እራስን ያለመሆን በሽታ! | አገሬ አዲስ

አንድ ሕዝብ ወይም ሰው የሚታወቅበት የራሱ የሆነ የማንነት መግለጫ ባህሪያት፣ታሪክ፣ባህል መልክ፣ቦታና ስም… ወዘተ አለው፡፤እነዚህን የመታወቂያ ገጾች ለሌሎች ሲል አሳልፎ የማይሰጠው ወይም የማይቀይረው እሴቶቹ ናቸው።ሌሎች ማንነቱን አክብረው  እንዲቀበሉት ማድረግ እንጂ ለሌሎች ሲል ማንነቱን ስሙን፣ባሕሉን፣ታሪኩን ለውጦና ቀይሮ መቅረብ በራሱ ላይ ቸንፈትንና ድክመትን አምኖ መቀበል፣በራስ አለመተማመን እንጂ ዘመናዊነትና ብስለት አይደለም።

Tensaye

ይህን አጭር ትችትና አስተያየት ለመሰንዘር የተገደድኩበት ዋናው ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በእኛ በኢትዮጵያውያን ጎልተው በመታየት ላይ ያሉ ድክመቶች እንዲታረሙና ወደማንነታችን እንድንመለስ፣በራሳችን እንድንኮራና እንድንተማመን የሚረዳ ሃሳብ ስለመሰለኝ ነው።

ከመግቢያው ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት እኛ ኢትዮጵያውያን በሌላው የዓለም ህብረተሰብ የምንታወቅበት ብዙ የሚያኮራ ታሪክና ባህል ሲኖረን አንዳንድ የምናፍርባቸው ግን ልናርማቸው የምንችላቸው ድክመቶችም አሉን።ከነዚህ ድክመቶቻችን ውስጥ ለውጭ ሃይሎች፣እምነቶች፣ ባህሎች፣ ልማዶች ፣ስያሜዎች መንበርከካችንና ማጎብደዳችመን ነው።

ሌላውን ብዥታ ወደጎን ትተን ትንሹንና አንዱን ፣ በስማችን ዙሪያ ያለውን ያለመሆን ችግር ነጥለን ብናይ ምን ያህል በራሳችን የምናፍርና የማንተማመን መሆናችንን ለመረዳት እንችላለን።

የሌላውን አገር ሕዝብ ከእኛው ሁኔታ ጋር ብናስተያየው ድክመታችንን ለማየት ይረዳናል።

በአሁኑ ጊዜ በእኛ በኢትዮጵያውያን በተለይም በአዲሱ ትውልድ የሚታየው እራስን ያለመሆን በሽታ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነው።ስምን ለውጦ የባዕድ አገር ስም መተካቱ እንደዘመናዊነት ወይም ስልጣኔ ተቆጥሮ የማንነት ውዥንብር ፈጥሯል።

በቅኝ ገዢዎች ወረራ ዘመን የተወራሪው አገር ዜጋ በተለይም ወጣት ወራሪዎቹ ለመጥራት እንዲመቻቸው በሚያወጡት  ስም እንዲጠራና እንዲቀበል እንደሚያስገድዱት  በሰባዎቹ መጨረሻ ላይ ዘ ሩት (The Root) የሚለው ፊልም ኪንታኩንቴ የሚባለው ወጣት አፍሪካዊ አገልጋይ የነጭ ጌታው ባወጣለት ቶቢ በሚልው ስም ለመጠራት አሻፈረኝ በማለቱ የደረሰበትን ስቃይ እንደምሳሌ መጥቀሱ ይበቃል።አሁንም የዚያ ውጤት በተለያዩ የቅኝ ግዛት በነበሩ አገሮች ዜጎች የስም ስያሜ ላይ ትልቅ ተጽእኖ እንዳሳደሩበት በገሃድ ይታያል።ተወላጁ ብቻ ሳይሆን መሬትና አገሩ ሳይቀር ነጮች በሚመቻቸው ስያሜ ይጠሩ እንደነበረና አሁንም እንደሚጠሩ እናውቃለን።አንዳንዶቹ አገሮችም ተነጥቀው የነበረውን የማንነትና አገር ስያሜ እያስመለሱ፣ከሰፈረባቸው የቅኝ ግዛት ተጽእኖ ለመላቀቅ ሞክረዋል።በመሞከርም ላይ ናቸው።ለምሳሌ ሮዴዚያ፣በዚምባብዌ፣ዳሆሜ በቤኒን…ወዘተ እየተተካ መጥቷል።

ኢትዮጵያውያን ግን የቀድሞ አባቶቻችን  ምስጋና ይድረሳቸውና ለዚህ ግዳጅ የተጋለጡ አልነበሩም፤እኛንም አላጋለጡንም።ለወራሪዎች ባለመንበርከካቸው አገራቸውን አሳልፈው አልሰጡም፤በዚያም ምክንያት ታሪክና ባህላቸውን፣ማንነታቸውን ሳያስደፍሩ ቆይተዋል።

ያ በአባቶቻችን ተከብሮ የቆየ የማንነት ስያሜ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ብለን ብንጠይቅ መልሱ የሚያሳፍር ሆኖ እናገኘዋለን።

በአገራችን ልማድ አንድ ልጅ ሲወለድ ስም የሚወጣለት፣ደስታን፣ተስፋን፣ምኞትን የሚያንጸባርቅ ወይም የነበሩበትን ሁኔታ የሚያስታውስ ትርጉም ያለው አጠራር ነበር።የአንዳንድ አገር ሕዝብም ለልጁ የሚያወጣው ስም ቋንቋው ቢለይም ከዚህ አይነቱ ስሜት እንደሆነ መገመት ይቻላል።የልጁን ስም ለሌላው ዜጋ ለአጠራር እንዲመችና እንዲቀለው ብሎ በማሰብ ብቻ ወይም የራሱን አሰያየም በመናቅና በመጥላት የሌላውን አገር ዜጋ የስም  አወጣጥ ካልተገደደ በቀር ወዶ የሚቀበል የለም።በእድገት የመጠቁ አገሮች እንደ ጃፓን፣ቻይና፣ሩስያ፣ህንድ…ወዘተ ያሉትን አገሮች የስም አወጣጥ ብናይ አንዱ የማንነታቸው መግለጫ በመሆኑ ከጊዜው ጋር እየቀያየሩ አለመምጣታቸውን እንገነዘባለን።ስማቸው ብቻ ሳይሆን አለባበሳቸው፣አመጋገባቸው፣ አነጋገራቸው ሳይቀር ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ማንነታቸውን የሚያንጸባርቅ ነው።እዚህ ላይ የሚታረመው አልታረመም ማለት አይደለም፣እንደአስፈላጊነቱ መሰረቱን ሳይለቅ የተሻሻለ አቀራረብ ጨምረውበታል፤ያም ተገቢና አስፈላጊ ነው።

ወደእኛ መለስ ብለን ውስጣችንን ብንመረምር፣ኢትዮጵያውያን ከመሆን እያፈገፈግን የመጣን መሆናችንን እንረዳለን፤በፖለቲካው ዙሪያ ወይም በጎሳው መነጽር ለሚታዩት ድክመቶች መነሻ  በራስ አለመተማመንና እራስን ያለመሆን በሽታ ነው።እራስን መሆን ደግሞ ስም፣ባህልንና እምነትን ጠቅልሎ የያዘ ማንነት ነው።

በአገራችን ከሃምሳ ዓመት ወዲህ ያቆጠቆጠው እራስን ያለመሆንና የመጥላት በሽታ አሁን ከሚታይበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።ወላጅ ልጅ ሲወልድ የሚሰጠው ስም እንደቀድሞው ማንነትን ፣ኢትዮጵያዊነትን፣እምነትን፣ተስፋን፣ምኞትን የሚያንጸባርቅ ሳይሆን ከውጭ አገር የስም አሰያየም፣ክርስቲያኑ ከይሁዲ፣እስላሙ ከሙስሊም አገሮችና ሕዝቦች ጋር ያለውን ትስስር የሚያጎላና የሚያጠናክር ሆኖ ይታያል።አብዛኛው ወጣትም እናትና አባቱ፣ያወጡለትን ትርጉመ ሰፊና ብዙ የሆነውን ስሙን  በማይናገረው ቋንቋ፣በውጭ አገር በተለያም በፈረንጆቹ አጠራር  ዩሃንስ በጆኒ፣ሙሉጌታ በሙለር፣ጎሳዬ በጎሲ፣ታደለ በቴዲ፣እመቤት በኤሚ፣ጃክሶ በጃኪ፣እጅግ አየሁ በጂጂ…ወዘተ እየለወጠ ወዶና ፈቅዶ ጥገኛ ለመሆን ሲወስን ይታያል።ለምን ቢባል ኢትዮጵያዊ ያልሆነው ለመጥራት እንዲመቸው ነው ይባላል።ያ ለመጥራት እንዲመቸው የሚታሰብለት የውጭ አገር ዜጋ ግን ኢትዮጵያዊያን ለመጥራት እንዲመቻቸው ብሎ ስሙን አልቀየረላቸውም።

አንድ ገጠመኝን ላካፍላችሁና ልደምድም

የልጅነት አብሮ አደግ ጓደኛዬ ጋር ከተለያየን ብዙ ዘመናት አልፈዋል፤የት ደርሶ ይሆን? እያልኩ ሳስብ ቈይቻለሁ።የዃላ ዃላ ወደውጭ አገር፣ወደ አሜሪካ መውጣቱንና ያለበትን ከተማ ለማወቅ ቻልኩ።በጣም ደስታ ተሰማኝ ፤ለመገናኘት በሚኖርበት አካባቢ የሚኖሩትን የማውቃቸውን ኢትዮጵያውያን  አድራሻውን እንዲሰጡኝ ወይም የእኔን እንዲሰጡት  ጥያቄ አቀረብኩ ግን ያቀረብኩላቸው ጥያቄ  ሳይሳካ ቀረ።ስሙ ብርሃኑ ነበር ፣በብርሃኑ ብዙ ተሞከረ፣ግን አቤት የሚል ብርሃኑ ጠፋ።ከዓመታት ሙከራ በዃላ በሰሜን አሜሪካው የኢትዮጵያውያን የስፖርት በዓል ዝግጅት አጋጣሚ ሆነና ከምፈልገው የልጅነት ጓደኛዬ እኔ በብርሃኑ ደምሴ የማውቀው ቤሪ ዴምስ ተብሎ አገኘሁት።ይህን ተለጣፊ ስሙን ግን እናትና አባቱ በአገር ቤት የሚኖሩት ዘመዶቹ በተለይም ገጠር የሚኖሩት ሳያውቁትና ሳይጠሩበት እስከአሁን እኔ በማውቀው ስሙ በብርሃኑ ደምሴነቱ እየጠሩት ይኖራሉ።ለፈረንጆቹ እንዲቀል ብሎ ያወጣው ስሙ ለቤተሰቡ አልተመቸም።እንደውም እንዴት ያወጣንለትን ስም ይቀይራል፣ምን  ነካው?ታሞ ነው በጤናው በማለት በተለይም ወላጅ አባቱ ምርር ብለው ማዘናቸውን ተረድቻለሁ።

ያገሬ ልጆች ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ለትንሽ ጥቅም፣ብላችሁ እራሳችሁን አትጥሉ፣በማንነታችሁ አትፈሩ፣እራሳችሁን አክብራችሁ አስከብሩ፣ስማችሁን፣ማንነታችሁን ፣ታሪካችሁን ለማስከበር ጠበቃ ሁናችሁ ቁሙ፤በወዶገባ፣ወይም በፈቃዳችሁ ማንነታችሁን አትካዱ።ስማችሁና ኢትዮጵያዊነታችሁ የማንነታችሁ ምልክት ተስፋ፣ምኞት ፍቅር ገላጭ የሆነ ባለብዙ ትርጉም ያለው ነው።እድገትና ስልጣኔ ስም በመለወጥ ሳይሆን እራስን በእውቀት መለወጥ ሲቻል ነው።ጎጅውን ባህል፣የመለያየትንና የጥላቻን መንፈስ፣እራስ ወዳድነትንና ቂም በቀልን ለማሶገድ መጣርና መወዳደር ተገቢ ነው።ከሌላው አገር ዜጋ ጋር መደረግ ያለበት ውድድር በችሎታ ዙሪያ እንጂ የራስን መታወቂያ ቀዶ በመጣልና የተውሶ ማንነትን ወይም እነሱ የሚፈልጉትን በመቀበል አይደለም።ሌላው ዜጋ ስማችሁን ለውጦ ቢጠራችሁ እንኳን አትቀበሉት፣በትክክለኛ ስማችሁ እንዲጠራችሁ አሳስቡት።እናንተ የውጩን ዜጋ በስሙ እንደምትጠሩት ሁሉ፣እናንተም በኢትዮጵያዊው ስማችሁ ለመጥራት ስታስገድዱት አስተካክሎ እንደሚጠራችሁ እመኑ።እራስን መሆንና በራስ መተማመን ከዚህ ይጀመራል።አገራችሁንም በሚያዳክምና በሚነጣጥል መልኩ፣ ማንነታችሁ በክልል አጥር ውስጥ ተወስኖ እንዲቀር ሲደረግ አትቀበሉ።ትልቅነታቸሁን በትንሽነት አትለውጡት።

ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ለዘላለም ይኑሩ!!

 

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s