ኢትዮጵያ በረሃብ በክፉ ድህነት ሳቢያ፣ በቀላሉ ሊፈነዳ የሚችል አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ የተቀረቀረች አገር ናት።

 Embedded image permalink
የኢትዮጵያ ድህነት፣ በጣም አደገኛ እንደሆነ፣ ለአፍታም ያህል ልንዘነጋው አይገባም ነበር። ግን፣ በተደጋጋሚ እየዘነጋነው፤ በአላስፈላጊ ንትርክና ግጭት ጊዜያችንን እናባክናለን።
ሰዎች፤ ዘንድሮ ያለ እርዳታ አመቱን መዝለቅ የማይችሉ ረሃብተኛና ችግረኛ ኢትዮጵያዊያን፣ ከ18 ሚሊዮን በላይ ናቸው። ድርቅ በማይከሰትበትና ከፍተኛ የእርሻ ምርት በሚሰበሰብበት አመት እንኳ፣ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ ያለ እርዳታ ከአመት አመት መሻገር አይችሉም። የውጭ የእህል እርዳታ ባይኖርኮ፣ ሕዝብ ያልቅ ነበር። ከዚህ የከፋ አደጋና ውድቀት ምናለ?
በከተሞች፣ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች፣ የሉም። በ1994 ዓ.ም በመካከለኛና ትላልቅ የኢንዱስትሪ ተቋማት የነበሩ ሰራተኞች ቁጥር መቶ ሺ ነበር። ዛሬ ከአስራ ምናምን ዓመታት በኋላ፣ ቁጥሩ 300ሺ ብቻ ነው። ለዚያውም፣ የሰራተኞቹ አማካይ የገቢ እና የኑሮ ደረጃ ሲታይ፤ በ40% የወረደ ነው (በብር ሕትመትና በዋጋ ንረት ሳቢያ)።
በከተማም ሆነ በገጠር፣ ኢትዮጵያ በክፉ ድህነት (በረሃብና በሥራ አጥነት) ሳቢያ፣ በቀላሉ ሊፈነዳ የሚችል አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ የተቀረቀረች አገር ናት።
ወገኛነት ተጠናውቶን፣ ‘የሃብት ልዩነትና የሃብት ክፍፍል’ እያልን እንደሰኩራለን – ሃብት መፍጠር ባቃተው አገር ውስጥ ሆነን። ስለ ‘ካርቦንዳይኦክሳይድ’ እና ስለ ‘አለም ሙቀት’ እንለፍፋለን – ነዳጅ ለመጠቀም አቅም በሌለው ድህነት ውስጥ ሆነን። መሬትንና ገጠርን፣ ግብርናንና ዘልማዳዊ አኗኗርን እያንቆለጳጰስን እናወራለን – የድህነት አጣብቂኝ ጋር የሙጢኝ ብለን ለመቀጠል።
ሰዎች እናስብ እንጂ። በእርሻ ብቻ፣ ከረሃብ የተላቀቀ አገር፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የለም። ያለ ኢንዱስትሪና ያለ ከተማ እድገት፣ ወደ ብልፅግና ለመራመድ ይቅርና፣ ከድህነት… ከረሃብና ከስራ አጥነት መውጣት አይቻልም። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ፣ የፋብሪካ ምርት ድርሻ፣ ከድሃ የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር እንኳ፣ ግማሽ ያህል አልተራመደም። (ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ – ገፅ 6)።
የመካከለኛና የትላልቅ ፋብሪካዎች ኢንቨስትመንት አልተስፋፋም። የስራ እድሎችን በገፍ ይፈጥራሉ እየተባለ ብዙ የተወራላቸው፣ “የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት”፣ በተግባር እንቅስቃሴያቸው ሲታይ፣ ከሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ የባሰ ቀርፋና ጎታታ ሆኗል። የፋብሪካ ምርት ፈቅ አለማለቱ መንግስትን ቢያስጨንቅ አይገርምም። እድገት ሲቋረጥና ስራ አጥነት ሲስፋፋ፣ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ አደጋዎች ይፈጠራሉ። የኢንዱስትሪ ጉዳይ፣ “የሞት ሽረት ጉዳይ ነው” ይላል – የእቅዱ ሰነድ።
ከዚህ የኢንዱስትሪ ልምሻ ላይ፣ የኤክስፖርት ድንዛዜ ሲጨመርበት ደግሞ፣ ይበልጥ ያስፈራል። ለዚህም ይመስላል፣ ሁለተኛው የሞት ሽረት ጉዳይ፣ ኤክስፖርት እንደሆነ ሰነዱ በተደጋጋሚ የሚገልፀው።
በእርግጥም፣ በአለማቀፍ ንግድ፣ የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ ካልተቻለ፣ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን ማፋጠን አይቻልም። እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ፣ በአምስት አመታት፣ ኤክስፖርትን ወደ ሦስት እጥፍ ማሳደግ ያስፈልጋል ተብሎ እቅድ ወጥቶ የነበረውም፤ በዚህ ምክንያት ነው።
ነገር ግን፣ ኤክስፖርት አላደገም። የኤክስፖርት ሽያጭ አምና፣ 10 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ ቢታቀድም፤ አልተሳካም። 3 ቢሊዮን ዶላር ላይ ደንዝዞ ቆሟል። ለምን? በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻ እየገነነ፣ በተቃራኒው ኢንቨስትመንት እየቀጨጨ ከመምጣቱም በተጨማሪ፣ ኤክስፖርትን ያደነዘዙ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።
አንደኛ፣ ባለፉት አምስት አመታት፣ መንግስት፣ በአላስፈላጊ የምዝገባ ቢሮክራሲና በአጥፊ የዋጋ ቁጥጥር አማካኝነት የአገሪቱን የቢዝነስ ድባብ ሲያተራምስ ቆይቷል።
ሁለተኛ፣ መረን በለቀቀ የገንዘብ ህትመት ሳቢያ፣ የአገሪቱ ብር መርከሱ እየታወቀ፣ የዶላር ምንዛሬ በዚያው መጠን እንዲስተካከል አለመደረጉ፣ ኤክስፖርትን ጎድቷል። የአለም ገንዘብ ድርጅት እንደሚለው፤ የዶላር ምንዛሬ፣ 27 ብር አካባቢ መሆን ነበረበት። ግን አልሆነም።
እንግዲህ አስቡት። ቡና ወይም ጫማ አምርታችሁ ወደ ውጭ በዶላር ብትሸጡ፤ መንግስት ዶላሩን ይወስድና፣ በራሱ ተመን በብር መንዝሮ ይሰጣቸዋል – ለአንድ ዶላር ወደ 21 ብር ገደማ። ከእያንዳንዱ ዶላር ስድስት ብር ይወስድባችኋል ማለት ነው። ምርት ወደ ውጭ የሚሸጡ ሰዎችንና ድርጅቶችን፣ እንዲህ እየዘረፍናቸው፣… ኤክስፖርት በሦስት እጥፍ እንዲያድግ መመኘት፣ ነውር አይደለም?
ለነገሩ፤ መንግስትም፣ አሁን አሁን ይህንን መካድ እየተወ ይመስላል። ብር በመርከሱ ምክንያት፣ የዶላር ምንዛሬ እንደተዛባ አምኗል። ይህም ብቻ አይደለም። ነገርዬው፣ ኤክስፖርትን እንደሚጎዳ፣ ትናንት አርብ በፓርላማ በፀደቀው፣ ባለ 185 ገፅ እቅድ ውስጥ፣ በግልፅ ተጠቅሷል። መጠቀስ ብቻ አይደለም። ባለፉት አምስት አመታት ካጋጠሙ ሦስት ትልልቅ ፈተናዎች መካከል አንዱ፣ ይሄው የብር መርከስ ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል። በገንዘብ ሕትመት ሳቢያ፣ ብር ሲረክስ፣ በዚያው መጠን የዶላር ምንዛሬ አለመስተካከሉ ኤክስፖርትን እንደሚጎዳ ሰነዱ ያመለክታል (ገፅ 53)። የውጭ ምንዛሬ ተመንን ማስተካከልና ለኤክስፖርት አመቺ እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ፣ በዋና ዋና እቅዶች ዝርዝር ውስጥ ገብቷል(ገፅ 78)። ጥሩ ነው። በእርግጥ፣ ዘግይቷል። እንዴት?
በብር መርከስና በዶላር ምንዛሬ አለመስተካከል ሳቢያ፣ ኤክስፖርት እየተዳከመ መሆኑን የሚተነትን ፅሁፍ ከሁለት አመት በፊት በአዲስ አድማስ መውጣቱን ማስታወስ ይቻላል።
“‘የስራ ፍሬውን ስንነጥቀው ይበረታታል’ ብሎ መመኘት ሃጥያት ነው” በሚል ርዕስ የቀረበው የያኔው ትንታኔ እንዲህ ይላል።
“ከመነሻው፣ የብር ኖት አለቅጥ ከማተም በመቆጠብ ብር እንዳይረክስ ማድረግ እንጂ፣ ብር ከረከሰ በኋላ፣ የዶላር ምንዛሪን በቀድሞው ተመን ላይ ቆልፎ ማቆየት አያዋጣም። እንዴት ሊያዋጣ ይችላል? በኤክስፖርት መስክ የተሰማሩ አምራቾችና የቢዝነስ ሰዎችን በግድ እየዘረፍናቸው (ከእያንዳንዷ የዶላር ገቢ ስድስት ብር ነጥቀን እየወሰድንባቸው)፤ በየአመቱ  ተጨማሪ ዶላር የሚያመጡ… የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆኑልን… አምነን መቀመጣችን፣ እጅግ አላዋቂነትም እጅግ ሃጥያትም ነው።”
ይሄ፣ ከሁለት ዓመት በፊት የተፃፈና የታተመ ነው። ግን፣ እስካሁን፣ ሁነኛ መፍትሄ ስላልተበጀለት፣ ኤክስፖርት እዚያው በድንዛዜ ተገትሮ ቀርቷል። ከሦስት ዋና ዋና አሳሳቢ የአገር ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀስም ሆናል።
ታዲያ፣ ቅጥ ያጣ የገንዘብ ህትመት… መዘዙ ይህ ብቻ አይደለም። መንግስት አለቅጥ በሚያሳትመው ገንዘብ ሳቢያ፣ ‘ብር መርከሱ’፣ እናም የዋጋ ንረት መከሰቱ፣ ብዙ ነገሮችን አበላሽቷል። ኢኮኖሚውን አተራምሷል። ኢንቨስትመንትን አዳክሟል። እንዴት?
ለእውነትና ለመረጃ ክብር የማይሰጥ፣ ጭፍን ፕሮፖጋንዳ
የዋጋ ንረት ሲፈጠር፣ መንግስት ሁሌም፣ በቢዝነስና በንግድ ሰዎች ላይ ነው የሚሳብበው። ግን፤ ውሸት እንደሆነ ይታወቃል። የዋጋ ንረት፣ ከብር መርከስ ጋር (ከገንዘብ ህትመት ጋር) የተቆራኘ እንደሆነ፣ በግልፅ ይታወቃል። ለዚህም፣ ተጠያቂው መንግስት ነው። ነገሩ ውስብስብ አይደለም። መንግስት፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ጋር በማይመጣጠን ፍጥነት፣ በገፍ ገንዘብ ካሳተመ፤ ብር ይረክሳል፣ የዋጋ ንረት ይፈጠራል። ቁርኝታቸው በጣም የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ፤… ለምሳሌ በአምስት አመት ውስጥ፣ የገንዘብ ሕትመትና ስርጭትን ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር በማነፃፀር፣ ምን ያህል የዋጋ ንረት እንደሚፈጠር መገመት ይቻላል።
የዋጋ ንረት= (የገንዘብ ስርጭት ፍጥነት) – (የኢኮኖሚ እድገት ፍጥነት)
ያው፣ የገንዘብ ስርጭት፣ ከሞላ ጎደል፣ ዞሮ ዞሮ በገንዘብ ህትመትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ‘የባንክ ቼክ’ ላይ የተመሰረተ ነው። እናም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣በገንዘብ ህትመትና በቼክ አማካኝነት፣ (የገንዘብ ስርጭት ከ54 ቢሊዮን ብር ወደ 167 ቢሊዮን ብር ጨምሯል – የብሔራዊ ባንክ የ2007 የመጨረሻ የሩብ ዓመት ሪፖርት አባሪ – ገፅ 8)። ማለትም… የገንዘብ ስርጭት በየዓመቱ፣ በአማካይ 25% በመቶ ሲስፋፋ ቆይቷል።
የኢኮኖሚ እድገትስ?
ባለፉት አምስት አመታት፣ በአማካይ በ10% እያደገ ነበር።
መረጃዎቹ ግልፅ ናቸው። ኢኮኖሚው አቅም በላይ፣ ምን ያህል የገንዘብ ስርጭት እንደጨመረ መመልከት እንችላለን። 15% ያህል ነው ልዩነቱ። ይሄ ነው፣ ዋነኛው የዋጋ ንረት መንስኤ። የዋጋ ንረት፣ ከወር ወር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሊዛነፍ ይችላል። ሁለት ሦስት አመት፣ ከዚያም እስከ አምስት ዓመት ሰፋ አድርገን ካየን ግን፤ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ስርጭት ቁርኝት፣ ፍንትው ብሎ ይታያል።
የዋጋ ንረት = (የገንዘብ ስርጭት ፍጥነት) – (የኢኮኖሚ እድገት ፍጥነት)
የዋጋ ንረት = (25%) – (10%) = 15%
የገንዘብ ስርጭቱ፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በላይ አለቅጥ መስፋፋቱን በማገናዘብ፤ በየአመቱ በአማካይ 15% የዋጋ ንረት እንደሚከሰት መገመት ይቻላል።
በተጨባጭስ፣ ባለፉት አምስት አመታት፣ ምን ያህል የዋጋ ንረት ተከሰተ?
የሸቀጦችን ዋጋ በየወሩ በማነፃፀር፣ የስታትስቲክስ ባለስልጣን የሚያወጣቸውን መረጃዎች መመልከት እንችላለን።
በየዓመቱ የሸቀጦች ዋጋ፣ በአማካይ በ15% ሲጨምር እንደቆየ፣ የስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ይሄ፣ በቀጥታ የሸቀጦችን ዋጋ በማነፃፀር ላይ የተመሰረተ መረጃ ነው።
የገንዘብ ህትመትንና ስርጭትን በማገናዘብ ካገኘነው የዋጋ ንረት ግምት ጋር ተመሳሳይ ነው።
በአጭሩ፤ የገንዘብ ሕትመት፣ ከብር መርከስ ጋር፣ እንዲሁም ከዋጋ ንረት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ፣ ከእነዚህ ተጨባጭ መረጃዎች መረዳት ይቻላል። ግን ምን ዋጋ አለው? መረጃንና እውነትን፣ ከምር የማናከብር ከሆነ፣ እስካሁን ያየነው ትንታኔ ሁሉ ከንቱ ይሆናል።
መንግስት፣ ወጪዎቹን ለመሸፈን፣ አለቅጥ በሚያሳትመው ገንዘብ ምክንያት፣ የዋጋ ንረት እንደሚፈጠር ቢታወቅም፤ ሁልጊዜ በቢዝነስ ሰዎችና በነጋዴዎች ላይ ያላክካል። ለምን? ለዛሬ ብቻ፣ ከወቀሳ ለማምለጥ በመመኘት ሊሆን ይችላል። ግን መዘዞች አሉት።
አንደኛ፤ ለመረጃና ለእውነታ ዋጋ የማይሰጥ፣ የአሉባልታና የፕሮፖጋንዳ፣ የጭፍን እምነትና የጭፍን ስሜታዊነት ባህልን ለማጠናከር፣ በወዶ ዘማችነት እየተሰለፈ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል። ዞር ብሎ ግን፣ ‘ተቃዋሚዎች፣ ተጨባጭ መረጃን ለመቀበል የማይፈልጉ፣ የኢኮኖሚ እድገትን የሚክዱ፣ ጭፍን ፕሮፓጋንዳ የሚራግቡ ናቸው’ እያለ  ያወግዛል። ግን፤ ሁለት ወዶ አይሆንም። ያሰኘው ጊዜ…. ‘ተጨባጭ መረጃን በጭፍን ፕሮፓጋንዳ እየሸፋፈነ’፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ‘ተጨባጭ መረጃ በጭፍን ፕሮፓጋንዳ እንዳይሸፈን እንከላከል’ ብሎ ቢሰብክ፣ ከንቱ ነው።
‘ከገበሬ ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪ ድረስ፣ ኢትዮጵያዊያን፣ በተጨባጭ መረጃ ላይ በተመሰረተ ስልጡን አስተሳሰብ አማካኝነት፣ ውጤታማ ምርታማነትን ማስፋፋትና መበልፀግ ይችላሉ’ ብሎ ይደሰኩራል። ትክክል ነው። ግን፣ ለተጨባጭ መረጃ ክብር የሚሰጥ ባህል፣ በአንዳች ተዓምር አይፈጠርም። በጎን በኩል፣ ለመረጃ ዋጋ የማይሰጥ የጭፍንነት ባህልን ዘወትር እየያጠናከርን፣ እንዴትና ከወዴት ስልጡን አስተሳሰብ ይመጣል? ግን ጉዳቱ ይህ ብቻ አይደለም።
ቢዝነስን እያንቋሸሹ፣ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት?
የዋጋ ንረትን በነጋዴዎችና በቢዝነስ ሰዎች ላይ ሲያላክክ፤ የብልፅግና መሰረትንም በእንጭጩ እየሸረሸረ መሆኑን አይገነዘብም። ቢዝነስ ማለት፣ በተፈጥሮው፣ ‘ማጭበርበርና ማታለል’ ማለት እንደሆነ ለማሳመን ዘወትር ይጣጣራል። በሌላ አነጋገር፤ ‘ትርፋማነት’ ማለት ‘አጭበርባሪነት ነው’፣ ‘ባለሃብት’ ማለት ‘አታላይ ነው’ የሚል ስብከት ይግተናል።
እንዲህ፣ ቢዝነስን፣ አትራፊነትን፣ ስኬታማነትን፣ ባለሃብትነትን ሲያንቋሽሽ ይከርምና፤… ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፤… “የፈጠራና የምርታማነት ክህሎት፣ የቢዝነስና የትርፋማነት ባህል አልዳበረም። ወጣቶች፣ እየገቡበት አይደለም” በማለት እሮሮ ያሰማል።
አሃ፤ ቢዝነስን የሚያናንቅ ስብከት ለአዲሱ ትውልድ እየጋትን፤ የቢዝነስ ጥበበኞችን በብዛት የሚያፈራ ስልጡን ባህል ለመፍጠር መመኘት… እንዴት አብሮ ይሄዳል?
ግን፣ ነገሩ በስብከት ብቻ የሚቆም አይደለም።
የዋጋ ቁጥጥር እየታወጀበት፣ ፋብሪካ ለመክፈት የሚጓጓ አለ?
የክልል የንግድ ቢሮዎች፣ የፌደራል የንግድ ሚኒስቴር፣ የሸማቾች ኤጀንሲ… ምናምን… ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ፣ የቢዝነስ ሰዎች ላይ የሚዝቱ፣ ከዛቻም አልፈው፣ የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን የሚያውጁ፣ የመንግስት አካላት ሞልተዋል።
አሁን አስቡት። እናንተ፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘብ ቢኖራችሁ፣ ምን ታደርጋላችሁ? የሳሙና ፋብሪካ ለመክፈት ትሞክራላችሁ? ወይስ የሳሙና ነጋዴ ለመሆን ትወስናላችሁ?
መንግስት፣ ካሁን በፊት እንዳደረገው፣ በማንኛውም ጊዜ፣ የሳሙና ዋጋ ላይ ቁጥጥር እንደሚያውጅና የዋጋ ተመን እንደሚያወጣ ታውቃላችሁ። ይህንን እያወቃችሁ፣ የሳሙና ፋብሪካ ለመክፈት ትደፍራላችሁ?
የሳሙና ንግድ ይሻላል። ስራው ቀለል ይላል። በዚያ ላይ፣ መንግስት የዋጋ ቁጥጥር ቢያውጅባችሁ፤ ብዙ ኪሳራ ሳይደርስባችሁ፣ የሳሙና ንግዳችሁን መተውና፣ ወደ ሌላ ንግድ መግባት ትችላላሁ። የሳሙና ፋብሪካ ግን፣ አስቸጋሪ ነው።
ከኪሳራ ማምለጫ አታገኙም። እና፤ ብዙ ሰው፣ ከፋብሪካ ቢዝነስ ይልቅ ወደ ንግድ ቢዝነስ ቢያተኩር ይገርማል?
በአጠቃላይ፣ መንግስት፣ በቅድሚያ ራሱን ለማስተካከል ይጣር። አደገኛው የድህነት አጣብቂኝ (ከአደገኛው የስራ አጥነትና የረሃብ አጣብቂኝ) መውጣት፣… ከዚያም ወደ ብልፅግና መራመድ የሚቻለው፣ በጭፍን የፕሮፓጋንዳ ባህል አይደለም። ቢዝነስንና ትርፋማነትን በሚያንቋሽሽ የውድቀት ጎዳና፣ ወደ ስኬት መጓዝ አይቻልም።

የኢትዮጵያ ድህነት፣ በጣም አደገኛ እንደሆነ፣ ለአፍታም ያህል ልንዘነጋው አይገባም ነበር። ግን፣ በተደጋጋሚ እየዘነጋነው፤ በአላስፈላጊ ንትርክና ግጭት ጊዜያችንን እናባክናለን።የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ያልተነቃነቀው፤ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ስለገነነና ቢዝነስን ስላቀጨጨ ነው። ሰዎች፤ ዘንድሮ ያለ እርዳታ አመቱን መዝለቅ የማይችሉ ረሃብተኛና ችግረኛ ኢትዮጵያዊያን፣ ከ18 ሚሊዮን በላይ ናቸው። ድርቅ በማይከሰትበትና ከፍተኛ የእርሻ ምርት በሚሰበሰብበት አመት እንኳ፣ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ ያለ እርዳታ ከአመት አመት መሻገር አይችሉም። የውጭ የእህል እርዳታ ባይኖርኮ፣ ሕዝብ ያልቅ ነበር። ከዚህ የከፋ አደጋና ውድቀት ምናለ?

በአነስተኛና ጥቃቅን፣ በየአመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የስራ እድል እየተፈጠረ ነው የሚባለው ወሬ ሃሰት መሆኑን… የአዲስ አድማስ ዘገባ መስከረም 2004 (‘የመንግስት ወከባ – ከፍርሃት የማያላቅቅ የህልም ሩጫ’ በሚል ርዕስ)
ኤክስፖርት መደንዘዙና አሳሳቢ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል። (“የስራ ፍሬውን ስንነጥቀው ይበረታታል” ብሎ መመኘት ሃጥያት ነው በሚል ርዕስ ታህሳስ 2006 ዓ.ም – አዲስ አድማስ)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s