የዞን ፱ ጦማርያን

ዞን ፱ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ “ለማንም ወገንተኛ ያልሆነ ተረክ ለመፍጠር” አልመው በአማርኛ ቋንቋ የሚጽፉ ዘጠኝ ገለልተኛ ጦማርያን ስብስብ ነው፡፡ መፈክራቸው “ስለሚያገባን እንጦምራለን” ይላል፡፡ ጦማሪያኑ የተዋወቁት በማኅበራዊ ሚዲያ እና በግል ጦማሮቻቸው እንቅስቃሴዎቻቸው ነው፡፡ ኋላ ላይ ጦማሪያኑ (ከሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ አራማጆች ጋር) ቤሩት፣ ሊባኖስ ቤተሰቦቿን ለመርዳት በቤት ሠራተኝነት ሂዳ በአሠሪዋ የተገደለችውን ወይዘሮ ዓለም ደቻሳ ቤተሰቦች ለመርዳት ባዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ኮሚቴ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኙ፡፡ የዞን ፱ ጦማር ስብስብ የተመሠረተው እንዲህ ዓይነቶቹ ችግሮች የሚቀረፉት በሕዝባዊ ውይይት ነው ብለው አባላቱ በማመናቸው ነው፡፡

ዞን ፱ የኢትዮጵያ ልዩ ሥሟ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች የታሰሩበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስምንት ዞኖች አሉት፡፡ ቃሊቲ ውስጥ የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞች ከወኅኒ ቤቱ ጊቢ ውጪ ያለውን የአገሪቱ ክልል በሙሉ ሐሳብን የመግለጽ እና የፖለቲካ ነጻነት የተገደበበት መሆኑን ለማመልከት ዘጠነኛው ዞን እያሉ ይጠሩታል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰፊ እስር ቤት ውስጥ ነው ያለው ማለታቸው ነው፡፡ ጦማሪያኑ ይህንን የተረዱት እና መጠሪያውን ለጦማራቸው ያዋሉት በወቅቱ የታሰረች ጋዜጠኛ ሊጎበኙ ቃሊቲ ሄደው ነው፡፡

የዞን ፱ ጦማር በግንቦት ወር 2004 ተመሠረተ፡፡ የጦማሪያኑ ስብስብ ዋና ዋና ሥራዎች በሦስት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ እነርሱም፡-

• በሕገ-መንግሥታዊ፣ ምጣኔሀብታዊ፣ ትምህርታዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት አዘል እና ሐተታዊ ጽሑፎችን በጦማራቸው ላይ መጻፍ፣

• በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥትም ይሁን መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የሚፈፀሙ የሰብኣዊ መብት እና የሕግ ጥሰቶችን መዘገብ፣

• የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አያያዝን እና የፍርድ ሒደት ይፋ በማድረግ ሕዝባዊ ትኩረት መሳብ፡፡

ለዚህም፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዘመቻዎችን በቡድን አድርገዋል፡፡ በተናጥልም፣ እያንዳንዳቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጽሑፎችን በመጻፍ አጋርተዋል፡፡ ጦማሩ ከዞን ፱ ጦማሪያን በተጨማሪ ለሌሎችም ሐሳባቸውን ማንፀባረቅ የሚችሉበትን ዕድል ሰጥቷል፡፡

የዞን ፱ ጦማር ግንቦት 2004 በተከፈተ በሁለት ሳምንት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታይ ታግዶ ነበር፡፡ የጦማሩን አድራሻ በመቀያየር ለመቀጠል ያደረጉት ሙከራ አዳዲሶቹ የጦማሮቹ አድራሻዎች እየተዘጉ በመቀጠላቸው ስኬታማ አልሆነም፡፡ እንደአማራጭ የማኅበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም ለአንባቢዎቻቸው ተዳራሽ ለመሆን ችለዋል፡፡ ስድስት የዞን ፱ ጦማርያን እና ከነርሱ ጋር ቅርበት ያላቸው ሦስት ጋዜጠኞች ሚያዝያ 17፣ 2006 ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ፣ ሐምሌ 11፣ 2006 ‹የሽብርተኝነት› ክስ ተመሥርቶባቸዋል፤ ክሱ ‹በሕግ ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መመሥረት፣ የሽብር ጥቃት ለማድረግ መዘጋጀት እና የመንግሥት ደኅንነት ኃይሎች እንዳይደርሱባቸው የዲጂታል ደኅንነት ሥልጠና መውሰድ› የሚሉ ነጥቦችን ይዟል፡፡ የክስ ሒደቱ ከ15 ወራት በላይ ከፈጀ በኋላ አምስቱ፣ ማለትም ሁለት ጦማርያን እና ሦስቱ ጋዜጠኞች፣ ክሳቸው ሐምሌ 1፣ 2007 ተቋርጦ ከእስር በድንገት ተፈትተዋል፡፡ ፍቺያቸው፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ በመሆኑ አንዳንዶች ጦማሪያኑ እና ጋዜጠኞቹ እንዲፈቱ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ግፊት አድርጓል ብለው ገምተዋል፡፡

ከሦስት ተጨማሪ ወራት በኋላ፣ በጥቅምት 5፣ 2008 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀሪዎቹን ጦማሪዎች ከሽብር ነጻ ናችሁ በሚል አሰናብቷቸዋል፡፡ ነገር ግን፣ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ አምስቱ ጦማሪያን አሁንም ጉዳያቸው በእንጥልጥል ላይ ነው፡፡ ሦስቱ የዞን ፱ መስራች ጦማርያን በአሁኑ ወቅት በስደት ላይ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ስድስት በአገር ውስጥ ያሉ ጦማርያን እና አብረዋቸው ታስረው የነበሩት ሦስት ጋዜጠኞች ከአገር የመውጣት መብታቸውን በሕገ-ወጥ መንገድ ተገፍፈዋል፡፡

ጦማር: http://zoneniners.com

ፌስቡክ: facebook.com/Zone9ers

ትዊተር: twitter.com/Zone9ners

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s