ማንንም የማይፈራው እውሩ መንግሥታችን!!! (ዲባባ ዘለቀ)

ማኅበረ ቅዱሳን “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ለ 1 ሳምንት ለማሳየት ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ ለዕይታ ለመቅረብ ሰዓታት ሲቀሩት “ባልታወቀ አካል” ቀጭን ትዕዛዝ መታገዱን በዘመኑ ፈጣን የመገናኛ መንገዶች ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም ተሰምቷል። በእርግጥም የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር የቤተ ክርስቲያኒቱን ገጽታ በሚገባ ለማሳየት፣ ርትዕት የሆነውን ትምህርተ ሃይማኖቷን በሚገባ ለመግለጥ፣ እንዲሁም ምእመናን ሌሎችን ወቃሽ ብቻ ሳይሆኑ ከቤተ ክርስቲያን ባገኙት የልጅነት ጸጋ እንዴት ማገልገል እንደሚችሉ ለማመላከት ይቻል ዘንድ ሌት ተቀን ደክመው ያዘጋጁት መርሐ ግብር በድንገት ሲሰረዝ እንኳን ለአዘጋጆቹ ለማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ምእመን አሳዛኝ ነው። ዓላማው በመሪ ቃሉ ላይ እንደተመለከተው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በአግባቡ መግለጥና የምእመናንን ድርሻ ማሳወቅ በመሆኑም ይህ እንዳይሆን የሚፈልግን/የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን በቂና ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት በማድረግ በመጨረሻው ሰዓት ካለምንም ድርድር መተግበር የሚችልን አካል)ማንነት ማወቅ ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ብሎም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አስፈላጊ ነው። ጉዳዩን በአጽንዖት እንድንመረምረው የሚያስገድደን ይህ አንድ ክስተት ብቻ ሳይሆን ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ መፈጸሙ ነው።

ለአብነት ወደ ኋላ ሄደን የታገዱትን ጉባኤያት እንመልከት:-

  • በሚሊየነሙ መግቢያ ላይ ከመላው ሀገሪቷ በተሰባሰቡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሊታይ ታቅዶ የትእይነቱ መድረክ እየተዘጋጀ ባለበት ሰዓት እንዲታገድ የተደረገው የቤተ ክርስቲያን የዝማሬ ትዕይንት፥
  • የማኅበሩን ምሥረታ 20ኛ ዓመት አስመልክቶ የተዘጋጀው ዝግጅት፥
  • ከአንድ ዓመት በፊት ከመላው ሀገሪቷ የተሰባሰቡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ፣
  • እንዲሁም በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ለመምከር ተጠርቶ የታገደውን ጥናታዊ ጉባኤ መጥቀስ ይቻላል።

በዓለም ላይ የሚታየው የሃይማኖት አክራሪነት አደጋ የሃይማኖትን ትምህርት በጥልቀት ካለመረዳት የመጣ መሆኑን ሁሉም ይስማማበታል። አንድ ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት በተገቢው መንገድ ከተማረ ትሁት፣ ሰውን አፍቃሪና አክባሪ፣ ለሌላው አመለካከት ክብር የሚሰጥ ነገር ግን ሁሉም እውነት በሆነው የእግዚአብሔር ቃል ራሱን እንዲመዝን የተቻለውን እገዛ የሚያደርግ ይሆናል እንጂ የእኔን ሃይማኖት ካልተከተልክ መጥፋት አለብህ ሊል አይችልም። ከዚህ አንጻር ብቻ እንኳን ብናየው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት “እንጠቅቅ” የሚለው አባባል በእምነቱ የጸና በምግባሩ የቀና ምእመን እንዲበዛ በማድረግ ከሃይማኖት ጋር ተቀላቅለው የሚመጡ ስሜታዊነትንና ግብታዊነትን በመግራት ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።

ከዚህ በላይ ሁሉም ምእመን ድርሻውን ካወቀ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ከተለያዩ አካላት ጋር ተግባብቶና ተረዳድቶ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊና ማኅበራዊ ተልዕኮ ለማፋጠን ይችላል። መንፈሳዊ መሪዎችን ከመውቀስና ለሁሉም ችግር እነርሱን ተጠያቂ ከማድረግ ሁሉም በተሰጠው መክሊት እያተረፈ በወንጌል እንደታዘዘው ቤተ ክርስቲያን የብጹአን ስብስብ ትሆናለች። ሃይማኖታቸውን በሚገባ የተረዱና ድርሻቸውን የሚያውቁ ምእመናን በሀገር ላይ ሲበዙ ለሀገር በረከት ይተርፋል። ከዚያም በላይ እንደ ሀገራችን ላሉ ሰፊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በበዙባት ሀገር የእርስ በእርስ መፈቃቀርና መተዛዘንን የምታስተምር፥ ላመኑትም ላላመኑትም ያለ አድልዎ የምትለግስ፣ ጥሩ ተቋማዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላት ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ለዚህም ነው ባደጉት ሀገሮች ለእምነት ተቋማት ከፍተኛ ክብርና የገንዘብ፣ የሕግና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ድጋፍ በየሀገሩ መንግሥታት የሚሰጠው። ታዲያ የቤተ ክርስቲያን መጠናከር እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች ካሉት ለምን ቤተ ክርስቲያንን የተመለከቱ፣ ለለውጥ የሚያነሳሱ ታላላቅ ተግባራት በተደጋጋሚ እንዲስተጓጎሉ ተፈለገ? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። ማነው ከዚህ ሁሉ ጀርባ ያለው?

ቤተ ክርስቲያንን በመዝረፍና በማዘረፍ ላይ በተሠማሩ ሙሰኞች ከኋላቸው የሚገፉት ፓትርያርክ አባ ማቲያስ የችግሩ ሁሉ ምንጭ አድርጎ መደምደም የብዙኃን ግምት ሊሆን ይችላል። ፓትርያርኩ ደብዳቤዎችን ከመፈረም፥ የሚናገሩት ነገር ተነግሮአቸው ስላልመረመሩትና መረጃ እንዲቀርብላቸው እንኳ ስላልጠየቁት ጉዳይ ካለምንም ይሉኝታ በየመድረኩ ከመናገር ያለፈ ምንም ድርሻ የላቸውም። ፖትርያርኩ ከተወሳሰበው የቤተ ክህነት አሠራር ለዘመናት ርቀው የኖሩ በመሆናቸው፣ ከትምህርት ዝግጅታቸውም አንጻር እየተደረገ ያለውን ነገር ለመረዳት በእጅጉ የሚቸገሩ በመሆናቸው እንደዚህ ያለውን የተጠና እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበትን ሁኔታ ለመምራት አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ እንደሌላቸው ይታወቃል። ምንም እንኳ ሁሉም የሚሆነው በእግዚአብሔር ፍቃድ ነው ብሎ ራስን መሸንገል ቢቻልም፣ የተመረጡበትን ሁኔታ፣ ከተመረጡም በኋላ የነበራቸው በጎ እቅዶች በፍጥነት እንዴት እንደተቀለበሱ ለሚረዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ፓትርያርኩ እንዲፈጽሙት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከመፈጸም ውጭ እየሰሩ ያሉት ነገር የለም። ስለሆነም የሌሎች ክፋት ማስፈጸሚያ መሣሪያ በመሆናቸው በተሰጣቸው መክሊት ብዛት እና ባላቸው ከፍተኛ ኃላፊነት ምክንያት ከተጠያቂነት የማያመልጡ ቢሆንም እርሳቸውን በመውቀስና በመርገም የሚገኝ ነገር ባለመኖሩ እንደሀገራችን ገበሬ “እዚያው ማርልኝ ያንን… ” ብለን ብናልፋቸው ሳይሻል አይቀርም። በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ግርግር እየፈጠሩና የፖለቲካ ታማኝነታቸውን የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለመዘረፍ የሚጠቀሙበትንም ከማንኛውም ተራ ወንበዴ የማይለዩትን ሙሰኞችም ለጊዜው ልንተዋቸው እንችላለን።

ነገሩን በሚገባ የምንረዳው ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ቤተ ክርስቲያንን ከተቻለ ህልውናዋን ማሳጣት፣ ያለበለዚያም በተከታታይ በሚተገበሩ ሥልቶች የማዳከም ዕቅድ ተይዞ ካለማቋረጥ እየተሠራ መሆኑን ስንመረምር ነው። ኢትዮጵያዊያን ሁልጊዜም የሚቀለንና በቀላሉ ትኩረታችንን የሚስበው የውጭ ኃይሎች ተጽእኖ አንድም በሥራ እንጂ ደጋግመን ስላወራነው ልናስቀረው የማንችለው በመሆኑ ደግሞም የከፋውንና ሊውጠን የቀረበውን የውስጥ ችግራችንን ከማየት የሚያዘናጋን በመሆኑ ለጊዜው እናቆየውና ወደ ውስጣችን ችግር እንመልከት።

ላለፉት 23 ዓመታት የሀገራችንን መንበረ መንግሥት የተቆጣጠረው የፖለቲካ ኃይል ከመነሻው ዓላማዎቹን ለማስፈጸም እንደ እንቅፋት የሚቆጥራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በመደብ ጠላትነት ፈርጆ እንደሚሠራ ቋሚ መረጃ የሚሆነው የዶ/ር አረጋዊ በርሄ የዶክተሬት ዲግሪ ማሟያ ጽሑፍ ነው።

“The church was viewed as a force standing in the way of the TPLF but one that should be handled with caution. The TPLF had never been anti-religion as such, although its Marxist ideology called for that. Nevertheless, there was no doubt that that it wanted to subordinate the church to its cause. The TPLF therefore took a series of coordinated steps to neutralize the church’s influence.” (p. 301)

ለዚህ ማሳያው ድርጅቱ ሀገሪቱን በተቆጣጠረበት ማግስት የቤተ ክርስቲያኒቱን 4ኛ ፓትርያርክ በተለመደ መሠሪ አካሄዱ ከመንበራቸው ሲያባርር (ቤተክህነቱ ሁሌም ተሸክሞት የሚኖረው ውስጣዊ የአሰራር ዝርክርክነትና የዘር ሽኩቻ ተጨምሮበት) የነበረበትን ሥጋት በቀላሉ መረዳት ይቻላል (የቀድሞውን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ላይኔን ምስክርነት ያስታውሷል)። ገሚሱ በተለመደው የቤተክሀነቱ የውስጥ ሽኩቻ ለማትረፍ ሌላው ደግሞ በተጠናወተን “እኔ ምን አገባኝ” ጉዳዩ እንደቀላል ታይቶ ዝም ተባለ። ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ የተደፈረችው ያኔ ነው። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ “ከመሞት መሰንበት“ ይሻለኛል ብለው ሀገራቸውንና ምእመናቸውን ጥለው እነሆ ለ23 ዓመታት በሰው ሀገር ሲያዝኑና ሲተክዙ ይኖራሉ። (ይህ ራስን ለበጎቹ አሳልፎ ከመሰዋት የተሻለ ነው የሚሉ ከሆነ የምርጫው ባለቤት እሳቸውና አምላካቸው ብቻ ያውቁታል። ሆኖም ግን በዚህ ቅዱስነታቸውን ለመውቀስ ሳይሆን አርአያነቱ የሚጠቅም ስለሆነ ጠቁሞ ለማለፍ ነው)።

ቤተክሀነቱ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር የተሻለ አቅምና ጥብዓት ያላቸው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት እንደነበሩት ባይጠረጠርም ከዚያ ወዲህ ግን ምንም ፍሬ እንዳያፈራ ከፍተኛ የማዳከም ዘመቻ ተከፍቶበታል። ኢህአዴግ በወቅቱ በተፈጠረው ግርግር በግላቸው በነበራቸው ከፍተኛ የመግባባት ችሎታና በላቀ የትምህርት ደረጃቸው ሁኔታውን ለማዘናጋት የተመቹትን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን በቀላሉ ወደ መንበሩ አመጣቸው። ከዚያም በትምህርተ ሃይማኖት ጽኑአን እና በምግባራቸው የሚታወቁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን እና ሊቃነ ጳጳሳትን በተለያየ ዘዴ በማዳከም በተጠናና በብዙ ዝግጅት የቤተ ክርስቲያኗን መዋቅር እንዲቆጣጠሩ ከበረሃ ጀምረው በሰለጠኑ “መነኮሳት” እና ጥቁር ራሶች የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ከሀገር እስከ ውጭ ሀገር እንዲያዝ አደረገ። አሁንም ከእነዚህ ታማኝ የፖለቲካ ስልጡኖች ጥቂት የማይባሉትን ወደ ጵጵስና ማዕረግ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። እውነተኞቹ አገልጋዮች እየተገፉ በተከበረው በምንኩስና ስም የቤተ ክርስቲያንን ሀብት የሚዘርፉና ተቀዳሚ ዓላማቸው የፖለቲካ መሳሪያነት የሆኑ ካድሬዎች ቆብ እያጠለቁ በወሳኝ መዋቅሮች ጭምር በኃላፊነት እንዲቀመጡ አደረገ። እነዚህ አካላት ከሀገር ቤት እስከ አሜሪካ በተዘረጋ ሰንሰለት ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጉ ከሁሉም አካላት ጋር እየመከሩ ቤተ ክርስቲያንን የማዋረድና ዓላማዋን የማደናቀፍ ሥራቸውን በፖለቲካው ሙሉ ድጋፍ እያከነዋኑ ይገኛሉ።

ይህም አልበቃ ብሎ ነብሰ በላ የሚባለው ደርግ እንኳን (የሚከተለው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮት “ቢፈቅድለትም”) እየፈራ እየተባ የሚያደርገውን ቤተ ክርስቲያንን እና አባቶችን የመዳፈር ተግባር ገዢው ፓርቲ ካላምንም ፍራቻ (ምንም የፖለቲካ ኪሣራ እንደማያስከትል በማስላት) ገፋበት። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ካለምንም ግብዣ ወደ ቤተክህነቱ በፈለጉበት ቀንና ሰዓት እየመጡ (ካላደረሳቸውም በስልክ) ለፓትርያርኩና ለሊቃነ ጳጳሳቱ መመሪያ እስከመስጠት ደረሱ። ሊቃነ ጳጳሳትን የሚደበድቡና የሚያስፈራሩ የቤተክህነት “ደህንነቶችም” ተፈጠሩ። ማንም የእነሱን ዘረፋ ለማስቆም የሚሞክር ቢገኝ የፈለጉትን ለማድረግ ሙሉ የመንግስት ድጋፍ እንዳላቸው በአደባባይ የሚናገሩና፣ ሲፈልጉም የተቃወማቸውን ሁሉ በወታደር እያስገፉ ከእስር ቤት መጨመር የሚችሉ የቤተክህነት “ባለሥልጣናት” ተፈጠሩ።

ይህ ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ባለበት ሁኔታ ራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ የተለያዩ ጥበቦችን እየተጠቀመ የዘለቀ (ብዙዎች ፍራቻ ነው ቢሉትም) ነገር ግን በቤተ ክርስቲያንና በሀገር ላይ ቀላል የማይባል አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ባለው ማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው የቤተ ክርስቲያን መርሐ ግብር እንዲስተጓጎል መደረጉ መታየት ያለበት በዚህ ዐውድ ነው።

ለመሆኑ ገዢው ፓርቲ ይህችን ቤተ ክርስቲያንና ይህንን የመሳሰሉ በጎ ተግባራትን በማጥፋት ምን ይጠቀማል? መልሱ ምንም ነው። ሆኖም ግን ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በፍራቻ፣ በሥጋትና በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ስለሚያራምድ ለፖለቲካ ዓላማው (በሥልጣን ለመቆየት)እንኳን የሚጠቅመው ምን እንደሆነ ለማመዛዘን ስለሚቸገር ነው። በሚገባ ካያነው ግን ራሱን እንደ ቀኝ ገዢ ለሚመለከት ሥርዓት ሥጋቱ የሚገባ ነው። እውነትም እነሆ እስከዛሬም ቤተ ክርስቲያን ለገዢው ፓርቲ ዓላማ እንቅፋት ሆናለች። የገዥው ፓርቲ የፕሮፖጋንዳ ማሽን በየቀኑ በሕዝቦች መካከል መለያየትን እና ጥላቻን ሲዘራ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ ትምህርት ግን አንድነትንና የሰው ልጆችን እኩልነት በማጉላት እነሆ በመላው የሀገራችን ክፍል ያለው ሕዝብ ከቀድሞ በበለጠ በማይበጠሰው መንፈሳዊ ትሥሥር ተጣምሮ ኢትዮጵያዊነት እያደር እየፈካ መጥቷል። የሕዝቦች አንድነት እየተጠናከረ የመጣው የገዢው ፓርቲ ፖለቲከኞች እውነታው እያንገሸገሻቸውም ቢሆን እንደሚሉት ሁሉም የራሱን ማንነት እያወቀ ስላመጣ ሳይሆን ትምህርቷ ሁል ጊዜም አንድነትንና ክርስቲያናዊ ፍቅርን የምትሰብክ ቤተ ክርስቲያን በመኖሯ ነው። ዛሬ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ክርስቲያኖች የተለያየ ቋንቋና ባህል ቢኖራቸውም የአምልኮ ሥርዓታቸው በአብዛኛው ተመሳሳይ በመሆኑ በፖለቲከኞቹ እንደሚሰበከው ሌላውን ጠላት አድርጎ ለመመልከት አይችሉም። ይልቁንም በእምነቱ እየፀና፣ ያልፀኑትን እያበረታ፣ ያላመኑትን ለማሳመን እየተጋ እንዲሁም የራሳችን እምነት አለን የሚሉትን ምርጫቸውን ተቀብሎ በሰላም የሚኖር ሕዝብ ያለን በአጋጣሚ/ በመታደል ሳይሆን በሚገባ መሠረት ላይ ተመስርቶ ክርስትና ስለተሰበከ ነው። ይህም በመሆኑ ፖለቲካው የተጠነጠነበት ዘረኝነትና ጥላቻ ተቀባይነት አጥቶ እነሆ የእምቧዩ ካብ እየተናደ ነው። ምክንያቱም ከዘረኝነትና ከቋንቋ የበለጠ ማኅበረሰቡን ለማስተሳሰር አቅም ባለው በሃይማኖት ገመድ የተሳሠረውን ምእመን ለመለያየት አልተቻለምና። ለዚህ ደግሞ “ተጠያቂዋ” ቤተ ክርስቲያን ነች። ይህንን የምንለው ግን የቤተ ክርስቲያንን መሠረተ ትምህርት መሠረት አድርገን ነው እንጂ በአሁኑ ወቅት የቤተክህነቱን አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በፖለቲካው ቁጥጥር ሥር የወደቀ መሆኑን ሳንደብቅ ነው።

የሚያስገርመውም በዚህ ሁሉ ተጽእኖ ሥር አሁንም የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለመፈጸም ያለው የአባቶቻችን እና የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ አገልጋዮች ቁርጠኝነት ነው። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በምትመራው ሀገራችን ከተፈቀደውና የተቀመጠውን መስመር የማይከተል ሁሉ ይጨፈለቃል። ከመጨፍለቁ ለመዳን ሳይሆን በሀገር ላይ የሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ በመገንዘብ በትእግስት ለመጓዝ የሚሞክሩት ጭምር እነሆ እየተገፉ የምንወዳትን ሀገራችንን ወደ ማይፈለግ አዘቅት ለመክተት ቁርጥ የተያዘ ይመስላል። እውነተኞቹ ክርስቲያኖችና ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ግን በበለጠ ትዕግስትና ማስተዋል ልንጓዝ ይገባል። 100 ሺ ዜጎች ይታደሙበታል የተባለ መርሐ ግብር ለዝግጅቱ ዓመት ከተደከመበት፣ ሕጋዊ ውል ከተፈረመ ከመንፈቅ በኋላ፤ ሰዓታት ሲቀሩት መሰረዙ የማያሳስበው ማንንም የማይፈራውን እውሩን መንግሥታችንን ብቻ ነው። በሀገሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣት በሚኖረው ተስፋ ቢስ ሕይወት መማረሩን ትቶ ቤተ ክርስቲያንን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል (በረከትን በመሻት) እያገለገለ በሚገኝበት በዚህ ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩትን የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሚያሳዝን እንዲህ ያለ ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ መወሰን በእርግጥም መታወር ነው። የሚመጣውንና የሚሆነውን ሁሉ የሚያውቀው እግዚአብሔር ቢሆንም እየተደረገ ባለው ነገር እየቆሰለ ያለው የሚሊዮን ምእመናን ልብ ገዢውን ፓርቲ ዋጋ ሳይስከፈለው አይቀርም። #Dejeselam#MinilikSalsawi #Ethiopia (ዲባባ ዘለቀ ለደጀ ሰላም እንደጻፉት)

(ዲባባ ዘለቀ ለደጀ ሰላም እንደጻፉት) – http://www.dejeselam.org/2016/03/blog-post_26.html

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s