ግንቦት 20 የበላቸው ቀሽ ገብሩዎች (በወይንሸት ሞላ )

ኢህአዴግ ታግዬ አስገኘኋቸው ከሚላቸው መብቶች መካከል አንዱና ሁሌም የሚያወራለት የሴቶች መብት ነው፡፡ በተለያዩ ፎረሞች ያደራጃቸው አባላቱም ኢህአዴግ የሴቶች መብትን እንዳስከበረ ለማሳየት ተደራጅተው ዶሮ የሚያረቡትን፣ ድንጋይ የሚቀጠቅጡትን ሴቶች ‹‹ተጠቃሚነት›› በመጥቀስ የፓርቲያቸውን ስኬት ሲያወድሱ መዋላቸው የዕለት ተዕለት ተግባር ነው፡፡Wonishet Mola (Blue Party )

በእውነቱ በባህልም ሆነ ከእምነት ጋር በተያያዘ ሴቶችን እንደሚጨቁኑ የሚወቀሱት የአረብ መንግስታት እንኳ ስለ ሴቶች መብት መከበር በሚጥርበት ወቅት ሴቶች ድንጋይ ስለፈለጡና ሌሎች አድካሚ ስራዎችን ስለሰሩ የሴቶችን መብት አስከብሬያለሁ የሚለው ዝባዝንኬ ውሃ የሚቋጥር ሊሆን አይችልም፡፡ በ1960ዎቹ ትውልድ ሴቶች የማይናቅ ተስትፎ እንዳደረጉ እነ ማርታን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ደርግ የሚያፍነው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ቢሆንም የሴቶች መብት ተለይቶ የተነፈገበት ጊዜ አልታየም፡፡ ኢህአዴግ ግን ራሱን ከደርግ ጋር በማወዳደር የተሻለ መብት እንደሰጠ የሚገልጸም ምን እንደሆነ በግልጽ አጥጠቀስም፡፡

ሆኖም የሴቶችን መብት አስከብሬያለሁ ድስኩር በውቅሩ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጭቆና ለመሸፈም ካልሆነ በእውነታው የምናየው አይደለም፡፡ በህወሓትኢህአዴግ ትግል ውስጥ በርካታ ሴቶች መሳሪያ አንግተው ስርዓቱን አዲስ አበባ ድረስ አድርሰውታል፡፡ እንደ አረጋሽ ያሉት በፖለቲካ ልዩነት ስርዓቱን ጥለው ሲወጡ ሌሎቹ ደግሞ የረባ ቦታ ሳይሰጣቸው በሌለ መስክ ሲሰማሩ ስልጣኑ በወንዶች ቁጥጥር ስር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ህወሓት ጋር ታግለው ስልጣን ላይ ከወጡት ይልቅ ጦር ሜዳ ላይ እያለች የተሰዋችው ቀሽ ገብሩ በርካታ ሰዎች ያውቋታል፡፡

መቼም በህወሓት/ኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ከቀሽ ገብሩ ውጭ ሌላ ቆራጥ ታጋይ ጠፍቶ ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁን በህይወት ያሉትን ቀሽ ገብሩዎች ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ ቀሽ ገብሩም ብትሆን ስለሞተች እንጅ በህይወት ብትኖር ይህ ነው የሚባል ቦታ ልታገኝ እንደማትችል አሁን ኢህአዴህ ካለው ተሞክሮ ለመረዳት ቀላል ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛዎቹ ለግንቦት 20 ያደረሱትን ሴቶች እንኳ የሚገባቸውን ክብርና ስልጣን ያልሰጠው ገዥው ፓርቲ የሴቶችን መብት አስከብሬያለሁ ቢል ከተለመደው ፕሮፖጋንዳ ያለፈ አይሆንም፡፡

በተቃራኒ ጎራ የሚገኙት የፖለቲካ ቡድኖችና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሴቶችን ስናይ ደግሞ መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ጀምሮ መልካም መልካም የሚባሉትን የዴሞክራሲና የነጻ ገበያ መርሆች አገራችን ህዝብ እንዳይደርሱ ሲከለክል የአገራችንን ባህል የሚጎዳውን ግን በሩን ከፍቶለታል፡፡ በደርግና በኃይለስላሴ ወቅት ሲወገዙና ሲከለከሉ የነበሩ የባህል ወረርሽኞች ኢትዮጵያውያንን እንዲያደነዝዙ በሩ ተከፍቶላቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋው ሴተኛ አዳሪነትና ሌሎች የባህል ወረርሽኞች ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም በኋላ ኢትዮጵያን መዳረሻቸው ያደረጉ ናቸው፡፡

በፖለቲካው መስክ ያለውን ካየን ደግሞ ይበልጡን የባሰ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በርካታ የተቀናቃኝ (ታጣቂም ሆነ ሰላማዊ) የፖለቲካ ቡድኖችን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ‹‹ኦነግ›› ተብለው ታስረዋል፡፡ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የሌሎች ቡድኖች አባላት የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን እስር ቤት ውስጥ ታጉረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሴቶች የሚገኙበት ሲሆን ወንዶቹ ደግሞ ሴት ልጆች፣ ሚስቶችና እናቶችን የሚያስተዳድሩ፣ የሚረዱና የሚያግዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አብዛኛዎቹን ሴቶች የሚጎዱ አሉታዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ አልተቆጠበም፡፡

በኢኮኖሚው መስክ ሴቶች ተጠቃሚ ናቸው ቢባልም ወደ ውጭ የሚሰደዱት እነሱው መሆናቸው ፕሮፖጋንዳው እርባና ቢስ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ከ18 አመት በታች የሆኑትን ጨምሮ በርካታ ሴቶች ወደ አረብ፣ ደቡብ አፍሪካና ጎረቤት የአፍሪካ አገራት ይጎርፋሉ፡፡ እነዚህ አብዛኛዎቹ እህቶቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱት ግንቦት 20 አመጣው የሚባለው ልማት ለእነሱ ጠቃሚ ባለመሆኑ እንጅ አገራቸውን ጠልተው አይደለም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ለሴቶች መብት ቆሜያለሁ የሚለው ኢህአዴግ በውጭ አገር ችግር ሲደርስባቸው ‹‹ህገ ወጥ›› አድርጎ የሚፈርጃቸውና ተገቢውን እርዳታ የማያደርግላቸው መሆኑ ነው፡፡

ለዚህ በምሳሌ ልጠቅሰው የምችለው ከሳውዲ አረቢያ ተባረው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ መንግስት ‹‹ህገ ወጥ›› ተብለው መፈረጃቸውና ለእነሱም ድምጽ ለማሰማት ሳውዲ አረቢያ ኢምባሲ የወጡ ኢትዬጵያውያን በኢትዬጵያ መንግስት የፌደራል ዱላ የተበተነ ሲሆን ይህ እንደሀገር መደፈራችንን ያየንበት እንደመንግስ ለህዝብ ተቆርቋሪነት ሞራል የጎደለው መሪ እንዳለን የሚያሳየን ነው፡፡ ታዲያ ከሳውዲዎች ጎን ቆሞ ኢትዮጵያውያንን ህገ ወጥ ብሎ የሚፈርጅ መንግስት እንዴት ለሴቶች መብት ቆሜያለሁ ሊለን ይችላል?

ምንም እንኳ ኢህአዴግ በተፈጥሮው ዶክመንተሪም ሆነ ሌላ ነገር አጋንኖ የሚያቀርብ ቢሆንም ቀሽ ገብሩ በዶክመንተሪው ላይ ስትናገር ከነበረው ለመረዳት የሚቻለው ወጣቷ ልክ ጥለውት እንደወጡት ሴቶች ትወጣ ካልሆነ ከኢህአዴግ ጋር አብራ መቆየት እንደማይቻል ነው፡፡ ደርግ ያችን ወጣት በርህራሄ ገድሏል፡፡ በርካቶችን አሰቃይቷቸዋል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ያንን ስቃይ በዶክመንተሪ እያሳየን የዘመኑን ቀሽዎች ማሰቃየቱን ተያይዞታል፡፡ ለዚህም ባል፣ አባት፣ ልጅና ሌሎች ወንዶች ዘመድ አዝማዳቸው ታስረውባቸው ከሚሰቃዩት በተጨማሪ በዚህ ስርዓት የተሰቃዩት ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርታ ህዝቧን ባገለገለች ወይዘሮ ሰልካለም ፋሲል ከባሏ ከታዋቂው ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ጋር እስር ቤት ታጉራ እዛው እስር ቤት ውስጥ እንድትወልድ ተደርጋለች፡፡

የሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም የጥንካሬ ምሳሌ የነበረችው ብርቱካን ሚዴቅሳ ኢህአዴግ በክፉ አይን ከሚያያቸው ሌሎች የወቅቱ ፖለቲከኞችም በላይ በእስር እንድትማቅቅ ተደርጋለች፡፡

በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ውስጥ የምትገኘው ርዕዮት አለሙ ግንቦት 20 1983 ዓ.ም ላይ ስልጣን የተቆናጠጠው ኢህአዴግ በሴቶች ላይ እየፈጸመው ለሚገኘው በደልና ግፍ ማሳያ ነው፡፡ ርዕዮት አለሙ ከእጮኛዋ ጨምሮ ከዘመድ አዝማድ እንዳትገናኝ ተከልክላለች፡፡ ጡቷ እየደማ ለብዙ ጊዜ ህክምና መከልከሏ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ትውልድም ከቀሽ ገብሩ የማይተናነሱ በርካታ ቆራጥ ሴቶች ለአገራቸው ዴሞክራሲ ራሳቸውን መስዋዕት እያደረጉ ነው፡፡ ደርግ ቀሽ ገብሩን አሰቃይቶ ገድሏታል፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከወጣ በኋላ በርካታ ከቀሽ ገብሩዎች የሚገባቸውን ቦታ ሳያገኙ ወንዶቹ ስልጣኑን ተቆጣጥረውታል፡፡ እነዚህ
የድሮዎቹ ቀሽ ገብሩዎች እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሴቶች አበሳቸውን እየበሉ ነው፡፡

በተቃራኒው ጦር ሜዳ ላይ ያልነበሩት በዝምድና፣ በውሽምነት፣ በሚስትነት…..የማይገባቸውን ጥቅም አግኝተው ከስርዓቱ ቁንጮ ወንዶች ጋር ሌሎች ሴቶችን በማስበደል ላይ ናቸው፡፡ አዜብ መስፍንን በምሳሌነት ባነሳ የምሳሳት አይመስለኝም፡፡ የወቅቱ ቀሽ ገብሩዎች ላይ የሚደርሰው ደግሞ ከሁሉም የባሰና መሪር ነው፡፡ በእነ ርዕዮት ላይ የሚፈጸመው አሁን በእነ በዞን ዘጠኝ ጦማሪ ሴቶችና በጋዜጠኞቹ ላይ ተከትሏል፣ ከ1960ዎቹ ትውልድ ቀጥሎ ትልቅ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን ያየንበት የሴቶች ቀን (march 8) በ ሴቶች ታላቁ ሩጫ ላይ አጋጣሚውን ተጠቅመው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በስርአቱ የመጀመርያ ተጠቂዎች ሴቶች እንደሆኑ ፣ነፃነትን እንደሚሹ ፣ ፍትህ የሰፈነባት ኢትየጵያን እንሻለን፣የአባቶቻችን ልጆች ነን፣የጣይቱ ልጆች ነን፣የአባ ጅፋር ልጆች ነን አታስደፍሩን በማለት የቀዘቀዘውን የሴቶች የትግል ተሳትፎ በአንድ እርምጃ ለመቀጠል ባደረጉት እንቅስቃሴ የመንግስት አፀፋ የጣይቱ ልጆች ነን፣ የሚኒልክ ልጆች ነን አሉ በሚል ክስ ለ 11 ቀናት አስሮ እንደፈታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ግን እነሱ የማን ልጆች እንደሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዩበት ትይንት ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚያሳየን ግንቦት 20 ለሴቶች ተጠቃሚነትን ሊያመጣ ቀርቶ ለአገራቸው ማበርከት የሚችሉትንም እንዳጠፋቸው የሚያስረዳ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለአለም ትኑር!!!

(ይህ ፅሁፍ የዛሬ ዓመት በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ ፅሁፍ ነው)

Advertisements

ግንቦትና ግንቦታውያን

– ከጌታቸው ሽፈራው
ግንቦት በሞቃታማው በጋ እና በክረምቱ መካከል የሚገኝ የሙቀትና የወበቅ ወር ነው፡፡ ይህ ወር አየር ንብረቱ በቅጡ የማይታወቅ፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ የሚፈራረቅበት እንደመሆኑ ለሰዎች ጤና ተስማሚ አይደለም፡፡ ሙቀትና ቅዝቀዜው ድብልቅልቅ ባለበት በዚህ ወር አብዛኛው አርሶ አደር በበሽታ ይጠቃል፡፡ በዝናብ እጥረትና በረዥሙ በጋ ምክንያት ከብቶቻቸው ያልቃሉ፡፡ በአጠቃላይ ግንቦት ለአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የመከራና የስቃይ ወር ነው፡፡
mengistu hailemariam
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ወሩን መልካም ነገር ይዞ እንዲመጣ አምላካቸውን ይማጸናሉ፡፡ ለአብነት ያህል ክርስቲያኖችና የሌሎች እምነት ተከታዮችም የግንቦት ልደታ ዕለት (አብዛኛዎቹ ከእምነት ይልቅ አምልኮ አዊ ያደርጉታል) ንፍሮ አንፍረው፣ ቡና አፍልተው የግንቦት ወር ጦስ በጭስና በንፍሮ ውሃ ለመሸኘት ይጥራሉ፡፡ ሆኖም ግን ለኢትዮጵያውያን ግንቦት የመከራ ዘመን፣ የደም ወር ከመሆን አላለፈም፡፡ ከዚህ ወር ጦሶች መካከል ለአሁኑ ዘመን መከራ ምንጭ የሆኑትን ግንቦታዊ ክስተቶች ብቻ እጠቅሳለሁ፡፡

26 አመታትን ወደኋላ ስንመለስ ኢትዮጵያ ለአሁኑ ፖለቲካዊ፣ ጂኦ ፖለቲካዊና ሌሎች አሉታዊ ገጽታዎች የዳረጋትን ውጥንቅጥ እናገኛለን፡፡ ግንቦት 8/1981 ዓ.ም፡፡ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮችና አመራሮቻቸው በጦርነት የተማረሩበት ወቅት ነበር፡፡ ከጀኔራሎቹም በላይ በእነ መንግስቱ ኃይለማርያም ይሁንታን ያገኘ ካድሬ ስለ ወታደራዊ ስትራቴጅ ለመተንተን የሚቃጣበትና ጀኔራሎቹን ያማረረበት ወቅት እንደነበር በርካቶች እማኝነ ታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በገፈፋና በግድ ጦር ሜዳ ይቀላቀሉ የነበሩ ወታደሮች በቁርጠኝነት ይዋጋ የነበረውን ሰራዊት መንፈስ ቀይረውታል፡፡ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ ያሳሰባቸው የጦሩ መሪዎች ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ከስልጣን ካልተወገዱ ኢትዮጵያ የገባችበት ችግር ሊፈታ እንደማይችል አመኑ፡፡ ‹‹በጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም›› ላይ ይሞከራል ተብሎ የማይታሰበውን መፈንቅለ መንግስትም ወጠኑ፡፡ አዲስ አበባና አስመራም የመፈንቅለ መንግስት መሪዎቹ ማዕከል ሆኑ፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባው ማታ ላይ እንዲሁም አስመራው ደግሞ ከአንድ ቀን በኋላ ግንቦት 8/1981 ዓ.ም ከሸፈ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ሙከራውን ያደረጉት ጀኔራሎች ራሳቸውን ገደሉ፣ ተገደሉ፣ ታሰሩ፡፡ አስመራ ላይ ደግሞ ግንቦት 9 የ102ኛ አየር ወለድ ክ/ጦር በምስራቅና በሰሜን የገጠማትን ጦርነት ሲመሩ የኖሩትን ጀኔራሎች ዓይናቸ ውን ጎልጉሎ፤ በየጎዳናው እየጎተተ፣ አንገታቸውን ቆርጦ ብቻ ወታደር በመሪዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ጠላት በማረካቸው ላይ ሊያደርገው በማይታሰበው አረመኔያዊ ድርጊት አስመራን የደም አላባ አደረጋት፡፡ በመፈንቅለ መንግስት በአጠቃላይ ከ137 በላይ የጦሩ አመራሮች ታሰሩ፡፡ ከእነዚህ መካከልም 28 ጀኔራሎች፣ 20 በላይ ኮሎኔሎች፣ 20 በላይ ሻለቃዎች፣ 20 በላይ ሻምበሎች ይገኙበታል፡፡ ገንጣይ አስገንጣይ የሚባሉት ሳይቀሩ አንዳንዶቹ ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ቀኝ እጁን በግራ እጁ ቆረጠ!›› ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ የጦር መሃንዲሶቿን ገደለች፣ በላች›› ብለው ጽፈውታል፡፡ በዚህ ምክንያት 270 ሺህ ያህል ኤርትራ ውስጥ የነበረው ሰራዊት አመራር አልባ ሆነ፡፡

መፈንቅለ መንግስቱ በከሸፈ በሁለተኛው ቀን ግንቦት 10 በርካታ የኢትዮጵያ ሰራዊት አመራሮች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩና ከጦሩ ሲርቁ እንዲሁም ሰራዊቱም ሆነ አመራሩ ሞራሉ ሲላሽቅ ሻዕቢያና ህወሓት የኢትዮጵያን ሰራዊት ይዞት የነበረውን ሰፊ መሬት ማስለቀቅ ጀመሩ፡፡ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ሰራዊት እንደ ውጭ ወራሪ ያለ ርህራሄ የተጨፈጨፈበት ጊዜ ነው፡፡ ህወሓትና ሻዕቢያ የተማረከውን ሰራዊት ሳይቀር መሬት ላይ አስተኝተው በመድፍ ጨፍልቀውታል፡፡ ቁስለኛውን በጅምላ ሲፈልጉ ወደ ገደል፣ ሲፈልጉ ወደባህሩ አሊያም በጅምላ የጨፈጨፉበት ወቅትም ነው፡፡ ይህ ወር ኤርትራና ትግራይ በኢትዮጵያ ሰራዊት ደም የጨቀየበት ክፉ ቀን ነው፡፡
ይህ ግንቦት ያመጣው ጦስ የኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ በገንጣዮቹ እጅ እንዲወድቅ አደረገ፡፡ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ለኢትዮጵያ አንድነት ‹‹አንድ ጥይትና አንድ ሰው›› እስኪቀር እንደሚዋጉ ቃል ገብተው እንደነበር ይነገራል፡፡ በእርግጥ እርሳቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያን ጦርነት ውስጥ ዘፍቀው መሸሸት እንደሌለባቸው በአደባባይ ነግረዋቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል በመጨረሻው ሸንጎ አንድ የሀይማኖት መሪ መንግስቱ ኃይለማርያም አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱትን ሀገርና ህዝብ ጥለው መሄድ እንደሌለባቸው በግልጽ እንዲህ ብለዋቸው ነበር፡፡ ‹‹….50 ሚሊዮን ህዝብ በጦርነት ባህር ማግደው፣ ቆስቁሰው፣ በእርስዎ ኃላፊነት 18 ዓመት ሙሉ መርተው ሳያደራድሩ፣ ሳያረጋጉ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእሳት ዳርገው፣ በአሁኑ ሰዓት ከመሞት በስተቀር፣ የቴዎድሮስን ጽዋ ከመጠጣት በስተቀር፣ ሌላ እድል የለዎትም፡፡ እንደሌሎች መሪዎች ኢሮፕ ይፈረጥ ጣሉ ብዬ እምነት የለኝም፡፡ እግዚያብሄር ምስክሬ ነው፡፡ ይህን ህዝብ አጋልጠው ይሄዳሉ አልልም፡፡ መንጌ፤ ከሷ ወንበር ላይ እንደቋንጣ ደርቀው እንደሚቀሩ አምንብዎ ታለሁ፡፡ ይህንን ባያደርጉ ግን ታሪክ ይፋረድዎታል፡፡››
በዚያ የሀይማኖት መሪዎች ስለ እውነት ይናገሩ በነበረው ወቅት ከንግግራቸው ሁለት የግንቦት ጦሶችን በግልጽ እንረዳለን፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ፕሬዝደንት መንግስቱ የፈጠሩትን ቀውስ ‹‹….50 ሚሊዮን ህዝብ በጦርነት ባህር ማግደው፣ ቆስቁሰው፣ በእርስዎ ኃላፊነት 18 ዓመት ሙሉ መርተው ሳያደራድሩ፣ ሳያረጋጉ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእሳት ዳርገው፣›› ሲሉ ስለ ቀውሱ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ይህን ህዝብ አጋልጠው ይሄዳሉ አልልም፡፡›› ሲሉ ህወሓትና ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል ጠላት እንደሆኑ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
meles zenawi
ግንቦት 13/1983 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ ‹‹ጓድ ሊቀመንበር››ን አሞካሽቶ የማይጠግበው ሚዲያ ‹‹ጦርነቱ ያስከተለውን ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም፡፡ ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆም፣ ስምምነት እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጭ ሄደዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን በመውረድ ሀገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ም/ፕሬዘዳንት ሌፍትናንት ጀኔራል ተስፋዬ ወ/ኪዳን ተክተው ይሰራሉ፡፡›› ተባለ፡፡
‹‹ከመንግስቱ ኃይለማርያም አመራር ጋር ወደፊት!›› ይል የነበር ካድሬ ደግሞ ጆሮው ሊቀበለው የማይችለውን ነገር ሰማ፡፡ ለመንግስቱ ኃይለማርያም ቆሞ አመራሮቹን በጭካኔ ያረደው፣ በጭካኔ ዓይና ቸውን ያወጣውንና አስከሬናቸውን በአስመራ ጎዳና የጎተተው የ102ኛ ሰራዊት የመጨረሻው ተስፋውን ቆረጠ፡፡ ‹‹መንጌ!›› ሲል የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ እጣ ፈንታው ‹‹ገንጣይ አስገንጣይ›› ሲባሉና ኢትዮጵያን ሊገነጥሉ ሲታገሉ በኖሩት ሻዕቢያና ህወሓት ስር ሆነ፡፡ ሻዕቢያና ህወሓት በሚጠሏት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈነጩበት መንገድ ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ጦሰኛ ግንቦት ወር አደጋ ውስጥ ገባች፡፡ ይባስ ብሎ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን የተኩት ተስፋዬ ወልደኪዳን መንግስቱ ጥሎ ከወጣበት ከሁለት ቀን በኋላ የኢትዮጵያ ጦር መሳሪያውን ለ‹‹ወንበዴ›› አስረክቦ ወደ ፈለገበት ቦታ እንዲሄድ አዋጅ አስነገሩ፡፡ ለአንድነት ሲዋጋ የኖረው ሰራዊትም መሳሪያውን እየጣለ ወደየትውልድ ቦታውና ወደ ከተማው ሲያቀና ለህወሓትና ሻዕቢያ እንዲሁም በደርግ ለተማረረው አርሶ አደር ጥይት ሰለባ ሆነ፡፡ እንደ ምንም ብሎ ህይወቱን ያተረፈው ደግሞ በዚህ ደሙን ባፈሰሰላት አገር ጎዳና ላይ ወደቀ፡፡

ሰራዊቱ ትጥቁን እንዲፈታ በጊዜያዊ ፕሬዝደንቱ መጠየቁን ተከትሎ ሻዕቢያ በወቅቱ ሁለተኛዋ የኢትዮጵያ ከተማ የነበረችውን አስመራን ተቆጣጠረ፡፡ አረመኔዎቹ የሻዕቢያ ታጋዮች ኢትዮጵያውያንን እንደ ወራሪ ጠላት መዓት አወረዱባቸው፡፡ ህወሓት ኢህአዴግ ከአራት ቀን በኋላ ግንቦት 20 አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡ ደርግ መሸነፉን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ይህ ወር መልካም ነገር ይዞ ይመጣል ብለው ቢጠብቁም ያመጣው ግን ተቃራኒውን ሆነ፡

ግንቦት 20… ጥቁሩ ቀን

በግንቦት ወር የመጀመሪያ ቀናት ሻዕቢያና ህወሓት አሜ ሪካን ጨምሮ ከምዕራባውያን መንግስታት ጋር ሎንደን ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ከዚህ ውይይት ዋና ጭብጥ መካከል አንዱ ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል በሚል ከምዕራባዊያኑ በተለይም ከአሜሪካ የተነሳው ሀሳብ ነበር፡፡ ይሁንና መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደማያስፈልጋት ሽንጡን ገትሮ በመከራከር ምን አል ባትም ‹‹ለማስተዳደር›› በሚፈልጋት አገር ሉዓላዊነትን አሳልፎ የሰጠ የመጀመሪያው መሪ የሚያደርገውን ከሃዲነት ፈጸመ፡፡ ግንቦት 21 ቀን ኤርትራ በሻዕቢያ ስር መተዳ ደር ጀመረች፡፡ ያ የተደከመበት፣ በርካታ የሰው ነፍስ የጠፋበት ሉዓላዊነት ግብጽ ጀምራው እነ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ሌሎች የአረብ አገራት ትኩስ ስንቅ እየቋጠሩላቸውና የደርግም ስህተት ተጨምሮበት በአገር አንድነት ላይ በተ ነሱት ‹‹ወንበዴዎች›› የበላይነት ተጠናቀቀ፡፡ ሉዓላዊነቷ ተደፈረ፡፡

ህወሓትና ሻዕቢያ ስልጣን ከመያዛቸው በፊትም ጀምረው ተሻርከው እንጨት፣ ብረት፣ ቡና፣ ወርቅ፣ ብር፣ ሳይሉ ያገኙትን የኢትዮጵያን ሀብትና ንብረት መዘበሩ፡፡ ከደርግ ጋርም ሆነ ካለፉት ስርዓት ጋር ግን ኙነት አለው ያሉትን ህዝብ ላይ እስራት፣ ግድያና ሌሎች አሰቃቂ እርምጃዎችን ወሰዱ፡፡ እርግጥ ነው ይህ ተባብሮ ኢትዮጵያን የመመዝበር ተግባር በስምምነት አልዘለ ቀም፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ለማጋበስ በመ ነበራቸው አለመግባባት እርስ በእርስ መነካከስ ጀመሩ፡ ፡ በዚህ የሁለት ጅቦች ጠብ ምክንያትም ህወሓት የሚ ገዛት ኢትዮጵያ ግንቦት 4/1990 ዓ.ም በሻዕቢያ ተወረ ረች፡፡ በሁለቱ ግለሰቦች፣ ፓርቲዎች ኢኮኖሚያዊና ድሮ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል በርሃ በነበሩበት ወቅት በተፈ ጠረ ቁርሾ 70 ሺ ያህል ህዝብ በዚህ ወርሃ ግንቦት በተፈ ጠረ ግጭት ሰበብ ውድ ህይወቱን አጣ፡፡ በዚህ ግጭት ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ጥርሳቸው ሳይቀር እየ ተነቀለ ከአስመራ ተባረሩ፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግም ቢሆን ያ አብዛኛውን ተግባሩን ካስተማረው ሻዕቢያ በቀሰመው ተሞክሮ መሰረት ምላሹን ሰጠ፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ እርዳታ ለመ ለመን እከተለዋለሁ ካለው የይስሙላ ዴሞክራሲ ስም አፋኝነቱን ያሰፈነ ድርጅት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ የራሱንና የሻዕቢያ ጥቅም አስቀድሟል፡፡ ኢትዮጵ ያውያንን በዘውግ ከፋፍሎ መግዛትን እንደዋነኛ ስልት ወስዶታል፡፡ የይስሙላህ ዴሞክራሲና ምርጫ አሰፈንኩ ቢልም ከመግዢያነት ያለፈ ግን አልነበረም፡፡ ለዚህም ህወሓት/ኢህአዴግ ስቃይ እያደረሰበት የሚገኘውን ህዝብ ጥላ ለመሆን በህገ መንግስቱ መሰረት የተቋቋሙት ፓርቲዎችና ፖለቲከኞቻቸው የደረሰባቸውን መከራ ማንሳት በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በየክልሉ ኦነግና ህወሓት/ኢህአዴግ ሲጨፈጭፉት የነበረውን ኢትዮጵያ ዊና የኢትዮጵያ አንድነት ለመታደግ የተነሳው መዐሕድ የመጀመሪያው ተጠቂ ነበር፡፡ የዚህ ፓርቲ መስራችና
እውቁ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ደግሞ የዚህ የግንቦት ዘራሽ አምባገነን ስርዓት ዋነኛ ተጠቂ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ እስር ቤት ሲማቅቁ ቆይተው ግንቦት 1/1991 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የሚገርመው መንግስቱ ኃይለማርያም እና ውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች በከፈቱላ ቸው ቀዳዳ በግንቦት ነፋስ ወደ ስልጣን ብቅ ያሉትና የአሁኑ ስርዓት ‹‹መሃንዲስ›› መለስ ዜናዊም በዚሁ የደም ወር እውቁ ፕሮፌሰር ተሰቃይተው በሞቱበት ቀን የተወ ለዱ መሆናቸው ነው፡፡ ፕሮፈሰሩ ከሞቱ በኋላ የመዐሕድ አካል የነበሩም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በ1997 ተጠናክረው በአዲስ ምዕራፍ ለትግል የመጡበት ዘመን ነበር፡፡ በተለይ የግ ንቦት 1997 ምርጫ ኢትዮጵያውያን ካሉበት አምባገነ ናዊ አገዛዝ ነጻ እንዲሚያወጣ በኢትዮጵያውያኑ ብቻ ሳይሆን ህወሓት/ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ፣ ለቀጠናውና ለዓለምም እንደማይመጥንና እንደማይበጅ በተረዳው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ነጻ ለመውጣት በሙሉ ልብ ወደ ምርጫ ጣቢያ የጎረፉ ትም በዚህ ቀን ነው፡፡ የሚያዝያው ሰልፍና ሌሎች መነ ቃቂያዎች ግንቦት 7 ኢትዮጵያውያንን ነጻ የምታወጣ ቀን አስመስሏታል፡፡ እነዚያ ንፍሮ ቀቅለው፣ ቡና አፍል ተው ግንቦት ክፉውን ይዞ እንዳይመጣ ተስፋ ሳይቆረጡ ሲልምኑ የኖሩት ኢትዮጵያውያን አሁን አዲስ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ ተስፋው ከአንድ ቀን በላይ አልዘለለም እንጂ፡፡

ተቃዋሚ አጣን ሲሉ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ማታ ላይ ብቅ ብለው ይህን የግንቦት 7 ተስፋ አቧራ ነሰነሱበት፡፡ ማታ በኢቲቪ ብቅ ብለው አሁንም ድረስ ኢትዮጵያውያንን ለቀየደው የጸረ ሽብር፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሚዲያ…..ሌሎች ቀያጅ አዋጆች መሰረት የሆነውን ጊዜያዊ አዋጅ አወጁ፡፡ በነጋታው ግንቦት 8/1997 ህዝብ ከቤት ውጭ ምንም አይነት ስብሰባም ሆነ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ተከለከለ፡፡ በዚሁ ቀን ‹‹አብዮታዊ›› ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ምንም ባላሳወቀበት ግንቦት 8 ከአዲስ አበባ ውጭ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ማሻነፉን በተቆጣጠረው ሚዲያ አሳወቀ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሰላማዊ ትግልን የቀፈደዱ በርካታ እርምጃዎች በዚሁና በቀጣዩ ግንቦቶች ተወስደዋል፡፡ ግንቦት 2002 ዓ.ም ምርጫ ደግሞ አፋኝነቱን ያጠናከረው ኢህአዴግ አስፈራርቶም፣ አጭበርብሮም 99.6 በመቶ አሸንፎ ‹‹አውራ ነኝ›› ያለበትን ኢትዮጵያውያንን በገዥነት እንደሚቀጥል ያቀደበት ወቅት ሆነ፡፡ ባለፉት 5 አመታት ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲካውን ያነቃቃሉ ብሎ የፈራቸውን ብሎገሮች አስሮ፣ ህዝቡን 1ለ5 ጠርንፎ፣ እና አጭበርብሮ የዘንድሮውን ምርጫ 100 በ100 እንዳሸነፈ እየተነገረ ነው፡፡ በእርግጥ በተለይ ከ1997 በኋላ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ኢህአዴግ የሚወዳደሩት ሳይሆን የሚታገሉት እንደሆነ በማመናቸው ምርጫውን 90፣99.6፣ 100 አሸነፍኩ ቢል የሚገርማቸው አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ግን ግንቦት ለኢትዮጵያውያን የመከራ ወር እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

በአጠቃላይ ግንቦት 20 ህወሓት/ኢህአዴግ ሳይገባው፣ ለኢትዮጵያውያን ሳያስብና ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ኢት ዮጵያን የተቆጣጠረበት፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ፕ/ር መስፍን እንደሚሉት ‹‹ህገ አራዊት›› መተግበር የጀመረበት፣ ዓለም አንድ በሆነችበት ወቅት መገንጠልን በወርቃማ መብትነት ያጸደቀበት፣ ኢትዮጵያውያን አገራ ቸው ውስጥ እንዳይዘዋወሩ የማንነት ግንብ የገነባበት ጥቁር ቀን ነው፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያዊ አላማ ያፈነገጠ መሆኑ፣ ኢትዮጵያው ያንን በስስ ማንነት መከፋፈሉ፣ ለራሱ ቡድናዊ ጥቅም መሯሯጡ ህወሓት/ ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትን ቀን ለኢትዮጵያውያን ጨለማ፣ አዲስ የጭቆና ዘመን ነው፡፡ ይህን ቀን ምናልባትም የጀርመኑ ሂትለር ለቤልጀም ሳይሆን ለራሱ የስልጣንና ልሂቃን ጥቅም፣ በበላይነት ተወጥሮ ቤልጀምን ከወረረበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግንቦት 1940 ተመሳሳይ ወቅት (ግንቦት 20) ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡ እንዲያውም ናዚዎቹ የጀርመንን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ቤልጀምን ሰጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት ግልጽ አላማ ይዘው ነው የገቡት፡፡ ህወሓት ግን እስካሁንም ድረስ፣ ለባለፉት 23 አመታት የሚጠላትን አገር የገንጣይ ስምና አላማውን እንዳነገበ እየገዛት ይገኛል፡፡ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያውያን ንፍሮ አንፍረው፣ ቡና አፍልተው ‹መከረኛውን› አምላካ ቸውን መለመናቸው ቀጥለዋል፡፡ ግንቦት የሰጠው ‹‹አብ ዮታዊ›› ፓርቲ ግን በከፍፍለህ ግዛ፣ በስራትና ግርፋት፣ በኑሮ ውድነት፣ በመሰረታዊ አገልግሎት እጥረት፣ በሙስና ኢትዮጵያን የመከራ ምድር አድርጓታል፡፡ ግንቦት ደግሞ በአየር ንብረት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ውም ውጥንቅጡ የወጣ ክፉ ወር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህም ነው ግንቦት አሁንም የህወሓት/ኢህአዴግ እንጂ የኢት ዮጵያውያን ወር አይደለም ለማለት የሚያስደፍረው፡፡

(ይህ ጽሁፍ ከመጠነኛ ማስተካከያ ውጭ ግንቦት 15/2006 ዓ.ም ነገረ ኢትዮጵያ ላይ የወጣ ነው)

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41779#sthash.9BNwT974.dpuf

የዛሬ 24 ዓመት ኢህአዴግ አዲስ አበባን ባይቆጣጠር ኖሮ ዛሬ የኢትዮያ እድገት ከብራዚል ጋር ይስተካከል ነበር

(የጉዳያችን ማስታወሻ)

ደርግ 17 ዓመታት ሙሉ በህወሓት እና ሻብያ የተከፈተውን ጦርነት ሲዋጋ እንደነበር እና ጦርነቱ በቀን ብቻ በሚልዮን የሚቆጠር ብር ያስወጣ ነበር።በመቶሺዎች የሚቆጠር ሰራዊት መግቦ፣ታንክ እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ነዳጅ
እና ግዥ ፈፅሞ ማደር በራሱ ከፍተኛ ወጪ ነበር።ይህ ገንዘብ እንዳሁኑ የእርዳታ እና የብድር ገንዘብ ሳይሆን ህዝቡ ለእናት ሀገር እያለ ከሚያዋጣው እንደነበር ይታወቃል።በእርግጥ የሩስያ እርዳታ እና ብድር እንዳለ ሆኖ።
addis-ababa-realethiopia-141
በአንድ ወቅት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርይም የሰሜኑ ጦርነት ባይኖር በጥቂት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በባቡር ማገናኘት በተቻለ ነበር።ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል።በተለይ ህወሓት በዋነኛነት ድልድዮች እና መንገዶችን ማፍረስ ስራዬ ብሎ ይዞ ስለነበር እነርሱን ተከታትሎ መጠገን ሌላው ሥራ ነበር።የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት (መኮድ) የተሰኘው ድርጅት አንዱ ስራው ህወሓት ያፈረሰውን
ድልድይ እና መንገድ መልሶ መጠገን ነበር።

በደርግ የመጨረሻ አመታት ታድያ ኮ/ል መንግስቱ የመንግስታቸውን ቅርፅ ለመቀየር ወስነው ነበር።ቅይጥ ኢኮኖሚ ታወጀ።ሚኒስትሮች በአዲስ መልክ ተሾሙ።ብዙዎቹ በምዕራብ ዓለም የተማሩ ነበሩ።ኢኮኖሚውም ሆነ ፖለቲካው ለቀቅ ያለ መስሎ ነበር።በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ዕድል እንዳላቸው ምህረት እንደሚደረገም ተወራ።ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያምን ጨምሮ ሌሎች ምሁራን ከአመታት በኃላ እንደገና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን የማናገር፣በሀገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ የመነጋገር ዕድል አገኙ።

በወቅቱ በተያዘው መልክ የሀገሪቱ ሰላም ቢረጋጋ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሃትን የጎሳ ፖለቲካ እና የሻብያ ኤርትራን የመገንጠል አጀንዳ እንደመጥላቱ በነበረው ሕብረት ቢቀጥል ኖሮ፣በውጭ ይኖር የነበረው ሕብረተሰብ ወደሀገር ቤት ገብቶ የመስራት፣በሀገር ውስጥ ያለው ካለ ምንም የጎሳ ክፍፍል የመስራት እና ትላልቅ ኩባንያዎችን የመመስረት እድሉ ሰፊ ነበር። ዛሬ ኤፈርት እና ጥቂት ባለ ሀብቶች የሃገሩትን ሀብት ሁሉ እንዲህ ጠቅልለው ሚልዮን ኢትዮጵያውያን በድህነት ውስጥ አይዳክሩም ነበር።

አሁንም በተጀመሩ የሽግግር ሂደት ደርግ ስልጣኑን ቢለቅ እና የሽግግር መንግስት ተመስርቶ ቀጥሎም ወደ እውነተኛ ምርጫ ኢትዮጵያ ሄዳ የእራሷ የሆነ መንግስት ቢኖራት ኖሮ ዛሬ ከ 24 ዓመታት በኃላ ኢትዮጵያ ካለምንም ጥርጥር ብራዚል ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ የመድረስ ዕድል ነበራት።እዚህ ላይ ብራዚል ቀደም ብላ በውጭ ኃይሎች የመገዛቷ እና በርካታ የባህል ተቃርኖ ቢኖርም እኛ ካለን የባህል ሀብት ጋር በምጣኔ ሀብት ደረጃ እና በፈጠራ እንዲሁም በአዲስ ቴክኖሎጂ ክህሎት ሁሉ በእጅጉ የምንራመድበት የመነቃቃት አመታት ነበሩ።በእነኝህ 24 አመታት ውስጥ ከተባለው ደረጃ ለመድረስ እንችል እንደነበር እንደማሳያ የምረዳኝን ኢትዮጵያ ሊኖሯት እና ላይኖሯት የሚችሉት ነገሮች ሁለት ክፍል ከፍዬ ለማሳየት እና እነኝህ ጉዳዮች ማለትም ኢትዮጵያ ሊኖሯት የሚችሉት ነገሮች ምን ያህል ወደፊት እንደሚያራምዱን እና ላይኖሩ የሚችሉት ደግሞ ምን ያህል ወደኃላ እንደወሰዱን ለመመልከት ይረዳናል።እነኝህን ነጥቦች ለመንደርደርያ አነሳሁ እንጂ ጠለቅ ያለ ጥናት ቢደረግ ብዙ ጉዳዮችን ሊያሳየን እንደሚችል መረዳት ይቻላል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ሊኖሯት የሚችሉት
eth Bank
1/ የባንክ ኢንዱስትሪያችን ቢያንስ በ 5 የአፍሪካ ሁለት የመካከለኛው ምስራቅ እና አንድ አውሮፓ እንዲሁም 3 በአሜሪካ ቅርንጫፍ ከፍተው ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም በሆኑ ነበር፣

2/ እነ ጣና በለስ የመስኖ ልማት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሞደል የተባለ ምርቶቹ ከኢትዮጵያ አልፈው ለመላው ዓለም የሚልክ በአውሮፓ የስቶክ ኤክስቸንጅ ገበያ የሚገባ ኩባንያ ይሆን ነበር፣

3/ ኢትዮጵያ ከሻብያ ጋር በኤርትራ ጉዳይ ባትግባባ ቢያንስ በአሰብ ጉዳይ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራድራ ወደቧን ታስከብር ነበር።በሌላ በኩል እንደ ህወሓት በመሃል ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኤርትራውያንን ከሀገር ስለማታስወጣ በሂደት እነኝሁ ትውልደ ኤርትራውያን የኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መኖር ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ በሆኑ ነበር።እዚህ ላይ በደርግ ዘመን ከፍተኛ ተደማጭ የነበሩ የኤርትራ ቆላው ተወካዮች የነበራቸውን ተሰሚነት ማሰብ ይገባል።እነኝህ ሁሉ በህወሓት ስሳደዱ እና ሲገፉ 24 ዓመታት ተቆጠሩ።

4/ ኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሏ ጠንካራ ስለነበር በደቡብ ሱዳን ጉዳይም ሆነ የሱማልያ አልሸባብ ፈፅሞ ስጋት ሊሆኑ አይችሉም ይልቁንም በአካባቢው ሃያል ሀገርነቷ እስከ ግብፅ እና መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ይናኝ ነበር።የአይኤስ ኤስ ጥቃት መፈፀሙ በተሰማ በ24 ሰዓታት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከደብረ ዘይት ተነስተው የሱዳንን የአየር ክልል ጥሰው በርካታ የአሸባሪው ይዞታዎችን ሊብያ ውስጥ ያጠቁ ነበር።በእዚህም ሌሎች ተቀናቃኝ ሀገሮችን ሊያስደምም ይችል ነበር።

5/ በጦርነት ውስጥ የነበረ ኢኮኖሚ ያንን ያህል የስራ ዕድል ለወጣቱ መፍጠር ከቻለ ከጦርነት በኃላ ላለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ከ አስር ያላነሱ ከባድ የብረት ኢንዱስትሪዎች፣የነዳጅ ማውጣት ሥራ (ሱዳን ባቅሟ ነዳጅ ስታወጣ ኢትዮጵያ በሙስና ያልባለገ መንግስት ቢኖራት ኖሮ እስካሁን የነዳጅ ምርት በጀመረን ነበር)፣

6/ በኢትዮጵያ ተጀምረው የነበሩት የመካናይዝድ እርሻ ልማቶች በሰፊ ይስፋፉ ነበር።ኢትዮጵያ ጤፍ በብዛት በማምረት ለዓለም ብቸኛ አምራች እና ላኪ ሀገር ትሆን ነበር።

7/ የበርካታ ሃገራት ትላልቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ይጎርፉ ነበር።በተለይ ደርግ የወደቀበት ወቅት የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ገና ከሩስያ ተፅኖ እየወጡ፣በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም እየተነቃቁ ስለነበር ከወቅቱ ጋር የሚሄድ የድርጊት መርሃ ግብር እና ከሙስና በተቻለ መጠን የፀዳ መንግስት ስለሚኖር ኩባንያዎቹ ከማንም የአፍሪካ ሃገራት ኢትዮጵያን እንደሚመርጡ ሳይታለም የተፈታ ነበር።ይህም ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከብራዚል እኩል የምትጠራ ሀገር ትሆን ነበር።

8/ ናዝሬት የተጀመረው የትራክተር መገጣጠምያ ፋብሪካ ምርቱን አሻሽሎ በሌሎች ቦታዎች ማምረት እና የኢትዮጵያን ገበሬ በከፊልም ቢሆን ከበሬ አስተራረስ ዘዴ እንወጣ ነበር።

9/ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ማሳደጊያ እና መንከባከቢያ ማዕከል ”ሕፃናት አምባ” በሁሉም ክፍለ ሀገሮች ተመስርቶ እናት አባት የሞቱባቸውን በተለይ ባለፉት 24 ዓመታት ቁጥራቸው በመቶ ሺዎች የሆኑትን ሕፃናት ወደ ማዕከሉ አስገብቶ ኃላፊነት የሚሰማቸው ትውልድ ማፍራት ይቻል ነበር።የማዕከሉም አስተዳደር በባለሥልጣን ደረጃ ተዋቅሮ ኢትዮጵያውያን በወር ከደሞዛቸው እያዋጡ በርካታ እናት አባት ያጡ ሕፃናትን ሕይወት መታደግ ይቻል ነበር።ኢህአዴግ ማዕከሉ የነበሩ ሕፃናትን የደርግ ልጆች ብሎ በምሽት እንዳባረራቸው እና ማዕከሉን አንዴ የካድሬ ማሰልጠኛ ሌላ ጊዜ የግብርና ማሰልጠኛ እያደረገው መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ላይኖሯት (ላይሆንባት) የሚችሉት

1/ ሀገሪቱ በጫት እንዲህ አትበከልም ነበር።ወጣቶቿ በስፖርት እና በልዩ ልዩ ሙያ ላይ እንጂ የጫት ተገዢ አይሆኑም ነበር፣

2/ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለግዳጅ ሥራ አይጋዙም ነበር፣

3/ የጣና በለስ ፕሮጀክት አይፈርስም ነበር፣

4/ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ሀገር አትሆንም ነበር፣

5/ ኢትዮጵያ በጎሳ የተደራጀ ፓርቲ አይኖራትም ነበር።ሀገሩም በጎሳ የተከፋፈለ አስተዳደር አይኖራትም ነበር።
6/ ኢትዮጵያውያን ጎሳቸው ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ በፈለጉት ቦታ ሄደው የመስራት መብት ይኖራቸው ነበር፣

7/ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ክብራችን ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ አይደረገም ነበር። አንድ ችግር ሲገጥመን ወደ ኤምባሲያችን ሄደን ችግራችንን እንፈታ ነበር፣

8/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለሁለት የተከፈሉ አባቶች አስተዳደር አይኖራትም ነበር፣

9/ ከ11 ቢልዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ከሀገር በሕገ ወጥ መንገድ አይወጣም ነበር፣

10/ የብሔራዊ ባንክ በቀትር ፀሐይ ወርቁን ለሌቦች አስረክቦ አርተፍሻል ወርቅ አይቀበልም ነበር፣

11/ የተማረ የሚከበርባት እና ሥራ የምያገኝባት እንጂ ኮብል ስቶን ተራቢ እንዲሆን አይደረገም ነበር፣

12/ የሕፃናት አምባ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ሕፃናት በምሽት በኢህአዴግ ወታደር አያባረሩም እና ሴቶች ለሴተኛ አዳሪነት ወንዶቹ ለጎዳና ተዳዳሪነት አይዳረጉም ነበር።
national bank of ethiopia
13/ ኢትዮጵያ ሕፃናቶቿን በጉዲ ፈቻነት በመሸጥ በአፍሪካ ቀዳሚ አትሆንም ነበር።

ባጠቃለይ ኢትዮጵያ በህወሓት አገዛዝ ስር እሩብ ክ/ዘመን (25 ዓመታት) ሊሞላት አንድ ዓመት ብቻ ቀራት።ሃያ አምስት አመታት በርካታ ሃገራት ወደ መካከለኛ ገብ ደረጃ የደረሱበት ነው።የዛሬ 24 ዓመት አንጎላ ጦርነት ላይ ነበረች።ዛሬ አንጎላ በከፍተኛ እድገት ላይ የምትገኝ ሀገር ነች። የዛሬ 24 ዓመት ቦትስዋና ብዙም የምትደነቅ ሀገር አልነበረችም ዛሬ ቦትስዋና የአልማዝ አምራች ሀገር ነች።የዛሬ 24 ዓመት ጋና ስሟ እምብዛም አይነሳም። ዛሬ ጋና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መንግስት የምትቀይር እና የነዳጅ ሀብት ባለቤት የሆነች ሀገር ነች።ሃያ አራት ዓመት እንደ ኢትዮጵያ ላለ ጠንካራ ሰራተኛ ሕዝብ፣በብዙ ውጣ ውረድ ላለፈ ሕዝብ እና በርካታ እድሎች ከፊቱ ላሉት ሕዝብ ዛሬ ብራዚል ለደረሰችበት ደረጃ የመድረስ አቅም ነበረው።ነገር ግን በጎሰኛ መንግስት ተጠልፎ የጥቂቶችን የተንደላቀቀ ሕይወት እየተመለከተ እንዲኖር ተፈርዶበታል።አሁንም ከነገ ዛሬ ይቀድማል እና ለኢትዮጵያ ነፃነት አንድነታችንን እናጠናክር።ከጎሰኞች ማዶ ለምትመሰረተው የሁላችንም ኢትዮጵያ የበኩላችንን እናድርግ።

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ግንቦት 20/2005 ዓም (ሜይ 28/2015)

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41799#sthash.ryD3xo6F.dpuf

ምርጫ ቦርድ የአስቂኙን ምርጫ ውጤት ይፋ አደረገ * ኢሕአዴግ 100% አሸነፈ አለ * ምንም አይነት ተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ወንበር አላገኘም

(ዘ-ሐበሻ) ኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶቹ የዘንድሮውን አሳፋሪ ምርጫ 100% ማሸነፋቸውን ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ገለጸ:: ምንም አይነት ተቃዋሚ ፓርቲ በፓርላማው ውስጥ መቀመጫ እንዳላገኘም ተገልጹዋል::
election board
የገዢው ፓርቲ መሳሪያና ገለልተኛ ያልሆነው ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ኢህአዴግ አዲስ አበባ ላይ ከ23 መቀመጫዎች ኢህአዴግ 23ቱንም መቀመጫዎች አግኝቷል።
– ከትግራይ ክልል ቦርዱ ከደረሱት የ31 መቀመጫዎች ውጤት ህውሃት/ኢህአዴግ 31 መቀመጫዎችን
– ከአማራ ክልል ከደረሱት የ107 መቀመጫዎች ውጤት ብአዴን/ኢህአዴግ 107 መቀመጫዎች
ከኦሮሚያ ክልል ቦርዱ ከደረሱት የ150 መቀመጫዎች ውጤት ኦህዴድ/ኢህአዴግ 150 መቀመጫዎችን
– በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ቦርዱ ከደረሱት የ16 መቀመጫዎች ውጤት ኢሶዴፓ 16 መቀመጫዎችን
– ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከደረሱት የሰባት መቀመጫዎች ውጤት ሰባቱንም ቤጉዴፓ;
– ከደቡብ ክልል ከደረሱት የ95 መቀመጫዎች ውጤት ዴኢህዴን/ኢህአዴግ 95 መቀመጫዎች፣
– በጋምቤላ ክልል ጋህዴፓ ከሶስት መቀመጫዎች ሶስቱንም፣ በሀረሪ ክልል ሀብሊ ከ2 መቀመጫዎች አንዱን ሲያገኝ አንዱን ኦህዴድ/ኢህአዴግ፣
– በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሁለቱ መቀመጫዎች አንዱን ኦህዴድ/ኢህአዴግ ቀሪውን ሶህዴፓ አግኝተዋል
– ከአፋር ክልል ከደረሰው ከደረሰው የስድስት መቀመጫዎች ውጤት አብዴፓ ስድስቱንም መቀመጫ አግኝቷል።

በአሳፋሪነቱ የሚጠቀሰው የዘንድሮውን ምርጫ የአውሮፓ ሕብረት; የአሜሪካ መንግስትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፍትሃዊ ያልሆነ ምርጫ ሲሉ አውግዘውታ:: ተቃዋሚዎችም የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል::

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41775#sthash.MJsCLsKz.dpuf

ውዝግብን ያስተናገደው የዛሬው የጦማሪያኑ እና የጋዜጠኞቹ የፍርድ ቤት ዝርዝር ዘገባ (ኤልያስ ገብሩ)

በትናንቱ የቪኦኤ ዘገባ ላይ አቃቤ ሕግ ቅሬታ አቀረበ
ጦማሪ አቤል ዋበላ ችሎት በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ
‹‹ሥነ-ሥርዓት ያዝ!›› ዳኞች
‹‹እናንተ ራሳችሁ ሥነ-ሥርዓት ያዙ! ይህ ችሎት ነው፡፡ ግልጽ ነው›› አቤል ዋበላ
‹‹ውሳኔው ለሁሉም ከሆነ፣ ለአቃቤ ህጉም ሆነ ለአለቃው ጠ/ሚኒስቴርም መሆን አለበት፡፡››
‹‹ጓደኛዬ (አቤል) የሚቀጣ ከሆነ ውሳኔው እኔም ላይ ይታዘዝ››
ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀElias Gibru

ትናንት ምሽት ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ (VoA)ን ሳዳምጥ ነበር፡፡ ከዘገባዎቹ መካከል ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ ስለሚገኙት ስድስቱ የዞን 9 ጦማሪያንና ሶስት ጋዜጠኞች በትናንትናው ዕለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የነበራቸውን የፍርድ ቤት ውሎ ይገኝበታል፡፡ ዘጋቢው ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ ጠበቃ አምሃ መኮንን በስልክ በማነጋገር የፍርድ ቤት ውሎውን አስደምጦን ለዛሬ በአዳሪ የተቀጠረ ጉዳይ መኖሩን ስሳማ ጠዋት ወደችሎት ላመራ ወሰንኩ፡፡ በችሎቱ ዛሬ በጥዋት ልደታ ፍርድ ቤት ደረስኩ፡፡ በችሎቱ በር አቅራቢያ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ፣ የአማሪካ ኤምባሲው ባልደረባ በላይ ለገሠና ሌሎች ጥቂት የውጭ ሀገር ዘጋቢዎች እና ዲፕሎማቶች ነበሩ፡፡ ከርቀት አብዲ ለሜሳንና ጓደኞቹን ሰላም አልኳቸው፡፡ ከነበላይ ጋር ስለሰሞኑ ምርጫ አወጋን፡፡ ትንሽ ቆይቶ የቪኦኤው ዘጋቢ መለስካሰካቸው አምሃም መጣ፡፡ ስለትናንቱ የዜና ዘገባው፣ ስለምርጫው ሁኔታ … ጥቂት አወጋን፡፡

ከ3፡50 ገደማ ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ ወደ ችሎቱ በፖሊሶች ታጅበው መጡ፡፡ [ጋዜጠኛ ተስፋለም ወደፍርድ ቤት ይዟቸው በመጣው የእስረኛ መኪና ውስጥ ሆኖ እጁን ለሰላምታ ሲያውለበልብ እኔና እና በላይ አይተነው ነበር፤ ላለፉት ዓመታት ከተስፍሽ ጋር ለፍርድ ቤት ዘገባ ነበር ልደታ የምንገኛኘው፡፡ አንዳንዴም አብረን ከቤት የምንወጣበት ጊዜም ነበር፡፡ ዛሬ እሱ ታሳሪ እኔ ደግሞ ዘጋቢ ሆኜ የሚመጣውን እያየን እንገናናለን፤ ይሄ ሀሳብ አዕምሮዬ ተመላለሰ – ውስጤ እንዳዘነ!] ሰላምታ ሰጥተናቸው ገቡ፡፡ እኛም እየተፈተሽን ወደችሎቱ ዘለቅን፡፡ ሁሉም ቦታ ቦታውን ያዘ፡፡ አቀማመጣቸውም ከፊት አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ ናትናኤል ፈለቀና ማህሌት ፋንታሁን ሲሆኑ፣ በመጨረሻው የእስረኞች ወንበር ላይ ደግሞ አቤል ዋበላ፣ ዘላለም ክብረት፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔና ተስፋለም ወልደየስ ተቀምጠው ነበር፡፡ ከረፋዱ 4፡10 ሰዓት ላይ የችሎቱ ዳኞች ተሰየሙና ‹‹እነሶሊያና ሽመልስ …›› በሚል የዕለቱ ችሎት ስራውን ጀመረ፡፡

የችሎቱ የቀኝ ዳኛ ጉዳዩ ለዛሬ ያደረበትን ጉዳይ ከገለጹ በኋላ ውሳኔ ማንበብ ጀመሩ፡፡ አቃቤ ሕግ ተጨማሪ ምስክሮች እንዲሰሙለት የጠየቀው ነገር ‹‹የደረጃ ምስክሮቹ በሥራ ምክንያት ስላላገኘናቸው›› ሲል ያቀረበው ሀሳብ ‹‹ሥለስራቸው በግልጽ አልተገነገረም››ና ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግን ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቶ ውድቅ ማድረጉን ገለጸ፡፡

‹‹የሚቀሩ ሲዲዎች አሉኝ›› በማለት አቃቤ ህግ በድጋሚ ያቀረበውን ጥያቄም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ አቃቤ ሕግ አቀርበዋለሁ የሚለው ሲዲ እንዲቀርብ ሲል ውሳኔ ሰጠ፡፡ ፍርድ ቤቱ ሲዲውን ከሰዓት በኋላ ማቅረብ ይችል እንደሆነም አቃቤ ህጉን ብርሃኑ ወንድማገኝን ጠይቆት ነበር፡፡ [ከቦታው ርቀት ከድምጹ ማነስ አኳያ የአቃቤ ህጉን መልስ ማድመጥ አልቻልኩም] ፍርድ ቤቱም ‹‹ሲዲው በጽ/ቤት በኩል ይግባና ዳኞች ካየነው በኋላ ‹ሲዲው በግልጽ ቢታይ ችግር አለው ወይስ የለውም? ቀሪ ተከሳሾችን ይጎዳል አይስ አይጎዳም?› የሚለውን አይቶ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 09 ቀን ቀጠሮ እንያዝ›› ብሎ ነበር፡፡

አቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝም ቅሬታ አለኝ በማለት ለችሎት ተናግረዋል፡፡ ሀሳብን በሚዲያ በመግለጽ በኩል ችግር መኖሩን ጠቁመው፤ ‹‹በትናንትናው ዕለት በቪኦኤ በቀረበው የፍርድ ቤት ዘገባ ላይ በጠበቃ አምሃ በኩል የቀረበው አስተያየት ሚዛናዊ ያልሆነና አንድ አካል ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው፡፡ የዘገባው አቀራረብ ትክክል አይደለም፡፡ በአንድ ወገን የቀረበ ነው፡፡ እንዲህ መዘገብ የለበትም፡፡ በአግባቡ ይዘገብ፡፡ በፍርድ ቤት ዘገባ ላይ ላይም ሥርዓት ይደረግ›› የሚል ይዘት ያለው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ጠበቃ አምሃም ‹‹አቃቤ ሕጉ በዚህ መድረክ ላይ አንድ ተከራካሪ ናቸው፡፡ ሥርዓት የማስያዝ መብት የላቸውም፡፡ ዘገባው ችግር አለበት ካሉ ‹‹በምን ቀን የትኛው ጉዳይ ስህተት እንደሆነ በግልጽ ለፍርድ ቤቱ አቅርበው ይታረምልኝ ማለት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የችሎቱን ሥራ እንደሚመራ መሆን አይገባም፡፡ ትክክል አይደለም፡፡ እዚህ ችሎት ውስጥ ብዙ ጋዜጠኞች እና ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ጉዳዩ በተለያየ መንገድ ይዘገባል፡፡ የችሎት ጉዳይ እንዴት እንደሚዘገብ እናውቃለን፡፡›› በማለት መልስ ሰጡ፡፡ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ እጁን አውጥቶ ‹‹መናገር የምፈልገው ነገር አለ›› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹ስለጉዳዩ ጠበቃው ተናግረዋል፡፡›› ሲሉ የመሃል ዳኛው ተናገሩት – እንዲተው፡፡ የመሃል ዳኛው ‹‹ዘገባው በፍርድ ቤት ውሎ ላይ የመደምደሚያ ነገር ቀርቧል›› ሲል አቃቤ ሕግ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ጠበቃውም ምላሽ ሠጥተዋል፡፡ ተወያይተን ብይን እንሰጥበታለን›› አሉ በድጋሚ፡፡

እኒሁ ዳኛ ወደናትናኤል እያዩ ‹‹3ኛ ተከሳሽ ያለኸው ችሎት ውስጥ ነው፡፡ ወደኋላ ዞረህ አታውራ፡፡ ቁጭ በል፡፡ ችሎቱን የሚመራው ፍርድ ቤት ነው፡፡ ተው ተው ስትባል ተው!›› አሉትና ‹‹በአጠቃላይ ዘገባን በተመለከተ ከዚህ በፊት አስጠንቅቀናል፡፡ ፍርድ ቤት በማስረጃ ተረጋግጧል /አልተረጋገጠም፤ ተመስክሯል/አልተመሰከረም/ ነጻ ነው /አይደለም ይላል፡፡ ይሄን የሚለው ሌላ አካል አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ነው መዘገብ ያለበት፡፡ ተመስክሯል አልተመሰከረም የሚለው አይሰራም፡፡ አቃቤ ህግ በዝርዝር ያቀረበው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን፣ በዚህ መንገድ ካልተዘገበ ለወደፊቱ ይስተካከል›› የሚል ብይን ሰጡ፡፡

ጦማሪ ናትናኤል እና ጋዜጠኛ አስማማው ወ/ጊዮርጊስ ‹‹የምንናገረው ነገር አለ›› ብለው እጃቸውን አወጡ፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ብይን ሰጥተናል ሌላ ነገር ከሆነ ነው …›› ሲሉ የመሃል ዳኛው በድጋሚ ተናገሩ፡፡ የማህሌት ጠበቃም እጃቸውን አውጥተው ‹‹ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ ጠበቃው ተናገሩ የተባለው ተነሳ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በሚኒስትር ደረጃ ያሉ ሰዎች …›› ብለው እየተናገሩ እያለ ሰብሳቢው ዳኛ አቋረጧቸውና ‹‹ጠ/ሚኒስትርን …በተመለከተ ችሎቱ አይመለከተውም፡፡ (በዚህ የፍርድ ቤት ጉዳይ ላይ ያልቀረበ ነገር ለማለት ይመስለኛል) እኛ እዚህ ያለውን ጉዳይ ነው የምናየው፡፡ ችሎትን በማወክ …›› ሲሉ መልስ ሰጡ፡፡

ናትናኤል መናገሩን ቀጥሎ ‹‹በዚህ ጉዳይ ሀሳባችንን በነጻነት የመግለጽ መብታችን ተከልክሏል›› አለ፡፡ ‹‹እኛ እኮ ውሳኔ ለሁሉም ሰጠን፡፡›› ሲሉ ዳኛው በድጋሚ ተናገሩ፡፡ ናትናኤልም ‹‹ውሳኔው ለሁሉም ከሆነ፣ ለአቃቤ ህጉም ሆነ ለአለቃው ጠ/ሚኒስትር መሆን አለበት፡፡›› ሲል ገለጸ፡፡

መጨረሻ ረድፍ ላይ የቆመው ጦማሪ አቤል ዋበላም እጁን አውጥቶ መናገር ፈለገ፡፡ ዳኞቹ ‹‹ሥነ-ሥርዓት ያዝ›› አሉት ፡፡ እሱም ቆጣ ብሎ ‹‹እኛም የምንናገረው ነገር አለ፡፡ እናንተ ራሳችሁ ሥነ-ሥርዓት ያዙ! ይህ ችሎት ነው፡፡ ግልጽ ነው›› አለ፡፡

ዳኞች እርስ በእርስ መነጋገር ጀመሩ፡፡ የማህሌት ፋንታሁን ጠበቃ (እኔ ሳየው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው) ወደአቤል ጋር መጥተው ትንሽ ተነጋገሩ፡፡ የቀኝ ዳኛው አዲስ ወረቅት አውጥተው መጻፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ጠበቃው ‹‹ተከሶሾቹ ሊጠይቁ የፈለጉት ሲቀርብ ስለታሰበው ሲዲ ነው፡፡ ከሶሊያና ጋር የሚገናኝ ሰለሆነ›› ሲሉ ለዳኞች ተናገሩ፡፡

ሰብሳቢ ዳኛው ‹‹አሁን ስለተፈጠረው ነገርስ (ስለአቤል ንግግር)?›› ሲሉ ጠበቃውን ጠየቋቸው፡፡ ‹‹በይቅርታ ይታለፍ›› የሚለው የጠበቃው መልስ ነበር፡፡ የቀኝ ዳኛው ‹‹ስለሚሉን ነገር (በይቅርታ ይታለፍ) ራሱ አቤል መልስ ይስጥ›› ካሉ በኋላ ‹‹ስሜታዊ መሆን ከእናንተ አይጠበቅም፡፡ የተማራችሁ ናችሁ፡፡ ፍርድ ቤትን ማክበር አለባችሁ›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ አቤል ‹‹መናገር የፈለኩት …›› ‹‹አይ እሱን አይደለም፤ አሁን በስሜት ስለተናገርከው ነገር (መልስ ስጥ ነው)›› አሉት ዳኞቹ፡፡

አቤል ወደፊት ቀረብ አለና ‹‹እኔ ምንም አላጠፋሁም፡፡ የጠየኩት ሕገ-መንግሥታዊ መብታችንን ነው፡፡ መናገር እየቻልን ጥያቄያችንን በጽሑፍ አመልክቱ ለምን እንባላለን?›› ሲል መለሰ፡፡ ሰብሳቢው ዳኛ ‹‹አሁን የምትመልሰው በችሎት ይቀዳ›› አሉት፡፡ አቤልም ‹‹በድምጽ አልቀዳም፣ ጥያቄያችን አልተሰማም፡፡ ፍርድ ቤቱ በግልጽ ይስማን›› በማለት ወደቦታው ተመለሰ፡፡ ችሎቱም ወዲያው አቤልን በችሎት መድፈር ወንጀል ጥፋተኛ እንዳለውና ተገቢውን ቅጣት ለመወሰን ቀጠሮ እንደሚሰጥ ተናገረ፡፡

ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉም ተነስቶ ቆመ፡፡ ዳኛው ‹‹ተቀመጥ›› አሉት፡፡ ‹‹አልቀመጥም፣ ጉዳዩ የእኔም ነው›› ሲል መለሰ፡፡ ከፊት ያለው ናትናኤልም ቆመ፡፡ ‹‹ተቀመጥ›› አሉት፡፡ ‹‹የጓደኛዬ ጥያቄ የእኔም ነው›› ሲል ተናገረ፡፡

ጠበቃውም ‹‹ደንበኛዬ ችሎት ለመድፈር ሆን ብሎ ሳይሆን ቀደም ሲል ከተሰጠው ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ ሊጠይቅ ሲል ዕድል የተነፈገ መስሎት ነው፡፡ ይሄንን በስሜት የተሞላ የተናገረውን ንግግር ችሎት በመድፈር ሳይሆን በተግሳጽ እንዲያልፈው ሲል እናመለክታለን›› አሉ፡፡ ዳኛው ይሄንን መልስ መዘገቡ፡፡
ችሎቱም በሰባተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም፣ እንዲሁም በ1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስን የሚመለከተውን የአቃቤ ሕግ የሲዲ ማስረጃ ቀደም ብሎ በመመልከት ‹‹ሲዲው በግልጽ ቢታይ ችግር አለው ወይስ የለውም? ቀሪ ተከሳሾችን ይጎዳል አይስ አይጎዳም? በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 08 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ናትናኤልም ‹‹ጓደኛዬ (አቤል) የሚቀጣ ከሆነ ውሳኔው እኔም ላይ ይታዘዝ›› ሲል ለችሎቱ ተናገረ፡፡ ዳኛውም ‹‹ሌሎቻችሁን አይመለከትም፡፡›› ካሉ በኋላ ለፖሊሶች ተከሳሾቹን ከችሎት እንዲያወጧቸው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ናትናኤልም ‹‹የሚደረገው ነገር ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፤ ለሌሎችም ትምህርት አይሆንም›› በማለት ለዳኞች ድምጹን ከፍ አድርጎ ነገራቸው፡፡ ሰብሳቢው ዳኛው ‹‹በስሜት እየተነጋገርን የችሎት ሥራ እንስራ ታዲያ? …›› ሲሉ መለሱ፡፡ ፖሊሶችም ወደጦማሪያኑንና ጋዜጠኞቹ ተጠግተው ‹‹ከችሎት ውጡ›› በማለት በር ላይ በካቴና እጆቻቸውን እያሰሯቸው ወደእስረኞች መኪና ይዘዋቸው ሄዱ፡፡

እኛም ከችሎት ወጣን፡፡ እኔም የዛሬ ፍርድ ቤት ውሎን በቀድሞ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙኑኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ‹‹የመለስ ትሩፋቶች›› በተሰኛው መጽሃፋቸው ላይ ባስተዋወቁን ‹‹የካሳንቺሱ መንግሥት›› መቀመጫ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ላፕቶቴን አውጥቼ ያየሁትን፣ የሰማሁትንና የተከታተልኩትን እንዲህ ከትቤ አስነበብኳችሁ፡፡

መልካም ቀን!

የወያኔ/ኢህአዴግ ተግባር ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ። በስብሰባ ጋጋታና በባዶ ፕርፖጋንዳ እንዳንፈታ ትግሉ ይፋፋም!

                                                                  የተሰጠ መግለጫ
የወያኔ/ኢህአዴግ ተግባር ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ። በስብሰባ ጋጋታና በባዶ ፕርፖጋንዳ እንዳንፈታ ትግሉ ይፋፋም!
ግንቦት 14 ቀን 2007ዓ.ም
የችግራችን ቀጣይ ክስተቶች ለትምህርተ ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆልና የውድቀት ጠርዝ መድረስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ባይካድም ያለፉትን መንግሥታት በመኮነን ከምንም በላይ ራሱን የለውጥ ሐዋሪያና የዕደገት ተምሳሌት አድርጎ የሚቆጥረው ወያኔ/ኢህአዴግ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የትምህርት አመራር ከመስጠትና ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ ውስብስብና ሊፈቱ ከማይችሉበት ደረጃ አድርሷቸዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች በመምህራን እጥረት፣በመማሪያ ክፍሎች፣ በማስተማሪያ መጻሕፍትና በሌሎችም የትምህርት ግብአቶች እጥረት የተነሳ የተሟላ ትምህርት የማያገኙበት፣ ተማሪዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተስፋ የቆረጡበት ፣ ፈተና በአንድና በሁለት ደቂቃዎች ሰርተው የሚያጠናቅቁበት፣ ጭራሹን ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የሚገደዱበት ወቅት ስለሆነ ትምህርት ቀውስ ውስጥ ገብቷል።
የዚህ ቀውስ አንዱ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ወያኔ/ኢህአዴግ በሶስት ምድብ አመቻችቶ የማደናገሪያ /የማጭበርበሪያ አጃንዳዎቹን ለማስፈጸም የሚሞክርበትን አካሄድ ቀጥሎ እንመልከት፡-
ከመምህራን ጋር ፡-በአንዳንድ አካባቢዎች በህዳር ወር 2007ዓ.ም መጀመሪያ ሳምንት በተደረገ የመምህራን ስብሰባ ከ2006ዓ.ም በፊት በነበሩት አመታት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች እስከ ህዳር ወር መጨረሻ 2007ዓ.ም ድረስ ትምህርት ቤት እንዲገቡ የሚል ሐሳብ በወያኔ ካድሬዎች ይቀርባል።ለዚህ የተሰጠው ምክንያት የምዕተ ዓመቱ ( የሚሊኒየሙ) የልማት ግብ በዚህ በያዝነው አመት ስለሚጠናቀቅ አሁን በመማር ላይ ያሉት መማር ከሚገባቸው ተማሪዎች ቁጥር ያነሰ በመሀኑ ያቋረጡትን “በቅስቀሳ “ በማምጣት ከመስከረም 2007ዓ.ም ጀምሮ እየተማሩ ካሉት ጋር እኩል ማድረስና የምዕተ ዓመቱን “ ትምህርት ለሁሉም” የሚለውን ግብ ማሳካት በሚል የቀረበ አጀንዳ ነበር። በዚህ አጀንዳ ላይ የመማር ተግባራቸውን አቁመው ለዓመታት ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው የቆዩ ተማሪዎችን የትምህርት መጀመሪያ ዓመት ካለፈ ከወራት በኋላ መቀበል ማለትም እስከ ሀዳር ወር 2007ዓ.ም ያልተማሩትን በምን ተአምር ትምህርት እንዲያገኙ ይደረጋል? ከትምህርት ተለይተው የቆዩት ተማሪዎች ለተለያዩ ደባል ሱሶች የተጋለጡ ሊኖሩ ስለሚችሉ በነባሮቹ ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር የትምህርት ቤቶችን ድሲፕሊን ይጎዳል በሚል መምህራን ተቃውመውታል።ሥርዓቱ ፊቱ ላይ የሚታየው የአፈጻጸም ሂደት የውጭ ርዳታ ማግኘትን ትኩረት ሰጥቶ ንዋይ መሰብሰብ ዋናው ዓላማ ሆኖ ትምህርቱና ትውልዱ እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል በማለት አስተያየት እየሰጡ ስብሰባውን ረግጠው እሰከመውጣት ደርሰዋል።
ከዚህ በመቀጠል በታህሣሥ ወር መጨረሻ 2007ዓ.ም በአማራ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች ለ3 ቀናት የሚቆይ

 •   የተሀድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ
 •   የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና በትግሉ የተገኙ ውጤቶችና ተግዳሮቶች
 •   የ2007ዓ.ም የትምህርት ንቅናቄ ሰነድ በሚሉ አጀንዳዎች ስልጠና የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የስልጠናው ዓላማ መምህራንና ተማሪዎች በተጀመረው የልማትና የመልካም አስተዳደር ላይ ግልጽነት እንዲኖር ለማድረግ የሚል ሆኖ ቀጥሎ ያሉት ንዑስ ዝርዝሮች ተካተዋል።
 1. የተጀመሩትን ኢክኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ከዳር ለማድረስና የአጋጠሙ ተግዳሮቶችን ፈትሾ የአገራችንን የተሀድሶ ጉዞ ከትምህርት ማህበረሰብ ጋር ያለውን ፋይዳ ለመመዘን፣
 2. ልማታዊ አስተሳሰብ የተሀድሶው መነሻ በመሆኑ ሁላችንም ልማታዊ አስተሳሰብ እንድንይዝ ለማስቻል፣
 3. የህዳሴው የጉዞ ደረጃና መድረሻ ምን እንደሆነ ለማስገንዘብ፣
 1. ችግሮችን መለየትና ለውጡን በጠራ አቅጣጫ ለመምራት የሚያስችሉ ግብአቶች ለማግኘት፣
 2. የተደራጀ የትምህርት የልማት ሠራዊት ግንባታ ለትምህርት ጥራት የማይተካ ዓላማ አለው፣ስለሆነም በተበታተነ
  አደረጃጀት ጥራት ማምጣት ካለው ፋይዳ ጋር ለመገምገም፣
 3. የ2007 ዓ.ም የትምህርት በጀት የዕድገትና የልማት ዕቅዱ ማጠቃለያ ስለሆነ የቀሩንን ለይተን ርብርብ ለማድረግ
  ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ወሳኝ ስለሆነ ፣
 4. የአገራችን የተሀድሶና የህዳሴ ጉዞ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች አውቆ ርብርብ ለማድረግ እንዲያስችል ታስቦ
  የተዘጋጃ መሆኑ በካድሬዎች ተነግሮ አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም የሚል ጥያቄና የአስተያየት ሀሳብ ከራሳቸው ከካድሬዎች ይነሳል።

ለነዚህ ከላይ ለተዘረዘሩት በትምህርት ስልጠና ስም በወያኔ ለቀረበው የፖለቲካ አጀንዳ የመምህራን መልስ ይህ አቀራረብ በየቀኑ ከምንሰማው ፕሮፖጋንዳ የተለየ አይደለም፣ ሰነዱ የስልጠና ይዘት የለውም፣ለስልጠናም የሚያግዝ የማቴርያል ( የቁሳቁስ) አቅርቦት የለም፣ እንዲያውም በትምህርቱ የንፍቀ ዓመት ( የሴምስተሩ አጋማሽ ወቅት) መዘጋጀቱ የትምህርትን ሂደት የሚጎዳ ስለሆነ አስፈላጊ አይደለም የሚል በመሆኑ ውዝግብ ተፈጥሮ ስልጠና ተብዬው ለግማሽ ቀን ያህል ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ከመምህራን ፍላጎት ውጪ በካድሬዎች ጫና ሊቀጥል ችሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከትምህርቱ ጉዳይ ጋራ በማጣመር የቀረቡት አንዳንድ ትምህርት ነክ አጀንዳዎች ዓላማቸው የወያኔን የተሳሳተ የፖለቲካ መሰመር ጥሩ ገጽታ ለማላበስ የቀረቡ ናቸው። ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት ፣ የብሔርና የሃይማኖት እኩልነት ተረጋግጧል በማለት የውሸት ድስኩሩን በሰብሰባዎቹ ወቅት አቅርበዋል።እንዲሁም ከአማራ ክልል የተወሰደ መሬት የለም፣የድሮዋን ኢትዮጵያ የተሻለች አድርጎ ማቅረብ፣ የአማራ ሕዝብ እንደተዋረደና ዝቅ ተደርጎ እንደሚታይ ማቀንቀን፣ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የታቀደ ነው ማለት ፣ የአንድ ብሔር የበላይነት እንዳለ አድርጎ መቀስቀስ የትምክህትና የጠባብነት መግለጫዎች ናቸው በማለት የወያኔ ካድሬዎች በሕዝብ ላይ የፈጸሙትንና እየፈጸሙ ያሉትን እውነት ክደዋል። መቼ ወያኔና እውነት ይታዋወቃሉ? በሀይማኖት ስም የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ወደ ሕዝብ መግባትና ሕገመንሥቱን መቃወምና ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት አንድ አገር፣ አንድ ሀይማኖት፣ በመጅሊሶቻችን መሪዎቻችንን እንዳንመርጥ መንግሥት ጣልቃ እየገባ ነው ፤የሸሪአ ሕግ መመስረት አለበት ፤ የእስላም መንግሥት እናቋቁማለን ፤ በትምህርት ቤቶች መስገጃ ቦታ ይፈቀድልን የመሳሰሉት በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች የሚንፀባረቁ የአክራሪነት መገለጫዎች ስለሆኑ በትግል መፍታት ይገባል ተብሎ በካድሬዎች በኩል ለቀረቡት አስተያየቶች የመምህራኑ መልስ ለካድሬዎች የቀና አልነበረም። ቀድሞውንም በስልጠናው ይዘትና አካሄድ ደስተኛ ያልነበሩት መምህራን ባንድ ድምፅ ተቃውሞቸውን በማሰተጋባት እኛ አንድ ነን፣ አትከፋፍሉን፣አንከፋፈልም በማለት በጩኸት፣ በፉጨት፣ በሞባይል ወኔ ቀስቃሽ የሆኑ የቀረርቶና የሽለላ ዜማዎችን በማሰማት የካድሬዎችን የውሸትና የተንኮል ፕሮፖጋንዳ ጆሮ ሳይሰጡ በወቅቱ መምህራን ያሳዩት ተቃውሞና የትግል ተነሳሽነት የሰርዓቱን ውድቀት አይቀሬነት አመላካች ነበር።
እንዲሁም በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በትምህርትና በመምህራን ላይ የሚፈጸመው በደል ዘርፈ ብዙ ነው። በደቡቡ የአገራችን ክፍል የእርከን ጭማሪ ለርዕሳነ መምህራንና ለሱፐርባይዘሮች ተፈቅዶ ለመምህራን የተከለከለ መሆኑን ለተለያዩ የዞን ት/ቤቶች አሰተዳደር ከደቡብ የትምህርት ቢሮ የተለከው ደብዳቤ ያሳያል። ወያኔ ለይስሙላው ምርጫ መጠቀሚያ ለማድረግ የድርጅቱ አባል የሆኑትን መምህራን በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ በትምህርት ሰዓት ስብሰባ በማካሄድ በትምህርት ላይ በደል እየፈጸመ ይገኛል። በ11/07/2007 በሀድያ ዞን ውስጥ በዋቸሞ መሰናዶ ት/ቤት ለወያኔ የምርጫ ድራማ ለ25 የወያኔ/ኢህአዴግ አባል መምህራንና ሰራተኞች ስልጠና በሚል የትምህርት ፕሮግራም ተቋርጦ ስብሰባ እንዲገቡ በመደረጉ የቀሩት የድርጅቱ አባል ያልሆኑ 75 መምህራን በድርጊቱ በመናደድ ፣ በትምህርት ቤት የትምሀርትን ክፍለ ጊዜ በማቃወስ የፖለቲካ ስብሰባ መካሄዱን ተቃውመው ወደ ቤታቸው ሄደዋል። ተማሪዎቹም አስተማሪ ስላጡ ወደየቤታቸው ለመሄድ ተገደዋል። በዚህም ሁኔታ የትምህርት ስራ ለሁለት ቀናት ተቋርጧል።ይህን ሁኔታ በመከተል በአካባቢው በሚገኙ ት/ቤቶች የሚያስተምሩ የወያኔ ደጋፊ ያልሆኑ መምህራን ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ተቃውሟቸውን አየገለጹ መሆናቸው ተረጋግጧል። መቀጠል ያለበት የትግል ስልት ነው።
ከተማሪዎች ጋር በተደረገው ስብሰባም ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል በሌሎች አገሮች የስልጣን ዘመን የተገደበ ነው።እናንተ ግን ወደ ስልጣን ከወጣችሁ 23 ዓመታት ሆናችሁ። ስልጣናችሁን ልቀቁ፣ እናንተን አንመርጥም፣ በቃችሁ። የሕግ የበላይነት አለ ትላለችሁ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከ6 ወራት በላይ እንዲሁም ሌሎችን ፍ/ቤት ሳታቀርቡ በእስር ማቆያታችሁ የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰአታት ውስጥ ፍ/ቤት የመቅረብ መብት አላቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አይጻረርምዎይ? በትምህርት ቤት ተማሪዎችን በኢህአዴግ አባልነት ትመለምላለችሁ ፣ በህዋስ በአንድ ላምስት ታደራጃላችሁ፣ ትምህርት ቤት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት ፣ ከፖለቲካ አመለካከቶችና ከባሕላዊ ተጽዕኖዎች ነፃ መሆን አለበት ከሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አይጻረርምዎይ? ተቃዋሚዎች ይህን በት/ቤቶች እንዲያደርጉ ተፈቅዳላችሁዎይ?—–የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሳትና ኢህአዴግ ይውደም!ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! የሚል መፈክር በማሰማት ስብሰባው ያለምንም መግባባት በልዩነትከመጠናቀቁም በሻገር ተማሪዎች ለነሷቸው ጥያቄዎች የወያኔ/ኢህአዴግ ካድሬዎች መልስ መስጠት ተስኗቸው እንደነበር ለመራዳት ተችሏል።

ወያኔ/ኢህአዴግ ከአባላቱ ጋር በጥር ወር 2007ዓ.ም መጨራሻ ባካሄደው ስብሰባ ከአባላቱ በርከታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል። ከነዚህም ለተቃዋሚዎች መፈራረስ የኢህአዴግ እጅ አለበት ፣ ኢህአዴግ ዲሞክራሲ አለ ይላል ግን ያስራል፣ ይገርፋል፣ ይገድላል። ይህን እየፈጸማችሁ ከደርግ በምን ትሻላለችሁ? የአማራ ወጣቶች በሌሎች ክልሎች ተቀጥረው አይሰሩም? የሌሎች ክልሎች ወጣቶች ግን በአማራው ክልል እስከ መሾም ይደርሳሉ። የእኛ አገር የሕዝብ ተወካዮችና ሌሎችም ምርጫዎች ከሌሎች አገሮች ምርጫዎች ጋር እንዴት ይነጻጸራል? ለመንግሥት ሠራተኞች የተሰጠው የደመወዝ ጭማሪ ፍትሐዊ አይደለም። አርሶአደሩ ከይዞታ መሬቱ ያለበቂ ካሣ እየተፈናቀለ ነው ለዘለቄታው ምን ታስቦበታል? የድርጅት አባላት ድርጅቶቻቸውን ያማርራሉ ችግሩ ምንድነው? አየለ ጫሚሶና መሰሎቹ የኢህአዴግ ሽርጥ ለባሾች እንጂ ተቃዋሚ አይደሉም —ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰጥተው ከመድረክ መሪዎች የተሰጡ ምላሾች ቁጣን በመቀስቀሳቸው ስብሰባው ያለምንም መግባባት ተጠናቋል።
በሌላ በኩል በመንግሥት መስሪያ ቤቶችም ሆነ በትምህርት ቤቶች በበጀት እጥረት የተነሳ ስራ ወደ መቆም የተቃረበበት ፣ ካድሬዎች ከምርጫ ጋር በተያያዘ በስብሰባ የተጠመዱበትና ፍርሃታቸው ከምንጊዜውም በላይ ገዝፎ እርስ በርስ አለመተማመን ደረጃ ላይ የደረሱበት ፣ ሰራተኛው ፊት ለፊት ስርአቱን እየሞገተ ጥላቻውን በግልጽ እያሳየና ለስርዓት ለውጥ ለሕዝባዊ እምቢተኝነት ራሱን እያዘጋጀ እንደሆነ ይታያል።
የኑሮ ውድነቱ፣ የስራ ዋስትና ማጣት ፣ የመብት ረገጣው፣ የመልካም አስተዳደር እጦት —–ያስመረራቸው መምህራን የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን በማንሳት ላይ ይገኛሉ።ከእነዚህ ውስጥ የሚጠቀሱ በደሴ ከተማ የሚገኙ የአንዳንድ ት/ቤቶች መምህራን ለተመሳሳይ ስራ ተመሳሳይ ክፍያ ይደረግ፣የመምህራን የዕድገት መሰላል ( Career Structure) በአንዳንድ ክልሎች ተሻሽሎ ተግባራዊ ሲሆን በሌሎች ክልሎች ለምን አይተገበርም ? የቤት አበል ( Housing allowance) ለምን ተግባራዊ አይሆንም? የቤት መስሪያ ቦታ ያለምንም ክፍያ በነፃ ልናገኝ ይገባል። የትምህርት ጥራትን እናረጋግጣለን እየተባለ በይድረስ ይድረስ በዘፈቀደ በለብለብ ለመህራንና ለሌሎች ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው፣ ይህ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን። የተሰጠው የደመወዝ ጭማሪ የኑሮ ውድነቱን ያላገናዘበ ስለሆነ እንደገና ማስተካከያ እንዲደረግበት የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት በየካቲት ወር 2007ዓ.ም መጀመሪያ ፒቴሽን ተፈራርመው ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ጥያቄዎቹ አስቸኳይ መልስ ካልተሰጣቸው የስራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ይህ በደሴ ከተማ መምህራን የተነሳው ጥያቄ በአገሪቱ የሁሉም መምህራን ጥያቄ፣ ከዚያም ባለፈ ባጠቃላይ የሠራተኞች ጥያቄ ስለሆነ ለተግባራዊነታቸው ዜጎች ሁሉ እንዲተባበሩና ትግሉን እንዲያግዙ በሰደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።
በዚህ ጽሑፍ ወያኔ/ኢህአዴግ መምህራንን ፣ ተማሪዎችንና የራሱንም አባላት በተለያዩ ጊዜያት ሰብስቦ ለማወያየት መሞከሩን አይተናል። በተለይ በመግቢያው ላይ በተመለከቱት የመወያያ አጀንዳዎች ላይ በነቂስ ለመተቸት አንድ መድበል የሚወጣው ስራ ይጠይቃል። በጥቂቱ ቀንጨብ አድርገን ለማሳየት እንገደዳለን። ልማታዊ አስተሳሰብ ምንጩ ጥሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። የፖሊሲው ቅኝት በአንድ ዘረኛ ፓርቲ ቁጥጥር በዋሉና ንብረትነታቸው የፓርቲው የሆኑ ኩባንያዎች ያለገደብ ያለውድድርም ተጠቃሚዎች በሆኑበት ስርአት ፣ ሌሎች የግል ባለሐብቶች ወደዳር በሚገፉበት ሁኔታ አባባሉ ጉንጭ አልፋ ከመሆን አይዘልም። የህዳሴው መነሻና መድረሻ ሕዝብ በወጉ እንዲያውቀውና እንዲቀበለው ያልተደረገ በሂደቱም የጠራ አቋም ይዞ በፍላጎት ላይ በተመሰረተ ስሜት የማይሳተፍበት ፣ የጉልበት፣ የዕውቀት፣ የማቴርያል፣ የገንዘብ እገዛ እንዲያደርግ የሚያዘጋጁ ስነልብናዊ ሁኔታዎች ባልተመቻቹበት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከየት ወዴት የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።በዚሁ ላይ ዕድገት በተመጽዋችነት ፣ በርዳታና በብድር ውጤታማ የሆነበት አገር በ50 እና 60 አመታት አልታየም። በተለይ ኢትዮጵያን በመሰሉ የአፍሪካ አገሮች ያተረፈው ነገር ቢኖር የአምባገነኖችን ኪስ ማሳበጥና የአገዛዝ ጡንቻቸውን ማጠንከር ሆኗል። ስለዚህ በአገዛዝ ስር ያለ ሕዝብ የዕድገትና ሽግግር መለኪያው የአገዛዙን ከንቱ ውዳሴ ከማጉላት ውጪ የሚታይ አይሆንም።
ስለትምህርት ፖሊሲው ሰንካላነት፣ ስለካርኩሉም፣ ስለመምህራን ምልመላና ስልጠና ስለትምህርት ግብአቶች ጥራትና ተደራሽነት ችግር—-በተለያዩ መግለጫዎች ለሕዝብ ለማሳወቅ ሞክረናል። ብዙ አገር ወዳድ ምሁራንም በተለያዩ ጊዜያት ስለትምህርቱ ውድቀትና ትውልድ ገዳይነት ትችት አቅርበውበታል።ሌላው ቀርቶ መምህራን በነፃነት በሙያቸው ተደራጅተው ስለትምሀርቱ ሂደት በተለይና ስለአገራቸው ጉዳይ ባጠቃላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዳያደርጉና ብሔራዊ ግዴታቸውን እንዳይወጡ በሚያግድ ፣በሚያደናቅፍና ማህበራትን በአንድ ፓርቲ ዕዝ በሚያስገባ ስርዓት “የተምህርት ሠራዊት ግንባታ” የሚል ርዕስ የተካተተበት አጀንዳ መምህራንን ለማደናገር ማቅረብ ቧልት በመሆኑ የወያኔ ስብሰባ ውሉ ጠፍቶበት መጠናቀቁ ታይቷል። ትምህርቱንና ትውልዱን የመግደል የወያኔ ስልት ገና ከመነሻው 42 የዩኒቨርሲቲ ዕውቅ መምህራንን በማባረር አሳይቷል።አሁን በቅርቡም ሁሉቱን ብርቱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን አባሯል። ስለትምህርቱ ጥራትና ውድቀት ከተባራሪዎቹ አንዱ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ያለበቂ ዝግጅት፣ ብቃት ያላቸው መምህራን ሳይኖሩ፣ የትምህርት ግብአቶች በሚፈለገው ደረጃ ሳይመቻቹ በየጨካው ዩኒቨርሲቲ መክፈት ምርታማ ዜጎችን የማያወጣና የአገሪቱን አንጡራ ሀብት እንደማባከን እንደሚቆጠር አመላክተዋል።ማን ያርዳ የቀበረ ፣ ማን ይንገር የነበረ እንዲሉ። ይህ ሕዝብን የማደንቆር ፖሊሲ አንድ ቦታ ካልቆመ
የትውልድ ግድያው ይቀጥላል። የትምህርት አፓርታይድ የተከለው ወያኔ ሕዝብን አደንቁሮ የመግዛት ኃይሉ እየጎለበተ ከመሔዱ በፊት ወላጆች፣ተማሪዎች ፣ ሌሎች የሕብረተሰቡ አካላት ለአሁኑና ለተተኪው ትውልድ ዕጣ ፋንታ መቆም ይጠበቅባቸዋል።
ለዚህ ነው መምህራን በየወቅቱ ፣ በየቦታው የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ያሉት። በራሳቸው ላይ ቤንዚን በማርከፍክፍ መስዋዕት የሆኑት። ጩኸታቸውን ኢትዮጵያውያን በያሉበት አስተጋበተው ትውልዱን ከድንቁርናና ከሞት እንዲታደጉ በሰደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል።
ለስርዓት ለውጥ ትግሉ ይፋፋም!! በትምህርትና በባለሙያዎች ላይ መቀለድ ያብቃ!! ትምህርት የዕድገት መሰላል ነው! መወጣጫው አይፋለስ!!

ፊታችንን ከምርጫ ፓለቲካ ወደ ሁለገብ ትግል እናዙር!- የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ

ginbot 7ምርጫ 2007 ተጠናቆ ተወዳዳሪም አወዳዳሪም የሆነው ህወሓት ይፋ ውጤት እስኪገልጽ እየተጠበቀ ነው። ሁሉ በእጁ ነውና ባለሥልጣኖቹ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚስማማቸው እስከሚነግሩን ጥቂት ቀናት ይወስዱ ይሆናል። ከፈለጉ ሁሉን የፓርላማ ወንበሮች ሊወስዷቸው ይችላሉ፤ ካሻቸው ደግሞ ጥቂቱን ለተቃዋሚዎች ሊሰጡ ይችላሉ። ወሳኞቹ እነሱ ናቸው። በዚህ የፓርላማ ወንበሮች እደላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ አንዳችንም ሚና የለውም።
ምርጫ የሕዝብ የሥልጣን ባላቤትነት ማረጋገጫ ከሆኑ አቢይ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት አንዱ መሆኑ የታወቀ ነው። ሆኖም ግን ነፃ ተቋማት በሌሉበት፤ በአምባገነኖች አስፈፃሚነት የሚደረግ ምርጫ የመራጮች ነፃ ፍላጎት መግለጫ በመሆን ፋንታ የገዢዎች ሥልጣን ማረጋገጫ መሣሪያ ይሆናል፤ ከአገራችን እየሆነ ያለውም ይህ ነው።
የዘንድሮው ምርጫ 2007 ከዚህ በፊት ከነበሩ በባሰ ለአፈና የተጋለጠ የነበረ መሆኑ ከጅምሩ በግልጽ የታየ ጉዳይ ነበር። በአንድነትና በመኢአድ ፓርቲዎች ላይ አገዛዙ የወሰደው የግፍ እርምጃ የዚሁ የምርጫ ዘረፋ ስትራቴጂ አካል ነበር። ከዚያ በተጨማሪም መራጮች እውነተኛ ፍላጎታቸውን በነፃነት መግለጽ እንይችሉ ዘርፈ ብዙ ጫናዎች ሲደረግባቸው ቆይቷል። የተወዳዳሪ ፓርቲዎች አባላት እንደተፎካካሪ ሳይሆን እንደጠላት ሲሳደዱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ ሰንብቷል። በምርጫው ሰሞንና በዕለቱ በተለይ ከተሞች በባዕድ ጦር የተወረሩ መስለው ነበር። ይህ ሁሉ ስነልቦናዊና አካላዊ ተጽዕኖ ታልፎ የተሰጠው ድምጽ ቆጣሪው ራሱ “ተወዳዳሪ ነኝ” ባዩ ህወሓት ነው።
በእንዲህ ዓይነት ምርጫ መሳተፍ ትርፉ “በሕዝብ ድምጽ ተመረጥኩ የማለትን እድል ለአምባገኑ ህወሓት መስጠት ነው”፤ “ለዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብም የተምታታ መልዕክት ማስተላለፍ ነው”፤ ”ለህወሓት ተጨማሪ ገንዘብ ማግኛና የኢትዮጵያን ሕዝብ መከራ ማራዘሚያ ነው“ በሚል በዚህ ምርጫ ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ አርበኞች ግንቦት 7 ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል። በርካታ ወገኖቻችን የምርጫ ካርድ ቢያወጡም የደረሰባቸውን ጫና ተቋቁመው በምርጫው ባለመሳተፍ ላሳዩት ጽናት አርበኞች ግንቦት 7 አድናቆቱን ይገልፃል።
ህወሓት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የምርጫ ጉዳይ እና የምርጫ ፓለቲካ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም የተጠናቀቀ ቢሆንም እንኳን ተጨማሪ ማስረጃ ለሚፈልጉ ግንቦት 16 ቀን 2007 መጥቶላቸዋል። አሁን ከፊታችን የተደቀነው ጥያቄ የሚከተለው ነው – አገራችን ከህወሓት አፈና ነፃ ለማውጣት ያለን አማራጭ መንገድ ምንድነው?
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ህወሓት ከኢትዮጵያዊያን ጫንቃ የሚወርደው ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽን ባቀናጀ ሁሉገብ ትግል ነው ብሎ ያምናል። በዚህም መሠረት ለሁለቱም የትግል ዘርፎች ተስማሚ የሆኑ አደረጃጀቶችን አዘጋጅቷል።
ሕዝባዊ እምቢተኝነት፣ ታጋዩ ከመኖርያ ወይም ከሥራ ቦታው ሳይለቅ በህቡዕ የሚከናወን ትግል ነው። ሕዝባዊ አመጽ ደግሞ ከመኖሪያና ሥራ ቦታ ለቆ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። ሁለቱም የትግል ዘዴዎች የህወሓትን ህጎች በመቃወም የሚደረጉ ናቸው። ሁለቱም የትግል ዘዴዎች ድርጅት፣ ዲሲሊንና ጽናትን ይጠይቃሉ። ለድላችን ሁለቱም የትግል ዘርፎች እኩል ዋጋ አላቸው። እናም ከዛሬ ጀምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደዝንባለውና አቅሙ በሚመቸው የትግል ዘርፍ ይሳተፍ። ሕዝባዊ ኃይልን መቀላቀል የቻለ ይቀላቀል፤ ያልቻለው በያለበት ተደራጅቶ በሕዝባዊ እምቢተኝነት ይታገል።
በየመኖሪያ ሠፈሩና በሥራ ቦታዎች የሚቋቋሙ የአርበኞች ግንቦት 7 ማኅበራት በርካታ ሥራዎች አሏቸው። ከሁሉ አስቀድሞ ድርጅትን ማጠናከር የሁላችንም ድርሻ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፤ እናም ትኩረታችን እዚያ ላይ እናድርግ። እያንዳንዳችን ከሚመስሉንና ከምናምናቸው ጋር ተነጋግረን እንደራጅ፤ ወያኔ የሸረሸረብንን በራስ መተማመን እና የእርስ በርስ መተማመንን መልሰን እንገንባ። ውስጥ ውስጡን ጠንካራ አገራዊ ኅብረት እንፍጠር፤ የዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን ደግሞ አካባቢያዊ ይሁኑ። ድርጅታችንን እያጠናከርን ወያኔን ከሁሉም አቅጣጫ እንሸርሽረው እንገዝግዘው። በዚህ መንገድ በሚደረግ ሕዝባዊ ትግል የሚገኝ ድል ፈጣን ከመሆኑን በላይ የድሉ ሕዝባዊነት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ይሆናል።
ስለሆነም እያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ታጥቆ እንዲነሳ፤ ወደ ተግባራዊ ትግል ፊቱን እንዲያዞር አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41754#sthash.k6FqTttQ.dpuf