የሰማዕታቱ ሰማዕትነት ለቤተ መንግስቱ እና ቤተ ክህነቱ የመጨረሻው የማስጠንቀቅያ ደወል ነው

cherkos addis ababa
ከጌታቸው በቀለ
(የጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)

ለሰማዕታቱ ለቅሶ አዲስ አበባ

ያለፈው ሳምንት እሁድ ለኢትዮጵያውያን እና ለመላው ዓለም አእምሮ የሚነሳ ግፍ ተፈፀመ። በአክራሪው አይ ኤስ ኤስ ስል ቢላዋ እና የጥይት አረር ሰላሳ ኢትዮያውያን ክርስቲያኖች ሊብያ ውስጥ ሰማዕትነት ተቀበሉ።ይህ መላው ዓለምን ያስደነገጠ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ቀልብ አስቶ ያስለቀሰ ጉዳይ ሌላ ሃዘን ተጨመረበት።ይሄውም ድርጊቱ ለመላው ዓለም የዜና አውታሮች በተለቀቀበት ሚያዝያ የሰንበት እለት ምሽት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገር ውስጡ ኢቲቪ ዜና ላይ ስለ ስማዕታቱ ለማየት እና የመንግስት የጉዳዩን አተያይ፣ቀጥሎም ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ የዕለቱ የመጀመርያ ዜና ሳይሆን ቀረ።ኢቲቪ የቱርክን ውለታ በቀዳሚ ዜናነት በጨርቃ ጨርቅ ምርት እያደረገች ያለችውን፣ቀጥሎ ኮርያ እያለ በሶስተኛ ደረጃ ድርጊቱን ”አይ ኤስ ኤስ የለቀቀው ዜና” የሚል ስም ከሰጠው በኃላ ”የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ካይሮ የሚገኘው ኤምባሲያችን እያጣራ ነው” በሚል ሰማዕታቱ ገና ለሞታቸውም እውቅና እንዳልሰጣቸው ተናገረ።የሚገርመው ይህንኑ ”ኢትዮጵያውያን መሆናቸው እየተጣራ ነው” የሚለውን አባባል ቤተ ክህነቱም ዘግየት ብሎ ደገመው።ይህ የሆነው የዓለም ታላላቅ የዜና አውታሮች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ባረጋገጡበት፣ገዳዩ ቡድንም በቪድዮ መልካቸውን እያሳየ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን በገለፀበት እና የሰማዕታቱ ቪድዮ በትትክክል ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አይደለም እኛ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎች በቀላሉ ሊለይ በሚችልበት መንገድ ነበር።

በሚቀጥሉት ቀናት የአዲስ አበባ ሕዝብ ማንም ሳይጠራው በእራሱ ያደረገው ሰልፍ እና ግፈኛውን ፅንፈኛ ቡድን አይ ኤስ ኤስ እና ኢህአዲግ/ወያኔን ያወገዘበት ሰልፍ የገዢዎቻችንን ልብ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም መክበራቸውን የዘነጉ የዘመናችን ቅምጥሎች የጥቅም ተጋሪዎችንም ሰውነት አራደ።የሚይዙት የሚጨብጡትን አጡ።የአዲስ አበባ ሕዝብ ”ሉዓላዊነት ማለት በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ዜጎችን መብት ማስከበር ማለት ነው!” የሚል እና ሌሎች መፈክሮችን ይዞ ወደ ቤተ መንግስት ተመመ።ስርዓቱ ሰራዊቱን አሰልፎ ለመግታት ሞከረ።ነገሩ ልመናም ነበረበት።ለተማፅኖ ከቀረበው መባ ውስጥ አንዱ እና ዋናው ”እባካችሁ ነገ ሮብ ሰልፍ ስለምንፈቅድ ያኔ በደንብ መሰልፍ ትችላላችሁ” የሚል ነበር።ህዝቡ ቤተ መንግስቱን ትቶ ወደ መስቀል አደባባይ እና ዋና ዋና መንገዶች ተመመ።በቀጣዩ ቀን ሮብ ሚያዝያ 14/2007 ዓም አዲስ አበባ ከአስር ዓመት በፊት ሚያዝያ 30፣1997 ዓም ወደነበረችበት የተቃውሞ መልክ ተቀየረች።ያለፈው ሳምንት ግን ከቀድሞው እጅግ በላቀ መልኩ ቁጣ፣ለቅሶ እና እልህ የተቀላቀለበት ነበር።

ቤተ ክህነቱ

ሰማዕታቱ የህዝብን አይን ይበልጥ ገለጡ፣የመሪዎቻችንን የስብዕና ደረጃ አየንባቸው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑት በሊብያ ሰማዕትነት የተቀበሉ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ጉዳይ በመንፈሳዊ ሚዛን ሲመዘን የቤተ ክርስቲያኒቱ የ21ኛው ክ/ዘመን መንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ በወርቅ ቀለም የሚፃፍ ታላቅ የሰማዕትነት ተግባር የፈፀሙ ናቸው።ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነት አዲስ ክስተት አይደለም።በዮዲት ጉዲት፣በግራኝ መሐመድ፣በፋሺሽት ጣልያን የአምስት ዓመት ወረራ፣ባለፉት 24 አመታት በ ደቡባዊ፣ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ስፍራዎች እና በጅማ በርካታ ክርስቲያኖች ሰማዕትነት ተቀብለዋል።

ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሰማዕትነት ክብር እንጂ ውርደት አይደለም።ጌጥ እንጂ ጉድፍ አይደለም። የፅናት ምልክት እንጂ የድክመት መገለጫ አይደለም።ይልቁንም በእዚህ ዘመን ያውም በወጣት አማኞቿ በእዚያ በበረሃ ከሳሽ እና ወቃሽ በሌለበት ለእምነታቸው የታመኑ ምዕመናን ዛሬም በፅናት መቆማቸውን የሚያሳይ ልዩ የተስፋ ችቦ ነው።የቅዱስ ጊዮርጊስን፣የቅዱስ ቂርቆስን እና የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እና የሌሎች አያሌ ሰማዕታትን የምትዘክር ቤተ ክርስቲያን ሰማዕታቱ አሁንም የክብር ፈርጦቿ ናቸው።በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በሰማእታቷ ይበልጥ ትነጥራለች እንጂ ፈፅሞ የኃልዮሽ ጉዞ ምልክት አታሳይም።

ሰማዕታት ዓለምን የሚንጡበት ልዩ መንፈሳዊ ኃይል አላቸው።በ1929 ዓም በፋሽሽት ጣልያን በጥይት የተደበደቡት የአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት መላ ኢትዮጵያን በአዲስ መንፈስ አስተሳሰረ።ከከተማ እስከ ገጠር ኢትዮጵያውያንን አነጋገረ። ፍርሃት ገፈፈ።ለኢትዮጵያ ነፃነት ኢትዮጵያውያንን አንድ ልብ አደረገ።በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጆችን አስነሳ።የኢትዮጵያ የታሪክ ተመራማሪ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ እናት እንግሊዛዊቷ ሲልቭያ ፓንክረስ ኢትዮጵያን ብላ ከሀገር ሀገር ተንከራተተች።በበረሃ ያሉ የኢትዮጵያ አርበኞች እና የከተማ የውስጥ አርበኞች በአዲስ መልክ ተነሱ።ስማዕታት መላው አለምን የመናጥ ኃይላቸው ልዩ ነው። የቅዱስ እስጢፋኖስ መወገር ከስምንት ሺህ በላይ የሚሆኑ የጉባዔው ታዳሚዎች ይብሱን በየስፍራው ተበትነው ክርስትናን አፀኑ።የቅዱስ እስጢፋኖስ ስማዕትነት ይብሱን አፅናቸው።የቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነትም እንዲሁ መላዋ ሮምን ብሎም አውሮፓን በሃይማኖት አፀና ከእዚህ ሁሉ አልፎ ክርስትና የሮም ቤተ መንግስትን አንዘፍዝፎ ወደ ክርስትና ቀይሯል።

ዛሬም የዘመን ልዩነት ካልሆነ በቀር የሰማዕታት ክብርም ሆነ የህዝብን አይን የመግለጥ ፀጋቸውን አይተንበታል።የመሪዎቻችንን የግፍ ዳር አየንባቸው፣ኢትዮጵያ ቤተ መንግስቷ ክፍት መሆኑን፣ውሳኔ የመስጠት ብቻ ሳይሆን ብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የማይድረዱ ሰዎች ስብስብ መሆኑን ከመቸውም ጊዜ በላይ ወደ አጥንታችን እስኪዘልቅ ድረስ ገባን።ከወጣት እስከ ሕፃን፣ ከህፃን እስከ ሽማግሌ በልበ ሙሉነት ኢትዮጵያን በጎሳ የከፋፈላትን ስርዓት በግልፅ በአደባባይ ”ሌባ ነህ” አሉት።የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ከእረጅም ዓመታት መተኛት በኃላ የዩንቨርስቲውን ኩሩ ታሪክ ከተጣለበት አቧራውን አራግፈው የቤተ መንግስቱን አጥር ”የሀገር አንበሳ የውጭ ሬሳ” እያሉ እየዘመሩ አለፉ። እርግጥ ነው።በእዚህ ሁሉ መሃል የስርዓቱ ቅልቦች ካለ አንዳች ርኅራኄ በወጣቶቹ ላይ የዱላ ውርጅብኝ አወረዱባቸው።ቂርቆስ የሚገኘው ሃዘንተኞቹ የተሰበሰቡበት ስፍራ በፖሊሶች ተበተነ።የኢትዮጵያ ልጆች በታሪካቸው ከተፈፀሙት አበይት ግፎች ውስጥ የሚዘከሩ ተግባራት በአዲስ አበባ ተደረገ።እናቶች አለቀሱ።ወጣቶች እግራቸው ተሰበረ፣እጃቸው በፖሊስ ዱላ ተቆለመመ።ሰማዕት በሆኑት ያለቀሰው ሕዝብ ዳግም በእራሱ ሀገር ፖሊስ ተደበደበ።በሺህ የሚቆጠሩ ታሰሩ።ወዳልታወቀ ቦታ ተውሰዱ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት በብዙ የአሰራር ጉድለቶች ሲወቀስ የነበረ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የአስተዳደር መዋቅር ወጥነት አለመኖር፣ግልፅ የገንዘብ አያያዝ አለመኖር፣ካለ ችሎታችው አገልጋዮችን በማይመጥናቸው ቦታ መመደብ፣የቅዱስ ሲኖዶስ አሰራር እና ደንብ በፓትራሪኩ ጣልቃ ገብነት መበላሸት፣ቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢው ቦታዋን በሁለንተናዊው የሀገሪቱ እንቅስቃሴ አለማግኘት እና ቤተ ክርስቲያን ለተበደሉት፣ፍትህ ላጡት ፣ለታሰሩት እና ለተሰደዱት ድምፅ አልባ መሆኗ ሁሉ የቤተ ክህነቱ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፈው ሳምንት ያሰማው ድምፅ የመጨረሻ ደወል አይደለም ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም።ቤተ ክህነቱ ከቤተ መንግስቱ ጋር የሚኖረው አግባብነት የሌለው መሞዳሞድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ትችቶች ብቻ ሳይሆን ምመናኗንም ከፍ ወዳለ ቅሬታ መርቶታል።ለችግሩ መፍትሄ ካልተሰጠው ሕዝብ አንድ ቀን በእራሱ ኃይል መፍትሄ እንደሚሰጠው መታወቅ አለበት።የሰማዕታቱ ደም በልቦናው የተቀበረ ምዕመን የኢህአዴግ/ወያኔ ቅልብ ወታደር ይፈራል ማለት ዘበት ነው። አሁንም ግን ቤተ ክህነቱ ይህንን ደውል በውቅቱ ተረድቶ ለማስተካከል መነሳት ካለበት አሁን ነበር።ግን አይመስልም።

ቤተ መንግስቱ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ በሕዝብ የታወቁ እና ያልታወቁ ሰማዕትነት የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም ሕዝብ ክፉኛ ያስደነገጠው የዛሬ አርባ ዓመት በደርግ የተገደሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የወቅቱ ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ።ከእዛ ወዲህ የጅማው የፅንፈኞች በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ላይ የፈፀሙት ግድያ እና አሁን በሊብያ የተፈፀመው ዋነኞቹ ናቸው።እዚህ ላይ ኢህአዴግ/ወያኔ ለሊብያው ጉዳይ የሰጠው ቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን አሁን በፅንፈኛው አይ ኤስ ኤስ የተከበቡትን ኢትዮጵያውያውን ክርስቲያኖች ለመርዳትም ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማሳየቱ አሁንም ሕዝብ በመንግስቱ ተስፋ ከቆረጠበት አያሌ ጥፋቶች ጋር ተዳምሮ ዛሬም ትኩስ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ አለ።

የኢህአዴግ/ወያኔ መንግስት ዘግይቶ የሶስት ቀን ሃዘን ማወጁን ይግለፅ እንጂ ይህንን ያደረገው በሕዝብ ተገዶ መሆኑ የድርግቶቹ ሂደት በእራሳቸው በሚገባ አጋልጠውታል።የኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይ ለማንኛውም አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጋለጧ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልፅ ሆኗል።በመንግስትነት የተቀመጠው አካል በሁለት መልክ ይገለጣል።የመጀመርያው መገለጫ ለዜጎቹ ምንም የማያደርግ ባጭሩ ሽባነት (Non-functionality) ሲሆን ሁለተኛው መገለጫው ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሳይሆን የጎሳ ዜጋ የሚያውቅ መሆኑ ነው። አሁን ጥያቄው ቤተ ክህነቱም ቤተ መንግሥቱም ቤተ ክህነቱም ያለፈው ሳምንት የህዝብ እንቅስቃሴ የሚያስተምሩት እና ሹክ የሚሉት ጉዳይ አድርገው ወሰዱት። የመጨረሻ ደውል! ከእዚህ በኃላ ”ቀሚሰ አወላከፈኝ” የለም።ሕዝብ ከተነሳ የሚመልሰው የለምና።
yilikal
ሽባነት (Non-functionality)

ኢህአዴግ/ወያኔ የመንግስት መዋቅሩም ሆነ አጠቃላይ እንቅስቃሴው ወደ ሽባነት (Non-functionality) መቀየሩ በግልፅ ታይቷል።አንድ መንግስት ወደ ሽባነት ሲቀየር የሀገር ውስጥ የፖለቲካ፣የምጣኔ ሀብት እና የማህበራዊ ችግሮችን ሁሉ በጉልበት ብቻ እና ብቻ ለመፍታት ይነሳል።እርግጥ ኢህአዴግ/ወያኔ ይህ በሽታ ከጀመረው መቆየቱ ይታወቃል።በእጅጉ የባሰበት ግን በ1997 ዓም ምርጫ ክፉኛ ከተመታ በኃላ መሆኑ ይታወቃል።ላለፉት አስር አመታት ምንም የማይሰራ የሽባነት በሽታው አድጎ አሁን በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን በባዕዳን መከራ ሲቀበሉ ምንም ማድረግ የማይችል ተመልካች ወደመሆን መቀየሩ በግልፅ ታይቷል።በሳውዲ አረብያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩኢትዮጵያውያኖች በግፍ ሲባረሩ ጠንከር ያለ መግለጫ ማውጣት አልቻለም።በተመሳሳይ መንገድ ሊብያ ለተፈፀመው የግፍ ተግባርም ሆነ በደቡብ አፍሪካ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን ሁሉ ከዝምታ ባልተሻለ መልክ ማለፉ ሌላው የሽባ መንግስት መገለጫ ሆነው ቆትይተዋል።

ለጎሳ ዜጋ ቅድምያ የመስጠት አባዜ

በሊብያ ሰማዕታት ጉዳይ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት ”ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ላጣራ” ያለበት ምክንያት እጅግ ታሪካዊ ስህተት የሰራበት ብቻ ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገዛውን ድርጅት ማንነት ለማወቅ የቻለበት ነበር።ምን ያህል ሰብዓዊ አስተሳሰብ የራቃቸው፣ከዓለም አቀፍ መረጃ የራቁ፣እንደመንግስት አይደለም እንደ አንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በፍጥነት ውሳኔ የመስጠት የአቅም ድህነት ላይ ያሉ እና የሚመሩትን ሕዝብ በጥላቻ እና በቂም የሚመለከቱ መሪዎች ኢትዮጵያ እንደተሸከመች ፍንትው ብሎ ታየ።የሚገርመው መንግስት ”ላጣራ” እያለ ሲያላግጥ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ዋይት ሃውስ ድርጊቱን ኮንነው ማዘናቸውን የሚገልፅ መግለጫ አወጡ።ሰማያዊ ፓርቲ ድርጊቱን ኮንኖ የመንግስትን ቸል ባይነት አስምሮ አወገዘ።ምን ይሄ ብቻ የሁለቱ የሟች ቤተሰቦች ከቤተ መንግስቱ ዝቅ ብሎ ቂርቆስ ሰፈር እያነቡ፣ሕዝቡም ለቅሶ እየደረሰ ነበር።

ይህ ጉዳይ በጣም አስደንጋጭ ነው።መላው ዓለም ስለእኛ ያለቅሳል፣ሃገራት የሃዘን መግለጫ ይልካሉ፣ሃዘንተኞች ለቅሶ ላይ ናቸው፣መንግስት ግን ”ኢትዮጵያዊነታቸውን ገና እያጣራሁ ነው” አለ።ይህንን ያለው ቪድዮው ለዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከተለቀቀ ከ 16 ሰዓታት በኃላ መሆኑን ልብ በሉ።ይህ ድርጊት ለመጪው ትውልድ አይደለም አሁን ላለነውስ ማን በትክክል ሊያስረዳን ይቻላል።ለምን አንድ መንግስት ነኝ ያለ አካል ዜጎቹን እና ሀገሪቱን በእንዲህ ያህል ደረጃ ስልጣጣኑን ወዶ ህዝብን ጠልቶ ይገኛል።ለምን? መልሱን ታሪክ በሚገባ ይመረምረዋል።ለጊዜው ግን አንድ ነገር ማለት ይቻላል።ለኢሕአዴግ/ወያኔ ”ኢትዮጵያዊ ዜጋ” የሚባለው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ብዙውን ምላሽ ያሰጣል። እንደ ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በጎሳ ካልተጠራን እንደማያውቁን አልጠፋንም።ችግሩ በመንግሥትነት የተቀመጠው አካልም በእራሱ በፈጠረው ዓለም ውስጥም ከጎሳውም ”ዜጋ” የሚለው ስም የተሰጣቸው ትናንሽ ”ልዑላን” ሃገሩን እንደሞሉት ያስረዳል።ለህወሓት የኪነት ቡድን ለደረሰበት የመኪና አደጋ ከሰበር ዜና ባላነሰ መደናገጥ ዜናውን ያነበበው ኢቲቪ፣”አንድ የቀድሞ ታጋይ አረፉ” ለሚል ዜና ቀዳሚ ዜናው የሚያደርገው ኢቲቪ፣ለሰላሳ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ቀዳሚ ዜና ማድረግ አቃተው።ለዚያውም ኢትዮጵያዊነታቸው አልተረጋገጠም አለን።
ethiopian killed by isil 1
ባጠቃላይ

በሊብያ ሰማዕትነት የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በሶስት ቀናት ውስጥ ብዙ ነገሮችን ቀይረዋል።
የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር አስጠብቀዋል፣
ከሊቅ እስከደቂቅ ልቡ እየነደደ የቤተ ክህነቱ እና የቤተ መንግስቱን ጥፋት ካለ አንዳች ፍራቻ ከማውገዙም በላይ ለማስተካከል ቃል የገባበት ታሪካዊ ኩነት ሆኗል፣
ሕዝብ እርስ በርሱ እንዳይፈራራ ፈር ቀዷል፣
የችግሩ ምንጭ ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ ማለትም የገዢው ኢህአዴግ/ወያኔ የተሳሳተ ፖሊሲ እና ስልጣን እንደ ከረሜላ የጣማቸው የስርዓቱ መዘውሮች መሆኑን ከእዚህ በፊት የደመደመውን ለመጨረሻ ጊዜ አረጋግጧል፣
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለህሊና በሚከብድ ደረጃ ለኢትዮጵያውያን ስቃይ እና መከራ ልባቸው የማይደነግጥ በባዕዳን ዘንድም የሌለ የጥላቻ እና የጭካኔ መንፈስ በመሪዎቹ ላይ ተመልክቷል።

በባዕድ ሀገር ስደት እና መገፋት ሊገታ የሚችለው ኢትዮጵያ በጎሳ ከፋፍሎ ከሚገዛት የኢህአዲግ/ወያኔ አገዛዝ ነፃ መውጣት ስትችል ብቻ መሆኑን ቀደም ብሎ በለዘብተኛነት የሀገሩን ጉዳይ ስመለከት የነበረው ኢትዮጵያዊ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተረዳበት እና የወሰነበት ጊዜ ነው።ያወቀ እና የወሰነ ሕዝብ ለማታለል መሞከር ደግሞ ብዙ ዋጋ ማስከፈል ብቻ ሳይሆን እንዳይሆኑ ሆኖ መውደቅን ያስከትላላ።

እነኝህ ሁሉ ክስተቶች ሕዝብ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እንደደረሰ በግልፅ አመላክተዋል።ጉዳዩን ኢህአዴግ/ወያኔም ምን ያህል በሕዝብ ታንቅሮ እንደተተፋ በአይኑ አይቷል።በጆሮው ሰምቷል።ይልቁንም በእዚህ ወቅት ብዙዎች ከጎኑ የነበሩ የስርዓቱ አካላት ትተው የሚኮበልሉበት ትክክለኛ ጊዜ መሆኑን ያለፈው ሳምንት ክስተቶች ሁሉ እንዳስተማሯቸው ከግምት በዘለለ መረዳት ይቻላል።አንድ ቀን የቦሌ መንገድም በሕዝብ ይዘጋል።አንድ ቀን ከቤት ሳሉ በሕዝብ ኃይል የመታሰር ዕጣ እንደሚገጥም ደጋፊዎቹ ከግምት የዘለለ እውነታ እየሸተታቸው ነው።ችግሩ ለመፍትሄው እራሳቸውን አንድ አካል ማድረግ እና ወደፊት ከመሄድ ይልቅ በትናንሽ አስተሳሰቦች እየተጠለፉ እራሳቸውን እየደለሉ መገኘታቸው ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ እና ጭላንጭል ማየት የጀመረው አሁን ነው። ያለው አማራጭ አንድ እና አንድ ብቻ መሆኑ በሰማእታቱ ደም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም በበለጠ ተከስቷ።ይሄውም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መንግስት አሁን በስልጣን ያለውን ስርዓት መቀየር ብቻ ነው።ይህ እንዴት ይሆናል? እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

ፖሊስ በ‹‹በሁከትና ብጥብጥ›› ተጠርጣሪዎች ላይ ሦስት መዝገብ አደራጅቻለሁ አለ •እነ ወይንሸት ለሁለተኛ ጊዜ 6 ቀን ተቀጥሮባቸዋል

•እነ ወይንሸት ለሁለተኛ ጊዜ 6 ቀን ተቀጥሮባቸዋል
•‹‹ወይንሸት ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ስታሸብር ነበር›› ፖሊስ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል፤ ተካፍላችኋልም›› በሚል ፖሊስ ባሰራቸው ሰዎች ላይ ሦስት የተለያዩ መዝገቦች ማደራጀቱን አስታውቋል፡፡
addia ababa
ዛሬ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ሌሎች በዕለቱ የተያዙ ሰዎችን በተመለከተ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ እንደገለጸው፣ ፖሊስ የራሱን ቡድን በማዋቀር ተጠርጣሪዎችን በሦስት መዝገቦች ስር እንደየተሳትፏቸው አደራጅቻለሁ ብሏል፡፡ በዚህ መሰረት በሶስተኛው መዝገብ ላይ ያካተታቸውን በርካታ ታሳሪዎች አጣርቶ መልቀቁን የገለጸው ፖሊስ፣ በሁለተኛውና በአንደኛው መዝገብ ላይ ባሉት ተጠርጣሪዎች ግን ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጹዋል፡፡

አንደኛው መዝገብ ላይ በእነ ወይንሸት ሞላ መዝገብ 5 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን አራቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፤ አንደኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች መሆኗን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለሆነም በዚህ መዝገብ የተካተቱት ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ማስተዋል እና የፓርቲው አባል ያልሆነችው ቤተልሄም ይገኙበታል፡፡ ማስተዋል በዛሬው ዕለት ቀደም ብሎ የተሰጠው የቀጠሮ ቀን ስላልደረሰ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡ ቤተልሄም ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሳልሆን አባል ነሽ እየተባልኩ ምርመራ ይደረግብኛል፤ ሌሊት እየተጠራሁ እመኝ እየተባልኩ ነው›› ስትል ለፍርድ ቤቱ ገልጻለች፡፡
weyeneshet molla
በሁለተኛው መዝገብ ላይ ደግሞ 15 ተጠርጣሪዎች ተካትተዋል፡፡ ፖሊስ በዚህ መዝገብ በተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክሱን ሲያሰማ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ተጠርጣሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሲያደርጉ ‹ጠንካራ መሪ እንጂ ጠንጋራ መሪ አንፈልግም›፣ ‹ወያኔ አሳረደን›፣ ‹ፍትህ የለም!››› በማለት ሁከት እንዲነሳ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡››

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በምርመራ ወቅት የገጠማቸውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ያሰሙ ሲሆን፣ በተለይ የሚደረግባቸው ምርመራ ከፓርቲው ጋር የተያያዘ እንጂ ከተጠረጠርንበት ጉዳይ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምርመራው ከጉዳዩ ጋር የሚገናኝ አይደለም፤ ሌሊት ሌሊት እየተጠራሁ ምርመራ ይደረግብኛል፡፡ የፓርቲ አባል መሆን ወንጀል እስኪመስለኝ በፓርቲ አባልነቴ ጫና ይደረግብኛል፡፡ በዚያ ላይ የጤና እከል ገጥሞኛል፤ ህክምና ያስፈልገኛል›› ስትል ለፍርድ ቤቱ ያስረዳችው ወይንሸት ሞላ፣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡

በሁለቱም መዝገብ የተካተቱት ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ በመጀመሪያው መዝገብ ላይ ያሉት እነ ወይንሸት ላይ የምርመራ ስራውን እንዳልጨረሰ በመግለጽ 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በተለይ ወይንሸት ሞላ ላይ ፖሊስ፣ ‹‹ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ተመሳስላ በመልበስ ስታሸብር ነበር›› በማለት ዋስትና እንዳይሰጥና የጠየቀው የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ በሁለተኛው መዝገብ ላሉት ደግሞ 7 ቀን ፖሊስ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በሁለቱም መዝገብ ላይ በተመሳሳይ የ6 ቀን ጊዜ በመስጠት ለሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች እስር አሁንም እንደቀጠለ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ በትናንትናው ዕለትም ሦስት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባላት (አንደኛው አሁን ላይ የሰማያዊ አባል) መታሰራቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በታሠሩ ጋዜጠኞች ብዛት በአፍሪካ አንደኛ ነች VOA

ryot

ኢትዮጵያ እሥር ላይ የምትገኘውን ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን፤ ቪየትናም ደግሞ የኢንተርኔት ፀሐፊዋን ወይም ብሎገሯን ታ ፎንግ ታንን እንዲለቅቁ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች፡፡

ኢትዮጵያ እሥር ላይ የምትገኘውን ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን፤ ቪየትናም ደግሞ የኢንተርኔት ፀሐፊዋን ወይም ብሎገሯን ታ ፎንግ ታንን እንዲለቅቁ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቃል አቀባይ ጄፍ ራትካ ናቸው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ይህንን የመንግሥታቸውን ማሳሰቢያ ያስተላለፉት፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዚህ ሣምንት እያወጣቸው ባሉ ተከታታይ የፕሬስ መግለጫዎች በዓለም ዙሪያ በየእሥር ቤቱ ያሉ ጋዜጠኞችን በየቀኑ እያነሣ ይገኛል፡፡

በዚህ “FREE THE PRESS” ወይም “ፕሬስን ነፃ አውጡ” በሚለው ዘመቻው የዛሬው የመሥሪያ ቤቱ መግለጫ ካተኮረባቸው ሁለት ጋዜጠኞች አንዷና ቀዳሚዋ የቀድሞ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህር ኢትዮጵያዊቱ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ነች፡፡

በፀረ-ሽብር ሕጉ መሠረት በተመሠረተባት ክሥ ጥር 10/2004 ዓ.ም ተፈርዶባት እስከዛሬ ወኅኒ ቤት እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ጄፍ ራትካ ጠቁመዋል፡፡

“… ርዕዮት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ በተመሠረቱባቸው ክሦች ምክንያት ከታሠሩ 18 ጋዜጠኞች አንዷ ስትሆን ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ በአህጉሩ ብዙ ጋዜጠኞችን በማሠር ቀዳሚዋ እንድትሆን አድርጓታል …” ብለዋል፡፡

ርዕዮት የመንግሥቱን ፖሊሲዎች የሚተቹ ፅሁፎችን በጋዜጣ በማውጣቷ ምክንያት በሰኔ 2003 ዓ.ም ተይዛ የሽብር ፈጠራ ክሥ ከተመሠረተባት በኋላ የ14 ዓመት እሥራት ተፈርዶባት እንደነበረ ያስታወሱት ራትካ የእሥራት ዘመኗ ወደ አምስት ዓመት ዝቅ እንዲል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በነሐሴ 2004 ዓ.ም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ክሡ ሙሉ በሙሉ እንዲሠረዝላት በተከታታይ ያቀረበቻቸው የይግባኝ አቤቱታዎች ውድቅ መደረጋቸውንም ራትኮ አመልክተዋል፡፡

“… ሃሣብን የመግለፅ ነፃነት መብቷን ተግባራዊ በማድረጓ ብቻ ታሥራ የምትገኘውን ርዕዮትን እንዲፈታ ለመንግሥቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን – ያሉት ራትኮ – መንግሥቱ ፀረ-ሽብር አዋጁን ሃሣብን በነፃነት የመለዋወጥን ተግባር ለመጠምዘዝ ጉዳይ ከመጠቀም እንዲቆጠብም እናሳስባለን …” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጄፍ ራትኮ በመቀጠልም በአውሮፓ የዘመን አቆጣጠር የ2013 ዓ.ም ጀብዱ ፈፃሚ ሴቶች ዓለምአቀፍ ሽልማት ያሸነፈችውና የቪየትናምን መንግሥትና ኮምዩኒስት ፓርቲውን የሚተቹ ፅሁፎችን ኢንተርኔት ላይ በማውጣቷ የአሥር ዓመት እሥራት ተፈርዶባት ወኅኒ የምትገኘው ታ ፎንግ ታንን የቪየትናም መንግሥት በአፋጣኝ እንዲለቅቅ መንግሥታቸው እንደሚያሳስብ አስታውቀዋል፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 25ኛ በዓለ ሢመታቸው መታሰቢያነቱ በሊቢያ ለተሰውት እንዲሆን አሳሰቡ

“…ይሁን እንጅ ይህ ጊዜ ልጆቻችን በስደት ሀገር በሃይማኖታቸው ምክንያት በሰይፍ እየታረዱ ያሉበት ጊዜ በመሆኑ የተዘጋጀው የ25ኛ ዓመት በዓለ ሲመት መታሰቢያ፣ የመርሐ ግብር ማሻሻያ ተደርጎበት፣ በሊቢያ ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፪ሺ፯ ዓ.ም ለተሰየፉትና በጥይት ተደብድበው ለሞቱት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የመታሰቢያ በዓል እንዲሆን ይደረግ ዘንድ በአክብሮት አሳስባለው።” [ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]

አባ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

Message from His Holiness Abune Merkorios

የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ

የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ
የተከበራችሁ ወገኖቼ፤ ከሰላሳ በላይ የሆኑ ወገኖቻችን አይ ሲስ በተሰኘ ህሊና ቢስ፣ ፀረ-ሰው እና ፀረ-ስልጣኔ ቡድን በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ የመገደላቸው መርዶ ከትናንት ወዲያ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓም ደርሶን ኢትዮጵያዊያን በያለንበት በመሪር ሀዘን ውስጥ ነን። ዛሬ “እግዜር ያጥናህ” ወይም “እግዜር ያጥናሽ” የሚባል ሰው የለም። ሁላችንም ሀዘንተኞች ነን። ካጣናቸው ቁጥራቸው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ወገኖቻችን አሁንም በአራዶች መዳፍ ውስጥ መሆናቸው ሀዘናችን እጅግ የበረታ ያደረገዋል። ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ ሆኖም በሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ሊቢያ ውስጥ ናቸው። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አሁንም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ናቸው። ሌሎች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ደግሞ በየመን ከሰማይም ከምድርም በቦንብና በጥይት እየተማገዱ ነው።
ለምንድነው ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እሳት ውስጥ ለመማገድ የምንደፍረው? መልሱ ግልጽ ነው። አገር ውስጥ ተስፋ የለም፤ ወያኔዎች ተስፋችንን አጨለሙት። ከሳዉዲ በመከራ የተመለሱ ወንድሞቻችን ናቸው በሊቢያ በኩል ለመሰደድ ሲሞክሩ በአይ ሲስ ተይዘው የታረዱት። ወያኔዎች አገራችንና ክብራችን ዘረፉን። ወያኔዎች ስብዕናችንን ገፈፉን።
የዘመኑ ጥቂት የህወሓት ቱጃሮች ፎቆችን እየገነቡ በነሱ መጥገብ እኛ እንድናገሳላቸው ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መራቡ፣ መታረዙ፣ መደህየቱ እውነት ነው፤ ሆኖም ግን “ተራብኩ”፣ “ታረዝኩ”፣ “ደኸየሁ” ብሎ መናገር አይችልም። እውነት መናገር ያስቀጣል፣ ያስወነጅላል። በፍርደ ገምድል ችሎት እውነት መናገር “ሽብርተኛ” ያስብላል። እስር ቤቶችን የተሞሉት ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለነፃናትና ለእኩልነት በቆሙ ሰዎች አይደለምን?
በአይ ሲስ ያሳረደን ማነው? መልሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነው። ያዋረደን፣ በአይ ሲስ ቢላዋ ያሳረደን ህወሓት ነው። እንደ አገርና እንደ ሕዝብ የደረሰብን ውርደት የትም ብንሄድ የምናመልጠው አልሆነም። በአገር ውስጥ የደረሰብንን ውርደት ለማምለጥ ስንሰደድ ውርደት ተከትሎን ይመጣል።
ወገኖቼ፤ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ የተሻለች አገር ሊኖረን አይችልም። ዛሬ የመሸሻ ጊዜ አይደለም። አገራችንን ከወያኔ ነጥቀን፤ በአገራችን ኮርተን በሰላም መኖር እንሻለን። ይህ መብታችን ነው። አገራችን የኛ ነች። አገራችን የጥቂት ወያኔዎች መፈንጫ አይደለችም።
ወገኔ፤ ዛሬ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓም በአርበኖች ግንቦት 7 ስም የማደርግልህ ጥሪ አድምጠኝ። በሀይማኖት፣ በብሔር፣ በጾታ ልዩነት ሳታደርግ ዛሬ በአንድነት እንደተሳህ አንድነትህን እንደጠበቅህ ቀጥል። አንድነትህን ለመሸርሸር ወያኔ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፤ ለወያኔ ዱለታ ጆሮህን አትስጥ። የወያኔ አገዛዝ እንዲያበቃ በአንድነት ተነስ። ዛሬ የጀመርከው ትግል እዳር ሳይደርስ እረፍት የለንም።
አርበኞች ግንቦት 7፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአፋር፣ ከኦጋዴን፣ ከጋምቤላ፣ ከቤሻንጉል ድርጅቶች ጋር በመጣመር የአገር አድን ኃይል የመገንባት ሥራውን እያጠናቀቀ ነው። እኛ ልጆችህ በብሔርም ሆነ በሀይማኖት ሳንከፋፈል፤ ከትግራይ እስከ ኦጋዴን፤ ከአፋር እስከ ጋምቤላ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ባካተተ ስብስብ ውስጥ አብረን ህወሓትን እየታገልን ነው። ይህ ትግል ግን የአንተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ነው። የትግሉም የአገሪቷም ባለቤት አንተ ነህ። ስለሆነም ተነስ! “እንቢኝ” በል። ዘርፈ ብዙ የትግል ስልቶችን በመጠቀም ወያኔን አዳክም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በትግልህ ፍሬ የአገርህ ባለቤት ሁን።
የመከላከያና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ሆይ!እናንተ የሕዝብ አካላት ናችሁ። የደረሰብንን ብሔራዊ ውርደት እያያችሁ፤ እሮሮዓችን እየሰማችሁ በሕዝብ ላይ መተኮስ በራሳችሁ ጭንቅላት ላይ መተኮስ ማለት መሆኑን ለደቂቃ እንኳን አትዘንጉ። ይልቁኑ ዛሬውኑ ነፃነትና ፍትህ ከጠማው ወገናችሁ ጎን ቁሙ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች፤ የወጣትነት የፈጠራ ችሎቻችሁ መፈተኛው አሁን ነው። ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳይ መመሪያ እስኪሰጣችሁ አትጠብቁ። እያሰላችሁ፣ እያጠናችሁ፣ እያደባችሁ፣ ወያኔን ታገሉ።
የታፈረች፣ የተከበረችና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን።

ዜጐችን ለስደት የሚዳርጉ አሳማኝ ምክንያቶች መፍትሔ ይፈለግላቸው!

ዜጐችን ለስደት የሚዳርጉ አሳማኝ ምክንያቶች መፍትሔ ይፈለግላቸው!

የዜጐችን ስደት በተመለከተ አገራችን ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ቆማለች፡፡ የአገሪቱን ዜጐች ለስደት የሚያነሳሳው ምክንያት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው የሚሉ ወገኖች ያሉትን ያህል፣ አገሪቱ ለዜጎቿ የምትመች ባለመሆኗ በምሬት

እየተሰደዱ ነው የሚሉም አሉ፡፡

ስደትን ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ አውጥተን ምክንያታዊ በሆኑ ትንተናዎች በመታገዝ ካልፈተሽነው በስተቀር፣ ለመፍትሔ የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሰው አገር ይኖራሉ፡፡ በየጊዜውም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ባገኙት መንገድ ሁሉ እየተሰደዱ ነው፡፡ አገሪቱ ለዘመናት ከተጫናት ድህነት ለመላቀቅ በምታደርገው ጥረት መጠነኛ የሆነ የገጽታ ለውጥ ብታደርግም፣ አስከፊውን ድህነት ለማስቆም አልተቻለም፡፡ በተለይ ወደ አውሮፓ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደ ደቡብ አፍሪካ ዜጐች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት እየነጐዱ ነው፡፡ አደጋው በከፋበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንኳ ስደቱ ቀጥሏል፡፡ ለምን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ስደቱን ለማስቆም ምን ማድረግ ይገባል ማለትም አለብን፡፡ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለይቶ ለማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡

መንግሥት አሁን የደረሰውን አሳዛኝ ክስተት ተንተርሶ፣ ዜጐች ከአደጋ ራሳቸውን ለመጠበቅ በሊቢያም ሆነ በሜዲትራኒያን ባህር፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የተፈጸሙትን ሰቆቃዎች እንደ ማስጠንቀቂያ እንዲያዩት ያሳስባል፡፡ ሕገወጥ ደላሎችንም በምክንያትነት ያቀርባል፡፡ በአገሪቱ የተፈጠረውንም መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ ይመክራል፡፡ በሌላ በኩል ግን አሁንም በጣም የተንሰራፋው ድህነት የብዙዎችን ተስፋ እያጨለመ ነው፡፡ ከአቅም በላይ የሆነው ሥራ አጥነት ለብዙዎች ከሚቋቋሙት በላይ ነው፡፡ በየጊዜው እየናረ የሚሄደው ኑሮ ብዙዎችን እያስመረረ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥረው አድሎአዊነት የምሬት ምንጭ ነው፡፡ በፖለቲካው ንፍቀ ክበብ ውስጥ የሚታየው አማራጭ አልባነትና የአንድ ወገን የበላይነት ብቻ መኖር ቅሬታውን እያጎላው ነው፡፡ የሥራ ዕድልን እያቀጨጨ ነው፡፡ የፖለቲካው መሳሳብ ለብዙዎች አግላይ ሆኗል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከገጠር ወደ ከተማ የሚካሄደው ፍልሰት ከመጠን በላይ ከመሆኑ የተነሳ ለመቆጣጠር አልተቻለም፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች በመከፈታቸው ምክንያት የምሩቃን ቁጥር ከአቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ ወጣት የሚበዛባት ኢትዮጵያ በተጠና የሥራ ፈጣሪነት ክህሎትና ዕውቀት ባላቸው ዜጐች አማካይነት ችግሮቿን መፍታት ካልቻለች፣ ስደት ወደፊትም ብሔራዊ ችግር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ደግሞ አሳማኝ የሆኑ የስደት ምክንያቶች መሬት ወርደው ሁሉን አሳታፊ የሆነ ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ መፍትሔ የሚገኘው ጥሬ ሀቁ ላይ መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው፡፡

በገጠር በቤተሰብ መበራከት ምክንያት የአርሶ አደሮች ማሳ እየጠበበ በሚሄድበት ጊዜ ወጣቶች መሬት አልባ ስለሚሆኑ ወደ ከተማ ይፈልሳሉ፡፡ በከተማ የሥራ ዕድሉም የተጣበበ ስለሚሆን ወደ ውጭ መሰደድን አማራጭ ያደርጋሉ፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶችም ተቀጥሮ ከመሥራት ጀምሮ ሥራ ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት መሰናክሉ ስለሚበዛ የሚታያቸው ስደት ነው፡፡ በአነስተኛና በጥቃቅን ተደራጅቶ ለመሥራት መሬት፣ የባንክ ብድርና ገበያ ማግኘት በጣም አዳጋች በመሆኑ ወጣቶች ለሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተበድረውም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ወስደው ካቅማቸው በላይ የሆነ ክፍያ እየፈጸሙ ይሰደዳሉ፡፡

ይህንን ዓይነቱን አደጋ የበዛበት ስደት ከሚያባብሱ ዋነኛ ችግሮች መካከል ደግሞ ተጠቃሽ የሚሆነው ተስፋ ቆራጭነት ነው፡፡ ይህ ተስፋ ቆራጭነት የሚመጣው ደግሞ ወጣቶች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በአስተዳዳሪዎች የሚፈጸሙ በደሎች ሲበዙ ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የሚያስተባብላቸው፣ ነገር ግን የሰላ ትችቶች የሚቀርቡበት በገጠር ከማዳበሪያና ከምርጥ ዘር ጀምሮ እስከ ዕርዳታ እህል ድረስ ሥርዓቱን በማይደግፉት ላይ ክልከላ መደረጋቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ በደል ሲፈጸም መንግሥት በተለያዩ መዋቅሮቹ አማካይነት ችግሮቹን መፈተሽ ባለመቻሉ ለወጣቶች ምሬት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ እንጀራ የሚፈልግ ሰው በመገፋቱ ምክንያት የፖለቲካ ስደተኛ ይሆናል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ጊዜያት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ብዙ የተባለበት ነው፡፡ የፖለቲካ ትስስር ያላቸው ብቻ ተጠቃሚ በመሆናቸው ምክንያት ብዙኃን እየተገለሉ ነው ሲባል ከማስተባበል ይልቅ ችግሩን ማረም ይበጃል፡፡ ይህም ጠንከር ያለ ዕርምጃ ይፈልጋል፡፡

ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ ጭርንቁስ ሠፈሮች ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች በተባባሰ ድህነት ውስጥ ስለሚኖሩ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስደትን ይመርጣሉ፡፡ በተለያዩ ሙያዎች ሥልጠና ያገኙ ወጣቶች ሳይቀሩ ሥራ አጥተው ይቦዝናሉ፡፡ ብዙዎቹም በመጠጥ፣ በጫት፣ በሺሻና በሌሎች ዕፆች ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በተስፋ መቁረጥ ውስጥም ሆነው እነዚህ ወገኖች አጋጣሚውን ካገኙ መሰደድ ነው ፍላጐታቸው፡፡ በቅርቡ በስደተኛ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው አረመኔያዊ ግፍ አገሪቱን ማቅ አልብሷት እንኳን፣ የመጣው ይምጣ ብለው ለመሰደድ የተዘጋጁ ብዙዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡ በሠለጠኑበት ሙያ ለመሥራት፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣትና ለመሳሰሉት አቅም በማጣታቸው መሰደድን አማራጭ ማድረጋቸውንም እየተናገሩ ነው፡፡ ዜጐች በአገራቸው ለምን ተስፋ ይቆርጣሉ? ዕድሎች ለምን አይመቻቹላቸውም? መጠነኛ ገንዘብ ኖሮአቸው ለመሥራት ሲፈልጉ እንኳ እንዲበረታቱ ለምን የተለየ አሠራር አይዘረጋም? ችግሮቹን ከሥር ከመሠረታቸው በማየት መፍትሔ ለምን አይፈለግም?

መንግሥት ዘወትር የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈጥሩዋቸው ምሬቶችን በተመለከተ ሲያወሳ ይሰማል፡፡ በተግባር ግን የሚታይ ለውጥ የለም፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች የታዩ ስኬቶች የኢትዮጵያ ወጣቶች መለያ እንደሆኑ ተደርጐ ሲቀርብ ይታያል፡፡ ችግሩ የብዙኃን አይደለም ተብሎ ይሸፋፈናል፡፡ እንዳለፈው ሳምንት ዓይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ግን ለብጥብጥ መነሻ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ዜጐች ውስጥ የሚሰሙ ቅሬታዎችና እሮሮዎች በታመቁ ቁጥር ድንገት ሲፈነዱ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ ወጣቶች በአፍላነታቸው ጊዜ ሲከፉና አደጋ የበዛበትን ስደት አማራጭ ሲያደርጉ እንደ አገር ሊከብደን ይገባል፡፡ ለመፍትሔውም መጨነቅ አለብን፡፡ መፍትሔውም ከወገንተኝነት የፀዳ ውሳኔ ነው፡፡

አገሪቱ ከድህነት ማጥ ውስጥ ለመውጣት እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ናት፡፡ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ የሚታዩት አዝማሚያዎችም ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ ነገር ግን የዛሬው ልፋት የዛሬውን ወጣት ማዕከል ካላደረገ ልፋቱ ሁሉ ውኃ መውቀጥ ነው፡፡ ልማቱ ሰብዓዊ ፍጡራንን ጭምር ያካት ሲባል የአገሪቱ ዜጐችን ታሳቢ ማድረግ አለበት ማለት ነው፡፡ ዜጐች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሲከበሩ፣ ከአገሪቱ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሲጠቀሙ፣ ሐሳባቸውን በነፃነት ሲገልጹ፣ ለቅሬታዎቻቸው በቂ ምላሽ ሲያገኙ፣ በገዛ አገራቸው የባለቤትነት ስሜት ሲሰማቸው፣ የፈለጉትን በሰላማዊ መንገድ መደገፍ ወይም መቃወም ሲችሉና በአገሪቱ ሁሉም ጉዳዮች ውስጥ ያለአድልኦ ሲስተናገዱ ስደትን ሙሉ በሙሉ ማቆም ባይቻል እንኳ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል፡፡ ለአገሪቱ ወጣቶች ስደት አንድ ምክንያት ብቻ እየመዘዙ ዲስኩር ማሰማት ከትርፉ ይልቅ ጉዳቱ ይብሳል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ስምምነት የለም፡፡ ብሔራዊ ጉዳዮቻችን ከስሜታዊነት ባልፀዱ አመለካከቶች እየተቃኙ ናቸው፡፡ በጋራ ጉዳያችን ላይ ተስማምቶ አንድ አቋም ለመያዝ ቀርቶ መነጋገር እንኳን ባለመቻሉ ክፍፍሉ አስጊ እየሆነ ነው፡፡ አንዱ ሌላው ላይ ጭቃ እየለጠፈ በጥላቻ በመፈራረጅ ላይ ጊዜውን ስለሚያጠፋ የወጣቶቻችንን ችግር በቅጡ ለማየት አልተቻለም፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከመበጀት ይልቅ መጠፋፊያ መስሏል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን በተስተዋሉ ክስተቶች ላይ እንኳን፣ በግራም በቀኝም ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በጊዜያዊነት መግባባት አቅቷቸው በየፊናቸው የመሰላቸውን አቋም ሲያራምዱ ታይተዋል፡፡ ይኼ እንደ አገር ሲታይ አስጊ ነው፡፡ ወጣቶቻችንን የስደት አለንጋ እያንገበገባቸውና ሕይወታቸውም እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ሲያልፍ፣ አንድ ላይ ሆኖ ለመምከር አለመቻል ትልቅ በሽታ ነው፡፡ ጽንፍ በረገጡ አቋሞች ምክንያት አንገብጋቢ የሆኑት ብሔራዊ ጉዳዮች እየተዘነጉ ከቀጠሉ ጉዞው የት ድረስ ይቀጥላል? ውጤቱስ ምንድነው? ካልተባለ ችግር አለ፡፡ ይህ በብርቱ ይታሰብበት፡፡ ጨርሶ ከመተው ዘግይቶም ቢሆን መጀመር የግድ ይላል፡፡

ወጣቶቻችን ትልቅ ትኩረት ይሰጣቸው፡፡ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸው ይታመን፡፡ ከተመሪነት ይልቅ ለመሪነት ይዘጋጁ፡፡ አገሪቱ ያላት አንጡራ ሀብት እነሱ ላይ ኢንቨስት ይደረግ፡፡ መብቶቻቸው ይከበሩ፡፡ አድልኦ አይፈጸምባቸው፡፡ በአገራቸው አንገታቸንው ቀና አድርገው የሚሄዱ ኩሩ ዜጎች ይደረጉ፡፡ አላስፈላጊ ከሆኑ ደባል ሱሶች ጥበቃ ይደረግላቸው፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ዕድሉ ይመቻችላቸው፡፡ በአገራቸው ጉዳይ ንቁና ዋነኛ ተዋናይ ይሁኑ፡፡ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለዚህ አገራዊ ጥሪ ርብርብ ያድርጉ፡፡ ለስደት መንስዔ የሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች መፍትሔ ይፈለግላቸው!

ኢትዮጵያ በየአመቱ በርካታ ወጣቶች ጥለዋት ከሚሰደዱ ሀገሮች ዋነኛዋ እንደሆነች የታወቀ ነው

ለወጣቶቹ መሰደድ ደግሞ ብዙ ምክንያቶች ይነሳሉ አልጄዚራ በድረ-ገጹ ባወጣው ፅሁፍ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በማለፍ ለኢትዮጵያውያኑ መሰደድ በዋነኛነት የሚነሱ ምክንያቶችን ዘርዝሯል

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገሮች መካከልም ስሟ የሚጠራ ቢሆንም ዜጎቿ ግን መሰደድን አላቆሙም በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ በሚመርጡት ህገወጥ ስደት ብዙዎች እየሞቱ ይገኛሉ

በከተሞች አካባቢ አጥጋቢ የስራ እድል አለመኖሩ, በአብዛኛው የሚሰሩ ስራዎች የዜጎችን ህይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚችል አለመሆኑ, በየጊዜው የኑሮ ውድነት እየጨመረ መምጣቱ እና ሌሎች ብዙ ምክንያቶች ይነሳሉ

አልጄዚራ ባወጣው ፅሁፍ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በፖለቲካ ሁኔታ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው አነስተኛ የሚባል አይደለም ለዚህም እንደማጣቀሻ ጥሩ የስራ እድል የሚያገኙ ዜጎች ከመንግስት የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ቅርበት ያላቸው መሆናቸው ይነገራል
ሁላችንም እንደምናውዘቀው በዜጎች ላይ እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ በግልፅ የሚታይ እውነታ ነው ነገር ግን ለሚደርሰው ጥፋት በዋነኛነት ተጠያቂ ሊሆን የሚችለውን አካል ለእያንዳንዳችን ግንዛቤ እንተወውና በሁላችንም ዘንድ ምን መፍትሄ ማምጣት ይቻላል?

ማን ምን ቢያደርግ ይሻላል ትላላችሁ? በኩራት ታሪክ እየጠቀስን ብቻ የሀገርን ገፅታ መለወጥ እንችላለን?

የኛ ሀገራዊነት ስሜት ስፖርታዊና ስፖርታዊ ባልሆኑ ውድድሮች ላይ ብቻ የሚንፀባረቅ አይመስላችሁም?

የእናንተ ሀሳብ ምንድነው?