የአሜሪካ የሕግ ምክር ቤት አባላት (ሴናተሮች) በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ መቆም አለበት እያሉ ይጮሃሉ!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

Cardin 6ባለፈው ሐምሌ ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ጎበኘ እና የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስበ (ህወሀት) አገዛዝ “ዴሞክራሲያዊ መንግስት” ነው በማለት አወጀ፡፡

ዘ-ህወሀት ዓይኑን በጨው ታጥቦ ተካሂዶ የነበረውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ መቶ በመቶ ወይም ደግሞ ሁሉንም 547 የፓርላማ መቀመጫዎች ያሸነፈ መሆኑን አይን ባወጣ ዉሸት ባለፈው ግንቦት ገለጸ፡፡

የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት ይህንን ጉዳይ በማስመልከት “አሳፋሪ” ሲል ጠራው፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የኦባማን መግለጫ “አስደንጋጭ” (በሬ ወለደ አንደማለት) በማለት ጠርቶታል፡፡

እኔ ደግሞ የወረደ እና አሳፋሪ ቅሌት በማለት ጠርቸዋለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 20/2016 ሴናተር ቤን ካርዲን (የሜሪላንድ ዴሞክራት)፣ ማሪያ ካንትዌል (የዋሺንግተን ዴሞክራት)፣ ፓቲ ሙሪ (የዋሺንግተን ዴሞክራት)፣ ኤድ ማርከይ (የማሳቹሴትስ ዴሞክራት)፣ ክሪስ ኩንስ (የዴላዋሬ ዴሞክራት)፣ ቦብ ሜንዴዝ (የኒው ጀርሲ ዴሞክራት)፣ ፓትሪክ ሊዚ (የቬርሞንት ዴሞክራት)፣ አል ፍራንከን (የሜኖሰታ ዴሞክራት)፣ ዱክ ደርቢን (የኢሊኖስ ዴሞክራት)፣ አሚ ክሎቡቻር (የሚኔሶታ ዴሞክራት) እና ማርኮ ሮቢዮ (የፍሎሪዳ ሬፐብሊካን) በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በዘ-ህወሀት እየተደረገ የሚገኘውን የሰብአዊ መብት ረገጣ በማውገዝ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

እርግጥ፣ “በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል” የሚለውን ሀረግ በትክክል ደፍረው ለመናገር አልተጠቀሙበትም፡፡ ሆኖም ግን ባሳለፉት ውሰኔ ላይ ማለት የፈለጉት በእርግጠኝነት ሌላ ሳይሆን ይህንኑ ጉዳይ ነበር፡፡

ሴናተር ካርዲን “በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃን መርዳት እና ሁል አቀፍ አስተዳደር እንዲሰፍን ማበረታታት“ በሚል ረቂቅ ሕግ ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ በመግቢያው ላይ እንዲህ ብለዋል፡

“በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች በተፈጸመው አረመኒያዊ ድርጊት እና ግድያው ለተፈጸመባቸው ቤተሰቦች በተሰጠው የሀዘን መግለጫ እጅግ በጣም ደንግጫለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ዜጎቹ በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብታቸውን ያጎናጽፋል እናም በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት እንደዚህ ያሉ እርምጃዎች በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በጋዜጠኞች ላይ እየተወሰዱ ያሉት ስልታዊ የመንግስት የኃይል እና የጭቆና እርምጃዎች እንዲሁም ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ለመሸበብ እና በሕጋዊ የፖለቲካ መንገድ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ለመከልከል እ.ኤ.አ በ2009 የወጣውን የጸረ ሽብር እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀም የዴሞክራሲያዊ ነጻነቶችን እና የሰብአዊ መብቶችን በመደፍጠጥ ላይ የሚገኝ ለመሆኑ ዋና ማሳያዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱ ከምትገኝበት አውዳሚ ድርቅ እና የወሰን የጸጥታ ደህንነት እጦት ጉዳይ አንጻር መንግስት ከምንጊዜውም በላይ የእራሱን ሕዝቦች ከመነጣጠል ይልቅ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቋቋም እንዲችል ከተፈለገ መሰረታዊ የሆኑትን የሰብአዊ መብቶችን መጠበቅ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡“

ሴናተር ሩቢዮ አንድ ዓይነት አስተሳሰብን በማራመድ እንዲህ በማለት ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ ተናግረዋል፡

“በኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች መሰረታዊ መብቶቻቸውን በመጠቀማቸው ብቻ ሰላማዊ አማጺዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ወትዋቾች በቁጥጥር ስር ውለዋል፣ ስቃይ እና ግድያም ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በመንግስት እየተፈጸሙ ያሉትን እንደዚህ ያሉትን ዓይን ያወጡ የተንሰራፉ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እና የኢትዮጵያን ሕዝቦች መሰረታዊ መብቶች መከልከልን አወግዛለሁ፡፡ የዩኤስ አሜሪካ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጠው እና የፖለቲካ የማሻሻያ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የኦባማን አስተዳደር እማጸናለሁ፡፡“

ኦባማ የሴናተር ሩቢዮን ተማጽኖ ጆሮዳባ ልበስ ብሎ አልፎታል፡፡ በቁስል ላይ እንጨት መስደድ እንዲሉ ኦባማ አዲስ አበባ በመሄድ ቀጥ ብሎ በመቆም እና አሳፋሪ በሆነ መልኩ ዘ-ህወሀት “ዴሞክራሲያዊ መንግስት” ነው በማለት አወጀ፡፡

ኦባማ እ.ኤ.አ ሐምሌ 2016 ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከመሄዱ ከጥቂት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በእራሱ ሕዝቦች ላይ እያካሄደ ስላለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ያሳሰባቸው መሆኑን  በመግለጽ ለኦባማ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሴናተር ሩቢዮ እንዲህ የሚል  ደብዳቤ በመጻፍ አስጠንቅቀው ነበር፡

“ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢትዮጵያ አሸባሪነትን ለመዋጋት እና በቀጣናው ውስጥ የተረጋጋ ጸጥታን ለማስፈን የጋራ የሆነ ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም ቅሉ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንሰራፋ ስላለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ጆሮዳባ ልበስ የሚል ምላሽ መስጠት የሌለበት ዋና ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ አማጺዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ሀሳባቸውን እንዳይገልጹ የፖለቲካ ሂደቱ፣ የሲቪል ማህበረሰቡ ወይም የመገናኛ ብዙሀን እንዳይንቀሳቀሱ መንገዶችን ሁሉ በመዝጋት በሀገሪቱ ውስጥ እየተፈጠረ ባለው ችግር ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ላይ ይገኛል፡፡“

በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሚወሰድ የኃይል እርምጃ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ኢሰብአዊ ወንጀል ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ባንኪሙን እንዲህ ብለዋል፣ “በሶርያ መንግስት እየተፈጸሙ እና እየቀረቡ ያሉት የጭካኔ እርምጃ ዘገባዎች ሁሉ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ኢሰብአዊ ወንጀሎች ወይም ደግሞ የጦር ወንጀሎች በመባል ይካተታሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ ኃይልን መሰረት ያደረጉ እርምጃዎች መመርመር አለባቸው እናም የወንጀል ድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡“

የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተሮች እየተናገሩ ያሉት እና በውሳኒያቸውም ጥሪ እያቀረቡ ያሉት ይህንኑ አንድ ዓይነት የሆነ ነገር ነው፡፡

የሴኔቱ ውሳኔዎች ግልጽ በሆነ ቋንቋ የሚያመላክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ በዘ-ህወሀት አገዛዝ በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ አማጺዎች አካሂደውት በነበረው ተቃውሞ የጸጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይልን በመጠቀም በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን የፈጸሙ ስለሆነ እነዚህ የጸጥታ ኃይሎች ላጠፉት ጥፋት በሕግ ለፍትህ አካል ቀርበው ተጠያቂ መሆን አለባቸው የሚል ነው፡፡

ሆኖም ግን ውሳኔው ቀላል መግለጫ ከመስጠት እና ትችትን ከማቅረብ በዘለለ መልኩ ተጫባጭነት ወዳለው የድርጊት እርምጃ መሄድ አለበት፡፡

ውሳኔው በአራት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሴናተሮችን አስተሳሰቦች፣ አመላካከቶች እና አቋሞች የሚወክል እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ውሳኔው፣

1ኛ) ዘ-ህወሀት የፈጸማቸውን ኢሰብአዊ ወንጀሎች ሙሉ በሙሉ አውግዟል፣

2ኛ) በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጋር በተያያዘ መልኩ ኦባማ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ተጨባጭነት ያለው ነገር ያላደረገ በመሆኑ ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ እና እየተሰላቹ የመጡ መሆናቸውን በግልጽ ያመላክታል፣

3ኛ) በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ወይም ደግሞ ዩኤስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የእርዳታ አጠቃቀም እንደገና መመርመር እና መጤን ያለበት ጉዳይ እንደሆነ አጽንኦ በመስጠት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀጥተኛ የሆነ የፖሊሲ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይጠይቃል፣

4ኛ) ዩኤስኤአይዲ/USAID በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞች እና ተግባራት የሰብአዊ መብትን ከማክበር እና የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ከማጠናከር አኳያ ተቃኝተው መቅረብ እንዳለባቸው ግልጽ የሆነ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡

በውሳኔው ላይ የተዘረዘሩት የዘህወሀት ኢሰብአዊ ወንጀሎች፣

በመጀመሪያው የውሳኔ ክፍል ዘ-ህወሀት በሰው ልጆች ላይ ስለፈጸማቸው ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበት ለሕግ አካል መቅረብ እንዲችል አንድ ዓይነት ዓላማ እና ፍላጎት እንዳለ አምናለሁ፡፡

የሴኔቱ ውሳኔ በዘ-ህወሀት ላይ እንዲህ በማለት ያውጃል፡

“የጸጥታ ኃይሎች ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን እና የመደራጀት ነጻነትን በመከልከል፣ ፖለቲካዊ ዓላማ ባላቸው ክሶች በመገፋፋት፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አባላትን እና ጋዜጠኞችን በማስፈራራት እና በማሸማቀቅ አስከፊ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ድፍጠጣ ላይ ማለትም ዜጎችን በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር በማዋል፣ በመግደል እና ስቃዮችን በመፈጸም ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል፡፡

በኦሮሚያ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች መብቶቻቸውን በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ በመሰብሰብ ቅሬታዎቻቸውን በማሰማታቸው ብቻ መንግስት መር ለሆነ የኃይል እርምጃ በመዳረግ የጋዜጠኞችን ነጻነት በማፈን የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ከሚያጎናጽው መብት ባፈነገጠ መልኩ በመሄድ ከዴሞክራሲዊ የአሰራር መርሆዎች በተጻራሪ ቆሞ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 ከተደረገው አጠቃላይ ምርጫ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷል፡፡

ምርጫን መቶ በመቶ አሸነፍኩ የሚል የሸፍጥ ምርጫ ተካሂዷል፡፡

የፕሬስ ነጻነትን ለመገደብ፣ ነጻ ጋዜጠኞችን ጸጥ ለማድረግ እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ለማሰቃየት የጸረ ሽብር አዋጅ እየተባለ የሚጠራ ሕግ በሸፍጥ ተዘጋጅቷል፡፡

የሲቪል ማህበረሰቡን እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በተለይም ደግሞ በመንግስት ባለስልጣኖች የሚካሄዱ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን እየመረመሩ በማውጣት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ የሚያሳውቁ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ መገደብ እና ሙሉ በሙሉም እንዲዘጉ አድርገዋል፡፡

ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን በማሰቃየት እና በፍርድ ቤት ቀጠሮ እያመላለሱ በማንገላታት በፕሬሱ ላይ የፍርሀት እና የጭቆና ድባብ ከባቢ አየር እንዲያጠላ እና እንዲንሰራፋ አድርገዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቢያንስ 200 እና ከዚያም ሊበልጥ የሚችል ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ አማጺዎች በጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡“

በውሳኔው የዘህወሀትን አገዛዝ ማውገዝ፣

የሴኔቱ ውሳኔ ያለምንም ማወላወል፣

ሀ) በዘ-ህወሀት የጸጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይልን በመጠቀም ባመጹ ተቃዋሚዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ያወግዛል፣

ለ) ዘ-ህወሀት ሰላማዊ በሆነ መንገድ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ሕገ መንግስታዊ የመሰብሰብ እና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብቶቻቸውን በመጠቀማቸው ምክንያት በጋዜጠኞች፣ ተማሪዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ወትዋቾች እና የፖለቲካ መሪዎች ላይ እያደረገ ያለውን በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር የማዋል እና ዘብጥያ የማዋሉን ድርጊት ያወግዛል፣ እንደዚሁም

ሐ) ዘ-ህወሀት ሰላማዊ የፖለቲካ እና የሲቪል ማህበረሰብ አመጸኞችን እና የጋዜጠኞችን ነጻነቶች ለማፈን እና ለማጥቃት ሲል ከሕግ አግባብ ውጭ እየተገበረ ያለውን የጸረ ሽብር ሕግ ያወግዛል፡፡

በውሳኔው በዘህወሀት አረመኒያዊ ድርጊት ላይ የቀረበ ጥሪ፣

የሴኔቱ ውሳኔ እንዲህ የሚሉ ውሱን የሆኑ ጥሪ በዘ-ህወሀት ላይ አቅርቧል፡

o   በጸጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ ከመጠን ያለፉ የኃይል እርምጃዎች በአስቸኳይ ይቁሙ፣

o   በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በገለጹ ንጹሀን ዜጎች ላይ በኦሮሚያ ክልል ከመጠን ያለፈ ኃይልን በመጠቀም እልቂት በፈጸሙ የጸጥታ ኃይሎች ላይ የተሟላ፣ ታማዕኒነት ያለው እና ግልጽ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ፣ እንዲሁም ጥፋቱን የፈጸሙ ወንጀለኞች ለፍትህ አካል ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ፣

o   ሰላማዊ አማጺዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ወትዋቾች እና 13 ጋዜጠኞች ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም ስለአመጽ እንቅስቃሴው የዘገቡ 14 ዜጎችን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣

o   በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 18፣ 19፣ 30 እና 29 በግልጽ የተቀመጡት በነጻ የመሰብሰብ እና ነጻነትን የሚያጎናጽፉት መብቶች ይከበሩ፣

o   መንግስት ለልማት እያለ ከሚያወጣቸው ስትራቴጂዎች በተለይም ዜጎችን ከመሬት ይዞታቸው የሚያፈናቅሉ ስትራቴጂዎችን ከመተግበሩ በፊት በይፋና ግልጽ በሆነ መልኩ ከዜጎች ጋር ውይይቶችን እንዲያደርግ፣

o   አገዛዙ የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር እና በማውጣት በሰላማዊ የፖለቲካ አንቅስቃሴ ወይም ደግሞ ለበለጠ የፖለቲካ ነጻነት  ተግባራት ላይ ተሰማርተው በመወትወት ላይ የሚገኙትን የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን ማስፈራራት ወይም ደግሞ ለዓላማዎቻቸው ማስፈጸሚያ የሚሆነውን ገንዘብ ከለጋሽ እና በጎ አድርጎት ድርጅቶች ማግኘት እንዳይችሉ ለማድረግ ያዘጋጃቸውን አዋጆች እንዲሰርዝ፣

o   ዜጎችን ከመሬት ይዞታዎቻቸው የሚያፈናቅሉት አዋጆች ይሻሩ፣ ወይም ደግሞ አግባብነት ያላቸው መፍትሄዎች ወይም ትክክለኛ እና ተመጣጣኝነት ያለው ካሳ በመክፈል ወይም ተፈናቃዮች ፍትህ ለማግኘት ግልጽና ነጻ ዳኝነት ማግኘት እንዲችሉ እንዲደረግ፡፡

ወደፊት የኦባማ አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት መሻሻልን በሚመከት ምንም ነገር ለማድረግየማያስችለውን ፖሊሲውን እርግፍ አድርጎ መተው አለበት፡፡

የሴኔቱ ውሳኔ የኦባማ አስረተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት መሻሻል ሁኔታ በጣም ትንሽ ወይም ደግሞ ምንም ነገር ያላደረገ መሆኑን ዴፕሎማሲያዊ በሆነ መልኩ ይፋ አድርጓል፡፡

ውሳኔው የኦባማ አስተዳደር በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ የተለያዩ ቃላትን በመጠቀም መናገር ብቻ እንጅ ምንም ነገር ያላደረገ እና እራቁቱን የቀረ መሆኑን እንዲሁም በየጊዜው ስለሰብአዊ መብት እየተናገረ የሰብአዊ መብት ጥበቃን እንደማይተገብር እና ምንም ነገር እንደማይሰራ ግልጽ አድርጓል፡፡

ውሳኔው ኦባማ እ.ኤ.አ ሐምሌ 2015 ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ የዘ-ህወሀትን መሪዎች ሲገናኝ የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን እንዲያጠናክሩት እና የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እና እንዲሻሻሉ እንዲነግራቸው ያውጃል፡፡ ሆኖም ግን እስከ አሁን ድረስ ያለው ሁኔታ እልቂት እና የበለጠ ጭቆና ነው፡፡

ውሳኔው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ሁኔታ አኳያ የሚሰጠው እርዳታ ከታለመለት ዓላማ አንጻር ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥቅም ስለመዋሉ አስተማማኝ እንዲሆን የደህንነት እርዳታው እንደገና እንዲጠና በማለት ለኦባማ አስተዳደር ጥሪ ያቀርባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ውሳኔው ለኢትዮጵያ ስለሚሰጠው የዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ዩኤስኤአይዲ/USAID ስለእርዳታው አጠቃቀም የበለጠ ትኩረት አድርገው እንዲከታተሉ እና ተጠያቂነትም እንዲኖር ጥሪ ያቀርባል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ የሴኔቱ ጽኑ ድጋፍ፣

የዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት “ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ እና ዜጎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የተሰጣቸውን ሕገ መንግስታዊ መብት ያለምንም መሸራረፍ መጠቀም እንዲችሉ የሴኔቱ ውሳኔ ያረጋግጣል፡፡”

ውሳኔው በእርግጠኝነት ምን ማለት ነው?

የሴኔቱ ውሳኔ (ቀላል ውሳኔ) በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን እና ወደፊት ምን መደረግ እንዳለበት የሴኔቱን የሕግ ማዕቀፍ ፍላጎት ዓላማ መሰረት ያደረገ መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡ (እ.ኤ.አ በ2/4/2015 የጸደቀውን የሴኔት ደንብ ቁጥር 30ን ይመልከቱ፡፡)

ሴኔቱ የእራሱን አመለካከት፣ ሀሳብ እና አቋም ለመግለጽ ሲፈልግ እና አጽንኦ ለመስጠት ወይም ደግሞ ስለአንድ ጉዳይ ጠቃሚነት ማስጠንቀቅያ ለማስተላለፍ እና መልዕክቱም በሁሉም ዘንድ እንዲደርስ ሲፈልግ ቀላል የሆነ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ በኢትዮጵያ የተላለፈው የሴኔቱ ውሳኔ የአብዛኞቹን ሴናተሮች ሀሳብ በመግለጽ ዓላማ ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡

እንደዚሁም ሁሉ እንደ መደበኛው ሕጎች እና ውሳኔዎች የሕግ ተፈጻሚነት አስገዳጅነት ወይም ደግሞ የፕሬዚዳንቱ ፊርማ ሳይኖርባቸው ሊተላለፉ የሚችሉትን ቀላል ውሳኔዎች መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡

ስለሆነም ምክንያታዊ ጥያቄ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው “ቀላል ውሳኔዎችን” ለማሳለፍ አሳሳቢ ሆኖ የሚቀርበው ለምንድን ነው? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ቀላል ውሳኔዎች የተፈጻሚነት አስገዳጅ የሕግ ግዴታ የሚጣልባቸው ባይሆኑም ቅሉ ጥቂት ጠቃሚ ተግባራትን ለማከናወን ያገለግላሉ፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት የሚከተሉትን ተግባራት ለማከናወን ያገለግላሉ፡

o   በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ ለመቀጠል እና የጋራ አቋም በመያዝ ድጋፍን ወይም ደግሞ ተቃውሞን ለመግለጽ በአንድ የተወሰነ ድርጊት፣ ፖሊሲ፣ የሕግ ረቂቅ፣ ሀሳብ፣ ዕቅድ፣ ፕሮግራም፣ ወዘተ ላይ በመመዝገብ ያገለግላሉ፣

o   በአባላት መካከል በአንድ በታሰበ ወይም በሚገመት ድርጊት ላይ ኃይልን ለማጠናከር አስቀድመው ድጋፍ ለማድረግ ወይም ደግሞ ለመቃወም ይረዳሉ፣

o   ሴኔቱ ወይም የተወካዮች ምክር ቤት በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ በጥልቀት እንዲያስቡ እና የበለጠ የተለመደውን የሕጋዊ አሰራር አስፈላጊነትን ሳይከተሉ እርምጃ ለመውሰድ እንደ ማሳሰቢያ ሆነው ያገለግላሉ፣

o   የዩኤስ ኮንግረስ አንድን የተወሰነ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እና አጽንኦ በመስጠት መመልከት እንዲችል ለዩኤስ መምሪያዎች፣ ኤጄንሲዎች እና የውጭ መንግስታት እንዲያውቁት ያደርጋሉ፣

o   አንድ ጉዳይ በአንድ በተወሰነ ሀገር ወይም አካባቢ በዩናይትድ ስቴትስ ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ከሆነ እና ሁኔታው በዚያው የሚቀጥል ከሆነ የሕግ እርምጃ ማዕቀፎችን ለመውሰድ እንዲቻል ለማድረግ በውጭ ጉዳዮች ላይ (ከውጭ መሪዎች) ጋር ለመግባባት ያገለግላሉ፣

o   በውጭ መንግስታት ላይ አስገዳጅ የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርጉ ተፈጻሚ ይሆናሉ፣

o   የፖሊሲ ለውጥ እንዲኖር ወይም ደግሞ ለቀጣይ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊነትን ግልጽ ያደርጋሉ፣

o   የሕዝብ ተደማጭነት እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡

ዋናው እና ተቀባይነት ያለው ነገር የሴኔቱ ውሳኔዎች በአብዛኞቹ የውጭ መንግስታት እና በዩኤስ መንግስት ኤጀንሲዎች እና መምሪያዎች ዘንድ በትኩረት እንዲታዩ ያደርጋሉ፡፡ የዘ-ህወሀት ደናቁርት በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚበሳጩ እና ነገሩን ከምንም እንደማይቆጥሩት መገመት ምክንያታዊ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2007 ተመሳሳይ ከሆነ የሕግ ማዕቀፍ ሁኔታ ጋር በተጋፈጡበት ጊዜ አሁን በህይወት የሌለው የዘ-ህወሀት አምባገነኑ መሪ መለስ ዜናዊ እጅግ በጣም በመበሳጨት እና ምጸታዊ በሆነ አነጋገር በዩኤስ ኮንግረስ መካከል በመገኘት እንዲህ በማለት የቃላት ጥዝጠዛውን/ዘለፋውን አጉርፎት ነበር፣ “የኢትዮጵያ መንግስት ያልተረጋጋ መንግስት ያላት ትንሽ ሀገር እና ወደ ውጭ በሚላክ በአንድ ምርት የውጭ ጥገኝነት ላይ የወደቀች ወይም ደግሞ በውጭ የገንዘብ እርዳታ የምትኖር ሀገር አይመኝም ወይም ደግሞ በዩኤስ ኮንግረስ ወይም በሌላ በማናቸውም ሀገር የምትሽከረከር ሀገር አይደለችም፡፡“ ድንቄም የምትሽከረከር አገር አይደለችም! ገበያ ባልወጣሽ ይሉሽን ባልሰማሽ ይላሉ ኢትዮጵያውያን ሲተርቱ፡፡

እ.ኤ.አ በ2009 የመለስ መንግስት በጂዳ ወይም በባህረ ሰላጤው እንደሚገኙ እንደማናቸውም ሀገሮች እንዲያዝ ይፈልጋል በማለት ገልጨ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አምባገነኑ መለስ በሚሊዮኖች ሄክታር የሚቆጠረውን የኢትዮጵያን ለም መሬት ሳውዲ እና የባህረ ሰላጤው ሀገሮች ኢንቨስተሮች እየተባሉ ለሚጠሩት እያቀራመተ ይቸበችብ ነበር፡፡ አሁንማ ኢትዮጵያ በነ ሳውዲና ቻይና ትሽከረከራለች።

በኢትዮጵያ ስለተላለፈው የሴኔት ውሳኔ ጉዳይ ዘ-ህወሀት ትኩረት ይሰጠዋል አላለሁ። ዘ–ህወሀት ግዙፍ የሆነ ገንዘብ በመመደብ ህሊናቸውን ለገንዘብ ብቻ ለሸጡት ወትዋቾች በማስታቀፍ ውሳኔውን በእንጭጩ ለማኮላሸት ወደኋላ እንደማይል አልጠራጠርም፡፡ ዘ-ህወሀት ከቀድሞው (ኤች. አር/H.R 2003ን እናስታውስ) ተሞክሮው በመማር በገንዘብ ለሚቀጥራቸው ወትዋቾች በየወሩ 50,000 ዶላር የሚከፍል ከሆነ በዩኤስ ኮንግረስ የሚተላለፈውን የሕግ ውሳኔ የውኃ ሽታ አድርጎ ሊያስቀረው ይችላል፡፡

በሴኔቱ ውሳኔ የዩኤስኤአይዲ/USAID የተጠያቂነት ጥያቄ፣

አንባቢዎቼ ቀደም ሲል የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ለሆነችው ለጋይሌ ኢ ስሚዝ እ.ኤ.አ መጋቢት 16/2016 በጻፍኩት ደብዳቤ በኢትዮጵያ ውስጥ በዩኤስኤአይዲ/USAID የሚተዳደረው እርዳታ ላይ ተጠያቂነት እና ግልጽነት እንዲኖር ጥያቄ ማቅረቤን ታስታውሳላችሁ፡፡ ሚስስ ስሚዝን እንዲህ በማለት ጠይቂያት ነበር፡

“በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገዥ አካል በእርዳታ ለሕዝብ የሚሄደውን 500 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለፖለቲካ ዓላማው እንዳይጠቀምበት ለማረጋገጥ እንዲቻል ምን ያስቀመጥሻቸው የተቀመጡ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች አሉ?

ከላይ የተጠቀሰውን ሰብአዊ እርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስተዳደር እና ከሙስና ለመከላከል ምን ዓይነት የተጠያቂነት ሂደቶች በስራ ላይ ውለዋል? በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ገዥ አካል ከተሰጠው 500 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ምን ያህሉን በእራሱ ስልጣን እንደሚጠቀምበት እና ምን ያህሉንስ በእራሱ ስልጣን ሊጠቀምበት እንደማይችል መጠኑ ይታወቃልን?“

ሴኔቱ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 20/2016 ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የፕሬዚዳንቱ የ2012 የሰብ ሰሀራ አፍሪካ ስትራቴጂን መሰረት ባደረገ መልኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ከየዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ጋር በመጥራት ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው እርዳታ ላይ መሻሻል እንዲኖር እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንዲጠይቃቸው የማድረጉን ጉዳይ በጉጉት የምጠብቀው ነገር ነው፡፡

እሰከአሁን ያልተመለሱ ጥያቄዎች፣

ስለሴኔቱ ውሳኔዎች በርካታ የሆኑ ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ዜጎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ጥያቄዎች መካከል እስቲ የሚከተሉትን  እንመልከት፣

1ኛ) ይህ የሴኔቱ ውሳኔ በአሁኑ ጊዜ እንዲተላለፍ የተደረገው ለምንድን ነው?

2ኛ) ለእነዚህ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሁሉ መወሰን የሚችሉት እነዚህ የሴኔቱ አባላት የት ገብተው ከርመው ነበር?

3ኛ) ይህ ውሳኔ በአሁኑ ጊዜ መወሰን ማለት ሴኔቱ ውሳኔውን በተግባር ለማሳየት እጅጌውን ከፍ ከፍ እያደረገ ነው ማለት ነውን?

4ኛ) ይህ በአሁኑ ጊዜ የተላለፈው ውሳኔ ዝም ብሎ ባዶ የአፍ ካራቴ እና የቃላት ጨዋታ እርባናቢስ የዥዋዥዌ ጨዋታ ንግግር ነውን?

5ኛ) በውሳኔው መተላለፍ ምክንያት በቀጣይነት ምን ሊከሰት ይችላል ተብሎ ይታሰባል?

6ኛ) ሴኔቱ በእርግጠኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብት ጥበቃ አያያዝ እንዲሻሻል የምሩን ጥረት እያደረገ እና ለተግባራዊነቱ በቆራጥነት እየሄደ ነውን?

7ኛ) ኢትዮጵያውያን ይህ የሴኔት ውሳኔ ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ሁኔታ ሊያሻሽል ይችላል ብለው ተስፋ ያደርጋሉን?

8ኛ) የሴኔቱ ውሳኔ ባዶ ንግግር ብቻ ሆኖ እና ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የማይደረግበት ሆኖ ሊቀር ይችላልን? ወዘተ፣ ወዘተ

ለእነዚህ ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ሁሉ ውሱን የሆኑ መልሶችን መስጠት ከባድ ነገር ነው፡፡

የዩኤስ የሕግ ሂደት ፕሬዚዳንቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣንን በተጎናጸፈበት ሁኔታ እና በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ሁለት የተለያዩ የሕግ አውጭ አካላት (ሴኔቱ እና የተወካዮች ምክር ቤት) ባለቡት ሁኔታ አንድን ሕግ በቀላሉ በማጽደቅ ወደተግባር የማሸጋገሩ ሁኔታ እጅግ በጣም ውስብስብ ነገር ነው፡፡ የአሜሪካ የሕግ ስርዓት መዋቅራዊ በሆነ መልኩ በጣም ዘገምተኛ እና ጥልቅ የማሰብ ሂደት የሚንጸባረቅበት እንዲሁም ለሕገ መንግስቱ እና ለውስጥ የሕግ ደንቦች ተገዥ ሆኖ የተቀየሰ ነው፡፡

ከልምድ ባለን ተጨባጭ መረጃ መሰረት የሰብአዊ መብት ጥበቃን እና ዴሞክራሲን ለማጠናከር በሚደረግ ጥረት ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እና ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ ለማድረግ መጠነሰፊ የሆኑ የውትወታ ጥረቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኤች.አር/HR. 2003ን (እ.ኤ.አ የ2003 የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እና የተጠያቂነት ድንጋጌ) ስንሰራ በነበረበት ጊዜ በጥልቀት እና በስፋት የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም ግን ያም ሆነ ለእኔ የሚያሳስበኝ ጉዳይ አይደለም፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መስራች አባቶች መካከል አንዱ ከሆኑት እና እ.ኤ.አ ታህሳስ 23/1776 እንዲህ በማለት ተናግረው ከነበሩት ከቶማስ ፔይኔ ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡

“የጭቆና አገዛዝ እንደ ገሀነም በቀላሉ ድል ሊደረግ የሚችል ጉዳይ አይደለም፣ ሆኖም ግን ይህ በስቃይ ላይ ያለ ምቾት በመካከላችን አለ፣ ይህም ማለት ግጭቱ እየመረረ እና እየከፋ በሄደ ቁጥር ድሉ ደግሞ የዚያኑ ያህል የጎመራ እና እንጸባራቂ ይሆናል፡፡ ርካሽ ሆኖ የምናገኘው ነገር እንዲህ የሚል ቀላል የሆነ ክብር እንሰጠዋለን፡ ማንኛውንም የእራሱን ዋጋ የሚሰጥ ሁሉ ውድ ነገር ነው…በችግር ወቅት ፈገግታ የሚታይበትን ሰው እወደዋለሁ፣ ምክንያቱም ከጭንቀት ጥንካሬን ተላብሷልና፣ እናም ጥንቃቄ የተሞላበት አስተሳሰብ እያደገ እና ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል፡፡“

ስለዚህ ፈገግ እላለሁ!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ሚያዝያ 17 ቀን 2008 .

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s