የጭቆናው ምክንያት አንባገነናዊ ሥርዓት ወይንስ የብሄር  ልዩነት | ይገረም አለሙ

Share

ወያኔ በተናጠልም ሆነ በቡድን  በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸውን  ድርጊቶች አስመልክቶ  የበደሉ ተጠቂዎችም ሆኑ ለተጠቁት ድምጽ የሚያሰሙ ወገኖች  በደሉ የተፈጸመው  አማራ ስለሆን/ኑ ነው ኦሮሞ ስለሆን/ኑ ነው ወዘተ በማለት በደሉን በብሄራቸው ምክንያት  የተፈጸመ አድርገው  ሲገልጹ ይሰማል፡፡ የሚፈጸሙት የግፍ ድርጊቶች  በተጠቂዎቹ ላይ የሚፈጥሩት ስሜት እንዲህ ሊያናግሩ ይችላሉ፡፡ በምክንያት ወደ ውጤት የሚጓዙ ሳይሆን በስሜት ህዝብ ማነሳሳት ላይ ለሚያተኩሩ ወገኖችም  ይህ አገላለጽ ቀላል መሳሪያ ነው፡፡ ዜጎች በብሄራቸው አስተሳሰብ ታጥረው የእርስ በርስ ልዩነታቸው ሲሰፋ ተጠቃሚ የሚሆኑ ወገኖችም  ይህን አገላለጽ ይፈልጉታል፤ያራቡታል፡፡ ነገር ግን ሰከን ብለን ካየነው አገላለጹ የነገሩን ትክክለኛ ገጽታ የሚያሳይ  ለመፍትሄም የሚበጅ አይደለም፡፡

tekawemo

ጠለቅ ያለ  መመርመር ሳያስፈልግ በቅርብ ያሉና በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን ብቻ በጥሞና መመልከት ብንችል እኔ ወይንም አኛ እንዲህ የሆነው ይሄ ይሄ በደል የተፈጸመብን በብሄራችን ምክንያት ነው ( አማራ ኦሮሞ ጉራጌ ወዘተ በመሆናችን ነው) ሲባል ይህ በደል ያልነካቸው  የብሄሩ አባላትን መዘንጋት ይሆናል፡፡ የጥቃቱ መነሻ ምክንያቱም ሆነ መድረሻ ግቡ ብሄር ተኮር ከሆነ ከተዘመተበት ብር መካከል መስፈርት እያወጣ የሚመርጠው አይኖርም፡፡ በእኛ ዘንድ የሚታየው አጥቂዎቹም ተጠቂዎቹም ከሁሉም ብሄር መሆናቸው ነው፡፡

ከየብሄሩ ከወያኔ በላይ ወያኔ ለመሆን የሚዳዳቸውና በብሄራቸው አባላት ላይ በደል የሚፈጽሙ፤በእኔ ካልደረሰ በማለት ካለው  ተስማምተው የሚኖሩ፤ጎመን በጤና ብለው ህሊናቸው እየቆሰለ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል አይነት የሚኖሩ ወዘተ ብዙ አጅግ ብዙ አሉ፡፡ ታዲያ የተበደልነው  አማራ/ኦሮሞ ወዘተ በመሆናችን  ነው ብለን ጅምላ ካደረግነው  የእነዚህ ወገኖች ጉዳይ  ምን ሊባል ነው፡፡ መቼም የብሄር ማንነነታቸውን መካድም መንሳትም አይቻልም፡፡ በመሆኑም ይህን ብቻ በማየት የበደል ጥቃቱ መሰረተ ምክንያት   የብሄረሰብ ማንነት  ሳይሆን የገዢዎች ጸረ ዴሞክራሲያዊነትና  የተጠቂው ዴሞክራሲ ናፋቂነት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ስለዚህ የበደሉ ምክንያት የዚህ ወይንም የዛኛው ብሄረሰብ አባል መሆን ሳይሆን  እኔ ሰው  ነኝ ማለት  ነው፤  እኔ ሰው ነኝ የሚል ሰው  ሎሌነትን  ይጸየፋል ፤ ነጻነቱን ይሻል፤ በጠመንጃ ሳይሆን በህግ መተዳደርን ይፈልጋል፤ በድምጹ የሚመርጠውን መንግሥት ማየት ወዘተ ይመኛል፡፡ እነዚህ ሁሉ  ቢሟሉ ደግሞ  አንባገነኖች በሥልጣን ላይ ውለው ማደር አንደማይችሉ ስለሚያውቁ  ተግባራዊ አየደርጓቸውም፡፡ እንደውም ሰው ነኝ የሚል ሰው የሚያቀርባቸው ጥያቄዎቸም ሆኑ ምኞት ፍላጎቶች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መሆናቸው ይቀርና  የስልጣን ጥያቄ ተደርገው በአንባገነኖች እየተተረጎሙ  ለጥቃት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ሁሉም ዜጋ እኔ ሰው ነኝ ማለቱንና ሰው በመሆኑ ሊኖሩት የሚገቡትን መብቶቹን  ትቶና ረስቶ አቤት ወዴት ብሎ ቢያድር ወያኔን ከነምናምኑ ተቀብሎ ቢኖር  የሚፈጸም ጥቃት ቀርቶ በደል አይኖርም፡፡ ስለሆነም እንግዲህ በዜጎችና በገዢዎች መካከል ያለው  መሰረታዊ ልዩነትም ሆነ  የጥቃት በደሉ ምክንያት የብሄር ማንነት ሳይሆን አንበገነናዊ አገዛዝ  ነው ማለት ይቻላል፡

ከላይ በተገለጸው የዜጎችና የአንባገነኖች መሰረታዊ ልዩነትና የበደል ጥቃት ምክንያት መስማማት ከቻልን የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ሊኖረው የሚገባው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች  በብሄረሰብ ልዩነት ምክንያት የሚለያዩ አይደሉም፡፡ አንዱ ብሄረሰብ ከሌላው ተለይቶ ለእኔ ብቻ የሚገባኝ ብሎ ሊያነሳቸው የሚችሉ ጥያቄዎችም ሆኑ የሚሻቸው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያሉ አይመስለኝም፡፡ሰለሆነም ልዩነቱ አንባገነንነትና አልገዛም ባይነት ነው፡፡መፍትሄው ደግሞ የአንባገነኖችን በደል በብሄረስብ እየሸነሸንን የየራሳችንን መልክና ቅርጽ እየሰጠን ከመከፋፈል ተላቀን  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት መቻል ነው፡፡

ኢትዮጵያችንን በዴሞክራሲያዊ ጽኑ መሰረት ላይ የቆመ መንግስት ባለቤት ማድረግ ቢቻል  የሁሉም  ልጆቿ የሰው ልጆች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚኖራቸው  ከልካይ አንጂ ሰጪ  የሌለው  መብታቸው፣ የዜግነት ክብራቸው፣የብሄር ማንነታቸው፣ እምነት አመለካከታቸው ወዘተ በእኩልነት የረጋገጣል፡፡ እነዚህ መብቶች ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ አባል በመሆን አለመሆን በመደገፍ በመቃወም ወዘተ ልዩነት ሳይደረግ በህዝብ ንቁ ተሳትፎና ይሁንታ ተግባራዊ የሚሆነውን ህገ መንግሥት አክብረው ለሚኖሩ ዜጎች ሁሉ በእኩል ተፈጻሚ ስለሚሆኑ በዜጎችና በመንግሥት መካከል የሚፈጠር መሰራታዊ ልዩነት አይኖርም፡፡ አበው ሰው በሀገሩ ቢበላ ሳር ቢበላ መቅመቆ ይከበር የለም ውይ ሰውነቱ ታውቆ ይሉት የነበረውም ያኔ እውን ይሆናል፡፡

አንድ ሁለት ተጨባጭ ጉዳዮቸን በመጠኑ አንመልከት

አማራው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሀገሬ ብሎ ሲኖር ለጥቃት ተጋልጧል በክልሉም በወያኔ ጥቃት እየደረሰበት ነው ስለዚህ መደራጀት አለበት ሲባል አንሰማለን፡ የተደራጁም አሉ፡፡በተለያዩ ክልሎች ይኖሩ በነበሩ ወገኖቻችን ላይ ጥቃት የተፈጸመው አማራ በመሆናቸው ነው ብሎ ለመቀበል የሚቸግረው እነዚህ ወገኖቻችን በዛ አካባቢ መኖር የጀመሩት ከብዙ አመታት በፊት በመሆኑ ጉዳዩ አማራነታቸው ከሆነ እስከ ዛሬ አንዴት በሰላም ኖሩ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው፡፡ መኖር ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ከሚኖሩ ሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ተጋብተዋል ተዋልደዋል በተለያዩ ማህበራዊ ግንኑነቶች ተሳስረዋል፡፡

ስለሆነም ነገሩን በወገኖቻችን ለይ የደረሰው በደል ከፈጠረብን ስሜት ሰከን ብለን ካየነው ችግሩ አማራነታቸው ሳይሆን የአንባገነኖች እርስ በእርስ እያጋጩ የሥልጣን ዘመንን የማራዘም እኩይ ሴራ ውጤት ነው፡፡  እነዚህ ወገኖች እኔ ሰው ነኝ ሳይሉ ተገዢነትን አሜን ብለው በወያኔ አገልጋዮች በኩል ለወያኔ እየገበሩ መስለው ተመሳስለው ቢኖሩ እንደማይነኩ ይገመታል፡፡ ስለሆነም ችግሩ የተፈጠረው በአማራነታችን/ቸው ነው ሲባል ይህን የወያኔ እኩይ ተግባር ማለምለም ይሆናል፡፡

አማራው በሚኖርበት ክልልም እየተበደለ መሆኑ አነጋጋሪ አይደለም፡፡ ይህም  አንደኛ ከላይ ለማየት አንደተሞከረው እኔ ሰው ነኝ በሚሉት ላይ አንጂ በሁሉም አማራ ላይ ባለመሆኑ፤ በወያኔ አገዛዝ ስር ባሉ ሁሉም ክልሎች የሚፈጸም በመሆኑ  እንዲሁም የበደሉ ፈጻሚዎች የወያኔ አገልጋይ አማሮች በመሆናቸው የበደሉ ምክንያት አማራነት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡

በኦሮሞዎችም ላይ የሚፈጸመው በደል የዚሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለሰሞነኛው ያላባራው ተቃውሞ ምክንያት የሆነውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ብንመለከት ኦሮሞን ለማፈናቀል ባህሉን ቋንቋውን ላማጥፋት በኦሮሞ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው የሚለው ትክክል አይመስለኝም፡ ምክንያቱም አንደኛ  አጋጣሚ ሆኖ አዲስ አበባ በኦሮምያ ክልል መገኘቷ አንጂ በአንድ ወይንም ከዛ በላይ በሆነ አቅጣጫ ሌላ ተጎራባች ክልል ቢኖር ማስተር ፕላኑ ሁሉንም ነበር የሚነካው፤ ስለሆነም ጉዳዩ  የወያኔ የመስፋፋትና መሬት የመቀራመት  እንጂ በተለየ ኦሮሞን የማጥቃት አይደለም፡፡ ሁለተኛም  እስካሁን በአዲስ አበባም ሆነ በአካባቢው  የተፈጸመው ማፈናቀል የቦታውን መፈለግ አንጂ በቦታው ላይ  የሚገኙ ዜጎችን ብሄረሰብ ማንነት መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ በሶስተኛ ደረጃም የድርጊቱ ዋና አስፈጻሚዎች ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ኦሮሞ በኦሮሞ ላይ የሚፈጽመው ጥቃት ብሄርን ምክንያት ያደረገ ሊባል አይችልም፡፡

ስለሆነም የችግሩ  ምንነትም  ሆነ የጥቃቱ ምክንያት አንበገነናዊ ሥርአት አንጂ የተጠቂዎች ብሄር ማንነት አይደለም፡፡ መፍትሄውም ጥቃቱን በየብሄር እየለያዩ መለያየት ሳይሆን በጋራ ትግል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መብቃት ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s