13. አማራነትና ኢትዮጵያዊነት – አሰፋ እንደሻው

74f3da87aa592b07926638fefa1936ecካሁን በፊት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪከ ስናጠና ዛሬ አገሪቱን የሞሏትን ህዝቦች አመጣጥ ለመመልከት ሞክረን ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ስለአማራውና ኦሮሞው ህዝብ ምንጭ ዘርዘር ያለ ውይይት አካሂደናል፡፡ ለጥናታችን መነሻ የሆኑን ባገር ውስጥና ባለም ዙሪያ ስለኢትዮጵያ ምርምር ያደረጉት አዋቂዎች ስራዎች ናቸው፡፡ የጥናታችን ውጤት አክሱም  ኢትዮጵያ–የህዝቦች ስብጥርና የአገዛዞች አወቃቀር አጭር ታሪክ በሚል በ2004 መልሶም በ2007 ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል፡፡ ዛሬ ያነሳነው ጉዳይ ያንን ጥናት እዚህ መልሶ ለማስፈር ሳይሆን በጉዳዩ ዙሪያ በተደጋጋሚ በክርክርም በመዘላለፍም በተለያዩ ወገኖች መካከል የሚቀርበውን ለመዳሰስና መረጃዎችን መሰረት ያደረጉ ትንታኔዎችን ለመሰንዘር ነው፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅግ እየተሰራጨ ስላለው “ሀበሻ” ስለሚለው ስያሜ ብንነጋገር; የ1894 አም የብሪታንያ ስንክሳር “ሃበሻ አገር” በሚል ስር እንዳሰፈረው “ሃበሻ አገር ወይም ባግባቡ ሃበሻ የሚለው ስያሜ አመጣጡ ሃበሽ ከሚል ያረብኛ ቃል ነው፤ ይህም ሲተረጎም ድብልቅ ወይም የሚያምታታ ማለት ሲሆን በህዝቡ የተደበላለቀ ባህርይ የተነሳ በአረቦች ላገሩ የተሰጠ ነው፡፡ ፖርቱጋሎች ሲመጡ ይኸንኑ ስም በላቲን “ሃበሻ” ወይም “ሃበሺኖስ” ወደሚል ለውጠውት የዛሬውን ስያሜ ይዟል፡፡ ሃበሾች ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ብለው ሲጠሩ አገራቸውን ደግም ኢትዮጵያ ወይም የኢትዮጵያ መንግስት ይላሉ፡፡” የህዝቡን ዘር በተመለከተ ይኸው ስንክሳር ይህንን ይላል፡- “የሃበሻ አገር ነዋሪዎች በርካታ የተለያዩ ነገዶችን ባካተቱ ቁርጥ ያሉ ዘሮች ይመደባሉ፡፡ አብዛኞች የነጭ ዘር ናቸው፣ ባጠቃላይም ሰውነታቸው በደንብ የዳበረና መልከመልካም፣ ቀጥተኛና በመጠኑ የተጠማዘዘ [ጠጉር]፣ ወደጥቁርነት የሚጠጋ ግን ደማቅ የወይራ ፍሬ ቀለም ያላቸው ናቸው…ትገሬ፣ አማራ፣ አገውና ወዘተ ውስጥ የሚኖሩት ከዚህ ዘር ናቸው፡፡”

ትረካው ሁለት የተምታቱ ነገሮችን ይዟል፡፡ ባንድ በኩል ሃበሻ የሚለው ስያሜ አረቦች ከቀይ ባህር ወዲህ ላለው ህዝብ ያወጡት መሆኑን በትክክል ጠቁሞ “ድብልቅ ወይም የሚያምታታ” ብለው የሚመለከቱትን ህዝብ እንዴት በአረብ ባህረሰላጤ ከሚገኙት ሴማዊ ህዝቦች ማለትም ራሳቸውን ከነጮች ጋር ከሚመድቡት ጋር እኩል “አብዛኞች የነጭ ዘር ናቸው” ብሎ ያርፋል; “ድብልቅ”ነት መቀየጥን አያመለክትም; መቀየጥ ደግሞ የዱሮውን ወይም የመጀመሪያውን ማንነት አይለውጠውም; ስለሆነም “ሃበሻ” የሚለው አጠራር ወይ ምንም ነጭነት ለሌላቸው ወይም ለተደባለቁት ብቻ ማለትም ነጭነታቸው ለቀረባቸው እንጅ ለነጮች የሚሰጥ ሊሆን የታቀደ አይመስልም፡፡ በዚህ አይነትማ በዛሬው የአረብ ባህረሰላጤ የሚኖሩትም ህዝቦች “ሃበሻ” ቢባሉ ምንም ችግር ባልፈጠረ! ነገር ግን ዱባና ቅል…አይነት ነው፡፡
ሁለተኛ፣ አብዛኞች የኢትዮጵያን ጥንታዊ የህዝብ ስብጥር በተመለከተ የታተሙ ትረካዎች በኢትዮጵያ ሰሜን ያለውን ህዝብ ከፍተኛ ክፍል ከአረብ ባህረሰላጤ የፈለሰ ነበር ስለሚሉ ሴማዊ (በተሸፋፈነ ቋንቋ “ነጭ”) አድርገው በመሳል ያገሪቱን ህዝብ ለሁለት ከፍለውታል፡፡ ሴማዊው ክፍል የስልጣኔው ምንጭ፣ የአገዛዙ ባለቤትና የነጭነት ባህርይ የተላበሰ ተደርጎ ኩሻዊው ወገን ደግሞ በተደራቢነትና በተከታይነት እንደኖረ ሲለፈፍ ኖሯል፡፡ ይህ ግን በማስረጃ የተደገፈ ሳይሆን በመላምትና በፈጠራ የተገጣጠመ አንዱ የውጭ ተመራማሪ ነኝ ባይ ለሌላው እየተቀባበሉ ሲያናፍሱት የቆየ እንደነበር እላይ በጠቀስነው ጥናታችን ተገልጾአል፡፡ በጣም ስመ ጥር ሆኖ ለብዙዎች ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ትምህርት መምህርና በምርምራቸው ስራ ላይ በፈታኝነት የሰራው ኤድዋርድ ኡሉንዶርፍ ሳይቀር ኩሻዊ ተብሎ የሚመደበውን

የኦሮሞ ህዝብ በድፍረት “ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ምንም ያበረከቱት የለም” ብሎ ኢትዮጵያውያን በሚለው መጽሃፉ ላይ አትቷል፡፡
ከአረብ ባህረሰላጤ ቀይ ባህርን ወደኢትዮጵያ ተሻግሮ አዲስ ግዛት ያቋቋመ አንዳችም የውጭ (ወራሪ; አሸናፊ;) ሃይል እንዳልነበረ የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ ከየት ብሎ የሴማዊ (ነጭ) ሰራዊት የበላይነት ቀርቶ የተስፋፋ ስፍራ እንደያዘ የሚተረከው ሁሉ ባዶ ስብከት ሆኖ ቀርቷል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች እንደተደረገው ሁሉ ጥቂት የደቡብ አረቢያ ስደተኞች ወደኢትዮጵያ ሸሽተው እንደኖሩ፣ ከሌላው ህዝብ ጋር ተደባልቀው ሰምጠው እንደቀሩ ግን ምልክቶች ተገኝተዋል፡፡ ይልቁንም አክሱማውያን ቀይ ባህርን ተሻግረው ደቡብ አረቢያን በተለይም ሳባውያንን አሸንፈው እንደገዙ የታሪክ ማስረጃዎች ሞልተዋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ምናልባት የህዝብ ፍልሰት ከነበረ ከኢትዮጵያ ወደመካከለኛው ምስራቅ ብሎም ወደሌላው አለም እንደተካሄደ ዛሬ በመላው አለም ሊቃውንት እየታመነበት መጥቷል፡፡ በደራሲው ምርምርና እስካሁን በታተሙት የዘር ምንጭ ጥናቶች ላይ ተመስርቶ በሚሰጠው ግምት ከኢትዮጵያ ወደመካከለኛው ምስራቅ የነጎደው ህዝብ በአብዛኛው የአባይን ወንዝ የተከተለ ይመስላል፡፡ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ገናና ሆኖ የወጣው የኢንካ ስልጣኔ ሳይቀር የሰፈረው ህዝብ ምንጭ ይኸው ከኢትዮጵያ ተነስቶ በመካከለኛው እስያ ብሎ በአላስካ ላይ ወደታች የተምዘገዘገው ፍልሰት ነበር፡፡ ይህ ትረካ ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም የዘር ጥናት ተመራማሪዎች ጭምር በየቀኑ እያረጋገጡት ነው፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ ምንጮች በነጭና በጥቁር ዘሮች ከፍሎ ከሚወተወተው ወሬ ተጠቃሚ የነበረው የአገው ነገስታትን ይዞታ ለማናጋትና ስልጣኑን መልሶ በአክሱማውያን እጅ ለማስገባት በተካሄደው ዱለታ ውስጥ “የሶሎሞናዊው ሃረግ” ተመዞ ወጥቶ ያንን ተመርኩዞ በትረ መንግስቱን የጨበጠው ወገን ነው፡፡ ይህም ባንድ በኩል በክርስትና ሃይማኖት መምጣት ያገሪቱ ቀደምት ነዋሪዎች (አገዎች) በክርስትናና በጥንታዊ (ኦሪት) እምነት ከመከፈላቸው ጋር ተሸናፊዎቹ ኦሪታውያን ለቀው (ፈልሰው) ወደደቡብ ምእራብ (ዳሞት)ና ወደስሜን እንዲሸሹ ከተደረጉ ወዲህ ስልጣኑን መልሰው ለመረከብ ሁሌም መታገላቸው ስላልበረደላቸው በጭራሽ ተስፋ ቆርጠው እንዲተው ለማድረግ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ክርስትናን ከመቀበላቸው በላይ በያቅጣጫው እምነቱንና ያገሪቱን ግዛት በማስፋፋት ስራ የተጠመዱትን የአገው ነገስታትም የስልጣን ባለቤትነታቸውን መሰረት ለማናጋት በጠቅላላውም በስልጣኑ ላይ ለሚነሳው ማናቸውም ፉክክር በሃረጉ ዙሪያ ለተደራጁ የርእዮታለም ድጋፍ ለማብጀት የተቀየሰ ነበር፡፡ ለንግስና ማእረግ ሴማውያን መሆን ብቻ ሳይሆን በመንበረ ዳዊት (ሰለሞን) ላይ የመቀመጥ ችሎታና ውልደት እንደሚያሻ መናፈሱ በቤተ ክህነት ጭምር ጸድቆ በኢትዮጵያው ቤተክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ በአናት ላይ የሚቀመጡትን የሚመርጡት የኮፕት ቀሳውስት ርእዮታለማዊ ድጋፉን ማስጨበጫ ስነጽሁፍም (ክብረ ነገስትን) በፈጠራ ደርሰው እስኪሰዱ የተቀነባበረ መመሳጠር ነበረበት፡፡ መጀመሪያ በጥንቱ ቋንቋ በግብጽኛ እስክንድርያ ላይ ወደ7ኛው መቶ አመት አካባቢ ተዘጋጅቶ በምስጢር ወደአክሱም ተልኮ ቆይቶ ቆይቶ አገዎች ስልጣኑን ሲተው ወደእግዝ ተተርጉሟል፡፡ ስልጣኑ ከአገው ነገስታት ተወስዶ ወደ አክሱማውያን (ወይም በራሳቸው ምርጫ ወደ ”ሰሎሞናዊያን”) ከተዛወረ በኋላ የሴምና የካም ዘሮች የገዥና ተገዢነት ድርሻ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ መተረኩ ቀጥሎ እስከ አጼ ሃይለ ስላሴ ዘመን ቆይቷል፡፡

በክብረ ነገስት አማካይነት ርዮታለማዊ ልባስ የተጎናጸፈውና በተጭበረበረ ታሪክ የተሸፋፈነው የሁለት ዝርያዎች (ሴማዊና ኩሽ) ጎን በጎን በኢትዮጵያ መኖር ጉዳይ የሚናድበት አዲስ አቅጣጫ በቅርብ ተከፍቷል፡፡ ተመራማሪዎች ስለኢትዮጵያውያን ትውልድ ሃረግ ባደረጉት ቀዳሚ ጥናት ከግማሽ በላይ የሆኑት ከየመንና አረብ አገሮች ይልቅ ከእስራኤልና ከሶርያ ጋር የበለጠ መመሳሰል እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ከ60 ሺህ አመታት በፊት ከአፍሪካ ወደውጭ የመሰደድ እንቅስቃሴም “ከኢትዮጵያ ወይም ከግብጽ” እንደተጀመረ፣ ምናልባትም ከደቡብ አረቢያ ተሰደው ከመምጣታቸው ይልቅ በምስራቃዊው የሳሃራ ጫፍ አካባቢ (ግብጽ፣ ሱዳን) ሰፍረው እንደኖሩ፣ በደቡብ አረብና በኢትዮጵያ አካባቢ የቋንቋ መመሳሰልም በይበልጥ ከባህል (ለምሳሌ የንግድ) ግንኙነት የመነጨ እንደሆነ፣ በሳባዊና በኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች መካከል መያያዝ መፈጠሩ ዱሮም ባካባቢው (ኢትዮጵያ) ነባር ህዝቦች ውስጥ ሴማዊነት ስለነበር ያንን ሁኔታ መዘንጋት እንደማይገባ የሚያመለክቱ በርካታ ስራዎች አሉ፡፡ ሄዶ ሄዶ ግብጻውያን ከየመናውያን ይልቅ ለኢትዮጵያውያን (ሴማዊም ኩሻዊም) በዘራቸው እንደሚቀርቡ፣ አልፎም ሞሮኳውያን፣ ቤድዊኖችና ዱሩዞች ሳይቀሩ እንደዚሁ ከየመኖች ይልቅ እንደሚጠጉ ጥናቶች እያመለከቱ ነው፡፡

የሰው ልጅ እንዴት ብሎ ከኢትዮጵያ ፈልቆ ወደሌላው አለም እንደተሰራጨ ለመተለም የሚደረገው የዘር ህዋስ የማጥናት ስራ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ እስካሁን በተገኙት አመልካች ውጤቶች ግን ከደቡብ አረብ የፈለሰ ህዝብ መኖሩ ቢያንስ ቢያንስ እጅግ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ከዚያ አልፎ የደቡብ አረባውያን ያካበቱትን ስልጣኔ ተውሶ ባገሪቱ ሰሜን ክፍል የተቆናጠጠ የአገዛዝ አይነት አልተገኘም፡፡ እስካሁን በተደረጉ ቁፋሮዎች የሃ ላይ ገናና የነበረው የዳማት (ምናልባትም ዳሞት) አገዛዝ ወይም ስልጣኔ በቀል እንደነበረ አመልክተዋል፡፡ የዳማት መፈራረስ ከሱ ቀጥሎ የነበረው የአክሱም አገዛዝ እንደደረሰበት አይነት ከበስተሰሜን በኩል ለረዥም ጊዜ የቆዩት ተቀናቃኞች ስራ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡

ወጣም ወረደ የዳማት መፍረስ ያስከተለው የአክሱም አገዛዝ ባህርይና በስሩ የነበረው የህዝብ ስብጥር በድንገት ከሰማይ ዱብ ያላለ መሆኑን መከራከር አይቻልም፡፡ አክሱምን ያቋቋመ አንድ የህዝብ አይነት ወይም ገናና ንጉስ ባላመሆኑ ከዳማት ፍርስራሽ የተሰባሰበው ተቋም የቀደሙትን ትውፊቶች መልሶ ሳይጨብጣቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ላይ የሃና አክሱም በጣም ተቀራራቢ ቦታና የአየር ንብረት የነበራቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም ሁለቱም አገዛዞች አንድ ቋሚ ወይም ተወራራሽ የሆነ ባህርይ እንደተቀባበሉ መናገር ይቻላል፡፡ ከዳማት (ወይም ዳሞት) በፊት ስለነበረው ሁኔታ ብዙ የምናውቀው ባይኖርም ምናልባት የፑንት ስልጣኔና ሌሎች ያካባቢው ስብስቦችም ለትውፊቱ ምንጭነት ወይም መንደርደሪያነት ሳያገለግሉ እንዳልቀሩ መገመት ያስኬዳል፡፡

ሄዶ ሄዶ የዳማትና የአክሱም አገዛዞች መሰረቶች የተለያዩ ግን በህብረት እየተደጋገፉ የሚኖሩ ህዝቦች (ነገዶች፣ ጎሳዎች ወዘተ) ይመስላሉ፡፡ ለህብረታቸውና ለመረዳዳታቸው የተጠቀሰው የሰሜን ወራሪ ወይም ተቀናቃኝ ህዝቦች (ቤጃዎች ምናልባትም ሌሎች ጋር ተዳምረው;) ተደጋጋሚ እንዲያውም የማያቋርጥ ጥቃት እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ቤጃዎች በጦርነት ችሎታቸው የላቁ ስለነበሩ ለግብጾች የጎን ውጋት ሆነው መኖራቸው ሲታወቅ ከነሱ በስተደደቡብ ለነበረው የዳማትና የአክሱም አገዛዞች የተለየ ዝንባሌ የሚያሳዩ አይሆኑም፡፡ ስለዚህ የማያቋርጠውን ወረራቸውን ለመመከት የሚያስችል ማህበራዊና ወታደራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ስርአት ማብጀታቸው የማይቀር ነበር፡፡ ከዚህም በላይ የዳማትና የአክሱም አገዛዞች የሚፈሩትን የወረራ ጥቃት ለመቋቋም ሁልጊዜ መዘጋጀቱ ብቻውን ስለማይበቃቸው እነሱም አጻፋውን ለመመለስ የጦርነትና የወረራ ባህል እየተላበሱ መሄዳቸው አስገዳጅ ውጤት የሆነ ይመስላል፡፡

በአክሱም አገዛዝና ስልጣኔ ውስጥ ሰፊ ድርሻ ካበረከቱት ህዝቦች ውስጥ አገዎች ዋና እንደነበሩ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን ሌሎችም በተደራቢነትና በአጋርነት ይወሳሉ፤ ከነዚህ ውስጥ አጋመ የሚባል ህዝብ በስተምስራቅ እንዲሁም ወለቃ የሚባል በስተምእራብ እንደነበሩ ይተረካል፡፡ ሌሎች ህዝቦች እንደነበሩ ማረጋገጫ ቢኖርም ስማቸውና የነበሩበት ቦታ ስለተለዋወጠ በርግጠኝነት ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ያገዛዙ አባሪነት ወይም የባለቤትነት ድርሻ ሳይኖራቸው በተቃራኒነት ግጭት እየፈጠሩ ከአክሱም ጋር ይተናነቁ ከነበሩት መሃል ስሜኖች በስተምእራብ፣ አግአዝያን በስተሰሜን የሚባሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የአክሱም አገዛዝ ካካባቢው ህዝቦች ጋር የነበረውን ግንኙነት በስምምነት ብቻ ሳይሆን በጦርነትና በማስገበር ስላዋቀረው የተደራጀ ጦር ሃይል አሰማርቶ ሁሌም ግዛቱን ለመጠበቅና ለማስፋት ይራወጥ ነበር፡፡ በስሩ ሆነው ግን እያመጹ የሚያስቸግሩትን ለመቆጣጠር ዋናውን ጦር በየስፍራው ማስፈር ብቻ ሳይሆን ተቀማጭ ያካባቢ ምልምሎችን ያበጅ ነበር፡፡ የዋናው ጦርና ያካባቢ ምልምሎች ቅንጅት የአክሱም ህልውናና መስፋፋት ቋሚ መሳሪያ፣ ያገዛዙ ባህርይ ቀራጭ ሆነ፡፡ ጦሩ በያቃጣጫው ዘምቶ፣ አስገብሮ፣ ያካባቢውን አስተዳደር በአካባቢው ሰዎች እጅ አስገብቶ መስራቱ ለህዝቦች መንቀሰቃስ፣ መፍለስና መደበላለቅ በር ከፍቶ ነበር፡፡ የጦር ሰራዊቱና የስምሪት ተግባሮቹ በተለይ ከህብረተሰቡ የተውጣጡ ነገር ግን አገልግሎታቸው ከያሉበት ተሰብስበው በጋራ እንዲኖሩና እንዲሰሩ ያስገደዳቸው በመሆናቸው ወደአንድ አካልነት እየተለወጡ እንዲሄዱ አደረጋቸው፡፡ ካንድ የተለየ ህዝብ የተመለመሉና አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ባለመሆናቸው የየራሳቸውን ባህልና ቋንቋ እየተው ነገር ግን የጋራ መግባቢያ ቀስበቀስ እየፈጠሩ እንዲገኙ ተገደዱ፡፡ ገዥዎቻቸው ግእዝ (በጥቂቱም የጽርእ ቋንቋ) ማወቃቸው ርግጠኛ ቢሆንም ሰራዊቱ መጀመሪያ ጉራማይሌ የመሰለ መግባቢያ (የመገበያያ ቋንቋ) ፈጥሮ ያንን በያለበት መጠቀምና ሌላውን ማስለመድ ተያያዘ፡፡

ከዚህ በፊት ይህንን ሂደት አክሱም  ኢትዮጵያ–የህዝቦች ስብጥርና የአገዛዞች አወቃቀር አጭር ታሪክ በሚለው ላይ ስለተረክነው እንደገና ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ የአማርኛ ቋንቋ አወላለድ በዚህ አኳሃን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አማራ የሚባል ህዝብ የትም ቦታ ስለመኖሩ ማስረጃም ፍንጭም አለመኖሩ በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በዚያ ስም የሚጠራ ህዝብ በአክሱም ሆነ ከዚያ በፊት ባለፈው ዘመን አለመኖሩ በዘር ደረጃ አማራ ሆኖ የተፈጠረ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ይህ በመላ ምትና በጋለ ስሜት በመወናጨፍ የሚደረስበት እውነት አይደለም፡፡ ፍቅሬ ቶለሳ በሚያስገርም አኳኋን እንደሚለው “የአማርኛ ቋንቋን በተመለከተ ከ3000 አመታት በፊት መወለድ ጀምረ፡፡ እንዲያውም ከተፈጠረ ከግእዝ በፊት አስቀድሞ ረዥም ጊዜ አድርጓል፡፡” ጨምሮም “ ቀዳማዊ ምኒልክ ሲለወለድ አማሮች ንጉስ ሰሎሞን ስለልጁ ምን እንደሚል ይጠይቁ ነበር፣ እናም ‘ምን ይልክ፣ አባትህ’ አሉት፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ከ3000 አመታት በላይ ባይኖር ኖሮ እንዴት ብለው ከ3000 አመታት በፊት ምኒልክን ‘ምንይልክ’ ይሉት ነበር;” ይላል፡፡ በግልጽ አነጋገር የቋንቋው አመጣጥ ከታሪክም ከማህበራዊ ሳይንስም ሳይሆን አይንን ጨፍኖ ከመተንበይ የሚገኝ ቢሆን ምን ያህል ጭቅጭቅና ውጣ ውረድ ይቀርልን ነበር፡፡ እንዲህ ካንድ ስም አሰጣጥ ላይ የሚገኝ ከሆነማ ምኑን ምርምር አስፈለገው፡፡ ለነገሩ ያህል ይህ ትረካ ስለዳግማዊ ምኒልክ እንጅ ስለዚያኛው አይደለም፡፡

ይሁንና አማራ የሚባለው ህዝብ ከቋንቋው መፈጠርና መበልጸግ ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ብርሃኑ አበጋዝ “የኢትዮጵያ አገዛዝ ስልትና እንቆቅልሽ የተሞላበት አማራ” በሚል ጽሁፍ በዘልማድ ምንም ማስረጃ ሳይቀርብ “አማራ” እየተባሉ የሚጠሩትን አካባቢዎች ከዘረዘረ በኋላ ዛሬ “አማራ” የተሰኘው ቃል በሶስት አይነት አጠቃቀም እንደሚውል ይናገራል፡፡ አንዱ የሃይማኖት መለያ ሲሆን፣ ሁለተኛው ብሄራዊ ማለትም የኢትዮጵያዊነት አመልካች፣ የፖለቲካዊ ማንነትን መግለጫ፤ ሶስተኛው የቋንቋውን ተናጋሪዎች የሚጠቁም ነው፡፡ ሁለተኛውን ገንጥሎ የተዳቀሉ ክፍሎች፣ በይበልጥ በከተሞች የሚኖሩት የሚጠሩበት አድርጎ ያወጣዋል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሃሳቡ ማስረጃ የለውም፡፡ የግምት አነጋገር ሰነዘረ እንጅ፡፡ ገና ከመነሻው የአማራ ህዝብን ማንነትና አመጣጥ ሳይመረምረው በይበልጥም የዛሬውን ትቶ የዱሮውን ሁኔታ ሳያጤነው መጨበጫና መቋጠሪያ የሌለው ትረካ ያቀርባል፡፡

በርግጥ “አማራ ነህ እስላም;” የሚለው የቆየ የዘልማድ አጠያየቅ እንደሚያመለክተው “አማራ” ማለት ለዘር (በውልደት ዝምድናው ለሚታወቅ) የተሰጠ ስያሜ ከመሆኑ በፊት የእምነት መለያ ሆኖ ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡ አሁን አሁን ያ አጠቃቀም እየቀረ “ክርስቲያን ነህ እስላም” ወደሚለው ተለውጧል፡፡ አማርኛ የሚናገር ሰው እስላምም መሆን ስለሚችል የቀድሞው አጠያየቅ ምናልባት በገጠሩ አንዳንድ አካባቢዎች ብቻ እስካሁንም ይነገር እንደሆን እንጅ በከሞች እጅጉን አይሰማም፡፡ በግልባጩ ደግሞ አማርኛ ስለተናገሩ “አማራ” ነው የሚያሰኝ ግምት እየጠፋ ሄዷል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሊ ሃብተ ወልድ ጄኔራል ታደሰ ብሩን በአማራነት መድቦ ስለኦሮሞዎች መማር ያለውን ስጋት ሲያካፍለው በዚያ የተሳሳተ ግምት ውስጥ እንደነበር ልንገምት እንችላለን፡፡
የብርሃኑ አበጋዝ ሁለተኛው የአማራነት ፍቺ እንዳልነው ማስረጃ ካለማቅረቡ ሌላ በውስጡ ብዙ ችግር አለበት፡፡ ዛሬ አማራ ተብሎ “ክልል” ተበጅቶለት በአንድ አስተዳደር ስር የገባው ህዝብ በሙሉ የዘር መሰረቱ የተደበላለቀ ነው፡፡ በታሪክ፣ ከመጀመሪያው (ካክሱም ዘመን) አንስቶ እስከዛሬ ድረስ፡፡ ስለሆነም ከያቅጣጫው በዘመቻ፣ በፍልሰት፣ በአስተዳደራዊ ምስቅልቅልና በሌሎችም ምክንያቶች አማርኛ ተናጋሪ ሆኖ የወጣው ህዝብ በአንድነት ተመድቦ “አማራ ነህ” መባሉ የጽንሰ ሃሳብና የፖለቲካ ችግሮች አሉበት፡፡ አንድ ህዝብ ለማንነቱ መግለጫው ከሁሉም በላይ ቋንቋ ይሁን እንጅ በብሄርነት ለመቆም እንዲችል የስነ ልቦና ውሁድነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ (ይህን ጉዳይ በተመለከተ በዚሁ መጽሃፍ ቁጥር 12ን ያንብቡ፡፡) ታዲያ በከተሞች ባብዛኛው የአማርኛ ተናጋሪነት እጅግ አስፈላጊና ለመኖርና ለመስራት አስገዳጅ እንደመሆኑ ባገሪቱ በሙሉ ያሉ ከተሞች የአማራ ከተሞች ናቸው ማለት አያስኬድም፡፡ ህዝቡም ቢሆን ሁኔታው እያስገደደው ካልሆነ በስተቀር ማንነቱን በቋንቋው ብቻ የሚለካና አማራነትን የሚቀበል ወይም የሚጠቅስ አይሆንም፡፡

ስለሆነም የብርሃኑ አበጋዝ የአማራነት መለያ ቁጥር 2 ከፊል ገጽታውን ወደሙሉነት የማሸገገር ያስተሳሰብ ዝላይ ነው፡፡ ማለትም ከአማራው ውጭ አንዳንድ አካባቢዎች “ኢትዮጵያዊነት”ን መቀበላቸው በሁሉም ዘንድ የተስፋፋና ስር የሰደደ ክስተት አይደለም፡፡ ባንድ በኩል፣ ብዙ ድግግሞሽ ውስጥ ሳንገባ፣ እንኳን አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ማዋደድ (ማጣመር፣ ማቀላቀል) ይቅርና በተለያዩ ህዝቦች መደበላለቅ ብቻ ወደአማራነት መሸጋገር ተችሏል ብሎ መናገር መሳሳት ነው፡፡ የአማራ ህዝብ እየተባለ የሚጠራው ራሱን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ያላንዳንች ችግር ቢቀበልም ሁሉም “አማራ ነን” ማለታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ በዚህ ላይ በአገዛዙ ላይ የበላይነት ኖሮት ለዘመናት የቆየው ገዥ ክፍል ራሱን በአማራነት እየቀረጸ መምጣቱና የጥቅም ክፍፍሉ በዚያው መልክ መወሰኑ እየገፋፋቸው “አማራ ነን” ማለትን የሚመርጡት አማርኛ ተናጋሪ ግን ሌላ ቋንቋ የናት ቋንቋቸው የሆኑ ዜጎች እውነተኛ ማንነት ጉዳይ ግልጽ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ያገሪቱ ትልቁ ችግር ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ከ1983 ወዲህ ህዝቡ በያለበት የራሱን ማንነት እንዲያበጃጅ በተፈጠረለት እድል ተጠቅሞ በሚያደርገው መነቃነቅ ስንቱ ነው በትክክል ይህን ሊረዳውና ወደሚመኘው ሊሸጋገር

የቻለው; የሚችለውስ; (የስልጤዎችንና መሰል ህዝቦች መተራመስ በአብነት ማንሳት ይበቃል፡፡)
በቅርቡ በካናዳ በተደረገ የሬዲዮ ቃለ ምልልስ አቶ አሰፋ ጫቦ በጋሞ ጎፋ ውስጥ ስላጋጠሙት “ነፍጠኞች” ያወራው አስደናቂ ነገር እዚህ ላይ ትዝ አለን፡፡ በሱ አመለካከት በምኒልክ ስር በአዛዥነት እንጅ በተራ ወታደርነት (በ“ነፍጠኛነት”) በጋሞ ጎፋ ሆነ በደቡብ ባጠቃላይ የዘመቱ ባብዛኛው ኦሮሞዎች ነበሩ! በጋሞ ጎፋ የነበሩትን አዛዦቹን ከነስማቸው እየዘረዘረ አማራ መሆናቸወን ሲያወሳ ሌሎች ግን ኦሮሞ እንደነበሩ እንደደረሰበት ተርኳል፡፡ ለካስ በደርግ ዘመን “በነፍጠኞች” ውስጥና መካከል እርስ በርስ መጋጨት ተፈጥሮ አቶ አሰፋ ጫቦ በአገር አስተዳዳሪነቱ ለማስታረቅ ባደረገው ጥረት ሁለቱም ተቀናቃኞች ስማቸው እስከአያታቸው ሲዘረዘር ኦሮሞ ነበሩ! ተከሳሾች (ጠብ ፈጣሪዎች) ኦሮሞነታቸውን ሸሽገው በአማራነት ራሳቸውን እንደመደቡ ሲተርክ የጥቅም ጉዳይ አይሎባቸው ከገዥዎች ጋር መወገናቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጾዋል፡፡

በተገላቢጦች መልክ ብርሃኑ አበጋዝ አማሮች ከሁሉም ህዝቦች በላይ የዘር ጉዳይ እንደማያስጨንቃቸው፣ ገዥዎቻቸውም (የሌቪንን ትንታኔ ተውሶ) ትልቅነታቸው ብዙ-ዘርን የሚያቅፍ (በዘር ሳይሆን በማህበረሰብነት) የአመራር ስልት እየተጠቀሙ የውጭ ወራሪን መቋቋማቸውንና የባህሎችን መጠጋጋት አከናውነው የታላቋን ኢትዮጵያ እቅድ ማራመዳቸውን ይጠቃቅሳል፡፡ ነገር ግን የአማራ ህዝብ ማንነት ገና በመዋቀር ላይ እንዳለ፣ ከተለያዩ ህዝቦች መቀያየጥ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሂደቱ እንዳልተጠናቀቀ እንጅ ከሌሎች ህዝቦች የተሻለ ወይም የተለየ ሰብእና (አገር የመገንባት ተልእኮ ወዘተ) ስላለው እንዳልሆነ አልታየውም፡፡ ዋለልኝ መኮንን በጉልበት ወደአማራነትና ኢትዮጵያዊነት የሚያመራውን የአገዛዙን አሰራር ከተቃውሞ ጋር የዘረዘረውን ብርሃኑ አበጋዝ በምጸት መልክ አንስቶ ጭራሽ የረሳው መልካም ነገር እንደነበርና (የምግብ አይነቶች፣ አንዱ ዘር ከሌላው ጋር መጋባት፣ “ይሉኝታ”) ያ የሚያወግዘው የእድገት ጎዳና የተለያዩ ባህሎችን ወደ “ኢትዮጵያዊነት” እንደሚሸጋግር ያትታል!

ለማጠቃለል፣ ለብዙ የብሄር/ብሄረሰብ ማንነትና ነጻነት ጉዳይ ተሟጋቾች አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ዛሬ ላይ ቆመው ወደኋላ ተመልክተው የዱሮውን እንደገና በፈለጉት አኳኋን ለመቅረጽ መፈለጋቸው ነው፡፡ የዛሬውን ምን ለማድረግ ከመወሰናቸውና የወደፊቱን ለመተለም ከማሰላሰላቸው በፊት የነበረውንና በታሪክና በፖለቲካ የተከናወነውን ከነምክንያቶቹ ፈልፍለው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአማራው ህዝብ አነሳስ፣ ምንነትና የወደፊት እድልም እንደዚሁ አስቀድመው በጭንቅላታቸው ውስጥ ባስገቡት ስሜትና በደም ፍላት የሚፈረድ አይደለም፡፡ ታሪኩን ያጥኑ፣ እስካሁንም ኢትዮጵያን የሚወሰውሷትን የእድገት ጎዳናዎችና የእንቅፋት ጉድጓዶች ይለዩ፡፡ ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰው የሌቪን አስተያየት ከአክሱም አገዛዝ ብሎም ከዛጉዌ ነገስታት የተወረሰ አመራር እንጅ ከአማራው ክፍል የተቀመመ እንዳልነበረ ያገኙታል፡፡

አሰፋ እንደሻው

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s