እባካችሁን ከባንዲራው ታረቁ – ታምራት ነገራ

12376792_558136384350717_6634417347526598899_n

ለውድ ወያኔ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

የእስከአሁኑ ጉዞአችሁ በየትኛውም አጋጣሚ ከኢትዮጵያ ብሔርተኞች የሚመጣውን ማንኛውንም ምክር በጥሞና እንደምትሰሙ አያሳይም፡፡ ምክር ስንሰጣችሁ ፤ ምክሩን ከሰማችሁም በኋላ ከምክሩ የሚጠቅመውን እና የሚጎዳውን ሃሳብ ለመለየት አንደምትጥሩ፤ ይጠቅማል እና ይጎዳል ብላችሁ የለያችሁትን ሃሳብም መልሳችሁ ከኢትዮጵያ ብሔርተኞቸ ጋር እንደምትወያይዩበት የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም፡፡
ይልቁንም ያለው መረጃ የሚያሳየው ከቀን ወደቀን የኢትጵያ ብሔርተኞችን ድምጽ ከየትኛውም ድምጽ እንደምትጸየፉ ነው፡፡ የኢትዮጵያን መንበር ከተቆነጣጣችሁበት ቀን ጀምሮ እኛ የኢትዮጵያ ብሔርተኞች ስልጣን መያዛችሁ ካልቀረ ኢትዮጵያን እና ሆነ የአፍሪካ ቀንድን ከእናንተ ቀድመን እንደማቅናታችን፤ ያለንን ልምድ እና እውቀት ለማካፈል አልታከትንም፡፡
በእኛ እና በእናንት መካከል ያለው የፖለቲካ ልዩነት እኛ ለአገራችን ለባንዲራችን፤ ለሉአላዊነታችን፤ ለአንድነታችን እና ለዳርድንበራችን ክብር ካለብን ተጠያቂነት ስለማይበልጥብን ከእናንተ ጋር ያለንን ልዩነት ሁሉ ችላ ብለን አብረናችሁ ልንሰራ ፈቃደኛነታችን ሁሌም ከመግለጽ ተቆጥበን አናውቅም፡፡
ይህን ትናንት ያደረግነውም ሆነ ዛሬም የምናደርገው አሽከር መሆን ስለምንመርጥ፤ አንገታችንን አይደለም በኩራት በእብሪት ቀና አድርጎ የሚስኬድ አከርካሪ ስለሌለን አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ሲሆን የምንሳሳው ምንም ነገር ስለሌለን እንደሆነ እናንተም ጠላቶቻችንም ያውቃሉ፡፡ የሚኒሊክን ክቡር እና ምርጥ መንበር ስትቆናጠጡ የሽንፈት ቁስላችን ደሙ ሳይደርቅ ነበር ከሱዳን ፤ ኤርትራ እና የተለያዩ ፀረ ኢትዮጵያ አገራት ጋር የያዛችሁት ግኑኝነት እንደማያዛልቅ ማስጠንቀቂያ የሰጠነው፡፡

አያያዛችሁ ኢትዮጵያን ለመሰለ በሺ ዓመታት የሚቆጠር የተገለፀ፤ የብሔራዊ ደሕንነት ፍላጎት፤ ጥቅም፤ እውቀት እና ልምድ ላላት አገር የማይመትን የማይጠቅም እና የማያዛልቅ እንደሆነ ከላይ ከታች የጮኅነው፡፡ በአዲስ መልክ ቆራርሳችሁ የቀረፃችሁት የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ምንኛ ቢያሳዝነን የእናንተ ስልጣን እነደተጠበቀ፤ ከነሽንፈታችን ፤አንገታችን ደፍተን የእናንተን የበላይነት ሳንቀናነቅ፤ አዲሱን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመጠበቅ እንድተፈቅዱልን ከማንም ቀድመን ወደ ምድብ ዘባችን እንድትመልሱን ማመልከቻ ያስገባነው እኛ እንደሆንን የተመዘገበ ማስረጃ በአደባባይ አለ፡፡
ከዚህ ይልቅ የሰጣችሁን መልስ እስርቤት እና መበታተን እና መባረር ነበር፡፡ አብሮ አደጋችሁ ሻቢያ ቀን ጠብቆ ጦርነት ሲያውጅ የተማመነው አንድ ነገር ነበር፡፡ እኛ ዳር ቆመን እንደምና፡፡ የተወረረው ትግራይ ነው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለም ብለን ጥግ የምንቆም የመሰለውን ሁሉ በሚያሳፍር መልኩ ትዳራችን በትነን ለዳርድንበራችን እንደገና መጣን፡፡

ከውጊያው በኋላ ለኢትዮጵያ ብሔርተኞች ውለታ የሰጣችሁት ምላሽ ምን ያህል አሳፋሪ እንደነበር እንደገና ማንሳት አያስፈልግም፡፡ ጥሎብን ኢትዮጵያን የምንወዳት ለምትከፍለን ውለታ አይደለም፡፡ ተረግመን ይሁን ተባርከን ለዳርድንበር የምንሰለፈው የደሞዙን መጠን አይተን አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ያለን ታማኝነት ከምን እነደሚመነጭ ፤ የአገር ነገር እንዲህ ለምን እንደሚያንዘረዝረን አይደለም ለእናንተ ለእኛ ለእራሳችን በቂ እና አሳማኝ ምክንያት የለንም፡፡
በዚህ አላበቃችሁም፡፡ ከዘውድ ዘመን ጀምሮ ከአገሪቷ ጥጋ ጥግ በቆላ ሆነ በደጋ ይሄ ነው የሚባል የጡረታ መብትም ሆነ ለልጅ እንኳን የማይወረስ ደሞዝ እየተሰጠው አገሩን ሲያገለገል የነበረውን አገር ወዳድ መምር ሆነ፤ መሃንዲስ፤ ሹፌር ሆነ ተራ የቢሮ ፀሀፊ አንድ በአንድ አፈናቀላችሁት፡፡ ሲቪል ሰርቪሱን አገሩን በሚወደው ሳይሆን በሆዳሙ እና በ መንደሬ ብሔርተኛው አጨቃችሁት፡፡
ለነገሩ ይሄ አሰራራችሁ የመነጨው ኢትዮጵያን ከአንድ አገርነት ወደ ትናንሽ ብሔሮች፤ ህዝብ፤ ጎበዞች፤ ጋጦች ምናምን ስብስብ ካዘቀጣት ህገመንግስት እንጂ በድንገት ከሰማይ አልወረደም፡፡ ኢትዮጵያን እንዲህ ከፋፍሎ ማስቀመጥ እና ዜጎችን እርስ በእርስ ማጣለት ለኢትዮጵያ ዘላቂነት እነደማይከጅል ከመጀመሪያው አሳሰብን፡፡ እሱ ባይታያችሁ ለገዛ ስልጣናችሁ ዘላቂነት እንደማያዋጣ መከርን፡፡ መልሳችሁ አሁንም ብስለት የታየበት ሳሆን አሳፋሪ ነበር፡፡
እናንተ አዲስ አበባ ስትገቡ ዳዴ ይሉ የነበሩ ልጆችን እናንተን የሚጠቅም መስሏችሁ በተገቢው የኢትዮጵያዊነት ሲቪክ ሃሳብ ሳሆን በትንንሽ መንደሬነት ኮትኩታችሁ አሳደጋችኋቸው፡፡ ይሄው የዘራችሁት ለምልሞ መጣ፡፡ በኮተኮታችሁት ጠባብነት ከምድር ከሰማይ የዘረፋችሁትን እንኳን በሰላም የማትበሉበት ቀን ከተፍ አለ፡፡
እኛ የኢትዮጵያ ብሔርተኞች አሁንም አገሪቷ ላይ የተጋረጠውን አደጋ እንደቀልድ አናየውም፡፡ አሁንም ከእናንተ ጋር ካለን ቅራኔ ይልቅ ለአገራችን ያለን ፍቅር እና ታማኝነት ሺ ቢሊዮን እጥፍ ይንተገተጋል፡፡ ይህ ትንታግ ኃይል ዛሬም በመቅጽፈት ኢትዮጵያን ከማንኛውም አደጋ ለመታደግ ዝግጁ ነው፡፡
ይህን አገልግሎታችን ለማቅረብ ስልጣናችሁን አንጠይቅም፡፡ ከእናንተ ጋርም ሆነ ለእናንተ ለማገልገል ከዘረፋችሁትም ሆነ ነገ ከምትዘርፉት 5 ሳንቲም አንጠይቅም፡፡ አገልግሎታችን ነፃ ነው ማለት ፍላጎት የለንም ማለት ግን አይደለም፡፡ ፍላጎታችን በአንድ ቃል ሊጠቃለል ይችላል፡፡ ከባንዲራው ጋር ታረቁ፡፡ በቃ!!

ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር በያዛችሁት ውሸታም የባንዲራ ቀን መሰል ቀልድ ሳይሆ እውነተኛ ተሃድሶ መልክ ስትታረቁ የእኛን አካል ብቻ ሳይሆን ነብሳችን ታገኙታላችሁ፡፡ ከባንዲራው ጋር መታረቃችሁን በቲቪ አውጃችሁ ሳይሆን በተግባር መታየት ይጀምራል፡፡ ቢያንስ በእነዚህ በሚከተሉት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ከእኛ ጋር በተገቢው መልኩ በይፋ መነጋገር እና መግባባት ትጀምራላችሁ፡፡

የዳር ድንበራችን ነገር

ከሱዳን እና ኤርትራ ጋር በዳር ደንበራችን ላይ የምታደርጉትን ሽንሸና አሁኑኑ ታቆማላችሁ፡፡ የሄደው ሄዷል የቀረውን እንዴት እናርግ የሚባልም ከሆነ የትኛውን ለዛሬ የትኛውን ለነገ እነደምናሳድር እንነጋገር፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች ነገር
ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው መናገራቸው፤ ተገቢ መጠን ያለው ቋንቋ የፌደራል ቋንቋ መሆኑ፤ ብሄሮች የፈለጉትን ልብስ መልበሳቸው፤ በፈለጋቸው ቀን እና ስፍራ መጨፈራቸው፤ ማጓራታቸው ፤ መዝለላቸው እናም ሌላም ሌላም ባህላቸው የሚያዛቸውን ነገር ማድረጋቸው ከፍቶን አያውቅም፡፡ የእናንተን ዘመን ልዩ የሚያደርገው አስራ ሁለት የማይሞሉትም ሆነ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩት አገር የመሆን ምኞት ከነ መዋቅሩ፤ ባዲራው፤ ሰራዊቱ አስረክቦ ጥግ ቆሞ ማየቱ ላይ ነው፡፡
ይህን ውሸታም እና እርባና ትዕቢት በህገመንግስት ፤ በክልሎች አወቃቀር፤ በትምህርት ፖሊሲ፤ በበጀት ሁሉ አጅባችሁ ያሳደጋችሁት እናንተ እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ አሁንም የምታሳዩት እርምጃ ለጥያቄው በተገቢው መንገድ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መልሶችን መስጠት ሳይሆን እሳቱን የበለጠ በሚያፋፍም ጭፍን ግድያ ብቻ ነው፡፡

ከላይ ባቀረብናቸው ጉዳዮች ከእኛ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኞች ሁኑ እንጂ አገሪቷን በጦርነትም፤ በጭፍጨፋም፤ በንግድም ፤ በጋብቻም በጭንገረድም በገበያም በጠላም፤ በጠጅም ያቀናናት እና የሰፋናት እኛው ነን እና ማን ላይ የትጋር እንዴት ምን አይነት እርምጃ እንደምትወስዱ እንደ አባይ ከረዘመው ታሪካችን እናጫውታችኋለን፡፡
እነደገና ይህን ምክር ሌላው ቢቀር የዘረፋችሁትን በሰላም የምትበሉበት እና በመቀጠልም የምትዘርፉት አገር እንዲኖራችሁ ስትሉ እንኳን አድምጡት፡፡ ውድ የአገር ልጅ ጥልሽ እንዳለው

ሳቅ ፈገግታ ደስታ ሁሌ የምናየው፤ ሀገር በነፃነት ኮርታ ስትኖር ነው
ጥሩ ልብስ ለብሰን፤ አምሮብን ተውበን የምንታየው
ሰዎች እንረዳ ቢገባን ትርጉሙ ሁሉም ባገር ነው

እና አንደገና እላለሁ ከባንዲራው ታረቁ፡፡ ከባንዲራው ከታረቃችሁ ሌላው ሁሉ ተከታይ እና ዝርዝር ነው፡፡

አሜን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: