በሻቢያ እርዳታ ይደረጋል የሚባለው የትጥቅ ትግል “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ”

ማሳሰቢያ
ይህች መጣጥፍ በቅርቡ እዚህ ድረገጽ ላይ ወጥታ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ጸሃፊው ያነሷቸው ጭብጦች ሰሞኑን ግንቦት ሰባት ጀምሬያለሁ ካለው የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴና ወያኔም ለዚህ ከሰጠው ምላሽ ጋር ወቅታዊነትና ቀጥተኛ መስተጋብር ያለው ሆኖ ስላገኘነው ለግንዛቤ ማዳበሪያ እንዲረዳ በድጋሚ አቅርበነዋል።

ከታደሰ አርጋው

መግቢያ
የወያኔ አገዛዝን በትጥቅ ትግል ለማስወገድ ኤርትራ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ ስለተባሉት “አርበኞች” ሰሞኑን በመካሄድ ላይ ያለው ውይይት በውጭ በሚገኙ የተለያዩ የኢትዮጵያውያን የዜና ማሰራጫዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶታል። በተለይም በአቶ አበበ በለው አዘጋጅነትና አቅራቢነት በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አካባቢ በሚሰራጨው አዲስ ድምጽ ሬዲዮ ላይ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት የቀረበው ውይይት እጅግ ጠቃሚ ሃሳቦች የቀረቡበትና በተለይም ኤርትራ ውስጥ ከዚህ ቀደም አርበኞች ግምባርን ተቀላቅለው ሁኔታውን በአይናቸው ያዩና በሂደቱ የተሳተፉበት እማኞች የቀረቡበት በመሆኑ ሁሉም አገር ወዳድ ወገኖች በጽሞና ሊከታተሉትና የራሳቸውን ግንዛቤ ሊወስዱበት የሚገባ ውይይት ነው። በውይይቱ ላይ የተገኙት እንግዶች አቶ ክንፉ አሰፋ ከኔዘርላንድስ፣ አቶ ሰናይ ገብረመድኅን ከአውስትራሊያ እንዲሁም አቶ ልዑል ቀስቅስና አቶ ካሣዬ ከጀርመን ናቸው።የተለያዩ አድማጮችም ስልክ በመደወል ተሳትፎ አድርገዋል። እኔም በውይይቱ ላይ የተንሸራሸሩትን ሀሳቦች አስመልክቼ የራሴን ግምገማና አስተያየት በዚህች አጭር መጣጣፍ አቅርቤያለሁ።

የውይይቱ ጭብጥ በሻቢያ እርዳታ ወያኔን ለመጣል የሚደረግ እውነተኛ ትግል አለ ወይ? ሻቢያስ እውነተኛ እርዳታ እያሰጠ ነው ወይ?

በቃለ መጠይቁ ውስጥ የተነሱት አበይት ጉዳዮች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከትና አጀንዳ ያላቸው ቡድኖች/ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የኦሮሞ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች፣ የቤንሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የትግራይና ሌሎችም ግምባሮች ለበርካታ ዓመታት በሻቢያ እርዳታ ወያኔን ለማስወገድ ኤርትራ ውስጥ ይገኛሉ ስለሚባሉት ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ላይ ከቀረቡት ነቀፋዎችና ትችቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። ሻቢያ ከተፈለፈለበት እ.አ.አ. ከ1970ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ አንግቦት የተነሳው መፈክር ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠልና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማውደምና በምትኳ የተዳከመች፣ እርሱ የሚቆጣጠራትና ተንሰራርታ ለህልውናው የማታሰጋው፣ ደካማ፣ የተከፋፈለችና የደቀቀች ጥሬ ዕቃ አቅራቢና የፋብሪካ ውጤቶች ማራገፊያ የሆነች አገር እንድትሆን ለማድረግ ነው።

በዚህም መሠረት ሻቢያኤርትራን ለመገንጠል ሁለት የቀደሙ የኢትዮጵያ መንግሥታትን ማለትም የኃይለ ስላሴንና የወታደራዊውን መንግሥታት በሚወጋበት ጊዜ እራሱ ፈጥሮ በረጨው “የኤርትራ ታሪክ” በመመርኮዝ ኢትዮጵያ ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ጉዳት አድርሷል። አሁንም ጦሱና መዘዙን ተሸክመን እየኖርን ነው።

ሻቢያ በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰው ጉዳት በጥቅሉ አሁን እንደምንሰማውና በረቀቀ ሁኔታ እየተጋትን እንዳለው የኢሳያስ አፈወርቂ “ የታሪክ መዛባት” ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ምሁራንና ታሪክ ጸሃፊዎች ኢትዮጵያዊነት ላይ ዘምተው ሲተናነቁን ኖረዋል። አሁን በኢሳያስ አፈወርቂ ተፈብርኮ በኢሳት በመስተጋባት ላይ እንዳለው “የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ወንድማማቾች ናቸው፤ የጋራ የሆኑ እሴቶች አሏቸው፣ ወዘተ….” እንደተባለው ሳይሆን ሻቢያ ለረዥም ዓምታት ሲያስተጋባና ሲለፍፍ የነበረው ኢትዮጵያ ኤርትራን በቅኝ ገዥነት ጨቁና ስትገዛ የነበረች ናት በማለት “ቅኝ ግዛት” ለሚለው ሀረግ በመላው ዓለም ከሚሰጠው ትርጉም ጋር በተጣረሰ መንገድ ልብ ወለድ ዝባዝንኬ በመደርደር ዓላማው የሆነውን ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመገንጠልና አዲስ ማንነት የመፍጠር እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ ለመለያየትና ደም ለማቃባት ተጠቅሞበታል።

የቅርብ ጊዜ ታሪክ

የታሪክ ማህደራትን ብንመለከት ጣሊያን ኤርትራን በቅን ግዛትነት ይገዛ በነበረበት ዘመን ኤርትራዊያን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሳይሆን እንደ ከብት ተዋርደው ይገዙ እንደነበር ይታወቃል።አሁንም ቢሆን በሕይወት ያሉ ስቃዩና በደሉ የደረሰባቸው እማኞች ጊዜ ያልሻረውን በደላቸውን ይናገራሉ። በዛ ጨለማ ዘመን ጣሊያኖች ኤርትራውያንን በረባው ባረባው በካልቾ መቀመጫቸውን እየጠለዙ፣ አፍንጫቸውን በቴስታ እያደሙና የስድብ ድንጋይ እያወረዱባቸው ለምሳሌ “አፋንኩሎ” “ቴስታ ዲጋሊኖ” ወዘተ እያሉ አዋርደውና አንቋሸው በባርነት እየቀጠቀጡ ሲገዣቸው አንደነበር ይታወቃል። ብዙዎች ኤርትራውያን ከዚህ አሳራቸውን ከሚያስቆጥራቸው የጣሊያን ባርነት እያመለጡ ወደ ወገናቸው ኢትዮጵያውያን በመግባት ተከብረውና አንቱ ተብለው የተለያዩ የማዕረግና የክብር ስሞች እየተሰጧቸው ለምሳሌ ራስ፣ ፍታውራሪ፣ ጀጃዝማች፣ ቀኝ አዝማች ወዘተ ተበለው ይኖሩ እንደነበርና አሁንም በመኖር ላይ እንዳሉ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

በዚህም መሠረት ከኤርትራ ክፍለ ሃገር ባዶ እጃቸውን የወጡ ወገኖቻችን ኢትዮጵያ አስተምራ ለወግ ለማዕረግ ያበቃቻቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም። እነዚህ ወገኖቻቸን በጦር አዛዥነት፣ በሚኒስትርነት፣ በአምባሳደርነት፣ ተመድበው ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን እንዲሁም በንግዱ ዘርፍ የትላላቅ ፋብሪካዎች፣ሱቆች፣ ጋራዦች፣የአስመጭና ላኪ ወኪሎች፣ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እንዲሁም የበርካታ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ሆነው ተደስተውና ተከብረው ይኖሩባት የነበረች፣ አሁንም እየኖሩባት ያለች አገር ኢትዮጵያ ናት። ይህንን አገር ያወቀውንና ጸሃይ የሞቀውን እውነታ በመደፍጠጥ ሻቢያ “ኢትዮጵያ ኤርትራን በቅኝ ግዛት ያዘች” በማለት የረጨው መርዝ የለከፋቸው ኤርትራውያን ያጎረሳቸውን የኢትዮጵያን እጅ የነከሱና የእግራቸውን ንቃቃት የደፈነላቸውን ኢትዮጵያ አገራቸውን እውስጧ ተቀምጠው ይገዘግዟትና በማጅራቷ ያርዷት የነበሩ ቀላል ቁጥር ያላቸው እንዳልነበሩ ሳይናገሩ ማለፍ በታሪክ ላይ ማላገጥ ስለሆነ ሊጠቀስ የሚገባውና በታሪክ መዝግብም በዝርዝር ሊሰፍር የሚገባው ነው።

ሻቢያ ለጎረቤት አገሮችና ለዐረቡ ዓለም የተሳሳተ መረጃ በማጠጣት ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በኤጼ ኃይለስላሴ መንግስት ከዐረቡ አለም መሪዎች ከግብጹ ፕሬዝዳንት ጀማል አብደልናስር አንስቶ ከሱዳን፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ፣ አልጀሪያ፣ ሞሮኮና ሌሎችም አገሮች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት አድርጋ የነበረችና በተለይም በሞሮኮና አልጀሪያ መካከል የነበረውን ጦርነት አስቁማ ያስታረቀች አገር ብትሆንም በአጸፋው ያገኘችው ግን በጠላትነት መታየትን ነው። በወታደራዊው መንግሥት ጊዜም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የፍልስጥኤም ህዝብ ጥያቄን አንግባ በመታገል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ብታበረክትም እንዲሁም ከሊቢያ፣አልጀሪያ፣ ምዕራብ ሰሃራ ግብጽ፣ሰሜንና ደቡብ የመን ጋር ወዳጅነት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጋ የነበረች ብትሆንም ሻቢያ በተደራጀና ስራዬ ብሎ ሌት ተቀን በሰራው ደባ ኢትዮጵያን ከአብዛኛው የአረብ አገሮች ጋር ጠላትነት ፈጥሮባት ኖሯል። ሻቢያም በዚህ ድርጊቱ ደንበር ጥሶ ኢትዮጵያን ከወረረው የሶማሊያው የሲያድ ባሬ መንግስት ባልተነሰሰ ሁኔታ ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሶባታል።

ከሁሉም በላይ ሻቢያ ወያኔን ከመፍጠሩም ባሻገር በሰው ኃይል በማጠናከር ማለትም መግቢያ መውጫውን በማሳየት፣ በማስታጠቅ በውጭ ከሚገኙ ጸረ- ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በማገናኘትና በሌሎችም መንገዶች ወያኔን አቅፎና ደግፎ ለስልጣን እንዳበቃው ይታወቃል። ሻቢያ ባይኖር ኖሮ ወያኔ እዛው የበቀለበት ደደቢት ዋሻ ደድቦ ይቀር እንደነበር የማይታበል ሀቅ ነው። ሻቢያና ወያኔ ተዛዝለውና ተደጋግፈው በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ዘመቻ ካጠናቀቁ በኋላ የባድመ ጦርነት እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ በጋራ አገሪቱን እየዘረፉ እንደገዙ ይታወቃል። በኢኮኖሚ ጥቅም መጋጨት ምክንያት የባድመ ጦርነት ከተነሳ በኋላ ወያኔና ሻቢያ ግንኙነታቸው የተበላሸ ቢመስልም፣ ሁለቱም ሻቢያም ሆነ ወያኔ አንዱ የሌላውን ህልውና ሊጎዳ የሚችል ድርጊት በተግባርና በተጨባጭ ሁኔታ ሲፈጽም አልታየም። እንደውም በመካከላቸው ቃል ኪዳን ወይም (ፓክት) ያለ በሚያስመስል ሁኔት አንዱ ሌላውን ሲጠብቅና ሲከላከል ነው የሚታየው። ለምሳሌ ያህል በ1997 ዓ.ም. ቅንጅት በምርጫ ባሸነፈበት ወቅት ወያኔ “ሻቢያ ሊወጋን ነው” በሚል ማታለያ አገራዊ አጀንዳ ለመቅረጽና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ለማግነት በተንቀሳቀሰበት ወቅት ሻቢያም በበኩሉ ሰራዊቱን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በማስጠጋት ወረራ የሚፈጽም በማስመሰል ለወያኔ ፕሮፓጋንዳ ማረጋገጫ አሳይቷል።በማያሻማና በማያወላዳ ሁኔታ አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚቻለው ሻቢያና ወያኔ ተዛዝለውና ተደጋግፈው ኢትዮጵያን እንደተቀራመቷት ሁሉ፤ ሁለቱም በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚችሉት ይህ የኃይል ሚዛን ሲጠበቅ እንደሆነ በደንብ አምነውበት ሥራ ላይ አውለውት እየተሰራበት ይገኛል።

“የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በወያኔና ሻቢያ መካከል አይሰራም በበርካታ ዓለም አቀፍ ግጭቶችና ጦርነቶች ውስጥ ሥራ ላይ የዋለው“የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚለው አካሄድ በወያኔና ሻቢያ መካከል መካካል ግን አይሰራም። ምክንያቱም ወያኔና ሻቢያ እርስ በርስ የተቆላለፈና የተሳሰረ ጥቅም እንጅ ጠላትነት የላቸውም። መሬት ላይ በመታየት ያለው ሀቅ የሚያሳየው ሁለቱ ቡድኖች መግባባታቸውን እንጅ ጠላትነታቸውን አይደለም። ኤርትራ ውስጥ አሉ የሚባሉት የኢትዮጵያ “አርበኞች/ ተዋጊዎች” ተጠናክረው የወያኔን ህልውና ላይ አደጋ ለመጣል የሚያስችል አቅም ያለው እንቅስቃሴ ቢፈጥሩና ለዚህም ሻቢያ ቢረዳቸው፣ አለምንም ማመንታትና መዘናጋት ወያኔ 100% ማለት እችላለሁ ድንበር ተሻግሮ በመግባት ሻቢያን ይደመስሰው ነበር። ሻቢያም በግዛቱ ውስጥ ከ 20 ዓመታት በላይ የኦነግና የአርበኞች ግንባር ተዋጊዎች አሉ እየተባለ ወሬው ቢናፈስም፣ወያኔን የማያስቆጣውን “የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ” (ትሕዴን/ደምህት) ነው በሰው ኃይል፣ በስልጠናና በትጥቅ ያጠናከረው። ያም ሆኖ ትሕዴን ወያኔ ላይ አደጋ ለማስከተል የሚበቃ አቅም እንደሌለው ይነገራል። ሻቢያ ሥልጣን ከወያኔ የሚነጥቅና በአሁን ጊዜ ያለውን በኢትዮጵያና በኤርትራ ውስጥ ያለውን የትግሪኛ ተናጋሪዎች የበላይነት የሚያዛባና የሚቀይር እርምጃ ማለትም የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ ወይም የአማራ ግንባሮችን አላጠናከረም። በወያኔም በኩል ያሉት የሻቢያ ተቃዋሚዎች ከወሬና በየሆቴሉ ድዳቸውን ከማስጣትና ጣራ ሲቆጥሩ ከመዋል ያለፈ ነግር ሲሰሩ አልታዩም፣ ሊሰሩም አይችሉም።

ወያኔ እነዚህን የሻቢያ ተቃዋሚዎች አጠናክሮ በመደገፍ ሻቢያ ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረስ ይችል ነበር። ሆኖም ወያኔ የሻቢያን ተቃዋሚዎች ሲጣሉ ከመሸምገልና በየአረቄውና በየሆቴል ቤቱ ከማሽሞንሞንና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ መጠቀሚያ ከማድረግ ያለፈ ነገር አልሰራም፣ ወደፊትም ይሰራል ተብሎ አይጠበቅም። እንደውም እንደ ስብሐት ነጋ ያሉ የወያኔ ቁንጮዎች አሁንም የሚናገሩት በፊትም ለኤርትራ ነጻነት ተዋግተናል፤ ኤርትራ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ችግር ቢፈጠር አሁንም እንዋጋለን ብለው በሁለቱ መካከል ያለውን የግንኙነት መጠን ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ሻቢያም ሆነ ወያኔ ተዝዛለው ወደ ሥልጣን ኮርቻ እንደወጡ፤ አንዱ ከሌለ ሌላው እንደማይኖር ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በግዛታቸው ላይ ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ አቅም ያለው ተቃዋሚ እንዲያቆጠቁጥ አይፈልጉም። ከዚህም በላይ ወያኔና ሻቢያ ባላቸው ያለመጠፋፋት ስምምነት ወይም ህልውናቸውን አስመልክተው በወሰዱት የጋር ግንዛቤ ለወደፊት ሊነሳባቸው የሚችለውን ተቃዋሚዎች/ተዋጊዎች ትግል አስቀድመው ለማኮላሸትና እንዲሁም እነዚሁ ተቃዋሚዎች ለወደፊቱ ሊያገኙ የሚችሉትን ሕዝባዊ ድጋፍ ለማጨናግፍና በሕዝብ ዘንድ ሊኖራቸው የሚችለውን አመኔታ ለማሳጣት ተልካሻና የማይረቡ ነጻ አውጭ ተብየዎችን በግዛቶቻቸው አሉ በማስባል ማወናበዱና ማዘናጋቱ ለሁለቱም ጥቅም እየሰጣቸው ይገኛል።

ግንቦት ሰባትና ሻቢያ

ግንቦት ሰባት የትጥቅ ትግል ጀመርኩ ካለ ሰባት ዓመታት በላይ ቢሆነውም አንድ መንደር ከወያኔ ነጻ ያላወጣ ወይም የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቆ በመግባት አንድ የወያኔ ጆሮ መቆንጠጥ እንኳ ያልቻለ በቅዠት ዓለም የሚዋትት ድርጅት ነው። በጎረቤት አገር ተረድተው ነጻ የወጡ ወይም የሚፋለሙትን አገዛዝ ወጥረው የያዙ በርካታ ግንባሮች ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ የጎረቤታችን የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጭዎች በዩጋንዳና ኬንያ በመረዳታቸው ምክንያት ተሳክቶላቸው አገራቸውን ነጻ አውጥተዋል። ወያኔና ሻቢያም በሱዳን በመደገፋቸው ያቀዱትን አሳክተዋል። ወያኔና ሻቢያ በመጨረሻ አዲስ አበባ ሲገቡ የሱዳን መንግሥት ታርጋ የተለጠፈባቸው ታንኮችና የጭነት መኪኖች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይታዩ እንደነበር እናስታውሳለን። በትክክል የሚረዳ የጎረቤት አገር እንዲህ ነው እርዳታውን የሚያሳየው። ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም እንደሚባለው ሻቢያ የኢትዮጵያን ተዋጊዎች ለመርዳት ቢፈልግ ኖሮ እስከ አሁን ድረስ አንድ የተጨበጠ የትጥቅ ትግል የሚያካሂድ ጠንካራ ሰራዊት ማቋቋም ያስችል ነበር።እውነተኛ ድጋፍ ከኤርትራ ቢገኝ ኖሮ ወይም እውነተኛ ተዋጊ ቢኖር ኖሮ ቢያንስ የኤርትራን መሬት በደጀንነት በመጠቀም ሰርጎ ገቦችን አሾልኮ በማስገባትና የሽምቅ ጦርነት በወያኔ ላይ ለማድረግ ይቻል ነበር። የዚህ ዓይነት ሁኔታ ለምሳሌ ከ1968 እስከ 1971 ባሉት ዓመታት “የምዕራብ ሶማሌ ነጻ አውጭ ድርጅት” ይባል የነበረው ድርጅት ከሶማሊያ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አቋርጦ በመግባት ጥቃት ይፈጽም ነበር። ይህ ሊሳካለት የቻለው የሲያድ ባሬ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ጠላትነት ምክንያት “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በማለት የኢትዮጵያን ጠላት የነበረውን የምዕራብ ሶማሌ ተዋጊዎችን በመርዳቱ ምክንያት ነው።

ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ባዶ ጭኽት የሚያሰማንና የህልም እንጀራ የሚቀልበን ግንቦት ሰባት እንደ ካሮት ወደታች የሚያድግ ካልሆነ በስተቀር እስከ አሁን ድረስ አንድም ተጨባጭ ነገር ሲሰራ አልታየም። ወደፊትም ሊሰራ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። በጣም የሚያሳዝነው ግንቦት ሰባት እውነተኛ ትግል የሚያደርግና ኤርትራ ውስጥ ጠለላና ከለላ የሚያገኙ መስሏቸው ኤርትራ በመሄድ ለመታገል ቆራጥነቱን ያሳዩ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን በሻቢያ እየተለቀሙ ሲገደሉ፣ ደብዛቸው ሲጠፋ፣ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው፣ ሲታሰሩና ሲዘረፉ ኖረዋል። ግንቦት ሰባት ለዚህ ወንጀል ተቃውሞ ማሰማትና ተቆርቋሪነት ማሳየት ሲገባው ሻቢያን ላለማስቀየም በማለት ትንፍሽ አላለም። በዚህም መሠረት ግንቦት ሰባት የወያኔና ሻቢያ የኃይል ሚዛን አስጠባቂ በመሆን የማዘናጋትና የማልፈስፈስ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ለመገንዘብ አያዳግትም። በተለይም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለወያኔ ተላልፈው የተሰጡበት እጅግ አጠራጣሪ ሁኔታና ተላልፈው ከተሰጡም በኋላ ከግንቦት ሰባት የተላለፉትን ተአማኒነት የጎደላቸው መግለጫዎች በጥንቃቄ ብንመረምር ግንቦት ሰባት ወያኔን በትጥቅ ትግል ለመጣል ፍላጎቱም ሆነ ዓላማው አለመሆኑንን ለማረጋገጥ አያደግትም።

ማጠቃለያ

ሻቢያ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች መጠናከርና ሥልጣን መጨበጥ በጣም የሚያሰጋውና እንቅልፍ የሚነሳው ነገር እንደሆነ ከላይ በዝርዝር ተጠቁሟል። በአንጻሩም የአንድነት ኃይሎች የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች መለያየትና የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን ያንገበግባቸዋል። ስለሆነም የአንድነት ኃይሎች ሥልጣን ቢጨብጡ የሚያደርጉት ነገር በመጀመሪያ እነዚህን የተበላሹ ነገሮች ማስተካከል ነው። ታዲያ ሻቢያ ምኑ ሞኝ ነው የለመደውንና ባህርዩን የሚያውቀውን ወያኔን በሌላ በአመለካከትና በእምነት በሚቃወመው ኃይል የሚተካው? “ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶሮህን በቆቅ ቀይር” እንደሚባለው ሻቢያ ምኑ ሞኝ ነው ኮትኩቶ ያሳደገውን ወያኔን በሌላ የሚቀይር? የአርበኞች ግንባር፣ ግንቦት ሰባትና የተለያዩ የኦነግ አንጃዎችና ሌሎችም በሻቢያ እርጥባንና ምጽዋት ወያኔን እንጥላለን ብለው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እስከዛሬ ድረስ በተግባር በተረጋገጠው መሠረት ያስመዘገቡት ምንም ዓይነት ውጤት ስለሌለና የሻቢያ መሳሪያ በመሆን የኢትዮጵያን ህዝብ እያወናበዱ ስለሆነ ሁላችንንም ኢትዮጵያውያን በቃችሁ ልንላቸው ይገባል።

በቀረበላቸው የተሳሳተ መረጃ ተወናብደው ለአገራችን ለኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል ለማድረግ ወደ ኤርትራ የወረዱ አገር ወዳድ ግለሰቦች ሻቢያ አሁንም ጽረ ኢትዮጵያ መሆኑን ተረድተውና ትግሉም መደረግ ያለበት አገር ውስጥ መሆኑን አውቀው፣ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ መውሰድ ይኖርባቸዋል። በወያኔ ላይ የሚደረገው ትግል ወደ አገር መመለስ አለበት። ኤርትራ ውስጥ ነጻ አውጭዎች አሉልን የሚለው ማዘናጊያና ማጃጃያ በአስቸኳይ መቆም አለበት። ኤርትራ ውስጥ በሻቢያ ደብዛቸው የጠፋው ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህና ሌሎችም የት እንዳሉ ማሳወቅ የግንቦት ሰባትና የአርበኞች ግንባር ኃላፊነት ነው።

እጅግ የሚያስተዛዝበው ለታሪክ ፍርድ የሚተወው ጉዳይ አስመራ ድረስ ተጉዘው የኢሳያስ አፈወቂን ጫማ ስመው የተነገራቸውን ውሸት ጠጥተው የመጡ ጋዜጠኞች ኤርትራ ውስጥ በእስር ለሚሰቃዩና ለጠፉ ኢትዮጵያውያን ለይስሙላ ከሚያወሩት በስተቀር ምንም ዓይነት ርህራሄ አለማሳየታቸው ነው። ኢሳያስ አፈወቂን እያደነቁና እያቆላመጡ በአንጻሩ የአንድነት ኃይሎች በአገራችን ጉዳይ የሚሰማንን እንዳንተነፍስ ማጥላላታቸውን ማቆም ይገባቸዋል። ማንም ግለሰብም ሆነ ቡድን አሥመራም ሆነ አቆርዳት ወይም ሰዋ ሄዶ የፈለገውን ማድረግ መብቱ ነው። በአንጻሩም ህዝብም ደግሞ የቀረበለትን መረጃ ትክክለኛነት የመመርመር፣ የመጠየቅ፣ የመቃወምና የማውገዝ መብቱ ሊጠበቅለት ይግባል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s