የባራክ ኦባማና የወይዘሮ አዜብ መስፍን ታሪካዊ ግንኙነት ይሄይስ አእምሮ

Azeb  Mesfin, wife of Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi

ጊዜው ትንሽ ራቅ ስለሚል ወሩንም ሆነ ዓመቱን አሁን በትክክል አላስታውስም፡፡ ያንን ጊዜ ዛሬ ጧት ያስታወሰኝ የዚያን ጊዜው አንዱ ልጄ የተናገረውን ነገር በጣም በተራራቀ ነገር ግን በጣም በሚመሳሰል አጋጣሚ ታናሽ ወንድሙ በሚያስደንቅና በሚያስገርም ሁኔታ በዚህች ዕለት ስለደገመው ነው፡፡ ታሪክ ለምን እንደማይሞት ዛሬ በሚገባ ተማርኩ – ከገዛ ልጄ፤ ታሪክ ራሱን እንደሚደግምም ጭምር፡፡ ለካንስ የሊቢያ እውነተኛ ባንዲራ ከ42 ዓመታት በኋላ የተነሣችው ለዚህ ኖሯል? እንግዲያውስ የኛም ብርቅዬና እየተገለባበጠች ለብዙ ሀገሮች ባንዲራነት የዋለች ሰንደቅ ዓላማችን እንደሞተች አትቀርም ማለት ነው፡፡

ሶሎሞን ተካልኝ ጎራ በቀየረና ወደ ወያኔ ገባ በተባለ ወቅት ዜናው በትኩስነት እየተስተጋባ ሳለ ያኔ ዕድሜው በአሥራዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ልጄ “ቴዲ አፍሮም እንዳይደገም” በማለት በፍሬ ሃሳቡ ብቻ ሣይሆን በፖለቲካ ግንዛቤው መዳጎስ በጣም አስገርሞኝ ነበር፡፡ አያችሁ – ታሪክ የሚጽፈው ቢጠፋ እንኳን አይሞትም – ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ሣይቀር ይተላለፋል፡፡ አባትና እናት እናት እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሲገናኙ የሆድ የሆዳቸውን የሚጫወቱት በአብዛኛው ታሪክ ቀመስ ነው፡፡ ስሆነም ትናንሾቹ የቤተሰብ አባላት ከብበው እኛን ሳይታወቀን የሚኮመኩሙት የኛን ጨዋታ ነው – ያልሰሙና ያልተከታተሉ እየመሰሉ ጭምር፡፡ በዚያም ምክንያት ያለ ውድ በግዳቸው እኛ የምንጠላውን ይጠላሉ፤ እኛ የምንወደውን ይወዳሉ፡፡ በልጆች አስተዳደግ ላይ የቤተሰብ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ የዚያኔው ሕጻን ልጄ የዛሬው … ጎረምሣ ከቤተሰቡ ሲቀስም ያደገውን ወያኔን የመጥላትና ተቃዋሚን ያለመጥላት ጠባይ የገለጠው “ቴዲ አፍሮም እንዳይደገም” በሚል ነበር – አሳስቦት፡፡ ከንግግሩ ጀርባ የሶሎሞንን ወያኔነት እንዳልወደደለት በተለይ እኔ አባቱ አሳምሮ ይገባኛል፡፡ በወያኔው ሸፍጠኝነት በተጨናገፈው የ1997ዓ.ም ብሔራዊ የቴሌቪዥን የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አንድ ዓመት አካባቢ ዕድሜ የነበረው አንዱ ሌላው ልጄ ደግሞ የቅንጅት ተራ ሲደርስ ፊቱ ፋሲካ እየመሰለና ሁለት ጣቶቹን ለማሳየት እየፈለገ ግና የቀለበት ጣቱ እያስቸገረችው ጭናችን ላይ ፊጥ ብሎ እንዴት በደስታ ይፍነከነክ እንደነበር ቤተሰቤ በሙሉ አሁን ድረስ ያስታውሰዋል፡፡ መንገድ ላይ ባለመውጣቱ ግን ጣቱ ሳይቆረጥና እንደታዳጊ ወጣት ነቢዩ ደረቱና ግንባሩ በአግዓዚ ቅልብ የወያኔ ጦር ሳይበሳሱ እስካሁን በሕይወት አለ፡፡ አሁን የማይታወሰኝ  የመግቢያ ሙዚቃ ገና ከመጀመሩ ምልክቱን እያሳዬ እንዲያ ይቅበጠበጥና ይደሰት የነበረው ምኑን ዐውቆትና ምንስ ገብቶት እንደነበር  ሲያስቡት በርግጥም ይገርማል፡፡ ምናልባት በደም ተላልፎበት? አዎ፣ ቤተሰብ እስካልጠፋ ሀገርም አትጠፋም!! ሃሌ ሉያ! ኢትዮጵያም ትነሣለች፡፡ አልሃምዱሊላህ – የሃይማኖትና የዘር ልዩነት የማይደረግባት ኢትዮጵያ ከወያኔ ከርሠ መቃብር ላይ ታብባለች – ብዙ ተምረናልና!

በነገራችን ላይ በየብሔር ብሔረሰቡ ቤተሰቦች ውስጥ በምናብ እየገባን ብንቃኝ አንዱ ላንዱ ያለውን ጥላቻና ውዴታ ልጆች ተሰባስበው በሚጫወቱበት ወቅት በሚወራወሯቸው የቀልድና የምር ቃላት በደንብ ልንረዳ እንችላለን፡፡ በአንፃራዊ ሁኔታ ይህ ዓይነቱ ክስተት የሁሉ እናትና ማረፊያ በሆነችው በእምዬ አዲስ አበባ ቀለል የሚል ቢመስልም ለወያኔው የዘር ከፋፋይ አገዛዝ ምሥጋን ይንሳውና በሌሎች አካባቢዎችና አነስተኛ ከተሞች ግን የጎላ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡

አንድ ወቅት እዚሁ አዲስ አበባ የሆነውን አሣዛኝ ነገር ልንገራችሁ፡፡ አንድ ልጅ አባቱ ይታሰርበታል፡፡ የሁለት ተኩል ወይ ግፋ ቢል የሦስት ዓመት ልጅ ቢሆን ነው ያኔ፡፡ ከቤተሰብ ጋር አባቱን ሊጠይቅ አሁን የአፍሪካ ኅብረት ወደተገነባበት የዱሮው ከርቸሌ ይሄዳል፡፡ አባቱ እስኪመጣ ታዲያ ሕጻኑ ከአንድ የእሥር ቤቱ ጠባቂ የፌዴራል ፖሊስ ጋር ጨዋታ ይይዛል – እነሱ በወያኔያዊ ተፈጥሯቸው ዐውሬ ቢሆኑም ደፍሮ የተጠጋቸውን ሕጻን መቼም ጨክነው ማባረር መጥፎ ግምት ያሰጣቸዋልና ያ ፌዴራል ፊት አልነሳውም፡፡ የሕጻን ነገር ሆነና ነገሩ ወታደሩን “እሹን ሽጠኝ” ይለዋል – ያነገበውን ክላሽንኮቭ፡፡ “ዋይ፣ ምን ይገበረልካ ማሙሼ ?”ብሎ ቢጠይቀው ሚስቶው ቋንቋ በደንብ የገባው የሚመስለው ሕጻን “ኢሃዲግን ልገልበት!” ይለዋል፡፡ አይ ሕጻንነት! ይሉኝታ የለ፤ ምሥጢር የለ፤ ሀፍረትና ፍርሀት የለ – ግልጽነት ብቻ፡፡ ወታደሩ በምንተፍረታዊ ሣቅ ቢሸፍነውም መደንገጡ ግን ያስታውቅ ነበር፡፡ እሥረኛ ሊጠይቅ የመጣው የሕጻኑ ቤተሰብም ክፉኛ ደነገጠ – በርግጥም ለጠርጣራና ጥላውን እንኳን ለማያምን የከሃዲዎችና የወሮበሎች መንግሥት አንድን ቤተሰብ በሽብርተኝነት ወንጀል ለመክሰስ ከዚህ በላይ ማስረጃ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፤ ደግነቱ ጊዜው ረዘም ስለሚል እንደምንም “የሕጻን ነገር” ተብሎ ታለፈ እንጂ “በኢቴጲያ ሁዝቮች ፈªድ ለፀደቀ ህገ መንግሥቱን በኃይሊ ለመናድ” ያ ሕጻን ያደረገው ሙከራ ቀላል አልነበረም፡፡ አለበለዚያ “ይህ ልጅ ከቤቱ እንደዚህ የመሰለ ታሪክ ባይሰማ ኖሮ እንዲህ ያለ የከረረና የመረረ ጥላቻ በዴሞክራሲያዊ መንግሥታችን ላይ ሊኖረው አይችልም ነበር” በሚል ቤተሰቡ ለእሥራትና ከዚያም ለባሰ የከፋ ችግር መዳረጋቸው አይቀርም ነበር – ወያኔን እያወቅነው! “አስበሃል” በሚል የትም የሌለ የወንጀል ዓይነት ይቅርና “ልታስብ ማሰብህን የደረስንብህ መሆናችንን ገልጸን ብናስጠነቅቅህም እምቢ ብለሃልና ፀረ ኢህወደግ ዕላማህን ከማሰብህ በፊት ለማሰብ ማሰብህን ልናስቆምህ ተገደናል” ብሎ በዓለም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ “ወንጀል” አስሮ የሚያሰቃይና ደብዛ የሚያጠፋ የማፊያ ቡድን ያለን መሆናችንን መቼም አንዘነጋም፡፡ እናም ይህ ሕጻን ለቤተሰቡ ጠንቅ ሊሆን ሲችል ፈጣሪ ታደጋቸው፡፡ ከፍላት የሚያወጣው አምላከ ኢትዮጵያ እኛንም ከነዚህ ጉግማንጉጎች በቶሎ ነፃ ያውጣን፡፡

ልጅ አስተዳደግ በማኅበረሰብ ቀረፃ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑ የሚነገረው እንግዲህ ለዚህ ነው፡፡ የፍልስጥኤምና የእስራኤል ልጆች ሒሳብ ሲማሩ “በአንድ ጥይት 50 እስራኤላውያንን/ፍልስጥኤማውንን ብትገድል በአሥር ጥይት ስንት እስራኤላውያንን/ፍልስጥኤማውያንን ትገድላለህ?” እየተባሉ እንደሚያድጉና ንጹሓንና አፍቃሪያን ሊሆኑ የሚጠበቅባቸውን ታዳጊ እምቦቀቅላዎች እየመረዙ እንደሚያሳድጉ እንሰማለን፤ ይህ ዓይነቱ ፀያፍና ኢ-ሰብኣዊ ነገር በአንድ ወይ በሁለት ሥፍራዎች የተወሰነ ሣይሆን በብዙ ቦታዎች እንደሚተገበር መገመት አይቸግርም፡፡ ተጠያቂዎቹ እንግዲህ ክፉና ደግን ለይተዋል የተባሉት ግን ወደ ክፋት ዓለም ገብተው በግል ቂም በቀልና ጥላቻ በመታወር መላ ኃይላቸውንና መላ ዕድሜያቸውን ለጠብና ለአምበጓሮ የተሠለፉ ዐዋቂ ተብየዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ዐዋቂ ማለት አስተዋይና ብልኅ ማለት ሊሆን ሲገባው በተቃራኒው መሆኑ ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል፡፡ ክርስቶስ “ሕጻናት ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው”፣ “ወደ ሕጻንነት ካልተመለሳችሁ መንግሥተ ሰማይን አትወርሱም” ወዘተ. የሚለን ትልቅ ስንሆን የሚቆራኘን ሰይጣናዊ መንፈስ በሕጻንነት ወቅት ይኖረብናል ተብሎ ስለማይጠበቅ ያኔ እውነተኛ የሰው ልጆች መሆናችንን ለማሳየት ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው – ትርጉሙ እውናዊ ሣይሆን ፍካሬያዊ ነው፡፡ እናም ሁላችንም ሕጻናት እንሁንና የጋራ ኢትዮጵያችንን እንደገና እንገንባት፡፡ ሕጻናት ቂም የላቸውም፤ ሕጻናት ስላለፈ ነገር እያነሱ እንደትልቆች አይጨቃጨቁም፤ አይወራከቡም፡፡ ለሕጻናት ትናንትናና ነገ ብዙም ዋጋ የላቸውም፡፡ ለሕጻናት ትልቅ ዋጋ ያላት ዛሬ ናት፡፡ ሕጻናት እጃቸው የገባችን ማንኛዋንም ዕድል በከንቱ አያባክኑም፡፡ ጠቀማቸውም ጎዳቸውም በጃቸው ያለ ጊዜ ወርቃቸው ነው፡፡

ከተነሣሁበት ጉዳይ በተገናኘ መልኩ ለማኮብኮብ ያህል ስለሕጻናት አስተዳደግ ከፍ ሲል በገደምዳሜ ትንሽ ሃሳብ ከሰጠሁ ዘንዳ የ15 ዓመት ዕድሜ ያለው ሌላኛው ልጄ ሰሞኑን የተናገረውን አስደናቂ ነገር ልጠቁምና ጅምሬን ልቋጭ፡፡

የርሱን የቴሌቪዥን ቻናል በኔው ፍላጎት ደፍጥጬበት አለውድ በግዱ የኔን ጣቢያ አብረን እየተመለከትን ነው፡፡ በዚያ ጣቢያ – ጥቂት ቀናትን ቆይቼ ቀደም ሲል ጀምሬው ወደነበረው መጣጥፍ በመምጣቴ ጣቢያውን በትክክል ማስታወስ አልቻልኩም ግን ኢሣት ይመስለኛል – ስለ አሜሪካውያን ፕሬዝደንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ በዜና ቀርቦ ሂደቱ እየተዘገበ ነበር፡፡ በዜናው ላይ “በአሜሪካ ህገ መንግሥት ድንጋጌ መሠረት ፕሬዝደንት ኦባማ ለሦስተኛ ዙር መወዳደር ስለማይችሉ ለተመራጩ አዲስ ፕሬዝደንት ሥልጣናቸውን አስረክበው በቀጣዩ ዓመት የፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ ቤተ መንግሥቱን  ለቀው ከነቤተሰባቸው ይወጣሉ፡፡” የሚለውን ወሬ እንደሰማን ይህ ልጄ “እሱም እንደ አዜብ እንዳይሆን” አለና እንደዋዛ ወሬ ጣል አደረገ፡፡ እኔም አትኩሮቴ በአብዛኛው ቲቪው ላይ ስለነበር የልጁን አነጋገር ከቁብ አልጣፍኩትም ነበር፡፡ ቢያንስ ለሞራሉ ስል ዝም ብዬ ላልፈው ደግሞ አልወደድኩም፡፡ ለምን እንደዚያ እንዳለ ታዲያ ፊቴን ወደሱ ሳላዞር እንደዋዛ ጠየቅሁት፡፡ “የመለስ ሚስት አዜብ ለኃይለ ማርያም ቤተ መንግሥቱን አላስረክብም ብላ በግድ አይደል እንዴ የወጣችው?” ሲለኝ ታሪኩ ትዝ አለኝና በራሴ አፈር አልኩ፡፡ ስንትና ስንት የነገር ብልት የማወጣ ሰውዬ “እዚያ ድረስ ሄዶስ አያስበውም” ከሚል በኔ ዘንድ እምብዝም ያልተለመደ አስተሳሰብ የልጄን የፖለቲካ ንቃት መናቄን ስገነዘብ ለራሴውና በውስጤ በገዛ ልጄ ፊት የመቅለል ስሜት ተሰማኝ፡፡ በርግጥም ይህ ልጅ በ13 ዓመት ዕድሜው የተከናወነን ሀገራዊ ጉዳይ በደንብ ያውቅ ነበር ማለት ነው – ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በ12 እና በ15 ዓመት ዕድሜው የተከሰቱ ሁለት የተለያዩ ፖለቲካዊ ኹነቶችን በማገናዘብ ከዴሞክራሲያውያን ቅቡልነት ያለው ልማድ ተነስቶ ኢ-ዴሞክራሲያውንን በምፀት ዱላ መምታት ይችላል ማለትም ነው፡፡ ሲገባኝና “ስባንን” ብዙም እንዳይታዘበኝ ብዬ ምክንያት ቢጤ ሰጠሁትና ጥቂት አዋራሁት፤ እርሱ ለቀልድ ያህል ቢናገረውም የአሜሪካ ህግ እንደኢትዮጵያ በአምባገነኖች መዳፍ ሥር የወደቀ ሳይሆን በህገ መንግሥት አስፈጻሚ መንግሥታዊ መዋቅሮች በአግባቡ የተያዘ በመሆኑ ማንም ከህጉ ውልፊት እንደማይል በእግረ መንገድ ነግሬው – እንደሚውቀው እየነገረኝም ጭምር – ወደሌላ ርዕስ ገባን፡፡

ኦ! ረስቼው፡፡ “ዐይን እንዳይገባብኝ” እንጂ ስለዚሁ ልጅ አንድ ሌላ ሰሞነኛ አጋጣሚም አለ፡፡ የወያኔ ሰንደቅ ዓላማ የሚከበርበት ዕለት ተማሪዎች ሁሉ በየት/ቤታቸው እንዲገኙ ታዘው ነበር፡፡ ይህ የኔው ልጅ እንደወትሮው ቁርሱን በጧት በልቶ እንዲሄድ ስቀሰቅሰው “አልሄድም” ይላል፡፡ ያስገረመኝ አለመሄዱ አይደለም፡፡ “ሰንደቅ ዓላማ ያለን ይመስል…” በማለት የሰጠው ከርሱ ያልጠበቅሁት መልስ ነው በጣም ያስገረመኝ፡፡ ወያኔዎች ጮርቃ ሕጻናትን አለርህራሄ የሚጨፈጭፉት ለካንስ “እባብ የወጣበትን ጉድጓድ አይረሳም” ከሚለው ነባር ብሂል በመነሣት “እነሱም ሲያድጉ የወላጆቻውን የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ወኔ ይቀሰቅሳሉ፤ ትልልቅ ሲሆኑ የጥንቷን ትምክህተኛ ኢትዮጵያ አፍርሰን በምትኳ በአዲስ መልክ የሠራናትን አዲሲቷን የብሔር/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር ኢትዮጵያን ገልብጠው የዱሮውን ሥርዓት ያመጡብናል”  ከሚል ፍራቻ መሆን አለበት፡፡ ሞኞች ናቸው፡፡ የኔ ልጅ እንዲህ ከሆነ – ስሙን ለጊዜው “አልፎአይቼው” ልበለውና –  ብዙ አልፎአይቼዎች በየቤቱ እንዳሉ እረዳለሁና የነገይቷ ኢትዮጵያ መፃዒ ሕይወት ለኔ እጅግ ብሩኅ ነው፡፡ አልደብቃችሁም – በፊት በፊት እፈራ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ተስፋየ እየለመለመ መጥቷል፡፡ የአንዳርጋቸው ጽጌና መሰል ቆራጥ ኢትዮጵያውያን ደም የውሻ ደም ሆኖ አይቀርም፡፡ አንዲ ለእምዬ ኢትዮጵያ የተሰዋ በበግ ያልተተካ ይሥሃቅ ነው፤ አንዲ አቤል በቀናተኛ ወንደሙ ቃየል መለስ የተገደለ ሰማዕት ነው፤ ግዴለም አልሞተም ቢባልም ስቃዩ ከሞት በላይ ነውና ሰማዕት ነው፡፡

ይገርማችኋል የዛሬ ልጆች በጣም የረቀቁ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹም ቢሆኑ ለቴክኖሎጂው ቅርበት ስላላቸው ይመስላል ከኛ ከነባር ገትጋታ ኢትዮጵያውያን በተለዬ በአንዳንድ መልካም ባሕርያት እየታነጹ መምጣታቸው ይሰማኛል፡- ለምሳሌ እንደኛ ዘረኞች አይደሉም፤ ስለዘር ሐረግ ሲነሣ ብዙዎቹ አይገባቸውም፤ ሰውን በሰውነቱ ነው ማየት የሚፈልጉት፡፡ ስግብግብነት ብዙም አላይባቸውም – እየተሻሙና እየተካፈሉ ሲበሉ እታዘባለሁ፤ ሲጋቡ ወያኔ በቀየሰላቸው የዘር መሥፈርት አጥንትና ደም እያነፈነፉ አይደለም፤ … ብቻ አለ አይደል … ብዙ ደስ የሚሉ ነገሮች አሏቸው – ወያኔያዊ ተፅዕኖዎች የሉም ማለቴ ግን አይደለም፡- ይሁንና እነዚህ ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት የተዘሩ የወያኔ ተፅዕኖዎች በጊዜ ሂደት ተሸናፊ መሆናቸውን መመስከር አይቸግረኝም፡፡

ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት በሕጻናት ተተኪዎቻችን ትልቅ ተስፋ አለን ማለት ነው – ከወያኔ የማያቋርጥ ጥቃት ግን እንታደጋቸው፤ የምንችል ከሆነና ራሳችንን መለወጥ የማይከብደን ከሆን በቤት ውስጥ በጥሩ ጠባይ እንቅረጻቸው፡፡ እንከታተላቸውና ከጥፋት እንታደጋቸው፡፡ ከወያኔ የትውልድ ማምከን ዕኩይ ተግባር የሚያመልጡ ልጆችን በወቅቱ እንድረስላቸውና ጭራሽ ጠፍተን እንዳንቀር ከዘንዶው አፍ እናድናቸው፡፡ በትምህርቱ ረገድም ቢሆን በቤት ውስጥ እናግዛቸው፡፡ ትምህርቱን ከቤት የማለፊያ ካርዱን ከትምህርት ቤት፡፡ “ኑሮ በዘዴ ጦም በኩዳዴ” ነው ወገኖቼ፡፡ አዎ፣ “ቀን እስኪያልፍ ያባትህ ባሪያ ይግዛህ”ስ እንል የለም? ምን እናርግ?

ከኛ ከድኩማኖቹ የተሻሉ ልጆችን ማፍራት አለመቻላችን ነበር የእስካሁኑ ችግራችን፡፡ እንደኛው አሲድና ቀናተኛ እየተካን ከድጥ ወደማጥ የመዘፈቅ ባህል ነበር ለብዙ ዘመናት ያዳከረን አባዜያችን፡፡ እንደኛው በሥልጣን አራራና ባልተገባ መንገድ ሀብት የማጋበስ ሱስ የተጠመዱ ልጆችን ማፍራት ነበር የዘመናት ዋና ተግባራችን፡፡ አባት ልጁን፣ ልጅ አባቱን በሥልጣን ሽሚያ ምክንያት የሚገድልና ቆንጥር ለቆንጥር የሚያሳድድ እርጉም ሽንት የመፈልፈል አባዜ ነበር ተጠናውቶን የቆየው፡፡ በመተትና በሟርት በመጠላለፍ አንዱ የሌላውን ውድቀት የሚያፋጥንበት ባህላዊ እሥር ቤት ውስጥ መዘፈቃችን ነበር ልንቀርፈው ያልተቻለን የዘላለም ራስ ምታታችን፡፡ ሀገርን የሚያቀጭጭና ከዕድገት ይልቅ ውድመትን የሚያስፋፋ የከንቱ ፉክክር እሥረኞች መሆናችን ነበር ትልቁ ወረርሽኛችን፡፡ አለመተሳሰብንና አለመተዛዘንን የተፈጥሮ ጠባያቸው ያደረጉ እርጉም ሽሎችን ወልዶ ማሳደግ ነበር ለከፋ ጉዳት እየዳረገን የመጣው የትውልድ መርገምታችን፡፡ … ከዚህ አዙሪት የወጡ በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ከሚገኝ ነፃ አስተሳሰብና መልካም የሰው ልጅ አመለካከት በብዙው የሚማሩ ወጣቶችና ጎልማሦች፣ በዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሥር ታንጸው የሚያድጉ ልጆችን ኢትዮጵያ ካገኘች እንደማንኛውም ሀገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልፍላታል፡፡ ሁሉም በየቤቱ ከክፋትና ከምቀኝነት አባዜ የፀዱ ልጆችን ለማፍራት ቢጥር ቀስ በቀስ እኛ ስንሞትና ቦታ ስንለቅ ደህናው ትውልድ ሀገሪቱን ተረክቦ በጥፋትና በውድመት ወደኋላ ሣይሆን በዕድገትና በሥልጣኔ ወደፊት ያሽቀነጥራታል፡፡ (አንድ ሀብታም ሰው ቢቸግረው አሉ – የጨነቀው እርጉዝ ያገባል (ስትወልድበት ገደል ይገባል) እንደሚበላው መሆኑ ይመስለኛል – ምቀኝነት ከጤፍ እንደሚመጣ ጭንቅላቱ ውስጥ ማን እንደተከለበት አላውቅም አንድያ ልጁን እንጀራ ሳይበላ እንደጣሊያኖች በፓስታና በመኮረኒ፣ በላዛኛና በአኞሎ ዲቢቴሎ አቀማጥሎ ከሀበሻ ምግብ በማራቅ አሳደገው አሉ፡፡ ሰውዬው ያለፈለት ማይም ቢጤ ነውና ልጁን በገዛ ሀገሩ አዲስ አበባ ላይ ከእንግሊዝኛ በስተቀር ሌላ ቋንቋ እንዳይችል አድርጎም ነው ያሳደገው፡፡ አሃ! ለካንስ ኢትዮጵያን ለመምራት በፕሬዝዳንትነት ቦታ እወዳደራለሁ ያለው ኃይሌ ገ/ሥላሤም ልጁን ያስተማረው “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ያስቀጣል” ብለው ማስታወቂያ ከለጠፉ ዘመናዊ ት/ቤቶች በአንደኛው በመሆኑ ሞልቃቂት በ“ትውልድ ሀገሯ” እምብርት አዲስ አበባ ውስጥ ከቤተሰቧ ጋር እየኖረች አንድም ሀገርኛ ቋንቋ ጠፍቷት በእንግሊዝኛ ነበር ስትኮላተፍ አንዴ በቲቪ ያየኋት! አይ ኢትዮጵያ! ማለፉ አይቀርምና ሲያልፍ ስንቱን አውርተን እንጨርሰው ይሆን? ውጭ ያሉትስ በያሉበት ሀገር ቋንቋ ቢኮላተፉ አማራጭ አጥተው ነው፡፡ እዚህ ስንቱ ደንቆሮ ማይም መሰላችሁ ለልጆቹ አማራጭ እያሳጣ እንትን ላይ ተቀምጦ እንት ገማኝ የሚል! እንዲያው በውነት ከማይምነት የከፋ ለሰው ልጅ ጠላት ይኖር ይሆን? ከሰማችሁ አደራ እንዳትደብቁኝ፡፡  ለነገሩ ይህን ይህን አሁን እዚህ ማንሳት አይገባም፡፡) የኔው አውግቼውና አልፎአይቼው በስንት ጣማቸው! ይቺ ነገር የምቀኝነት ታስመስልብኝ ይሆን እንዴ? “ያጣ ወጉ ነው” ልባል፤ ግዴለኝም እችለዋለሁ፡፡ ለማንኛውም ደህና ሰንብቱልኝ እስኪ፡፡

yiheyisaemro@gmail.com

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47793#sthash.uE5jrz7S.dpuf

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s