መስከረም 03/2004 ዓ.ምን ሳስታውሳት… (አንዷለም -ወ- እስክንድር) – ኤልያስ ገብሩ

Andualem and Eskinder  - Sateanw 1

Andualem Aragie - Satenawመስከረም 03 ቀን 2004 ዓ.ም እኔና ጓደኛዬ አናንያ ሶሪ በወቅቱ እንሰራባት ለነበረው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ፣ በከፍተኛ ትምህርት ጉዳይ ዙሪያ ፊቸር ጽሑፍ በጋራ ለማዘጋጀት አቅደን፤ ለመረጃ ግብዓት መቅረፀ ድምጻችንን ይዘን በቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ቢሮ በጥዋት ደረስን፡፡ ለተወሰኑ ጥያቄዎቻችን መረጃ እንዲሰጡን ቀድመን ጥያቄ በማቅረብ ቀጠሮ ይዘን የነበረው ከአቶ አስራት ጣሴ ጋር ነበር፡፡ እሳቸውም ከቀጠሯችን ቀደም ብለው በቢሯቸው ተገኝተዋል፡፡ ከሰላምታ ቀጥለን ወደዋናው ጉዳያችን ዘለቅን፡፡ በዚህ መካከል የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የፓርቲው ፀሐፊ አቶ አንዷለም አራጌና በአሁን ወቅት የዘነጋሁት አንድ ሰው አቶ አስራት ቢሮ ድረስ በሩን በማንኳኳት ገቡ፡፡ከሰዓት ከሁሉም ጋር ሰላምታ ተሰጣጠን፡፡ የእነአንዷለም አመጣጥ አቶ አስራትን ጠርተው አጠር ያለች ኢ-መደበኛ ስብሰባ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ከንግግራቸው ተረድተናል፡፡ ‹‹አስቸኳይ ነው›› ስለተባለ አቶ አስራት እኛን ይቅርታ በመጠየቅ ቀጠሯችንን ከሰዓት በኋላ ማድረግ እንችል እንደሆነ በትህትና ጠየቁን፡፡ እኔ እና አናንያም ሁኔታውን በመረዳት 10፡00 ሰዓት ላይ በድጋሚ ቀጠሮ ይዘን ወጣን፡፡ በወቅቱም አንዷለም አንድ ቀልድ ፈገግ እያለ በመናገር አስቆን እንደነበረም አስታውሳለሁ፡፡
Andualem and Eskinder - Sateanw 1እኔና አናንያም ጊዜውን ለመጠቀም በሚል፣ ሽሮሜዳ አሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ወደሚገኘውና በዶ/ር ተስፋዬ ተሾመ ዋና ዳይሬክተርነት ወደሚመራው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አግባብነትና የጥራት ኤጀንሲ (Higher Education Relevance and Quality Agency) መ/ቤት በመሄድ ከህዝብ ግንኙነት ባለሙያው የምንፈልገውን የሰነድ እና የድምጽ መረጃ አገኘን፡፡ ከቀጠሯችን ቀደም ብለንም አቶ አስራት ቢሮ ደረስን፡፡ የአቶ አስራት ፊት ግን ጥዋት እንዳየነው አልነበረም፡፡ ደስ የማይል ስሜት አረብቦባቸዋል፡፡ ‹‹አንዷለምን እኮ ፖሊሶች አሁን ወሰዱት›› ብለው የሚያውቁትን ያህል ዘርዝረው ነበሩን፡፡ ‹‹ጥዋት ህጻን ልጁ ለመጀመሪያ ጊዜ ት/ቤት ገብቶለት ከሰዓት በኋላ ደስ ብሎት ከት/ቤት ሊያመጣው አቅዶ እንደነበረ ነግሮኝ፣ በጣም ያሳዝናል›› አሉ፡፡ እኛም በአቶ አስራት ቢሮ በጋራ አዘንን፡፡ በዚህ ደስ በማይልና ባልተረጋጋ ስሜት ውስጥ ቃለ-መጠይቁን ማድረግ በድጋሚ ሳንችል ቀረንና ከፓርቲው ቅጥር ግቢ ወጣን፡፡ ከቢሮው ጀምሮ እስከዋናው አስፋልት ድረስ ፊታቸውን ከስክሰው፣ ፈንጥር ፈንጠር ብለው በመቆም አካባቢውን በአይነ ቁራኛ የሚመለከቱ፣ በእኔ አጠራር ‹‹ተከታትሎ አደሮች›› ነበሩ፡፡ በዋናው የአራት ኪሎ መገናኛ መንገድ ዳር በሚገኘው ‹‹ፍሮስቲ ባርና ሬስቶራንት›› መግቢያ በር ጋር ቆሞ ከፓርቲው ቢሮ መውጣታችንን ያወቀው አንድ ጠቆር ያለ ‹‹ተከታትሎ አደር›› አፈጠጠብን፤ እኛም አፍጥጠን አጸፋውን መለስንለት፡፡ እርሱም ወዲያው አንገቱን ለማቀርቀር ጥረት አደረገ፡፡ [ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ሰዎች ይገርሙኛል፤ ልባቸው በፍርሃት ውስጥ ሆኖ፣ ሰው እንዲፈራቸው የሚያደርጉት የደካማ ሥነ-ልቦና የትግበራ ሙከራቸው በጣም ያናድደኛል]
የእኔና አናንያ ቢሮ እዚያው ቤል-ኤር አከባቢ ስለነበረ ወዲያው ገባን፡፡ ሁሉም የጋዜጣዋ ባልደረቦች እስሩን ሰምተዋል፡፡ አቤል ዓለማየሁ፣ በዚሁ ቀን፤ ቀትር ላይ የዛሚዋን ሚሚ ስብሐቱ ‹‹እነአንዷለም ይታሰሩ›› የሚል ይዘት ያለው ‹‹የእስር ዋረንት›› ዘመቻዋን ካደመጠ በኋላ ከሰዓታት በፊት ለአንዷለም ስልክ ደውሎለት እንደነበረ በቁጭት ሲናገር አደመጥነው፡፡ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን መታሰርም በዚሁ ቢሮ ውስጥ ተረዳን፡፡ ሀዘን …ዝምታ …ቁጭት …ድጋሚ የሀዘን ስሜት ….ተፈራረቁ፡፡
የጋዜጣዋ ባልደረቦች፣ ኢ-መደበኛ ኤዲቶሪያል ስብሰባ አድርገን፣ በቀጣይ ዕትም ላይ ንጹሕ ወገኖቻችንን ዋጋ እያስከፈለ ስለሚገኘው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ፊቸር ጽሑፉ እንዲደረግ ተስማማን፣ በቅዳሜ ዕትምም ተደረገ፡፡ ምሽት በሁለት ሰዓት ላይ፣ በቀድሞ የኢቴቪ ዜና እወጃ የአንዷለምንና የእስክንድርን የእስር ሁኔታ በፎቶ ግራፍ ተደግፎ ተመለከትን፡፡ ….
በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር የወቅቱን የዓረብ ሀገራት አብዮት አስመልክቶ ሙያዊ ትንታኔ እንዲሰጠን እና ከዚህም አኳያ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በእርሱ አተያይ ምን እንደሚመስልና ተያያዥ ሀገራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ከእኔ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አደርግን – በአራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል፡፡
እስክንድርን ቃለ-መጠይቅ እያደረኩለት ባለሁበት ወቅት፣ በዓለም ሀገራት ላይ ስለተደረጉ አብዮቶች አነሳስና ውልደት ታሪካዊ የዓ.ም ፍሰታቸውን ሳያዛንፍ ሲተነትን መስማቴ አስደምሞኝ ነበር፡፡ ቃለ-ምልልሱ አልቆ ቢሮ ገባሁና ወደወረቀት ላይ ልገለብጠው ስል የቃለ ምልልሱ ድምጽ የለም፡፡ በጣም ግራ ተጋባሁ፣ ከባልደረቦቼ ጋር ደጋመን ሞከርነው ግን ምንም የእስክንድር ድምጽ የለም፡፡ ለካ በስህተት ከባልደረባዬ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር የማይሰራ መቅረፀ-ድምጽ መቀያየሬን ዘንግቼው ነበር፡፡ በጣም ተናደድኩ – መሰል ነገር በጋዜጠኝነት ሕይወት የሚገጥም ነገር መሆኑን ባውቅም፡፡ ከቢሮ ወጥቼ ተረጋግቼ አሰብኩ፡፡ ያን የመሰለ ቃለ-ምልልስ መቅረት የለበትምና በድፍረት ለእስክንድር እውነቱን ልነግረው ወስኜ ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ቃለ-ምልልስ ካደረጉ በኋላ ድንገት መሰል ነገር መፈጠሩ ሲነገራቸው በጣም ይናደዳሉ፤ በድጋሚ ቃላቸውን ለመስጠት ፍቃደኛም ላይሆኑ እንደሚችሉ አውቃለሁ፡፡ እስክንድር ግን በጣም በሚገርም ደወልኩለትሁኔታ ሁኔታውን ተረድቶ በትህትና ‹‹መቼ ይመችሃል›› አለኝ፡፡ በጣም ደስ ብሎኝ በነጋታው ከሰዓት በኋላ እዚያው ቱሪስት ሆቴል ተቀጣጠርን፡፡
ቃለ-ምልልሱን ከመጀመራችን በፊት ወደእኔ ጠጋ አለና ‹‹ከጀርባህ ደህንነቶች አሉ፤ እነሱ መኖራቸውን ሳታስብ ጥያቄህን ጠይቀኝ›› አለኝ፡፡ ዞሬ አየኋቸው፤ ሁለት ናቸው፡፡ ሁለመናቸው እኛ ጋር ነው፤ እየታወቁም ፍጥጥ ብለው ሲያዩና ጆሯቸውን ሲቀርሱ ምንም እፍረት አይነበብባቸውም፡፡
ቃለ-ምልልሱ ሲጀመር ግን ረሳኋቸው፤ የእስክንድር ተመስጧዊ ትንታኔ ብዙ ነገር ያስረሳ ነበር፡፡ በመጨረሻም ደስ የሚል ቃለ-ምልልስ ከእስክንድር ጋር አደረግን፡፡ ‹‹በግሌ፣ ትንታኔህ በጣም ማርኮኛል፤ ከአንተ ጋር አንድ ቀን ተገናኝተን ካንተ ብዙ መማር የምፈልጋቸው ነገሮች አሉኝ›› አልኩት፡፡ ‹‹ኤልያስ እኔ ራሴ ካንተ ብዙ ነገር መማር እፈልጋለሁ፤ ደስ ይለኛል፤ ከአዲስ ዓመት በኋላ እንገናኛለን›› አለኝ በሚያስገርም ትህትና፡፡
መስከረም 02 ቀን 2004 ዓ.ም ለእስክንድር ደወልኩለት፡፡ ለመስከረም 05 ቀን ልንገናኝ ቀጠሮ ያዝን፡፡ ‹‹እንዲያውም አንተ ከፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን ጋር ያደረከውን ሰፊ ቃለ-ምልልስ አንብቤ በአንድ ጉዳይ ላይ ጽሑፍ አዘጋጅቻለሁ፡፡ በባለፈው ዕትም ቃለ-ምልልሴ ስለወጣ ጋዜጣው ላይ በተደጋጋሚ ቦታ እንዳልይዝ ለቀጣይ እትም አደርሳለሁ›› አለኝ፡፡
ለኮሚሽነር አሊ ‹‹አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ከኢትዮጵያ የተመዘበረ 8.4 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ ከውጪ ባንክ መገኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ምን ምላሽ አለዎት? …ብሩ በኢትዮጵያ አቅም በቃላሉ የሚታይ ነው እንዴ?!›› የሚሉ ተከታታይ ጥያቄዎችን አቅርቤላቸው ነበር፡፡ ኮሚሽነሩም ‹‹ግድ የለህም …ይ…ሄ…ን…ን ከጥያቄህ ብታወጣ? ሌላ ዓላማ ስላለው ነው፡፡ ከሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Money Laundry) ጋር አብሮ ተያይዞ የሚመጣ ነገር አለ፡፡ ለእናንተ ለሚዲያ የማይጠቅም ነገር ነው፡፡›› በማለትና ተጨማሪ ነገር መግለጽ ሳይፈልጉ የተዳፈነና የተድበሰበሰ መልስ ሰጥተውኝ ነበር፡፡ እስክንድር እንደነገረኝ ከሆነም፣ ከዚህ ጥያቄና መልስ በመነሳት፣ ይህ የተመዘበረ ገንዘብን በተመለከተ እና ኮሚሽነር አሊ ይህህን አስመልክቶ ለምን ለመመለስ እንደከበዳቸው የራሱን ምልከታ ለመግለጽ ነበር ጽሑፉን ያዘጋጀው፡፡ ግን ምን ያደርጋል በቀጠሯችን መሰረት ከእስክንድር ጋር ተገናንተን ሳንወያይ እና ጋዜጣዋ ላይ ሙስናን አስመልክቶ እንዲታተም ያዘጋጀውን ጽሑፍ ሳይሰጠኝ ነበር ልክ የዛሬ አራት ዓመት የበኩር ልጁን ከት/ቤት አውጥቶ ወደቤታቸው ሊሄዱ ሲሉ ነበር በግፍ በፖሊሶች የተያዘው! ልክ የዛሬ አራት ዓመት ነበር፣ ውድ ልጁን ከእጁ መንጭቀው በህጻን ልጁ ፊት የብረት ካቴና ያጠለቁለት! የአብራኩ ክፋይ የሆነው ናፍቆት እያለቀሰ ነበር ይዘውት ወደቤቱ ለብርበራ ያመሩት፡፡ አንዷለምም ቢሆን ት/ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የገባለትን ልጁን እንደአባት ከትምህርት ቤት በደስታ ሊያወጣው እንደናፈቀ ነበር ወደማዕከላዊ የተላከው፡፡
እንግዲህ እንዲህ ነች ኢትዮጵያ ሀገራችን!!!
…..እናንተ የህሊና እስረኞች፡- አንድ ቀን ከእስር የምትፈቱበትንና ከውድ ቤተሰቦቻችሁ እና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የምትገናኙበትን ቀን እሻለሁ!!!
በእስራችሁ ሳቢያ ከባድ ዋጋን በመክፈል ላይ ለሚገኙት ውድ ቤተሰቦቻችሁም በሙሉ፣ ፈጣሪ ይበልጥ ውስጣዊ ጥንካሬን ይስጣቸው፤ ተስፈኛም ሁኑ እላለሁ!!!

– See more at: http://www.satenaw.com/amharic/archives/10531#sthash.iy2IbPKr.dpuf

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s