ግንቦት 20 የበላቸው ቀሽ ገብሩዎች (በወይንሸት ሞላ )

ኢህአዴግ ታግዬ አስገኘኋቸው ከሚላቸው መብቶች መካከል አንዱና ሁሌም የሚያወራለት የሴቶች መብት ነው፡፡ በተለያዩ ፎረሞች ያደራጃቸው አባላቱም ኢህአዴግ የሴቶች መብትን እንዳስከበረ ለማሳየት ተደራጅተው ዶሮ የሚያረቡትን፣ ድንጋይ የሚቀጠቅጡትን ሴቶች ‹‹ተጠቃሚነት›› በመጥቀስ የፓርቲያቸውን ስኬት ሲያወድሱ መዋላቸው የዕለት ተዕለት ተግባር ነው፡፡Wonishet Mola (Blue Party )

በእውነቱ በባህልም ሆነ ከእምነት ጋር በተያያዘ ሴቶችን እንደሚጨቁኑ የሚወቀሱት የአረብ መንግስታት እንኳ ስለ ሴቶች መብት መከበር በሚጥርበት ወቅት ሴቶች ድንጋይ ስለፈለጡና ሌሎች አድካሚ ስራዎችን ስለሰሩ የሴቶችን መብት አስከብሬያለሁ የሚለው ዝባዝንኬ ውሃ የሚቋጥር ሊሆን አይችልም፡፡ በ1960ዎቹ ትውልድ ሴቶች የማይናቅ ተስትፎ እንዳደረጉ እነ ማርታን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ደርግ የሚያፍነው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ቢሆንም የሴቶች መብት ተለይቶ የተነፈገበት ጊዜ አልታየም፡፡ ኢህአዴግ ግን ራሱን ከደርግ ጋር በማወዳደር የተሻለ መብት እንደሰጠ የሚገልጸም ምን እንደሆነ በግልጽ አጥጠቀስም፡፡

ሆኖም የሴቶችን መብት አስከብሬያለሁ ድስኩር በውቅሩ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጭቆና ለመሸፈም ካልሆነ በእውነታው የምናየው አይደለም፡፡ በህወሓትኢህአዴግ ትግል ውስጥ በርካታ ሴቶች መሳሪያ አንግተው ስርዓቱን አዲስ አበባ ድረስ አድርሰውታል፡፡ እንደ አረጋሽ ያሉት በፖለቲካ ልዩነት ስርዓቱን ጥለው ሲወጡ ሌሎቹ ደግሞ የረባ ቦታ ሳይሰጣቸው በሌለ መስክ ሲሰማሩ ስልጣኑ በወንዶች ቁጥጥር ስር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ህወሓት ጋር ታግለው ስልጣን ላይ ከወጡት ይልቅ ጦር ሜዳ ላይ እያለች የተሰዋችው ቀሽ ገብሩ በርካታ ሰዎች ያውቋታል፡፡

መቼም በህወሓት/ኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ከቀሽ ገብሩ ውጭ ሌላ ቆራጥ ታጋይ ጠፍቶ ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁን በህይወት ያሉትን ቀሽ ገብሩዎች ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ ቀሽ ገብሩም ብትሆን ስለሞተች እንጅ በህይወት ብትኖር ይህ ነው የሚባል ቦታ ልታገኝ እንደማትችል አሁን ኢህአዴህ ካለው ተሞክሮ ለመረዳት ቀላል ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛዎቹ ለግንቦት 20 ያደረሱትን ሴቶች እንኳ የሚገባቸውን ክብርና ስልጣን ያልሰጠው ገዥው ፓርቲ የሴቶችን መብት አስከብሬያለሁ ቢል ከተለመደው ፕሮፖጋንዳ ያለፈ አይሆንም፡፡

በተቃራኒ ጎራ የሚገኙት የፖለቲካ ቡድኖችና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሴቶችን ስናይ ደግሞ መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ጀምሮ መልካም መልካም የሚባሉትን የዴሞክራሲና የነጻ ገበያ መርሆች አገራችን ህዝብ እንዳይደርሱ ሲከለክል የአገራችንን ባህል የሚጎዳውን ግን በሩን ከፍቶለታል፡፡ በደርግና በኃይለስላሴ ወቅት ሲወገዙና ሲከለከሉ የነበሩ የባህል ወረርሽኞች ኢትዮጵያውያንን እንዲያደነዝዙ በሩ ተከፍቶላቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋው ሴተኛ አዳሪነትና ሌሎች የባህል ወረርሽኞች ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም በኋላ ኢትዮጵያን መዳረሻቸው ያደረጉ ናቸው፡፡

በፖለቲካው መስክ ያለውን ካየን ደግሞ ይበልጡን የባሰ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በርካታ የተቀናቃኝ (ታጣቂም ሆነ ሰላማዊ) የፖለቲካ ቡድኖችን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ‹‹ኦነግ›› ተብለው ታስረዋል፡፡ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የሌሎች ቡድኖች አባላት የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን እስር ቤት ውስጥ ታጉረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሴቶች የሚገኙበት ሲሆን ወንዶቹ ደግሞ ሴት ልጆች፣ ሚስቶችና እናቶችን የሚያስተዳድሩ፣ የሚረዱና የሚያግዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አብዛኛዎቹን ሴቶች የሚጎዱ አሉታዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ አልተቆጠበም፡፡

በኢኮኖሚው መስክ ሴቶች ተጠቃሚ ናቸው ቢባልም ወደ ውጭ የሚሰደዱት እነሱው መሆናቸው ፕሮፖጋንዳው እርባና ቢስ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ከ18 አመት በታች የሆኑትን ጨምሮ በርካታ ሴቶች ወደ አረብ፣ ደቡብ አፍሪካና ጎረቤት የአፍሪካ አገራት ይጎርፋሉ፡፡ እነዚህ አብዛኛዎቹ እህቶቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱት ግንቦት 20 አመጣው የሚባለው ልማት ለእነሱ ጠቃሚ ባለመሆኑ እንጅ አገራቸውን ጠልተው አይደለም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ለሴቶች መብት ቆሜያለሁ የሚለው ኢህአዴግ በውጭ አገር ችግር ሲደርስባቸው ‹‹ህገ ወጥ›› አድርጎ የሚፈርጃቸውና ተገቢውን እርዳታ የማያደርግላቸው መሆኑ ነው፡፡

ለዚህ በምሳሌ ልጠቅሰው የምችለው ከሳውዲ አረቢያ ተባረው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ መንግስት ‹‹ህገ ወጥ›› ተብለው መፈረጃቸውና ለእነሱም ድምጽ ለማሰማት ሳውዲ አረቢያ ኢምባሲ የወጡ ኢትዬጵያውያን በኢትዬጵያ መንግስት የፌደራል ዱላ የተበተነ ሲሆን ይህ እንደሀገር መደፈራችንን ያየንበት እንደመንግስ ለህዝብ ተቆርቋሪነት ሞራል የጎደለው መሪ እንዳለን የሚያሳየን ነው፡፡ ታዲያ ከሳውዲዎች ጎን ቆሞ ኢትዮጵያውያንን ህገ ወጥ ብሎ የሚፈርጅ መንግስት እንዴት ለሴቶች መብት ቆሜያለሁ ሊለን ይችላል?

ምንም እንኳ ኢህአዴግ በተፈጥሮው ዶክመንተሪም ሆነ ሌላ ነገር አጋንኖ የሚያቀርብ ቢሆንም ቀሽ ገብሩ በዶክመንተሪው ላይ ስትናገር ከነበረው ለመረዳት የሚቻለው ወጣቷ ልክ ጥለውት እንደወጡት ሴቶች ትወጣ ካልሆነ ከኢህአዴግ ጋር አብራ መቆየት እንደማይቻል ነው፡፡ ደርግ ያችን ወጣት በርህራሄ ገድሏል፡፡ በርካቶችን አሰቃይቷቸዋል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ያንን ስቃይ በዶክመንተሪ እያሳየን የዘመኑን ቀሽዎች ማሰቃየቱን ተያይዞታል፡፡ ለዚህም ባል፣ አባት፣ ልጅና ሌሎች ወንዶች ዘመድ አዝማዳቸው ታስረውባቸው ከሚሰቃዩት በተጨማሪ በዚህ ስርዓት የተሰቃዩት ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርታ ህዝቧን ባገለገለች ወይዘሮ ሰልካለም ፋሲል ከባሏ ከታዋቂው ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ጋር እስር ቤት ታጉራ እዛው እስር ቤት ውስጥ እንድትወልድ ተደርጋለች፡፡

የሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም የጥንካሬ ምሳሌ የነበረችው ብርቱካን ሚዴቅሳ ኢህአዴግ በክፉ አይን ከሚያያቸው ሌሎች የወቅቱ ፖለቲከኞችም በላይ በእስር እንድትማቅቅ ተደርጋለች፡፡

በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ውስጥ የምትገኘው ርዕዮት አለሙ ግንቦት 20 1983 ዓ.ም ላይ ስልጣን የተቆናጠጠው ኢህአዴግ በሴቶች ላይ እየፈጸመው ለሚገኘው በደልና ግፍ ማሳያ ነው፡፡ ርዕዮት አለሙ ከእጮኛዋ ጨምሮ ከዘመድ አዝማድ እንዳትገናኝ ተከልክላለች፡፡ ጡቷ እየደማ ለብዙ ጊዜ ህክምና መከልከሏ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ትውልድም ከቀሽ ገብሩ የማይተናነሱ በርካታ ቆራጥ ሴቶች ለአገራቸው ዴሞክራሲ ራሳቸውን መስዋዕት እያደረጉ ነው፡፡ ደርግ ቀሽ ገብሩን አሰቃይቶ ገድሏታል፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከወጣ በኋላ በርካታ ከቀሽ ገብሩዎች የሚገባቸውን ቦታ ሳያገኙ ወንዶቹ ስልጣኑን ተቆጣጥረውታል፡፡ እነዚህ
የድሮዎቹ ቀሽ ገብሩዎች እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሴቶች አበሳቸውን እየበሉ ነው፡፡

በተቃራኒው ጦር ሜዳ ላይ ያልነበሩት በዝምድና፣ በውሽምነት፣ በሚስትነት…..የማይገባቸውን ጥቅም አግኝተው ከስርዓቱ ቁንጮ ወንዶች ጋር ሌሎች ሴቶችን በማስበደል ላይ ናቸው፡፡ አዜብ መስፍንን በምሳሌነት ባነሳ የምሳሳት አይመስለኝም፡፡ የወቅቱ ቀሽ ገብሩዎች ላይ የሚደርሰው ደግሞ ከሁሉም የባሰና መሪር ነው፡፡ በእነ ርዕዮት ላይ የሚፈጸመው አሁን በእነ በዞን ዘጠኝ ጦማሪ ሴቶችና በጋዜጠኞቹ ላይ ተከትሏል፣ ከ1960ዎቹ ትውልድ ቀጥሎ ትልቅ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን ያየንበት የሴቶች ቀን (march 8) በ ሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ አጋጣሚውን ተጠቅመው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በስርአቱ የመጀመርያ ተጠቂዎች ሴቶች እንደሆኑ ፣ነፃነትን እንደሚሹ ፣ ፍትህ የሰፈነባት ኢትየጵያን እንሻለን፣የአባቶቻችን ልጆች ነን፣የጣይቱ ልጆች ነን፣የአባ ጅፋር ልጆች ነን አታስደፍሩን በማለት የቀዘቀዘውን የሴቶች የትግል ተሳትፎ በአንድ እርምጃ ለመቀጠል ባደረጉት እንቅስቃሴ የመንግስት አፀፋ የጣይቱ ልጆች ነን፣ የሚኒልክ ልጆች ነን አሉ በሚል ክስ ለ 11 ቀናት አስሮ እንደፈታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ግን እነሱ የማን ልጆች እንደሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዩበት ትይንት ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚያሳየን ግንቦት 20 ለሴቶች ተጠቃሚነትን ሊያመጣ ቀርቶ ለአገራቸው ማበርከት የሚችሉትንም እንዳጠፋቸው የሚያስረዳ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለአለም ትኑር!!!

(ይህ ፅሁፍ የዛሬ ዓመት በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ ፅሁፍ ነው)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s