የኢትዮጵያ የረሃብ አዙሪት ችግር፣ ሳይንሳዊና ፖለቲካዊ ጠቋሚ መፍትሄዎቹ | ዶ/ር ዘላለም ተክሉ

 

 

በሰሞኑ በኢትዮጵያ ለረሃብ የተጋለጡትን ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖቻችን አስመልክቶ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ የሃሳብ ልውውጥና ክርክር እየተደረገ ይገኛል:: አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው “መንግስት” ችግሩ በቁጥጥሩ ስር እንደሆነና፣ የምግብ እጥረቱን በውጭ ግዥ ለማሟላት በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ እንዳል ይገልጻል:: በሌላ ወገን የሚከራከሩ ወገኖች ደግሞ ችግሩ “መንግስት” እንደሚለው ቀላል እንዳልሆነ፣ ሁኔታዎችም ከቁጥጥሩ ውጭ እየወጡ እንደሆነና መላው ህዝባችን( የሃገር ውስጥና ውጭ ያለው ሁሉ)ተባብሮ ካልተንቀሳቀሰ ረሃቡ ለብዙ ወገኖቻችን እልቂት ምክንያት እንደሚሆን ስጋታቸውን እየገለጹና ዕርዳት በማሰባሰብ ላይ እንደተጣደፉ እንደሆነ ይስተዋላል::

File Photo

የረሃቡን ምክንያት በተመለከተ የገዢው “መንግስት” ባላስልጣናት ችግሩ “ኤልኒኖ” በተባለ የተፈጥሮ መዛባት ምክንያት የመጣ መሆኑን፣ ነገር ግን ሃገሪቱ ቀደም ባሉት አመታት ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ ልማት በተለይም በከፍተኛ የግብርና እድገት ምክንያት እስከ 270 ሚሊዮን ኩንታል እህል በዓመት የማምረት አቅም በመፍጠሯ ችግሩን በሃገር ውስጥ ጥረት ብቻ መቋቋም እንደሚቻል በኩራት ሲናገሩ ይሰማል::

ይህን “የመንግስት” ተደገገሚ ምክንያት የሚቃወሙ ወገኖች ደግሞ በእውነት ላለፉት 10 አመታት የተፎከረለት ዕድገት ቢኖርና በየዓመቱም ከ 270 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት የተቻለ ቢሆን ኖሮ 15 ሚሊዮን ይቅርና አንድም ሰው ሊራብ እንደማይገባው ይከረከራሉ:: የእስከሚሰለች የሚነገረን የ 10 ዓመቱ ዕደገትና የግብርና ምርቱ ብዛት እንዴት  ለገበሬው ትርፍ ጥሪት አላጎናጸፈውም ብለው ይጠይቃሉ፣ ብዙ ሚሊዮነሮችን ያፈራው ዕድገት እንዴት በአንድ ክረምት ኤልኒኖ የሚጠቁ 15 ሚሊዮን ወገኖችን ሊየፈራ ቻለ ብለው ይሟገታሉ:: በዚህም የተነሳ  ብዙዎች ከዚህ ቀደም እንደሚሉት “የመንግስት ዕድገት” ከቁጥር ቅቀላ የማያልፍ “ የፕሮፖጋንዳ ዕድገት” እንደሆነ  አበክረው ያሳስባሉ::

እኔም በዚህ አጭር ጽሁፍ እውነት ዕድገት ቢኖር ኖሮ ቅንጣት ታክል እንኳን ረሃብ ሊኖር አይገባም የሚለውን መከራከሪያ በመደገፍ ሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳብና ተሞክሮን በማጎዳኘት ሙግቱን ለማጣናከር እሞክራለሁ:: ለዚሁ ሙግት እንዲረዳኝ በመጀመሪያ “ድህነትና ረሃብን” በተመለከተ የኢኮኖሚክስ ኖቤል ተሸላሚ የሆነው ህንዳዊው ምሁር አማርቲ ሴን ፈጠራ ሥራ የሆነውን ንድፈ ዝርዝር ጥናት ተጠቅሜአለሁ::

የአማርቲ ሲን ንድፈ ሃሳብ የሚጀምረው የሰው ልጅ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች የማግኘት መብቱ ወይም በእንግሊዝኛ “ Entitlement” ተብሎ ከሚጠራው መነሻ ትርጓሜ ይሆናል:: የዚህ ትርጓሜ ቀጥተኛ እንግሊዝኛ ይዘቱም እንደሚከተለው ሲሆን:-

A person’s “entitlement set” is the full range of goods and services that he or she can acquire by converting his or her “endowments” (assets and resources, including labor power) through “exchange entitlement mappings” (Sen, 1981, Vol 96, No 3, pp 433-465).

የአማርኛ ግርድፍ ትርጉሙም ማንኛውም የሰው ልጅ ያለውን ጥሪት፣ ሃብትና ጉልበት ገበያ ወስዶ በመቀየር ለእለት ኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶችን ማግኘት የመቻል መብት አለው ማለት ነው::

አማርቲ ሴን ይህን ጥቅል “endowment” ምግብን ከማግኘት ህጋዊ አቅም አንጻር በአራት ንዑስ ሃሳቦች ይከፍለዋል::

1) ምግብ ማምረት ከመቻል መብት አንጻር “production-based entitlement “

2) ምግብ መግዛት ከመቻል መብት አንጻር “trade-based entitlement”

3) ምግብ ለማግኘት ከመስራት መብት አንጻር “own-labor entitlement”

4)ምግብን ከሌሎች ወገኖች በዕርዳታ ከማግኘት አንጻር “inheritance and transfer entitlement”

በዚሁ መሰረት የሰው ልጅ ለህይወቱ የሚያስፈሉጉትን ቁሳቁሶች ከላይ ከተዘረዘሩት ንዑስ ህጋዊ መብቶችና ምንጮች ውስጥ የተወሳኑት ወይም አብዛኞቹ ካልተሟሉለት ለረሃብ ይጋለጣል ተብሎ ይታመናል::

አማርቲ ሴን ከላይ የተዘረዘረውን ንድፈ ሃሳብ በመጠቀም እ.ኤ.አ በ1943 በህንድ ቤንጋል፣ በ1973 በኢትዮጵያ ወሎና በ 1974 በባንግላዴሽ ተከስተው ከመቶ ሺህ እስከ ሚሊዮን ህዝብ ያለቀበትን የረሃብ ወቅቶች ገምግሞ የእልቂቱ ምክንያት የምግብ እጥረት ሳይሆን ከላይ የተዘረዘሩት ምግብ የማግኛ አቅሞችና መብቶች entitlements ካለሟሟለት እንደሆነ  አራጋግጧል::በተለይም በኢትዮጵያ በወሎ ክፍለሃገር እ.ኤ.አ ከ 1973 -1974 ለተከሰተው ረሃብ መነሻ ምክንያት ለሁለት ዓመታት የቆየው የዝናብ እጥረት ቢሆንም እንኳን እስከ  200,000 የሚገመት ህዝብ በረሃብ የረገፉት በተለይ ከራያና ቆቦ፣ የጁና አምባሰል አውራጃዎች ምግብ በበቂ ሁኔታ ማምረትና ከገበያ የመግዛት መብትና አቅም ቀድሞውኑም ያጡ ምስኪን  ድሆች እንደነበሩ ጥናቱ አረጋግጡዋል:: የዝናብ እጥረቱ በወሎ ክፍለ ሃገር ባጠቃላይ የምግብ እጥረት ቢፈጥርም እንኩዋን በሌሎቹ የወሎ አውራጃዎችና፣ ከተሞች የሚገኘው አብዘኛው ህዝብ ለእለት የሚያስፈልገውን የካሎሪ መጠን ሊያሟላ የሚችል ምግብ ከሌሎች ክፍለ ሃገሮች በማስመጣት ችግሩን አልፏል:: እዲያውም  በረሃቡ ወቅት ከወሎ ወደ አዲስ አበባና አስመራ የተጫነ እህል እንደነበር የሚያረጋግጥ መረጃ እንደነበር ተረጋግጡዋል:: በዛን ጊዜ በወሎ ክፍለሃገር ይተዳደሩ የነበሩት የአፋር ዘላን ወገኖች እንኳን ምግብ ማግኘት በመቻላቸው አንድም ግለሰብ ለረሃብ እንዳልተጋለጠ ተመዝግቧል::

ከላይ የተገለጹት መረጃዎች ሲመረመሩ ለረሃቡና እልቂቱ ምክንያት የምግብ እጥረቱ ነው ብሎ መደምደም እንደማይቻል መያስረዷል:: እጥረቱ ቢኖርም እንኩዋን ወደ ወሎ  ክፍለ ሃገር የሚወጣና የሚገባ የምግብ ዝውውር ነበርና:: ዋናው ችግር በምግብ ዝውውሩ ለመሳተፍ የማይችሉ የህብረተሳብ ክፍሎች ቀድሞውኑም መኖራቸው ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው ምግብ የማምረት፣ ገዝቶ ራሳቸውን የመመገብ መብታቸውና አቅማቸው በመሟጠጡ እንደሆነ ለማወቅ ይቻላል::

በነዛ ሶስት አውራጃዎች በረሃብ እየተጠቁ ወገኖች ምግብ በቶሎ አድርሶም ከሞትለመታደግ ያልተቻለው የትራንስፖርት ተቋማት በወሎ ክፍለ ሃገር በበቂ ሁኔታ አለመኖር ነው የሚልም መከራከሪያ በወቅቱ ቀርቦ ነበር:: ነገረ ግን ለእነዚህ አውራጃዎች የሚሚያገለግሉ የመርጂያ ጣቢያዎቾ ባብዛኛው ከአዲስ አበባ አስመራ በሚያደርሰው ዋና አውራ ጎዳና ላይ የተቋቋሙ በመሆናቸው ይህ ምክንያት ውሃ እምደማይቋጥና ለእልቂቱ ዋነኛ ምክንያት ከ entitlement እጦት ውጭ እንዳልነበረ የበለጠ ማራጋጋጫ ሆኖ ተመዝግቧል::

ከላይ የተገለጠውን ትንተና መሰረት በማድረግ እኔም  በሃይለስላሴና በደርግ ዘመናት ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው “መንግስታችን” አገዛዝ ዘመን እየተደጋገመ ያለው የረሃብ አዙሪት ምስኪኑ የገጠሩ ህዝባችን በገጠመው ምግብ የማምረት፣ ጥሪት አፍርቶ ራሱንና ቤተሰቡን የመመገብ፣ ችግር ሲገጥመው በወቅቱ የምግብ ዕርዳታ የማግኛት መብትና አቅም በመጣቱ ብቻ ነው እላለሁ::እስቲ በወያኔ ዘመን ያለውን የገበሬውን አቅምና መብት (entitlement) እንመልከት:

1 ምግብ ማምረት ከመቻል መብት አንጻር

90 በመቶ የሚሆነው ገበሬ ምግብ የሚያመርተው ከሁለት ሄክታር ባነሰ መሬት ላይ ሲሆን ከዛሬ 60-70 ዓመታት በፊት በሚጠቀምበት የሞፈርና ቀንበር ቴክኖሎጂ ሳይወጣ እንዴት አድርጎ ራሱንና ቤተሰቡን ሊመግብ የሚችል እህል እንዴት ማምረት እንደሚችል መገመት በጣም ይቸግራል:: ያም አልበቃ ብሎ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ መድሃኒት በብድር ወስዶ እንዲጠቀም ገበሬው በወያኔ ካድሬዎች እየተገደደ ይገኛል:: በሌላም በኩል ገበሬው ቤተሰቡ እየጨመረ ሲሄድና ለአቅማዳምና ለሥራ የደረሱ ልጆቹ ከዛችው ብጣቂ መሬት ላይ ድርሻቸውን እየወሰዱ ሲሄዱ የቤተሰቡ ምግብ የማምረት መብትና  አቅም እንዴት እየተገፈፈ እንደሚሄድ መረዳት ተፈላሳፊነት አይጠይቅም:: ሌላም ነገር አለ:: ገበሬው በቤቱ ዙሪያ ዛፍ ወይም ሌሎች ቋሚ ተክሎች ላይ መዋእለ ነዋይ ለማፍሰስ አይደፍርም፣ ምክንያቱም የመሬት ይዞታው የራሱ ሆኖ ለዓመታት  እደሚዘልቅ ምንም ዋስትና የለውም:: ባላፈፉት 10 ዓመታትም የያዘውን ብጣቂ መሬት እየተነጠቀ ለውጭና ለወያኔ ወጋኝ “ ልማታዊ” ሰፈፊ እርሻ አልሚዎች መሰጠቱ ብዙ ድሃ ገበሬዎች ምግብ የማምረት መብትና አቅም እንዳሳጣቸው በስፋት ይነገራል::

2 ምግብ መግዛት ከመቻል መብት አንጻር

በተበጣጠሰና የይዞታ ዋስትናው ባልተረጋገጠ መሬት እንዲያርስ መደረጉ፣ ኋላ ቀር ቴክኖሎጂና አለፍላጎቱ ማደበሪያ ገዝቶና ተበድሮ እንዲጠቀም መገደዱ፣ የሃገራችንን  አብዛኛው ገበሬ ምግብ የማምረት መብቱንና አቅሙ እንዲዳከም እንዳደረገው ከላይ መተንተኑ ይታወቀል:: ገበሬው ከሁለት ሄክታር ባነሰች ኩርማ መሪቱ ካመረታት ጥቂት ኩንታል እህል ውስጥ የተበደረውን ብድር እንዲከፍል ሲገደድ፣ በጎተራው የምትቀረው እህል እንዴት ተሟጣ እንደምትቀር ይታያችሁ:: በዚህ ሁኔታ የገበሬው ምርት የተሟጠጠ ከሆነ ለዓመት አይደለም ለወራት እንኳን ቤተሰቡን መመገብ አይችልም፣ ለረጅም ጊዜም የሚረዳ የምግብና ገንዘብ ጥሪት ሊይዝም አይችልም::   ሁኔታዎች እንደዚህ ባሉበት ሁኔታ የዝናብ እጥረቱ ከአንድ ወደ ሁለት ዓመታት ከተሸጋገረ፣ አብዛኛው ገበሬ የሚያመርተው ምርት አይኖርም:: ካለፉት ዓመታት ምርቱም ምንም ጥሪት ባለመያዙ ከትርፋማ አካባቢ በርካሽ ዋጋ እህል በገበያ ቢቀርብ እንኳን ገበሬው የመግዛት ዓቅም አይኖረውም::

አሁን ለረሃብ የተጋለጡት 15 ሚሊዮን ወገኖቻችን የዚሁ ምግብ የመግዛት መብትና አቅም መሟጠጥ ውጤት ናቸው:: ከ 6 – 7 ወራት በፊት መንግስትና ረጂ ድርጅቶች ለረሃብ ተጋለጡ ሲሏቸው የነበሩት ወገኖች ከ 2 እስከ 3  ሚሊዮን አይበልጡም ነበር:: የረሃብተኛው ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ከፍ እያለ የመጣው የዝናብ እጥረቱ ሁለት የምርት ዘመናትን እየሸፈነ በመምጣቱና በዚህም ምክንያት በሚከሰተው የምርት እጥረት የመግዛት አቅማቸው እየተመናመነ የመጣባቸው ወገኖች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ነው:: አያድርገውና  የዝናብ እጥረቱ ለተጨማሪ ክረምት ከቀጠለ፣ በመግዛት መብትና አቅም በመመናመን የሚራቡት ወገኖቻችን ብዛት ወደ 20 እና  25 ሚሊዮኖች ሊሸጋገር እንደሚችል  ስጋቶች እየታዩ ነው::

3ምግብን ከሌሎች ወገኖች በዕርዳታ ከማግኘት አንጻር

በምግብ እጥረት ወቅት በረሃብ የተጋለጡ ወገኖች ምግብ በአፋጣኝ እንዲያገኙ ስለሚደረግ ጥረት አማርቲ ሴን የህንድን የ 1966/67 እና የ የ ቻይና የ 1958-61 ረሃቦችን በምሳሌነት ተጠቅሟል:: ህንድ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ እስክትወጣ ድረስ ለተደጋጋሚ ረሃብና እልቂት ተጋልጣለች:: ከነጻነቷ በኋላ በ1966/67 የተከሰተው የቢሃር ረሃብ ግን በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል:: ይህም ሊሆን የቻለው ህንድ የብዙሃን ፓርቲና ዲሞክራሲ ማስፈን ከቻለች በኋላ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ባህል መዳበር፣ የህዝብን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ አገር አስተዳዳሪዎችና የስራ አስኪያጆችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥና ሃላፊነታቸውን ባግባቡ መወጣት ካልቸሉ መሻር በመቻሉ፣ የምግብ እጥረት ሲከሰት በአፋጣኝ እርዳታ እንዲደርስ የሚዘግብና የመፍትሄ እርምጃዎችም በወቅቱ መወሰዳቸው የሚከታተል ነጻ ሚዲያ መፈጠች በመቻሉ ነበር::

ከ 1958-61 በቻይና የተከሰተው ረሃብ ግን ምንም ህዝብና የፖለቲካ ልሂቃንና ተቋማቶች ሳያውቁት ከ 16.5 እስከ 29.5 ሚሊዮን ህዝብ  እንዳለቁ ተዘግቧል:: ማኦ ዜዱንግና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲም ይህን ያህል ህዝብ እንዳያልቅ መከለከል ያልተቻለበት ምክንያት ምግብ የማምረትና የመግዘት መብቱና አቅሙ የተሟጠጠበት ህዝብ ዕርዳት በአፋጣኝ አለማግኘቱን የሚያጋልጡና የሚከታተሉ ነጻ ፕሬሶች አለመኖራቸው እንደሆነ ማመናቸውና ከዚያም በኋለ ብዙ ማስተካከየ እርምጃዎችን እንደወሰዱ ተዘግቧል::

በሃገራችን በኢትዮጵያም ለረሃብ የተጋለጡ ወገኖች ለሞት ሳይደርሱ የምግብ ዕርዳት አላማግኘት ችግር በሃይለስላሴ ፣በደርግ እና በወያኔ ዘመንም ተመሳሳይ ነው:: በሁሉም ጊዜያት የገዢው ወገኖች ከፍተኛ የሆነ  የልደትና የፓርቲ ድግሶችን እያደረጉ ባሉበት ወቅት የተራቡ ወገኖች ወደከተማ እንዳይሰደዱ፣ በቲሌቪዝንና በሬዲዮ እንዳይሰሙ እዲሁም የተራቡት ወገኖች ብዛት ቁጥሮችን ማሳነስ የተለመዱ የመሸፋፈኛ እርምጃዎች ናቸው::የወያኔ መንግስት ማንኛውንም የሃገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች ባሁኑ ሰዓት እየተባባሰ ስለመጣው ረሃብ ምንም ነገር እንዳይዘግብ የከለከለ ሲሆን “በወቅቱ ረሃብ ልጄ ሞተብኝ” ብለ ለ BBC ዘጋቢ ሃሳቧን የሰጠችውን የወሎ  ረሃብተኛ መልሳ እንድታስተበብል መደረጓ ተሰምቷል:: ይኽው “ መንግስት” ባንድ በኩል ችግሩን በቁጥጥሩ ስር እንዳደረገው፣ ያለማንም ዕርዳታ ምግብ ከውጭ ገዝቶ ለችግረኞቹ እንደሚደርስላቸው ሲፎክር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለማቀፉ ህብረተሰብ ችግሩን ለመፍታት አልተንቀሳቀሰ በማለት ወቀሳ እየቀረበ ይገኛል:: በዚህ ግርግር መሃል ግን የተራበው ወገናችን ምግብ ባፋጣኝ ሊደርስላቸው እንዳልቻለና በዚያውም ምክንያት ብዙ ወገን በሞት አፈፍ ላይ እንደደረሱ እየተዘገብ ይገኛል::

ባጠቃላይ “መንግስታችን” እንደሚፎክረው በሁለት ዲጂት እያደገ ባለበት ኢኮኖሚና ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩት ወገኖቻች መጠን ከ 44% ወደ 31% ዝቅ ማለቱ በተለፈፈበት ሁኔታ፣ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምግብ የማምረት፣ የመግዛትና ዕርዳታ የማግኘት መብትና አቅም ያጡ ገበሬዎች መከሰታቸው ሲታይ  የወያኔ  ፖለቲካ “ሁሉም ዜሮ ዜሮ” የሆነ “ፕሮፓጋንዳ” ብቻ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል::

የተራቡት ወገኖቻችንን ከሞት ለመታደግ ዕርዳታ ማሰባሰብና እንዲደርሳቸው ማድረግ ታላቅ የዜግነት ግዴታችን ነው:: ነገር ግን በየ 5 እና  10  ዓመታቱ የሚከሰተውን የረሃብ አዙሪት በዘላቂነት ከመፍታት ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ግን በጣም አናሳ ነው:: የዚህ የረሃብ አዙሪት ዘላቂው መፍትሄ  የገበሬውን ምግብ የማምረት፣ ምግብ የመግዛትና በእህል ምርት እጥረት ጊዜ ባፋጣኝ ምግብ የሚያገኝበት መብትና አቅም እንዲገነባ ማድረግ ነው:: ለዚህ መሳከት ደግሞ ዲሞክረሲና ነጻ ገበያን ማዕከል ያደረጉ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና እስትራቴዎጅን ተግባሪዊ ማድረግ ብቸኛ መንገድ ነው:: በኔ ግምት እነዚህ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና እስትራቴዎጅ  አሁን እየገዛን ባለው “ መንግስታችን” ተግባሪያዊ እየሆኑ አይደሉም ይሆናሉ ብዬም በፍጹም አልጠብቅም:: ስለዚህ በየጊዜው እየተራቡ የሚሰቃዩትን ወገኖቻችንን በዘላቂነት ለመታደግ ከፈለግን፣ ያለውን ገዢ “መንግስት” በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመለወጥ እየተደረገ ላለው ትግል የራሳችንን አስተዋጽዖ ማድረግ ግዴታች ነው ብዬ አምናለሁ፣ ጥሪም አስተላልፋለሁ::

በተረፈ ቸር ይግጠመን::

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48566#sthash.r3TAEAfg.dpuf

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s