ወንድም እህቶቻችን የት አሉ ? – ግርማ ካሳ

 

 

7351f611-5578-43d0-a1df-f9d835cdc3b6ሁለት ወንድማማቾች ናቸው። ቃየን እና አቤል ይባላሉ። በዘፍጥረት ምእራፍ 4 ላይ የተጻፈው ነው። “ቃየን አቤልን ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ አቤል ላይ ተነሳበት። ገደለዉም” ይለናል ቃሉ። ደም ፈሰሰ። የወንድም ደም በወንድም እጅ። እግዚአብሄር በሆነው ነገር አዘነ። ለቃየንም ጥያቄ አቀረበለት። “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው። ቃየንም መለስ “ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” አለ።

የቃየን መንፈስ ደም የማፍሰስ መንፈስ ነው። የቃየን መንፈስ የጥላቻና የክፋት መንፈስ ነው። የቃየን መንፈስ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ምን አገባን የሚል መንፈስ ነው። የቃየን መንፈስ ከተማ፣ አገርን እና ህዝብን የሚያጠፋ የተረገመ መንፈስ ነው።

b5778839-8d13-48a7-abf1-6ec3189b2d1dበአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ የቃየን መንፈስ ሥር ሰዶ የብዙዎቻችንን አይምሮና ልብ የሰለበበት ሁኔታ ያለ ነው የሚመስለው። በምንኖርበት ቦታና በመስሪያ ቤቶቻችን በየጊዜው ግፍ እየተፈጸመ “እኔ ላይ እስካልደረሰ ድረስ እኔ ምን አገባኝ? እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን” ብለን ዝምታን የመረጥን እጅግ በጣም ብዙዎች ነን። ብዙዎቻችን እግዚአብሄርን የምናምን ነን። ቤተ ክርስቲያናትን፣ የተለያዩ የጸሎት ቤቶችን እናዘወትራለን። ጥሩ ነው። ተገቢም ነው። ሆኖም እግዚአብሔርን ማምለክና መዉደድ ሰዉን ከማገልገል ጋር የተቆራኘ መሆኑን ግን በጣም ዘንግተናል። እግዚአብሄር “ወንድሞቻችሁ፣ እህቶቻችሁ የት አሉ ?” ነው የሚለን።

ከራሳችን አልፈን፣ ወደ ጎን ወደ ወንድሞቻችን የማንመለከት ከሆነ፣ የተጎዱትንና የወደቁትን የማናነሳ ከሆነ፣ የፈለገ መንፈሳዊ ተግባራትን ብናደርግ፣ የፈለገ ያሬዳዊ ዜማ ብንቀኝ፣ የፈለገ ቴዎሎጂ ተምረን ግሪክና እብራይስጥን ብንተረጉም፣ የፈለገ የቤተ ከርስቲያን ሹመት ቢኖረን፣ የፈለገ ሁዳዴና ፍልሰታን ብንጾም፣ የፈለገ በየከተሞች የሚደረጉ መንፈሳዊ ኮንፈራንሶችን ብንካፈል … በጌታ ዘንድ ዋጋ አይኖረዉም። የተለያዩ ኃይማኖታዊና መንፈሳዊና ዉጫዊ መገለጫዎች  ለብቻቸዉ እግዚአብሄርን አያስደስቱትም። በኢሳያስ ምእራፍ አንድ ቁጠር 13 እና 14 ላይ እንዲህ የሚል ተጽፏል ፡

«የመስዋታችሁህ ብዛት ለኔ ምን ይጠቅመኛል ? ይላል እግዚአብሄር። የሚቃጠለዉን የአዉራ በግ መሥዋእትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቢያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአዉራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃቹህ የሚሻ ማን ነዉ ? ምናምንቴዉን ቁርባን ጨምራቹህ አታምጡ፤ እጣን በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነዉ። መባኦቻችሁና ሰንበታችሁንም በጉባዔ መሰብሰባችሁን አልወድም ……. እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ አይኔን ከናንተ እሰዉራለሁ። እሰዉራለሁ። ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም»

ለምንድን ነው እግዚአብሄር መንፈሳዊ ጉባዔያችንን የሚጸየፈዉና ጸሎታችንን የማይሰማው የሚል ጥያቄ ከጠየቀን መልሱ ደግሞ በዚሁ ኢሳያስ ምእራፍ አንድ ዉስጥ ወረድ ብሎ በቁጥር 17 ላይ እናገኘዋለን። «እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል። ታጠቡ ሰዉነታችሁንም አንጹ። የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ። ክፋ ማድረግን ተዉ። መልካም መሥራትን ተማሩ። ፍርድን ፈልጉ። የተገፋዉን አድኑ።ለድሃ አደጉ ፍረዱለት።ስለ መበለቲቱ ተሟገቱ» ይላል።

አንድ ወቅት እስራዔላዉያን ጾም ጸሎት አድርገው እግዚአብሄር ፊቱን ያዞረባቸዉ ጊዜ ነበር። የዚህን ጊዜ እየጾሙ እየጸለዩ ለምን እግዚአብሄር እንደተዋቸዉ መጠየቅ ጀመሩ። እግዚአብሄርም መልስ ሰጣቸው። ቃሉ እንዲህ ይላል፡« ስለምን ጾምን ? አንተም አልተመለከትከንም። ስለምን ሰዉነታችህንንስ አዋረድን፣ አንተም አላወቅህም ? ይላሉ። እነሆ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ። ሰራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ። በግፍ ጡጫም ተማታላችሁ። እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነዉን ? …. በእዉኑ ይህ ጾም በኔ ዘንድ የተወደደ ነዉን ? እኔ የመረጥኩት ጾም የበደልን እሥራት ተፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ፣ የተገፉትንስ አርነት ትሰዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንም ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራንስ ለተራበ ትቆርሱ ዘንድ፣ ስደተኞች ድሆችን ወደ ቤታችህ ታገቡ ዘንድ፣ የተራቆቱትን ብታዩ ታለብሱ ዘንድ አይደለምን ? “ (ኢሳ 58 ፡ 6 -7)

በአገራችን ኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ሁሉ እዚህ ለመዘርዘር በጣም አስቸጋሪ ነው። ከብዛታቸው የተነሳ። ሁላችንም የምናውቀዉና የምናየዉ ነዉ። በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለረሃብ የተጋለጡ ናቸው። ብዙዎች በቀን አንዴ ነዉ የሚመገቡት። የኑሮ ዉድነቱ ከቁጥጥር ዉጭ እየሆነ ነዉ። ብዙዎች በጉልበተኞች በግፍና በጭካኔ ተገድለዋል። አሁንም እየተገደሉ ነው። በቅርቡ እንኳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በኦሮሚያ ክልል፣ በሰሜን ጎንደር፣ በኮንሶ ፣ ሕጻን፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ ሳይባሉ፣ እንደ ቅጠል ረግፈዋል። ነፍስ የገደሉ በጠራራ ጸሃይ በአደባባይ ሲመላለሱ ወንጀል ያልሰሩ፣ በፖለቲካ እምነታቸዉ ምክንያት ፍርድ እየተዛባ፣ ፍትህ ተጓድሎ ከፍርድ ሥርዓቱ ዉጭ በግፍ እየታሰሩ ነዉ። ብዙዎች ከመሬታቸውና እና ከቅያቸው እየተፈናቀሉ ነው። የተወሰኑት መሬታቸው ለልማት ይፈለጋል በሚል ፣ ሌሎች ደግሞ ከዚህ ዘር ናችሁ እየተባለ።

ታዲያ ይሄ ሁሉ ግፍ፣ ኢፍትሃዊነትና ጭካኔ በወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ፣ “እኛ የወንድሞቻችን ጠባቂ ነንን ? “ ብለን ዝምታን ከመረጥን እና የዘመኑ ቃየኖች ከሆንን እንደ አገር እንዴት መዝለቅ እንችላለን ?

የአሥራ ስድስት አመት ወጣት ነበረች። በዘጠና ሰባት፣ በኮተቤ አካባቢ፣ በጥይት ተመታ ወደቀች። ሽብሬ ደሳለኝ። እግዚአብሄር ይጠይቃል። “ሽብሬ ደሳለኝ የት ነው ያለችው ?” ይላል። ሰርግ ለማድረግ እየተዘጋጀች ነበር። ሰላማዊ ሴት ናት። በኦሮሚያ የተነሳዉን ተቃዉሞ በሃይል ለመጨፍለቅ ታጣቂዎች ወደ መንደሯ ገቡ። ተኮሱ። ይች ወጣት ወደቀች። ሻሺቱ ትባላለች። እግዚአብሄር ይጠይቃል ሻሺቱ የት ነው ያለችው ? የ28 አመት ወጣት ነው። የቤት አስተዳዳሪ። በአምቦ እርሱም በጥይት ረገፈ።፡ግርማ ረጋሳ ይባላል። እግዚአብሄር ይጠይቃል ፤ “ግርማ ረጋሳ ወዴት ነው ?” ይላል።

እኛ ግን መልሳችን “የሽብሬ፣ የሻሺቱ፣ የግርማ ረጋሳ ጠባቂ ነንን ?” የሚል አይነት ሆኖ ግፍ ተፈጸሞ እንዳልተፈጸመ፣ ከንፈር መጥቶ ዝም ከማለት ዉጭ ብዙም ያደረገነው ነገር የለም። የዘመኑ ቃየኖች !!!!

በእዉኑ “ቃየንነታችንን”፣ በኛ ወይንም በቤተሰቦቻችን በቤተሰቦቻችን ላይ ችግር እስካልደረሰ ወይንም እኛ እስካልተነካን ድረስ በሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰዉን ግፍ አይተን ዝም ማለታችን፣ እግዚአብሄር የሚወደዉ ነገር ነዉን ? በጭራሽ አይወደዉም።

አንድ የተማረ ወዳጄ ከቴክሳስ ደወለ። በጨዋታችን መሃል የአገር ጉዳይ ተነሳና «አንተ ክርስቲያን ነህ። ፖለቲካ ዉስጥ ለምን ትገባለህ? ከፖለቲክ ዉጣ። አርፈህ በቤተ ክርስቲያንህ እግዚአብሄርን አገለግል» አለኝ። እኔም መለስኩ። «የኔ ወንድም። አሁን የማደርገዉ እኮ ክርስቲያን ስለሆንኩኝ ነዉ። የእግዚአብሄር ቃል ለፍትህ እንድንቆም፤ ዜጎች በግፈኞች ሲገፉ ለነርሱ እንድንሟገት፣ ድምጻቸዉ ለታፈነ ድምጽ እንድሆን፣ የተጣሉትን እንዳስታርቅ አዞናል። የሕሊና እሥረኞች እንዲፈቱ የማደርገዉ እንቅስቃሴና ፣ በማንም ይሰሩ የሚሰሩ ግፎችን ማዉገዜ፣ ቅዳሴ ከማስቀደስና በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ከመዘመርና ከመስበክ ያልተናነሰ እግዚአብሄርን የሚያስደስት ነዉ» አልኩኝ። ይህ ሰው አገር ቤት ትልቅ ቢዝነስ ያለው ወንድም አለው። “እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠየቅህ። አንድ ቀን በሆነ ምክንያት ወንድምህ ቢታሰር ፣ ወንድምህ እንዲፈታ በየሰልፉ ቀዳሚ ሆነህ የምትቆም፣ ፔተሽኖችን የምትፈርምና የምታስፈርም፣ በሶሻል ሜዲያ ዘመቻ የምታደረግ አትሆንም ወይ ?” አልኩት። “እርሱማ ነው” አለኝ። “ታዲያ የራሳችን የሥጋ ወንድማችን ሲታሰር የምናደርገውን ነገር ሌላው ሰው ላይ ሲደርስ አለማድረግ እና አርፈን መቀመጥ አለብን ማለት ተገቢ ነው ወይ ? ራስ ወዳድነት አይደለም ወይ ? “ ብዬ ጠየኩ። ይህ ወዳጄ የሚመልሰውን አጣ።

ዉድ ወገኖች ፣ ብሶት ማውራት፣ ማጉረምረም፣ ነጻነትን እና ፍትህን ሌሎች ጥቂቶች ብቻ ሞተው፣ ጥቂቶች ብቻ ታስረው፣ ሌሎች በከፈሉት መስዋእትነት ለማግኘት መመኘት እና እየደረሰብን ላለው ችግር ራሳችንን ሳንጠይቅ በሌሎች ላይ ማሳበብ የደካሞች መንገድ ነው። የደካሞች ፖለቲካ ነው። ሁላችንም ወደ ራሳችን መመለስ አለብን። ለአገር ነጻነት ከማሰብ በፊት ነጻነት መጀመር ያለበት ከራሳችን ነው። ራሳችንን በግለሰብ ደረጃ ከፍርሃት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከቃየን መንፈስ ነጻ ስናወጣ፤ የሌላው ሕመም ሲሰማን፣ እጆቻችን ሌላውን ለመገደል፣ ለመደብደብ ሳይሆን ሌላውን ለማንሳት ሲዘረጉ፣ ከናፍርቶቻችን ሌላውን ለመስደብ፣ ለመርገም፣ ለማሳነስና ለማዋረድ ሳይሆን ሌላውን ለማበረታታት፣ ለማጽናናትና ለመባረክ ሲከፈቱ ያኔ በርግጥም የኢትዮጵያ ትንሳኤ ጅማሬ ሆነ ማለት ነው። የአገር ትልቅነት የሚመነጨው በሕዝቧ ትልቅነት ነው። የሕዝቧ ትልቅነት የሚመነጨው በእያንዳንዱ ዜጋ ትልቅነት ነው። የእያንዳንዱ ዜጋ ትልቅነት የሚመነጨው ሌላውን በማገልገልና ለሌላው በማሰብ ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

<span>%d</span> bloggers like this: