አቡነ ቴዎፍሎስ ‹ያላረፉት› ፓትርያርክ – ከዳንኤል ክብረት


fiseha desta

ሰሞኑን የቀድሞው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የጻፉትንና ‹አብዮቱና ትዝታዬ› የተሰኘውን መጽሐፍ ሳነብብ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ አሟሟት የጻፉትን አገኘሁ፡፡ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ እስካሁን ከጻፉት የቀድሞ ባለሥልጣናት በሁለት ነገር ተለይተውብኛል፡፡ የመጀመሪያው በቡድንና በጋራ ለሠሯቸው ስሕተቶች ይቅርታ መጠየቃቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሁሉም ወገኖች የተፈጠሩትን ያለፉትን ስሕተቶች ለማረም ያስችላል ያሉትን የጋራ መድረክ ሐሳብ ማቅረባቸው ነው፡፡

ምንም እንኳን በዘመነ ደርግ የተፈጠሩት ስሕተቶችና ጥፋቶች ደርግ ብቻውን ያደረጋቸው ባይሆኑም አንዱና ዋነኛው ተዋናይ ደርግ ነበርና ለተሠሩት ጥፋቶች ይቅርታ መጠየቃቸው ለሌሎች አካላትም አርአያነት ያለው ነው፡፡ ዋናው የደርጉ መሪ ያ ሁሉ ጥፋት ሲሠራ ‹እኔ አላውቅም ነበር›› ብለው በካዱበት ሁኔታ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የራሳቸውን ይቅርታ መጠየቃቸው ለሰማዩም ለምድሩም ጉዟቸው ምትክ አልባ ተግባር የሚሆን ነው፡፡ ክብር ይስጥልን፡፡

ያ ዘመን በተሻለ እንመራለን ብለው የተነሡ ፖለቲካዊ ኃይሎች እንደየዐቅማቸው ስሕተቶችን የሠሩበትና ጥፋቶችን ያጠፉበት ዘመን ነው፡፡ ሁሉንም ጥፋት ለደርግ በመስጠት እጅን መታጠብ አይቻልም፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም የደርግን ባለ ሥልጣናት ብቻ ወደ ፍርድ ከማቅረብ ይልቅ የነበረው ጥፋት ከየአቅጣጫው የሚፈተሽበትና ሁሉም እንደ ጥፋቱ የሚከሰስበት ወይም የሚወቀስበት አለበለዚያም ደግሞ ይቅርታ የሚጠይቅበት መንገድ ቢመቻች መልካም ነበር፡፡ ችግሩንም በተቻለ መንገድ ሊፈታው የሚችለው ሁሉን አቀፍ የሆነው አካሄድ ነበር፡፡ አሁንም መሪ ተዋናዮቹ ከማለፋቸው በፊት ሁሉም እንደየድርሻው ኃላፊነቱን የሚወስድበትና ይቅርታ የሚጠይቅበት ሥርዓት ቢመቻች መልካም ነበር፡፡

ያ ካልሆነ ግን ሥርዓት በተቀየረና ሕጎች በተሻሻሉ ቁጥር ተከድነው የሚንተከተኩ ነገሮች እንደገና የመውጣታቸውና በመድረቅ ላይ ያሉ ቁስሎችን የማመርቀዝ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ፕላስተር የተለጠፈበት ቁስል ሁሉ አይድንምና፡፡

ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ግን ጥያቄ እንዳነሣ ያደረገኝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የተመለከተ፡፡ በመጽሐፉ ላይ የሚከተሉት ነገሮች ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መገደል ጋር ተያይዘው ቀርበዋል፡፡

  1. 1. ቤተክህነት መሬቷ ስለተነጠቀ አብዮቱን እንደተቃወመች

abuneእግዚአብሔር የለም ብሎ የሚክደው ኮሚንስታዊ መንግሥት ሲመጣ ቤተ ክህነት ባትቃወም ነበር የሚገርመው፡፡ በተለይም የመሬት ለአራሹ አዋጅ የጭሰኛውን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ ቢሆንም የፈጠራቸውም ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በመሬት ላይ በመሆኑ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትም የመተዳደሪያ መሬት ነበራቸው፡፡ ልክ ዛሬ የመተዳደሪያ ሕንጻና ገንዘብ እንዳላቸው ሁሉ፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ስለነበሩም ለቤተ ክርስቲያን የመሬት ስጦታ ሰጥተዋል፡፡ የመሬት ላራሹ ዐዋጅ ሲታወጅ ግን የካህናትንና የገዳማውያን ሁኔታ ግምት ውስጥ ሊያስገባ አልቻለም፡፡ እንደ አንድ በመሬት የሚተዳደር ኢትዮጵያዊ ዜጋ ካህናቱና መነኮሳቱ ለአንድ ገበሬ የተመደበውን መሬት እንዲያገኙ እንኳን አልተደረገም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስም መኳንንቱ ይዘውት የነበረው  መሬት ከግምት ውስጥ አልገባም፡፡ ቢያንስ በቶፍነት ሥርዓት ውስጥ የነበሩትን ካህናት እንኳን አብዮቱ ሊያያቸው አልፈቀደም፡፡ ሲሆን ቅርስና ባሕል ጠባቂ እንደመሆናቸው በተለይ ገዳማቱ ተጨማሪ የጋራ መሬት ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ የወቅቱ የደርግ ባለሥልጣናት ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመጀመሪያው በጠላትነት ስለፈረጁ የድርሻዋን እንኳን ለመስጠት አልቻሉም፡፡ በምዕራብ ሸዋ የነበረው ደብረ ጽሙና ገዳም መሬቱን ሙሉ በሙሉ አጥቶ ሊፈርስ ሲል ኮሎኔል ደበላ ዴንሳ በሰጡት መመሪያ ጥቂት መሬት አግኝቶ መትረፉን አረጋውያኑ ዛሬም ከምስጋና ጋር ያስታውሱታል፡፡

ገዳማትና አድባራቱ ከልክ በላይ የያዟቸው መሬቶች ከነበሩ መጠኑን መቀነስና በቂ ነው የተባለውን ያህል መስጠት እንጂ ያላቸውን በሙሉ ነጥቆ በድህነት እንዲማቅቁ ማድረግ በምንም መልኩ ፍትሐዊ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ‹‹ኮሚኒዝም ማለት ድህነትን እኩል ማካፈል ነው – an even distribution of poverty›› የተባለው ነው የተፈጸመው፡፡ ፍትሐዊነት ያላገኘውን አካል እንዲያገኝ አድርጎ እኩል ማድረግ እንጂ ያገኘውን እንዲያጣ አድርጎ በድህነት ማስተካከል አይደለም፡፡ ይኼንን የወቅቱ ቤተ ክህነት ብትቃወመውና ከአብዮቱ ጋር ለመጓዝ ቢቸግራት ተገቢ ነው፡፡ ያውም በበቂ ሁኔታ አልሄደችበትም፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1967 ዓም ለዘመን መለወጫ ባስተላለፉት መልእክት ‹‹በጦር ኃይሉና በሕዝቡ የተጀመረው የተቀደሰ እንቅስቃሴ መልካም ውጤት እንዲያስገኝ ፈጣሪያችን ይርዳን›› ነበር ያሉት፡፡(ሐዲስ ሕይወት፣ ግንቦት 1፣ 1967 ዓም፣ ገጽ 17)፣ የዕድገት በኅብረት ዘመቻንም ፓትርያርኩ በበጎ ነበር ያዩት፤ ይህም ጥቅምት 3 ቀን 1967 ዓም በሰጡት መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡(ገጽ 17)

ይኼ ጉዳይ በከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ዐዋጁም ጊዜ ተከሥቷል፡፡ ብዙ ምእመናን ብጽዐት ገብተው እየሠሩ፣ ሲሞቱም እያወረሱ ለአድባራትና ገዳማት የሰጧቸው ቤቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ቤቶች በሀገር ቤት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌም ከተማ ሳይቀር ይገኙ ነበር፡፡ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ዐዋጅ ሲታወጅ ግን ለአንድ ሰው የሚኖርበት የ500 ካሬ ሜትር ቦታና አንድ ቤት ሲፈቅድ ለአድባራትና ገዳማት ግን ምን አልተፈቀደም፡፡ በሙሉ ነው የተወረሰው፡፡ ራሳቸው ፍሥሐ ደስታ እንደመሰከሩት ዐዋጁ ጠላ ሽጣ፣ ማገዶ ቸርችራ ድኻዋ የሠራቺውን፣ ኮርያና ኮንጎ ዘምተው ባገኙት የደም ዋጋ መለዮ ለባሾች የገነቡትን ሁሉ ሀብት ከተትረፈረፋቸው ጋር እኩል በመውረሱ ‹‹ብዙዎች አብዮቱን የደገፉ ጭቁኖች ከበዝባዦች ጋር አብዮቱን ያጥላሉ ጀመር››(ገጽ 160)፡፡

ከነዚህ በዐዋጁ ከተጎዱት መካከል አብያተ ክርስቲያናቱ አንዱ ናቸው፡፡ ቢያንስ የተወሰነውን ቤት እንዲያገኙ መደረግ ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ደርግ የተመለከተበት መነጽር ችግሩን እንዳያይ የሚጋርደው ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቤተ ክህነት ለውጡን በበጎ ልታየው ያልቻለቺው፡፡ በርግጥ መንግሥት 4 ሚሊዮን ብር ምትክ ካሣ ሰጥቻለሁ ብሎ ነበር፡፡ በጎላ ወስዶ በጭልፋ መመለስ ማለት እንዲህ ነው፡፡ ያውም አራት ሚሊዮን ብሩ ሳይጨመር ሳይቀነስ በደርግ ዘመን ሁሉ የኖረ ነው፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስ በ60ው ባለ ሥልጣናት የግፍ ግድያና በንጉሠ ነገሥቱ ሞት በእጅጉ አዝነው ነበር፡፡ የንጉሠ ነገሥቱን አስከሬን ወስደው በክብር ለመቅበር በነሐሴ 1967 ዓም ደርግን ጠይቀው አልተፈቀደላቸውም፡፡ ከዚህም አልፎ ለንጉሠ ነገሥቱ በይፋ የፍትሐት ጸሎት እንዳያደርጉም ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው(ፍሥሐ ደስታና ሌሎችም ቢዘሉትም)፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ከዚህ በኋላ ነው ለውጡን በሥጋት ማየት የጀመሩት፡፡

2     2. አቡነ ቴዎፍሎስ የራሳቸውን ወገኖች በመሾም በአብዮቱ ላይ ውስጥ ውስጡን ሤራ እንደሠሩ

አቡነ ቴዎፍሎስ የራሳቸውን ሰዎች ሾሙ ያሰኛቸው ሦስት አባቶችን በጵጵስና መሾማቸው ነው፡፡ ደርግ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ተለያይተዋል፤ እንዱ በሌላው ጣልቃ አይገባም ብሎ ዐወጀ፡፡ ፓትርያርኩ ይህንን ተከትለው ደርግን ሳይጠይቁ ሦስት አባቶችን ሾሙ፡፡ አቡነ ጳውሎስን፣ አቡነ ባስልዮስና አቡነ ጴጥሮስን፡፡ ሦስቱም አባቶች በነበራቸው ዕውቀት የተሾሙ እንጂ ለአቡነ ቴዎፍሎስ በነበራቸው ዝምድና አልነበረም፡፡ በሀገር ልጅነትም ሆነ በዝምድና አይገናኟቸውም ነበር፡፡ ደርግን ተደፈርኩ አስብሎ ፓትርያርኩን እንዲያሥር ያደረገው ይኼ የፓትርያርኩ ሳያስፈቅዱ መሾማቸው ነው፡፡ ያሠረውም ፓትርያርኩንና አዲስ የተሾሙትን ኤጲስ ቆጶሳትን ነው፡፡

3  3. አቡነ ቴዎፍሎስን በተመለከተ የቤተ ክህነት ሰዎች ለመንግሥት አቤቱታ አቅርበው ነበረ ፡፡

በሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ መጽሐፍ ላይ የቤተ ክህነት ሰዎች አቡነ ቴዎፍሎስን በተመለከተ ያቀረቧቸው ክሶችና አቀራረቡን ገልጠውታል፡፡ የመጀመሪያው ክስ አቡነ ቴዎፍሎስ አባ መልእክቱ ተብለው መነኩሴ እያሉ በአቡነ ጴጥሮስ ግድያ ላይ እጃቸው አለበት የሚለው ነው፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ አዲስ አበባ ከቤተሰቦቻቸው ጠፍተው የመጡት በ1920 ዓም ነው፡፡ የሄዱትም በአዲስ ዓለም ማርያም ወደነበሩት ሐዲስ ተክሌ ዘንድ ነው፡፡ ሐዲስ ተክሌ በቀለም አያያዛቸው ስለወደዷቸው አቀረቧቸው፡፡ አባ መልእክቱ ከአዲስ ዓለም ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው በ1930 መነኮሱ፡፡ ጣልያን ሀገሪቱን ሲወር እርሳቸው የመምህራቸው የሐዲስ ተክሌ ደቀ መዝሙር ሆነው በአዲስ አበባ ነበሩ፡፡

በወቅቱ የነበሩት አባቶች የጣልያን ወረራን በተመለከተ ሁለት ዓይነት ሐሳብ ነበራቸው፡፡ እንደ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ያሉት ከዐርበኞች ጋር ሆነው ጣልያንን ለመፋለምና ሀገሪቱን ነጻ ለማውጣት ወሰኑ፡፡ ሌሎች አባቶች ደግሞ ሕዝቡ ያለ እረኛ መቅረት የለበትም የሚለውን ሐሳብ ደግፈው የሊቃውንት ጉባኤ በማቋቋም ወደ ሀገራቸው የሄዱትን  ግብጻዊውን አቡነ ቄርሎስን ተክተው መሥራት ጀመሩ፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስ የአቡነ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደመሆናቸው መምህራቸውን ተከትለው ከማገልገል ያለፈ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ በተፈጸመው ግፍ እጃቸው ነበረበት የሚል ምንም ዓይነት ማስረጃ እስካሁን አልቀረበም፡፡ ደግሞም በዚያ ጊዜ በነበራቸው ሁኔታ ይህንን ለመፈጸም የሚበቃ ሥልጣን አልነበራቸውም፡፡ የጠሉትን ሰይጣን፣ የወደዱትን መልአክ ማለት ልማድ ሆኖ ጠላቶቻቸው ለውጡን ተጠቅመው ለጥብስ አቀረቧቸው እንጂ ማስረጃ ሊያቀርቡበት የሚችሉበት ነገር አልነበረም፡፡ ደርግም ማስረጃ አልጠየቀም፤ ለማጣራትም አልሞከረም፡፡ ሌ/ ኮሎኔል ፍሥሐም አገላለጣቸው ‹ቤተ ክህነቱ ስለከሰሳቸው አሠርናቸው እንጂ ነገሩ ከኛ አልመጣም› ዓይነት ነው፡፡ የአቡነ ቴዎፍሎስን ሕይወት የቀጠፈው ግን ክሱ ሳይሆን ‹ከፍርድ በፊት ወንጀለኛ የሚያደርገው› የደርግ አሠራር ነበር፡፡ በዚያ ላይም ሳያስፈቅዱኝ ሾሙ ብሎ ደርግ ምክንያት ፍለጋ ላይ ነበር፡፡

ሁለተኛው ክስ ‹በቤተ ክህነት ሤራና አሻጥር ይሠራሉ› የሚለው ነው፡፡ ምን ዓይነት ሤራና አሻጥር እንደሆነ አልተገለጠም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ በመጣ ቁጥር ሰውን የመክሰሻ ቀላሉ መንገድ ‹ለውጡን ይቃወማል፣ ያለፈውን ሥርዓት ይደግፋል፣ ውስጥ ውስጡን አድማ ይመታል› የሚሉት አቤቱታዎች ናቸው፡፡ ምግቡን ለበዪው እንዲስማማ አድርጎ ማቅረብ፡፡ ይህንን እንድገምት ያደረገኝ ክሱን ያቀረቡትን አካላት በተመለከተ ኮሎኔሉ የሰጡን መረጃ ነው፡፡ ‹ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ገዳማት ፈርመውበት ነበር›(ገጽ 199) ይላል፡፡

እጅግ አስገራሚ መረጃ ነው፡፡ ሳይበጠር ይከካ፣ ሳይለቀም ይፈጭ እንደነበር የሚያሳይ፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በ1972 ዓም ባካሄደው የሰበካ ጉባኤ ቆጠራ የኢትዮጵያ ገዳማት ቁጥር 1000 እንደነበረ ያመለክታል፡፡(ከ1966-1972 ባለው ጊዜ እንኳን አዲስ የሚቋቋምበት ያሉትም በፕሮፓጋንዳውና በለውጡ እየተንገዳገዱ ነበር) ያ ዘመን እንዳሁኑ መንገድ ያልተስፋፋበት፣ ሞባይል ስልክ የሌለበት ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱም የግርግር በመሆኑ ገዳማውያን ከበኣታቸው እንዲወጡ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ራሳቸው ፍሥሐ ደስታ እንደነገሩን ገዳማቱ ሁሉ መሬታቸውን ተወርሰዋል፡፡ እንዴት ሆነው ነው በአብዮቱ ቅር የተሰኙ 900 ገዳማት ተገናኝተው በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ ሊፈራረሙ የሚችሉት? በየቦታቸው ሆነው ፈረሙ ቢባል እንኳን ማነው በዚያ ዘመን ከዋልድባ እስከ ማንዳባ፣ ከደብረ ዳሞ እስከ ደብረ ወገግ፣ ከማኅበረ ሥላሴ እስከ ዝቋላ፣ ከደብረ ቢዘን እስከ ደብረ ሊባኖስ ተዘዋውሮ ገዳማቱን ሊያስፈርም የሚችለው(ያውም ያኔ የኤርትራንም ገዳማት ይጨምራል)፡፡ ገዳማቱ ያሉበት አስቸጋሪ አካባቢ፣ የገዳማቱ ብዛትና የወቅቱ ሁኔታ ተደምሮ 10 በመቶ ገዳማት እንኳን ሊፈርሙ አይችሉም፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ናቸው የፈረሙት እንዳንል እንኳን እነርሱም ቁጥራቸው በ1972 ዓም ከ25 ሺ በላይ ነበሩ፡፡ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው፡፡

የአቡነ ቴዎፍሎስ ሞትና አሟማት አሁንም ያልተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በሞታቸውና አሟሟታቸው ሦስት አካላት የነበራቸው ሚና አሁንም በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ ቤት ክህነት(ከጳጳሳት ጀምሮ)፣ ደርግና ሌሎች አካላት(ለምሳሌ አስያዛቸው የሚባለው ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጎፋ አካባቢ ነበረ)፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የእኒህን አባት ሁኔታ በሚገባ ማጣራት ይኖርባታል፡፡ አንድም ዋና ተዋንያን የነበሩት የቤተ ክህነትና የቤተ መንግሥት ሰዎች መረጃውን ይዘውት ጨርሰው ከማለፋቸው በፊት፤ ሁለት ቤተ ክህነቱንም ሆነ ደርግን የሚያስወቅስ ያልተሰማ መረጃ ነገ ከመውጣቱና ማጣፊያው ከማጠሩ በፊት፡፡ ቤተ ክህነት አንድ አጣሪ አካል አቋቁማ ታሪኩ የተጣራ እንዲሆን ማድረግ አለባት፡፡ የአብዮቱን ዘመን ታሪክ የምትነግሩን አካላትም መጻፋችሁ የሚያስመሰግናችሁ ቢሆንም የምትሰጡን መረጃ ግን እውነትና ሊታመን የሚችል ቢሆን በታሪክ ውስጥ የሚኖራችሁን ሥፍራ ምቾት የሚሰጠው ይሆናል፡፡

የአቡነ ቴዎፍሎስን አሟሟት በተመለከተ ሻለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስም ሆኑ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በሁለተኛው እትሞቻቸው የሚያብራሩት ነገር ሊኖር ይገባል፡፡ አዲስ እየጻፋችሁ ያላችሁም አስቡበት፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s