤት መሆናቸውን በማረጋገጥ ነው ወያኔ የፈረመላቸው፡፡ ለዚህ ነው የተፈረመው በዚህ በአዲሱ ውል ግብጽና ሱዳን እ.ኤ.አ. 1959ዓ.ም. ስለተፈራረሙት የቀድሞው ኢፍትሐዊ ውል በዚህ አዲስ ውል ስለ መሻሩ ወይም መተካቱ የሚገልጸው ምንም ነገር እንዳይኖር ተደርጎ የተረቀቀው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አላወቀውም እንጅ ይህ ዜና ሁሉንም በየቤቱ መርዶ የሚያስቀምጥ ክፉ ዜና ነበር፡፡

ይሄንን ስል ውሉን ያነበባቹህ ወገኖች ሳትቀሩ “እንዴ! እንዴት ሆኖ? ውሉ ይሄንን ነው እንዴ የሚለው?” ብላቹህ ደንገጥ ማለታቹህ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እንዴት እንደሆነ ላስረዳ፡- ወያኔ ሱዳን ላይ ፈረምኩ የሚለው ውል “የግድቡ ተግባር” በሚለው አንቀጽ ስር እንደተገለጸው የዐባይን ግድብ ውኃ ወይም የዐባይን ወንዝ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት በስተቀር ለመስኖም ሆነ ለሌላ ውኃን ለሚጠቀም ለሚቀንስ ለሚያጎድል ምንም ዓይነት አገልግሎት መጠቀም እንዳይችል የሚያስር ውል ላይ ነው ፊርማውን ያስቀመጠው፡፡ በዚህም መሠረት ከእንግዲህ ሀገራችን ከዐባይ ግድብም ሆነ እግዚአብሔር ከሰጣት ታላቅ ሀብቷና ጸጋዋ ከዐባይ ወንዝ ውኃ አንድ ስኒ ውኃም እንኳን ቢሆን መቅዳት መጠቀም አትችልም፡፡ ከዚህ በኋላ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከላይ እንደገለጽኩት ሁሉ ሕጋዊ መሠረት የሌለው ቢሆንም ስለ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ጉዳይ እንዳታነሣ ታስራለች፡፡ ጥያቄውን የማንሣት መብት እንዳይኖራት ተደርጎ በብልጣብልጦቹና ዐይነ ደረቆቹ ግብጻዊያንና ሱዳናዊያን የዲፕሎማቲክ (የአቅንኦተ ግንኙነት) ቡድኖች ብቃታቸውን በሚገባ ባሳዩበት ውል ታስራለች፡፡ በውሉ ላይ በአንቀጽ 3 “ፍትሐዊ ክፍፍል” የሚል ቃል ቢሰፍርም ውሉ ፍትሐዊ ክፍፍል የሚለውን ሐሳብ የኢትዮጵያ ድርሻ ወንዙን ለኃይል ማመንጫነት መጠቀም ብቻ እንደሆነ ብልሀት ባለው ቅንብር አስፍረውታል፡፡ አንቀጽ 4 ላይ ደግሞ “ሌላውን ያለመጉዳት መርሕ” በሚለው አንቀጽ ደግሞ “በወንዙ አጠቃቀም ላይ ዓይነተኛ አደጋ አለመሆን” የሚለውን ቃል ውኃውን ለመስኖና ተመሳሳይ ተግባራት አለመጠቀም ማለት እንደሆነ በሚያስገነዝብ መልኩ ሰፍሯል፡፡ ባጠቃላይ ውሉ እንደሚያረጋግጠው የዐባይ ውኃ በዐባይ ግድብ ተገድቦ ተያዘም አልተያዘ ግብጽና ሱዳን እንደሚያምኑት ሁሉ የዐባይ ውኃ የእነሱ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ውሉ ይሄንን በማረጋገጡ ውኃው ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት ብቻ ግድቡን ለመሙላት በግድቡ ታቁሮ መያዙ ግብጽንና ሱዳንን የሚያሳስብ ሆኖ አላገኙትም፡፡ ምክንያቱም ውኃው በኢትዮጵያ ግዛት በኢትዮጵያ ግድብ ውስጥ ቢሆንም አንድ ስኒ እንኳን ሳይቀነስ ኃይል አመንጭቶ ወደ እነሱው እንደሚላክ ወያኔን በፊርማው እንዲያረጋግጥ አድርገዋልና ነው፡፡ ውሉ ከዚህም አልፎ ግብጽንና ሱዳንን “ግድባችን” የሚል ቃል በመጠቀምና በግድቡ የምህንድስና ሥራ ላይ ሁሉ ማለመብት አደድርጓቸዋል፡፡

በርካታ ሰዎች ይህ የተፈረመው ውል በአሻሚና ውሎ አድሮም ለውዝግብ በሚዳርጉ ግልጽ ባልሆኑ ቃላት የተሞላ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይምሰላቸው እንጅ ውሉን በግብጽና ሱዳን በኩል ቆሞ ለሚያየው ውሉ ምንም የሚያሻማ ነገር የሌለበት ጥርት ያለ ነው፡፡ ውሉ በአሻሚ ቃላት የተሞላ ሆኖ የሚታየው በእኛ በኩል ሆነን ስናየው ብቻ ነው፡፡ ይህ ውል ከፍተኛ የማታለል ብቃት ባላቸው ዲፕሎማቶች (አቅናኤ ግንኙነቶች) በሚገባ ታስቦበት እንደተዘጋጀ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የውሉ መሠረታዊ የአጻጻፍ ስልት A=B=C \ A=C የሚለውን የአተካኮ (substitution) አመክንዮን (logic) መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ወያኔ እንደደንቆሮነቱ በዚህ ስልት ወይም ቀመር የተቀናበረው ውል ምኑም አልገባው ሊገባውም አይችልም የሚያስረዳው ኖሮ አስረድተውት ቢገባውም ውሉ የሀገርን ጥቅም እንጅ ይዚህን የጥፋት የእርግማን ኃይል ቡድን ጥቅም የሚጎዳ ባለመሆኑ ግድ የለውም አይጸጸትምም፡፡

ቀድሞውንም ቢሆን ወያኔ ሥልጣን ከያዘ ማግስት 1985ዓ.ም. ጀምሮ ግብጽ ድረስ በመሔድ ምንነቱ ያልታወቀ ለሕዝብ ያልተገለጸና የተደበቀ ውል አቶ መለስ ከሆስኒ ሙባረክ ጋር ተፈራርሞ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚያም ተከትሎ “ዐባይን የማልማት የጋራ እንቅስቃሴ” (Nile basin initiative) እያለ ሲጠራው ከነበረው እንቅስቃሴ ጀምሮ ይንቀሳቀስ የነበረው በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለአፉ “የቅኝ ግዛትን ውል አንቀበልም፣ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ያስፈልገናል” ይበል እንጅ እንቅስቃሴውን ያደርግ የነበረው ግን ልክ ያ የቅኝ ግዛት ውል ይል እንደነበረው ሁሉ ግብጽንና ሱዳንን የዐባይ ወንዝ ባለመብትና ባለቤት እንደሆኑ አድርጎ በቆጠረ ግንዛቤ እባካቹህ እኔም እንድጠቀም ፍቀዱልኝ በሚል የልመናና የልምምጥ መንፈስ ነበር ያንን ሁሉ ዓመታት በገዛ ሀብታችን ባዕዳንን ደጅ ሲጠና የቆየው፡፡ በዚህም ወያኔ እራሱ ከማዋረዱ ባሻገር ውርደቱ ለሀገራችንም ተርፏል፡፡ እነሱንም የልብ ልብ እንዲሰማቸውና ይሄንን ያህል አብጠው እንዲታበዩ  አድርጓል፡፡ ወያኔ እንዲህ እራሱንም ሀገሪቱንም ባዋረደ መልኩ ይለማመጥ የነበረው በትጥቅ ትግሉ ወቅት ግብጽ “ኢትዮጵያን በማዳከምና የተረጋጋች እንዳትሆን ማድረግ” በሚለው መርሕ መሠረት ወያኔን በከፍተኛ ደረጃ ስትረዳ ስለነበረና ወያኔም የዐባይን ውኃ በተመለከተ ለግብጽ የገባላት ቃል ስለነበረ ነው፡፡ ስለሆነም ወያኔ እጅ የሰጠውና ክህደት የፈጸመብን አሁን ሳይሆን ገና ከድሮውም ጀምሮ ነበር፡፡

ሲናገረው የነበረው ነገር ሁሉም ሲተውንብንና ሕዝብ የሱን የክፋት የክህደት የጠላትነት ተግባሩንና ማንነቱን ዐውቆበት እንዳያምፅበት ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት የግብጽንና የሱዳንን ስምምነት “የቅኝ ግዛት ውል ነው አልቀበልም፣ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል መኖር አለበት” ምንትስ ይበል እንጅ ይህ አሁን የፈረመው ውል ከዚህ ቀደም በዚህች ሀገር ላይ ክህደት እየፈጸመ እንዳደረጋቸው በርካታ ክህደቶች ሁሉ ይህችን ሀገር መቀመቅ ለማውረድ አሲሮ እንደፈጸማቸው ክህደቶች ሁሉ ይሄንንም ውል የፈረመው ሳይገባው ሳያውቀው ቀርቶ ሳይሆን ተረድቶት አውቆት አምኖበት እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም የዐባይን ወንዝ በተመለከተ ይናገራቸው የነበሩት ቃላቶች የማስመሰልና የመደለያ እንደሆነ የሚያረጋግጠው ሲለው የነበረውን ሁሉ ገደል የከተተ ውል ሰሞኑን መፈረሙ ነው፡፡ ጉዳዩ የሦስትዮሽ መሆኑና በተለይም የግብጽ ሕዝብ ምን እየተካሔደ እንደሆነ በንቃት ስለሚከታተልና በግልጽ የማወቅ ፍላጎት ስላለው የግብጽ ባለሥልጣናትም ለወደፊቱ እማኝ እንዲሆናቸው ጉዳዩን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቅላቸው ስለፈለጉ ጉዳዩን መደበቅ አልተቻለም እንጅ እንደወያኔ ሐሳብና ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕይታና ይሁንታ ውጭ በድብቅ እንደፈረማቸው የክህደት ውሎች ሁሉ ይሄንንም ማንም ሳይሰማና ሳያይ በስውር ፈርሞ ቁጭ ሊል ነበር ፍላጎቱ አልሆነም እንጅ፡፡

እንደኔ እምነት አሁንም ቢሆን ማለትም ፊርማው ቢፈረምም ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በኃይል የተጫነ እንጅ በኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታና ምርጫ ሥልጣን የያዘ አካል ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔ በፈረማቸው ስምምነቶች ሁሉ የመገዛት ግዴታ አይኖርበትም፡፡ ይሄንን ማድረግ የምንችለው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ በተፈረመው ውል ላይ ተቃውሞውን ማሰማት የቻለ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ አሁን ይሄንን ማድረግ ካልቻልን ግን በውሉ እንደተስማማን ተደርጎ ተቆጥሮ ወደፊት የሚመጣው መንግሥት “ውሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታን ያገኘ አይደለም አልገዛበትም የሀገሬን ጥቅም አስከብራለሁ” ብሎ ለማለት እንዳይችል ያደርገዋል ወይም ይሄንን የማለት መብት ያሳጣዋል፡፡ መጪው በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን የሚይዘው የኢትዮጵያ መንግሥት ይሄንን የማለት መብት እንዲኖረው ማድረግ የምንችልው አሁን እኛ ይሄንን የክህደት ውል ተቃውመን የወጣን እንደሆን ብቻ ነው፡፡

ግብጽንና ሱዳንን በተመለከተ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለባት ግዴታ ቢኖር በሌሎች አህጉራት እንዳሉት እንደማንኛውም የላዕላይ የተፋሰስ ሀገራት ሁሉ ሰብአዊና ሞራላዊ (ቅስማዊ) እንጅ ሕጋዊ አይደለም ሊሆንም አይችልም፡፡ ሰብአዊውና ቅስማዊው ግዴታም ቢሆን የራስን ጥቅም ለአደጋ ባልዳረገ መልኩ እንጅ የራስን ጥቅም ለአደጋ ከመዳረግም አልፎ ሙሉ ለሙሉ 100% አሳልፎ እስከመስጠት አይደለም፡፡ “ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል” የሚለው ቃል ራሱ ትክክለኛ ያልሆነና ሱዳንና ግብጽ በእ.ኤ.አ. 1959ዓ.ም. እንዳደረጉት ውል ሁሉ የግብጽንና የሱዳንን ባለመብትነት ያከበረ የተቀበለ ቃል ነው፡፡ እየተጠቀሰ ያለውም በእኛ ላይ ብቻ ነው፡፡ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ክፍፍሉት ተቀበሉ ከተባለም ሀገራችን ለዐባይ ውኃ የምታበረክተው 86% በመሆኑ በቀረው 14% የነጭ ዐባይ መጠንም የባሮ ወንዝ ድርሻ ያለው በመሆኑና በቀጥታ አይሁን እንጅ መሬት ውስጥ በመስረግ የኦሞ፣ የማጎ፣ የጎጀብ፣ የጊቤ ወንዞችም ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ከዚህ ግዙፍ አስተዋጽኦዋ አኳያ የውኃው ክፍፍል ፍትሐዊ የሚሆነው ምን ያህሉ ድርሻ የኢትዮጵያ ቢሆን ነው ክፍፍሉ ፍትሐዊ የሚሆነው የሚለውምው ነገር መጤን ያለበት ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡

እንደኔ እንደኔ ግን በዐባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ በሌሎች አህጉራት እንዳሉት እንደ ሌሎቹ የላዕላይ ተፋሰስ ሀገራት ሁሉ ነገሩን ከሰብአዊነትና ከሞራል አንጻር ዕያየን በመተሳሰብ እያስተናገድን በመቀጠል ምንም ዓይነት ውል ላለመፈራረም የጸና አቋም መያዝ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም “መፈራረም መዋዋል” የሚባለው ጉዳይ እንደምናስበው ቀላል ያልሆነ ከጥቅም አንጻር ብቻ ሳይሆን ብዙ እጅግ የተወሳሰበና የሉዓላዊነት የነጻነትም ጉዳይ ያለበት ውስብስብ ጉዳይ ነውና፡፡ ይህ ወያኔ የፈጸመብን ክህደት በዓለም ታሪክ የማንም ሀገር ምንግሥት አድርጎት አያውቅም ወያኔ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከወያኔ ባለሥልጣናት አንደበት እንደሰማቹህት አሁን ወያኔ ከዚህ ውል አገኘው እያለን ያለው ጥቅም ልክ ውኃው የሚፈሰው ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ይመስል ለሰማው ሁሉ እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ “ግብጽ ውኃውን እንድንጠቀም ፈቀደች፣ በውኃው የመጠቀም መብት እንዳለን እውቅና ሰጠች፣ የዐባይ ግድብ እንዲሠራ ፈቀደች ተስማማች” በማለት ነው ነገር ግን “የመጠቀም” እያለ የሚገልጸው መብት የመብራት ኃይልን ለማመንጫነት ብቻ እንደሆነ በፍጹም ሊገልጽ አልፈለገም፡፡

ግብጽና ሱዳን ጉዳዩን እንደራሳቸው አድርገው ሊያዩት ይገባል፡፡ በሰው እጅ ያለን ንብረት የራሴ ነው ብሎ ማፍጠጥ ዐይን ያወጣ ሌብነት ነው፡፡ ሱዳንን እንደ ነዳጅ ዘይቷ አድርጋ እንድታየው ሊነገራት ይገባል፡፡ ሱዳን የነዳጅ ዘይትም እንደ ዓባይ ውኃ ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት ነው ብላ በነጻ ስትሰጥ ስታድል አላየንም፡፡ ግብጽም ብትሆን የዐባይን ውኃ ለመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በቧንቧ በማስተላለፍ ለመሸጥ ፕሮጀክት (የሥራ አቅድ) ነድፋ ስትንቀሳቀስ ውኃ የተፈጥሮ ሀብት ነው እኔም ያገኘሁት በነጻ ነውና በነጻ እንዳገኘሁት ሁሉ ውኃ ለቸገራቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በነጻ ልስጥ አላለችም፡፡

እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ካለህ ወያኔ እንደሚመለከትህም ተንቀሳቃሽ ሬሳ ካልሆንክና ነፍስህ ካለ ሀገሬ የምትል ከሆነ ዛሬ ነገ ሳትል ይሄንን የተፈጸመብህን ከፍተኛ ክህደት በኃይለኛ ንዴትና ቁጣ በመቃወም ወያኔ የፈረመው ውል አንተን እንደማይገዛ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ በማረጋገጥ ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጠህን የታላቁን ወንዝ የግዮንን የባለቤትነት መብት መልሰህ በእጅህ እንድታስገባ ሀገር አጥብቃ ትጠይቃለች፡፡ በሀገር ውስጥና ውጭ ያላቹህ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሕዝባዊ ማኅበራትና የሃይማኖት ተቋማት እንደሕዝብ አካልነታቹህ ይሄንን ሕዝባዊ ተቃውሞ በማስተባበርና በተሳካ ሁኔታ ተፈጻሚ በማድረግ የሚጠበቅባቹህን ታሪካዊ ኃላፊነት እንድትወጡ እንደ አንድ ዜጋ አሳስባለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!! ወያኔ ይውደም!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን አርጋው፡፡

satenaw

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s