የፓርቲዎቹ ጉባኤዎች (ይገረም አለሙ)

ይገረም አለሙ

ሰሞኑን ህውኃትና የፈጠራው ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሂደዋል፡፡ የህውኃት ጭንብል የሆነው ኢህአዴግ ጉባኤም ይቀጥላል፡ከእነዚህ ጉባኤዎች የሚጠበቅ አዲስ ነገር ባለመኖሩ መነጋገሩ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም እኔ በዚህች ጽሁፍ የማነሰው የሀገራችንን የዴሞክራሲ ተስፋ በማጨለሙ በታሪክ ሲጠቀስ ሊኖር የሚችለው ምርጫ 2007 ማግስት ስለተካሄዱ የአራት ተቀዋሚ ፓርቲዎች (በሀገር ውስጥና በውጪ) ጉባኤ ነው፡፡

ጠቅላላ ገባኤ የፓርቲ የመጨረሻው የሥልጣን አካል እንደመሆኑ ሲሰበሰብ ያለፈን ገምግሞ የወቅቱን ሁኔታ ፈትሾ ወዴትና አንዴት እንደሚኬድ አቅጣጫ አመላክቶ ውሳኔዎች እንዲያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ጉባኤዎች ፍጻሜ በኋላ ያነበብነውም ሆነ የሰማነው እንደስከዛሬው ሁሉ ጉባኤ አካሄድን ከሚለው የፕሮፐጋንዳ ፍጆታ የዘለለ ቁም ነገር አለመከናወኑን ነው፡፡ ጉባኤ በመተዳደሪያ ደንብ ላይ በይህን ያህል ግዜ ይካሄዳል ስለተባለ ብቻ የሚከናወን ከሆነ ለጉባኤው ማካሄጃ የሚወጣውን ገንዘብ ያህል እንኳን ቁም ነገር የሚሰራ አይሆንም፡፡ በመሆኑም የአራቱም ፓርቲዎች ጉባኤዎች መሬቱ የሚፈልገውን ትቶ አራሹ ያሻውን ዘራ ይሉ አይነት ስራ ነው የተሰራባቸው፡፡ እስቲ በትንሽ በትንሹ በተናጠል አንያቸው፡፡

የኢህፓ ጉባኤ ፤በዚህ ጉባኤ አንድ ታላቅ ቁም ነገር ተከናውኗል፤ተበታትነው ግን በአንድ ኢህአፓ ስም ይጠሩ የነበሩ ፓርቲዎችን ወደ አንድ በማምጣት ኢህአፓ አንድነት በሚል ስም ለመንቀሳቀስ የተደረሰበት ስምምነት በጎ ተግባር ነው፡፡ለመለያየት ምክንያት የሆኑ ነገሮች ተመርምረው ዳግም ያ መለያየት መቼምና በማንም እንዳይከሰት የሚያስችል መተማመን ተፈጥሮ የተፈጸመ ከሆነ ይህ ምስጢር አይደለምና ቢገለጽ የእንቧይ ካብ እየሆነ ለሚያስቸግረው ለፓርቲዎች እየተባበሩ መለያየት እየተገነቡ መፍረስ ትምህርት በሆነ ነበር፡፡

ጉባዔው የኢትዮጵያን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት ከገመገመ በኋላበማለት የዘረዘራቸው 15 የሚደርሱ ጉዳዮች በሙሉ ወያኔ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሳቸው በደሎች ናቸው፤ እነዚህ ከቃላት በላይ በቀን ከቀን ህይወታችን የምናያቸው በመሆናቸው አዲስ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ኢህአፓ በአንድ ወቅት የትግሉ ግንባር ቀደም ተሰላፊ የነበረና የከተማውንም የጫካውንም ትግል የሞከረ ከአርባ አመት ለሚበልጥ ግዜም በሂደቱ ውስጥ ያለ እንደመሆኑ በተለይ ባለፉት ሀያ አራት አመታት ከወያኔ ጋር የተደረጉ ትግሎች መስዋእትነት እንጂ ውጤት ማስገኘት ያልቻሉበትን ምክንያት መርምሮ ችግሮችን ማሳየት መፍትሄውንም ማመላከት ከወያኔ አገዛዝ የመላቀቂያውን ስልትና መንገድም መጠቆም በቻለ ነበር፡፡ የወያኔን ድርጊትማ በተግባር እያየነው ነው፡፡

ጉባኤው ስለ ቀጣይ ሁኔታ ሲገልጽም ጉባዔው የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ሀገር አፍራሽና አጥፊ ፖሊሲዎቹን በጥብቅ አውግዟል። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት፣ የወያኔ/ኢህአዴግን አገዛዝ ማስወገድ እንደሚገባ አረጋግጦ የበለጠ ተጠናክሮ መታገል እንደሚገባ በድጋሚ አረጋግጧል። ይላል፡፡ ይህ ማንኛውም የወያኔ አገዛዝ የአንገሸገሸው ኢትዮጵያዊ የሚለው ነው፡፡ ከአንድ ያውም የረዥም ግዜ ልምድ ካለው ፓርቲ ጉባኤ መወጣት የነበረበት በሀያ አራት አመታት ትግል የወያኔን አገዛዝ ማስወገድ ያልተቻለው በእነዚህ ምክንያቶች ነው፤እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ይህን ይህን ማድረግ ያስፈልጋል፤ እንዲህ ካደረግን በዚህ ስልትና መንገድ መጓዝ ከቻልን ለድል እንበቃለን፤ይህን ለማድረግም ፓርቲያችን የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፣ወዘተ የሚል መሆን ነበረበት አልሆነም፡፡ በመሆኑም የተበታተኑትን ማሰባሰብ ችሎ ካልሆነ በስተቀር ከጉባኤው የሰማነው አንዳችም አዲስ ነገር ባለመኖሩ ተስፋ አልሰነቀብንም፡፡

ሸንጎ፣ ሸንጎው ከጉባኤው በኋላ ባወጣው መግለጫ ለመመስረት ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ሲገልጽ …. ሸንጎ እንዲመሰረት ያስገደደው ዋና የፖለቲካ አደረጃጀትና የአመራር ክፍተት የተበታተነውና እርስ በእርሱ የሚጠላለፈው አገር ወዳድ ተቃዋሚ ኃይል ተባብሮ፤ ተመካክሮ፤ ተናቦ፤ ተደራጅቶ፤ ብቁነት ያለው አመራር መስርቶና የጋራ ሰነድ አዘጋጅቶ በተከታታይ ትውልድና ታሪክ ሊጠቀስ የሚችል አስተዋፆ ለማድረግ ሲችል ብቻ ነው የሚል እምነት ስላለው ነው። ብሏል፡፡ ነገር ግን ይህን ለመመስረቱ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ምን ያህል እንዳሳካ ፣ምን ተግዳሮት እንደገጠመው፣ በሂደት ከተገነዘበው ተነስቶ ምን መደረግ እንዳለበት አላሳየም፡፡

በስልጣን ላይ የሚገኘው የህወሓት/ኢህአደግ አገዛዝ ለዴሞክራሲ መስፈን፤ ለእርጋታ፤ ለሰላም፤ ለዘላቂና ፍትሃዊ እድገት እንቅፋት የሆነ ስርዓት በመሆኑ መወገድ እንዳለበት መቀበልና ያልተቆጠበ ጥረትና አስተዋፆ ማድረግ ናቸው። የሚልም በመግለጫው ወስጥ ተጽፎአል፡፡ የወያኔን ማንነትና ምንነት በመናገር ረገድ ችግርም ልዩነትም የለም፡፡መወገድ ያለበት በመሆኑም እንደዚሁ፡፡ እንዴትና በምን ሁናቴ የሚለውና በተለይም ከቃል ይልቅ ተግባር ላይ መገኘቱ ነው ችግሩ፡፡ ወያኔን የሚያል 17 አመት ገሎና ሞቶ በጠመንጃ ሥልጣን የያዘና ሀያ አራት አመታት በምርጫ እያጭበረበረ በጠምንጃ ሥልጣኑን አስከብሮ የኖረ ሀይል በጥረትና በአስተዋጽኦ ከቤተ መንግሥት ይወጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ጥረት ሳይሆን ትግል፣ አስተዋጽኦ ሳይሆን መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ነው በሸንጎ ጉባኤ መግለጫ ላይ የሰፈሩት ለለውጥ ሊታገል ከተደራጀ ወይንም የተደራጁ ኃይሎችን ካሰባሰበ ድርጅት ጉባኤ የወጡ ያልመሰሉት፡፡

የሸንጎ ጉባኤ ያለፉትን ትግሎች አደረጃጀት ስልትና ተግባራዊነት ገምግሞ ውጤት አልባ ያደረጋቸውን ምክንያት ተረድቶ መፍትሄ ማመላከት የትግል አይነትና ስልት መንደፍና የተግባር መንገድ ማሳየት ነበረበት፡፡

መድረክ፤ መድረክ በዚህ ስሙ ሁለት ምርጫዎች የተወዳደረ ለ99.6 እና ለመቶ በመቶ ውጤት ባለድርሻ እንደመሆኑ፤በተናጠልም አንዳንዶቹ በተቀዋሚነት የወያኔን የሥልጣን እድሜ ያህል የቆዩ እንደመሆናቸው በዚህ ወቅት የተጠራው ጉባኤ በሰማነው መልኩ የምናውቀውን የወያኔን ድርጊት ነግሮን የተለመደውን ውግዘት አሰምቶን መጠናቀቅ አልነበረበትም፡፡ ለመሆኑ መቼ ይሆን ራስን ማየት የምንደፍረው፡፡

ወያኔ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ለማለት የበቃው አጭበርብሮ ቢሆን ተወዳድሮ ነው፡፡ ዋንኛ ተፎካካሪ እየተባለ ሲገለጽ የነበረው ደግሞ መድረክ ነውና ለተገኘው ውጤት ባለድርሻ ነው፡፡ ስለሆነም በጥቅሉ መድረክ በተናጠል አባል ድርጅቶች በምርጫው ወቅት የነበራቸው ድክመትና ጉድለት በጉባኤው በድፍረት መፈተሽ ነበረባቸው፡፡ የ2002 የ99.6 ሽንፈት ሳይፈተሸና ትምህርት ተወስዶ ዝግጅት ሳይደረግ በዘልማድ ጉዞ ምርጫ ለ2007 ተገባና የመቶ በመቶ ሽንፈት መጣ፡፡ አሁንም በተድበሰበሰ ሁኔታ በሰላማዊ ትግሉ እንቀጥላለን በማለት የሚያደርጉት ጉዞ ምንም ተስፋ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ድክመት ሳይታወቅ እንዴት መሻሻል ይመጣል፡፡

መድረክ እንደ ስሙ ስራው የገነነ አለመሆኑን ባቀረባቸው እጩዎች ብዛት አይተናል፡፡የፓርላማውን ወንበር ግማሽ እንኳን የሚሆን ዕጩ ማቅረብ ያልቻለው ለምንድን ነው? በዚህ ቁጥርስ እናሸንፋለን የተባለው እንዴት ነው? ምርጫ ቦርድ ትክክለኛውን የመድረክ ዕጩዎች ብዛት ሳይናገር በደፈናው ከኢህአዴግ ቀጥሎ ዕጩዎችን ያቀረበ እያለ ሲያሞካሸው የነበረው ለማባበል ወይንስ ለማማለል፡?( መድረክ ያቀረባቸው የዕጩዎች ብዛት እንደዚህ የሚያስብል አልነበረምና) ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድንና ጠመንጃውን ካልጣለ አይሸነፍም ከተባለና እንዳልጣለ ከታወቀ በምርጫ የመሳተፉ ፋይዳ ምንድን ነው? ጫናው አባላትን ከማሰር አልፎ ወደ መግደል ሲደርስ በምርጫው መቀጠል ነበረብን ውይ? ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለመባሉ የእኛ አጃቢነት አስተዋጽኦ አላደረገም ወይ?ወደ ፊት የምንቀጥለው እስካሁን በመጣንበት አኳኋንና መንገድ ነው ወይ? ወዘተ እነዚህና መሰል ጥያቄዎች የጉባኤው መነጋገሪያ ሊሆኑ በተገባ ነበር፡፡

ይህም ብቻ አይደለም በመድረክ ስም ተሰባስበው ያሉ ፖለቲከኞች በርግጥ ለለውጥ ከሆነ የሚታገሉት በዚህ መልክ የምንፈልገውን ለውት ማምጣት እንደማይችል ከመቼውም ግዜ በበለጠ ዛሬ ተረድተናል ስለሆነም በዚህ ጉባኤ ውህደት ፈጥረናል፡ በአንድነትና በጽናት ለለውጥ ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል ብለው ማወጅ በቻሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሀገራዊ ለውጥ በላይ የእነርሱ የፓርቲ መሪነት ያሳስባቸዋልና እስሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ እንመክራለን ገና አንደራደራለን አሉ፡፡ አሳዛኝ፡፡ ሌላም ታዝበናል፡፡መድረክ ከምስረታው ጀምሮ ከተጣባው የቁጥር በሽታ ዛሬም አልተላቀቅም፡፡ በዚሁ ጉባኤ ዘገባ ላይ አንዴ የአምስት ፓርቲዎች ሌላ ግዜ የሰባት ፓርቲዎች ስብስብ ተብሎ ሲገለጽ ሰምተናል፡፡ ቁም ነገሩ ብዛቱ አይደለም ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡መድረክ ግን የቁጥር ጨዋታ ይወዳል፡፡

ሰማያዊ፤ ይህኛው ፓርቲ ምርጫ ሲወዳደር የመጀመሪያው ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ የግዜ ሰሌዳ ባወጣ ሰሞን ነጻነት ለፍትሀዊ ምርጫ የሚል ዘመቻ የጀመረው ሰማያዊ ወደ ምርጫ የገባው ነጻነት መኖሩን አረጋግጦ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እናም ወደ ምርጫ የገባው አለምንም ዝግጅት በመሆኑ ምርጫ የገባበት ምክንያት ወዶ ይሁን ተገዶ ግልጽ አይደለም::

ሰማያዊ ያወዳደራቸው እጩዎች ከመቶ የዘለሉ አልነበሩም፡፡ (ትክክኛውን ቁጥር እነርሱም ም/ቦርድም አልተናገሩ) ከእነዚህም አብዛኛዎቹ አንድነት ሲፈርስ ወደ ሰማያዊ የሄዱ ናቸው፡፡ታዲያ በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ምርጫ ውስጥ የተገባው ለምንድን ነው? የአንድነት አባላት ወደ ሰማያዊ መሄድ በፓርቲው በኩል የአቋም ለውጥ አስከትሏል ወይ ? ምርጫ ቦርድ ከመቶ በላይ ዕጩዎቻችንን አልመዘግብ አለን ፤ለቅስቀሳ የምንጽፈው ሳንሱር ይደረግብናል፤አባላቶቻችን ወከባ እየደረሰባቸው ፣እየታሰሩ ነው ወዘተ ከተባለ በዚህ አይነቱ ሂደት እስከመጨረሻው አጃቢ ሆኖ መዝለቅ ለምን አስፈለገ? ሰላማዊና ዴሞካራሲያዊ ምርጫ ለመባሉ የእኛ አስተዋጽኦ የለም ወይ? ወዘተ እነዚህና መሰል ጉዳዮችን አንስቶ የሰማያዊ ጉባኤ ሊመክርና ስለ ቀጣዩ የትግል ሂደት ምንነትና እንዴትነት ላይ ውሳኔ ሊያሳልፍ በተገባ ነበር፡፡የወጣቶች እየተባለ የሚነገርለት ፓርቲ በአስተሳሰብም ሆነ በአሰራር ከተለመደው መንገድ ያልወጣ መሆኑን በዚህ ጉባኤው አረጋገጠ፡፡ሳይድግ ያረጀ እንዳይሆንም ያሰጋል፡፡

ብዙ ከሚጠበቅበት ጉባኤ ከጉባኤው ጉልቶ የወጣው ዜና ኢ/ር ይልቃል በድጋሚ ተመረጡ የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሥልጣን ሽኩቻ ነበር እንዴ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ፓርቲዎችን ሁሉ እግር ከወርች እያሰረ በዳዴ የሚያስኬዳቸው የሥልጣን ጉዳይ ነው፡፡ብዙ ምለው ተገዝተው ከወንበሩ ሲቀመጡ በአንዴ ይለወጡና አጠገቤ አትድረሱ ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር አዲስ ፓርቲ በመመስረት ወይንም አዲስ ሰው ወደ መሪነት በማምጣት የሚፈታ አይደለም፡፡ወጣት ሽማግሌ ሳይል፣በፖለቲካው ውስጥ የኖረ ወይንም አዲስ የመጣ ብሎ ሳይለያይ ሁሉንም ያጠቃና ስር የሰደደ የአስተሳሰብ በሽታ አለ፡፡ስለሆነም መጀመሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ራስን ሳይለውጡ ለውጥ ማምጣት አይቻልምና፡፡ ከአራቱም ጉባኤዎች አዲስ ነገር ማየት ያልቻልነውም በዚሁ በሽታ ምክንያት ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s