ግልፅ ደብዳቤ ለአቶ ባራክ ኦባማ – አንዱዓለም አራጌ (ከቃሊቲ) ትርጉም – መስፍን ማሞ ተሰማ (ሲድኒ)

የተከበሩ ፕሬዚዳንት ኦባማ
እኔ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ህይወት ቤተሰቡን ሲያስተዳድር የኖረና አሁንም የሚኖር የድሃ ገበሬ ልጅ ነኝ። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ቤተሰብ ለመበልፀግ የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በአግባቡ ሲስተናገዱ ነው ብሎ – በሩቅም ቢሆን – በማመን የአባቱንም ሆነ የራሱን የህይወት ዘይቤ ያልቀየረው የዚያ ገበሬ ልጅ ነኝ፤ እኔ። ክቡር ፕሬዚዳንት፤ በኢትዮጵያ አገዛዝ በሽብርተኝነት ተፈርጄ ራሴን ከማግኘቴ በፊት – በዩኒቨርሲቲ ካምፓስ በነበርኩበት ወቅት እንደ ተማሪው መሪነቴም ሆነ ሁዋላም እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኛ መሪነቴ በነበረኝ ህልም የህዝብን የኑሮ ሁኔታ በተሻለ ለመለወጥ የጣርኩ የዚያ ገበሬ ልጅ ነኝ። ከኢትዮጵያ የሰቆቃ እስር ቤቶች መካከል ቀንደኛ በሆነው ቃሊቲ ወህኒ ቤት ዕድሜ ልክ ተበይኖብኝ በመማቀቅ ላይ እገኛለሁ።

Andualem-Aragie-5ክቡር ፕሬዚዳንት፤ የሰው ልጅ መገኛ ዕምብርት (ራስዎም ሉሲን በጎበኙበት ውቅት እንዳረጋገጡት)፤ የጥንታዊ ሥልጣኔና የገዳ ዴሞክራሲ ባለቤት፤ ከቶም በቅኝ አገዛዝ ሥር ካልወደቁት ሁለት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ፤ ከድፍን አፍሪካ የራስዋ መለያ ፊደል ያላት ብቸኛ ሀገር በመሆንዋ – ኩራት የሚሰማው <em>‘ሽብርተኛ’ </em>ነኝ። ደግሞም የዛሬ 120 ዓመት በአድዋ ጦርነት ጀግኖች ሴትና ወንድ አያቶቻችን በፈፀሙት ገድልም የምኮራ <em>‘ሽብርተኛ’ </em> ነኝ። እርስዎም እንደሚያውቁት የአድዋው ድል በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ሲማቅቁ ለኖሩት በአፍሪካና በመላው ዓለም ለሚኖሩ ትውልደ አፍሪካ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ ድል ነው። የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ላደረጉት ጦርነት “አዋላጅ” የሆነችው ሀገሩ ባበረከተችው ሚና የምኮራም ነኝ።

በሀገሬ በተንሰራፋው ፀረ ዴሞክራሲ አስተዳደራዊ ሥርዐት፤ ዓመታትን ባስቆጠረውና ለአያሌ ወጣቶች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት በሆነው የርስ በርስ ጦርነት፤ በአስከፊው ድህነት፤ ተደጋጋሚ ድርቅና ረሀብ ሁሉ የምንገፈገፍና የምቆጭ ‘<em>ሽብርተኛ’</em>ም ነኝ። የችግራችን ምንጭ የሆነውን አምባገነናዊነት ከሥሩ መንግሎ ለመጣል ሠላማዊ ትግልን እንደ ሃይማኖት የተቀበልኩና የተገበርኩ <em>‘ሽብርተኛ’</em>ም ነኝ።

ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ‘ኢትዮጵያውያን ሀይለኛ ተዋጊዎች ናቸው’ ብለዋል። አዎ፤ ሉዐላዊነታችን በወራሪዎች ሲደፈር ለመከላከል ሀይለኛ ተዋጊዎች ነን። ይሁንና በሚያሳዝን ጎኑ ደግሞ ሉዐላዊነታችን ከራሳችን በወጡ አምባገነኖች ሲደፈር ሀይለኛ ተዋጊነታችን ሲደገም አይታይም። ለአስራሰባት ዓመት የዘለቀው ከደርግ ወታደራዊ ጁንታ ጋር የተካሄደው እልህ አስጨራሽ ጦርነት በደርግ መገርሰስ ሲጠናቀቅ ለብዙዎቻችን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጎህ የቀደደ መስሎን ነበር። አለመታደል ሆኖ ግን እስካሁን ያለን ከወደቀው የተሻለ አይደለም። ከላፉት 25 ዓመታት ጀምሮ በጭቆና ማጥ ውስጥ እንደተሰቃየን አለን። ቢሆንም ታዲያ እጆቻችንን አጣጥፈን ግን አልተቀመጥንም።

የአድዋ ጦርነት በቅኝ ግዛትና በጭቆና አገዛዝ ውስጥ የሚማስኑትን ለመብታቸው እንዲዋጉ እንዳነሳሳቸው ሁሉ፤ የህንድ ህዝብና በአሜሪካ የሲቪል መብት ንቅናቄ ተሟጋቾች ያካሄዱት ሠላማዊ ትግል ደግሞ ለአንዳንዶቻችን አርአያ ሆኖን በሀገራችን ዴሞክራሲን ለማስፈን በምናደርገው ትግል ተጠቅመንበታል።

በ2005 (እአአ) በተደረገው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ የትግላችን ጥረት የሰመረ መስሎ ነበር። ተስፋችን ግን ምርጫውን ባጭበረበረው አምባገነን መንግሥት ጨለመ። ይባስ ብሎ መረን የለቀቀውን የአገዛዙን በትር በአብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ ለምሳሌ ምርጫውን ባሸነፈው ቅንጅት (እኔም ከአመራሮቹ አንዱ የሆንኩበት) መሪዎች፤ ደጋፊዎችና አባላት ላይ በማሳረፍ ወደ ወህኒ ቤት አግዟቸዋል። ዴሞክራሲን የማፈን ተግባሩ ዓይን ያወጣ ከመሆኑ የተነሳ ዓለም ዐቀፉ ማህበረሰብ በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ የአውሮፓ ምርጫ ታዛቢ ልዑክ ሞራለ ቢስ የሆነውን የአገዛዙን ተግባር አውግዘዋል። ይሁን እንጂ የሁዋሊት ጉዞውን በቀላሉ መቀልበስ አልተቻለም።

እነሆ በዚህን ወቅት – በመጀመሪያው የወህኒ ቤት ቆይታ ጊዜዬ – ነበር በአንድ መፅሄት አማካኝነት ከእርስዎ አዲስ አስተሳሰብ ጋር የተዋወቅሁት። ከሃያ ወራት እስር በሁዋላ – ሃያ አራት የምንሆነው የዕድሜ ልክ እስራት ተበይኖብን ነበር – በምህረት ተለቀቅን። ከወህኒ እንደወጣሁ፤ የህይወቴ የፍቅር ቀንዲል ከሆነችው ከዶ/ር ሠላም አስቻለ ጋር ተጋባን። ከእስር ነፃ በቆየሁባቸው ቀጣይ አራት ዓመታት እኔና ባለቤቴ የሁለት ወንዶች ልጆች ወላጆች በመሆን ተባረክን። ይሁን እንጂ በውስጤ እንደ ወላጅ የማሳደግ ዕድል የሌለኝን ልጆች ወደዚህች ምድር እንዳመጣሁ ይሰማኝ ነበር። ለዚህም ዕለት ተዕለት ይካሄድ የነበረው ክትትል መጪውን ፅልመት ጠቋሚ ነበርና።

<em>ይህም ሆኖ ታዲያ በልቡናዬ ያኔም ሆነ አሁን በጥልቅ እንደማምነው ለአረመኔ አምባገነን ሰግዶና አደግድጎ ከመኖር ይልቅ በወህኒ ቤት መሞት ክብር ነው።</em>

በእኒያ ከወህኒ ውጪ በቆየሁባቸው ዓመታት እርስዎ ለተባበረው የአሜሪካ መንግሥት ቢሮ ፕሬዚዳንትነት ያደረጉትን የመጀመሪያ ዘመቻ ለማየት ታድያለሁ። ያካሄዷቸውንም የመድረክ ክርክሮች በሙሉ በቀጥታ ስርጭት ተከታትያለሁ። ተሳትፎዬ ሁሉ ከግምት ውስጥ ይገባል ብዬ ባይሆንም – በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደጋፊዎችዎን ተቀላቅዬ በየጊዜው ወቅታዊ የሆነ የኢሜል መልዕክት ከሚደርሳቸው አንዱ ነበርኩ። ሴናተር ጆን ማኬን እና እርስዎ ያደረጓቸውን የቅበላ ንግግሮችንም በቀጥታ ሥርጭት አዳምጫለሁ። ዕውነቱን ለመናገር፤ ክቡር ፕሬዚዳንት፤ በሀገርዎ ምርጥ የዴሞክራሲ ባህል በእጅጉ ነበር የተመሰጥኩት – በሀገሬ ውስጥ እንደዚያ ያለ ባህል ይኖር ዘንድ ካለኝ ፍላጎት።

በኢትዮጵያ ሀገሬ እንደዚያ ያለ ዴሞክራሲ መመኘት ይቅርታ የማያስገኝ ሀጢያት ነው። ወ/ሮ ሮዛ ፓርክስ መቀመጫዋን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆንዋ ታስራ 14 ዶላር እንደተቀጣችው፤ እኔም ፓርቲዬን – አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ – በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊነት በኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ሳገለግል ነበር የታሰርኩት። ለሁለተኛ ጊዜ <em>‘ሽብርተኛ’ </em> በሚል ክስ የዕድሜ ልክ እስራት ተበየነብኝ። እነሆም ላለፈው አራት ዓመት ተኩል ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ካሉት ጋር እንኳ ሲነፃፀር በአስከፊነቱ ወደር ከማይገኝለት ወህኒ ቤት ውስጥ በመማቀቅ ላይ እገኛለሁ።

ከእጅ መዳፍ የማትበልጠውን ሠማይ አሻቅቤ እያየሁ አእምሮዬ በየአቅጣጫው ሲባዝን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን አውጠነጥናለሁ። በቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ ከራሴ ጋር ስሟገት፤ በቆምኩለት ዓላማ ንፁህነትና ቀናነት ውስጥ መሸሸጊያ እያገኘሁ፤ የእስር ቤቱን ሰቆቃ አስችሎኝ የሠላም እንቅልፍ እተኛለሁ።

ስለባለቤቴ አስባለሁ፤ በተለይም ያለአባት ተምሳሌ ስለሚያድጉት ሁለቱ ልጆቼ። የበኸር ልጄ ሩህ፤ የሶስት ዓመት ልጅ ሆኖና ት/ቤት በመግቢያው የመጀመሪያ ቀን፤ ኖላዊ ደግሞ የአስር ወር ህፃን እንደነበር ነው እኔ ወደ ወህኒ ቤት የተጋዝኩት።

እርስዎ በመፅሀፍዎ “<em>the Audacity of Hope” </em>ገፅ 72 ላይ ሲያወጉ ስለሴቶች ልጆችዎ አንስተው ሌሎቹም ታዳጊ ቤተሰቦች ያሏቸው ሴኔተሮች ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ስለሚያደርጉት ጥረት ገልፀዋል። ክቡር ፕሬዚዳንት፤ በቤተሰቦቼ በተለይም በልጆቼ ላይ እየደረሰ ያለውን የስቃይ ስሜት ይጋሩኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

የእኔ ልጆችና በእስር ላይ የሚገኙት <em>የአያሌ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ልጆች</em> ማባሪያ የሌለውንና መልስ የማይገኝለትን የተለያዩ ጥያቄዎች ይጠይቃሉ፤ ለምሳሌ አባቶቻቸው ወደ ቤታቸው ሳይመጡ የቆዩበትን ምክንያት። ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ይህንን የመሳሰሉ ነፍስና ሥጋን የሚያስጨንቁ ጥያቄዎችን ላለፉት አራት ዓመታት ሲጠይቁ ስለቆዩት ልጆቼ አንስቼ ጊዜዎን ላባክን አልሻም።

ክቡር ፕሬዚዳንት፤ እንኳንና እንደ ኢትዮጵያ ባለው ላለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት የተንሰራፋውን አምባገነንነቱን መሸፈኛ ምርጫን በጭንብልነት ለሚጠቀም አገዛዝ ቀርቶ በዴሞክራሲ ሀገራትም የህዝብ ውክልና እስከምን ድረስ እንደሆን ጠይቆ ቀላል መልስ ማግኘት ይከብዳል።

በ2005 (እአአ) በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ወቅት የተጀቦነበት ጭምብል ቢገፈፍም ቅሉ አገዛዙ ግን ምርጫውን በ99.6% ‘ሲያሸንፍ’ በ2015 (እአአ) ደግሞ 100% ‘በማሸነፍ’ ዴሞክራሲ በምድረ ኢትዮጵያ እንደ ፀሀይ ብርሃን በማንፀባረቅ ላይ መሆኑን እየሰበከ ይገኛል። ዓለምም ይህንን ቅጥፈት ለመቀበል ዝግጁ ሆኗል። እርስዎም እንኳን ሳይቀሩ፤ ክቡር ፕሬዚዳን፤ በጉብኝትዎ ወቅት – የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የህዝብ ድጋፍ ያለው መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል። ዕውን ይህንን የተናገሩት ከልብዎ ነበርን?

<strong>“ሁሉም ሰው እኩል ነው”</strong>

<strong>    </strong>የሀገርዎ መስራች አባቶች አሳምረው እንዳስቀመጡት – ክቡር ፕሬዚዳንት – ሁላችንም የተፈጠርነው እኩል ሆነን ነው። በመንገድ ደርዝ የሚገኝ “የድሃ ድሃም” ይሁን ወይም በቤተመንግሥት ያለ “የንጉሦች ንጉሥ” ሁላችንም በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠርን እኩዮች ነን። በመሆኑም ሁላችንም በተስተካከለ መንገድ ልንስተናገድ ተገቢ ይሆናል። ማንም በማንም የበላይነት ስር በማንኛውም አይነት ሁኔታ ሊገዛ አይገባውም።

የዴሞክራሲንና የፍትህን ጉዳይ አስመልክተው በመጀመሪያው የፕሬዚዳንትነት ውድድር ዘመቻ ወቅት ያደረጉትን መሳጭና ውብ ንግግር ማንም የሚክደው አይደለም። ይህንንም “<em>the Audacity of Hope” </em>በሚለው መፅሀፍዎ ውስጥ አስቀምጠውታል። የርስዎ ክርክርና ስኬታማ መሆን አንዳንዶቻችንን ራሳችንን ለማንኛውም ጉዳይ ካዘጋጀን የማይቻል ነገር አለመኖሩን እንድናምን አድርጎን ነበር። ይሁንና <em>በአፍሪካ ለምንገኘው እንደንግግርዎ ሁሉ ተግባርዎም ልባችንን የነካው አይመስለኝም።</em>

እንደ ኢትዮጵያ በርቀት በሚገኙ ሀገሮችም ይሁን ወይም እንደ ጎረቤት ሀገር ኩባ፤ ግንኙነቱም ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ይኑረው ወይም አይኑረው፤ በሀገራት መካከል ዕውነተኛው ወዳጅነት ሊገነባ የሚገባው የህዝብን የሉዐላዊነት መብት መሰረት በማድረግ ሊሆን ይገባዋል። እርስዎ ራስዎ በሚገባ ጠንቅቀው እንደሚረዱት በኢትዮጵያና በዩኤስ አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ይህንን መሰረት ያደረገ አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ህዝብ ቃልዎን ተንተርሶ ሊራመድ ሲሻ ቡጢ ጨብጦ የተነሳው ክንድዎ የታለ፤ ክቡር ፕሬዚዳንት? በኢትዮጵያ ጉብኝትዎ ወቅት መሪዎቻችንን እንዳብጠለጠሉ ሰምቻለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍትህና ለዴሞክራሲ በሚያደርገው ትግል የተባበረው የአሜሪካ መንግሥት ፕሬዚዳንት ማድረግ የሚችለው ርዳታ – በቃ ይኸው ነው?

ክቡር ፕሬዚዳንት፤ እርስዎ በሀገርዎ ታሪክ ከአሜሪካ ታላላቅ ፕሬዚዳንቶች አንዱ ሆነው እንደሚሰፍሩ አምናለሁ። ደግሞም፤ እንደ ዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንትነት በቆዩባቸው ሁለት የአገልግሎት ዘመናት አፍሪካውያን ለዴሞክራሲና ለፍትህ በሚያደርጉት ትግል ውስጥ አንዳችም ፋይዳ ያላበረከተ አፍሪካዊ ትውልድ ያለው የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተብለው በታሪክ እንደሚፈረጁም አምናለሁ።

ገና በጠዋቱ፤ ብዙዎች እርስዎ ያደርጓቸው የነበሩትን ፖለቲካዊ ህብስተ ዲስኩሮች፤ ከዋሽንግተን የፖለቲካ መዘውር አንፃር፤ ወደ ተግባር የማይተረጎሙ ናቸው በማለት ጥርጣሬያቸውን ይናገሩ ነበር። መለስ ብዬ ሳየው፤ ለካስ ዕውነታቸውን ኖሯል።

ዛሬ ድረስ የሚገርመኝ ቢኖር፤ እንደርስዎ ብቃት ያለው ፕሬዚዳንት ህዝቦች እግዚአብሄር የሰጣቸውን ሰብዓዊ መብት ሲገፈፉ በዝምታ መመልከት መቻሉ ነው። ይህ የሆነው፤ ከተግባር ፖለቲካ ምልከታ አንፃር {ፕራግማቲዝም}? በገንቢ ውይይት በማመን? ወይስ ‘ውስጥን በመፈተሽና ማስተካከያም በማድረግ’ ወደ ቀድሞው ዘመን የግንኙነት መስመር መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ?

ዕውነቱን ለማናገር በእስር እየማቀቅሁ እንኳን የእርስዎን ወደ ተወዳጅዋ ሀገሬ ለጉብኝት መምጣት በልቡናዬ አበክሬ ነበር የደገፍኩት። የእርስዎ ጉብኝት ለፍትህና ለዴሞክራሲ መስፈን የሚደረገውን ትግል ይረዳል የሚል ዕምነትና ተስፋ በውስጤ ውስጥ ነበረኝና።

እርስዎ ግን ጭርሱኑ “አገዛዙ ህዝባዊ ነው” በማለት አደባባይ ተናገሩ። ዕውን ይህ ምን ማለት ነው፤ ክቡር ፕሬዚዳንት? እንደማምንበት ከሆነ ህዝባዊነትን አሳምሮ መግለጫው ነፃና ወገንተኛ ያልሆነ ምርጫ ሲኖር ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ነፃና ወገንተኛ ያልሆነ ምርጫ በታሪካችን እስካሁን ተካሂዶ አያውቅም። እና እንደምን  ቢሆን ነው አገዛዙ ህዝባዊነቱ የተረጋገጠለት? ሳዳም ሁሴን በ100% ምርጫ ‘ሲያሸንፍ’ ህዝባዊ ነበርን?

አገዛዙ ምርጫውን በ100% ካሸነፈ ዓመት ገደማ ሲሆነው፤ ታዲያ እንዴት ቢሆን ነው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች፤ ለምሳሌ በኦሮምያ በትግራይ በጋምቤላ ለመብታቸው በመታገል ላይ የሚገኙት? ህዝቡ በገፍ እየተገደለና እየታሰረም ነው። ማንም ቢሆን ይህንን ከህዝብ መንግሥት የሚጠብቀው አይደለም።

የህዝብ ድጋፍ አላቸው ተብለው የሚታመኑትን ፓርቲዎች ሰርጎ የሚገባ፤ መሪዎችንም የሚያስር፤ የፕሬስ ነፃነትን የሚቀበትት፤ ጋዜጠኞችን ወህኒ የሚያጉርና ህዝብን በጠመንጃ አፈሙዝ ገድቦ የያዘ አገዛዝ እንደምን ህዝባዊ ሊሆን ይችላል?

ለአስራሁለት ተከታታይ ዓመታት ኢኮኖሚው በጥንድ አሃዝ ያለማቋረጥ በማደግና የህዝቡም የገቢ መጠን መራራቅ እየጠበበ በመሄድ ላይ ነው ብሎ በሚናገር አገዛዝ ውስጥ፤ ከአስር ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ከለጋሽ ማህበረሰባት ምፅዋት እየጠበቁ ይገኛሉ። በማደግ ላይ ነው የሚባልለት ኢኮኖሚ ለአንድ ዓመት እንኳን የተራቡ ኢትዮጵያውያንን ሊታደግ አልቻለም። ይህ በራሱ ህዝባዊ ድግፍ ያለው መንግሥት ሥራ ውጤት አይመስለኝም።

የኢትዮጵያ ወጣት ባገኘበት አቅጣጫ ከሀገሩ እየኮበለለ ይገኛል። ከህዝባዊ መንግሥታቸው የሚኮበልሉት ስለምን ይመስልዎታል፤ ክቡር ፕሬዚዳንት? እርስዎም አሳምረው እንደሚያውቁት እኒህ አንዳቸውም የዲሞክራሲያዊ መንግሥት ምልክቶች አይደሉም። ዴሞክራሲያዊ አስተዳደሮች ፓለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መረጋጋቶቻቸው ናቸው መለያቸው።

ጀምስ ሜርዴዝን መቸም ጠንቅቀው ያውቁታል ብዬ አምናለሁ። በጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ – አስተዳደሩ ምንም ያህል ቢቃወምም – ሚሲሲፒ ዩኑቨርሲቱ ለመግባት ችሏል። በሳውዝ አፍሪካ የዘር መድልዖ ዘመን እንኳን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እስር ቤቶቹ በፍትህ ሥርዐቱ ላይ ዕምነት ነበራቸው።

በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ሲከሰሱ አይደለም የሚታሰሩበት ዘመን ብዛት የሚታወቀው። እንደ <em>እስክንድር ነጋ፤ ውብሸት ታዬ፤ ተመስገን ደሳለኝ እና አያሌ ጋዜጠኞች </em>የአገዛዙን ተግባራት ተቃውመው ስለፃፉ ወይም <em>እንደ በቀለ ገርባ እና ሀብታሙ አያሌው የመሳሰሉ ልበ ሙሉ ፖለቲከኞች</em> ተቃዋሚዎችን በመቀላቀላቸው ምክንያት በወህኒ ቤቶች ሲማቅቁ ሲታይ እንጂ። ደግሞም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻም ሳይሆን ትዕዛዙ ከቤተመንግሥትም ጭምር ሲወጣ ሲታይ ጭምር እንጂ። መዋቅራት የአንድን ፓርቲ ህልውና ለማስረገጥ የቆሙ ናቸው፤ ክቡር ፕሬዚዳንት።

ሀገሩን የሚወድ የትኛውም ግለሰብ የሀገሩን ገፅታ ማጥለም አይፈልግም። እኔ ሀገሬን እያሳጣዃት አይደለም፤ እወዳታለሁና። ልጆቼና ባለቤቴ ሳይቀሩ እየተጋቱት ያለውን – በሀገሬ የሰፈነውን ኢፍትሃዊ መራራ ዕውነት ለማሳየት እንጂ፤ ክቡር ፕሬዚዳንት።

አራት ሰዎች በእኔ ላይ የሀሰት ምሥክርነት እንዲሰጡ ተገርፈዋል። ሁለቱ አልቻሉም። እና አድርጉ የተባሉትን ፈፅመው ተለቀዋል። የተቀሩት ሁለቱ፤ <em>ናትናኤል መኮንን</em> እና <em>ክንፈሚካኤል ደበበ</em> ግርፋቱን ችለው በዚሁ ሳቢያ ይኸው እስካሁን እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ሁለቱም ናትናኤልና ክንፈሚካኤል የ18 እና የ16 ዓመት ፍርደኞች ናቸው፤ በቅደም ተከተል። መቸም አገዛዙን በህዝባዊነት በማወደስ ከእርስዎ ጋር ባለመወገኔ አዝናለሁ።

<strong>የዘመናችን አድዋ</strong>

በሀገርዎ በ1868፤ ጆን ዊልክስ ቡዝ፤ አብረሃም ሊንከንን ለመግደል ተሳክቶለታል። ነገር ግን በዘር መድልዖ ላይ መንጋቱን ግና ሊያቆመው አልቻለም። ሰው ሁሉ እኩል ተፈጥሯልና፤ የእርሱ ዓለማ ግን ዕኩይ ነበርና። የህንዱ ጋንዲ ከእንግሊዝ ዘውዳዊ አገዛዝ የህንድን ህዝብ ነፃነቱን እንዲቀዳጅ አድርጓል። ሰው ሁሉ እኩል ተፈጥሯልና፤ የጋንዲም ዓላማ የእኩልነት ነበርና። ክቡር ፕሬዚዳንት እንደሚያውቁት፤ አዶልፍ ሂትለር የአርያን ጎሳ የበላይነት ለማስረገጥ ያደረገው ጥረት መክኗል። ሰው ሁሉ እኩል ተፈጥሯልና፤ የርሱ ዓላማ ግን ዕኩይ ነበርና። ልክ የዛሬ 120 ዓመት ሴቶችና ወንዶች አያቶቻችን በአንድነት ቆመው የጣሊያንን ወራሪ ሃይል አሸንፈዋል፤ ምክንያቱም ዓላማችን ፍትሃዊ ነበርና – ሁሉም ሰው እኩል ተፈጥሯልና። ማንም የማንንም ሀገር ወይም መብት የመውረር መብት የለውና።

ነገር ግን ሴትና ወንድ አያቶቻችን በሀገራቸው ‘ሰው ሁሉ እኩል ተፈጥሯል’ በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ የማደር እድል አልገጠማቸውም። በኮርያና በኮንጎ በተሳተፉት የሠላም አስከባሪ አያቶቻችንና ዛሬ ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሠላምን ለማስከበር በተሰለፉት ሁሉ ተግባር እኮራለሁ። ታዲያ የዚህ ሽሙጥ የሆነው ደግሞ፤ ለሌሎች ሀገራት በገፍ የሚሞቱት ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው የራሳችን ነው የሚሉት መንግሥት የሌላቸው መሆኑ ነው። ኢትዮጵያውያን በቤታቸው ገና ያላጠናቀቁት ሥራ አለባቸው።

በተባበረው የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ በ60ዎቹ እንደነበሩት የሲቪል መብቶች ተሟጋቾች እኛም በዕውነት በሠላማዊ ትግል ዕምነታችን ፅኑ ነው። ታዲያን አክራሪ ሃይማኖተኞች በመሆናችን አይደለም። ነገር ግን ከአምባገነን ጋር በሚደረግ ትግል ዘላቂ ሠላምንና ብልፅግናን ለማምጣት የማይመክን መሳሪያ በመሆኑ እንጂ። የመጣው ቢመጣ፤ በትግላችን ድልን እንደምንቀዳጅ አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም። ምክንያቱም ዓላማችን ፍትሃዊ ስለሆነ፤ ሁሉም ሰው እኩል ተፈጥሯልና።

እኛ ሽብርተኞች አይደለንም፤ ክቡር ፕሬዚዳንት። እኛ የዕውነተኛ ዴሞክራሲና ፍትህ ርዕያን እንጂ። እኛ የነፃነት ታጋዮች ነን። በዘመኑ ከቶም ይሆናል ያልተባለው ነገር ግን የእኛ ሴትና ወንድ አያቶቻችን በአድዋ ጦርነት ድልን እንደተቀዳጁ፤ እኛም የግፍ አገዛዝን መንግለን የዴሞክራሲ ገነት የሆነች ኢትዮጵያን በመመሥረት ዘመናዊውን የአድዋ ድል እንፅፋለን። የችግራችን ሁሉ አስኳል የዴሞክራሲ ዕጦት ነው ብዬ አምናለሁና። ትግላችን ያፈራ ዘንዳም አያሌ ኢትዮጵያውያን ተነግሮ የማያባራ መስዋዕትነትን እየከፈሉ ይገኛሉ፤ ክቡር ፕሬዚዳንት።

እኛ አሳሪዎቻችን እንደሚሰይሙን አይደለንም። የእኛን ግብና የዓላማችንንም ንፁህነት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ጉዳዩ፤ የእኛ ግብ የእነሱ አይደለም፤ የእነሱም የእኛ አይደለምና። መሠረቱ ይኸው ነው።

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በአንድ ወቅት እንደተናገረው፤ <em>ክፉ ዓላማ ያላቸው ሰዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት በሚፈጥሩት ዘዴና በጊዜ አጠቃቀማቸው በጣም ብልጦች ናቸው</em> – ብሎ ነበር። በኢትዮጵያ ገዢዎቻችን የሚያደርጉትም ይህንኑ ነው። ይሁን እንጂ የማታ ማታ ድሉ የእኛ ይሆናል።

<strong>    መታሰቢያዎን እያኖሩ ነው</strong>

ክቡር ፕሬዚዳንት፤ የእርስዎ ተቀዳሚ ተግባርና ሃላፊነት የአሜሪካንን ህዝብ ፍላጎት ማስጠበቅ መሆኑን በሚገባ እገነዘባለሁ። ይሁንና ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳመለከተው – <em>የሰው ልጆች ሁሉ ዕጣ ፈንታ የተቋጠረው በአንድ እራፊ ጨርቅ ነው።</em> የዴሞክራሲና የፍትህ ግብ የሰው ልጆች ሁሉ ግብ ሊሆን ይገባዋል። ይህም ከማንም የማይጎዳኝ መብት ጋር የሚፃረር አይደለም። እንደውም ከማንኛውም ሀገር ዘላቂ ሠላምና ብልፅግና ጋር የሚጎዳኝ እንጂ።

የግፍ አገዛዝ ምንጭ አንድ ሀገር አይደለም፤ አይሆንምም። ለተለያዩ አምባገነኖች የተለያዩ የአሜሪካ መንግሥት መሪዎች የሚያደርጉት ድጋፍ አፍራሽ ውጤት ያለው መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ለዴሞክራሲና ለፍትህ የሚደረግን ትግል መደገፍ ከሀገርዎ መስራች አባቶች መርህና የዴሞክራሲ መብቶችን ፍሬዎች ከሚያጣጥሙት የሀገርዎ ሰዎች መስመር ጋር የሚስማማ ነው።

ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ  ጁኒየር፤ <em>ኢፍትሃዊነት በየትኛውም ሀገር ለሚገኝ ፍትህ አደገኛ ነው</em> – ብሎ መናገሩ ስህተት ይሆን? በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሚገኝ ‘ግሎባላይዜሽን’ ይህ አባባል ስሜት አይሰጥምን? በእርስዎ አስተሳሰብ፤ እኛ ብቻችንን መራመድ አለብን ይሆን፤ ክቡር ፕሬዚዳንት?

እንደርስዎ ሀገር ካሉ ዴሞክራሲያዊ ሀገራት ድጋፍ ያለመኖሩና ገደብ የለሹ የገዢዎቻችን ረገጣ በኢትዮጵያ የነፃነት ጎህ መጥቢያውን ጊዜ ሊያዘገየው ይችል ይሆናል። በበኩሌ ተረግጦ ለማይቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ትግል ያለኝን ቁርጠኛ ዕምነት እነሆ ዳግም አረጋግጣለሁ።

እርስዎ የእኛን ጉዳይ ጣጥለውታል ማለት እችላለሁን? አልችልም፤ ስለምን? ምክንያቱም፤ በእርስዎ በኩል ቀናነቱና ውስጣዊ ግፊቱ ካለ በፖለቲካው ጎራ ካልዎት ተደማጭነት ጋር ተዳምሮ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በአፍሪካ ለዴሞክራሲና ለፍትህ የሚደረገውን ትግል ለመርዳት አሁንም ጊዜው አልዘገየብዎትም ብዬ አምናለሁና።

የእርስዎ ዘላቂ መታሰቢያ በአፀደ ሥጋዎ {በአፍሪካዊ ደምዎ} ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ጭምር ክብራቸውን በገዢዎቻቸው እጅ ከተገፈፉት ህዝቦች ጋር የተቆራኘ ሊሆን ይገባዋል። በአጠቃላይ በአፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ህዝቡ የሚያደርገውን ትግል ጊዜ ሰጥተው በማስታወስ አስፈላጊውን ድጋፍና ርምጃ ይወስዱ ዘንድ በትህትና አሳስባለሁ።

&nbsp;

ከአክብሮት ጋር

አንዱዓለም አራጌ ወሌ

(የህሊኛ እስረኛ)

ማርች 2 2016

*************/////////////*****************

<em>    </em>

ምንጭ፤ <a href=”http://www.freeandualemaragie.org/archives/641″>http://www.freeandualemaragie.org/archives/641</a&gt;

(ትርጉም፤ ሚያዚያ 2008 ዓ/ም {ኤፕሪል 2016} ሲድኒ፤ አውስትራሊያ)

<a href=”mailto:mmtessema@gmail.com”>mmtessema@gmail.com</a>

****************************************************************************************************

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s