ኤሊኖ ወይስ አውሮቦሮሶች?

 

ነጋ አባተ ከእስራኤል

ሰሞኑን ድኅረ- ገፆቻችንን ያጥለቀለቀው ዓቢይ ጉዳይ “ርሃብ” በሚባል ጨካኝ ምጣድ ላይ ተዘርግፈው እየተቆሉ ላሉ ወገኖቻችን የእንድረስ ጩኽትን የሚያስተጋባ የፌስ ቡክ “የክፉ ቀን” ዘመቻ ይመስለኛል። ምንም እንኳን ዕንቅስቃሴአችን ከጩኽት መዝለሉን እርግጠኛ ባልሆንም እኔም በጓደኞቼ አማካኝነት ተሳታፊ ሆኛለሁ። ቆይ ግን ጎበዝ! ቆም እንበል በእውነት ክፉ ቀን ወይስ ክፉ ጠላት? ኤሊኖ ወይስ አውሮቦሮሶች?። “አህያውን ሲፈሩ መደላድሉን” እንዳይሆን ብየ ነው።

hanger
የፌስ ቡኩን ዘመቻ የከፈቱት ወገኖቼ በንጉስ በአጤ ምኒልክ ዘመነ- መንግስት ከ1880-1884 የተከሰተውንና ወገናችንን በመሮ ጥርሱ አድቅቆ በትውልድ መካከል የማይደብስ ጠባሳ ጥሎብን ያለፈውን እነኝያ “ክፉ ቀን” በመባል የሚታወቁትን ድርብርብ አሰቃቂና ማቅ-ለበስ ዐመታት ስያሜ በመውሰድ የተጀመረ ዕንቅስቃሴ ይመስለኛል። አዎ! ከባድ ዓመታት ነበሩ ክፉ ቀን የሚል መጠሪያ ይዘውም በታሪክ መዝገብ ከነግሳንግሳቸው ሰፍረዋል። ሌላው ሳይቀር ወራሪው የጣሊያን ጦርም ስለርሃቡ መረጃው ስለነበረው ይህንን ክፉ አጋጣሚ ተጠቅሞበታል ይባላል። ግን ወዴት ወዴት“ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል ይባል የለ” ያ ክፉ ቀን ወዴት የአሁኑ (?) ወዴት።
በዚያ ክፉ ቀን ህዝቡ በሞት የተሸነፉ ዘመዶቹን እየቀበረም እየጣለም እሱም ከሞት ጋር ግብግብ እየገጠመና በነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ እየተጣደፈ ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫ ወደ ንጉሱ ዓጤ ምኒልክ ቤተ-መንግስት በጥቁር እንግዳነት ከአሸለቱ ቁመናዎቹ ጋር የተገጠገጠው ችግረኛ ቁጥር እንዲህ ቀላል የሚባል አልነበረም። በዘመኑ ይህንን የሰቆቃ ትዕይንት በዓጤ ምኒልክ ቦታ ሆኖ ላየው ይጨንቃል አቅል ይሰውራል። ይሁን እንጅ ንጉሱ ከእውነቱ ዘወር አላሉም ይልቁኑም በተሰበረ ልብ እንዳመጣጡ ተቀበሉት እንጅ። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ምንድነው ህዝብ የሚያምነው መሪ ሲያገኝ የአባት ያክል ያምነዋል። ህመሙን ፤ ጭንቀቱን፤ የሆዱን ብሶት ሊያካፍለው ይፈልጋል። ከእግዚአብሄር ቀጥሎ ህዝብ ልቡን የሚጥለው በእርሱ ላይ ነዋ!። ዓጤ ምኒልክ ይህ ግርማ ሞገስ በህዝባቸው ላይ ነበራቸው እምየ የሚለውን ስም ያገኙትም በነኚህ የጭንቀት ቀናት ነው ይላሉ ብዙዎቹ። ለሩህሩህነታቸውና ለደግነታቸው ከህዝብ የተሰጠ የፍቅር ስጦታ!።
ደጉ ንጉስ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ ከባድማው የተሰደደውን መፃተኛ እንደዛሬዎቹ ጅቦችና ዘግቶ በላዎች፤ ሲቀጥልም የዘመናችን ኦውሮቦሮሶች፤ ክቡሩን የሰውን ልጅ በስቃይ ጅራፍ እይነረተ እመሬት ላይ ስለሚደባልቀው፤ ብሎም እነርሱ ራሳቸው ጎትተው ስላነገሱት የችጋር ጭራቅ መስማት እንደማይፈልጉት የአፍ ጉልበተኞች የመስቃን ቃል አልተናገሩም ፈሪሃ እግዚአብሄር አላ!። በእኔ የንግስና ዘመን ? የምን ርሃብ? ብለው የአካኪ ዘራፍ ምላስ አልወነጨፉም። ከዚህ ይልቅ በቅርባቸው ለነበሩት የሃይማኖት አባቶች እግዚአብሄር ምህረቱን ይልክ ዘንድ አጥብቀው እንዲለምኑ አሳስበዋቸው እሳቸው ግን ከዙፋናቸው ወርደው በእጃቸው የተገኘውን ያድሉ ገቡ። በአካልም በአስተሳሰብም የሸመገሉት ንጉስ ምኒልክ ያደረጉት ይህንን ነው።
የእኛዎቹ የዘመናችን አውሮቦሮሶች ግን በመለኮት እቅድ ምክኒያት ግንዘተ-ልቦና ሆኖባቸዋልና ክፉ ዘርን ይዘሩ ዘንድ በመርዝ በተሞሉ አለብላቢት ምላሶች ላይ በመቆማቸው፤ መልካም ዜና ከነርሱ ዘንድ ላይሰማ እነርሱ ለጸባዖት የራቁትን ያህል ለእነርሱም የራቀ ነው። ከዚያ ይልቅ በደደቢቱ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተው፤ ነገር ግን ጠረጴዛ ላይ ተፈትኖ ለመውጣት በምሁራን መካከል ለመገኘት የሚቅለሰለሰውንና የዓይን-ዐፋሩን የኢኮኖሚክስ ስሌታቸው የ”ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ” ድምር በሁለት አሃዝ ተመንድገናል እያሉ እንደልጅ ይቧርቃሉ። ወደ ጉልምስና የማይመጣ የተፈጥሮ ህግጋትን የናደ ውበት አልባው ልጅነት! ድንክየነት! ይሏል እንግዲህ ይህ ነው። ለዚህ ነው ታላቁ መጽሓፍ መጽሓፍ ቅዱስ “ንጉሶቿ ህጻናት ለሆኑ ለዚያች ሃገር ወዮላት” የሚለን በልጅነት አዕምሮ መጡ በልጅነት አዕምሮ አረጁ በልጅነት አዕምሮ ወደ መቃብር መውረዱን ተያይዘውታል። የሸመገለና የተፈታ ልብማ እርቅ እርቅ ይሸተዋል፤ ሁሉን የሚሸከምበት ሰፊ የፍቅር ቋት ይኖረዋል፤ ማንም ያለጭንቀት የሚያርፍበት የመንፈስ ጥላ ይኖረዋል።
ምድራችን ለቁጥር የሚታክቱ ለስልጣናቸው የሚንሰፈሰፉ ነገስታትንና አምባገነኖችን አስተናግዳለች ይሁን እንጅ የህዝባቸውንና የሃገራቸውን ክብር የሚነካ ጉዳይ ሲገጥማቸው ግን ሁሉም ማለት ይቻላል ግንባር ቀደም ሆነው ዘብ በመቆም አያስነኬዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከል አንዱ አጤ ምኒሊክ ናቸው። ንጉሱ ስልጣን ይገባኛል ብለው ታግለዋል ተራራ ወጥተው ወርደዋል። በህዝብ ላይ ርሃብ በመጣ ጊዜ ግን ህዝቤ፤ ድሆቼ ብለው ከልብ በተሰበረ መንፈስ አነቡ አንጅ የተሟገገውን ገላ አይተው ጎሽ የኔ ልጅ በእኔ የንግስና ዘመን ጠግበኸልኛል ብለው የሳሳውን ገላውን በፕሮፐጋንዳ ሳማ አልገሸለጡትም። እንደ ወንጭት የተጠረበውን ባቱን አይተው እንዲያ እንጅ ጠብደሃል በል በሚል የግፍ ቃል አንገቱን አስደፍተው ባይተዋር አላደረጉትም።
እዚህ ላይ እንደ ዋቢ የምጠቅሰውና “እውነት” የሚለው ክቡር ቃል ይገልጠዋል ብየ የማስበው የሶፎክለሱ ንጉስ ኤዲፕስ ትዝ አለኝ። በእርሱ ዘመን የአቴናን ምድር ያንቀጠቀጠ አንዳች የመቅሰፈት ምች ከተማዋን ያደቅቃት ያልማት ጀምሯል ። ህዝቡም በደረሰበት አደጋ ተደናግጦ፤ ተጎሳቁሎና እንደሞት ሰራዊት በአስፈሪ ድባብ ታጅቦ ወደ ቤተ መንግስቱ ይተም ይዟል። ይህን የተረዳው እውነተኛውና አስተዋዩ ንጉስም ህዝቡን ለመቀበል ከነሞገሱ ወደ ሰገነቱ ይወጣል። በሚያየው ነገር ግን ልቡ ይናጥ ይደማ ጀምሯል። አይን-ስውሩን ነቢይ የዚህ መቅሰፍት መንስኤና መፍትሄው ምን እንደሆነ እንዲነግረው አጥብቆ ይጠይቀዋል። ከብዙ የዙሪያ ንግግርና ከሽማግሌዎቹ መዘምራን ምክር በኋላ ንጉሱ እውነቱ ካልወጣ መፍትሄ የለም በሚል እሳቤና ፤ እውነትንና ፍትህን በአደባባይ ለማቆም ቆርጦ በመነሳቱ ምክኒያት አውጫጭኙ ከሯል። ሁሉም ክርክሩ በፈጠረው ግለት በፍርሃት እየተለበለበ ጥግጥጉን ይዟል ይባስ ብሎም ንጉሱ ችግሩና መፍትሄው ካልተገኘ ደግሞ በየደረጃው ያሉትን ሃላፊዎችን ተገቢውን ቅጣት እንደሚያከናንባቸው ዛተ። የነገሩ ስር ከግራ ከቀኝ እየተቧካ በስተመጨረሻው ፍርጥርጡ ወጣና ንጉሱ የመርገሙ ምክኒያት ሆኖ ተገኘ። እዚህ ላይ ነው የኤዲፐስ ማንነት የሚታየው ከተጠያቂነት ለመዳን ልሸፍን ላዳፍን፤ ስልጣኔን ንግስናየን ላስጠብቅ አላለም በራሱ ላይ አስቃቂውን እርምጃ በመውሰድ ስልጣኑን ለቆ ከምቹው ቤተ-መንግስት በመውጣት የእውነትንና የፍትህን ጫፍ አሳየ። እዚህ ላይ ከንጉሱ አስገራሚ ባህሪዎች ሁለት ዋና ዋና ቁምነገሮችን ልናይ እንችላለን በመጀመሪያ ከኔ የተሻለ ዕውቀት ሌሎች ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብና ሌላው ደግሞ እውነት እንዳትዳፈን መድከሙ ናቸው። የአቀባበላቸው ዳኝነት እውነት መሆኑ ደግሞ ሁለቱን ንጉሶችን አመሳሰለብኝ።
የመጣጥፌ ዋና ዓላማ የዘመናችንን አውሮቦሮሶች ጥላሸት በመቀባት የፖለቲካ ትርፍ በማግኘት በጭንቅ ውስጥ ባሉ ወገኖቼ ህይወት ላይ ቁማር ለመጫወት እንዳልሆነና ሰውን ያክል ክቡር ፍጥረት እንደሰው በስፍራችን መገኘት አቅቶን በነገር ዘባተሎ እየተጠላለፍን በወደቅንበት በዚያ ቁመናውም ልኩም በማይታወቅ የውዝግባችን ቅርቃር በመሸንቆር ያስተሳሰብ ብልግና ውስጥ ራሴን ለመጣል በመፈለግም አይደለም።
ጥያቄየ ግን እውነቱ ወዴት ነው ? ነው። የርሃባችን አቢይ ምክኒያት ብዙዎቻችን እንዳልነው የቀኑ ክፋት ወይስ የገዥዎቻችን ክፋት ? ወይስ እነሱ እንዳሉት ኤሊኖ?። ኤሊኖ! አይ ቅጥፈት! ነገ ደግሞ የሆነ ችግር ቢፈጠር የዚህ ችግር ዋና ምክኒያት የህዳሴው ግንባታ ያመጣብን ጣጣ ነው ሊሉን ይችላሉ ምን ችግር አለው? ባፈጠጠ የህሊና ጥሰት ለሚኖር እጓለ ምዑት ሰፈር እኮ ውሸት አንድ ሙዚቃ ነው። ምነው ገዥዎቻችን ራሱን እንደሚበላ አውሬ አረመኔነቱን አጦዙትሳ? የዚህ በለየለት የህዝብ የጠላትነት ጫፍ ላይ መቆም ጉዳይስ የሂሳብ አወራረዱን ምን ያስመስለው ይሆን?። ደግሞስ በዚሀ በሰለጠነ ዘመን ሰለ ርሃብ ማውራት አይቀፍም ወይ?። ለገባውማ ይቀፋል ይጎፈንናል እንጅ! ለደደቢት ምሩቃን ግን ይህ የመርህ ጉዳይ ነውና እንደ ታላቅ ስኬት ይቆጠራል።
በአጤ ምኒልክ ዘመን ከደረሰብን ርሃብ አርባ ዓመት ቀደም ብሎ በድንች ላይ ጥገኛ በነበረው የአየርላንድ ህዝብ ላይ የደረሰው አሰቃቂ ርሃብ አየርላንዶቹ ታሪካቸውን በሃዘን የሚገልጡት ምዕራፋቸው ነው። “ The great famine” ተብሎ በተሰየመው በዚህ ርሃብ “The potato blight” የሚባል የድንች በሺታ ተከስቶ በሚሊዮን የሚቆጠር የአየር ላንድን ህዝብ አርግፏል አሰድዷል። ለዚያ ርሃብ በህዝቡ በኩል የቀረበው ምክኒያት በጊዜው በነበረው የአስተዳደር ብልሹነት ነው ሲል በሹሞቹ በኩል ግን የለም በጊዜው የተከሰተውን የድንች በሺታ ነው በሚል የተነሳው ውዝግብ ቀጥሎ ግን ሳይቋጭ እንደተንጠለጠለ የቀረ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጅ ያ የርሃብ ምች እንደኛ እያሰለሰ አዚም ላይሆን ዳግመኛም ተከሰቶ የአየርላንድን ህዝብ ላይቀጥፍ አሸልቦ በአየርላንዳዊያን ግብዓ- ተመሬቱ ተፈጽሟል። የእኛ የርሃብ አዙሪት ግን እኛኑ ሊቀብረን እየሰለለን ይመስላል እውነተኛውን መንሰኤውንና መፍትሄውን ገና አላገኘነውማ!።
በዚህ በምኖርበት በእስራኤል ሃገር እስራኤላውያኖቹ የሚሉት እኔንም የሚገርመኝ ነገር አለ። ይኸውም መሬታቸው በአብዛኛው አሽዋማ ነው ግን ይሰሩበታል፤ የተስተካከለ የዝናብ ወቅት የላቸውም እነርሱ በዚያም ጥገኛ አይደሉም፤ የመሬታቸው የቆዳ ስፋት ትንሽ ነው ግን ከሚበላው የሚደፋው ይበልጣል። እነርሱም በኩራት የሚናገሩት እዚህ ላይ ነው። “በካርታ ላይ እስራኤል ብሎ ለመጻፍ ቦታ እንደሌለ ሁሉ መሬታችንም ጠባብ ናት ግን እስራኤል ሃገር ርሃብ የለም።” ይላሉ። ስለአንዱ የገጠር መሬታቸው ትንሽ ልንገራችሁ ትንሿ ገጠር יוטבטה’’ (ዮትባታ) ትባላለች በሃገሪቱ ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል ትገኛለች። የዚህች መንደር መሬት አሽዋ ነው የመንደሯ ነዋሪዎች አርሰው ለማምረት ሲፈልጉ መጀመሪያ መሬቱን አጥበው ጨውን ማስወገድ አለባቸው ከዚያ በኋላ ነው ዘር የሚዘሩት ታዲያ የዚህች ትንሽ የገጠር መንደር ገበሬዎች በመላ እስራኤል የእርሻ ምርታቸውንና የወተት ተዋጾዖቻቸውን በማቅረብ ይታወቃሉ። እስኪ በስራኤል ዓይነት የእኛን ሁኔታ እንመልከት።
ወደ ጉዳያችን ስመለስ የዘንድሮው ጠኔ ገድ አልባ ሆኖና እንደ ቀላዋጭ እንግዳ ተሰልችቶ ነው ብቅ ያለው። በም ዕራባውያን በኩል ከሰራተኛው ህዝብ ከሚሰበሰበው ግብር እየተቆረሰ የሚላከው ገንዘብ የገዥዎቻችን የብልግና ጡንቻ ማፋፊያ እንደሆነና አውሮቦሮሶችም መናጢ ደፍቶ በላ ትዝቢዎች መሆናቸውን ከተገንዘቡ ውለው አድረዋል። እናም የሚራራው ልባቸው ተዘግቷል። እዚህ ላይ አንድ ገጠመኜን በምሳሌነት ላንሳ በስደት ከሃገሬ ከመውጣቴ በፊት በሙያየ ለአንድ መያድ (NGO) የ 30 ደቂቃ አጭር ተውኔት እንዳዘጋጅላቸው እየተነጋገርን ባለንበት ጊዜ ድርጅቱን በገንዘብ አቅርቦት የሚደግፍው የኖርዌይ ልዑካን ቡድን ለግምገማ ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡበት ወቅት ነበር። ልዑኩ የስራ ግምገማውን ከጨረሰ በኋላ የደርሰበት ድምዳሜ ከሚንቀሳቀሱት ጣቢያዎች መካከል ሰባቱን መዝጋት መወሰኑን አሳወቀ ምክኒያቱስ ተብሎ ሲጠየቅ ልዑኩ የሰጠው አጭር መልስ “ የሃገራችሁ ባለጠጎች የሚይዟቸውን መኪኖች ስንመለከት በእኛ ሃገር በብዙ ሰዎች የማይያዙ ንብረቶች ናቸው እኛ ይህንን የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ስናንቀሳቅስ ከድሆች እየለመንን ነው። በእኛ ግንዛቤ እነዚህ ባለጠጎቻችሁን በታግባቧቸው ይህን ፕሮጀክት ሊያንቀሳቅሱ ይችላሉ ብለን እናምናለን።” በማለት ውሳኔአቸውን አጸኑ።
አስተውሉ እነዚህ የኖርዌይ ሰዎች እየተናገሩ ያሉት ሰው ስለሚባለው ሰው ነው። ወገኖቹ በርሃብ ሲያልቁ ከአልጋው ወርዶ መሬት በመተኛት ያለውን ስለሚያካፍለው ሰው!። ከሚያማርጠው ውስኪ ወጣ ብሎ ለወገኖቹ አንድ ጣሳ ውሃ ማቅረብ ስለሚችል ሰው!። ልቦናውን እንደተሰረቀውና እንደ አለሌ የሜዳ አህያ ከሚፋንንበት ርቆና ከህሊናው ጋር ታርቆ ስለሚኖረው ሰው!። በነርሱ ሃገር የህሊና ግዴታ የሚባል ነገር አላ!። ይህማ ባይሆን ከሃገራቸው ኢትዮጵያ ድረስ ምን አንከራተታቸው?። እነዚህ እንግዶች የኢትዮጵያ ባለጠጎች ይሳተፉ ማለታቸው በሰው ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ህሊና መሰረት አድርገው ነው። ህሊናውን በጣለ የወዲኒ መንጋ መካከል መኖራቸውን አላወቁም ነበር።
የወደቅንበትን እናስተውል የማዕድ በጀት አልባ ሆኖ በቆሻሻ ገንዳ ከውሻ እና ከአሞሮች ጋር እየተናጠቀ ጉሮሮውን ዘግቶ በሚያድርባት ሃገር ሌላው የሁለት ሚሊዮን ብር ይዞ ሲንፈላሰስ የህሊና ህግ ስለተጣሰ አይጠየቅም!። የፋራ ነው!። ውሃ ባአግባቡ ማቅረብ ባልቻለች ሃገር ውስጥ ጥቂቶች ውስኪ እንደ ውሃ የሚራጩባት የጉድ ሃገር መሆንዋን ስናይ የሰው ያለህ ብለን በባይተዋርነት እንንገደገዳለን። ምንጩ ሲመረመር ደግሞ አይን ያወጣ ሌብነት በሃገሪቱ በመንሰራፋቱ ነው። የወረድንበት የዝቅጠት ልክ ሲለካ አራዊትን እንኳን አልመጠነም ቀልለን ተገኜን። ምን ማለቴ ነው በቡድን የሚጓዝ የአራዊት መንጋ ዞጉን አይነካም ነውር ነው ህገ-አራዊት ወሰናይ አላቸውና! ቢጣሉ እንኳን አይገዳደሉም ። ኃይላቸውን ለሌላው ባላንጣቸው ይጠብቁታል እርስ በርሳቸው ቢገዳደሉ ለነገ የመኖር ዋስትና እንደሌላቸው ያውቁታል ይህ ዕውቀት አላቸው። ያደኑትን ተካፍለው ይበላሉ ከመሃከላቸው አውራ የተባለው እንኳን ኃላፊነት ተሰምቶት ከርሱ ለሚያንሱት ትቶላቸው ዘወር ይላል። ሃገራችን ግን በአውሮቦሮሶች ተውርራለች።
በግሪካውያን ጥንተ-እምነት ጥናት መሰረት አውሮቦሮስ የሚባል የድራጎን አይነት ነበር። ፕሌቶ ስለዚህ ዝርያ ሲናገር “ዝርያው ዓይን ስለሌለው አድኖ የሚበላውን አያይም ፤ ጆሮም ስለሌለው አዳምጦ የሚጎመርበት ፍጥረት የለም አፈርና ውኃ ሲልስ አድጎ በመጨረሻ ከጅራቱ በመጀመር ራሱን እየበላ ወደ ግብዓ- ተመሬቱ ያዘግማል። እናም ፕሌቶ ስለዚህ አሳዛኝ አውሬ ሲደመድም ራሱን የሚበላ ፍጥረት በዚህች ምድር ህልውና የለውም።’’ ይህን የድራጎን ዘር ከእኛዎቹ ወዲኒዎች ጋር ያመሳሰልኩበት ምክኒያትም የሚሰሙበት ጆሮ የሚያዩበት ዓይን ስለሌላቸው ነው። ያላቸው አፍ ብቻ ነው። ያ ነው ጉልበታቸው። ያንም ህዝባቸውን ለመብላት እየተጠቀሙበት ነው ሌላውን ለማሸነፍ አፍ ብቻውን ጉልበት አይሆንም ። ግን ርቀቱ እስከየት ነው?። ህዝብ በስደት ውኃና በርሃ እየበላው አንድ ወፍ የሞተ ያክል እንኳን የዚያን ህዝብ ዕልቂት ከቁብ አይቆጥሩትም የዕልቂቱ ምክኒያትም እነርሱ መሆናቸውን ባለመቀበል በክህደት ይደመድሙታል። ከዚህ በላይ የራስን ህዝብ ራስንም ከመብላት የበለጠ አረመኔነት በየትኛው ፍጥረት ይታያል?። 15 ሚሊዮን ህዝብ ተርቦ ውሸት ነው ብለው በፕሮፐጋንዳቸው ለማፈን ተሯሯጡ በርሃብ እየተጠበሰ ካለው ህዝብ ይልቅ የእንቧይ ካብ ስልጣናቸው በልጦባቸው በተራበው ህዝብ ላይ ቀለዱ። ይባስ ብለው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመበጀት ህወሐትና ብአዴን (EPRDF) ለአስረሽ ምቺውና ለሴሰኝነታቸው ማስገሪያ እየበተኑ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ዜጋ በሚል ፈሊጥም ፊታቸውን በአሞሌ ታጥበው ለአንድ ሰው 25 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቤት እየሰሩ እንደሆነ ነግረውናል። እነዚህ ሰዎች የህዝብን ገንዘብ ሰርቀው የግላቸው ሲያደርጉ ኢሞራላውነትና ኢሰብዓዊነትን እያነገሱ ነው ይህንም ሲያደርጉ ህዝብንም ትውልድንም እየበሉ እንደሆነ አላወቁም ትውልድን ሲበሉ ራሳቸውን እየበሉ መሆኑንም ገና አልተገለጠላቸውም ። ከዚህ በላይ በህዝብ ላይ ንቀትና ጥላቻስ በምን ይገለጣል?። የናረ የህዝብ ጠላትነት!። ግን አንድ ነገር እመኛለሁ ደብቶ ከያዘን ከዚህ አዚም ስንወጣ! ያኔ ለጠላቶቻችን ዕድሜ የሰጠናቸው እኛ መሆናችን ሲገባን ራሳችንን እንወቅሳለን።
The enemy of the people (የህዝብ ጠላት) ከሚለው የኢብሰን ተውኔት ትንሽ ማለት ፈለግሁ። በኢብሰን ተውኔት ውስጥ ከህዝብ ጎን በቆመው ሃኪም እና በህዝብ ጠላትነት በቆመው የከተማዋ ከንቲባ ገጸ፟-ባህሪያት መካከል ያለውን ፍትጊያ በአጭሩ ስናይ ሃኪሙ የከተማዋን ነዋሪ እያረገፈው ያለውን ሞት ምክኒያት ለማወቅ ሲወድቅ ሲነሳ ይቆይና ምክኒያቱን ያገኘዋል ያም የከተማዋ ህዝብ የሚጠቀምበት ውኃ በመመረዙ ነው። ሃኪሙ መንስኤውን በማግኘቱ ትንሽ ተደስቶ ወደ መፍትሄው ሲዞር ደግሞ መፍትሄ ብሎ ያገኘው የከተማዋን ህዝብ ወደ ሌላ ስፍራ ማዞር ነው ይህንንም ለከተማዋ ከንቲባ ያማክረዋል። የከተማዋ ከንቲባም ለሃኪሙ ምክኒያቱንም መፍትሄውንም እንዳይናገር ይከለክለዋል ይባስ ብሎ በከተማዋ ከሚገኘው ታዋቂ የጋዜጣ ኤዲተር ጋር በመመሳጠር የፕሮፕጋንዳውን ስራ ያጧጡፉታል። ለህዝቡ ሞት ደንታ ያልሰጠው ከንቲባ የሃኪሙንም የመናገር መብቱን ከለከለው። የከንቲባው ዋና ዓላማ ህዝብ አይደለም ስልጣንን ማስጠበቅ ነው ለዚህም የፕሮፕጋንዳውን ስራ ማጧጧፍ ነው። ትንቅንቁ ይቀጥላል። የህዝብ ጠላት የሆኑ ሹሞች ጉዳያቸው ከስልጣናቸው ጋር እንጅ ከህዝብ ጋር አይደለም ይህ ስራቸው ደግሞ በህዝብ ጠላትነት ጎራ ያስፈርጃቸዋል።

 

ቸር ያገናኘን።

– See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48595#sthash.tsPzO5sI.dpuf

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s