በ1857 ዓ.ም በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን በኢትዮጰያ የመጀመርያው የቁንጅና ውድድር በጎንደር ከተማ ተደርጎ ነበር፡፡

የዛሬ አንድ መቶ ሃምሳ አንድ ዓመት በ1857 ዓ.ም በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን እንዲህ ሆኖ ነበር፡፡
የመስቀል በዓል በዋለ በሁለተኛው ቀን በዓሉን ምክንያት በማድረግ ምናልባት በኢትዮጰያ የመጀመርያው የቁንጅና ውድድር በጎንደር ከተማ ተደርጎ ነበር፡፡ ከልደታ ምሥራቅ ለአበራ ጊዮርጊስ ሰሜን ከሆነችው በቀሃ ወንዝ አጠገብ ከምትገኘው አጤ ሰቀላ ከምትገኘው ኮረብታ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ ሸራ ድንኳን ተተከለ፡፡ ከጧቱ ከሶስት ሰዓት ጀምሮ በዓሉ ወደሚከበርበት ሜዳ የከተማውና የገጠሩ ሕዝብ ይጎርፍ ጀመር፡፡

4 ሰዓት ሲሆን ምርጥ መሣርያ የያዙ ወታደሮች እና አጋፋሪዎች ሰለፈኛውን ለማስተናበር ጸጥታውን ለማስከበር በበዓሉ ሜዳ ተሠማሩ፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬ በሠራዊቱ ታጅቦ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ አጤ ሰቀላ ደረሰና የዙፋኑን አቀማመጥ ተመለከተ፡፡ እንዲሁም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በፈረሶች በሚሳብ ሠረገላ ተቀምጠው ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል ባሠለጠናቸው ወታሮች እየታጀቡ መጥተው በዙፋናቸው ላይ እንደተቀመጡ እምቢልታ እና መለከቱ ተብላላ፡፡ ነጋሪት አጅብር አጅብር ውጋው ውጋው እያለ ይጎሰም ጀመር፡፡

ዘፋኞች ይዘፍናሉ፡፡ አዝማሪዎች ይዘምራሉ፡፡ ወታደሮች ይጨፍራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ይዞታ ተድላ ደስታ ሆኖ ሲደባለቅ በመካከሉ ለውድድሩ የታጩት ወይዛዝርት ጥልፍ ቀሚሳቸውን እያንሰረተቱ፣ ተቀብተው፣ ተኩለው ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ ያልፋሉ፡፡ ቀጥሎም ምርጫው በሚፈጸምበት ጎል እየገቡ ውበታቸው እና ደም ግባታቸው፣ የላሕየ ገጻቸው አወራረድ፣ የፀጉራቸው ሥሬት፣ የቁንዳላቸው እርዝመት፣ ሽንጣቸው ዳሌያቸው እና ተረከዛቸው እየተመረመረ የምርጫው ሥነ ሥርዓት ይጀመራል፡፡

በመካከሉ በሰቀልት ወረዳ ከመቋሚያ ማርያም የመጣችው ትውልዷ ከመቄት አዝማቾች ወገን የሆነ የደጃዝማች ይልማ አሰፋ ልጅ ልጅ፤ ጣይቱ ይልማ አንደኛ ስትሆን፤ እንዲሁም ከጎንደር አዲስ ዓለም የመጣችው የመሐመድ ኩርማን ሚስት የሼህ መሐመድ ጌታ ልጅ ተዋበች በጠጉሯ ማማር፣ በቁንዳላዋ አወራረድ እና መርዘም ሁለተኛነትን አግኝታለች፡፡

ከዚህ በኋላ ዮሐንስ ቤል እና ፊታውራሪ ገብርዬ የምርጫውን ውጤት ለንጉሠ ነገሥቱ ለመንገር ወደ ዙፋኑ ይቀርባሉ፡፡ ወዲያውም ጣይቱ ይልማ አንደኛ፣ ተዋበች መሐመድ ጌታ ሁለተኛ ከገለጹ በኋላ ተመራጮች ከዙፋኑ ፊት በመቅረብ እጅ እየነሡ ሽልማታቸውን ተቀብለው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖ በሰባት ሰዓት እንደተለመደው ለመሳፍንት፣ ለሊቃውንት፣ ለመኳንንትና ለካህናት የምሳ ግብዣ ተደረገ፡፡ ከውድድሩ በኋላ ጣይቱ ይልማ (ወርመር) ኦርማኤል የተባለውን በጋፋት የመድፍ ሠራተኞች አለቃ በሚስትነት አግብቶ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ወልደዋል፡፡ አሁንም ጋይንት ውስጥ በኦርማኤል ስም የሚጠራ መሬት አለ፡፡

ምንጭ፦ የቋራው አንበሳ አባ ታጠቅ ካሣ ከተሰኘ በገሪማ ታረፈ የተጻፈ መጽሀፍ
በተጨማሪም ጻዉሎስ ኞኞ በፃፉት አጼ ቴዎድሮስ በሚለዉ መጽሃፍ ዉስጥም ይህ ታሪክ ተገልፆል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s