ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ፣ (ይገረም ዓለሙ)

ይገረም ዓለሙ

ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ወደ መጨረሻ የሥልጣን ዘመናቸው አካባቢ “ ብታምኑም ባታምኑም ንቀውናል ተዋርደናል በቁማችን ሞተናል” በማለት የተናገሩት ዛሬ ብሶ ተባብሶ እየታየ ነው፡፡ ወያኔዎች ኢትዮጵያዉያንን በንቀት ማየታቸው ሊገታ አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ በጌታው የተማመነ ሎሌ ሁሉ እሱም እንደ አቅሙ ሕዝብን እየናቀ እያጠቃና ለጌታው ጥቃት እያመቻች ሎሌነቱን አስከብሮ ለመኖር እየታተረ ነው፡፡ ወያኔ ደግሞ ሎሌ መረጣው ይሳካለታል፡፡አንዱን ተጠቅሞ ሲጥል ሌላውን ያገኛል፡፡Ethiopia's food crisis

ሚስትህ አረገዘች ወይ ቢሉት ማንን ወንድ ብላ እንዳለው ሰው ወያኔዎቹም ሆኑ “የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ ” ብለው በየቦታው ያሰማሩዋቸው ሎሌዎች ማንን ሰው ብለው አደብ ይግዙ፤ ማንን ፈርተው ንቀታቸውን ያቁሙ፤ በማን ተገደው ከግፍና በደል ተግባራቸው ይገቱ፡፡አዎ በድክመታችን ተንቀናል፣ በመበታተናችን ተዋርደናል፣ እናም በቁማችን ሞተናል የሚለው የመንግሥቱ ኃለማሪያም አባባል መነገር ካለበት ከምንግዜውም በላይ ዛሬ ነው፡፡

እየገደሉ፣ እያሰሩ፣ ከቤት ንብረት እያፈናቀሉ፣ እያሳየቃዩና ከሀገር እያሰደዱ ሲያላግጡብን፣ ዶክመንተሪ ፊልም ሲሰሩብን ፣ ጮቤ ሲረግጡብን ወዘተ የገጠማቸው የበረታ ተቃውሞ ባለመኖሩ ንቀታቸው ጣሪያ ደርሶ አንባገነንታቸው ለከት አጥቶ እነሆ ዛሬ በመራባችን ይመጻደቁ ይሳለቁብናል፡፡ዓለም ስለ ርሀባችን ሲያወራና የእርዳታ እጁን ሲዘረጋ እነርሱ ጮማ እየቆረጡና ውስኪ እየተራጩ ዳንኪራ ይረግጣሉ፣ በበአል ስም እየተጠራሩ አሸሸ ገዳሜ ይላሉ፡፡ ከዚህ በላይ ንቀት በምን ይገለጣል፡፡

በርግጥ እኛ ከመማማረር አልፈን ማምረር አልችል ብለን እንጂ፤በየራሳችን ሲደርስ ከመጮህ አልፈን ተባብረን አገዛዝ በቃን ማለት አለመቻላችን እንጂ የቃል እንጂ የተግባር ሰው መሆን አቅቶን አንጂ ወዘተ ወያኔዎች ደርግን በማሸነፋቸው ራሳቸውን ለማንም ለምንም የማይገሩ አድረግው በማየት ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ነቀት ማሳየት የጀመሩት ገና አዲስ አበባን በቅጡ ሳይለማመዱ ነው፡፡

በ1985 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለኤርትራ መገንጠል ሽንጣቸውን ገትረው የሰሩትን የወቅቱን የተመድ ዋና ጸኃፊ ግብጻዊውን ቡትሮስ ጋሊ አዲስ አበባ መምጣት በመቃወም ሰልፍ ሲወጡ ገና የግቢያቸውን አጥር ሳይጨርሱ ነበር የቆመጥ ሲሳይ የጥይተ እራት ያደረጉዋቸው፡፡ ያንን የጭካኔ ተግባር የሚያውቅ ሁሉ እንደሚያስታውሰው ከአረመኔያዊ ድርጊታቸው ባልተናነሰ ሰልፉን ለመበተን ጥይት የተጠቀምነው ካለፈው መንግሥት የወረስነው አድማ መበተኛ አስለቃሽ ጭስ እና ውኃ መርጫ መኪና ባለመኖሩ ነው በማለት በንቀት የተናገሩት ቆሽት የሚያሳርር ነበር፡፡ በዚህም ሳያበቁ ይህም ሆኖ የሞተው አንድ ሰው ርሱም ኢሰፓ ነው በማለት የአንድ ሰው ህይወት ለእነርሱ ሕይወት ያለመሆኑን ኢሰፓ የሆነን ሰው ደግሞ እንደ ሰው የማይቆጥሩ መሆናቸውን ነበር ያረጋገጡልን፡፡

ከዛን ግዜ ጀምሮ ወያኔዎች በድርጊትም በንግግርም ለሕዝብ ያላቸውን ንቀት እያሳዩ ሀያ አራት አመታት በሥልጣን ቢቆዩም ዛሬም ለህዘብ ያላቸው ንቀት ሊገታ አልቻለም፡፡የሚፈጽሙብንን ሁሉ ችለን ተባብረንና በርትተን ከመታገል ርስ በርስ እየተናቆርንና በደሉን ሁሉ ችለን እንደ ግመሏ ህእ እያልን መኖራችን የልብ ልብ ሰጥቶአቸው ዛሬ ደግሞ በመራባችን ይሳለቃሉ ያፌዛሉ፡፡ ንቀታቸውን ያሳያሉ ፡፡አቶ ሬዲዋን ሁሴን ከግንኙነት ምኒስትር ቦታቸው ከመነሳታቸው በፊት በአፋር ከብቶች የሞቱት ውኃ በወቅቱ ስለማያጠጡዋቸው ነው አሉ፡፡ ስልጤው ሬድዋን ህይወቱ ከከብት ጋር ለተሳሰረው አፋር ለከብት ውኃ ስለማጠጣት ሊያስተምሩት፡፡ ወይ ንቀት!! በዚህ አጀኢብ ስንል ወጪ ጉዳይ ምኒስትሩ ከ96 ሚሊየን ሕዝብ 8 ሚሊየን ቢራብ ምንድን ነው በማለት ህውኃት ለኢትዮጵያውያን ያለውን ንቀት በግልጽ ነገሩን፡፡ ወያኔዎች የሞተው አንድ ሰው እሱም ኢሰፓ ነው እንዳሉት ዛሬም የተራቡት ርሻቸውን ትተው በተቀዋሚነት የተሰለፉ ናቸው አለማለታቸው እድገት ማሳየታቸው ይሆን!

ሕዝብ በሚፈራበትና ሕግ የበላይ በሆነበት ሀገር ቢሆን ዶ/ሩ ይህን ተናግረው በሥልጣናቸው አይቀጥሉም ነበር፡፡ ሁሉም ባለመኖሩ ግን ነገሩ በዚህ አላበቃም፡፡ የናቁትን ሀገር በአህያ ይወሩታል እንደሚባለው ወያኔ በየቦታው ያስቀመጣቸው ራሳቸው ያልሆኑና የማይሆኑ ሰዎች በጌቶቻቸው ትዕዛዝ በመራባችን መሳለቃቸውን ምን ታመጣላችሁ ንቀታቸውን ማሳየታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ ለአፉ ለከት የሌለው አቶ ጌታቸው ረዳ አቶ ሬድዋን ከነበረበት ወንበር ላይ ሆኖ ርሀብ የለም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዓለም ኣቀፍ ደረጃ የተረጋገጠውን የካሎሪ መጠን እያገኘ ነው በማለት የተሳለቀው በዚሁ መንገድ ነው፡፡

ዛሬም ከጫካ አስተሳሰባቸውና ከደደቢት ትልማቸው ያልተላቀቁት ወያኔዎች የናቁት ህዝብ ምንም እንደማያውቅ አድርገው በማየት ሁሉን ነገር ደብቀው ለማለፍ ይጥራሉ፡፡ (በርግጥ ዛሬም ድረስ ያልተጋለጠ ገድለው የቀበሩዋቸው አፍነው የሰወሩዋቸው (ከራሳቸወም ከተቃዋሚዎችም) ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡) የደበቁት ሲደረስባቸው የዋሹት ሲነቃባቸው ታዲያ ቢሆንስ ምን ታመጣላችሁ አይነት ንቀታቸውን ያሳያሉ፡ እብሪታቸውን ለአደባባይ ያበቃሉ፡፡በዚህ የማይሆን ሲሆን ደግሞ የማስቀየሻ ስልት ይፈልጋሉ የክርክሩን አቅጣጫ ለማስለወጥ ይንደፋደፋሉ፡፡

ሊደብቁት ሞክረው ባልተሳካላቸው ርሀብ ምክንያት የወያኔዎች ሁለቱም ባህሪያቸው ታይቷል፡፡ ፈጣን ተከታታይ ባለ ሁለት አሀዝ እድገት እየተባለ ብዙ የተወራለት ዕድገት አንድ የአዝመራ ወቅት መሻገር ባለመቻሉ በተጨባጭ የሌለ የፕሮፓጋንዳ እድገት መሆኑ እንዳይጋለጥና የአመታት ልፈፋቸው ውሀ እንዳይበላው ለማድረግ የማይሞከር ነገር ርሀብን ለመደበቅ ሞከሩ፡፡ በመረጃ ዘመን ርሀብን የሚያህል ነገር እደብቃለሁ ብሎ ማሰብ ራሱ እብሪትና አንባገነንነት ምን ያህል የአዕምሮን ማሰቢያ ክፍል እንደሚደፍኑ የሚያሳይ ነው፡ ርሀቡ በአለም ደረጃ ሲጋለጥ ደግሞ መኖሩን አምኖ ችግሩ ኤሊኖ ያመጣው ነው በማለት የችግሩን እንዴትነት አቅጣጫ ለመለወጥ ተሞከረ፡፡ በኤሊኖም ይሁን በማናቸውም የአየር ሚዛን መዛባት የሚፈጠር የዝናብ እጥረት ድርቅ ማስከተሉ አጠያያቂ አይደለም፡ አጠያያቂው የዝናብ እጥረት ድርቅ ማስከተሉ ነው፡፡ ይበልጥ ወያኔ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ድግሞ ፈጣኑ ተከታታይ ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እውነት ከሆነ እንዴት አንድ የዝናብ ወቅት መሻገር ተሳነው የሚለው ነው፡፡

ኢሊኖን የችግሩ ምክንያት አድርጎ ከሚረጨው ውኃ የማይቋጥር ፕሮፓጋንዳ በተጨማሪ ችግሩ ከመንግሥት አቅም በላይ እንዳልሆነ ተደርጎ የሚነገረው መመጻደቅ፣ በጎን ደግሞ ርዳታ መለመንና በየባለሥልጣናቱ የሚነገረው አንዱ ከአንዱ የማይዛመድ ቅጥፈት በወያኔ ሰፈር እንዴት አንድ ከትከሻው በላይ ጭንቅላቱ የከበደው ሰው ይታጣል የሚያሰኝ ነው፡፡ አቤት የድህነታችን ስፋት፡፡

ከለንደን አዲስ አበባ ተጉዙ በአንፍናፊ ሙያው ረሀብ ህይወት ከቀጠፈበት ቆቦ ከአንድ መንደር ዘልቆ ምስል ከድምጽ ያቀነባበረው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ያሰራጨውን የርሀብ ዜና ለማስተባበል ተብሎ ልጇ በረሀብ መሞቱን ለቢቢሲው ጋዜጠኛ የነገረችው እናት ለወያኔ ጋዜጠኞች በበሽታ ነው የሞተው ብላ አንድትናገር መደረጉን አይተናል ሰምተናል፡፡ ከዚህ የከፋ ጨካኝነት፣ ከዚህ የባሰ የህዝብ ንቀት መገለጫ ምን ይኖራል፡፡ ለነገሩ ማስተዋል ብሎ ነገር የሌላቸው ሆነው ለማስተባበል ብለው በሰሩት ዜና ቢቢሲን ማየት ለማይችለው ሁሉ መርዶውን አደረሱት አረመኔነታቸውንም አሳዩበት፡፡

ምንም ተባለ ምን ርሀብ መኖሩ ተረጋግጧል፤ወያኔዎችም ተገደው አምነዋል፤ርዳታም ልመናም ገብተዋል፤ ልመና ራስን ካለመቻል የሚመጣ በመሆኑ የአቶ ኃይለማሪያም በምግብ ራሳችንን ችለናል ፉከራ ባዶ መሆኑ ታይቷል፡፡ በአቶ መለስ ተጀምሮ አንዳይቆም ተናዘው የሞቱ ይመስል ፕሮፓጋንዳው የቀጠለው ፈጣን ተከታታይ ባለሁለት አሀዝ እድገትም የወረቀት እድገት መሆኑ ተጋልጧል፡፡ስለሆነም ልመና የገባ መንግሥት ያለውን ይቆጥባል፣ የቅንጦት ነገሮች ያቆማል፣ ከምንም ነገር በላይ የሰው ህይወት ይበልጣልና ፓርላማው መክሮ የመንግሥት ቀዳሚና ዋና ተግባር የዜጎችን ህይወት መታደግ እንዲሆን አመራር ይሰጣል በጀት ይወስናል ወዘተ፡፡ ወያኔዎች ግን ማንን ሰው ብለው ፣ ከ96 ሚሊየን ህዝብ ስምንትም ሆነ አስራ አምስት ሚሊየን ቢራብ ምን ጉዳያቸው ሆኖ፡፡

አለም እየጮኸበትና እየጮኸለት ያለ ርሀብ ተከሰቶ እየለመኑ መቀናጣት እየተበደሩ አሸሸ ገዳሜ ማለት ህዝብን ከመናቅ ውጪ ምን ሊባል ይችላል፡፡ብአዴን ለወያኔ በሎሌነት የገባበትን ክብረ በአል በአሸሸ ገዳሜ ለማክበር አወጣው የሚባለው ገንዘብ እንኳንስ በዚህ በርሀብ ወቅት ቀርቶ በማናቸውም ጤናማ ወቅት በአንዲት በድህነት በምትታወቅ ሀገር በሚኖር ያውም የራሱ ነጻነት ለሌለው አንድ ድርጀት በአል ማክበሪያ ሊውል የሚገባው አይደለም፡፡ ብአዴን እኔም እንደ አባቴ ብሎ ምንስ ሎሌ ብሆን ህውኃት ያደረገው እንዴት ይቀርብኛል ብሎ ሰሞኑን የፈጸመው ድርጊት ከምንም በላይ ለህዝብ ላይ ያለውን ንቀት ያሳያበት ነው፡፡

ብአዴን በርግጥ ራሱን የቻለ ድርጅት ከሆነ ይህንን ማሳየት ማስመስከርና ማረጋገጥ ያለበት ከህውኃት ጋር በአል በማክበር ፉክክር አይደለም፡፡ አወክለዋለሁ እንደሚለው ሕዝብ ብዛት በፌዴራል ደረጃ ተመጣጣኝና ወሳኝ የሥልጣን ቦታዎችን በመያዝ፤በክልል ደረጃ ከይስሙላ የክልል መንግሥትነት ወደ ትክክለኛ መንግስትነት በመሸጋገር፤ ከሎሌነት ወጥቶ በነጻነት መቆም በመቻል፣ወዘተ ነው ፡፡ በህውኃት የተፈጠረና ለህውኃት እያገለገለ ያለ ድርጅት ከዚህ መውጣቱን በተግባር ማሳየት እስካልቻለ ድረስ ልብወለድ ታሪክ ቢያወራ ሀውልት ቢገነባ በአል ደግሶ አሸሸ ገዳሜ ቢል እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ አይደለም አባሌ የሚላቸውንና አብረው ሲጨፍሩ የከረሙትን እንኳን ማሳመን አይችልም፡፡

ህዝብ በርሀብ በሚሰቃይበት ወቅት 300 ሚሊየን ብር አውጥቶ ሀውልት በመገንባትም ሆነ ዳንኪራ በመርገጥ ከህውኃት ጋር መፎካከር ብአዴንን ነጻነት ያለው ድርጅት አያስመስለውም፡፡ በዚህ ተግባሩም ሎሌ አለመሆኑን ማረጋገጥ አይችልም፡፡ ለህዝብ ያለውን ንቀት ግን በሚገባ አሳይቷል፡፡ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ እንደሚባለው ወያኔ ከእነ ፈጠራቸው ድርጅቶች ሕዝብን የሚንቁ ባይሆኑ ኖሮ ሌላው ሌላው ቢቀር በረሀባችን ባልተሳለቁ ነበር፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s