ኹራፋተ ተኩላት ወዳንኤል ክብረት! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

እንደምታስታዉሱት ባለፈው ጊዜ ከቤተክርስቲያን ትከሻ ላይ ተፈናጦ የወያኔ ቅጥረኛ በመሆን የሀገርን የቤተክርስቲያንንና የሕዝብን ታሪክ ማንነትና እሴት እየቆነጻጸለ እያጠፋፋ እያሳከረ እያወደመ ስላለው ተኩላ ዳንኤል ክብረት ከወያኔነት ድፍረቱ በመነጨ ሳይፈራና ሳያፍር በድፍረት የጻፋቸውን ጽሑፎቹንና የሰጣቸውን ቃለ መጠይቆችን መረጃ በመጥቀስ አንባቢያንና ምእመናን ይጠነቀቁበት ዘንድ በሁለት ጽሑፎች ማንነቱን ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ ጀሌዎቹ ዳንኤል ተከታትለው ለወጡት ጽሑፎቸ አሳምሮ ምላሽ እንደሚሰጥ ተስፋ አድርገው እየተጠባበቁ ነበር፡፡ እኔ ዳንኤል ለእነኝህ ጽሑፎች በራሱ ስም መልስ ለመስጠት እንደማይሞክር እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ በሦስት ምክንያቶች 1ኛ ዳንኤል መልስ ልስጥ ብሎ መልስ ለመስጠት ቢሞክር በሚሰጠው መልሱ ይበልጥ ማንነቱ እንዲገለጥ ስለሚያደርገውና ይሄ እንዲሆን ስለማይፈልግ፡፡ 2ኛ. እንደልማዱ መልስ እሰጣለሁ ብሎ ጽሑፉ ላይ ከማተኮር ይልቅ እኔን ለማጥቃት በማሰብ በእኔ ማንነት ላይ አነጣጥሮ ፈጥሮም አጋኖም በሚጽፈው ነገር ለራሱ ዓሣ እጎረጉራለሁ ብሎ ዘንዶ እንደሚያወጣ ስለሚያውቅ፡፡ ማለትም እራሱ በቀደደው መንገድ የሚሰጠውን ተመሳሳይ ምላሽ የሚቋቋመው ስለማይሆን፡፡ ስንት ጉድ አለበት መሰላቹህ ይሄ ጉደኛ? 3ኛ. የተጻፈበት ጽሑፍ በሚገባ በመረጃ የተጠናከረና መረጃዎቹም በሰው እጅ ያሉ በመሆናቸው አምኖ ከመቀበል ውጪ ፈጽሞ ሊያስተባብለው የሚችለው ነገር ስላልሆነ፡፡ በእነኝህ 3 ምክንያቶች መልስ ለመስጠት እንደማይሞክር እርግጠኛ ነበርኩ፡፡

ጀሌሎቹ ግን ዳንኤል ምን ዓይነት ችግር ውስጥ እንዳለ ባለመረዳት በሌሎቹ ላይ በለመደው ቀላጤ አፉ ተንጰርጵሮ ዋሽቶም ወስልቶም አንጀታቸውን እንደሚያርስላቸው እርግጠኛ በመሆን ምላሹን እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ይሁንና ዳንኤል የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረባቸው፡፡ ምስጥ የበላው እንጨት ድጋፋቸው ዳንኤል ምንም ለማለት ባለበቻሉ በሐፍረት ተሸማቀቁ ቅስማቸው ተሰበረ፡፡ ከዚያም በየፊናቸው በየ ድረ ገጻቸውና ብዙዎቻችንም በምንጽፍባቸው ድረ ገጾች ማንነታቸውን ደካማነታቸውን ድውይነታቸውን አላስተዋይነታቸውን ከሚያሳይ በስተቀር ፍሬ አልባ እንቶ ፈንቶ ጽሑፎችን እየቸከቸኩ በመለጠፍ የተጫናቸውን የሐፍረት ሸክም ለማቅለልና አሁንም ቢሆን ለተኩላው ያላቸውን ታማኝነት ለማረጋገጥ ጥረቶችን ሲያደርጉ ሰነበቱ፡፡

አሁን በመጨረሻ የስለአዳም ለት (8-8-2007ዓ.ም) ዲ/ን ዶክተር መሐሪ ወሰን በተባለ ሰው ስም በፒ.ዲ.ኤፍ. የሰነድ አቀማመጥ (file format) የተጻፈና በኢትዮሚዲያ ድረ ገጽ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ አንድ የዳንኤል ጀሌ ላከልኝና አነበብኩት፡፡ ሊጻፍለት የሚገባ ምንም ፍሬ ቢስና ነውረኛ ቢሆንም ወደ ኋላ በምገልጻቸው ምክንያቶች ለዚህ ጽሑፍ ግን መልስ ለመስጠት ግድ አለኝ፡፡ ጽሑፉን ሳነበው በጣም ነበር የተገረምኩት፡፡ የተኩላውን ቡድን ማንነት ይበልጥ እንድረዳ የረዳኝ ጽሑፍ ነበር፡፡ ጽሑፉ ጅማ ባለ አንድ ዶክተር ነኝ በሚል ምን ዶክተር ብቻ ዲ/ንም ነኝ በሚል ሰው እንደተዘጋጀ ይገልጣል፡፡ ጽሑፉ በዶክተር እንዲሁም በዲያቆን የተዘጋጀ ነው ይበል እንጅ የሰውየውን ዶክተርነትና ካህንነት ሊያሳየኝ ሊያስገነዝበኝ የሚችል ብስለት፣ መረዳት፣ ግንዛቤ፣ አደብ፣ የሞራል (የቅስም) ከፍታና ትሕርምት ምንም አላገኘሁም፡፡ የተማረ ሰው ለሞራል (ለቅስም) ድንጋጌዎች ዋጋ ይሰጣል ክህነትን ሲጨምር ደግሞ ለሃይማታዊ ድንጋጌዎች ዋጋ የሚሰጥ ይሆንና ሰውየውን የበለጠ ከፍታ ላይ እንዲገኝ ያደርገዋል ትሕርምተኛ ያደርገዋል፡፡ ሆኖ የተገኘው ግን በተቃራኒ አቅጣጫ ላይ ነው፡፡ አንድ ዶክተርና ዲ/ን የሆነ ሰው አግባብነት በሌለው ጥላቻ ምክንያት የጠላውን ለመጉዳት ሲል ብቻ ማንም ሰው በቀላሉ ሊያረጋግጣቸው የሚችላቸውን ነጫጭ ውሸቶችንና ፈጠራዎችን ፈልስፎ ሰውን በመወንጀል እራሱን አያዋርድም ለትዝብት አይዳርግም አምላኩን አያሳዝንም፡፡ ይሄ የደናቁርቱና የእርኩሳኑ መለያ እንጅ የምሁርና የእግዚአብሔር አገልጋይ መለያ አይደለም፡፡ እንግዲህ በወያኔዎች ቤት ዱክትርና በየሱቁ እየተሸመተ የሚያጌጡበት ስም ከሆነ ቆይቷልና ይሄም ሰው እንግዲህ የዚሁ ተቋዳሽ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሊሆን ይችላል ምሁራዊ ተዋስዖ ልናገኝበት ያልቻልነው፡፡

ይህ ጽሑፍ በዚህ ሰው ስም ወጣ እንጅ የተዘጋጀው በዚህ ዶተርና ዲያቆን ነኝ ባለን ሰው ብቻ አይደለም፡፡ ጽሑፉ የተጻፈው በደቦ ነው ይሄንን የሚያሳዩ በርካታ ጉዳዮች ከመኖራቸውም በላይ እያዘጋጁ እንደነበር መረጃው ነበረኝ፡፡ በደቦው ውስጥ ዳንኤል ዋነኛው መጋቢ ነው፡፡ እነኝህ ተኩላት ይንን ጽሑፍ ለመጻፍ ሲወስኑ ምንም ሊሉ የሚችሉት ነገር ባይኖርም እንኳን እንደነሱ ግምት ምንም ይሁን ምን የሆነ ነገር ተብሎ ከበድ ያለ መልስ አለመሰጠቱ በጀሌዎቻቸው ላይ የሚያደርሰውን የቅስም ስብራት የከፋ ያደርገዋል ከሚል ግምት ለዚህ ሲባል ብቻ ይሄንን ከንቱነታቸውን ይበልጥ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ጽሑፍ ለመጻፍ ቻሉ፡፡ እንዳልኳቹህ ይህ ጽሑፍ ሲዘጋጅ እየተዘጋጀ እንደነበረ መረጃው ነበረኝ፡፡ ስማቸውን ብጠቅስ ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር ነገር ግን ጽሑፋቸው ላይ ሲሉ እንደሰማቹሀቸው እንከሳለን እያሉ እየዛቱ ስለሆነ ከሳሾቸን ላለማብዛት ስል ስም ከመጥቀስ እቆጠባለሁ፡፡ እነዚህ በማኅበረ ቅዱሳን በተለያየ የአገልግሎት ኃላፊነት የነበሩ ጀሌዎቹ በየአቅጣጫው ተሰማርተው የሚያውቀኝን ሁሉ “እስኪ ስለ አምሳሉ የምታውቁትን ንገሩን?” እያሉ መረጃ ለመቃረም ጥረት ሲያደርጉ ነበር የሰነበቱት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ያገኙት መረጃ ግን ያልፈለጉትና ግልባጭ ሆነ፡፡ መጥፎ መጥፎ የተባለውም በፈለጉት ደረጃ እኔን ሊያረካክስ የሚችል ሳይሆን ቀረ፡፡ ይባስ ሐፍረት ተሰማቸው በጽሑፌ ላይ በማተኮር ሥርዓት ባለው መንገድ ሐሳብን በሐሳብ ከመሞገት ይልቅ የተሰበረ ቅስማቸውን ለመጠገን እኔን አዋርዶ ግዳይ መጣል ብቸኛ የመጠገኛ ተስፋቸው ነበርና፡፡ መሬት ላይ ያለው ሀቅ እንዲህ ተስፋቸውን ከንቱ ሲያደርግባቸው ሌላ አማራጭ አላጡም ይህም የተካኑበትና ከወያኔነታቸው ያገኙት ትሩፋት ነው፡፡ “የእማማ ዓለሚቱን ቅቤ” በመቀባት በውሸት ወይም በፈጠራ ወሬ ስሜን ማርከስና በዚያ መርካት፡፡

አንዴ አንድ ቦታ በነበርኩበት ጊዜ ነው አንድ ቀን እዚያ ቦታ ካሉ ሰዎች አንደኛቸው የሆኑ እናት እማማ ዓለሚቱ ድካም ቢጤ ተጫጫናቸውና ለአንድ አፍታ ሸለብ አድርጓቸው ትንሽ ቆዩና ወዲያው ተነሡ፡፡ ሲነሡ ከማሸለባቸው በፊት የነበረው ከፊታቸው ይታይ የነበረው የድካም የመጠውለግ የመኮሰስ የረሀብ የመታከት ስሜቶች በሚደንቅና በሚያስገርም ሁኔታ ድራሻቸው ጠፍቶ በምትካቸው በደስታና እርካታ የረሰረሰ ፊት ይዘው ተነሡ፡፡ እኔ የዚህ ምክንያት መስሎኝ የነበረው ጥሩ ሕልም ስላዩ መስሎኝ ነበር፡፡ እማማ ዓለሚቱ እንደተነሡ ጥንቃቄ በተሞላበት እንቅስቃሴ በተቀመጡበት ቀስ ብለው ግድግዳውን ደገፍ አሉ፡፡ የልብሳቸውን አንገትየ በጥንቃቄ ወደ ውስጥ እየሰበሰቡ በቀኝ እጃቸው በጠባቡ ከአንገታቸው ስር ያዙት፡፡ ፊታቸው ላይ የሚነበበው የደስታ የንቃት የእርካታ ስሜት ሌላ ነው! ትንሽ እንደቆዩ በቀኝ እጃቸው አጥብበው ይዘውት የነበረውን የልብሳቸውን አንገትዬ በጥንቃቄ ለግራ እጃቸው አስያዙና በቀኝ እጃቸው አመልካች ጣት በጣም በጥንቃቄ መሀል አናታቸውን ነካ ነካ አደረጉት፡፡ ሁለተኛ ጣት ጨመሩና እንደገና ዳሰስ ዳሰስ አደረጉ፡፡ ማረጋገጥ የፈለጉትን ነገር ስላላረጋገጡ በአምስቱም ጣቶቻቸው ጭንቅላታቸውን ዳሰሱ፡፡ ያ በደስታ በእርካታ ስሜት ተጥለቅልቆ የነበረ ፊታቸው ከመቅጽበት አመዱ ቡን አለ ድንጋጤ ወረረው፡፡ ጮክ አሉና ውለዷት በሚል ስሜት “ቅቤውስ?” በማለት ዐይናቸውን አፍጥጠው ጠየቁን፡፡ ስለምን እንደሚያወሩ አልገባንም ነበርና “የምን ቅቤ እማማ ዓለሚቱ?” አልናቸው፡፡ አንዳች ነገር ሊል እንደፈለገ ሰው አፋቸውን ከፍተው ቆዩና የእኛን ግራ መጋባት ባዩበት ቅጽበት ለካ ከቁም ቅዠታቸው ነቅተው ኖረው እጅግ በሚያሳዝንና ልብን በሚነካ የሀፍረት ስሜት ተውጠው ምልስ አሉ፡፡

እማማ ዓለሚቱ ያን ሰሞን ቅቤ መቀባት አምሯቸው “እንዲያው ቅቤ መቀባት አምሮኝ ነበር” እንዳሉ ነበር የሰነበቱት፡፡ ለካ ሸለብ አድርጓቸው እያለ ያ አምሮታቸው የፈጠረባቸው ስሜት በቀን የተመኙትን በሕልም ሰጥቷቸው አንድስ የሚያክል ቅቤ መሀል አናታቸው ላይ ምርግ አድርገው ተቀብተውት ኖሮ ያቅቤ ልብሳቸውን እንዳያበላሽ ኖሯል ለካ ከሸለብታቸው እንደነቁ የልብሳቸውን አንገትየ ወደ ውስጥ ሰብስበው በጠባቡ እንቅ አድርገው ይዘውት የነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ በዚያ ቦታ የሌለ የማይጨበጥ የፈጠራ ነገር ሲወራ ሲነገር “የማማ ዓለሚቱ ቅቤ” ይባላል፡፡ የውሀ ሽታ ሆኖ የቀረውን ነገርም “ምነው ነገሩን የማማ ዓለሚቱ ቅቤ አደረከውሳ?” እየተባለ ይተረታል፡፡

የተኩላው ቡድን ስለ እኔ መጻፍ ሲያስቡ የእኔ ማንነት በጻፉት መልኩ እንዲሆን እጅግ በመመኘት ነበር ስለ እኔ ለመቃረም ተሰማርተው የነበረው ሳይቀናቸው ተመለሱ፡፡ ቢሆንም ግን ከቁም ቅዠታቸው መንቃት አልፈለጉም፡፡ ከቁም ቅዠታቸው ነቅተው በገጠማቸው ስብራት ሕመም ከመሰቃየት በቁም ቅዠት መቆየትን መረጡ፡፡ የእማማ ዓለሚቱን ቅቤ በመቀባትም እፎይ አሉ እረሰረሱ፡፡ የተኩላውን ቡድን ከእማማ ዓለሚቱ የሚለየው እማማ ዓለሚቱ ቅቤው የቁም ቅዠት መሆኑን አውቀው ሐፍረት እየተሰማቸው ሲመለሱ የተኩላው ቡድን ግን ከቁም ቅዘታቸው ነቅተው በስብራታቸው ሕመም ከመሰቃየት በቁም ቅዠታቸው ውስጥ ቆይተው በቁም ቅዠታቸው ተቀባን በሚሉት ቅቤ ሰው እየሳቀባቸው መቆየትን መምረጣቸው ነው፡፡ ይህን የተኩላት ቡድን ጽሑፍ ባስቀመጡት የሐሳብ ቅደም ተከተል መሠረት ከንቱነቱን ዕንይ፡-

ከርእሳቸው እንጀምር “ኹራፋተ አምሳሉ” ይላል የተኩላቱ ጽሑፍ ርእስ፡፡ ኹራፊው ብሎ እንደጀመረ ኹራፊው ብሎ ነው የሚጨርሰው፡፡ በሰዋስው ሕግ መሠረት ቃሉ ግስ ሲሆን ኾረፈ ቅጽል ሲሆን ኾራፊው ጥሬ ዘር ሲሆን ኹረፋ እያሉ መጠቀም ሲኖርባቸው ለሁሉም አጠቃቀም ኹራፊው በማለት ጀምረው ጨረሱ፡፡ የቃሉን አጠቃቀም ካላወቁ ምን አለ ትዝብት ላይ ከሚወድቁ ባይጠቀሙትስ? ለነገሩ “ምን ይሉናልን” ሲያውቁ አይደል! ትችታቸውን ሲጀምሩ በ2 ክፍል አቅርቤው ከነበረው ጽሑፍ ውጪ በመሔድ እንዲህ በማለት ነበር የጀመሩት፡-

ኹራፊው አምሳሉ ገብረኪዳን የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት አስመልክቶ በፌስቡክ ገጽ ላይ ፤ ‹‹ …የመውለጃዋ ጊዜ በደረሰ ጊዜ ጌታዋ ፈጣሪዋየኋላልጇ ለመለኮታዊ ክብሩ፣ ለልዑልነቱ፣ ለሁሉንቻይነቱ፣ ለፈጣሪነቱ፣ ንጹሕ ነገር ፈላጊ ለንጹሐ ባሕርይነቱ በምትስማማ መልኩ ምንም ምክንያት እንዳይገኝባት አድርጎ ንጹሕ ጽዱ ፍጹም ቅድስት አድርጎ ፈጥሮ አዘጋጃትና ሰዓቱ ሲደርስ ያንን ንጹሕ ፍጹም ጽዱ ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባትበዚህ ሥጋውም ዓለሙን ሁሉ ተቤዠው፡፡›› የሚል ኑፋቄን ከእውነተኛው ትምህርት ጋራ የቀየጠ ጽሑፍ አስፍሮ ነበር፡፡

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሦስት መሠረታዊ የኑፋቄ ትምህርቶች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ‹‹የኋላልጇ›› የሚለው ነው፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊት ሌላ ልጅ እንደአላት አድርጎ ጌታችንን ‹‹የኋላልጇ›› ሲል ኑፋቄውን ጽፏል፡፡

ሁለተኛው የኹራፊው አምሳሉ ኑፋቄ፤‹‹ ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› የሚለው ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን፤ ‹‹ሥጋዋን ነሥቶ ወይም ተዋሕዶ›› ይባላል እንጂ በፍጹም ‹‹ሥጋዋን ወርሶ›› አይባልም፡፡ ምስጢረ ተዋሕዶውም በእንዲህ ዓይነት ወሊጥ ቃል ተገልጾም አይታወቅም፡፡ ሲቀጥልም ‹‹ተወለደባት›› አይባልም፡፡ ‹‹ሥጋዋን ነሥቶ ወይም ተዋሕዶ ተወለደ፤›› እንላለን እንጂ ‹‹ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› አንልም፡፡ ‹‹ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› የምንል ከሆነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ‹‹እንበለ ኅድረት – ያለኅድረት፤ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም በነሣው ወይም በተዋሐደው ሥጋ ተወለደ›› የሚለውን የቤተክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት ያፋልሳል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነቱን ወሊጠ ቃል አትጠቀምም አሉ፡፡

የቤተክርስቲያንን እንደውቅያኖስ የሰፋና የጠለቀ ትምህርት ወይም ዕውቀት እኛ የማናውቀው የቤተክርስቲያን አይደለም በሚል አቀራረብ በእነሱ ኢምንት የንባብ ልምድ ቤተክርስቲያንን ለመገደብ ለመወሰን ጥረት ማድረጋቸው እጅግ ደንቆኛል፡፡ ተኩላቱ ቤተክርስቲያን ነሣና ተዋሐደ የሚሉትን ቃላት ብቻ ነው የምትጠቀመው አሉን ተሳስተዋል ከነሱም በተጨማሪ ወረሰ፣ አደረ፣ ወሰደ፣ ተካፈለ፣ ያዘ እነዚህ ሁሉ ቤተክርስቲያን ስለ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው መሆን ስትናገር እንደየ አገባባቸው የምትጠቀምባቸው ቃላት ናቸው ሥጋዋን ወርሶ (ወሪሶ) ማለት የራሱ አድርጎ ማለት ነው የቃሉ ትርጉም በአማርኛውም በግእዙም አንድ ነው ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› የምንል ከሆነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ‹‹እንበለ ኅድረት – ያለኅድረት፤ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም በነሣው ወይም በተዋሐደው ሥጋ ተወለደ›› የሚለውን የቤተክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት ያፋልሳል በማለት የተገለጸው ምኑን ከምን ለማገናኘት እንደተሞከረ ትዝብት ላይ የሚጥላቸውና ለራሳቸውም ግልጥ አይደለም፡፡ አማርኛ ካልቻሉ ዝም ቢሉ መልካም ነበር፡፡ ወረሰ ወይም የራሱ አደረገ የሚለው ቃል የተዋሕዶን ምሥጢር በትክክል የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ኃደረ (አደረ) የሚለውን ቃል ተጠቅሟል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ቀጥሎ በምጠቅሰው ቃል ያዘ፣ ተካፈለ የሚለውን ቃል ተጠቅሟል “…እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሐት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም” ዕብ.2፤14-16

ተኩላቱ ቀጠሉና ምን አሉ የኹራፊው አማሳሉ ገብረ ኪዳን ሦስተኛው ኑፋቄያዊ ሕፀጽ ፤‹‹… በዚህ ሥጋውም ዓለሙን ሁሉ ተቤዠው›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በነገረ ድኅነት ትምህርታችን ትልቁ ኑፋቄ ነው፡፡ ይህም በሁለት መልኩ ይገለጻል፡፡ የመጀመሪያው፤ ‹‹ድኅነተ ዓለም የተፈጸመው በሥጋ ነው›› የሚል ኑፋቄን ሲያመጣ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፤‹‹ ሥጋ መለኮትን ውጦና አጥፍቶ በሩቅ ብእሲ ሥጋ ድኅነት ሆነ›› የሚለውን ኑፋቄ ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ ቤዛ ዓለም አልተፈጸመም እንደ ማለት ነው አሉ፡፡ ተኩላት ሆይ! ክርስቶስ ስለ ራሱ ሲናገር ብዙ ጊዜ “የሰው ልጅ” የሚለውን ቃል ይጠቀም ነበር ሉቃ. 9፤26, 19፤10, 21፤27 ጥራዝ ነጠቃዊያን ሆይ! ክርስቶስ እራሱን “የሰው ልጅ” እያለ ስለተናገረ መለኮት ያልተዋሐደው ሥጋ ነው የያዝኩት ማለቱ ነው እያላቹህ እንደሆነ ይገባቹሀል? ሊቃውንቱ ለምሳሌ አባ ሕርያቆስ “ከድንግል በነሣው ሥጋ ዓለሙን አዳነው” ማለታቸው መለኮት ባልተዋሐደው ሥጋ ነው ክርስቶስ ዓለሙን ያዳነው ማለታቸው ነውን?

በአጭሩ የኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን፤‹፣ … የኋላ ልጇ … ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት፤ በዚህ ሥጋውም ዓለሙን ተቤዠው፡፡›› የሚለው ፍጹም ኑፋቄያዊ ሕፀጽ፤ ‹‹ዓለምን የተቤዠው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ውላጤ፣ እንበለ ሚጠት፣ እንበለ ኅድረት፣ እንበለ ቡዐዴ፣ እንበለ ትድምርት፣ እንበለ ቱሳኤ በተዋሕዶ ነው፡፡›› ከሚለው ርቱዕ ትምህርት ጋር የሚጋጭ ክህደት ነው፡፡ በማለት ነበር፡፡ ማንም የፌስ ቡክ (የመጽሐፈ ገጽ) ገጼን ከፍቶ እውነቱን ሊያረጋግጥ በሚችልበት ደረጃ ከአጋንንታዊ ማንነታቸው የተነሣ የሐሰት ክሳቸውን የጀመሩት፡፡ የመጽሐፈ ገጽ ገጼን ክፈቱና ጃንዋሪ 6 ላይ የለጠፍኩትን እንኳን አደረሳቹህ! ለማለት ከባሕላዊ የጌታ ልደት ሥዕል ጋር አጭር የ8 መስመር ጽሑፍ የጻፍኳትን ተመልከቱልኝ፡፡ መልዕክቷ ከዚህ በታች ያለውን ትመስላለች፡-

“የአምላክ ሰው የመሆኑ ከድንግል የመወለዱ ነገር እንደ ውኃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ አይደለም፡፡ ቅድስት ድንግል እናቱ ዓለም ከመፈጠሩ በፊትም በእሱ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር፡፡ ይህች ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ከእናቷ ከቅድስት ሐና ከአባቷ ከቅዱስ ኢያቄም የመወለጀዋ ጊዜ በደረሰ ጊዜ ጌታዋ ፈጣሪዋ የኋላ ልጇ ለመለኮታዊ ክብሩ፣ ለልዑልነቱ፣ ለሁሉን ቻይነቱ፣ ለኃያልነቱ፣ ለፈጣሪነቱ፣ ንጹሕ ነገርን ፈላጊ ንጹሐ ባሕርይነቱ በምትስማማ መልኩ ምንም ምክንያት እንዳይገኝባት አድርጎ ንጹሕ ጽዱ ፍጽምት ቅድስት አድርጎ ፈጥሮ አዘጋጃትና ሰዓቱ ሲደርስ ያንን ንጹሕ ፍጹም ጽዱ ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት፡፡ በዚህ ሥጋውም ዓለሙን ሁሉ ተቤዠው፡፡ እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳቹህ!!! ” የሚል ነበር፡፡

ተኩሎቹ ግን ለክስ እንዲመቻቸው ወላዲተ አምላክ እንደቃሉ ሁሉ ጌታን የወለደችው በድንግልና መሆኑን የሚናገረውን ከፊት ያለውን 3 መስመር ለሐሰተኛ ክሳቸው የማይመች ስለሆነ ገደፉና ‹‹የኋላልጇ›› የሚለው ነው፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊት ሌላ ልጅ እንደአላት አድርጎ ጌታችንን ‹‹የኋላልጇ›› ሲል ኑፋቄውን ጽፏል በማለት እንደ ግብር አባታቸው ከይሲ የቀረውን ጽፉፍ አጣመው የተሳሳተ ትርጉም ለማስያዝ ጥረት አደረጉ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ቤተክርስቲያን የምታውቀው የመናፍቃን ኑፋቄ የነበረው በማቴ. 13፣55 ላይ ያለውን ቃል አጣመው በመተርጎም ወንድሞቹና እኅቶቹ ተብለው የተጠቀሱትን ወላዲተ አምላክ ጌታን ከወለደች በኋላ የወለደቻቸው እንደሆኑ አድርገው የሚናገሩትን ኑፋቄ ነበር፡፡ እስከዛሬ ድረስ እንኳን ክርስቲያን ነን የሚሉት መናፍቃን ይቅርና እስላሞችም እንኳን ወላዲተ አምላክ ጌታን የወለደችው በድንግልና መሆኑን የሚጠራጠርና ከጌታ በፊት ልጅ ወልዳለች የሚል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ይሄ በቅዱስ ቃሉ በግልጽ የሰፈረ በመሆኑ ትን. ኢሳ. 7፣14, ማቴ. 1፣23 ይሄንን የሚሉ የሚጠራጠሩ መናፍቃን ከተኩላቱ ቡድን ስናገኝ አሁን እንግዲህ የመጀመሪያ መሆኑ ነው፡፡

መናፍቃኑ ወንድሞቹ እኅቶቹ የሚለውን የአይሁድን አባባል ይዘው ይቅር ይበላቸውና እንዳያስተውሉ አድርገው አዚም የረጩባቸውን አጋንንት ይጣልላቸውና እመቤታችንን ከጌታ በኋላ የወለደቻቸው ናቸው ይላሉ፡፡ በጥቅሱ ላይ ያለውን የአይሁድ ቃል ትክክል ነው ብለው ካመኑማ እንግዲያውስ ዮሴፍም የጌታ የሥጋ አባት ነዋ! ምክንያቱም በጥቅሱ ላይ አይሁድ ጌታን “ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ…. ” ብለዋልና፡፡ አይሁድ ጌታን የዮሴፍ ልጅ ያሉበት ምክንያት የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ ያምኑ ስለነበረ ነው፡፡ ሊያምኑ የቻሉበት ምክንያትም ጌታ ጌታ ነኝ ብሎ በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና መወለዱ በሕዝቡ ሁሉ ታውቆ ተጸንሶ እስኪወለድ ተወልዶም ሲያድግ እንደ አምላክነቱ ለአምላክነቱ በሚገባ እንክብካቤታ መስተንግዶ በተለየ ሁኔታ መኖርን ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው ሕግ ሥርዓትና ሌሎች ሁኔታዎችን ሁሉ አክብሮ እስከ ጊዜው ድረስ ተመሳስሎ መኖርን ስለነበረ የፈለገው እግዚአብሔር ድንግልን በእጮኛ ስም ለዮሴፍ ሰጥቶ የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ እንዲያስቡ አድርጎ ጌታ እንዲወለድና እንዲያድግ አደረገ፡፡ እንዲህ ባያደርግ ኖሮና ያለ እጮኛ እንደ ፀነሰች ቢያስቡ ኖሮ በኦሪቱ ሕግ ዘኁ. 5፣19 መሠረት በዝሙት ጸንሳለች ብለው ወግረን እንገላለን ይሉ ስለነበርና ለእጮኛ ሳትሰጥ በድንግልና ጸነስኩ ብትላቸው አይሁድ ስለማያምኑና እሷንም ለችግር ሊዳርጓት ስለሚችሉ ይህ ችግር እንዳይደርስባት ነበር እግዚአብሔር ዮሴፍና ወላዲተ አምላክ ብቻ በሚያውቁት ምስጢር በጥበብ ለአይሁድ ይምሰል በእጮኝነት ስም ለዮሴፍ እንድትታጭ የተደረገው፡፡ ወላዲተ አምላክ ለዮሴፍ የታጨችበት ምክንያት ይሄ ነው ደካሞች እንደሚያስቡት ለሌላ አይደለም፡፡ በዚህም መሠረት አይሁድ ጌታን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ቻሉ፡፡ “የጸራቢው ልጅ አይደለምን” ያሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ታዲያ የተጠቀሱት ሰዎች ወንድሞቹና እኅቶቹ ካልሆኑ ለምን እንደዚያ ተባለ? ቢባል የዮሴፍ ልጆች ስለሆኑ ነው ዮሴፍ ከሟች ሚስቱ የወለዳቸው፡፡ ለዚህም ነው በዚያ ጥቅስ ላይ ወንድም ተብሎ የተጠቀሰው ይሁዳ መልእክቱን ሲጽፍ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ… በሚል ቃል መልእክቱን መጻፍ የጀመረው ይሁ. 1፤1

ወደ ቀጣዩ የተኩላት ሐሰተኛ ክስ ስናልፍ፡-

ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን መች ከዚህ ኑፋቄያዊ ሕፀጹ ብቻ ተገትቶ፡፡ ከተዘፈቁ አይቀር እንዲህ ነው፤ ‹‹በአይሁዶች መርዘኛ ጥርስ የገባች ሀገር ኢትዮጵያ!›› በሚል ርእስ ተሸካሚነት ፀረ ሴማዊነቱንና ለዚህ ፀራዊ ስሜቱ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት በማዛባት በገለጠበት በዚያ ማወየቢያ ጽሑፉ ውስጥ ሁለት ትምህርተ ሃይማኖታዊ ርእሰ ጉዳዮችን አዛብቶ ቅርቧል፡፡ የመጀመሪያው፤ ‹‹ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ‹ ለይሁዳ ወለዱ ወለዉሉደ ዉሉዱ ይደምሰስ › ትላለች፤›› ተብሎ፤ በማትለውና ግድፈት በተሞላበት ግእዝ የተገለጠው አሳበ ጥቅስ ነው፡፡ ተዛብቶ የቀረበውና ቤተክርስቲያን ብላው በማታውቀው (ግእዝ አይሉት አማርኛ) መንገድ የቀረበው አሳበጥቅስ፤ ቤተክርስቲያኒቱ በምትለው ትክክለኛ ግእዝ ሲቀመጥ፤ ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወለ ዉሉደ ወልዱ ይደምሰስ›› በሚል ነው፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ በዕለተ ስቅለት ብቻ በቤተክርስቲያን የዋለ ሰው እንኳን የማይገድፈውን አሳበ ጥቅስ የገደፈው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ነው፡፡ ይኸው ሰው ነው፤ የአባጊዮርጊስን ‹‹ውዳሴ መስቀል›› ፣በ ‹‹አራቱኃያላን›› መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱትን የአቡነ በጸሎተ ሚካኤል፣ የአቡነፊልጶስ፣ የአቡነ አኖሬዎስ እና የአቡነ አሮን ገድላትን ተርጉሞና ጥልቅ ጥናታዊ ማብራሪያ የሰጠውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን፤ ያለአንዳች ተጨባጭ ማስረጃ፤ በግእዝ ጨዋነት ለመጠርጠር የዳዳው፡፡ ኹራፊው አምሳሉ ይህ ግድፈቱ ሳያንሰው በዚሁ በገደፈው ግእዙ የራሱን ፀረ ሴማዊ ፍላጎት በመቀንበብ፤ ቤተክርስቲያን ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወለዉሉደ ወልዱ ይደምሰስ›› በሚል የሚለውን አሳበ ጥቅስ በዕለተ ዓርብ የምትጠቀመው፤ ‹‹አይሁዶችን ለማውገዝነው›› ሲል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በፀረ አይሁድነት ፈርጆ ሊያስፈርጃት ይጣጣራል፡፡

እውነታው ግን ወዲህ ነው፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ነበር፡፡ ነገር ግን የተመረጠበትን ሐዋርያዊ ተግባር ትቶ ከሰቃልያነ እግዚእ ጋር ተባብሮ ጌታውንና መምህሩን አሳልፎ በመስጠቱ፤ በኋላም በጥፋቱ ተፀፅቶ እንደ ጴጥሮስ ንስሐን ሳይሆን በብልጠት ምሕረትን ስለ ፈለገና ራሱን ስለገደለ የእርግማን እርግማን ተፈጽሞበታል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ይህን ለመዘከር፤ልዩ ልዩ መዝሙራትን በማስተዛዘል በሚጸለይበት ጊዜ ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወዉሉዱ ይደምሰስ›› የሚል የመርገም ቃል አዝማች እንዲ ነገር ታደርጋለች፡፡ ከዚህ ፀራዊ አስተሳሰብ ብቻ እንኳን ተነሥተን እንፈርጅ (ፍረጃ ተገቢ ባይሆንም) ብንል፤ በፀረ ሴማዊነት እኩይ መንፈስ አብዶ፣ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት ለፀረ ሴማዊነት ወይም ለፀረ አይሁድነት ቅስቀሳ አዛብቶ በመጠቀም፤ ኩላዊት የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን በፀረ አይሁድነት ፈርጆ ሊያስፈርጅ እየዳከረ የሚገኘው ኹራፊው አምሳሉ ነው

በማለት ስለ እነሱ እጅግ ያፈርኩበትን በማይውቁት ጉዳይ ባለማወቃቸው ሳያፍሩና ሳይሳቀቁ ሌላኛውን ክሳቸውን ያቀረቡት፡፡ እኔ ጤነኝነታቸውም እራሱ በጣም ነው የሚያጠራጥረኝ ከላይ ቤተክርስቲያን በፍጹም አትልም አሉ ወረድ አሉና ደግሞ ትላለች የምትለውም እንደዚህ ነው አሉ፡፡ እኔ የሰጠሁትን ትርጉም ትክክል አይደለም ካሉ በኋላ ትክክለኛ ነው የሚሉትን ትርጉም ሊናገሩ አልቻሉም፡፡

የተኩላው ቡድን ለራሱ አጣርቶ ሳያውቅ ተመልሳቹህ ከጽሑፌ እንደምታረጋግጡት “ለይሁዳ ወልዱ ወለ ውሉደ ውሉዱ ይደምሰስ” ብየ የጠቀስኩትን ጥቅስ አወለጋግደው “ለይሁዳ ወለዱ ወለዉሉደ ዉሉዱ ይደምሰስ” ብሏል በማለት ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ትክክለኛው ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወለ ዉሉደ ወልዱ ይደምሰስ›› የሚለውን ነው ብለዋል፡፡ ምነው የማያውቁትን ነገር ባይዘባርቁስ? ማን አስገደዳቸው? ወይ ደግሞ እንዲህ ከሚዋረዱ ሊቃውንቱን ቀርበው ቢጠይቁስ ምን አለ? እስከመቸ ድረስ ነው በድንቁርና ድፍረት ምን ይሉናል ሳይሉ በግምት የሚዘባርቁት? ደሞ ትክክል ነው ያሉትን እንደያዙ ቢቆዩስ ምን አለ? እንደገና ደግሞ ወደታች ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወዉሉዱ ይደምሰስ›› ይሉና ይቀይሩታል፡፡ ስሕተታቸው ምንድን ነው? ትክክለኛው ግእዝ ብለው መጀመሪያ የጠቀሱት “ለይሁዳ ወልዱ ወለ ዉሉደ ወልዱ ይደምሰስ” ከሚለው “ዉሉደ ወልዱ” የሚለው ነው፡፡ ስሕተቱም ውሉደ ሲጻፍ ልክ እኔ እንደጻፍኩት በካዕቡ (ው) ይጻፋል እንጅ በሳድሱ (ዉ) አይጻፍም ቀጥሎ ያለውም ቃል እኔ እንዳልኩት ሁሉ በብዙ ቁጥር ውሉዱ ይባላል እንጅ በነጠላ ቁጥር ወልዱ አይባልም ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ብዙ ልጆችን ይወልዳሉ እንጅ አንድ ልጅ በብዙ ሰዎች አይወለድምና፡፡ ግስ ወይም ቁጥር እንዴት እንደሚረባ ካላወቁ ዝም ቢሉስ ምን አለ? እኔም የግእዝ ሊቅ ነኝ ማለቴ አይደለም ግን ቢያንስ ያውም እኔን “እንግዲህ ተመልከቱ በዕለተ ስቅለት ብቻ በቤተክርስቲያን የዋለ ሰው እንኳን የማይገድፈውን አሳበ ጥቅስ የገደፈው ኹራፊው አምሳሉ” በማለት እያንኳሰሱ በአላዋቂነት የከሰሱ ሆነው እያሉ እንዴት አይጠነቀቁም? ሊቃውንቱን ጠይቀው በቅጡ ቢረዱ ምናለ? ትክክለኛ ነው ብለው ከታች የጠቀሱት ላይ ደግሞ ወውሉዱ የሚለውን ገድፈው አስቀምጠውታል ደግሞ “…ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን፤ ያለአንዳች ተጨባጭ ማስረጃ፤ በግእዝ ጨዋነት ለመጠርጠር የዳዳው” ይባልልኛላ! ማፈሪያ ሁላ፡፡

ቀጠሉና “ፀረ ሴማዊ፣ ቤተክርስቲያንን በፀረ ሴማዊነት ሊያስፈርጅ ይጣጣራል” አሉኝ ለመሆኑ ፀረ ሴማዊ ማለት ብን ማለት ነው? እኔ እራሴ ምን ነኝና? ፀረ አይሁድ (የእስራኤላዊያንን ዘር ማለት ሳይሆን የጨነገፈውን መሲሑን ያልተቀበለውን የአይሁድን እምነት የሚከተሉ ማለት ነው) እናም እንዲህ ማለታቹህ ከሆነ በዚህ በጨነገፈው አይሁድነትና በክርስትና መሀል ጠላትነት ከተጀመረ እኮ ቆየ! ሁለት ሽህ ዓመታት አለፉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አይሁድ እስከዛሬ ድረስ ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱት የሚጠሉት የሚንቁት፡፡ ቤተክርስቲያን “ለይሁዳ ወልዱ ወለ ውሉደ ውሉዱ ይደምሰስ” ብላ ስትል ቃሉን ከጊዜ በኋላ የፈጠረችው ሳይሆን ነቢዬ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት በትንቢት በመዝ. 108(109)ላይ ስለ ይሁዳና ሰቃልያነ እግዚእ ካስቀመጠባቸው የእርግማን ቃል ጥቂቱን በመውሰድ የሚነገር ቃል ነው፡፡ ተኩላት ሆይ! የእግዚአብሔር ቃል “የእፉኝት ልጆች” ማቴ. 3፣7 የሚላቸው እነማንን ይመስላቹሀል? ክርስቶስ “ለዘለዓለሙ ፍሬ አይገኝብሽ” ማቴ. 21፣18 ብሎ የረገማት በለስ እነ ማን ናቸው? ልበ አምላክ ዳዊት ስለ ክርስቶስ ስቅለት በተነበየበት መዝሙሩ 21፣12-30 “ውሾች፣ የክፋተኞች ጉባኤ” እያለ የገሰጻቸው እነማንን ነው? አይሁድ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ቃላትን “በፀረ ፀረ ሴም” እንቅስቃሴ ሽፋን ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠፋት መንቀሳቀስ ከጀመሩ ቆይተዋል ይመስለኛል እነ ተኩላትም የዚህ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ከዝንባሌያቸው እንዳያቹሀቸው በእርግጠኝነት እንዲህ ዓይነቶችን ቃላት አጥፉ ቢባሉ የሚያንገራግሩ አይመስለኝም፡፡

ተኩላት ቀጠሉና … በሥርዓቱ መሠረት አንድ ካህን በትዳር ሕይወት እያለ ባለቤቱ ወይም ሚስቱ ሰርቃ ከሌላ ወንድ ብትደርስና ከሌላ ወንድ መድረሷን አወቀም አላወቀ ከሌላ ከደረሰች በኋላ እሱ ቢደርስባት ሥልጣነ ክህነቱ ይፈርሳል፡፡ ከዚያ በኋላ በዚያ ሥልጣነ ክህነት መጠራትና ማገልገል አይችልም፤ መቅደስ ውስጥም መግባት ፈጽሞ አይችልም፡፡ የሚለው ነው፡፡ በየትኛው ሥርዓት መሠረት እንደሆነና የሥርዓቱም ድንጋጌ በየትኛ አንቀጽና ቁጥር እንደሚገኝ ያልገለጸው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን የራሱን ድንጋጌ ‹‹በሥርዓቱ መሠረት››

በሚል ሽፋን የዋሃንን ለማደናገር ቢሞክርም ለዛሬ አልተሳካለትም፡፡ በየትኛውም የሥርዓት መጽሐፋችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት የቅጥፈት ድንጋጌ የለም፡፡

‹‹ሁለት ጊዜ ያገባ፤ ሁለት ሚስት ያለው፤ ከሴሰኛ ሴት የደረሰ፤ በአገልግሎት ምክንያት ሚስቱን የተለየና የፈታ፤ እመነኩሳለሁ፣ ተባሕትዎ እይዛለሁ ብሎ ሚስቱን ያሰናበተ ካህን ከሹመቱ ይሻራል፡፡›› ብለዋል፡፡ ዲያቆን ከሆነ  ደግሞ፤ ‹‹ሁለት ሴት ያገባ፣ ወይም በተሾመ ጊዜ ከሴት ርቄ ንጽሕና ጠብቄ እኖራለሁ ብሎ ተሥሎ ከተሾመ በኋላ  ሥዕለቱን አፍርሶ ሚስት  ያገባ ወይም ከዘማዊት ሴት የደረሰ፣ ተደብቆ ተክሊል ያደረሰ ወይም እመነኩሳለሁ ተባሕትዎ እይዛለሁ ብሎ ሚስቱን የፈታ ከዲቁናው ማዕረግ ይሻራል፡፡›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፤ 1993፣ 120–123)

ይህን የሊቁን ትንታኔና የፍትሕ መንፈሳዊ ድንጋጌ ይዘን የኹራፊውን የአምሳሉ ገብረ ኪዳንን ግለ ድንጋጌ ስንፈትሽ፤ እውነት አልባ መሆኑን ከመረዳት ባሻገር፤ አንድ ካህን ያለ ራሱ በደል ክህነቱን የሚያጣበት ምንም ዓይነት ቀኖናዊ መሠረት የሌለ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ በሚስቱ ስርቆት ተፈጸመ ቢባልና ይህም በማስረጃ ተረጋገጠ ቢባል በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት ሚስቱ በዝሙት ወድቃ ተገኝታለችና ጋብቻው ሊፈርስ ይችላል እንጂ ክህነቱ ሊፈርስ የሚችልበት ምንም ዓይነት ቀኖናዊ መሠረት የለውም

በማለት ሌላኛውን ጉዳቸውን ጎለጎሉት፡፡ መቸም ቀኖና ቤተክርስቲያን እንደዚህ ዘመን የተደፈረበት ዘመን የለም፡፡ እኔ ዓላማቸው ምን እንደሆነ አይገባኝም እንዲህ መሰል ቀኖና ቤተክርስቲያን ሲጠቀስ አይወዱም ሊሽሯቸውም ይፈልጋሉ መሰለኝ እንደሌለ አድርገው ያወራሉ፡፡ አሁን አሁን ዲያቆናት ነን የሚሉቱ የሚበዙቱ እኔ መጠበቅ ስለማይፈልጉ አውቀው ይሁን ምን አላውቅም ዲቁና ምን ግዴታ እንዳለበት፣ ከምን መጠበቅ እንዳለበት፣ ሥልጣኑን ምን እንደሚያሽረው ጨርሰው የማያውቁ ናቸው፡፡ እኔ ማን ክህነቱን እንደሚሰጣቸውም አላውቅም፡፡ ተኩላቱ አምሳሉ ፈጥሮ ነው ያሉትን ቀኖና ቤተክርስቲያን እንኳን ዲያቆን ነኝ የሚል ይቅርና ከምእመናን እንኳን የማያውቀው የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ይህ ሥርዓት ከተደነገገበት የቀኖና መጻሕፍት አንዱ ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንዱ ነው ከአንቀጽ 6 እስከ 9 ድረስ ተዘርዝሯል፡፡ ሌላኛው ሲኖዶስ የሚባለው መጽሐፍ ነው መጽሐፈ ብርሃን የሚባል ሌላ መጽሐፍም አለ፡፡ በሌሎች የቀኖና መጻሕፍትም ክህነትን ስለሚያፈርሱ ጉዳዮች በተለያየ መንገድ ይጠቀሳሉ፡፡ ተኩላቱ ካልጠቀሷቸው ክህነትን ከሚያስፈርሱ ነገሮች ውስጥ ነፍስ ማጥፋት፣ ኑፋቄ፣ ሃይማኖትን መካድ፣ ጋብቻ ሳይፈጽሙ ምንም ትሁን ምን ሚስት ካልሆነች ሴት ጋር ተራክቦ መፈጸም፣ ካገቡ በኋላም ከሚስ ውጭ ዝሙት መፈጸም ናቸው፡፡ ተኩላቱ ያሉት ሁለተኛ ሚስት ማግባትማ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም፡፡ አንድ ምእመን ድንግልና ከሌለው ዲቁና ከዚያም ቅስና ሊካን አይችልም፡፡ በግብጽ ቤተክርስቲያን መጻኢ ወይም አዲስ አማኝ ከሆነ ድንግልና ባይኖረውም በአረማዊነቱ ወይም በኢአማኒነቱ ዘመን የሠራው ኃጢአት ተደምስሶለት እንደድንግል ተቆጥሮ ክህነትን ማግኘት ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግን ይህ አይቻልም፡፡

አሁን አሁን ዕያየን እንዳለነው ግን ይሄ ሁሉ ቀኖና ቤተክርስቲያን ድብልቅልቁ ወጥቶ “ድንግልና የለውም ለክህነት አይበቃም!፣ አፍርሷል ማገልገል አይችልም!” የሚባል ነገር ቀርቶ በቅድስናው ስፍራ ላይ የጥፋት እርኩሰት በገፍ የሚፈጸምበት ዘመን ሆኖ ቤተክርስቲያን የነ አፍኒንና ፊንሐስ መፈንጫ ሆናለች፡፡ አባቶችም እንደ ዔሊ ሁሉ ኧረ ዔሊ እንኳን የተቻለውን ያህል ተናግሯል እነዚህ ግን ዐይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ጭጭ በማለት የእግዚአብሔርን ክብር የሚያስደፍሩ አፍኒንና ፊንሐሶችንም ለከፋ ፍርድ የሚዳርጉ ሆነዋል፡፡ ለዚህ የድፍረት ኃጢአታችንም በሚገባን የቅጣት ሰይፍ እየተበላን እንገኛለን፡፡

ተኩላቱየኹራፊውን የአምሳሉ ገብረ ኪዳንን ግለ ድንጋጌ ስንፈትሽ፤ እውነት አልባ መሆኑን ከመረዳት ባሻገር፤ አንድ ካህን ያለ ራሱ በደል ክህነቱን የሚያጣበት ምንም ዓይነት ቀኖናዊ መሠረት የሌለ መሆኑን እናረጋግጣለንበማለትም ለቅድስት ቤተክርስቲያን ቀኖናና ሥርዓት ምን ያህል ሩቅ መሆናቸውንና ላይ ላይዋን እንጅ ጠልቀው እንደማያውቋት አረጋገጡ “ከሱ ውጪ መሔዷን ሳያውቅ ከደረሰባት” ቢሉ እንኳን በመሰለላቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን ጭራሽ ከሱ ውጪ እንደሔደች ዐውቆ የረከሰችውን ሚስቱን እየደረሰባትም ነው ያለ ራሱ በደል ክህነቱን የሚያጣበት ምንም ዓይነት ቀኖናዊ መሠረት የሌለ መሆኑን እናረጋግጣለን በማለት በቤተክርስቲያን እንደ ሲኖዶስ ያለ ሥልጣን እንዳለው አካል አሳሳችና ተኩላዊ የጥፋት ማረጋገጫ የሰጡት፡፡ ቀኖና ቤተክርስቲያንን ካላወቁ ዝም ቢሉስ ምን አለ? ጌታ በወንጌሉ ምንድን ነው ያለው፡- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው አለም፡- ስለዚህ ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ማቴ. 19፣4-5 ብሎ ያለው ቃል ምን ማለት ነው የሚመስላቸው? “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርሷም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ አይተዋት ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርሷ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ አትተወው፡፡ ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሷልና ያላመነች ሚስትም በባሏ ተቀድሳለች አለዚያ ልጆቻቹህ ርኩሳን ናቸው አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው” 1ቆሮ. 7፤12-16 እንግዲህ የባል ቅድስና ለሚስት ወይም የሚስት ለባል እንደሚደርስ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳረጋገጠ ተመልከቱ፡፡ እንደ አንድ ሥጋነታቸው የባል ለሚስት የሚስት ለባል የሚደርሰው ቅድስና ብቻ ሳይሆን ኃጢአትም ጭምር ነው፡፡ ባል ባልሠራው ጽድቅ ሲቀደስ ይቻላል ብለን ወደን ተቀብለን ባልሠራው ኃጢአት ግን አይረክስም ልንል የምንችልበት ምንም ዓይነት አስተምህሮም ሆነ አመክንዮ የለም፡፡ ተኩላት ሆይ! “ስናውቅ በድፍረት ሳናውቅ በስሕተት የሠራነውን የማይሠራ ኃጢአት እግዚአብሔር ይፍታ” ማለት ምን ማለት ነው? እነ ለብ ለብ ሆይ! እባካቹህ ቤተክርስቲያንን ጠልቃቹህ ዕወቋት ተሳስታቹህ አታሳስቱ፡፡ ወይ ክህነታችን ስለፈረሰብንና በዚህ ምክንያት ዲያቆን እከሌ ቄስ እከሌ መባሉ እንዳይቀርብን ነው ብላቹህ በግልጽ ተናገሩ፡፡ ነገር ግን ይሄ ከሆነ ምክንያታቹህ እግዚአብሔር በዲያቆንነት ካላወቀ ሰው ቢል እግዚአብሔር በቄስነት ካላወቀ ሰው ቢል ምን ይጠቅማቹሀል? ይህ ድፍረታቹህ ከእግዚአብሔር በረከትን ሳይሆን መርገምን ካመጣባቹህ ሰው ዲያቆን ቄስ ቢል ምን ታተርፋላቹህ? ንስሐን ከቶውንም ሳታውቋትና ሳትጠቀሙባል ማለፋቹህ አይደለም ወይ?

እንቀጥል ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን አስቀድመን እንደገለጥነው ሃይማኖታዊ ድቀት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ድቀትም አግኝቶታል፡፡ አሰላለፉም ከወያኔያዊ ማንነቱ እንደሚመነጭ ያረጋገጠልንን ነጥቦችን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው፤ ‹‹ተኩላው፤ ‹‹ስማችሁ የለም›› በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ እጅግ በጣም በሚገርም ድፍረት የወያኔነቱን ተልእኮ ከውኗል፡፡ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ ‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በሚል ርእስ በጻፈው ጽሑፍ ላይ… በክብረ  ነገሥት ላይ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶ የሚተረከውን በዓለማውያኑ የታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ‹‹ሰሎሞናዊ›› በቤተክርስቲያን ደግሞ ‹‹የዳዊት መንግሥት›› እየተባለ የሚጠራውን ሥርዎ መንግሥት በሀገራችን አልነበረም በማለት ክብረ  ነገሥትንና ይኼንን የክብረ ነገሥትን ታሪካዊ ትረካ የሚጠቅሱና የሚያረጋግጡ ከገድላት እስከ ድርሳናት፣ ከተአምራት እስከ ፍካሬያት፣ ከሊቃውንት እስከ ትርጓሜያት ያሉትን የቤተክርስቲያን መጻሕፍት ሐሰተኞች አድርጓቸዋል፡፡›› በሚል ያልተባለውን እንደተባሉ አድርጎ ያቀረበው ነጥብ ነው፡፡ በአንደኛ ደረጃ በዚህ በኹራፊው ጽሑፍ ውስጥ የሐቅ (Fact) ችግር አለ፡፡ ይኸውም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በሚል ርእስ፤ ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን በመናድ ለተጠመደው ተስፋዬ  ገብረ አብ ምላሽ በሰጠበት ጽሑፍ ውስጥ፤ ‹‹… ‹ሰሎሞናዊ› የሚባል የተለየ መንግሥት አልነበረም፡፡ ነገሥታቶቻችን ሁሉ ራሳቸውን ከኢየሩሳሌም ጋር ያያይዙ ነበር፡፡ ዐፄ ካሌብም ……አለ እንጂ ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን፤ ‹‹ሰሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥት በሀገራችን አልነበረም›› ብሎ የገለጸው ዓይነት ዐረፍተ ነገር በዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ ውስጥ በጭራሽ የለም፡፡ (ስማችሁ የለም እና ሌሎች፤ 2006፣ 138) አሉ፡፡

ጤነኞች አይደሉም ልበል? ነው ወይስ ቆርጠው ማውጣት አስበው ረስተው ሳያወጡት ቀርተው ነው? ይሄው አልተባለም የሚሉትን ቃል እኮ አሁንም ደገሙት … ‹ሰሎሞናዊ› የሚባል የተለየ መንግሥት አልነበረም ይሄንን ካሉ በኋላ ደግሞ በጭራሽ የለም ሲሉ እዚሁ ላይ ትንሽም ሐፍረት ሳይሰማቸው ሸምጥጠው ካዱ፡፡ የነውረኛነታቸው ነውረኛነት በመጽሐፍ ታትሞ በሰዉ እጅ የገባን ነገር ለማስተባበል መሞከራቸው ነው፡፡ ተኩላው የለም ያለውን ሰሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥት እንዳልነበረ ለማሳመን ብዙ ርቆ ሔዶ ይህ ታሪካዊ ተረክ በአቡነ ተክለሃይማኖት ገድል ላይ በሚገባ ያለ ሆኖ እያለ የለም ብሎ እስከመካድም ነው የደረሰው፡፡

ተኩላቱ ቀጠሉና በሁለተኛ ደረጃ፤ በዚህ በኹራፊው ጽሑፍ ውስጥ የእውቀት ችግር እናገኛለን፡፡ ይኸውም ‹‹በዓለማውያን የታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ‹‹ሰሎሞናዊ›› በቤተክርስቲያን ደግሞ ‹‹የዳዊትመንግሥት›› በማለት ሁለት የተለያዩ ፅንሰ ሐሳቦችን አንድ በማድረግ አቅርቧል፡፡ በመጀመሪያ ቤተክርስቲያንም ‹‹ሰሎሞናዊ›› የሚለዉን ቃል እንደምትጠቀመው ሁሉ የታሪክ ጸሐፍቱም ‹‹የዳዊት መንግሥት›› የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፡፡ አንዱን ቃል ለአንዱ ብቻ መስጠት አይቻልም፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የታሪክ ምሁራኑም ሆኑ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ‹‹የዳዊት መንግሥት›› የሚሉት ከዳዊት ዘር ሲወረስ ሲወራረስ የመጣውን ቅብዓ ንግሥና የፈጸምንና ስዩመ እግዚአብሔር ነን ብለው የዳዊትን ኮከብ የመንግሥታቸው መለያ ያደረጉ ነገሥታትን በሙሉ ሲሆን፤ ‹፣ሰሎሞናዊ›› የሚሉት ደግሞ በ1270 ዓ.ም. ተመለሰ የሚባለውን የይኩኖ አምላክን መንግሥት ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያሳያችሁ የእነዚህን ሁለተ ፅንሰ ሐሳቦች ልዩነት ሳያውቅ ነው የጨነገፈ ብዕሩን ለትችት ያነሣው አሉ፡፡

እኔ እኮ የምለው ጤነኛ የሆኑ ሰዎች ሽዎች የሚያነቡትን ነገር ዝም ብለው በግምት ይቀባጥራሉ ብላቹህ ታስባላቹህ? ዳዊትና ሰሎሞን አባትና ልጅ መሆናቸውን አያውቁም እንዴ? እንዴት ሆኖ ነው “ሁለት የተለያዩ ፅንሰ ሐሳቦች” የሚሆኑት? “የዳዊት መንግሥት የሚባሉት እስከ… ያሉትን ነው ሰሎሞናዊ የሚባሉት በ1270 ተመለሰ የሚባለውን የይኩኖ አምላክን መንግሥት ነው” ይባላል እንዴ? “ተመለሰ” የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል? ለ333 ዓመታት በመሀል ዛጉዌዎች ገብተው ተቋርጦ የነበረውን ሥርዎ መንግሥት መመለስ አይደለም ወይ የሚያመለክተው? የዳዊት መንግሥት የተባለውም ሰሎሞናዊ የተባለውም አንዱን ከቀዳማዊ ምኒልክ የሚጀምረውን ሥርዎ መንግሥት ከሆነ የዳዊት የሰሎሞን የሚባሉት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ምን አመጣው? እንዴትስ ሊሆን ይችላል? በአቡነ ገድለ ተክለሃይማኖት ምእራፍ 27፣7 ላይ ለይኩኖ አምላክ “የአባቱን የዳዊትን መንግሥት” መልሸለታለሁ ማለቱ ምን ማለት ነው? አብያተ መንግሥታቱ አብያተ ክርስቲያናቱ ወይም ምልክቶቹን ይዘው ሊቆዩ የሚችሉ ቋሚ ቅርሶች በግራኝ አሕመድ ወረራ በመፈራረሳቸው በመጥፋታቸው ምክንያት የሩቆቹን ትተን የመሀከለኞቹን ማለትም የጎንደርንና የቅርቦቹን የነዐፄ ምኒልክን የነ ንግሥት ዘውዲቱን የነዐፄ ኃይለሥላሴን ስናይ የዳዊት ኮከብ መለያቸው አልነበረም ወይ? በጎንደር አብያተ መንግሥታት ዋነኛው የፋሲል ግንብን ጨምሮ በሁሉም ላይ ከበር ጀምሮ ከግንቡ የውስጥ ግድግዳ ግራና ቀኝ ከዙፋን ችሎት ፊትለፊት የዳዊት ኮከብ አለ አይደለም ወይ? እውነቱ ይሄ ሆኖ እያለ ተኩላው በቅዱስ ላሊበላ አብያተ መቅደሳት ያለውን የዳዊት ኮከብ ምልክት ብቻ በመጥቀስ ምልክቱን ዛጉዌዎቹ ናቸው ሲጠቀሙበት የነበሩት ማለት ለምን አስፈለገው? ማረጋገጫው የዳዊት ኮከብ ብቻ አይደለም “ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ” የሚለው ቃልም እንጅ፡፡ አየ እነ ተኩላትi ሥራ ስላስፈታቹህኝ ብቻ ነው የማዝነው!

የዛጉዌ ሥርዎ መንግሥት ሰሎሞናዊ መባል ካለበት መባል የሚኖርበት የዳዊት ኮከብን ምልክታቸው ስላደረጉና ኢየሩሳሌምን ተሳላሚ ስለነበሩ አይደለም ይሄ በጣም ደካማ የመከራከሪያ ነጥብ ነው እንደመከራከሪያ ነጥብ መቅረቡም በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰሎሞናዊ ወይም የዳዊት መንግሥት የሚለውን የሥርዎ መንግሥት ሥያሜ የሚያሰጠው አፍቃሪ ኢየሩሳሌም መሆን ሳይሆን የዘር ኃረግ ነውና፡፡ ንግሥተ ሳባ ቀዳማዊ ምኒልክን ከዳዊት ልጅ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለወለደችና እግዚአብሔር ደግሞ ለዳዊት በትረ መንግሥትን ከዘሩ እንዳይወጣ ቃል ስለገባለት ከዚህ ዘር የወጣ ብቻ ነው የዳዊት መንግሥት ወይም ሰሎሞናዊ የሚባለው፡፡ የእኛ ሥርዎ መንግሥት ሰሎሞናዊ የሚባለው ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የዳዊት መንግሥት የመጣልን በሰሎሞን በኩል ስለሆነ ነው፡፡ እናም ዛጉዌዎቹ ሰሎሞናዊ መባል የሚኖርባቸው በአፍቃሬነታቸው አይደለም ነገር ግን አባታቸው ከንግሥተ ሳባ ገረድ ከሰሎሞን ስለተወለደ እንጅ፡፡ አባታቸው የገረዲቱ ልጅ ከመሆኑ በቀር እንደ የንግሥተ ሳባ ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ ሁሉ ከሰሎሞን የተወለደና የዳዊት ዘር በመሆኑ ሰሎሞናዊ መባል የሚገባቸው በዚህ ምክንያት ነው እሽ እነ ተኩላት?

ቀጠሉና በሦስተኛ ደረጃ በዚህ በኹራፊው ጽሑፍ ውስጥ አምታችነት እናያለን፡፡ ይኸውም ‹‹ክብረ ነገሥትን እና ይኼንን የክብረነገሥትን ታሪካዊ ትረካ የሚጠቅሱና የሚያረጋግጡ ከገድላት እስከድርሳናት፣ ከተአምራት እስከ ፍካሬያት፣ ከሊቃውንት እስከ ትርጓሜያት ያሉትን መጻሕፍት ሐሰተኞች አድርጓቸዋል፡፡›› በሚል አምታቻዊነት ሰብዕና የቀረበው ሐሰት ነው፡፡ …… ደግሞ ክብረነገሥትን የሚጠቅሱም ሆኑ የሚያረጋግጡ አንተ የጠቀስካቸውን ዓይነት መጻሕፍት እስከ አሁን አልደረስኩባቸውምና የታተሙበትን ዓመተ ምሕረትና ገጻቸውን እየጠቀስክ ብትነግረኝ ጥሩ ነበር፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ ግን ክብረ ነገሥትን የሚጠቅሱ ገድላትም ሆኑ የድርሳን መጻሕፍት፣ የተአምርም ሆኑ የትርጓሜ መጻሕፍት የሉም፡፡ እናም የሌለባቸውን አለባቸው በማለት መጻሕፍቱን ሐሰተኞች ያደረጋቸው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን እንጂ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አይደለም አሉ፡፡

አየ እነ ተኩላት! ቤተክርስቲያንን መቸ ታውቋትና! የሚገርመውም እኮ እሱው ነው በማታውቁት ነገር መዘባረቃቹህ መቀባጠራቹህ! እስኪ ከየዓይነታቸው መጻሕፍቱን አንድ አንድ ብቻ ልጠቁማቹህ ድርሳነ ጽዮንን አክሱምና ጣና ቂርቆስ የሚገኝ የታቦተ ጽዮንን አመጣጥ የሚተርክ የብራና መጽሐፍ፣ ገድለ ተክለሃይማኖትን፣ መጽሐፈ ምስጢርን፣ ፍካሬ ኢየሱስን፣ ተአምረ ማርያምን፣ ወንጌል አንድምታን አንብቡ ገጽና ቁጥር ያላቹህትን አልናገርም በዚህ ምክንያት መጻሕፍቱን ስታነቡ ምናልባት ቤተክርስቲያንን ጠልቃቹህ ያለመረዳታቹህ ችግራቹህ ሊቀረፍላቹህ ይችል ይሆናል የሚል ተስፋ በመያዝ፡፡

ተኩላት ቀጠሉና ዲያቆን ዳንኤል ‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በሚለው ጽሑፉ በፍጹም ያላለውን ‹‹በገድለ ተክለ ሃይማኖት ውስጥ ስለ ሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥትና ስለ ሲሦ ድርሻ የሚተርከውን ታሪክ የለም ብሎናል›› ሲል እንደ አለ አድርጎ አቅርቧል አሉ፡፡ “ ….አቡነ ተክለሃይማኖት ሲሦ መንግሥት አግኝተዋል የሚለው ትረካ መንግሥት ወደ ጎንደር ከተቀየረ በኋላ (17ኛው መ.ክ.ዘ) በተጻፈው በብዕለ ነገሥት ላይ የተገለጠ ነው፡፡ ብዕለ ነገሥት የነገሥታትን ሀብት ለማሳየት የተጻፈ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ነው ከይኩኖ አምላክ ጋር ቃል ኪዳን ገብተዋል ተብሎ የተጻፈው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው መንግሥት ወደ ጎንደር ሲዛወር ደብረ ሊባኖስ ከማዕከላዊው መንግሥት ራቀ፡፡ አካባቢውም ክርስቲያን ባልሆኑ ሕዝቦች ተከበበ፡፡ የጎንደር ነገሥታት ገዳሙን እንዳይረሱትም በብዕለ ነገሥት የአባታቸውን ይኩኖ አምላክን ቃል ኪዳን እንዲያስታውሱ የሚያደርግ ነገር ተጻፈ፡፡ እናም ተስፋየም ሆነ ሌሎች እንደሚሉት አቡነተክለሃይማኖት ከቅድስና ሥራ በቀር የገቡበት ፖለቲካ የለም” እያልኩት የወሸከትኩት እኔ ነኝ እንዴ? “ሲባል እንደኖረው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሦ መንግሥት ቢቀበሉ ኖሮ…..” እያልኩ የቀባጠርኩትና ቤተክርስጢያን በአቡነ ተክለሃይማኖት አማካኝነት ሲሦ መንግሥት እንደተቀበለች የሚተርከው ገድለ አቡነ ተክለሃይማኖት ሐሰተኛ ተደርጎ እንዲቆጠር የጣርኩት እኔ ነኝ? “ይኩኖ አምልክና አቡነ ተክለሃይማኖት የተግባቡት ቃል ኪዳን እውነት ቢሆን ኖሮ አቡነ ተክለሃይማኖት ደብረ ሊባኖስን ሲያቀኑ ችግር ሊገጥማቸው አይገባም ነበር” የሚል የተኩላው መከራከሪያ የበሰለ መከራከሪያ ነው? በወቅቱ ሥልጣንን ከዛጉዌዎች የተረከበው የይኩኖ አምላክ መንግሥት ገና ካለመደላደሉ የተነሣ እንኳንና ለቤተክርስቲያን የገባውን ቃል ለመፈጸም ይቅርና ለራሱስ በቂ ገቢ ነበረው ወይ? ወደ ኋላ ግን ይህ ሰሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥት ሲደላደል የተገባው ቃል ሲፈጸም ኖሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ተኩላው እንዳለው መንግሥት ወደ ጎንደር ከተዛወረ በኋላ ሳይሆን ሳይዛወር ገና ሸዋ እያለ ጀምሮ በታሪክ መጻሕፍት ሰፍሮ እንደሚገኘው (ለምሳሌም የተክለ ፃዲቅ መኩሪያ የግራኝ አሕመድ ወረራ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ) ሲሦው ድርሻ ግብር ደብረ ሊባኖስ ይገባ የነበረው፡፡

ተኩላቱ ቀጠሉና ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ኹራፊው አምሳሉ አገላለጽ ከሆነ ‹‹አገው›› ማለት ፀረ አማራነት ነው፡፡ ኹራፊው አምሳሉ፤ አገዎች ‹‹ፀረ አማራዎች›› ስለሆኑና ዳንኤል ደግሞ አገው ስለ ሆነ ‹‹ፀረ አማራ›› ነው፤ አለን፡፡ ይህን ከራሱ ከአምሳሉ አመክንዮ አንጻር ስንገለብጠው አማራዎችም ፀረ አገው ናቸው ማለት ነው፡፡ ኹራፊው አምሳሉ ደግሞ ራሱን የአማራ ጠበቃ አድርጎ ስለ አቀረበ ፀረ አገው ነው ማለት ነው ሲሉ ሐሰተኛ ክስ አቀረቡ፡፡ ይሄንን አገው ፀረ አማራ ነው አማራ ፀረ አገው ነው ያለው በወያኔ እኩይ ፀረ ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ የተቃኘው የተሞላው የናንተው እኩይ እርጉም ጭንቅላት እንጅ እኔ አልወጣኝም በጭራሽም ሊወጣኝ አይችልም፡፡ ይሄንኑ እኩይ ወያኔያዊ ዓላማቹህን ወደ ቤተክርስቲያን ይዛቹህ መግባታቹህን አጥብቄ ተቃወምኩ እንጅ፡፡ ሕዝቡም ይሄንን እኩይና ሰይጣናዊ አስተሳሰብና ዓላማቹህን እንዲቃወመው እንዲህ በማለት ጭምር ነበር ያሳሰብኩት የነበረው “ስለ እግዚአብሔር ብላቹህ ንቁ! ተከላከሉ፣ ጠብቁ፣ የጥፋት ሥራዎቻቸውን አጋልጡ፣ ከሁሉም በላይ የጎሳና የጥላቻ መርዘኛና አጥፊ አመለካከትና አስተሳሰባቸውን ተዋጉ ለሀገርም ለሕዝብም ለቤተክርስቲያንም ለማንም አይጠቅምምና፡፡ ይህንን ማድረግ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታው ነው፡፡ ለክርስቲያኑ ደግሞ ሃይማኖታዊ ግዴታው እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል” በማለት እንዲያው ነገሩን ካመጣቹህት ዘንዳ ይሄን አልኩ እንጅ በአሁኑ ሰዓት ብሔረሰብ የሚለው ፈሊጥ ውሸት ነው፡፡ “ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጥፋት የሚታደገው ብቸኛው መንገድ” የሚለውን ጽሑፌን አንብቡ፡፡

 

ተኩላቱ ኹረፋቸውን ሲቀጥሉ፡- ሌላው ኹራፊው አምሳሉ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ‹‹ወያኔ ነው›› ለማለት እንደ ማስረጃ የጠቀሰው ‹‹ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥትና ሲሦ መንግሥት የለም›› ብሏል፤ የሚለውን ነው፡፡ ይህን ከሦስት አቅጣጫ እንፈትሸው፡፡ የመጀመሪያው ከወያኔ የታሪክ ትንተና አቋም አንፃር ነው፡፡ ወያኔ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደሚለው፤ ‹‹ሰሎሞናዊ የሚባል የተለየ መንግሥት አልነበረንም፡፡ ሲሦ መንግሥት ለቤተክርስቲያን በአቡነ ተክለሃይማኖት በኩል አልተሰጠም፤›› አይልም፡፡ ወያኔ ‹‹አዲስ ራእይ›› በተባለው ንድፈ አሳባዊ መጽሔቱም ሆነ ለኢንዶክትሪኔሽን በአዘጋጀው መጻሕፍቱ፤ ‹‹በሰሎሞናዊው እና በዛግዌ ሥርወ መንግሥታት መካከል በነበረው ሽኩቻ አቡነ ተክለሃይማኖት ለይኩኖ አምላክ አድልተውና ይኩኖ አምላክም የሸዋ ሰው ስለ ሆነ ለዘራቸው አድልተው መንግሥትን ከዛዌ ሥርወመንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት እንዲሸጋገር አድርገዋል፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖት ለሰሎሞናዊ ሥርወመንግሥት በዋሉት ውለታ ለቤተክርስቲያን ሲሦ መንግሥት ተሰጠ፡፡›› ነው የሚለው አሉ፡፡ እየ እነ ተኩላትi እኔ የማውቀው ወያኔ ሀገራችንን የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ያላት ኢትዮጵያ የተፈጠረችው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ነው ማለቱን ነው፡፡ እሱን እሱን እናንተው ካድሬዎቹ ንገሩን እሽ እነ ተኩላትi ወያኔ እንዲህም ብሎ ነበራ በካድሬነት ሥለጠናቹህ ላይ በጠቀሳቹሀቸው መጻሕፍት ያሠለጠናቹህ?

ተኩላቱ ይቀጥሉና ሦስተኛው ከ‹‹ሐመር›› መጽሔት ምልከታ አንፃርነው፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤‹‹ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ለዘራቸው አድልተው መንግሥት ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት እንዲሸጋገር አድርገዋል፡፡ በውለታም ለቤተክርስቲያን ሲሦ መሬት ተሰጥቷቸዋል፤›› የሚለውን ትረካ አጽንዖት ሰጥቶ ‹‹የለም›› ያለውን፤ ‹‹ሐመር›› መጽሔት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ‹‹አፈ ታሪክ›› ብሎታል፡፡ ስለዚህ በኹራፊው በአምሳሉ ገብረኪዳን የፍረጃ ስሌት መሠረት ‹‹ሐመር›› መጽሔት እንዲህ በማለቷ ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት የወያኔ ልሳን ነበረች ልንል ነው? የፖለቲካ ድንቁርና ይሉታል ይኼ ነው አሉ፡፡ አየ እነ ተኩላትi ከላይ ፈጽሞ አላለም እያላቹህ ልባችንን ስታወልቁት ቆይታቹህ አሁን ደግሞ እንደገና ጭራሽ “አጽንዖት ሰጥቶ ‹‹የለም›› ያለውን” በማለት አረጋገጣቹህልን? አሁን እናንተ ጤነኞች ናቹህ? ቆይ ለመሆኑ ሐመር መጽሔት ያንን ጽሑፍ ያስተናገደችው በርእሰ አንቀጽ ላይ ነው ወይስ የተለያዩ ሐሳቦች በሚስተናገዱበት ሌሎች ዓምዶች ላይ? በርእሰ አንቀጽ ላይ እንደዛ ተብሎ ከሆነ እንዳላቹህትም ሐመር የወያኔ ልሳን ሆናለች ማለት ይቻላል፡፡ እስከማውቀው ድረስ ግን ሐመር መጽሔት በርእሰ አንቀጽ እንዲህ ዓይነት የደነቆረና ፀረ የኢትዮጵያ ታሪክ ጽሑፍ አላስተናገደችም፡፡

 

ተኩላቱ ቀጥለዋል እንግዲህ ‹‹መንበር ይሰደዳል›› ብሎ ፖለቲካዊ አቋም ከያዘው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ተለይቶ፤ ‹‹መንበር አይሰደድም›› ብሎ ሃይማኖታዊ አቋም የያዘውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚ የሚያሰኘው ከሆነ፤ኹራፊው ራሱ እንዳለው በየጊዜው የወያኔ ጅራፍ የሚያርፍበት ማኅበረ ቅዱሳን፤ ‹‹መንበር አይሰደድም›› የሚል ሃይማኖታዊ አቋም አለውና የወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚ ነውን? ከተጠረጠሩ በአማራ ብሔርተኛነት እና በፀረ ወያኔነት ይጠረጠሩ ካልሆነ በስተቀር በወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚነት በፍጹም የማይጠረጠሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፤ ‹‹መንበር አይሰደድም፤ ሕገ ወጥ ሲኖዶስ ማቋቋም ግን ሕዝብ ስለ ሚከፋፍል መንበሩን ከመልቀቅ የከፋ ሌላ ጥፋት መጨመር ነው፡፡›› የሚለውን ሃይማኖታዊ አቋም በፖለቲካ ተዋስዖ /Discourse/ ተንትነው ያቀረቡት የወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚ ስለሆኑ ይሆን? ከኹራፊዉ አምሳሉ ገብረ ኪዳን ውጪ ሌላ ሰው አዎን የሚል ያለ አይመስለኝም አሉ ተኩላቱ፡፡ እኔም አዎ አልልም አሁን በናንተ ቤት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ልታጣሉኝ አሲራቹህ ሞታቹሀል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለምን እንዲህ የሚል አቋም እንደያዘ ራሱን ጠይቁት፡፡ በግሌ ለማኅበሩ ባለኝ ቀና አመለካከትና ስስት የማይመስሉኝን ትክክል አይደለም የምላቸውን አንዳንድ ነገሮችን ሲፈጽም ቀርቤ ለአመራሮቹ ወይም በምጽፋቸው ጽሑፎች የሚመስለኝት ትክክል ነው የምለውን ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ ለምሳሌ “የፓትርያርክ ምርጫ” ተብሎ በምርጫ ሽፋን አባ ማትያስን ለመሾም ሽር ጉድ በሚደረግበት ወቅት ማኅበሩ በሒደቱ በመካፈሉ ወይም በመሳተፉ የሠራውን ስሕተት ሰምተውኝ ባይታረሙም ገና ከጅምሩ ለዋናው አመራር ለማስረዳት ሞክሬያለሁ ተከራክረንበታልም፡፡ ውጤቱም አስቀድሜ የተነበይኩት ነው የሆነው፡፡ ማኅበሩ አማራጭ ከማጣትና ህልውናውን ለማስቀጠል አውቆ የሚሳሳታቸው ነገሮች እንዳሉ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ መሆን ቢያስፈልግም እነዚህ የሚሠሩ ስሕተቶች እየበዙ ሲሔዱ ሳያውቁት ማንነቱን እንዳይለውጡት ሥጋቴ ነው፡፡ ሰጥቶ መቀበል የሚለው መርሕ የሚሠራው በፖለቲካው መስክ ነው እንጅ በሃይማኖት ጉዳይ አይደለም በመስጠቱ ሒደት መርከስ ሕግን ቀኖናን ሥርዓትን መሻር አለና፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን በተመለከተ እንደዛ በማለታቸው ትክክል እንዳልሆኑ ብገነዘብም ከምን አውድ አንጻር እንዲያ እንዳሉ ግልጽ ነውና ምንም ማለት አያስፈልገኝም፡፡

ተኩላቱ ሌላም የጠቀሷቸው ታሪክ ጸሐፊ አሉ፤ የታሪክ መምህር ተብሎ አንድ ሌላ የተጠቀሰውን ግን እነሱ ቢጤአቸው እንዳይቀርባቸው ፈልገው ነው እንጅ ከቁጥር የሚገባ አይደለምና ተውት፡፡ ለማንኛውም እኔ በታሪክ አጥኝዎች ዙሪያ ያለኝን ሐሳብ እዛው ላይ ገልጫለሁ፡፡ የገረመኝ ነገር ቢኖር ተኩላቱ ከቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ይልቅ እውነቱን ለማወቅ አቅም የወሰናቸውንና የመሰላቸውን የጻፉትን ግለሰቦች ጽሑፍ እንዲሁም ምን እንደሚሉ የማያውቁትን ጫት አመንዣኪ በጫት ምርቃና የቀባጠረውን ቅዠት ከደቂቃ በኋላ ሲጠየቅ እንደዚህ ብያለሁ እንዴ? ብሎ የተናገረውን የማይደግመውን ቀባዣሪ የቅዠት ዲስኩር፣ የነጭ ቅጥረኛውን እንቶ ፈንቶ አመኑ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን እንቶ ፈንቶ እየለቃቀሙ እውነቱ ይሄ እንጅ የቅድስት ቤተክርስቲያን መረጃዎች አይደሉም ይላሉ፡፡ ታዲያ እኔን ተኩላ ብየ እንድጠራቹህ ምን አስገደደኝና ይሄው ተኩላዊ ግብራቹህ አይደለምን? የኢትዮጵያን ታሪክ አጥኚ ነን ብለው የመሰላቸውን እንቶ ፈንቶ የሚያወሩ ሰዎች የኢትዮጵያ ታሪክ እንዴት እንደሚጠና እንኳን ጨርሶ የሚያውቁ አይደሉም፡፡ ታሪካችን ከሚያጠኑ የተሻለ ሥራ የሠሩ ሰዎች የሉም እያልኩ አይደለም፡፡ እነኝህም ቢሆኑ ግን ገናናውን ታላቁን በኩሩን የሀገራችንን ታሪክ አዳፍኖ ለማስቀረት በሐሰተኛና መርዘኛ ወሬ ለመበረዝ በዘረኛና እኩያን ነጮች ሲደረግ የኖረውን እየተደረገም ያለውንና ወደፊትም የሚቀጥለውን ሸር ሴራና ተንኮል እየተከታተሉ የማክሸፍ የማጋለጥ የመከላከል የመመከት እውነቱን የማጥራት እልህ ጥንካሬ ጽናትና ትጋት ያላቸው አይደሉም፡፡ ከታሪክ አጥኝዎቻችን ብዙዎቹ በነጮቹ ሴራ ተጠልፈው ቅጥረኛ በመሆን በዚያው በነጮቹ ላይ የራሳቸውን የሚጨምሩ ናቸው፡፡ አንዳንድ የተናገሯቸውን ነገሮች እየጠቀስኩ ከምን ዓላማና ተነሳሽነት እንዲያ ሊሉ እንደቻሉ ብናገር ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሌሎች ሀገራት ታሪክ አይደለም፡፡ የተወሳሰበ የተሰወረ በርካታ ነገሮች አሉት፡፡ የሚጠናበት የራሱ የሆነ የተለየ መንገድ አለው፡፡ የረቀቀ አእምሮንና ቅድስናን ይጠይቃል፡፡ የሀገራችንን ታሪክ መቶ በመቶ ትክክለኛውን መሬት ላይ የነበረውን የሚያውቁት በየበረሀው በየዋሻው በየፍርኩታው በየገዳሙ መንነው ከተጋድሏቸው የተነሣ የቅድስና ደረጃ የደረሱት ቅዱሳን እናት አባቶቻችን ብቻ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ አጥኝ ነን ከሚሉ ግለሰቦች እስከ አሁን ሀገራችን ታሪኳን ለማጥናት የምትጠይቀውን አቅምና ብቃት አሟልቶ አይደለም በጥቂቱ እንኳን የያዘ የለም፡፡ ቅዱሳኑ መቶ በመቶ ትክክለኛውን ታሪካችንን ይወቁት እንጅ ይሄንን የሚያውቁትን ይናገራሉ ማለቴ አይደለም፡፡ መናገር የማይፈልጉበት ምክንያት ታሪካችን ከሌሎቹ በተለየ መልኩ አሳፋሪ ስለሆነ አይደለም፡፡ በእርግጥ ሀገራችን የዚህች ኢፍትሐዊና የግፍ አውድማ ምድር አካል እንደመሆኗ እንደ ማንኛውም ሀገር ሁሉ አንዳንድ ደስ የማያሰኝ ታሪክ ሊኖረን ይችላል፡፡ ይሁንና ቅዱሳኑ የሚያውቁትን ትክክለኛውን ታሪካችንን በሚፈለገው መጠን መናገር የማይፈልጉባቸው ምክንያት እሱ አይደለም፡፡ ሌሎች ምክንያቶች አንድ ሁለት ሦስት የሚሆኑ አሉ፡፡

ለማንኛውም የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሌሎቹ ሀገራት ማንም ጫት አመንዣኪውም፣ የመጠጥ ሱሰኛውም፣ ጎጠኛውም፣ ቅጥረኛውም፣ ባንዳውም፣ ምኑም ሊያጠናው አጥንቶም ሊደርስበት የሚችለው ታሪክ አለመሆኑን አበክሬ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ተኩላቱም ሆኑ ሌላው ሰው ይሄንን እውነት መረዳት ይኖርበታል፡፡ ወደ ቀረው የተኩላቱ ኹረፋ እንለፍ፡-

አሁንም ተኩላቱ እኔን ለማሳጣት በማሴር ቀጠሉና ምን አሉ በኢስላም አስተምህሮ አለማመን እና የእነርሱን ነቢያት አለመቀበል አንድ ነገር ሆኖ መሪያቸውን ክብረ ነክ በሆነ አጠራር መጥራትን ትክክል የሚያደርግ የክርስትና አስተምህሮ የለም አሉ፡፡ አየ እነ ተኩላትi ለመሆኑ ጌታ በወንጌል “ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ” ማቴ. 24፤11 የሚላቸው እነ ማንን ነው? ምን ማለትስ ነው? ይሄ ቃል የኔ ይመስላቹሀል እንዴ? ወይ ፖለቲከኝነታቹህን ማለትም ወያኔነታቹህን ምረጡ ወይ እውነትን ማለትም ክርስቶስን ምረጡ ሁለቱንም ይዞ መቀጠል አይቻልም እሺ? ለነገሩ ስታስመስሉ እንጅ እናንተ እንኳን ያዋጣናል ያላቹህትን ውየናቹህን ይዛቹሀል፡፡

እነዚህ ነውረኞች ይግረምህ አሉና ስርዋጽ ማለት ተፈልጎ ሱሯጽ አሉና ምን አሉ፡- ከዚሁ ጋራ በተጨባጭ የማውቀውን እንደሱሯጽ (as side issue) ልንገራችው፡፡ ኹራፊው አምሳሉ በተለይ ከአቶ ኤርሚያስም ለተስፋዬ የተሰጠው ምላሽ ያንገበገበው ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው በ1990ዎቹ ውስጥ የካድሬነት መልማይ የጡት አባት በመሆን ትንሽ የወያኔን ፍርፋሪ እንዲያገኘ ያደረገው ተስፋዬ ነበር፡፡ ሁለተኛው ሥራ በፈታባቸው ዓመታት ውስጥ እንጀራ የሆኑት የተስፋዬ

የጥፋት መጻሕፍት ነበሩ፤ አሁን ደግሞ የአቶ ኤርሚያስ መጽሐፍ፡፡ እኛም በመጽሐፍ ቅርጽ እያዘጋጀ የሚሸጣቸውን ፎቶ ኮፒ ‹መጽሐፍ› ገዝተን ያነበብነው እርሱ ከአሰማራቸው መጻሕፍት አዟሪዎች ነበር፡፡ ከእነዚህ በቀጥጣ ከማውቃቸው መረጃዎች ተነሰቼ ስደመደም

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስቀድሞ ለተስፋዬ÷ በኃላ ለአቶ ኤርሚያስ በሰጠው ጹሑፍ መደምደሚያ  ላይ‹‹ ሌላውንም ነገር የሚነግሩን እንዲህ ሐሰት ይዘው ነው ማለት ነው›› ማለቱ አስቆጥቱታል ማለት ነው፡፡ ዲያቆን ዳንኤል እንዲህ መደምደሙ መጻሕፍቱ በሰፊው ተሰራጭተው፣ ሰዉ አንብቧቸው፣ የሥርዐቱን ፀረ ዲሞክራሲያዊነት እንዳይረዱና የተአማኔነት ችግር እንዲገጥማቸው ሊያደርግ ይችላል ከሚል በጎ መንፈስ ሳይሆን÷ የመጻሕፍቱን መረጃ ተአማኔነት ዋጋ በማሳጣት ገዥ ሊያሳጣኝ ይችላል ከሚል ጥቅመኝነት የመነጨ ቁጣ ይመስለኛል እኔ እኮ የሚገርመኝ ከላይ በፀረ ወያኔ ፖለቲከኝነት ሲከሱኝ ቆይተው አሁን ደግሞ እንደገና ሰላይ ያደርጉኛል፡፡ የጻፉት ሁሉ ምንም እንኳን ልብ ወለድ ድርሰት ቢሆንም ድርሰትም እኮ ወጥነት ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ እንዲህ ውጥንቅጡ የወጣ ምን ሊል እንደፈለገ በውል ያልተረዳ ጽሑፍ እንዴት ይጻፋል? ይሄን ያህል ናቸው እንግዲህ፡፡ ቆይ ግን የምራቸውን ነው? ያሉት ነገር በእርግጥ ስለ እኔ ነው የሚያወራው? ነው ወይስ እኔ የማላውቀው በእኔ ስም የሚነግድ ሌላ አምሳሉ አለ? ተስፋዬ በ1990ዎቹ በካድሬነት የመለመለኝ እኔን አምሳሉን ነው? ከዚያም ሥራ ፈትቸ እያለሁ የሱን መጻሕፍት አሁን ደግሞ የኤርሚያስን መጻሕፍት በቅጅ እያባዛሁ ስሸጥ የነበርኩትና እየሸጥኩ ያለሁት የመጽሐፍ ነጋዴ እኔ አምሳሉ ነኝ? እንዴ! እኔ የማላውቀው ሌላ እኔ ያለ እስኪመስለኝ ድረስ እኮ ተጠራጠርኩ! ሰው ሲዋሽ ቢውል በዚህ ደረጃ ፍጥር ተደርጎ ይዋሻል? የሚያውቁኝ ሰዎች ይህ ነጭ ውሸት ፈጠራ ምን ያህል ይገርማቸው! ይሄንን የተኩላት ቡድንስ ምን ያህል ይታዘቡት ይሆን! የኔ ማንነት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ቀጥ ባለ መስመር ያለና ማንም በቀላሉ ሊያየው ሊረዳው ሊያረጋግጠው የሚችለው ሆኖ ሳለ እንዲህ ብለው መዋሸታቸው ማንን ያሳስትልናል ብለው ነው እንዲህ ዓይነት ነውረኝነታቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሐሰት የሚያወሩት? አንባቢውንስ ምን ያህል ቢንቁት ነው ነገ አጣርቶ የሚደርስበትን ነገር ፈጥረው ሊያወሩ የቻሉት? ይሄንን በሐሰትና ማወናበድ የተሞላ ጽሑፍ ጽፈው መልካም ስም ያላቸውን ድረ ገጾችን ለጥፉልን ብለው ሲያስለጥፉስ እንዴት ለድረ ገጾቹ ስምና ክብር አያስቡም? አሁን እነዚህ ናቸው የተማሩ? አሁን እነዚህ ናቸው የእግዚአብሔር አገልጋዮች? እነዚህ አይደለም የእግዚአብሔር አገልጋዮጭ ሊሆኑ ይቅርና እንዲያው በእግዚአብሔርስ ያምናሉ ብላቹህ ታስባላቹህ? ሥራቸው የሚያሳየው ማመናቸውን ነው? በእግዚአብሔር ቢያምኑ እሱን መፍራቱ ይቅርና ትንሽም እንኳን ሳያፍሩት ለርካሽ የውንብድና ጥቅማቸው ሲሉ በዚህ ደረጃ በአደባባይ እራሳቸውን ለትስብት ይዳርጉ ነበር? ለምንስ ይሄንን ፈጥረው ማውራት አስፈለጋቸው? እነዚህ ሰዎች “አሸባሪ ጽሑፎችን (መጻሕፍትን) እያባዛ በማሰራጨት” ብለው ወንጅለው ወኅኒ ሊወረውሩኝ አስበው ለዚያ ሲያመቻቹኝ ይሆን? በጣም የሚገርሙ ጉዶች ናቸው፡፡

ተኩላቱ ቀጥለዋል እንዲህም አሉ፡- ኹራፊው አምሳሉ በሀገሬ፣ በቤተክርስቲያንና በውድ ሕዝቧ ሸፍጥ ሲፈጸም አልችልም፤ በፈንጅ ነው የምፈጀው›› እያለና እየቀባጠረ በፀረ ወያኔ ቆብ ከወያኔ ባልተናነሰ በወያኔያዊ መንገድ በሀራችን ሕዝብ አብሮነት ላይ ሸፍጥ እየፈጸመ የሚገኘው ተስፋዬ ገብረ አብን አይደለም በፈንጅ÷በብዕር ምንም አላለውም ተስፋዬ ገብረአብ ስለ አኖሌ የጻፈው የፈጠራና ሰይጣናዊ ዓላማ ያለው እንደሆነ ማንም ያውቃል ስለ ወያኔ የጻፈው ግን እንዲያውም የሚገባውን ያህል እንዳልጻፈ መረዳት ይቻላል አሉ፡፡ ስለ ተስፋዬ እኩይነት እኮ እዛው ላይ እንዲህ በማለት ጽፌያለሁ “ተስፋዬ ገብረ አብ ስለ አኖሌ የጻፈው የፈጠራና ሰይጣናዊ ዓላማ ያለው እንደሆነ ማንም ያውቃል ስለ ወያኔ የጻፈው ግን እንዲያውም የሚገባውን ያህል እንዳልጻፈ መረዳት ይቻላል” በማለት፡፡ በዝርዝር ከሆነ የተፈለገው ስለዚህ ተስፋዬ ስለሚባለው ሸአቢያ በምጽፍበት ጊዜ ይጠብቁ፡፡ አሁን የጻፍኩት ግን ስለ እሱ አይደለምና በዝርዝር መጻፍ አይጠበቅብኝም፡፡

ተኩላቱ የዳንኤል ሚስት ወ/ሮ ጽላት ትግሬ አይደለችም ከአማራ ቤተሰቦቿ የተወለደች አማራ ናት፡፡ ስሟ ጽላት ስለሆነ ነው ትግሬ ናት ያለ…. ዳንኤልም አገው አይደለም አማራ ነው፡፡ አምሳሉ ትግሬ የሆነ ሁሉ ወያኔ ነው የሚል እምነት ስላለው ነው…. አሉ፡፡ ተኩላት ሆይ! ጽላት የሚለው ቃል ትግርኛ ነው ያለው ማን ነው? የመታወቂያዋን ኮፒ ላውጣው እንዴ? አዎ ትግሬ የሆነ ሁሉ መቶ በመቶ ወያኔ ነው ማለት ባይቻልም በእኔ ግምት 99 በመቶ የሚሆኑት ትግሬዎች ግን ወያኔ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ እኔ ወያኔ ስል ሕወሀትን ብቻ ማለቴ አይደለም ለዝርዝሩ “የትግራይ ሕዝብ ወያኔን ፈጠረ ወይስ ወያኔ የትግራይን ሕዝብ?” የሚለውን ጽሑፍ አንብቡ፡፡ ዳንኤልም አማራ ነው አሉ፡፡ አዎ ለሽፋን የሚጠቀመው አማራነትን እንደሆነ እኮ እዛው ላይ ገልጫለሁ፡፡

ባጠቃላይ በዚህ “እንቶ ፈንቶ” መባል እርባና ቢስነቱን በማይገልጸው ጽሑፋቸው ይሄንን የተኩላት ቡድን እጅግ በጣም ነው የታዘብኩት ከጻፉት ነገር ሁሉ አንድ እውነት የተናገሩት ነገር ቢኖር እኔ የ 12ኛ ክፍል ትምህርት አጠናቅቄ ከዚያ መቀጠል ያልቻልኩ የቀለም ሽፍታ ስለመሆኔ ያሉት ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱንም ቢሆን ቆይ! ግድ የለም! ሥልጣን ኖሮኝ በሙስና ብር የማግኘት ዕድል አግኝቸ እኔም እንደነሱ ሁሉ በቀላሉ መግዛት ባልችልም ብር ከየትም ከየትም ብየ አምጥቸ እንደእነሱው ሁሉ ወደ አንዱ ሱቅ ጎራ ብየ ዶክትሬቴን ከቻልኩ ፕሮፌሰርነቴን ገዝቸ ከእነሱው ጋር እኩል ዶክተር ፕሮፌሰር ተብየ ባልጠራ እኔ አምሳሉ አይደለሁምi

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን:

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

<span>%d</span> bloggers like this: