በኢህአዴግ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በድርቅና በድህነት ምክንያት በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ችግር መጠን ሊድበሰበስ አይገባም!! – መድረክ

በኢህአዴግ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በድርቅና በድህነት ምክንያት በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ችግር መጠን ሊድበሰበስ አይገባም!!
(ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)
ሀገራችንን ላለፉት 25 ዓመታት ሲገዛ የቆየው ኢህአዴግ ባለ2 አሀዝ ፈጣን እድገት እያስመዘገብኩ ሀገራችን በምግብ ራሷን እንዲትችል፣ ከስንዴ ልመና ለመውጣትና እያንዳንዱ ዜጋም በቀን ቢያንስ ሶስት ጊዜ ለመብላት እንዲበቃ እያደረኩ ነኝ ብሎ በሚያሰራጨው የፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ሕዝባችንን የተስፋ ዳቦ እየመገበ ለማኖር ቢሞክርም በአገዛዙ ጊዜ የተፈጥሮ ድርቅ በሚከሰትበትም ሆነ በሌላ ወቅት በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ችግርና መጎሳቆል የፕሮፓጋንዳውን ባዶነት በተጨባጭ በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ሀገራችንን በዓለማችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ በአጭር ጊዜ ለማሰለፍ የሚያስችል ፈጣን እድገትና ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ነን፣ በማለት በሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳም የጥቅት የሥርዓቱ ገዥዎችና ምንደኞች በስተቀር የብዙሃኑ ሕዝባችን ኑሮው ሲሻሻል አልታየም፡፡
አህአዴጎች ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ሀገራችን በምግብ ራሷን እንዲትችል ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያም ለማቅረብ በቅተናል፣ በማለት በተደጋጋሚ ድስኩር ባሰሙ ማግስት፣ በአንድ የምርት ወቅት ብቻ እንኳ የተከሰተው የዝናብ እጥረት የድስኩራቸውንና የፉከራቸውን ባዶነት እያጋለጠ እርቃናቸውን ሲያስቀራቸው ለማየትና ለመታዘብ ችለናል፡፡ በእጂጉ የሚያሳስበን ይህንን ባዶ ፕሮፓጋንዳቸውን ለመሸፋፈን ሲሉ በሕዝባችን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን በትክክል ባለመግለጽ ሕዝባችንን ለባሰ ጉዳት እየዳረጉት መገኘታቸው ነው፡፡ ለእነዚህ ችግሮች ዋና መሠረቱም ኢህአዴጎች ብዙ የሚያወሩለት የኢኮኖሚ እድገት ፖሊሲ የምልአተ-ሕዝባችንን የኑሮ ችግሮች በተጨባጭ ሊቀርፍና ሊያስወግድ በሚያስችልና ዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚ በሚሆኑበት አቅጣጫ ያልተመራ መሆኑ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ሕዝባችን እንዳለፉት ሥርዓቶች ሁሉ በትናንሽ የመሬት ይዞታዎች ላይ በተመሠረተ እጅግ ኋላ ቀርና የዝናብ ጥገኛ በሆነው የግብርና ምርት አመራረት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ለአንድ የምርት ወቅት የሚከሰት የዝናብ እጥረት ለመቋቋም የሚያስችል ምርት በግልም ሆነ በሀገር ደረጃ ማምረት ባለመቻሉ የበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት ለአስከፊ አደጋ ሲጋለጥ ቆይቷል፡፡
ከ2007 ዓ ም ጀምሮ በበርካታ የሀገራችን አከባቢዎች የተከሰተው የዝናብ እጥረትም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበርካታ ዜጎቻችንን ሕይወትና ንብረት በተለይም በሰብል ምርትና የእንሰሳት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ሕዝባችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ዜጎቻችንና የቤት እንሰሳት የሚበሉትንና የሚቀምሱትን አጥተው በረሃብና በውኃ እጦት የሚጎዱበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሎአል፡፡ ይህንንም አሳዛኝ ክስተት የኢህአዴግ አገዛዝ እጅግ አቃልሎ በጣም ጥቂት ዜጎችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ፣ እንደዚሁም በመንግስት አቅምና በሀገር ውስጥ ባለ የምግብ ክምችት ችግሩን መቋቋም እንደሚቻል አስመስሎ ስያድበሰብስ ቆይቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የውጭ ሀገር ሚዲያዎች የችግሩን መጠን ይፋ ሲያደርጉም ኢህአዴግም እንደ ቀደምቶቹ የሀገራችን አምባገነን ገዥዎች ለማስተባበልና ለመሸፋፈን እየሞከረ ይገኛል፡፡

እስከአሁን ድረስም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በትክክል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለዓለም ሕብረተሰብ ባለመግለጹና የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር እርዳታ በተገቢው ደረጃ ለማሰባሰብና ለማሰራጨት ባለመንቀሳቀሱ እጅግ በርካታ የድርቁ ተጎጂ ወገኖቻችን እርዳታ በወቅቱ እየደረሳቸው አለመሆኑ በእጂጉ ያሳስበናል፡፡ በአንዳንድ አከባቢዎች እርዳታው በወቅቱ ያልደረሰላቸው ወገኖቻችን ጠብቀው በማጣታቸው እርዳታ ፍለጋ ለመሰደድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ድረስ የሚታይ ቢሆንም የኢህአዴግ ካድሬዎች እርዳታውን በማድረስ ችግሩን ከመፍታት ፋንታ ሕዝቡ በግድ ባለበት እንዲቆይ በማድረግ ሥራ ላይ አተኩረው ይገኛሉ፡፡
እርዳታው እየደረሰ ባለበት አንዳንድ አከባቢዎችም በኢህአዴግ ዘንድ የተለመደውን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በማንጸባረቅ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ለሆኑ ተጎጂዎች “ፓርቲያችሁ አምጥቶ ይስጣችሁ” በማለት፣ ሰብአዊ እርዳታን ለፖለቲካ መሳሪያነት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ በአንዳንድ እርዳታው እየተከፋፈለ ባለባቸው አከባቢዎችም የእርዳታ እህልና ዘይቱን እየሸጡ ለምንም የማይበቃ ትንሽ ገንዘብ ለተጎጂዎች እየሰጡና ለልማት እያሉም ተጎጂዎቹን ገንዘብ እንደሚያስከፍሉ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ በድርቅ ምክንያት ምርት ለማግኘት ያልቻሉ አርሶ አደሮችም አመታዊ ግብር መክፈል ባልቻሉባቸው አከባቢዎች እርዳታውን ሳይቀበሉ እንዲፈርሙና ለእርዳታ የተመደበላቸው እህል ተሸጦ በግብር ስም ለመንግሥት ገቢ እንዲደረግ ሕገወጥና ኢ-ሰብአዊ ጫናዎች በአርሶ አደሮች ላይ እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሎአል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በቅርቡ በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ ኢህአዴግ ላለፉት አሥር ተከታታይ አመታት አስገኘሁ ያለው የኢኮኖሚ እድገት የጥቂት የሥርዓቱን ባለሟሎች ሕይወት ከመለወጥ በስተቀር ሰፊውን ሕዝባችንን በአንድ የምርት ወቅት የሚከሰተው የዝናብ እጥረት ከሚያስከትለው የምግብ እጥረት ሊታደግ ያልበቃ መሆኑ ሀገራችን በምን ያህል ችግር ውስጥ እንዳለች ያሳያል፡፡ የኢህአዴግ አገዛዝም እንደቀደምቶቹ ሥርዓቶች ሁሉ ለሕዝባችን ችግሮች ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጥ ለራሱ አባል ድርጅቶች አመታዊ ክብረ በዓላት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ገደብ በሌለው ወጪ የሀገር ሀብት በማባከን የሚሠማራ አምባገነናዊ መንግሥት መሆኑን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሕዝባችን በችግር ላይ ባለበት ወቅት ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎችም ሆነ በየአከባቢው ባሉት የካድሬ ሠራዊቱ አማካይነት በስፋት ትኩረት ሰጥቶ በማሰራጨት ላይ ያለው ፕሮፓጋንዳ፣ በሕዝባችን ላይ እየደረሱ ያሉትን የረሃብና የኑሮ ችግሮች ለሕዝባችንና ለዓለም ሕብረተሰብ በማሳወቅና ለችግሩ መፍትሔ በመሻት ላይ ሳይሆን፣ ለአባል ድርጅቶቹ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ድምቀት ከፍተኛ ሀብት በማባከን በሚከናወን ፈንጠዚያ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህም “ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንዲሉ ቀደምት አምባገነናዊ ሥርዓቶች ሕዝባችን በድርቅ ሲጠቃ በነበረባቸው ጊዜያት በረሃብ የሚሰቃየውን ሕዝብ ችግሮች ችላ ብለው ለራሳቸው ክብረበዓላትና ለቤተሰቦቻቸው የልደት ቀናት አከባበር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው የሀገር ሀብት ሲያባክኑ ከኖሩበት አሰነዋሪ ተግባራት ጋር ተመሳሳይ ድርጊት ነው፡፡
ስለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ/መድረክ/ የኢህአዴግ አገዛዝ ከዚህ አስነዋሪ ተግባሩ ተቆጥቦ ፡-
1ኛ፡- በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ረሃብ ስፋትና ጥልቀት ለሕዝባችንና ለዓለም ሕብረተሰብም በትክክል እንዲያሳውቅና የተጎዱት ወገኖቻችን የሚገባቸውን ያህል እርዳታ በወቅቱ የሚያገኙበትን ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲያመቻች፣
2ኛ፡- ለተራበው ሕዝባችን እርዳታ ከሀገር ውስጥ በማሰባሰብ በውጭ ልመና ያጠለሸውን የሀገራችንን ገጽታ የማጥራት እርምጃ እንዲወስድ፣
3ኛ፡- በረሃብ ለተጎዳው ሕዝብ የሚሰጠው እርዳታም ካለአንዳች አድሎኦና የፖለቲካ ወገንተኝነት ለተጎዳው ዜጋ ሁሉ በትክክል እንዲዳረስ እንዲያደርግ፣ የእርዳታ እህሉን በሚሸጡና የልማት መዋጮ ክፈሉ በማለት ተጎጂዎችን ገንዘብ በሚያስከፍሉ ካድሬዎች ላይም ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ፣
4ኛ፡- ለአባል ድርጅቶቹ ክብረበዓላትም ሆነ ሕብረተሰቡን ለመደለል ለሚያዘጋጃቸው የተለያዩ የመደለያ ፕሮግራሞች ያለገደብ እየባከነ የሚገኘውን የሀገር ሀብት በድርቁ ለተጎዳው ሕዝባችን እርዳታ እንዲውል እንዲያደርግ፡-
5ኛ፡- ኢህአዴግ ሕዝባችንን ከድህነትና ከረሃብ ያላላቀቀውን “የፈጣን የኢኮኖሚ እድገት” አምጥቻለሁ የሚለውን ባዶ ፕሮፓጋዳ አቁሞ፣ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በዘላቂነት የሕዝባችንን ኑሮ በተጨባጭ የሚያሻሽልና ከድህነትና ከረሀብ በሚያላቅቅ ስልት እንዲመራ እንዲያደርግ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት
መድረክ/መድረክ/
ህዳር 20 ቀን 2008 ዓ ም
አዲስ አበባ

ኤሊኖ ወይስ አውሮቦሮሶች?

 

ነጋ አባተ ከእስራኤል

ሰሞኑን ድኅረ- ገፆቻችንን ያጥለቀለቀው ዓቢይ ጉዳይ “ርሃብ” በሚባል ጨካኝ ምጣድ ላይ ተዘርግፈው እየተቆሉ ላሉ ወገኖቻችን የእንድረስ ጩኽትን የሚያስተጋባ የፌስ ቡክ “የክፉ ቀን” ዘመቻ ይመስለኛል። ምንም እንኳን ዕንቅስቃሴአችን ከጩኽት መዝለሉን እርግጠኛ ባልሆንም እኔም በጓደኞቼ አማካኝነት ተሳታፊ ሆኛለሁ። ቆይ ግን ጎበዝ! ቆም እንበል በእውነት ክፉ ቀን ወይስ ክፉ ጠላት? ኤሊኖ ወይስ አውሮቦሮሶች?። “አህያውን ሲፈሩ መደላድሉን” እንዳይሆን ብየ ነው።

hanger
የፌስ ቡኩን ዘመቻ የከፈቱት ወገኖቼ በንጉስ በአጤ ምኒልክ ዘመነ- መንግስት ከ1880-1884 የተከሰተውንና ወገናችንን በመሮ ጥርሱ አድቅቆ በትውልድ መካከል የማይደብስ ጠባሳ ጥሎብን ያለፈውን እነኝያ “ክፉ ቀን” በመባል የሚታወቁትን ድርብርብ አሰቃቂና ማቅ-ለበስ ዐመታት ስያሜ በመውሰድ የተጀመረ ዕንቅስቃሴ ይመስለኛል። አዎ! ከባድ ዓመታት ነበሩ ክፉ ቀን የሚል መጠሪያ ይዘውም በታሪክ መዝገብ ከነግሳንግሳቸው ሰፍረዋል። ሌላው ሳይቀር ወራሪው የጣሊያን ጦርም ስለርሃቡ መረጃው ስለነበረው ይህንን ክፉ አጋጣሚ ተጠቅሞበታል ይባላል። ግን ወዴት ወዴት“ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል ይባል የለ” ያ ክፉ ቀን ወዴት የአሁኑ (?) ወዴት።
በዚያ ክፉ ቀን ህዝቡ በሞት የተሸነፉ ዘመዶቹን እየቀበረም እየጣለም እሱም ከሞት ጋር ግብግብ እየገጠመና በነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ እየተጣደፈ ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫ ወደ ንጉሱ ዓጤ ምኒልክ ቤተ-መንግስት በጥቁር እንግዳነት ከአሸለቱ ቁመናዎቹ ጋር የተገጠገጠው ችግረኛ ቁጥር እንዲህ ቀላል የሚባል አልነበረም። በዘመኑ ይህንን የሰቆቃ ትዕይንት በዓጤ ምኒልክ ቦታ ሆኖ ላየው ይጨንቃል አቅል ይሰውራል። ይሁን እንጅ ንጉሱ ከእውነቱ ዘወር አላሉም ይልቁኑም በተሰበረ ልብ እንዳመጣጡ ተቀበሉት እንጅ። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ምንድነው ህዝብ የሚያምነው መሪ ሲያገኝ የአባት ያክል ያምነዋል። ህመሙን ፤ ጭንቀቱን፤ የሆዱን ብሶት ሊያካፍለው ይፈልጋል። ከእግዚአብሄር ቀጥሎ ህዝብ ልቡን የሚጥለው በእርሱ ላይ ነዋ!። ዓጤ ምኒልክ ይህ ግርማ ሞገስ በህዝባቸው ላይ ነበራቸው እምየ የሚለውን ስም ያገኙትም በነኚህ የጭንቀት ቀናት ነው ይላሉ ብዙዎቹ። ለሩህሩህነታቸውና ለደግነታቸው ከህዝብ የተሰጠ የፍቅር ስጦታ!።
ደጉ ንጉስ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ ከባድማው የተሰደደውን መፃተኛ እንደዛሬዎቹ ጅቦችና ዘግቶ በላዎች፤ ሲቀጥልም የዘመናችን ኦውሮቦሮሶች፤ ክቡሩን የሰውን ልጅ በስቃይ ጅራፍ እይነረተ እመሬት ላይ ስለሚደባልቀው፤ ብሎም እነርሱ ራሳቸው ጎትተው ስላነገሱት የችጋር ጭራቅ መስማት እንደማይፈልጉት የአፍ ጉልበተኞች የመስቃን ቃል አልተናገሩም ፈሪሃ እግዚአብሄር አላ!። በእኔ የንግስና ዘመን ? የምን ርሃብ? ብለው የአካኪ ዘራፍ ምላስ አልወነጨፉም። ከዚህ ይልቅ በቅርባቸው ለነበሩት የሃይማኖት አባቶች እግዚአብሄር ምህረቱን ይልክ ዘንድ አጥብቀው እንዲለምኑ አሳስበዋቸው እሳቸው ግን ከዙፋናቸው ወርደው በእጃቸው የተገኘውን ያድሉ ገቡ። በአካልም በአስተሳሰብም የሸመገሉት ንጉስ ምኒልክ ያደረጉት ይህንን ነው።
የእኛዎቹ የዘመናችን አውሮቦሮሶች ግን በመለኮት እቅድ ምክኒያት ግንዘተ-ልቦና ሆኖባቸዋልና ክፉ ዘርን ይዘሩ ዘንድ በመርዝ በተሞሉ አለብላቢት ምላሶች ላይ በመቆማቸው፤ መልካም ዜና ከነርሱ ዘንድ ላይሰማ እነርሱ ለጸባዖት የራቁትን ያህል ለእነርሱም የራቀ ነው። ከዚያ ይልቅ በደደቢቱ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተው፤ ነገር ግን ጠረጴዛ ላይ ተፈትኖ ለመውጣት በምሁራን መካከል ለመገኘት የሚቅለሰለሰውንና የዓይን-ዐፋሩን የኢኮኖሚክስ ስሌታቸው የ”ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ” ድምር በሁለት አሃዝ ተመንድገናል እያሉ እንደልጅ ይቧርቃሉ። ወደ ጉልምስና የማይመጣ የተፈጥሮ ህግጋትን የናደ ውበት አልባው ልጅነት! ድንክየነት! ይሏል እንግዲህ ይህ ነው። ለዚህ ነው ታላቁ መጽሓፍ መጽሓፍ ቅዱስ “ንጉሶቿ ህጻናት ለሆኑ ለዚያች ሃገር ወዮላት” የሚለን በልጅነት አዕምሮ መጡ በልጅነት አዕምሮ አረጁ በልጅነት አዕምሮ ወደ መቃብር መውረዱን ተያይዘውታል። የሸመገለና የተፈታ ልብማ እርቅ እርቅ ይሸተዋል፤ ሁሉን የሚሸከምበት ሰፊ የፍቅር ቋት ይኖረዋል፤ ማንም ያለጭንቀት የሚያርፍበት የመንፈስ ጥላ ይኖረዋል።
ምድራችን ለቁጥር የሚታክቱ ለስልጣናቸው የሚንሰፈሰፉ ነገስታትንና አምባገነኖችን አስተናግዳለች ይሁን እንጅ የህዝባቸውንና የሃገራቸውን ክብር የሚነካ ጉዳይ ሲገጥማቸው ግን ሁሉም ማለት ይቻላል ግንባር ቀደም ሆነው ዘብ በመቆም አያስነኬዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከል አንዱ አጤ ምኒሊክ ናቸው። ንጉሱ ስልጣን ይገባኛል ብለው ታግለዋል ተራራ ወጥተው ወርደዋል። በህዝብ ላይ ርሃብ በመጣ ጊዜ ግን ህዝቤ፤ ድሆቼ ብለው ከልብ በተሰበረ መንፈስ አነቡ አንጅ የተሟገገውን ገላ አይተው ጎሽ የኔ ልጅ በእኔ የንግስና ዘመን ጠግበኸልኛል ብለው የሳሳውን ገላውን በፕሮፐጋንዳ ሳማ አልገሸለጡትም። እንደ ወንጭት የተጠረበውን ባቱን አይተው እንዲያ እንጅ ጠብደሃል በል በሚል የግፍ ቃል አንገቱን አስደፍተው ባይተዋር አላደረጉትም።
እዚህ ላይ እንደ ዋቢ የምጠቅሰውና “እውነት” የሚለው ክቡር ቃል ይገልጠዋል ብየ የማስበው የሶፎክለሱ ንጉስ ኤዲፕስ ትዝ አለኝ። በእርሱ ዘመን የአቴናን ምድር ያንቀጠቀጠ አንዳች የመቅሰፈት ምች ከተማዋን ያደቅቃት ያልማት ጀምሯል ። ህዝቡም በደረሰበት አደጋ ተደናግጦ፤ ተጎሳቁሎና እንደሞት ሰራዊት በአስፈሪ ድባብ ታጅቦ ወደ ቤተ መንግስቱ ይተም ይዟል። ይህን የተረዳው እውነተኛውና አስተዋዩ ንጉስም ህዝቡን ለመቀበል ከነሞገሱ ወደ ሰገነቱ ይወጣል። በሚያየው ነገር ግን ልቡ ይናጥ ይደማ ጀምሯል። አይን-ስውሩን ነቢይ የዚህ መቅሰፍት መንስኤና መፍትሄው ምን እንደሆነ እንዲነግረው አጥብቆ ይጠይቀዋል። ከብዙ የዙሪያ ንግግርና ከሽማግሌዎቹ መዘምራን ምክር በኋላ ንጉሱ እውነቱ ካልወጣ መፍትሄ የለም በሚል እሳቤና ፤ እውነትንና ፍትህን በአደባባይ ለማቆም ቆርጦ በመነሳቱ ምክኒያት አውጫጭኙ ከሯል። ሁሉም ክርክሩ በፈጠረው ግለት በፍርሃት እየተለበለበ ጥግጥጉን ይዟል ይባስ ብሎም ንጉሱ ችግሩና መፍትሄው ካልተገኘ ደግሞ በየደረጃው ያሉትን ሃላፊዎችን ተገቢውን ቅጣት እንደሚያከናንባቸው ዛተ። የነገሩ ስር ከግራ ከቀኝ እየተቧካ በስተመጨረሻው ፍርጥርጡ ወጣና ንጉሱ የመርገሙ ምክኒያት ሆኖ ተገኘ። እዚህ ላይ ነው የኤዲፐስ ማንነት የሚታየው ከተጠያቂነት ለመዳን ልሸፍን ላዳፍን፤ ስልጣኔን ንግስናየን ላስጠብቅ አላለም በራሱ ላይ አስቃቂውን እርምጃ በመውሰድ ስልጣኑን ለቆ ከምቹው ቤተ-መንግስት በመውጣት የእውነትንና የፍትህን ጫፍ አሳየ። እዚህ ላይ ከንጉሱ አስገራሚ ባህሪዎች ሁለት ዋና ዋና ቁምነገሮችን ልናይ እንችላለን በመጀመሪያ ከኔ የተሻለ ዕውቀት ሌሎች ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብና ሌላው ደግሞ እውነት እንዳትዳፈን መድከሙ ናቸው። የአቀባበላቸው ዳኝነት እውነት መሆኑ ደግሞ ሁለቱን ንጉሶችን አመሳሰለብኝ።
የመጣጥፌ ዋና ዓላማ የዘመናችንን አውሮቦሮሶች ጥላሸት በመቀባት የፖለቲካ ትርፍ በማግኘት በጭንቅ ውስጥ ባሉ ወገኖቼ ህይወት ላይ ቁማር ለመጫወት እንዳልሆነና ሰውን ያክል ክቡር ፍጥረት እንደሰው በስፍራችን መገኘት አቅቶን በነገር ዘባተሎ እየተጠላለፍን በወደቅንበት በዚያ ቁመናውም ልኩም በማይታወቅ የውዝግባችን ቅርቃር በመሸንቆር ያስተሳሰብ ብልግና ውስጥ ራሴን ለመጣል በመፈለግም አይደለም።
ጥያቄየ ግን እውነቱ ወዴት ነው ? ነው። የርሃባችን አቢይ ምክኒያት ብዙዎቻችን እንዳልነው የቀኑ ክፋት ወይስ የገዥዎቻችን ክፋት ? ወይስ እነሱ እንዳሉት ኤሊኖ?። ኤሊኖ! አይ ቅጥፈት! ነገ ደግሞ የሆነ ችግር ቢፈጠር የዚህ ችግር ዋና ምክኒያት የህዳሴው ግንባታ ያመጣብን ጣጣ ነው ሊሉን ይችላሉ ምን ችግር አለው? ባፈጠጠ የህሊና ጥሰት ለሚኖር እጓለ ምዑት ሰፈር እኮ ውሸት አንድ ሙዚቃ ነው። ምነው ገዥዎቻችን ራሱን እንደሚበላ አውሬ አረመኔነቱን አጦዙትሳ? የዚህ በለየለት የህዝብ የጠላትነት ጫፍ ላይ መቆም ጉዳይስ የሂሳብ አወራረዱን ምን ያስመስለው ይሆን?። ደግሞስ በዚሀ በሰለጠነ ዘመን ሰለ ርሃብ ማውራት አይቀፍም ወይ?። ለገባውማ ይቀፋል ይጎፈንናል እንጅ! ለደደቢት ምሩቃን ግን ይህ የመርህ ጉዳይ ነውና እንደ ታላቅ ስኬት ይቆጠራል።
በአጤ ምኒልክ ዘመን ከደረሰብን ርሃብ አርባ ዓመት ቀደም ብሎ በድንች ላይ ጥገኛ በነበረው የአየርላንድ ህዝብ ላይ የደረሰው አሰቃቂ ርሃብ አየርላንዶቹ ታሪካቸውን በሃዘን የሚገልጡት ምዕራፋቸው ነው። “ The great famine” ተብሎ በተሰየመው በዚህ ርሃብ “The potato blight” የሚባል የድንች በሺታ ተከስቶ በሚሊዮን የሚቆጠር የአየር ላንድን ህዝብ አርግፏል አሰድዷል። ለዚያ ርሃብ በህዝቡ በኩል የቀረበው ምክኒያት በጊዜው በነበረው የአስተዳደር ብልሹነት ነው ሲል በሹሞቹ በኩል ግን የለም በጊዜው የተከሰተውን የድንች በሺታ ነው በሚል የተነሳው ውዝግብ ቀጥሎ ግን ሳይቋጭ እንደተንጠለጠለ የቀረ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጅ ያ የርሃብ ምች እንደኛ እያሰለሰ አዚም ላይሆን ዳግመኛም ተከሰቶ የአየርላንድን ህዝብ ላይቀጥፍ አሸልቦ በአየርላንዳዊያን ግብዓ- ተመሬቱ ተፈጽሟል። የእኛ የርሃብ አዙሪት ግን እኛኑ ሊቀብረን እየሰለለን ይመስላል እውነተኛውን መንሰኤውንና መፍትሄውን ገና አላገኘነውማ!።
በዚህ በምኖርበት በእስራኤል ሃገር እስራኤላውያኖቹ የሚሉት እኔንም የሚገርመኝ ነገር አለ። ይኸውም መሬታቸው በአብዛኛው አሽዋማ ነው ግን ይሰሩበታል፤ የተስተካከለ የዝናብ ወቅት የላቸውም እነርሱ በዚያም ጥገኛ አይደሉም፤ የመሬታቸው የቆዳ ስፋት ትንሽ ነው ግን ከሚበላው የሚደፋው ይበልጣል። እነርሱም በኩራት የሚናገሩት እዚህ ላይ ነው። “በካርታ ላይ እስራኤል ብሎ ለመጻፍ ቦታ እንደሌለ ሁሉ መሬታችንም ጠባብ ናት ግን እስራኤል ሃገር ርሃብ የለም።” ይላሉ። ስለአንዱ የገጠር መሬታቸው ትንሽ ልንገራችሁ ትንሿ ገጠር יוטבטה’’ (ዮትባታ) ትባላለች በሃገሪቱ ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል ትገኛለች። የዚህች መንደር መሬት አሽዋ ነው የመንደሯ ነዋሪዎች አርሰው ለማምረት ሲፈልጉ መጀመሪያ መሬቱን አጥበው ጨውን ማስወገድ አለባቸው ከዚያ በኋላ ነው ዘር የሚዘሩት ታዲያ የዚህች ትንሽ የገጠር መንደር ገበሬዎች በመላ እስራኤል የእርሻ ምርታቸውንና የወተት ተዋጾዖቻቸውን በማቅረብ ይታወቃሉ። እስኪ በስራኤል ዓይነት የእኛን ሁኔታ እንመልከት።
ወደ ጉዳያችን ስመለስ የዘንድሮው ጠኔ ገድ አልባ ሆኖና እንደ ቀላዋጭ እንግዳ ተሰልችቶ ነው ብቅ ያለው። በም ዕራባውያን በኩል ከሰራተኛው ህዝብ ከሚሰበሰበው ግብር እየተቆረሰ የሚላከው ገንዘብ የገዥዎቻችን የብልግና ጡንቻ ማፋፊያ እንደሆነና አውሮቦሮሶችም መናጢ ደፍቶ በላ ትዝቢዎች መሆናቸውን ከተገንዘቡ ውለው አድረዋል። እናም የሚራራው ልባቸው ተዘግቷል። እዚህ ላይ አንድ ገጠመኜን በምሳሌነት ላንሳ በስደት ከሃገሬ ከመውጣቴ በፊት በሙያየ ለአንድ መያድ (NGO) የ 30 ደቂቃ አጭር ተውኔት እንዳዘጋጅላቸው እየተነጋገርን ባለንበት ጊዜ ድርጅቱን በገንዘብ አቅርቦት የሚደግፍው የኖርዌይ ልዑካን ቡድን ለግምገማ ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡበት ወቅት ነበር። ልዑኩ የስራ ግምገማውን ከጨረሰ በኋላ የደርሰበት ድምዳሜ ከሚንቀሳቀሱት ጣቢያዎች መካከል ሰባቱን መዝጋት መወሰኑን አሳወቀ ምክኒያቱስ ተብሎ ሲጠየቅ ልዑኩ የሰጠው አጭር መልስ “ የሃገራችሁ ባለጠጎች የሚይዟቸውን መኪኖች ስንመለከት በእኛ ሃገር በብዙ ሰዎች የማይያዙ ንብረቶች ናቸው እኛ ይህንን የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ስናንቀሳቅስ ከድሆች እየለመንን ነው። በእኛ ግንዛቤ እነዚህ ባለጠጎቻችሁን በታግባቧቸው ይህን ፕሮጀክት ሊያንቀሳቅሱ ይችላሉ ብለን እናምናለን።” በማለት ውሳኔአቸውን አጸኑ።
አስተውሉ እነዚህ የኖርዌይ ሰዎች እየተናገሩ ያሉት ሰው ስለሚባለው ሰው ነው። ወገኖቹ በርሃብ ሲያልቁ ከአልጋው ወርዶ መሬት በመተኛት ያለውን ስለሚያካፍለው ሰው!። ከሚያማርጠው ውስኪ ወጣ ብሎ ለወገኖቹ አንድ ጣሳ ውሃ ማቅረብ ስለሚችል ሰው!። ልቦናውን እንደተሰረቀውና እንደ አለሌ የሜዳ አህያ ከሚፋንንበት ርቆና ከህሊናው ጋር ታርቆ ስለሚኖረው ሰው!። በነርሱ ሃገር የህሊና ግዴታ የሚባል ነገር አላ!። ይህማ ባይሆን ከሃገራቸው ኢትዮጵያ ድረስ ምን አንከራተታቸው?። እነዚህ እንግዶች የኢትዮጵያ ባለጠጎች ይሳተፉ ማለታቸው በሰው ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ህሊና መሰረት አድርገው ነው። ህሊናውን በጣለ የወዲኒ መንጋ መካከል መኖራቸውን አላወቁም ነበር።
የወደቅንበትን እናስተውል የማዕድ በጀት አልባ ሆኖ በቆሻሻ ገንዳ ከውሻ እና ከአሞሮች ጋር እየተናጠቀ ጉሮሮውን ዘግቶ በሚያድርባት ሃገር ሌላው የሁለት ሚሊዮን ብር ይዞ ሲንፈላሰስ የህሊና ህግ ስለተጣሰ አይጠየቅም!። የፋራ ነው!። ውሃ ባአግባቡ ማቅረብ ባልቻለች ሃገር ውስጥ ጥቂቶች ውስኪ እንደ ውሃ የሚራጩባት የጉድ ሃገር መሆንዋን ስናይ የሰው ያለህ ብለን በባይተዋርነት እንንገደገዳለን። ምንጩ ሲመረመር ደግሞ አይን ያወጣ ሌብነት በሃገሪቱ በመንሰራፋቱ ነው። የወረድንበት የዝቅጠት ልክ ሲለካ አራዊትን እንኳን አልመጠነም ቀልለን ተገኜን። ምን ማለቴ ነው በቡድን የሚጓዝ የአራዊት መንጋ ዞጉን አይነካም ነውር ነው ህገ-አራዊት ወሰናይ አላቸውና! ቢጣሉ እንኳን አይገዳደሉም ። ኃይላቸውን ለሌላው ባላንጣቸው ይጠብቁታል እርስ በርሳቸው ቢገዳደሉ ለነገ የመኖር ዋስትና እንደሌላቸው ያውቁታል ይህ ዕውቀት አላቸው። ያደኑትን ተካፍለው ይበላሉ ከመሃከላቸው አውራ የተባለው እንኳን ኃላፊነት ተሰምቶት ከርሱ ለሚያንሱት ትቶላቸው ዘወር ይላል። ሃገራችን ግን በአውሮቦሮሶች ተውርራለች።
በግሪካውያን ጥንተ-እምነት ጥናት መሰረት አውሮቦሮስ የሚባል የድራጎን አይነት ነበር። ፕሌቶ ስለዚህ ዝርያ ሲናገር “ዝርያው ዓይን ስለሌለው አድኖ የሚበላውን አያይም ፤ ጆሮም ስለሌለው አዳምጦ የሚጎመርበት ፍጥረት የለም አፈርና ውኃ ሲልስ አድጎ በመጨረሻ ከጅራቱ በመጀመር ራሱን እየበላ ወደ ግብዓ- ተመሬቱ ያዘግማል። እናም ፕሌቶ ስለዚህ አሳዛኝ አውሬ ሲደመድም ራሱን የሚበላ ፍጥረት በዚህች ምድር ህልውና የለውም።’’ ይህን የድራጎን ዘር ከእኛዎቹ ወዲኒዎች ጋር ያመሳሰልኩበት ምክኒያትም የሚሰሙበት ጆሮ የሚያዩበት ዓይን ስለሌላቸው ነው። ያላቸው አፍ ብቻ ነው። ያ ነው ጉልበታቸው። ያንም ህዝባቸውን ለመብላት እየተጠቀሙበት ነው ሌላውን ለማሸነፍ አፍ ብቻውን ጉልበት አይሆንም ። ግን ርቀቱ እስከየት ነው?። ህዝብ በስደት ውኃና በርሃ እየበላው አንድ ወፍ የሞተ ያክል እንኳን የዚያን ህዝብ ዕልቂት ከቁብ አይቆጥሩትም የዕልቂቱ ምክኒያትም እነርሱ መሆናቸውን ባለመቀበል በክህደት ይደመድሙታል። ከዚህ በላይ የራስን ህዝብ ራስንም ከመብላት የበለጠ አረመኔነት በየትኛው ፍጥረት ይታያል?። 15 ሚሊዮን ህዝብ ተርቦ ውሸት ነው ብለው በፕሮፐጋንዳቸው ለማፈን ተሯሯጡ በርሃብ እየተጠበሰ ካለው ህዝብ ይልቅ የእንቧይ ካብ ስልጣናቸው በልጦባቸው በተራበው ህዝብ ላይ ቀለዱ። ይባስ ብለው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመበጀት ህወሐትና ብአዴን (EPRDF) ለአስረሽ ምቺውና ለሴሰኝነታቸው ማስገሪያ እየበተኑ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ዜጋ በሚል ፈሊጥም ፊታቸውን በአሞሌ ታጥበው ለአንድ ሰው 25 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቤት እየሰሩ እንደሆነ ነግረውናል። እነዚህ ሰዎች የህዝብን ገንዘብ ሰርቀው የግላቸው ሲያደርጉ ኢሞራላውነትና ኢሰብዓዊነትን እያነገሱ ነው ይህንም ሲያደርጉ ህዝብንም ትውልድንም እየበሉ እንደሆነ አላወቁም ትውልድን ሲበሉ ራሳቸውን እየበሉ መሆኑንም ገና አልተገለጠላቸውም ። ከዚህ በላይ በህዝብ ላይ ንቀትና ጥላቻስ በምን ይገለጣል?። የናረ የህዝብ ጠላትነት!። ግን አንድ ነገር እመኛለሁ ደብቶ ከያዘን ከዚህ አዚም ስንወጣ! ያኔ ለጠላቶቻችን ዕድሜ የሰጠናቸው እኛ መሆናችን ሲገባን ራሳችንን እንወቅሳለን።
The enemy of the people (የህዝብ ጠላት) ከሚለው የኢብሰን ተውኔት ትንሽ ማለት ፈለግሁ። በኢብሰን ተውኔት ውስጥ ከህዝብ ጎን በቆመው ሃኪም እና በህዝብ ጠላትነት በቆመው የከተማዋ ከንቲባ ገጸ፟-ባህሪያት መካከል ያለውን ፍትጊያ በአጭሩ ስናይ ሃኪሙ የከተማዋን ነዋሪ እያረገፈው ያለውን ሞት ምክኒያት ለማወቅ ሲወድቅ ሲነሳ ይቆይና ምክኒያቱን ያገኘዋል ያም የከተማዋ ህዝብ የሚጠቀምበት ውኃ በመመረዙ ነው። ሃኪሙ መንስኤውን በማግኘቱ ትንሽ ተደስቶ ወደ መፍትሄው ሲዞር ደግሞ መፍትሄ ብሎ ያገኘው የከተማዋን ህዝብ ወደ ሌላ ስፍራ ማዞር ነው ይህንንም ለከተማዋ ከንቲባ ያማክረዋል። የከተማዋ ከንቲባም ለሃኪሙ ምክኒያቱንም መፍትሄውንም እንዳይናገር ይከለክለዋል ይባስ ብሎ በከተማዋ ከሚገኘው ታዋቂ የጋዜጣ ኤዲተር ጋር በመመሳጠር የፕሮፕጋንዳውን ስራ ያጧጡፉታል። ለህዝቡ ሞት ደንታ ያልሰጠው ከንቲባ የሃኪሙንም የመናገር መብቱን ከለከለው። የከንቲባው ዋና ዓላማ ህዝብ አይደለም ስልጣንን ማስጠበቅ ነው ለዚህም የፕሮፕጋንዳውን ስራ ማጧጧፍ ነው። ትንቅንቁ ይቀጥላል። የህዝብ ጠላት የሆኑ ሹሞች ጉዳያቸው ከስልጣናቸው ጋር እንጅ ከህዝብ ጋር አይደለም ይህ ስራቸው ደግሞ በህዝብ ጠላትነት ጎራ ያስፈርጃቸዋል።

 

ቸር ያገናኘን።

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48595#sthash.tsPzO5sI.dpuf

ሰመጉ ብሔር ተኮርና ልማትን መሠረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ እየተባባሱ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ብሔር ተኮርና ልማትን መሠረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ እየተባባሱ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

ሰመጉ ብሔር ተኮርና ልማትን መሠረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተባብሰዋል አለ

የአገር ውስጥና የውጭ የመገናኛ ብዙኃን አባላት፣ የተለያዩ ኤምባሲ ተወካዮችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከአፋር ክልልና ከምዕራብ ሸዋ ዞን የመጡ የጥቃት ሰለባዎች በመንግሥትና በመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች ተፈጸመብን ያሉትን በደል አሰምተዋል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁላቸውና መንግሥትም ወደ ታች ወርዶ ያለውን ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን የኖኖ ወረዳ ነዋሪ የነበሩ ሁለት አርሶ አደሮች በአካባቢው ከፍተኛ ብሔር ተኮር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ በቅርቡም የአማራ ብሔር ተወላጆች በሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የቤት ማቃጠልና በጎተራ ውስጥ የነበረን እህል የማንደድ ወንጀል መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዓለሙ አስፋው የተባሉ የአካባቢው የሚሊሻ አዛዥ እንደነበሩ የተነገረላቸው ግለሰብ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ባሰሙት ንግግር፣ በአካባቢው ተመሳሳይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸም የጀመሩት ቆየት ብለው ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱም አሁንም ተባብሰው መቀጠላቸውን አስታውሰዋል፡፡ ቤትና ንብረትን ከማቃጠል ባለፈ የሕይወት ማጥፋት ወንጀሎች በማናለብኝነት መፈጸማቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በ1996 ዓ.ም. መዳሉ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 52 የአማራ ብሔር ተወላጆች ቤቶች መቃጠላቸውን፣ በኖኖ ወረዳ በ2002 ዓ.ም. በ150 ቤቶች በተመሳሳይ ሁኔታ መቃጠላቸውን የገለጹት አቶ ዓለሙ፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ይህ ነው የሚባል አቋም ባለማሳየቱ በ2007 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወንጀሎች በመፈጸማቸው እነዚሁ የጥቃት ሰለባዎች ከአካባቢው በመሰደድ ጉራጌ ዞን ለመጠለል መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ዓለሙ ገለጻ የጥቃቱ ሰለባዎች በተደጋጋሚ ሕጋዊ የዜግነት ጥያቄያቸውን ለክልሉ መንግሥት ያቀረቡ መሆናቸውንና በምላሹ ምንም ዓይነት መፍትሔ አለማግኘታቸውን ገልጸው፣ ከክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነር በስተቀር ማንም የመንግሥት አካል እንዳልጎበኛቸው ተናግረዋል፡፡ “በመከላከያ ሠራዊት አባልነት ለስምንት ዓመታት ያህል ግዳጄን የተወጣሁና የአገሬን ጥሪ ተቀብዬ ላይቤሪያ ድረስ ሰላም ያስከበርኩ ዜጋ ነኝ፡፡ ዛሬ ግን በአገሬ ውስጥ ሰላም አጥቻለሁ፣” በማለት ብሶታቸውን ያሰሙት አቶ ዓለሙ፣ በዜግነታቸው ከመኩራት ይልቅ ማፈር እንደጀመሩና ምንም ዓይነት የሰውነት ከለላ የሌላቸው ዜጋ ሆነው መቅረታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከአፋር የመጡ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በልማት ምክንያት የእርሻ መሬታቸው በመንግሥት እንደተነጠቀባቸውና የተከሏቸው የቴምር ዛፎችም እንደወደሙባቸው በመግለጽ፣ ምንም ዓይነት የካሳ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸውና ይህም በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ተፈጽሞ የማያውቅ ኢሰብዓዊ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከአካባቢው የመጡ አርሶ አደር በአስተርጓሚያቸው አማካይነት እንደገለጹት፣ ፍየሎቻቸውንና በጎቻቸውን ሸጠው አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ለመንግሥት አቤት ቢሉም መፍትሔ አላገኙም፡፡

የሰመጉ ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ቁምላቸው ዳኜ እነዚህን መሰል ብሔር ተኮርና ልማትን ሽፋን ያደረጉ ኢሰብዓዊ ጥሰቶች በአገሪቱ ተባብሰው መቀጠላቸውን በመግለጽ፣ እነዚህን የጥቃት ሰለባዎች ለማግኘት የሰመጉ ባልደረቦች  በከፍተኛ ሥጋትና እንግልት ውስጥ ማለፋቸውን አስታውቀዋል፡፡ “ሰመጉ በአሁኑ ጊዜ በብቸኝነት ማለት በሚቻል ሁኔታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየተከታተለ ለመንግሥትና ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ሒደት ውስጥ ያለና ከፍተኛ ጫናን እየተጋፈጠ ያለ ተቋም ነው፣” በማለት ድርጅቱ ምን ያህል አስቸጋሪ ጊዜ ላይ መድረሱን አቶ ቁምላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ እንኳን በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ለማድረግ መገደዱ ነባራዊ ሁኔታውን በግልጽ የሚያመላክት አጋጣሚ መሆኑን ይጠቁማል ብለዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው ለምን በሌላ ሥፍራ እንዳልተሰጠ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የሰመጉ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብዙየሁ ወንድሙ በበኩላቸው፣ ከአሥር ቀናት በፊት ለኢትዮጵያ ሆቴል ክፍያ ተፈጽሞ መርሐ ግብሩ የተያዘ ቢሆንም፣ ከጋዜጣዊ መግለጫው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሆቴሉ በስልክ የመርሐ ግብሩን መሰረዝ እንዳሳወቃቸው ገልጸዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ከተገኙ እንግዶች መካከል የቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ (ቪኢኮድ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ደርሰህ ግርማ፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት አዋጅ ከተደነገገበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ከስመው፣ ዛሬ ሦስት ያህል ብቻ መቅረታቸውን አሁን ያለው ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሰመጉ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እያደረገ ባለው አገራዊ አስተዋጽኦ ሊመሰገን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ሰመጉ በ1984 ዓ.ም. ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ 36 መደበኛ መግለጫዎችንና 139 ልዩ መግለጫዎችን ማውጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ብሔር ተኮር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዳካተቱም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡

Reporter Amharic

የረሃብ አደጋውን፣ ‘ዱብዕዳ’ ወይም ‘ጊዜያዊ’ አናስመስለው!

 

 

 

Written by  ዮሐንስ ሰ.  • ‘ግድብ-መስኖ አትስሩ’ የሚል ዘመቻ፣ እና ተመፅዋች ረሃብተኛ

1. ከሃያ የዓለማችን ድሃ አገራት አንዷ! በየዓመቱ 10 ሚ. ችግረኞች፣ እርዳታና ድጎማ ይቀበላሉ። ዘንድሮ ግን፣ የተረጂዎቹ ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ጨምሯል።

2. አስቸኳይና የሚያዛልቁ መፍትሄዎች! የለጋሾች እርዳታ እንዲዳረስ በጥንቃቄና በፍጥነት መስራት። ግድብና መስኖ፣ ‘የሞት ሽረት’ ጉዳይ እንደሆኑ መገንዘብ።

3. ቢከለክሉንስ? ዩኤን – ለኢትዮጵያ፡ በድርቅ ለተጠቁት፣ የለጋሾችን እርዳታ እየመዘገበ ያስተባብራል። ‘ግድብና መስኖ አትስሩ’ የሚለውን አለማቀፍ ዘመቻ ያስተጋባል።

የረሃብ ጥቃት የሚቆረቁረን ሰዎች፤ የመስኖና የግድብ ‘ተቆርቋሪ’ መሆን የለብንም? የድርቅ እና የረሃብ አደጋው ካንገበገበን፣… የገደል አፋፍ የድህነት ኑሮ እንደ እሬት ከመረረን፣ ተመፅዋችነት በአካልና በመንፈስ ከቆረቆረንና ውጋት ከሆነብን፤… ሕይወትን ከማበልፀግ የበለጠ አንዳችም ቁምነገር እንደሌለ፣ ሕይወትን ከማሻሻል ውጭ ቅንጣት በጎነት እንደማይገኝ፣ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም።
ረሃብና መስኖ፣… ‘የሞት ሽረት’ ጉዳይ መሆናቸውን መገንዘብ እንደማለት’ኮ ነው።
በዚህ መሃል፣… ኢትዮጵያ፣ በግድብና በመስኖ እንዳትጠቀም፣ አለማቀፍ ዘመቻ ሲታወጅ ብንመለከት፤… በሕይወታችን ላይ አልተዘመተም እንላለን? ዘመቻው፣ ሚስጥራዊ ሴራ አይደለም። የዘመቻው ሰነድ፣ በዩኤን የእርዳታ ማስተባበሪያ ድረገፅ ላይ፣ ቦታ ተሰጥቶት፣ ፊት ለፊት ይታያል።
አስገራሚው ነገር፣ የዩኤን “የእርዳታ ማስተባበሪያ” ድርጅት፣ የዛሬ ሰላሳ ዓመት ገደማ የተቋቋመው፣ በኢትዮጵያ ሰበብ ነው – በ77 ዓ.ም ድርቅ። እስከዛሬም፣ ከድርጅቱ መደበኛ ስራዎች መካከልም፣ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሚሊዮኖች ለረሃብ ተጋልጠዋል’ እያለ  የእርዳታ ጥሪ ማስተላለፍ ነው። (reliefweb.int/country/eth የሚለውን ድረገፅ መመልከት ይቻላል)። የእርዳታ ጥሪው፣ ከወር ወር፣ ከዓመት ዓመት አይቋረጥም።
ከዓለማችን የመጨረሻ ድሃ አገራት አንዷ!
አለማወቃችን እንጂ፣ የዘንድሮው የረሃብ አደጋ፣ ድንገተኛ ‘ዱብዕዳ’፤… ወይም ያልተለመደ ጊዜያዊ አደጋ አይደለም። ቀድሞውንም፣ ከአደጋ የራቅንበት ዓመት የለም።
በጭፍን፣ “ሽራፊ የኢኮኖሚ እድገት አልተገመዘገበም” ለማለት ፈልጌ አይደለም። እንዲያውም፣ ሰሞኑን፣ የዓለም ባንክ ያሰራጨውን ሪፖርት መመልከት እንችላለን። እንደ አበባ፣ እንደ ርችት፣ የደመቀ የተንቆጠቆጠ ሪፖርት ነው።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት፣ ልዩ እና አስደናቂ መሆኑን ይተነትናል – ይሄው አዲስ የዓለም ባንክ ሪፖርት። እናም፣ ከ15 ዓመት በፊት፣ “የዓለማችን ሁለተኛዋ ድሃ አገር” የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በፈጣን እድገት ተሻሽላ፣ “የአለማችን፣ 11ኛዋ ድሃ አገር” ለመሆን እንደበቃች ሪፖርቱ ይገልፃል።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ድህነት ከመብዛቱ የተነሳ፣ “ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት” የሚል ሙገሳ ውስጥ እንኳ፣ የአገሪቱ ድህነት ጎልቶ ይታያል። ድንገት የተከሰተ ዱብዳ፣ አልያም ለከርሞ ብን ብሎ የሚጠፋ ‘ጊዜያዊ እንቅፋት’ አይደለም። የአገራችን የረሃብ አደጋም፣ እንደዚያው ነው።
አምናና ካቻምና፤ ዘንድሮና በሚቀጥለው አመት…
ከዘንድሮው የድርቅ አደጋ በፊትም ቢሆን፣ ከዓመት ዓመት፣ የእህል እርዳታ ወይም ድጎማ ካላገኙ፣ ኑሮን መቋቋም የማይችሉ የገጠር ነዋሪዎች፣ አስር ሚሊዮን ይሆናሉ።
“የምግብ ዋስት” ድጎማ
በአንድ ወገን፤ ‘ከጥር በኋላ፣ ጓዳቸው ይመናመናል’ ተብለው ለድጎማ የሚመዘገቡ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ። ድጎማ ካላገኙ፣ ኑሯቸው ይናጋል። እናም ከጥር እስከ ሰኔ ድረስ፣ የእህል ወይም የብር ድጎማ ይሰጣቸዋል – በየዓመቱ። “የምግብ ዋስትና ፕሮግራም” ይሉታል። ይሄ ብቻ አይደለም።
“ደራሽ እርዳታ”
ደራሽ እርዳታ፣… “ክፉኛ፣ ለረሃብ ተጋልጠዋል” ተብለው ለሚመዘገቡ ሰዎች የሚዘጋጅ እርዳታ ነው። የእነዚህ ተረጂዎች ቁጥር፣ በየዓመቱ፣ አነሰ ቢባል፣ ወደ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ይሆናል።
በአጠቃላይ፣ በየዓመቱ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ 10 ሚሊዮን ሰዎች፣ ለረሃብ ይጋለጣሉ ማለት ነው። ለዚያውም፤ የዝናብ እጥረት በሌለበት ዓመት!
የዝናብ እጥረት ሲያጋጥምስ?
ድርቅ ከመጣ፣ የችግረኞችና የተረጂዎች ቁጥር እንደሚጨምር፣ የረሃብ አደጋውም እንደሚባባስ፣ ምን ጥርጥር አለው? የዝናብ እጥረትና ድርቅ ደግሞ፣ አልፎ አልፎ መከሰቱ እንደማይቀር ግልፅ ነው። እንዴት ይጠፋናል?
ያው፤ የዘንድሮ ዓይነት ድርቅ ሲከሰት፤ የዘንድሮ ዓይነት የረሃብ አደጋ መፈጠሩ፤ በጭራሽ ‘ዱብዳ’ አይደለም።
በእርግጥ፤ ከረሃብ አደጋ ርቀን የተጓዝን ይመስል፤ የዘንድሮውን አደጋ፣ ‘ጊዜያዊ እንቅፋት’ ሊያስመስል ይሞክራል – መንግስት። ነገር ግን፣ አደጋው፣ ‘ከስኬት ሆይሆይታ’ የሚያስተጓጉል፣ ‘ጊዜያዊ እንቅፋት’ አይደለም።
በተቃራኒው፣ ከአጠገባችን ርቆ የማያውቅ፣ ነባር አደጋ ነው። ‘ጊዜያዊ እንቅፋት ነው’ እያሉ መነዛነዝ ምን ዋጋ አለው? በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ተረጂዎች ነበሩ። ዘንድሮ ወደ 15 ሚሊዮን ጨመረ። ማለትም፣… ‘ነባሩ አደጋ’ ነው ዘንድሮ የተባባሰው።
በርካታ ተቃዋሚዎችም እንዲሁ፤ የረሃብ አደጋው፣ በኢትዮጵያ ያልነበረና፣… ድንገት መንግስት ጎትቶ ያመጣው፣ ‘ዱብዳ’ እንግዳ ያስመስሉታል።… ለነገሩ፤ በሚቀጥለው ዓመት፣ ዝናቡ ደህና ከሆነ፣ የረሃብ አደጋው፣ ትንሽ ይቃለላል። እናም፤ አደጋው ጨርሶ የጠፋ ያህል፣ መነጋገሪያ መሆኑ ይቀራል፤ ይረሱታል።
አደጋውን የምንረሳው ግን፤… የተረጂዎቹ ቁጥር፣ ከ15 ሚሊዮን ወደ አስር ሚሊዮን ስለሚቀንስ ብቻ ነው! አደጋው ካልከበደ በቀር፤ የመናቆሪያ ሰበብ ሊሆንልን ስለማይችል፤ እርግፍ አድርገን እንተወዋለን።
ለዘለቄታውስ?
በእስካሁኑ አያያዛችን የምንቀጥል ከሆነ፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ እንደገና የዝናብ እጥረት መከሰቱና የረሃብ አደጋ መክበዱ አይቀርም። ያኔ፣ እንደገና፣ በውግዘትና በማስተባበያ፣ የመናቆር ጩኸት ይጋጋላል።… ግን አደጋው ቀለል ሲል፤ እንዘነጋዋለን፤… ያው፤ ተመልሶ እስኪባባስ ድረስ።
ማለቂያ የሌለው አዙሪት!
የዛሬውን ከባድ አደጋ ከማቃለል ጎን ለጎን፤ ለዘለቄታውም ማሰብ ካልጀመርን፣ … ከገደሉ አፋፍ ለመራቅ ዘዴ ካላበጀን፣… እያሰለስን፣ ወደ ከባዱ አደጋ ስንመላለስበት… ይታያችሁ።
እናም፣ አደጋውን እንደ አዲስ፣ “ድንገተኛ ዱብዳ” እያስመሰልን እሪ የምንልበት፣ “ጊዜያዊ እንቅፋት” እያስመሰልን በማስተባበያ የምንነዛነዝበት አጋጣሚ ሲሆንልን አስቡት።
ለመሆኑ ከምር ይቆረቁረናል ወይ?
ከእርሻ ተሻግሮ በኢንዱስትሪ ለማደግና የስራ እድል ለመፍጠር ያልቻለ ኢኮኖሚ… የድህነት ኢኮኖሚ የመሆኑን ያህል፤በዝናብ ላይ ብቻ የሚተማመን እርሻ፣… የድህነት እርሻ ነው። የገደል አፋፍ ላይ የተንጠለጠለ ኑሮ፤ ቢበዛ ቢበዛ፣ ከእጅ ወደ አፍ ስለሆነ፤ትንሽ ዝናብ ሲዛባ፣ ወደ ከባድ የረሃብ አደጋ እንገባለን።
ጥያቄው እዚህ ላይ ነው። ‘የረሃብ አደጋ’፣ የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ካርድ መስሎ ካልታየን በቀር፣… ‘የሞትና የሕይወት ጉዳይ’ መሆኑን ከምር የምንገነዘብ ከሆነ፤ ተመፅዋችነት ከምር የሚቆረቁረን ከሆነ፤…  የኢንዱስትሪ፣ የግድብ፣ የመስኖ ‘ተቆርቋሪ’ መሆን የግድ አይደለም ወይ?
ታዲያ፤ በኢትዮጵያ፣ የግድብ ግንባታ እንዳይጀመር፣ የተጀመረውም እንዲቋረጥ… ሰፊ ዘመቻ ሲካሄድ፣ ምነው አልቆረቆረን? የአለም ባንክ፣… ከዚያም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣… ለግድብ ግንባታ አንዳችም ብድር ላለመስጠት ሲወስኑ፣ ያን ያህልም አላሳሰበንም።
ለምንድነው፣ ብድር የከለከሉት? “የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ነን” በሚል ነው። ‘የወንዝ ነባር ጎርፍ’፣ ‘የአካባቢውን ነባር ገፅታ’፣ ‘ነባሩ የእርሻ አሰራርና አኗኗር’፣…
እንደ ድሮው ተጠብቆ መቀጠል አለበት። ግድብ ከተገነባ ግን፣ “ተፈጥሯዊ ያልሆነ”፣ “አርቴፊሻል ኃይቅ” ይፈጠራል በማለት ይቃወሙታል። መስኖ ከተዘረጋ፣ የድሮው እርሻና አኗኗር ይለወጣል በማለት ያወግዙታል።
በእርግጥም፣ መስኖና ግድብ፣ “ከአካባቢ ጥበቃ” እና “ከባህል ጥበቃ” ጋር ይቃረናል። ምን ጥርጥር አለው? ግድብና መስኖ የሚገነባው፤ ነባሩን አካባቢና አኗኗር ለመቀየር ነው። … ለማሻሻል። ከሁለቱ፣ አንዱን መምረጥ የግድ ነው። አንድም፤ “የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች” እንደሚነግሩን በነባሩ መንገድ፣ ረሃብተኛና ተመፅዋች ሆኖ መቀጠል ነው። አልያም፤ የረሃብ አደጋው ይቆረቁረናል የምንል ከሆነ፤ በመስኖ ከረሃብና ከተመፅዋችነት ለመውጣት ተጣጥረን ሕይወትን ለማሻሻል መምረጥ እንችላለን – የሕይወት፣ የመስኖ ተቆርቋሪነትን መምረጥ። ከየትኛው ነን?
ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ በኢትዮጵያ የግድብና የመስኖ ግንባታዎችን በመቃወም፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች አለማቀፍ ዘመቻ ጀምሯል። ይሄ ይቆረቁረናል ወይ?
ወይስ፤ የዩኤን የእርዳታ ማስተባበሪያ ድረገፅ ላይ እንደምናየው፤ በአንድ በኩል የእርዳታ ጥሪ እየለፈፍን፤ ከዚሁ ጎን ለጎን፣ ረሃብተኛና ተመፅዋች ሆኖ መቀጠልን እንፈቅዳለን? ኢትዮጵያ፣ ግድብንና መስኖን እንዳትጠቀም ለመከልከል የተዘጋጀውን የዘመቻ ሰነድ ማስተጋባት ወይም በቸልታ መመልከት፣ ሌላ ትርጉምና ውጤት ሊኖረው አይችልም – ነባሩን ረሃብና ምፅዋት በፀጋ እንደመቀበል ነው።

ድርቅ ባይኖርም በየቀኑ፣ከ500 በላይ ሕፃናት ይሞታሉ; የኢትዮጵያ ችግር፣ ከቢቢሲ ዘገባም ይብሳል!

Written by  ዮሐንስ ሰ.=== በኢትዮጵያ የረሃብ አደጋ ላይ ያተኮረው የቢቢሲ ዘገባ፣ ይሄውና ብዙዎችን እያወዛገበ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል።
የጋዜጠኛውን ዘገባ፣ በአድናቆት የሚያሞግሱ በርካታ ሰዎች፣ ‘መንግስት፣ የረሃብ አደጋውን ችላ ብሏል፤ መረጃም ደብቋል’ በማለት መራራ ትችት አውርደውበታል።


መንግስት በበኩሉ፣ በቢቢሲ ዘገባ ተቆጥቶ፣ በየአቅጣጫው ሲያስተባብል ሰንብቷል። በአንድ የዜና ዘገባ፣ እንዲህ ግራ ቀኙ በውዝግብ መተራመሱ አይግረማችሁ። እንዲያውም፣ በዘገባው መሃል በገባች አንዲት አጭር ዓረፍተነገር ነው፣ አገር ምድሩ የተናወጠው።
“በአንድ አካባቢ፣ በየእለቱ ሁለት ህፃናት እንደሚሞቱ ዩኤን ይገልፃል” ብሏል የቢቢሲው ጋዜጠኛ። “The UN says that in one area, two babies were dying every day”…
በ13 ቃላት የተነገረች አጭር አረፍተነገር ናት። ግን የተራራ ያህል፣ ከፍተኛ ድንጋጤ፣ ቁጣ፣ እና ውዝግብን ፈጥራለች።
በጣም አስደንጋጩ ነገር… ምን መሰላችሁ?
ያቺ፣ አስደንጋጯ ዓረፍተነገር፣ ከእለት ተእለት፣ ከዓመት ዓመት፣ የአገራችን የዘወትር ሕይወት ናት።
የኢትዮጵያ ድህነት፣ የሕፃናት ሞት…
ከባድ ድርቅ ባያጋጥም እንኳ፣ ‘ደህና’ በሚባለው ዓመትም፣ ብዙ ሕፃናት የሚሞቱባት፣ እጅግ ድሃ አገር ናት – ኢትዮጵያ። በየቀኑ፣ ከ500 በላይ ሕፃናት እንደሚሞቱ ታውቃላችሁ? በዓለም ወይም በአፍሪካ ማለቴ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ!
ብዙዎቻችን ይህንን አናውቅም። ለምን? የአገራችንን የድህነት መጠን፣ በደንብ አንገነዘበውም። አምና 190ሺ ህፃናት ሞተዋል – እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት። እንዲሁ ልናስበው ስለማንፈልግ እንጂ፣ ይሄ ሚስጥር አይደለም። የዩኤን፣ የዩኤስኤአይዲ፣ የአለም ባንክ ሪፖርቶች ላይ በየዓመቱ የሚመዘገብ፣ ቁጥር ነው። ካቻምና ወደ ሁለት መቶ ሺ ገደማ፣ ህፃናት ሞተዋል። ዘንድሮም፣ እንደዚሁ…
በመላ አገሪቱ፣ በየወረዳው፣ በየቀኑ… ከ500 የሚበልጡ ሕፃናት ይሞታሉ።
ለምን? ከቅርባችን የምናገኘው ትልቁ የሞት መንስኤ፣ ድህነት ነው። በርካታ ህፃናት፣ ተርበው ባይሞቱም እንኳ፣ በምግብ እጥረት ይዳከማሉ። ከመቶ ሕፃናት መካከል፣ አርባ ያህሉ በምግብ እጥረት የተጎዱ ናቸው። አስር በመቶ ያህሉ ደግሞ፣ ሰውነታቸው እጅጉን ይመነምናል። በሽታ የመቋቋም አቅማቸው ይዳከማል። እናም፣ ለወባ ወይም ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሲጋለጡ፤ ብዙዎቹ ይሞታሉ። ማለትም… በየእለቱ 500 ህፃናት!
የአገራችን ድህነት፣ የዚህን ያህል የከፋ ነው። …ከሦስት ሰዎች አንዱ፣ ከሦስት ሕፃናት አንዱ፣ በምግብ እጥረት የሚቸገረው፣ ሁልጊዜ ነው። መደበኛ የዘወትር ሕይወት! (ድርቅ በሌለበት ዓመትም ጭምር… ወይም፣ “በእህል ምግብ፣ ራሳችንን ችለናል” በተባለበት ዓመትም ጭምር)።
ታዲያ፤ በእንዲህ አይነት ድህነት መሃል፣ መንግስት፣ “በእህል ምግብ ራሳችንን ችለናል” ብሎ ሲያውጅ፣ አይገርምም?
ባለፉት አስር ዓመታት፣ ፈጣን እድገት ታይቷል፣ ብሎ መናገር፣ አንድ ነገር ነው። ከድህነት እንደተላቀቅንና የምግብ እጥረት እንደተቃለለ አድርጎ መናገር ደግሞ፣ ሌላ ነገር ነው። የኢትዮጵያ ድህነት፣ ከብዙዎቹ ድሃ የአፍሪካ አገራትም እንደሚብስ ይረሳዋል መሰለኝ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአገሪቱ ድህነትና ረሃብ፣ የመንግስት ችግር ብቻ የሚመስላቸውም ሞልተዋል – የአገሪቱን የድህነት መጠን በትክክል ባይገነዘቡት ነው። ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት፣ ‘ከዓለም አንደኛ’ በተባለ ፍጥነት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢያድግ ብላችሁ አስቡ። ድንቅ ነው። ግን፣ “ከድህነት ለመላቀቅ የሚረዳ፣ ጅምር ጉዞ”… ከመሆን አያልፍም። ያኔም፣ ከአብዛኞቹ ድሃ የአፍሪካ አገራት በታች፣ ከመሆን አያድነንም።
ስለየትኛው አገር ነው የምናወራው?
አንድ ሁለት መረጃዎችን ልድገምላችሁ።… በአመት አንዴ፣ ስጋ ለመብላት የሚቸገር ሕዝብ ያለባት፣ በጣም ድሃ አገር ውስጥ ነን ያለነው። ከ15 ሚሊዮን ቤተሰቦች መካከል፤12 ሚሊዮን ቤተሰቦች፣ በአመት አንዴ፣ ቢያንስ ቢያንስ ለዓመት በዓል፣ በግ ወይም ፍየል ለማረድ አቅም የላቸውም። እሱስ ይቅር። 6 ሚሊዮን የገበሬ ቤተሰቦች፣ የእርሻ በሬ የላቸውም።
እዚህች አገር ውስጥ፣… “የከብቶች እበትና ትንፋሽ፤ ለአለም ሙቀት መጨመር አደጋ ስለሆነ፤ እርምጃ መውሰድ አለብን” ተብሎ ሲነገር ይታያችሁ። በስህተት ያመለጠ፣ ተራ ንግግር እንዳይመስላችሁ! ለዚያውም፤ በአመታዊ የፓርላማ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነው፤ ይሄ የተነገረው። የመንግስትና የኢህአዴግ ጥፋት ከመሰላችሁም ተሳስታችኋል። ብዙዎቹ ምሁራንና ብዙዎቹ ፓርቲዎች የሚስማሙበትና የሚደግፉት ጉዳይ ነው።
“የአካባቢ ጥበቃ” እና “የአለም ሙቀት መጨመር”፣ “አረንጓዴ ልማት” … እየተባለ፣ ሌትተቀን በየሚዲያው የጋዜጠኛ፣ የምሁር፣ የፖለቲከኛና የባለስልጣን፣ የገዢና የተቃዋሚ ፓርቲ ተመሳሳይ ዲስኩር የምንሰማው ለምን ሆነና! የከብቶች ትንፋሽና እበት ያስጨንቃቸዋል – በአመት አንዴ ስጋ ለመብላት የሚቸገር ሕዝብ በሞላበት ድሃ አገር ውስጥ ሆነው።
ከአስር የገበሬ ቤተሰብ መካከል አራቱ፣ የእርሻ በሬ የላቸውም… እንዲህ፣ ድህነት ክፉኛ በደቆሳት አገር ውስጥ ሆነን፤ “የከብቶች እበት፣ ለአለም ሙቀት አደገኛ ነው… ወይም አደገኛ ሊሆን ይችላል” … ብለን እንጨነቅ?
ይህም ብቻ አይደለም።
የኢትዮጵያ ገበሬዎች፣ በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ አጠቃቀም፣ እጅጉን ወደ ኋላ ቀርተው እንደቆዩ ይታወቃል። ያው፣ በድህነትስ ወደ ኋላ ቀርተን የለ!
ታዲያ፣ በዚህችው አገር፣ ምርጥ ዘርንና ማዳበሪያን በማጥላላት፣ የተቃውሞ ዘመቻ ሲካሄድ ማየት ነበረብን? ‘ምርጥ ዘርን መጠቀም፣ ነባር የዘር ዓይነቶችን ማግለል ነው’ የሚል ተቃውሞ፤ እንደ ቁምነገር ተቆጥሮ ሲስተጋባ አይገርምም? ለዚያውም፣ በመንግስታዊ ተቋም… ለዚያውም በምሁራን… ለዚያውም፣ መዓት ሕዝብ በተራበበት ዓመት፡፡  ስለየትኛው አገር ነው የሚያወሩት?
ሌላስ?
26ሺ የገጠር ቤተሰቦች፣ “በፀሐይ ኃይል፣ ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ መሳሪያ” ተገጥሞላቸዋል የሚል ሪፖርት አለላችሁ። ወጪውን ደግሞ ልንገራችሁ፤ 270 ሚሊዮን ብር!
መሳሪያው የተገጠመው፤ ለገጠር ጤና ጣቢያ፣ ለትምህርት ቤትና ለመሳሰሉት ቢሆን እሺ። ለምን? ቀን ላይ፣ ለስራ ነው፣ ኤሌክትሪክ የሚፈልጉት። ቀን ላይ፣ ብዙውን ጊዜ፣ ፀሐይ ይኖራል። በመኖሪያ ቤት ወይም ጎጆ ውስጥ ግን፣ በአብዛኛው፣ ማታ ማታ ነው ኤሌክትሪክ የሚያስፈልገን። ግን፣ ማታ ፀሃይ የለም። እና፣ ይሄ ሁሉ ብር የሚባክነው፣ ለምንድነው?
“ምናልባት፣ ቀን ላይ ምግብ ለማብሰል ይጠቀሙበት ይሆናል” እንበል? ዋናውን የኤሌክትሪክ መስመር፤ ወደ ሁሉም የገጠር ቤተሰብ ማድረስ አይቻልም። ስለዚህ፣ ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም፣ የፀሃይ ሃይል መሳሪያ ይገጠምላቸው? በአገሪቱ ድህነት ላይ፣ ተጨማሪ ሸክም ቢሆንም…
እሺ ይሁን። ግን፣ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ፣ ለኮንዶምኒዬም ቤቶችም፣ ‘በፀሐይ ሃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ መሳሪያ’ ይገጠምላቸዋል የሚል መግለጫ በቅርቡ ሰምተናል። እንዴት ነው ነገሩ? ኤሌክትሪክ የሚቸግረን፣ በማታ ነው። ማታ ደግሞ፣ ፀሐይ የለም። ይሄ ግልፅ አይደለም?
ደግሞምኮ፣ ኮንዶምኒዬም ቤቶቹ፣ እንደማንኛውም የከተማ ቤት፣ መደበኛው የኤሌክትሪክ መስመር ይዘረጋላቸዋል። የፀሐይ ሃይል መሳሪያው፣… ተጨማሪ ነው።
ተጨማሪ ጥቅም የለውም። ተጨማሪ ወጪ ብቻ! መሳሪያውን ለመግጠም፣ በገጠር፣ ለአንድ ቤተሰብ፣ ከ10ሺ ብር በላይ ወጪ ያስከትላል። ፍሪጅ፣ ኤሌክትሪክ ምጣድ፣ ካውያና ወዘተ በበዛበት ከተማማ፣ ለአንድ መኖሪያ ቤት፣ የ10ሺ ብር መሳሪያ አይበቃውም። ምንም ተጨማሪ ጥቅም ለማያስገኝ ነገር፣ እንዲህ በከንቱ፣ የድሃ አገር ሃብት ለማባከን መቻኮል ምንድነው? በደፈናው፣ “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “ታዳሽ ሃይል”፣ “አረንጓዴ ልማት” ለሚሉ ቃላት ነው፤ ያን ሁሉ ሃብት በከንቱ የምንገብረው። እና ደግሞ፤ ዞር ብለን፣ ስለ ኢትዮጵያውያን ረሃብ፣ ተቆርቋሪ ሆነን እናወራለን።
እንዴ… ካሁን በፊት፣ በነፋስ ተርባይን ሳቢያ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የድሃ አገር ሃብት ባክኗል። እስካሁን ከተተከሉት ተርባይኖች ይልቅ፣ በ5 ቢሊዮን ብር የተገነባ ግድብ ይሻላል። ብዙ የኤሌክትሪክ መጠን ያመነጫል። ለነፋስ ተርባይኖቹ የወጣው ወጪ ግን፣ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ቀላል ብክነት አይደለም። የአስር ቢሊዮን ብር ብክነት? ዘንድሮ በድርቅ ለተጠቁ ሰዎች የሚያስፈልግ እህል፣ አሟልቶ ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ነው።
አሁን ደግሞ፣ “የፀሐይ ሃይል” እየተባለ… ሃብት ይባክናል።
አላዋቂነትና ቀልድ አልበዛም? አገሪቱ፤ በኤሌክትሪክ ሃይልና በብልፅግና የተንበሸበሸች ብትሆን ኖሮ፣… ብክነቱን ስንመለከት፣ … “ጥጋብ ነው” ብለን ባጣጣልነው ነበር። ኢትዮጵያ ግን፣ ከሃብታም አገራት ጋር ሳይሆን፣ ከድሃ የአፍሪካ አገራት ጋር ስትነፃፀር እንኳ፣ በድህነትና በኤሌክትሪክ እጦት፣ ወደኋላ የቀረች ጨለማ አገር ናት። በእርግጥ፣ ሌሎች ድሃ የአፍሪካ አገራትም… ያው ጨለማ ናቸው። ግን፣ ከእነሱ ጋር ሲነፃፀር፣ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ፍጆታ፣ ግማሽ ያህል እንኳ አይደርስም። እና እዚህች አገር ውስጥ ነው፤ የነፋስ ተርባይን እና የፀሃይ ሃይል እየተባለ፣ ሃብት የሚባክነው።
ይሄ ሁሉ ሃብት የሚባክነው ደግሞ፤ “አረንጓዴ ልማት”፣ “የአለም የሙቀት መጠን”፣ “የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት”፣ “የአካባቢ ጥበቃ”… በሚሉ ዝባዝንኬ መፈክሮች ነው!
“ካርቦንዳይኦክሳይድ”?
ኢትዮጵያ ጨርሶ የሌለችበትን! መች ነዳጅ ለመጠቀም በቃንና!
“የአለምን ሙቀት እንዲጨምር ያደርጋል” የሚባለው ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ከሞላ ጎደል፣ ከነዳጅ ፍጆታ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ፣ እጅግ ድሃ ከመሆኗ የተነሳ፣ የነዳጅ ፍጆታዋ፣ ከአለም እጅግ… እጅግ ዝቅተኛ ነው። ከቁጥር የሚገባ አይደለም።
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የ150 ሰዎች የነዳጅ ፍጆታ፣ በበለፀጉት አገራት፣ የአንድ ሰው ፍጆታ ነው። የበለፀጉትን አገራት እንተዋቸው። አጠገባችን ያሉት ድሃ የአፍሪካ አገራት እንኳ፣ የነዳጅ ፍጆታቸው ከኢትዮጵያ በአስር እጥፍ ይበልጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በፍፁም በፍፁም፣ ስለ ‘ኮርባንዳይኦክሳይድ’ መወራት አልነበረበትም።
ግን፣ ዋና ወሬ አድርገነዋል። ምን ማውራት ብቻ! በዚሁ ዝባዝንኬ መፈክር ሰበብ፣ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ሃብት እንዲባክን ይወስናሉ። የት አገር ያሉ እየመሰላቸው ይሆን? ግን፣ ብዙዎቻችን፣ ብክነቱን እንፈቅዳለን፤ እንደግፋለን፤ እናጨበጭባለን።
ያው፣ መንግስትን አምርረው የሚተቹ ብዙ ፖለቲከኞችና ዜጎችም፣ አገሪቱን በወጉ አያውቋትም። በአንዱ ፓርቲ ምትክ፣ ሌላ ፓርቲ ስልጣን ላይ ቢወጣ፣ አንዱ ባለስልጣን ተሽሮ፣ በቦታው ሌላ ቢሾም… በአንዳች ተዓምር፣ በማግስቱ፣ የኢትዮጵያ ድህነትና ችጋር፣ ብን ብሎ የሚጠፋ ይመስላቸዋል። ወይም… በአመት፣ ቢበዛ ደግሞ በሁለት ዓመት፣ ዘገየ ከተባለ ደግሞ በአምስት ዓመት፣… ብልፅግና እንዲፈጠር ይመኛሉ። የአገሪቱን የድህነት አይነትና መጠን በወጉ አልተገነዘቡትም።
አንዳንዶቹ ደግሞ፣ …የሆነች ያህል ገንዘብ ብናዋጣና ብንለግስ፣ የአገሬው ችግር ሁሉ መፍትሄ የሚያገኝ ይመስላቸዋል። በቃ፤ ያኔ… የተቸገረ አዛውንት ሁሉ በምቾት ይኖራል።… የታመመ ሁሉ፣ ያሻውን ያህል ይታከማል።… ምግብና መጠለያ ያጣ ሰውም፣ ከችጋር ነፃ ይሆናል… ብለው ያልማሉ – በመዋጮና በምፅዋት።
እውነታው ግን፣ የአገሪቱን እንቁላሎች ሁሉ፣ ለህዝቡ እናካፍል ብለን ብናዋጣና ብንለግስ፣ አዳሜ… በዓመት ከአንድ እንቁላል በላይ አይደርሰውም። የሌለንን እንቁላል ከየት አምጥተን እንለግሳለን? ሌላውም ችግር ተመሳሳይ ነው። ለልገሳ የሚሆን ብዙ ሃብት የለም። አገሬው ድሃ ነው። ይህንን ከፍተኛ ድህነት፣… እውነታውን  ከምር ብንገነዘብ ኖሮ፣ በቢቢሲው ዘገባ፣ ቅንጣት የምንወዛገብበት ምክንያት አይኖርም ነበር። ይልቅ፣ መፍትሄ ለመፈለግና ለማበጀት እንተጋ ነበር።እውነታውን ሳንገነዘብ፣ ወይም ለመገንዘብ ፈቃደኛ ሳንሆን የምንቀጥል ከሆነ ግን፤ መፍትሄውን የማሰብና የማግኘት ተስፋ አይኖረንም። ወይ፣ በዝባዝንኬ ሰበቦች፣ ሃብትን እናባክናለን። አልያም፣ ፓርቲና ባለስልጣን በማፈራረቅ ብቻ፣ ተዓምረኛ ለውጥ የምናመጣ መስሎን፣ ያለፋታ እየተናቆርን፣ በአዙሪት ጉዞ ሕይወታችንን እናባክናለን። በሌላ አነጋገር፤ የቢቢሲ ጋዜጠኛ፣ ችግራችንን እስኪነግረን ድረስ እየጠበቅንና መወዛገቢያ እያደረግን፤ እኛው እንባክናለን።

ከመጠምጠም መማር ይቅደም | መስፍን ወልደ ማርያም [ፕሮፌሰር]

 

mesfin

በፌስቡክ የምንሰባሰበው ለመወያየት፣ አንዱ ከሌላው እንዲማር፣ መረጃዎችን በነጻነት እንድንለዋወጥ፣ ይህንን ሁሉ በማድረግ ራሳችንን ለማሻሻል፣ የእኛ መሻሻል እየተራባና እየተባዛ የአገርና የሕዝብ መሻሻል እንዲሆን፣ ከተቻለንም ከአገራችንና ከሕዝባችን አልፈን የምንታይ የዓለም አካል እንድንሆን መስሎኝ ነበር፤ ሳየው በዚያ መንገድ ላይ ያለንና ፌስቡክን ለበጎ ዓላማ እየተጠቀምንበት ያለን አይመስለኝም፤ ስለዚህ ወይ መታረም፣ አለዚያም በፌስቢክ ጊዜ ማጥፋቱን መተው ምርጫ ሊሆንብን ነው፡፡

ምናልባት 99.99% በእኔ ሰፈር ያሉ የፌስቡክ ተሳታፊዎች ወደፌስቡክ የሚገቡት ለመናገር ነው፤ መናገር የህልውናቸው ምስክር ወይም ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱት ጥቂት አይደሉም፤ ካልተናገሩ የሌሉ ይመስላቸዋል፤ ዋናው ነገር መናገር ይሆንና የሚናገሩት ነገር ወይም ጉዳይ ሌላው ቀድሞ ከተናገረው ጋር የሚያያዝ (የሚቃወመው ወይም የሚደግፈው) ሳይሆን ፈጽሞ ወደተለየ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ አዲስ ርእስ መክፈት የተለመደ ነው፤ የአብዛኛው ፍላጎት ማስተማር ወይም ማሳወቅ ነው፤ ማስተማር ወይም ማሳወቅ ቀላል ነው፤ መናገር የሚችል ወይም ፊደሉን አውቆ መጻፍ የሚችል ማስተማር ይችላል፡፡

የትምህርት ቤት ጓደኛዬ በጃንሆይ ዘመን ትልቅ ሚኒስትር ነበር፤ በደርግ ዘመን ለብዙ ዓመታት ታስሮ ሲወጣ ሥራ አልነበረውም፤ ችሎታውን ስለማውቅ በዩኒቨርሲቲ እንዲያስተምር አመቻቸሁለትና ማስተማር ጀመረ፤ ከጥቂት ወራት በኋላ ስንገናኝ ‹‹እኔ ማስተማር ቀላልና እረፍት የሞላበት ሥራ ይመስለኝ ነበር፤ ለካ አንቅልፍ የሚያሳጣ ነው! እዝናናለሁ ባልሁ ቁጥር አንድ ክፍል ሙሉ ተማሪዎች ተሰብስበው ዓይኖቻቸውን እያቁለጨለጩ ምን እንደማስተምራቸው ሲጠብቁ ይታዩኛል! እረፍት ይነሡኛል!›› አለኝ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ማስተማሩን ተወ፤ ኅሊና ላለው ሰው ማስተማር ቀልድ አይደለም፤ ያደክማል፤ ለማስተማር መማር ያስፈልጋል፤ ለማሳወቅ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ከመማር ይልቅ ማስተማር፣ ለማወቅ ከመጣር ይልቅ ለማሳወቅ መጣር የሚቀልለው ሰው የእውቀት ሰው አይደለም፤ ሌላ ሥራ ቢመርጥ ይሻለዋል፡፡

ሳያውቁ ለማሳወቅ አደባባይ መውጣት ከችኮላ ወይም ከስንፍና፣ ከትዕቢት ወይም ከግዴለሽነት የሚመጣ ነገር ይመስለኛል፤ ውሎ አድሮ ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም፤ በአደባባይ መናገር ወይም መጻፍ የመጨረሻው መጋለጥ ነው፤ በአደባባይ መናገርና መጻፍ በሕዝብ ፊት መጋለጥ መሆኑን ብዙ ሰዎች አያውቁም፤ በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ሰዎች ይህንን መጋለጥ ፈርተውትና ሸሽተውት የሚርቁት አሉ፤ መጋለጥን ፈርተው ዓይኖቻቸውን ዘግተው፣ ጆሮዎቻቸውን ደፍነው፣ አፋቸውን ለምግብና ለመጠጥ በቀር የማይጠቀሙበት፣ ዝምታ ወርቅ ነው እያሉ ወርቅ የሚሸምቱበት ብዙ ናቸው፤ ከሕዝብ ጋር እየተጓዙ፣ በሕዝብ መሀል እየኖሩ የሕዝብ ጉዳይ (ፖሊቲካ) አይመለከተንም የሚሉ የማሰብ ችሎታቸውን ህልውና ይጠራጠሩ፤ የማሰብ ችሎታ ከሌለ የማወቅ አምሮት ወይም ምኞት የሚኖር አይመስለኝም፤ የማወቅ አምሮት በሌለበት የማሳወቅ አምሮት ጎልቶ ሲወጣና ሲደናበር ማየት በጣም የተለመደ እየሆነ ነው፤ ፌስቡክ የሚባለው መድረክ የመደናበሪያ መድረክ እየሆነ ነው፡፡

የማሰብ ችሎታው የሌላቸው ሰዎች ከሁለት አንዱን መንገድ በመምረጥ፣ ወይም በሁለቱም መንገዶች በመጠቀም ይሳተፋሉ፡– የማያውቁትን ለማሳወቅ በመሞከርና በዘለፋ! የማያውቁትን ለማሳወቅ መሞከርና ዘለፋ የባሕርይ ግንኙነት አላቸው፤ አሁን እዚያ ውስጥ አንገባም፤ በተለያዩ መስኮች፣ በተለያዩ ጉዳዮች፣ በተለያዩ የእውቀት ጥበቦች በሚያሰራጩት ፍንጥቅጣቂ በአእምሮና በመንፈስ ለመበልጸግ በመጣር ፈንታ በአጉል ትዕቢትና ፉክክር፣ በማይጠቅም ዘለፋና ማስፈራራት የፌስቡክን መድረክ ማበላሸትና ማርከስ ወደኋላ ይጎትተናል እንጂ ወደፊት አያራምደንም፡፡

መሠረታዊ የማሰብ መነሳችን ሳንገነዘብ የማሰብ ትርምስምስ ውስጥ እንገባና መውጣት ያቅተናል፤ ለምሳሌ በእውቀትና በእውነት መሀከል ያለውን ልዩነት ሳንገነዘብ እምነትን ስንሞግት የራሳችንንም ሆነ የሌላውን ጊዜ እናጠፋለን፤ እውቀትን በሙግት ለማጣራት ሲመጡብን ደግሞ ቶሎ ወደእምነት እንዞራለን፤ አጉል መሽከርከር ውስጥ እንገባለን፤

እንዲያው በሆነ ባልሆነው፣ ባወቅነውም ሆነ ባላወቅነው የመጣልንን ሁሉ መዘርገፍ አዋቂ አያሰኝም፤ ጎበዝ አያሰኝም፤ ብልህ አያሰኝም፤ ግን ባለጌ ያሰኛል፤ ባለጌ ነጻነትን አያውቅም፤ ለባለጌ ስድነት ነጻነት ይመስለዋል፤ ነጻነት ባለቤቱ ያጠረው ገደብ ወይም ወሰን አለው፡፡

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48557#sthash.NrWmoUlG.dpuf

የኢትዮጵያ የረሃብ አዙሪት ችግር፣ ሳይንሳዊና ፖለቲካዊ ጠቋሚ መፍትሄዎቹ | ዶ/ር ዘላለም ተክሉ

 

 

በሰሞኑ በኢትዮጵያ ለረሃብ የተጋለጡትን ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖቻችን አስመልክቶ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ የሃሳብ ልውውጥና ክርክር እየተደረገ ይገኛል:: አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው “መንግስት” ችግሩ በቁጥጥሩ ስር እንደሆነና፣ የምግብ እጥረቱን በውጭ ግዥ ለማሟላት በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ እንዳል ይገልጻል:: በሌላ ወገን የሚከራከሩ ወገኖች ደግሞ ችግሩ “መንግስት” እንደሚለው ቀላል እንዳልሆነ፣ ሁኔታዎችም ከቁጥጥሩ ውጭ እየወጡ እንደሆነና መላው ህዝባችን( የሃገር ውስጥና ውጭ ያለው ሁሉ)ተባብሮ ካልተንቀሳቀሰ ረሃቡ ለብዙ ወገኖቻችን እልቂት ምክንያት እንደሚሆን ስጋታቸውን እየገለጹና ዕርዳት በማሰባሰብ ላይ እንደተጣደፉ እንደሆነ ይስተዋላል::

File Photo

የረሃቡን ምክንያት በተመለከተ የገዢው “መንግስት” ባላስልጣናት ችግሩ “ኤልኒኖ” በተባለ የተፈጥሮ መዛባት ምክንያት የመጣ መሆኑን፣ ነገር ግን ሃገሪቱ ቀደም ባሉት አመታት ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ ልማት በተለይም በከፍተኛ የግብርና እድገት ምክንያት እስከ 270 ሚሊዮን ኩንታል እህል በዓመት የማምረት አቅም በመፍጠሯ ችግሩን በሃገር ውስጥ ጥረት ብቻ መቋቋም እንደሚቻል በኩራት ሲናገሩ ይሰማል::

ይህን “የመንግስት” ተደገገሚ ምክንያት የሚቃወሙ ወገኖች ደግሞ በእውነት ላለፉት 10 አመታት የተፎከረለት ዕድገት ቢኖርና በየዓመቱም ከ 270 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት የተቻለ ቢሆን ኖሮ 15 ሚሊዮን ይቅርና አንድም ሰው ሊራብ እንደማይገባው ይከረከራሉ:: የእስከሚሰለች የሚነገረን የ 10 ዓመቱ ዕደገትና የግብርና ምርቱ ብዛት እንዴት  ለገበሬው ትርፍ ጥሪት አላጎናጸፈውም ብለው ይጠይቃሉ፣ ብዙ ሚሊዮነሮችን ያፈራው ዕድገት እንዴት በአንድ ክረምት ኤልኒኖ የሚጠቁ 15 ሚሊዮን ወገኖችን ሊየፈራ ቻለ ብለው ይሟገታሉ:: በዚህም የተነሳ  ብዙዎች ከዚህ ቀደም እንደሚሉት “የመንግስት ዕድገት” ከቁጥር ቅቀላ የማያልፍ “ የፕሮፖጋንዳ ዕድገት” እንደሆነ  አበክረው ያሳስባሉ::

እኔም በዚህ አጭር ጽሁፍ እውነት ዕድገት ቢኖር ኖሮ ቅንጣት ታክል እንኳን ረሃብ ሊኖር አይገባም የሚለውን መከራከሪያ በመደገፍ ሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳብና ተሞክሮን በማጎዳኘት ሙግቱን ለማጣናከር እሞክራለሁ:: ለዚሁ ሙግት እንዲረዳኝ በመጀመሪያ “ድህነትና ረሃብን” በተመለከተ የኢኮኖሚክስ ኖቤል ተሸላሚ የሆነው ህንዳዊው ምሁር አማርቲ ሴን ፈጠራ ሥራ የሆነውን ንድፈ ዝርዝር ጥናት ተጠቅሜአለሁ::

የአማርቲ ሲን ንድፈ ሃሳብ የሚጀምረው የሰው ልጅ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች የማግኘት መብቱ ወይም በእንግሊዝኛ “ Entitlement” ተብሎ ከሚጠራው መነሻ ትርጓሜ ይሆናል:: የዚህ ትርጓሜ ቀጥተኛ እንግሊዝኛ ይዘቱም እንደሚከተለው ሲሆን:-

A person’s “entitlement set” is the full range of goods and services that he or she can acquire by converting his or her “endowments” (assets and resources, including labor power) through “exchange entitlement mappings” (Sen, 1981, Vol 96, No 3, pp 433-465).

የአማርኛ ግርድፍ ትርጉሙም ማንኛውም የሰው ልጅ ያለውን ጥሪት፣ ሃብትና ጉልበት ገበያ ወስዶ በመቀየር ለእለት ኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶችን ማግኘት የመቻል መብት አለው ማለት ነው::

አማርቲ ሴን ይህን ጥቅል “endowment” ምግብን ከማግኘት ህጋዊ አቅም አንጻር በአራት ንዑስ ሃሳቦች ይከፍለዋል::

1) ምግብ ማምረት ከመቻል መብት አንጻር “production-based entitlement “

2) ምግብ መግዛት ከመቻል መብት አንጻር “trade-based entitlement”

3) ምግብ ለማግኘት ከመስራት መብት አንጻር “own-labor entitlement”

4)ምግብን ከሌሎች ወገኖች በዕርዳታ ከማግኘት አንጻር “inheritance and transfer entitlement”

በዚሁ መሰረት የሰው ልጅ ለህይወቱ የሚያስፈሉጉትን ቁሳቁሶች ከላይ ከተዘረዘሩት ንዑስ ህጋዊ መብቶችና ምንጮች ውስጥ የተወሳኑት ወይም አብዛኞቹ ካልተሟሉለት ለረሃብ ይጋለጣል ተብሎ ይታመናል::

አማርቲ ሴን ከላይ የተዘረዘረውን ንድፈ ሃሳብ በመጠቀም እ.ኤ.አ በ1943 በህንድ ቤንጋል፣ በ1973 በኢትዮጵያ ወሎና በ 1974 በባንግላዴሽ ተከስተው ከመቶ ሺህ እስከ ሚሊዮን ህዝብ ያለቀበትን የረሃብ ወቅቶች ገምግሞ የእልቂቱ ምክንያት የምግብ እጥረት ሳይሆን ከላይ የተዘረዘሩት ምግብ የማግኛ አቅሞችና መብቶች entitlements ካለሟሟለት እንደሆነ  አራጋግጧል::በተለይም በኢትዮጵያ በወሎ ክፍለሃገር እ.ኤ.አ ከ 1973 -1974 ለተከሰተው ረሃብ መነሻ ምክንያት ለሁለት ዓመታት የቆየው የዝናብ እጥረት ቢሆንም እንኳን እስከ  200,000 የሚገመት ህዝብ በረሃብ የረገፉት በተለይ ከራያና ቆቦ፣ የጁና አምባሰል አውራጃዎች ምግብ በበቂ ሁኔታ ማምረትና ከገበያ የመግዛት መብትና አቅም ቀድሞውኑም ያጡ ምስኪን  ድሆች እንደነበሩ ጥናቱ አረጋግጡዋል:: የዝናብ እጥረቱ በወሎ ክፍለ ሃገር ባጠቃላይ የምግብ እጥረት ቢፈጥርም እንኩዋን በሌሎቹ የወሎ አውራጃዎችና፣ ከተሞች የሚገኘው አብዘኛው ህዝብ ለእለት የሚያስፈልገውን የካሎሪ መጠን ሊያሟላ የሚችል ምግብ ከሌሎች ክፍለ ሃገሮች በማስመጣት ችግሩን አልፏል:: እዲያውም  በረሃቡ ወቅት ከወሎ ወደ አዲስ አበባና አስመራ የተጫነ እህል እንደነበር የሚያረጋግጥ መረጃ እንደነበር ተረጋግጡዋል:: በዛን ጊዜ በወሎ ክፍለሃገር ይተዳደሩ የነበሩት የአፋር ዘላን ወገኖች እንኳን ምግብ ማግኘት በመቻላቸው አንድም ግለሰብ ለረሃብ እንዳልተጋለጠ ተመዝግቧል::

ከላይ የተገለጹት መረጃዎች ሲመረመሩ ለረሃቡና እልቂቱ ምክንያት የምግብ እጥረቱ ነው ብሎ መደምደም እንደማይቻል መያስረዷል:: እጥረቱ ቢኖርም እንኩዋን ወደ ወሎ  ክፍለ ሃገር የሚወጣና የሚገባ የምግብ ዝውውር ነበርና:: ዋናው ችግር በምግብ ዝውውሩ ለመሳተፍ የማይችሉ የህብረተሳብ ክፍሎች ቀድሞውኑም መኖራቸው ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው ምግብ የማምረት፣ ገዝቶ ራሳቸውን የመመገብ መብታቸውና አቅማቸው በመሟጠጡ እንደሆነ ለማወቅ ይቻላል::

በነዛ ሶስት አውራጃዎች በረሃብ እየተጠቁ ወገኖች ምግብ በቶሎ አድርሶም ከሞትለመታደግ ያልተቻለው የትራንስፖርት ተቋማት በወሎ ክፍለ ሃገር በበቂ ሁኔታ አለመኖር ነው የሚልም መከራከሪያ በወቅቱ ቀርቦ ነበር:: ነገረ ግን ለእነዚህ አውራጃዎች የሚሚያገለግሉ የመርጂያ ጣቢያዎቾ ባብዛኛው ከአዲስ አበባ አስመራ በሚያደርሰው ዋና አውራ ጎዳና ላይ የተቋቋሙ በመሆናቸው ይህ ምክንያት ውሃ እምደማይቋጥና ለእልቂቱ ዋነኛ ምክንያት ከ entitlement እጦት ውጭ እንዳልነበረ የበለጠ ማራጋጋጫ ሆኖ ተመዝግቧል::

ከላይ የተገለጠውን ትንተና መሰረት በማድረግ እኔም  በሃይለስላሴና በደርግ ዘመናት ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው “መንግስታችን” አገዛዝ ዘመን እየተደጋገመ ያለው የረሃብ አዙሪት ምስኪኑ የገጠሩ ህዝባችን በገጠመው ምግብ የማምረት፣ ጥሪት አፍርቶ ራሱንና ቤተሰቡን የመመገብ፣ ችግር ሲገጥመው በወቅቱ የምግብ ዕርዳታ የማግኛት መብትና አቅም በመጣቱ ብቻ ነው እላለሁ::እስቲ በወያኔ ዘመን ያለውን የገበሬውን አቅምና መብት (entitlement) እንመልከት:

1 ምግብ ማምረት ከመቻል መብት አንጻር

90 በመቶ የሚሆነው ገበሬ ምግብ የሚያመርተው ከሁለት ሄክታር ባነሰ መሬት ላይ ሲሆን ከዛሬ 60-70 ዓመታት በፊት በሚጠቀምበት የሞፈርና ቀንበር ቴክኖሎጂ ሳይወጣ እንዴት አድርጎ ራሱንና ቤተሰቡን ሊመግብ የሚችል እህል እንዴት ማምረት እንደሚችል መገመት በጣም ይቸግራል:: ያም አልበቃ ብሎ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ መድሃኒት በብድር ወስዶ እንዲጠቀም ገበሬው በወያኔ ካድሬዎች እየተገደደ ይገኛል:: በሌላም በኩል ገበሬው ቤተሰቡ እየጨመረ ሲሄድና ለአቅማዳምና ለሥራ የደረሱ ልጆቹ ከዛችው ብጣቂ መሬት ላይ ድርሻቸውን እየወሰዱ ሲሄዱ የቤተሰቡ ምግብ የማምረት መብትና  አቅም እንዴት እየተገፈፈ እንደሚሄድ መረዳት ተፈላሳፊነት አይጠይቅም:: ሌላም ነገር አለ:: ገበሬው በቤቱ ዙሪያ ዛፍ ወይም ሌሎች ቋሚ ተክሎች ላይ መዋእለ ነዋይ ለማፍሰስ አይደፍርም፣ ምክንያቱም የመሬት ይዞታው የራሱ ሆኖ ለዓመታት  እደሚዘልቅ ምንም ዋስትና የለውም:: ባላፈፉት 10 ዓመታትም የያዘውን ብጣቂ መሬት እየተነጠቀ ለውጭና ለወያኔ ወጋኝ “ ልማታዊ” ሰፈፊ እርሻ አልሚዎች መሰጠቱ ብዙ ድሃ ገበሬዎች ምግብ የማምረት መብትና አቅም እንዳሳጣቸው በስፋት ይነገራል::

2 ምግብ መግዛት ከመቻል መብት አንጻር

በተበጣጠሰና የይዞታ ዋስትናው ባልተረጋገጠ መሬት እንዲያርስ መደረጉ፣ ኋላ ቀር ቴክኖሎጂና አለፍላጎቱ ማደበሪያ ገዝቶና ተበድሮ እንዲጠቀም መገደዱ፣ የሃገራችንን  አብዛኛው ገበሬ ምግብ የማምረት መብቱንና አቅሙ እንዲዳከም እንዳደረገው ከላይ መተንተኑ ይታወቀል:: ገበሬው ከሁለት ሄክታር ባነሰች ኩርማ መሪቱ ካመረታት ጥቂት ኩንታል እህል ውስጥ የተበደረውን ብድር እንዲከፍል ሲገደድ፣ በጎተራው የምትቀረው እህል እንዴት ተሟጣ እንደምትቀር ይታያችሁ:: በዚህ ሁኔታ የገበሬው ምርት የተሟጠጠ ከሆነ ለዓመት አይደለም ለወራት እንኳን ቤተሰቡን መመገብ አይችልም፣ ለረጅም ጊዜም የሚረዳ የምግብና ገንዘብ ጥሪት ሊይዝም አይችልም::   ሁኔታዎች እንደዚህ ባሉበት ሁኔታ የዝናብ እጥረቱ ከአንድ ወደ ሁለት ዓመታት ከተሸጋገረ፣ አብዛኛው ገበሬ የሚያመርተው ምርት አይኖርም:: ካለፉት ዓመታት ምርቱም ምንም ጥሪት ባለመያዙ ከትርፋማ አካባቢ በርካሽ ዋጋ እህል በገበያ ቢቀርብ እንኳን ገበሬው የመግዛት ዓቅም አይኖረውም::

አሁን ለረሃብ የተጋለጡት 15 ሚሊዮን ወገኖቻችን የዚሁ ምግብ የመግዛት መብትና አቅም መሟጠጥ ውጤት ናቸው:: ከ 6 – 7 ወራት በፊት መንግስትና ረጂ ድርጅቶች ለረሃብ ተጋለጡ ሲሏቸው የነበሩት ወገኖች ከ 2 እስከ 3  ሚሊዮን አይበልጡም ነበር:: የረሃብተኛው ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ከፍ እያለ የመጣው የዝናብ እጥረቱ ሁለት የምርት ዘመናትን እየሸፈነ በመምጣቱና በዚህም ምክንያት በሚከሰተው የምርት እጥረት የመግዛት አቅማቸው እየተመናመነ የመጣባቸው ወገኖች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ነው:: አያድርገውና  የዝናብ እጥረቱ ለተጨማሪ ክረምት ከቀጠለ፣ በመግዛት መብትና አቅም በመመናመን የሚራቡት ወገኖቻችን ብዛት ወደ 20 እና  25 ሚሊዮኖች ሊሸጋገር እንደሚችል  ስጋቶች እየታዩ ነው::

3ምግብን ከሌሎች ወገኖች በዕርዳታ ከማግኘት አንጻር

በምግብ እጥረት ወቅት በረሃብ የተጋለጡ ወገኖች ምግብ በአፋጣኝ እንዲያገኙ ስለሚደረግ ጥረት አማርቲ ሴን የህንድን የ 1966/67 እና የ የ ቻይና የ 1958-61 ረሃቦችን በምሳሌነት ተጠቅሟል:: ህንድ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ እስክትወጣ ድረስ ለተደጋጋሚ ረሃብና እልቂት ተጋልጣለች:: ከነጻነቷ በኋላ በ1966/67 የተከሰተው የቢሃር ረሃብ ግን በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል:: ይህም ሊሆን የቻለው ህንድ የብዙሃን ፓርቲና ዲሞክራሲ ማስፈን ከቻለች በኋላ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ባህል መዳበር፣ የህዝብን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ አገር አስተዳዳሪዎችና የስራ አስኪያጆችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥና ሃላፊነታቸውን ባግባቡ መወጣት ካልቸሉ መሻር በመቻሉ፣ የምግብ እጥረት ሲከሰት በአፋጣኝ እርዳታ እንዲደርስ የሚዘግብና የመፍትሄ እርምጃዎችም በወቅቱ መወሰዳቸው የሚከታተል ነጻ ሚዲያ መፈጠች በመቻሉ ነበር::

ከ 1958-61 በቻይና የተከሰተው ረሃብ ግን ምንም ህዝብና የፖለቲካ ልሂቃንና ተቋማቶች ሳያውቁት ከ 16.5 እስከ 29.5 ሚሊዮን ህዝብ  እንዳለቁ ተዘግቧል:: ማኦ ዜዱንግና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲም ይህን ያህል ህዝብ እንዳያልቅ መከለከል ያልተቻለበት ምክንያት ምግብ የማምረትና የመግዘት መብቱና አቅሙ የተሟጠጠበት ህዝብ ዕርዳት በአፋጣኝ አለማግኘቱን የሚያጋልጡና የሚከታተሉ ነጻ ፕሬሶች አለመኖራቸው እንደሆነ ማመናቸውና ከዚያም በኋለ ብዙ ማስተካከየ እርምጃዎችን እንደወሰዱ ተዘግቧል::

በሃገራችን በኢትዮጵያም ለረሃብ የተጋለጡ ወገኖች ለሞት ሳይደርሱ የምግብ ዕርዳት አላማግኘት ችግር በሃይለስላሴ ፣በደርግ እና በወያኔ ዘመንም ተመሳሳይ ነው:: በሁሉም ጊዜያት የገዢው ወገኖች ከፍተኛ የሆነ  የልደትና የፓርቲ ድግሶችን እያደረጉ ባሉበት ወቅት የተራቡ ወገኖች ወደከተማ እንዳይሰደዱ፣ በቲሌቪዝንና በሬዲዮ እንዳይሰሙ እዲሁም የተራቡት ወገኖች ብዛት ቁጥሮችን ማሳነስ የተለመዱ የመሸፋፈኛ እርምጃዎች ናቸው::የወያኔ መንግስት ማንኛውንም የሃገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች ባሁኑ ሰዓት እየተባባሰ ስለመጣው ረሃብ ምንም ነገር እንዳይዘግብ የከለከለ ሲሆን “በወቅቱ ረሃብ ልጄ ሞተብኝ” ብለ ለ BBC ዘጋቢ ሃሳቧን የሰጠችውን የወሎ  ረሃብተኛ መልሳ እንድታስተበብል መደረጓ ተሰምቷል:: ይኽው “ መንግስት” ባንድ በኩል ችግሩን በቁጥጥሩ ስር እንዳደረገው፣ ያለማንም ዕርዳታ ምግብ ከውጭ ገዝቶ ለችግረኞቹ እንደሚደርስላቸው ሲፎክር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለማቀፉ ህብረተሰብ ችግሩን ለመፍታት አልተንቀሳቀሰ በማለት ወቀሳ እየቀረበ ይገኛል:: በዚህ ግርግር መሃል ግን የተራበው ወገናችን ምግብ ባፋጣኝ ሊደርስላቸው እንዳልቻለና በዚያውም ምክንያት ብዙ ወገን በሞት አፈፍ ላይ እንደደረሱ እየተዘገብ ይገኛል::

ባጠቃላይ “መንግስታችን” እንደሚፎክረው በሁለት ዲጂት እያደገ ባለበት ኢኮኖሚና ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩት ወገኖቻች መጠን ከ 44% ወደ 31% ዝቅ ማለቱ በተለፈፈበት ሁኔታ፣ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምግብ የማምረት፣ የመግዛትና ዕርዳታ የማግኘት መብትና አቅም ያጡ ገበሬዎች መከሰታቸው ሲታይ  የወያኔ  ፖለቲካ “ሁሉም ዜሮ ዜሮ” የሆነ “ፕሮፓጋንዳ” ብቻ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል::

የተራቡት ወገኖቻችንን ከሞት ለመታደግ ዕርዳታ ማሰባሰብና እንዲደርሳቸው ማድረግ ታላቅ የዜግነት ግዴታችን ነው:: ነገር ግን በየ 5 እና  10  ዓመታቱ የሚከሰተውን የረሃብ አዙሪት በዘላቂነት ከመፍታት ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ግን በጣም አናሳ ነው:: የዚህ የረሃብ አዙሪት ዘላቂው መፍትሄ  የገበሬውን ምግብ የማምረት፣ ምግብ የመግዛትና በእህል ምርት እጥረት ጊዜ ባፋጣኝ ምግብ የሚያገኝበት መብትና አቅም እንዲገነባ ማድረግ ነው:: ለዚህ መሳከት ደግሞ ዲሞክረሲና ነጻ ገበያን ማዕከል ያደረጉ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና እስትራቴዎጅን ተግባሪዊ ማድረግ ብቸኛ መንገድ ነው:: በኔ ግምት እነዚህ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና እስትራቴዎጅ  አሁን እየገዛን ባለው “ መንግስታችን” ተግባሪያዊ እየሆኑ አይደሉም ይሆናሉ ብዬም በፍጹም አልጠብቅም:: ስለዚህ በየጊዜው እየተራቡ የሚሰቃዩትን ወገኖቻችንን በዘላቂነት ለመታደግ ከፈለግን፣ ያለውን ገዢ “መንግስት” በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመለወጥ እየተደረገ ላለው ትግል የራሳችንን አስተዋጽዖ ማድረግ ግዴታች ነው ብዬ አምናለሁ፣ ጥሪም አስተላልፋለሁ::

በተረፈ ቸር ይግጠመን::

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48566#sthash.r3TAEAfg.dpuf