(ሳተናው) በዝዋይ ወህኒ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በኩላሊት ህመም በመሰቃየት ላይ የሚገኝ ቢሆንም የወህኒ ቤቱ አስተዳደር
ህክምና እንዳያገኝ ማድረጉን ውብሸት ሊጎበኙት ለሄዱ ወዳጆቹ ተናግሯል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት የጸረ ሽብር አዋጁ ተጠቅሶበት ለእስር የተዳረገው ውብሸት 14 ዓመት ተፈርዶበት በዝዋይ ወህኒ ቤት የእስር ጊዜውን እያሳለፈ ይገኛል፡፡
በወህኒ ቤቱ ለታሳሪዎች የሚቀርበው የመጠጥ ውሃ ንጽህናው ያልተጠበቀ በመሆኑም ብዛት ያላቸው እስረኞች ለኩላሊት ህመም እንደሚዳረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ውብሸት ወደዝዋይ ከመውረዱ በፊት የኩላሊት ህመም እንደማያውቀው የሚናገሩ የቅርብ ሰዎቹም ህመሙን ከወህኒ ቤቱ ማግኘቱን ይገልጻሉ፡፡
በዝዋይ ወህኒ ቤት ለእስረኞች የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ለመስጠት የተቋቋመ ክሊኒክ ቢኖርም የክሊኒኩ ሰራተኞች ለሁሉም አይነት በሽታዎች ፓራሲታሞል የሚያዙ በመሆናቸው ለጋዜጠኛው የኩላሊት ህመምም ፓራሲታሞል ማዘዛቸው ታውቋል፡፡
ውብሸት ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ በክሊኒኩ ሪፈር ተጽፎለት የነበረ ቢሆንም የወህኒ ቤቱ ኃላፊዎች መኪና የለንም በማለት ለወራት ለስቃይ ዳርገውታል፡፡ውብሸት በመጨረሻ ወደ አዲስ አበባ ቂሊንጦና ቃሊቲ ወህኒ ቤቶች ቢያመራም ወህኒ ቤቶቹ ህክምናውን ሳያገኝ ወደ ዝዋይ እንዲመለስ አድርገውታል፡፡
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በዝዋይ የሚገኙትን ጋዜጠኞች ተመስገን ደሳለኝንና ውብሸት ታዬን ለመጎብኘት ወደስፍራው ባመሩበት ወቅት የፓርቲው አመራሮች ተመስገንን ለመጠየቅ ባይፈቀድላቸውም ውብሸትን ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
ውብሸት ለቀድሞዎቹ የአንድነት አመራሮች ‹‹በኩላሊት ህመም እየተሰቃየሁ ቢሆንም ህክምና እንዳላገኝ ተደርጊያለሁ›› ማለቱን የፓርቲው የህዝብ ግኑኝነት የነበረው አቶ አስራት አብርሃም በማህበራዊ ድረ ገጹ አስፍሯል፡፡