የዶክተር መረራ የገመድ ላይ ጉዞ (ኄኖክ የማነ-ስባት ኪሎ)

 

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ላለፉት አምስት ዐሥርት ዓመታት በኦሮሞ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ በጽናት እና በታማኝነት ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የሰባት ኪሎ ጸሐፊ ኄኖክ የማነ በአማርኛ የጻፏቸውን ሁለት መጻሕፍት እና የፒ.ኤች.ዲ መመረቂያ ጽሑፋቸውን አንብቦ ከልጅነታቸው ጀምሮ እስከ ጉልምስናቸው ድረስ የዘለቀ የመንታ ልብ ባለቤት ናቸው ይላል። ለዚህ መንታ-ልብነት የዳረጋቸው ኦሮሞነትን እና ኢትዮጵያዊነትን አቻችሎ ለማስኬድ የሄዱበት ጉዞ እንደኾነም ያወሳል፤ ይህ በሚውገረገር ገመድ ላይ የሚደረግ ጉዞ ክፉኛ እያንገዳገዳቸው ነውም ይላል።

ዶክተር መረራ ጉዲና
ዶክተር መረራ ጉዲና

ዶክተር መረራ ጉዲና ከ25 ዓመታት በላይ ካገለገሉበት እና ከሚወዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በግፍ መሰናበት (“አንዳንዴ ሳስበው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምወጣው ለቀብሬ ብቻ ይመስለኝ ነበር” ይላሉ) የሚያሳዝን እና የሚያስቆጭ ቢኾንም ስውር ሲሳይ ይዞ ብቅ ያለ ይመስላል፤ የአደባባይ ምሁርነትን። ዶክተር መረራ በሦስት ዓመታት ልዩነት ውስጥ ሁለት ማንኛውም የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚከታተል ሰው ሊያነባቸው የሚገቡ መጻሕፍት በአማርኛ ጽፈው አበርክተዋል፤ የመጀመርያውና እና ከዩኒቨርሲቲ ከመሰናበታቸው በፊት በ2005  ዓ.ም ያሳተሙት “ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ እና የሕይወቴ ትዝታዎች፤ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢሕአዴግ” (ከዚህ በኋላ “ኢፖምጉሕት”) የተሰኘው መጽሐፍ ሲኾን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከስንብት በኋላ በ2008 ዓ.ም ለንባብ የበቃው “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞች፤ የኢሕአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ” (ከዚህ በኋላ ኢታፈሚሕ) የሚል ርእስ ያለው ነው። ካሁኑ አያያዛቸው በመነሳት ዶክተር መረራ ወደፊት በሚኖራቸው ሰፋ ያለ ነጻ ጊዜ ተጨማሪ መጻሕፍትን እና አጫጫር ጽሑፎችን ለሕዝብ እንደሚያቀርቡ ተስፋ ማድረግ ይቻላል።

እውቁ ፖላንዳዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊ ቼስላፍ የስማን ከ53 ዓመታት በፊት ባሳተሙት The Ethiopian Paradox በተባለ መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ ታሪኳ ሸክም የኾነባት አገር እንደኾነች ጽፈው ነበር። ኢትዮጵያዊው የታሪክ ምሁር ዶክተር ገብሩ ታረቀ በበኩላቸው ከኻያ ዓመታት በፊት በታተመው እና በዐፄ ኀይለሥላሴ ዘመን በተካሄዱ የገበሬ ዐመፆች ላይ ባተኮረው “Ethiopia: Power and Protest” በተሰኘው ድንቅ መጽሐፋቸው ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ ታሪካቸው መርገምም በረከትም የኾነባቸው የአፍሪካ አገሮች እፍኝ የማይሞሉ እንደኾኑ ያስቀምጣሉ። ገብሩ ይህን ከተናገሩ ከስምንት ዓመታት በኋላ የታሪክ ሸክሙ የባሰ እየከበደ መምጣቱን በማስተዋል ይመስላል ኢጣልያዊው የኢትዮጵያ የታሪክ ተመራማሪ አሌክሳንድሮ ትሩይልዚ “Battling with the Past: New Frameworks for Ethiopian Historiography” የሚል ርእስ በሰጡት አጭር ግን ሰርሳሪ ጽሑፋቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ሸክም ከልክ በላይ ተቆልሎ አደጋ እየፈጠረ ስለመኾኑ ያተቱት።

ይነስም ይብዛ የታሪክ ሸክም የሌለበት አገር ፈልጎ ማግኘት የሚቻል ነገር አይደለም። ይኹንና በዚህ ዘመን እንደ ኢትዮጵያ በታሪካቸው የጎበጡ አገሮች ግን እጅግ ጥቂት ናቸው። ሁለቱ የዶክተር መረራ መጻሕፍት መልእክትም ይህንኑ ሐቅ የሚያጠናክር ይመስላል፤ መልእክቱ ትክክል ኾነም አልኾነም። የኢትዮጵያ ታሪክ በራሱ አገሪቷን ለማጉበጥ የሚያስችል ክብደት ባይኖረውም ለማመን በማይቻል ኹኔታ በተወሳሰበ መንገድ በተሸመኑ ቆርጦ ቀጥል ርዕዮተ ዓለማዊ ትርክቶች መጠቅጠቁ የተለየ ግዝፈትን ጨምሮለታል። ላለፉት 25 ዓመታት ትርክቶቹ እንዲደረጁ ያላሰለሰ እና በፖሊሲ የተደገፈ ጥረት በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ሲደረግ መቆየቱ ደግሞ ኹኔታዎችን የበለጠ አጠላልፏቸዋል።

ታዲያ ዶክተር መረራ በዚህ ታሪካዊ ፖለቲካዊ አውድ (context) ውስጥ ነው በኢፖምጉሕት እና በኢታፈሚሕ ትውስታዎቻቸውን እና ትዝብቶቻቸውን የሚያቀርቡት። የመጻሕፍቱ ርእሶች በራሳቸው ስለ መጻሕፍቱ አጠቃላይ ይዘት እና ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውጥንቅጥ ፍንጭ የሚሰጡ ናቸው። “የታሪክ ፈተናዎች”፣ “የሚጋጩ ሕልሞች”፣ “ምስቅልቅል ጉዞ”፤ እነዚህ ሐረጎች ከረጃጅም ርእሶች የተወሰዱ ናቸው። መጠነኛ የትኩረት ልዩነት ቢኖራቸውም ሁለቱ መጻሕፍት ካላቸው የይዘት እና የቅርጽ ጥብቅ ቁርኝት አንጻር “ቅጽ አንድ” እና “ቅጽ ሁለት” ተብለው እንደ አንድ መጽሐፍ ሊነበቡ ይችላሉ። ይህ ዳሰሳም የተጠቀሰውን ቁርኝት ታሳቢ አድርጎ የተጻፈ ነው።

የቋንቋ አጠቃቀም አጻጻፍ ዘይቤ እና ለዛ

ዶክተር መረራ ሐሳባቸውን በጥሩ አማርኛ በግልጽ እና በቀላሉ መግለጽ እንደሚችሉ ከሁለቱ መጻሕፍት መረዳት ይቻላል። ሐዘንና ደስታቸውን፣ ጨለምተኝነትና ተስፋቸውን፣ ቁጣና ትዕግስታቸውን አንባቢ ባይጋራቸውም እንኳ እንዲረዳቸው ማድረግ ይችላሉ። በተለይ የሕይወት ታሪካቸውን በብዛት የያዘው የኢፖምጉሕት ከባለታሪኩ አስደናቂ የሕይወት ውጣ ውረድ ጋር ተዳምሮ እንደ ልብ ወለድ ሊነበብ የሚችል ነው። ጠጠር ያሉ የፖለቲካ ኀልዮቶችንም ቢኾን አብዛኛው አንባቢ ያለ ችግር ሊረዳቸው በሚችል መልኩ ማብራራት ይችላሉ። መረራ ጎበዝ ተራኪም ናቸው። በልጅነታቸው ከደረሰባቸው ቁም ስቅል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከተሰናበቱበት ኹኔታ፣ ከእስር ቤት ቆይታቸው እስከ ምርጫ 97 ትርምስ፤ ከቤተሰባቸው አባላት እስከሚቃወሟቸው ባለሥልጣናት ጋራ ያላቸውን ግንኙነት እና ሌሎች በርካታ ኹነቶች የሚተርኩበት መንገድ ፈጣን፣ ለስላሳና ቀልብ-ገዢ ከመኾኑ የተነሳ “ምናለ ትንሽ ቢጨምሩበት?” የሚያሰኙ ናቸው።

ለአድናቂዎቻቸው “ጫዎታ አዋቂ” ለነቃፊዎቻቸው “ቧልተኛ” የኾኑት ተቃዋሚው ምሁር አለመቀለድ ፈጽሞ የሚችሉ አይመስሉም፤ “ካልቻሉ እንኳንም” ያልቻሉ ያሰኛሉ ሁለቱ መጻሕፍት። ኢፖምጉሕትን እና ኢታፈሚሕን ተነባቢ እንዲኾኑ ካደረጓቸው ነገሮች መካከል በውስጣቸው የያዟቸው ዘና የሚያደርጉ ቀልዶች፣ አሽሙሮች እና ስላቆች ተጠቃሽ ናቸው። ወይዘሮ ገነት ዘውዴን እና ዶክተር እንድርያስ እሸቴን የመሳሰሉ ሹመኞችን (እንድርያስ “ፕሮፌሰር” መኾናቸውን የሚያሳይ ምንም ዐይነት ማስረጃ እንደሌለ በጥናት እንደተደረሰበት በአጽንዖት ይገልጻሉ- ዶክተር መረራ) በአሽሙር የሚሸነቁጡበት መንገድ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ጣል የሚያደርጓቸው ሥነ ስላቃዊ ትችቶች የሚያስፈግጉ ናቸው። ለአብነት በውጪ አገር ስለሚገኙ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያናት በትግርኛ እና በአማርኛ መከፋፈልን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፤ “ጦርነቱ በምድርም በሰማይም የሚቀጥል መኾኑን የሚያሳይም ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ያላለቀው የዮሐንስ እና የምኒልክ ጦርነት ነው ብለው የሚቀልዱ ጓደኞችም አሉኝ” (ኢታፈሚሕ ገጽ 61)። ይህን ቀልድ የተናገሩት ራሳቸው ዶክተር መረራ እንደኾኑ የሚጠረጥሩ ሰዎች በርካታ ናቸው። የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ኩም ያደረጉበትን አጋጣሚም እንደሚከተለው አቅርበውታል፤ “ዕድሉን ሲያገኝ አቶ መለስ ተቀናቃኝን የማብሸቅ ጠባዮች አሉት፤ ለአብነት ቅንጅቶች ተፈተው፤ እነ ዶክተር ብርሃኑ አሜሪካ ሄደው ስለቀሩ እኔንም ለማብሸቅ ‘አሜሪካ ሄደህ የሸፈትክ መስሎኝ ነበር፤ መጣህ እንዴ?’ አለኝ። ሽፍትነት ካማረኝ አምቦ ይቀርበኛል አልኹት። ከእኔ ጋራ የነበሩ የፓርላማ አባላት ሳቁ፤ እርሱም ፊቱ በፍጥነት እየተለዋወጠ ሄደ” (ኢፖምጉሕት ገጽ 219)። ይህቺ ታሪካዊ ገጠመኝ ዶክተር መረራን ደህና አድርጋ ሳታኮራቸው የቀረች አትመስልም። በኢታፈሚሕም ደግመዋታል። በሚቀጥለው መጽሐፋቸውም ቢያሰፍሯት ድጋፋቸውን የሚገልጹ አያሌ አንባቢዎች እንደሚኖሩ በቀላሉ መገመት ይቻላል። ለማንኛውም የአደባባይ የፖለቲካ ቀልድ በማይታሰብበት አገር እንደ ዶክተር መረራ ዐይነት ፖለቲከኛ መኖሩ መልካም ነገር ነው።

ከባድ የሚባሉ ባይኾኑም በመጻሕፍቱ ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል ያልኾኑ የቋንቋ አጠቃቀም እና የአጻጻፍ እንከኖችም አሉ። ሲጀመር ርእሶቹ ከመጠን በላይ ረጃጅም ናቸው። ከመርዘማቸው የተነሳም ከርእስነት ይልቅ ለጨመቅነት (summary) የሚቀርቡ ናቸው። እንደውም በሽፋን ገጾቹ ላይ ያሉት ቃላት መበርከት መጻሕፍቱን መጽሔት አስመስሏቸዋል ማለት ይቻላል። ከትኩረት የሚያናጥቡ ተደጋጋሚ የፊደላት እና የሥርዐተ ነጥብ ሕጸጾችም ጥቂት አይደሉም። በተለይ የሚከተሉት ሐረጎች እና አገላለጾች በአሰልቺ ኹኔታ ይደጋገማሉ፤ “ያለ ደረሰኝ ማስረከብ”፣ “ቅርጫ የኾነ/ያልኾነ ምርጫ”፣ “ሳያስቡ እንደ ሎተሪ”፣ “በሚገባው ቋንቋ”፣ “እስገባኝ ድረስ”፣ እና “የሕዝብ ጎርፍ”።

ዶክተር መረራ አንዳንዴ ለትኹት አባባሎች (political correctness) የሚጨነቁ አይመስሉም። ለምሳሌ በአንድ የምርጫ ክርክር ወቅት ወይዘሮ ገነት ዘውዴ የተዛባ አኀዛዊ መረጃ እንዳቀረቡ ሲነገራቸው “የታይፒንግ ስህተት” ነው በማለታቸው “ወይዘሮ ገነት በእኛ ዩኒቨርሲቲ የጽሕፈት ሥራ ስታስተምር ስለነበር ‘ሞያሽም ከዳሽ እንዴ’ ልላት ነበር” ይላሉ።  ወይዘሮ ገነት ክብር የሚገባቸው ሰው እንዳልኾኑ ግልጽ ቢኾንም ለእርሳቸው የታለመው አሽሙር ለሌሎች ቀጥታ ስድብ ሊኾን ይችላል። ሌላው ደግሞ መደማመጥ የሌለበትን “ውይይት” ለመግለጽ “የደንቆሮዎች ውይይት” የሚለውን ሐረግ መጠቀማቸው ነው። ይኼ ማብራሪያ የሚያስፈልገውም አይመስልም። በተቃራኒው ግን ኦሮምኛ ቋንቋን ለመግለጽ “ኦሮሚፋ” የሚለውን የኦሮምኛ ቋንቋ ይጠቀማሉ። በአማርኛ ጽሑፍ ውስጥ ኦሮሞዎች የሚናገሩትን ቋንቋ ለመግለጽ ኦሮምኛ ቃል መጠቀም ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም። “ኦሮምኛ” የሚለው ቃል ስድብ ነው እስካልተባለ ድረስ።

 

የዘውጋዊ እና አገራዊ ማንነቶች ሚዛን ጥበቃ

እንዲህ እንደ አሁኗ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ማለት የዘውጋዊ ትርክቶች አስከፊ ፍልሚያ በኾነበት እና መፋለሚያው ሜዳ ተደርምሶ ተፋላሚዎቹንም አፋላሚዎቹንም የመዋጥ አደጋ በተደቀነበት ኹኔታ እንደ ዶክተር መረራ ዐይነቱ ፖለቲከኛ ዋጋው ከፍ ይላል። አዎ፤ ዶክተር መረራ የኦሮሞ ብሔረተኛ ናቸው። ግን ደግሞ ለየት ያሉ የኦሮሞ ብሔረተኛ ናቸው። እንደ ነባሩ ኦነግ ወይም እንደ አሁኑ ዘመነ ግዩራን (Diaspora) ኦሮሞ ብሔረተኞች ምናባዊ እና ገሃዳዊ ማንነቶችን በማምታታት የደጋፊዎቻቸውን ስሜት በከፊል ፈጠራ የመጋለብ አጀንዳ ያላቸው አይመስሉም። በሁለቱ የአማርኛ መጻሕፍት ባያነሱትም በፒ.ኤች.ዲ የመመረቂያ ጽሑፋቸው ውስጥ የኦሮሞን ጥያቄ የሚረዱበት መንገድ ከኦነግ እንዴት እንደሚለይ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ኦሮሞ ተወራሪ ብቻ ሳይኾን ወራሪ፣ ተበዳይ ብቻ ሳይኾን በዳይ፣ ሟች ብቻ ሳይኾን ገዳይ እንደኾነም ያስረዳሉ። “የኦሮሞ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” ብለው ለሚከራከሩት ደግሞ “የትኛው ጋናዊ ቅኝ ተገዢ ነው የእንግሊዝን ንግሥት ሲያገባ የምታውቁት?” የሚል ፈታኝ ጥያቄ ያቀርባሉ። ኦሮሞነት እና ኢትዮጵያዊነት ተጻራሪ ሊኾኑ አይገባም፤ አይደሉምም የሚል የቆየ ጽኑ አቋም አላቸው ብሎ መከራከር ይቻላል።

ለዚህ አቋማቸው እንደ ምክንያት የሚያነሱት በልጅነታቸው የደረሰባቸውን አንድ አሳዛኝ አጋጣሚ ነው። የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲመለሱ፦ “እንደ ወንድሜ የምመለከትው” የሚሉትን “ቡሬ” የተባለውን በሬ ጨምሮ የአባታቸውን በሬዎች በሙሉ ያጧቸዋል፤ ተሰርቀው ነበር። በሬዎቹን በአውጫጪኝ ማግኘት ስላልተቻለ የመረራ አባት እና እናት (እናታቸው እያለቀሱ) በአካባቢው ለነበሩ አንድ የኦሮሞ ባላባት በሬዎች ማፈላለጊያ የሚኾን አንድ ወይፈን ይሰጣሉ። ባላባቱ ግን በሬዎቹን በመስረቅ ከሚጠረጠሩት ሰዎች ጉቦ ተቀብለው ነበርና የበሬዎቹ ደብዛ እንደጠፋ ቀረ። ቡሬም በአንደኛው ባላባት ቤት ታርዶ እንደተበላ ብዙ ሰዎች ለብላቴናው መረራ አረዱት። አስከፊ ድህነት እነ መረራ ቤት ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ። ይህን አጋጣሚ “በቀሪው የሕይወት ዘመኔ ከአእምሮዬ መፋቅ አልቻልኩም” ይላሉ (ኢፖምጉሕት ገጽ 13)። አጋጣሚው በዶክተር መረራ ፖለቲካዊ ሥነ-ልቡና ላይ ዘላቂ እና ወሳኝ ተጽዕኖ ማሳረፉን ከሚከተለው የመረራ ትዝብት መረዳት ይቻላል፤ “ከዚህ የተነሳ ‘የኦሮሞ ፊውዳሎች ነፍጠኛ ከሚባሉት ለኦሮሞ የተሻሉ ናቸው፤ ለድኻው ኦሮሞ የበለጠ ያዝናሉ’ የሚባለው አባባል በጭራሽ አልተዋጠልኝም። ስለዚህም ነው በተማሪዎች ንቅናቄ ዘመንም ኾነ ከዚያ በኋላ ነው ሁሉም በጅምላ ከሚሳተፍበት የብሔር ንቅናቄ ይልቅ በመደብ ትግሉ ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔር ድርጅቶች የበለጠ ይስቡኝ የነበረው” (ኢፖምጉሕት ገጽ 13-14)።

የበሬዎቹ መጥፋት ኅብረ ብሔራዊውን ብቻ ሳይኾን በተዘዋዋሪ መንገድ ዘውጋዊ ብሔረተኛውን መረራንም የመቅረጽ ሚና ተጫውቷል። አንድ ፍሬው ልጅ መረራ በሬዎቹን ለማስመለስ ፍርድ ቤት ሲመላለስ የታዘበው ኹነት ዶክተር መረራ ቋንቋን በሚመለከት አሁን ለሚያራምዱት አመለካከት መሠረት ጥሏል። መረራ ገጠመኛቸውን እንዲህ ይገልጹታል፦ “ከሁሉም የበለጠ ልብ የሚሰብረው ግን ለመከራከር በማይችለው ቋንቋ ሞት ተፈርዶበት ሞት እንደተፈረደበት ለመንገር አስተርጓሚውን ስለሚጨንቀው፣ ሞት የተፈረደበትን ሰው ለሌላ ቀን ተቀጥረኻል ሂድ ብሎ ሲያሰናብት ማየት ነው። አንድ ሰው በማያውቀው ቋንቋ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት፤ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ሳያውቅ ጥሩ እንደተሠራለት እጅ ነስቶ እና አመስግኖ መሄድን የመሰለ ግፍ የለም። ዛሬ በቋንቋ ላይ ያለኝ አቋምም መቀረጽ የጀመረው በዚያን ጊዜ ይመስለኛል” (ኢፖምጉሕት 14)።

ታዲያ እነዚህ በትንሹ መረራ አእምሮ ውስጥ አንድ ላይ የተወለዱ እና ተፎካካሪ የሚመስሉ ሁለት አመለካከቶች (ዘውጋዊነት እና ኅብረ-ዘውጋዊነት) ከሞላ ጎደል አንድ ላይ አድገው ነበርና ዩኒቨርሲቲ ለገባው ወጣቱ መረራ ከባድ የምርጫ ፈተና ደቀኑበት። የተማሪዎች ንቅናቄ አፍላ ወቅት ስለነበረ የትኛውን ድርጅት (የኦሮሞ ብሔረተኛ የኾነ ወይስ ያልኾነ) መቀላለቀል እንዳለበት ማወቅ አልቻለም። “መሬት ላራሹ የነፍጠኛ ልጆች ጥያቄ ነው” የሚለው የወቅቱ የኦሮሞ ብሔረተኛ አቋም ባይዋጥለትም ኅብረ-ዘውጋዊ ድርጅቶችን በቀጥታ ለመቀላቀል የሚያበቃ ድምዳሜ ላይ አልደረሰም ነበር ወጣቱ መረራ። ትንሽ ጊዜ ወስዶ በቂ መረጃ ለማግኘት ሲያነብ ከቆየ በኋላ “መሬት ላራሹ የነፍጠኛ ልጆች አቋም ነው” ሲሉ የነበሩ አንዳንድ ኦሮሞዎች ከ“ነፍጠኛ ልጆች” ጋራ አብረው ሲሠሩ አስተዋለ። ከአንዳንድ የኦሮሞ ብሔረተኛ ተማሪዎች ጋራ የመጀመርያ ስር የሰደደ ቅያሜዬም የተፈጠረው በዚሁ ላይ ነው” ይላሉ ዶክተር መረራ በወቅቱ የነበረውን ኹኔታ ሲያስረዱ (ኢፖምጉሕት ገጽ 51)። ከብዙ ውዝግብና ማሰላሰል በኋላ ኅብረ-ዘውጋዊውን መኢሶንን መቀላቀላቸውን ይገልጻሉ ምሁሩ ከኛ። መኢሶንን የተቀላቀሉበት ርግጠኛ እና ዝርዝር ምክንያቶች ግን ምን እንደኾኑ አይገልጹም።

ዶክተር መረራ በጊዜው የነበራቸው ኅብረ-ዘውግ አቋም እጅግ ጠንካራ ከመኾኑ የተነሳ በተለያዩ የኦሮሞ ብሔረተኛ ድርጅቶች ውስጥ የተደራጁ ኦሮሞዎች የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም እንዲያስችላቸው “የኦሮሞ ብሔረሰብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦብዲን) የሚባል ድርጅት ከመኢሶን ጓደኞቻቸው ጋራ እስከማቋቋም ደርሰው ነበር። የኦብዲን ምሥረታ ታክቲካዊ ብቻ ስለነበረ ይመስላል ዶክተር መረራ የንቅናቄው መጨረሻ ምን እንደኾነ አይናገሩም።

ኾኖም ያ ከልጅነታቸው የጀመረው መንታ ልብ (ambivalence) እስከ አሁን ድረስ አብሯቸው ዘልቋል። ኦሮሞነትን እና ኢትዮጵያዊነትን አቻችሎ ለማስኬድ ከዓመታት በፊት የጀመሩት “የገመድ ላይ” ጉዞ ከሁለቱም ጽንፎች በሚነሱ ተጻራሪ ፖለቲካዊ ወጀቦች እየተመታ ክፉኛ ሲያንገዳግዳቸው ይታያል።

በእንግሊዝኛ በሚጽፏቸው ጽሑፎች በተለይ በፒ.ኤች.ዲ መመረቂያ ጥናታቸው በምሁራዊ ግልጽነት እና ፍትኀዊነት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግሮች የሚተነትኑት ዶክተር መረራ በኢፖምጉሕት እና ኢታፈሚሕ ዘውገኝነታቸው ሲያመዝንባቸው ይስተዋላል። ርግጥ ሁለቱ መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ የምርምር ሥራዎች አይደሉም። ፖለቲካ ቢጫናቸው የሚገርም ጉዳይ አይደለም። ፖለቲከኛው መረራ የአቋም ለውጥ አድርገውም ከኾነ ለውጡ በራሱ ችግር ሊኾን አይችልም። ዋናው ጉዳይ ኦሮሞነትን እና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ወጥነት የሚጎድለው እና ለመከራከር አስቸጋሪ የኾኑ አመለካከቶችን ማንጸባረቃቸው ነው።

የኦሮሞን ጥያቄ ታሪካዊ መሠረቶች ለማስረዳት ከሚጠቅሷቸው ምሳሌዎች ሁለቱን እንመልከት፦ የመጀመርያው በኢጣልያ ወረራ ወቅት ለጣልያኖች ያደሩ የኦሮሞ ልኂቃንን ይመለከታል። እንደ ዶክተር መረራ እምነት በወረራው ወቅት ራስ አበበ አረጋይ እና በቀለ ወያን የመሳሰሉ ስመ ጥር አርበኞች ለኢትዮጵያ ነጻነት የታገሉ ቢኾንም ሌሎች የኦሮሞ ልኂቃን ለጣልያን ያደሩት በመገፋት ስሜት በመኾኑ የነበራቸውን ዘውጋዊ ብሔረተኛ ንቃተ ኅሊናና የነጻነት ጥያቄ የሚመለከት ነው።  በኢጣልያዊው ጸሐፊ አልቤርቶ ስባኪ አኀዘዊ መረጃ ላይ ተመሥርተው በተደረጉ ትንተናዎች መሠረት በኢጣልያ ወረራ ወቅት የውግያ አቅም ከነበራቸው ኢትዮጵያውያን መካከል በአርበኝነት የተሠማሩት ቁጥር ከ10 እስከ 15 በመቶ ብቻ የሚገመት ነው። 85 ከመቶ ኢትዮጵያውያን በጣልያን ላይ ጠመንጃ አላነሱም ማለት ነው። በ1940 ዓ.ም የባንዳው ጦር ቁጥር ወደ 15 ከመቶ ተጠግቶ ነበር። በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ምክንያት ለጣልያን አድረዋል። ስለዚህ ለዶክተር መረራ ተገቢ የሚኾነው ታላላቆቹ የኦሮሞ አርበኞች ለምን ጣልያንን ለመውጋት ቆረጡ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው።

ሁለተኛው ምሳሌያቸው በጀነራል ዋቆ ጉቱ የተመራው የባሌ ገበሬዎች ዐመፅ ነው። ዶክተር መረራ ይህ ዐመፅ የኦሮሞ ሕዝብ የመብት ትግል እንደኾነ ለማሳየት በሁለቱም መጻሕፍት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደርጋሉ። አያሌ ውስብስብ መነሻዎች የነበሩት እና በሶማልያ መንግሥት ያልተቋረጠ ድጋፍ የተቀጣጠለ እና የተካሄደን ዐመፅ የኦሮሞ ሕዝብ የመብት ጥያቄ ብቻ እንደኾነ ለማሳመን መሞከር ምን ጥቅም ሊሰጥ እንደሚችል የሚያውቁት ራሳቸው ዶክተር መረራ ብቻ ናቸው። ዶክተር ገብሩ ታረቀ በPower and Protest እንደሚያብራሩት ዐመፁ ዘውጋዊ ይዘት ቢኖረውም (እሱም ቢኾን የኦሮሞዎች ብቻ ሳይኾን የሱማሌዎችም ጭምር ነው) ሃይማኖታዊ ይዘትም ነበረው። የዐመፁ መሠረታዊ መነሻዎች ግን ዶክተር ገብሩ እንደሚሉት የመደብ ልዩነት እና ሥር የሰደደ የአስተዳደር በደል ናቸው።

ከሁሉም የሚያስገርመው የዶክተር መረራ አቋም የሚከተለው ነው፤ “በአጭሩ የኦሮሞ ጥያቄ የተፈጠረው እንደ ትግራዩ እና ኤርትራውያኖቹ ጥያቄዎች በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ መፈጠር ጋር ነው ማለት ይቻላል” (ኢታፈሚሕ ገጽ 23)። አንደኛ፦ የትግራዩን የሕወሓት ርዕዮተ ዓለማዊ ትርክት ለጊዜው እንተወው እና የኤርትራውያኑን ጥያቄ ብንመለከት የኤርትራ የነጻነት ጥያቄ የተፈጠረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሳይኾን በኻያው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኀይለሥላሴ ዘመን ነው፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጣልያን ሽንፈት በኋላ ኤርትራውያኑ በራሳቸው ተነሳሽነት ከኢትዮጵያ ጋራ ለመቀላቀል/ ለመተሳሰር ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር። ሁለተኛ፦ የኦሮሞ የመብት ጥያቄ የተፈጠረው ከዐፄ ምኒልክ የደቡብ ዘመቻ ማግስት መኾኑን ከልባቸው የሚያምኑ ከኾነ ሁለት ጥያቄዎችን መመለስ ይኖርባቸዋል። ሀ) የመብት ጥያቄው እንዲፈጠር ያደረገውን የምኒልክን የደቡብ ወታደራዊ ዘመቻ ሲካሄድ በመሪነት እና በተዋጊነት ወሳኝ ሚና የተጫወቱትን የሸዋ ኦሮሞዎች ምነው ዘነጓቸው? ለ) በወረራ እና በሽንፈት ማግስት የመብት ጥያቄ የሚፈጠር ከኾነ ከሲዳሞ እስከ ትግራይ- ከቤኒሻንጉል እስከ ኦጋዴን በኦሮሞ ተስፋፊዎች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ማንነታቸው እና መሬታቸው የተወሰደባቸውን የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የመብት ጥያቄ ዶክተር መረራ (ሌላ ጊዜ እንደሚያደርጉት) በነካ ብዕራቸው ለምን አልዳሰሱትም? ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔረተኞችን ለማስደሰት ከኾነ ያሳስባል።

መረራ በማወቅም ይኹን ባለማወቅ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን የአማሮች አጀንዳ ብቻ አድርጎ የማቅረብ አባዜ የተጠናወታቸው ይመስላል። “ድርጅታችን እስከ አሁን ሙሉ በሙሉ ማለፍ ያልቻለው ፈተና በአማራ ልኂቃን በሚመራው ብሔረተኝነት እና በኦሮሞ ልኂቃን በሚመራው የኦሮሞ ብሔረተኝነት መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ በጋራ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመፍጠር ተግባር ላይ እንዲሰለፉ ማድረግን ነው።” ይላሉ ድልድይ ለመገንባት የሚሞክሩት መረራ (ኢፖምጉሕት 162-63)። በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ የአማራ ልኂቃንን ሲወቅሱ “በአማራ ልኂቃን በኩል ያለው ችግር ወይ የአማራ ልኂቃንን የሚያሰባስብ ጠንካራ ድርጅት መፍጠር አልቻሉም፤ ወይ ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር ምንም ጠብ ከሌላቸው ኀይሎች ጋር ከልብ ለመሥራት አልተዘጋጁም” በማለት ያማርራሉ (ኢታፈሚሕ 137)። እንደ “ቅንጅት”፣ “አንድነት”፣ እና “ሠማያዊ ፓርቲ” ያሉ ኅብረ-ዘውግ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ደግሞ በተዘዋዋሪ “በአማራ ልኂቃን የሚመሩ” ይሏቸዋል (ኢታፈሚሕ 60)።

ቢያንስ አብዛኞቹ የአማራ ልኂቃን የኢትዮጵያ ብሔረተኝነት ደጋፊዎች መኾናቸው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። ችግሩ ዶክተር መረራ አማራ ያልኾነ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ብሔረተኛ ሊኾን አይችልም (ምናልባት አይገባምም) የሚል አንደምታ ያለው መልእክት በዘወርዋራ ለማስተላለፍ መሞከራቸው ነው። ችግሩ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን እና አማራነትን መቀላለቀል አማራ ያልኾኑ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን መደገፍ (ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ምንም ይኹን ምን) ማለት የዘውግ ማንነታቸውን መጣል ማለት እንደኾነ እንዲሰማቸው ለማድረግ መሞከሩ ነው። ዞሮ ዞሮ መሬት ላይ ያለው ኹኔታ ዶክተር መረራ ትክክል አለመኾናቸውን ያሳያል። ለምሳሌ የአንድነት አመራር አባል የኾኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ፓርቲያቸው በዶክተር መረራ “በአማራ ልኂቃን የሚመራ” መባሉን ክፉኛ በመቃወም “አንድነት” ኅብረ-ዘውግ እንደኾነ እና “የአማራ ልኂቃን” ማለት ኦሮሞ ያልኾነ ማለት ከኾነ ዶክተር መረራ በግልጽ ሊናገሩ እንደሚገባ ኢታፈሚህን በተቹበት አጭር ጽሑፍ ያሳስባሉ። ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን የሚያቀነቅነው ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አባላቱ አብዛኞቹ አማራ ያልኾኑ ኢትዮጵያውያን እንደኾኑም ይታወቃል። ዶክተር መረራ በአንድ ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የኾነ ሰው ያቀረበውን (ከራሳቸው ትንተና ጋራ የሚጋጭ) ሮሮ እንደሚከተለው አስፍረውታል፤ “መታወቂያ ለማውጣት ቀበሌ ሄድኩ፤ ባለሥልጣኑ ‘ብሔርህ ምንድነው?’ ብሎ ጠየቀኝ፤ ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’ አልኹት፤ የቀበሌው ባለሥልጣን ስቆብኝ ‘አማራ’ ብሎ ሞላው። በአገሬ ማንነቴን በአንድ ቀበሌ ሹም ተቀማሁ፤ ከዚህ በላይ ምን ነውር አለ?” (ኢታፈሚሕ ገጽ 154)። መረራ ቀጠል አድርገው “በነገራችን ላይ ምሁሩ የጉራጌ ብሔረሰብ አባል ነው” የሚል ማብራርያ ያክላሉ። ሌላው ምጸታዊ ክስተት ደግሞ በርካታ የአማራ ልኂቃን አማራ የኢትዮጵያውያን ሰለባ ኾኗል በሚል እምነት የአማራ ብሔረተኝነትን የሚያቀነቅኑ ድርጅቶችን በአሁኑ ወቅት እያቋቋሙ መኾናቸው ነው። እነዚህ የአማራ ልኂቃን የሚያስተጋቡት ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ትርክት ይዘት የአማራ ልኂቃንን በዘውግ መደራጀት የሚመኙትን መረራን “አሳ ጎርጓሪ” እንደሚያደርጋቸው በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።

“የቡዳ ፖለቲካ” ምንድን ነው?

እንደ ዶክተር መረራ እምነት ላለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንኳር እንቅፋት ከኾኑ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ፖለቲካው “የቡዳ” መኾኑ ነው። “የቡዳ ፖለቲካ” የሚለውን ሐረግ በአንድ ትውፊታዊ ተረት ላይ ተመርኩዘው የቀረጹት መረራ ትርጉሙን ከልክ በላይ ለጥጠውታል። ሐሳቡን በሦስት መንገድ መረዳት ይቻላል። በአንደኛው አረዳድ የመወነጃጀልና የዜሮ ድምር ጫዎታ (Zero – sum game) ማለት ሲኾን ፖለቲካው ውስጥ ስር የሰደደውን የመጠላለፍ እና የመጠፋፋት ጠንካራ ዝንባሌ የሚገልጽ ነው። ይህን ዝንባሌ ዶክተር መረራ ወጥነት ባለው መንገድ በተለያዩ ቋንቋዎች እና መድረኮች አምርረው ሲተቹ ኖረዋል፤ ከመተቸትም አልፈው መፍትሄው ተቀራርቦ መሥራት እና ለማመቻመች (compromise) ዝግጁ መኾን እንደኾነ በማመን ቃልና ተግባራቸውን ለማገጣጠም እንደጣሩ መታዘብ ይቻላል። በዚህ ጉዳይ ላይ አብረዋቸው ለመሥራት የሞከሩ አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን ጥረቱ ከልባቸው መኾን አለመኾኑን ለማወቅ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ። ቢያንስ ግን በሁለቱ መጻሕፍት ውስጥ የዜሮ ድምር ጫዎታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቁልፍ ችግር መኾኑን በማያሻማ ኹኔታ ለማሳየት ችለዋል። ትክክለኛ ነው የሚሉትን መፍትሔም ጠቁመዋል።

ሁለተኛው “የቡዳ ፖለቲካ” አረዳድ አጠቃላይ የፖለቲካ አቋም ልዩነት እና ግጭትን ይመለከታል። ይኼኛው ትርጉም እንደ አስፈላጊነቱ በኢትዮጵያ ታሪክ አተረጓጎም ላይ የሚነሱ ልዩነቶችንም ሊጨምር ይችላል። በዚህ ረገድ ዶክተር መረራ እንደምሳሌ የሚያነሱት ባንድ ወቅት “አንድ የኢትዮጵያውያን ከበርቴዎች ቡድን” ያቀረበላቸውን ጥያቄና የሰጡትን ምላሽ ነው። ከበርቴዎቹ ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላትን ኬንያ ጋብዘው “አንድ ፓርቲ፣ አንድ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ አንድ አርማ፣ አንድ መሪ” እንዲያመጡ እንደጠየቋቸው ገልጸው የተጠየቁትን ከፈጸሙ “ኢትዮጵያን ነጻ ማውጣት የሚያስችላችሁን ገንዘብ ለማሰባሰብ እንችላለን” አሉን ይላሉ። ይህን ሐሳብ አጥብቀው የተቃወሙት መረራ “ሐሳቡም እንዳይሳካ የቡዳነት ሚና የተጫወትኹት እኔው መኾኔ ነው” በማለት ሐሳቡን ለምን እንደተቃወሙት ያብራራሉ (ኢታፈሚሕ ገጽ 204)። ለተቃውሟቸው ተግባራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ያቀረቡ ሲኾን ፖለቲካዊው ምክንያት የሚታገሉለት የፖለቲካ አቋም እንዳይሸረሸር ከመጠንቀቅ ጋራ የተያያዘ ነው። ይህ የዶክተር መረራ ገጠመኝ እንደሚያመለክተው በሁለተኛው አረዳድ “የቡዳ ፖለቲካ” የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ብቻ ሳይኾን የየትኛውም አገር የፖለቲካ ችግር ነው። የጠንካራ/ ግትር አቋሞች እና ፍላጎቶች መፎካከር እና መላተም የፖለቲካ ተፈጥሯዊ ጠባያት ናቸው። መሠረታዊ የዲሞክራሲ ተቋማትን አስፈላጊ ከሚያደርጓቸውም ሐቆች አንዱም ይኸው ሊጠፋ የማይችል በየትኛውም የተወሳሰበ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖር የአመለካከት ብዝኀነት (diversity of views) ነው።

የታሪክ አተረጓጎምም ቢኾን በአንድ ወገን ሲታይ ከፖለቲካ አመለካከት ጋር በጥብቅ የተሣሠረ ሊኾን ይችላል። ዶክተር መረራ “ለፖለቲካችን መበታተን” እና “ለቡዳ ፖለቲካ” ከዳረጉን ምክንያቶች አንዱ በአገር ደረጃ የሚያስማማ ወይም አሰባሳቢ የታሪክ ውርስ ትተው ያለፉ መሪዎች አለመኖር መኾኑን በአጽንዖት ይገልጻሉ። አሜሪካውያን ጆርጅ ዋሽንግተን እና አብርሃም ሊንከን፣ ቻይናውያን ማኦ ዜ-ዱንግ፣ ሩስያውያን ሌኒን እና ወዘተ ስላሏቸው በየአገሮቻቸው ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ስምምነት እንዲኖር ለማድረግ እንደቻሉ ያምናሉ ዶክተር መረራ። ውርሶቻቸው እጅግ በጣም የሚያወዛግቡትን ማዖን እና ሌኒን እንዲያው ዝም ብለን እንለፋቸው እና አሁንም በአብዛኞቹ አሜሪካውያን የሚከበሩትን እና የሚወደዱትን የመጀመርያውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሽንግተንን እንመልከት፦ ርግጥ ነው ዋሽንግተን ለአሜሪካ እንደ አገር መመሥረት እና በሁለት እግር መቆም እንዲሁም ለዲሞክራሲዋ ቀጣይነት እጅግ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ክብርም ፍቅርም የሚበዛባቸው አይደሉም። በሌላ በኩል ደግሞ በአሁን መነጽር ሲታዩ በርካታ ግፎችን የፈጸሙ መሪም ናቸው፤ በመሞቻቸው ጊዜ ነጻ እንዲወጡ ቢናዘዙም ከ300 በላይ ባርያዎች ባለቤት ነበሩ። ባንድ በኩል ለባሮች ከንፈር እየመጠጡ በሌላ በኩል ባርነት እንዳይጠፋ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው እስከመታገል የደረሱ ናቸው። በአሜሪካ ምሥረታ ማግሥት የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ ፊላደልፊያ (ፔንሲልቬንያ) ስለነበረና ፔንሲልቬንያ ውስጥ ባርነት እየጠፋ በመምጣቱ ዋሽንግተን ባሮቻቸውን ላለማጣት አስደናቂ ዘዴዎችን እስከመጠቀም ደርሰው ነበር። ባሮች ጠፍተው ባርነት ወደሌለባቸው ስቴቶች ሲሄዱ ተይዘው በግድ ወደ ጌቶቻቸው እንዲመለሱ የሚያደርገውን ‘Fugitive Slave Law’ እና የተባለውን ሕግ እንዲጸድቅ ሳያቅማሙ የፈረሙ ናቸው። ኢረክዋ (Iroquois) የተባሉት የተወላጅ አሜሪካውያን (Native Americans) መንደሮች እንዲቃጠሉ በይፋ ትዕዛዝም ሰጥተዋል- ለዚህ ተግባራቸውም “ከተማ አውዳሚ” (town destroyer) የሚል ቅጽል በሰለባዎቻቸው ተሰጥቷቸዋል። ይኹን እንጂ ዶክተር መረራ የባርያ ንግድ እንዲጠፋ አዋጅ የደነገጉትን፣ ምርኮኞቻቸውን አሳድገው ባለሥልጣን እና የቤተሰባቸው አባል ያደርጉትን ዐፄ ምኒልክን ግን እንደ አሰባሳቢ አይቀበሏቸውም። ዐፄ ምኒልክ አወዛጋቢ መኾናቸው የማይካድ ነው – ውዝግቡ ስሜት ሰጠም አልሰጠም ። ቁም ነገሩ በታሪክ አተረጓጎም ላይ የሚነሱ ክርክሮች ከሞላ ጎደል ሁሌም የትም የመኖራቸው ሐቅ ነው። ዶክተር መረራ ወይ ጆርጅ ዋሽንግተንን በቅጡ አያውቋቸውም፤ ወይ ዐፄ ምኒልክ ላይ “ዐይነጥላ” አለባቸው፤ ወይ ሁለቱም ይኾናሉ። ምክንያቱ የቱም ቢኾን ዶክተር መረራን የሚያስገምት ነው።

ሦስተኛው “የቡዳ ፖለቲካ” አረዳድ ጥፋትን ማመንን እና ኀላፊነትን መውሰድን ይመለከታል። በመጀመርያ “ትንኝ እንኳን አልገደልኩም” የሚለውን የመንግሥቱ ኀይለማርያምን ታሪካዊ ክህደት አስታውሰው ዶክተር መረራ ወደ ኢሕአፓና እና መኢሶን ማባርያ የሌለው መወነጃጀል ይሄዳሉ። “ለአብነት፤ የቡዳ ፖለቲካችን (አንዱ ሌላውን የሚከስበት) የተጀመረው በአንጋፋዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን በመኢሶን እና በኢሕአፓ መካከል ነበር። እነሱ የተፈጠሩበት የዛሬ 45 ዓመት ገደማ ይቅርና ዛሬ እንኳ የሁለቱ ድርጅቶች አባላት የስህተት ድርሻዎቻቸውን ውሰዱ ሲባሉ በተገቢው የታሪክ ሚዛን ላይ አስቀምጠው ድርሻዎቻቸውን የሚወስዱ አይመስለኝም” ይላሉ አንጋፋው ተቃዋሚ የቀድሞው የመኢሶን አባል (ኢታፈሚሕ ገጽ 198)። መረራ ይህን ይበሉ እንጂ ራሳቸው ቀንደኛ “ቡዳ” ኾነው ብቅ የሚሉበት ጊዜ አለ። በተለይ በኢፖምጉሕት መኢሶንን እና መሪውን ዶክተር ኀይሌ ፊዳን ነጻ በማውጣት ኢሕአፓን እና አባሎቹን ተጠያቂ በማድረግ ሥራ ላይ ተጠምደው ይታያሉ። እስከ አሁን በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ከተጻፉ መጻሕፍት የተሻለ ነው የሚሉት የሕይወት ተፈራን Tower in the Sky (“ማማ በሰማይ” በሚል ወደ አማርኛ ተተርጉሟል) እንደኾነ መረራ ይናገራሉ። ኢሕአፓ የመጀመርያውን ግድያ በመፈጸም ሁለቱ ድርጅቶች በጥይት ወደመጠፋፋት እንዲያመሩ እሳቱን የለኮሰ እና ለዚህ ኀላፊነቱን መውሰድ ያለበት፣ የትምህርት ደረጃቸው (ከመኢሶን መሪዎች ጋራ ሲነጻጸር) ዝቅተኛ በኾነ ችኩል እና ስሜታዊ ወጣቶች የሚመራ፣ ፀረ-ኦሮሞ አመለካከት የነበረው ድርጅት መኾኑን ለማሳመን ዶክተር መረራ ጥረት ያደርጋሉ። በአንጻሩ መኢሶን በጣም በተማሩ ሰዎች የሚመራ፣ (ከ25 ከፍተኛ አመራር አባላት 14ቱ (52%) ፒ.ኤች.ዲዎች ነበሩ ይላሉ መረራ)፣ ውስብስብ እና አደገኛ ኹኔታዎች ሲፈጠሩ ሰከን ብሎ የሚያስብ ድርጅት የነበረ ሲኾን እንደ ዶክተር መረራ እምነት በይፋ በኃላፊነት ሊጠየቅበት የሚገባ አንድም ነገር አልተጠቀሰም። ደርግን አስተምሮ እና አንቅቶ እንዲደላደል ማድረጉ መኢሶንን በኃላፊነት የሚያስጠይቀው ጉዳይ ነው ብለው አያምኑም ዶክተር መረራ። መኢሶን ታላቅ ወንድማቸው ዲማ ጉዲና የሞተለት እና ራሳቸውም የአምስት ዓመታት እስርን ጨምሮ ብዙ ዋጋ የከፈሉለት ድርጅት በመኾኑ ዕይታቸው ሊዛባ እንደሚችል የሚጠበቅ ቢኾንም ድርጅቱ ከጅምላ ተጠያቂነት ውጭ እንደ ድርጅት ኃላፊነት የሚያስወስደው ጥፋት እንደሌለ ለማድረግ መሞከራቸው ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል።

ኢሕአዴግ በዶክተር መረራ ዐይን

ዶክተር መረራ የኢሕአዴግን አምባገነንነት ለማሳየት የተለየ ጥረት አያደርጉም፤ ኾኖም ገዢው ፓርቲ ምን ዐይነት አምባገነን እንደኾነ እና ለምን አምባገነን እንደኾነ ለማስገንዘብ ዘለግ ያለ ትንተና ያቀርባሉ። የአምባገነንነቱ ባሕርይ፣ የአፋኝነቱ መጠን እና የጭካኔውን ጥልቀት በደርግ ዘመን ከነበረው ጋራ በማነጻጸር ስለ ኢሕአዴግ ያላቸውን አመለካከት ግልጽ ለማድረግ ይሞክራሉ። በሁለቱ መጻሕፍት ከኻያ በላይ የተለያዩ ገጾች ላይ ኢሕአዴግን እና ደርግን ከአምባገነንነት አንጻር ያወዳድራሉ። ከደርግም አልፈው የኢሕአዴግን የአፈና መዋቅር ከሰሜን ኮርያ ጋራ አነጻጽረው የትኛው እንደሚከፋ ለመናገር ርግጠኛ እንዳልኾኑ ይገልጻሉ። ደርግ እና ኢሕአዴግ በተነጻጸሩባቸው የአምባገነንነት ባሕርያት (በርካታ ናቸው) ኢሕአዴግ ከደርግ ተሽሎ የተገኘው በአንዱ ብቻ ሲኾን እርሱም እንደ ዶክተር መረራ አመለካከት በደርግ ዘመን ስብሰባ ላይ ማጨብጨብ ግዴታ የነበረ ሲኾን በኢሕአዴግ ዘመን ግን ግዴታው በደርግ ዘመን የነበረውን ያህል ጠንካራ መኾኑን ርግጠኛ አይደሉም። “ፈረንጆቹ የማይደርሱባቸው እስር ቤቶች እና በማያውቋቸው እስረኞች ላይ (ከደርግ) የከፋ ስቃይ እንደሚደርስባቸው” በቁጭት የሚገልጹት መረራ “አንዳንዶቹ የምርመራ ዘዴዎቻቸው ከደርግም አልፈው ስለሚሄዱ ከእስራኤል፣ ከቻይና ወይም ከሲአይኤ (CIA) ተምረውት ሊኾን እንደሚችል ይገምታሉ (ኢፖምጉሕት ገጽ 108)። የፖለቲካ እስረኞችን የፍትሕ ጥያቄ በሚመለከት ኢሕአዴግ ከደርግ እንደማይሻል የሚያምኑት መረራ ለእናታቸው ቀብር ወደ ትውልድ አካባቢያቸው በሄዱበት ወቅት የኦሕዴድ ባለሥልጣኖች ወደ ቀብር ቦታ የሚሄደውን ሕዝብ ለማቆም የመጓጓዣ አገልግሎት መከልከላቸውን “የደርግ ዘመንን የዘቀጠ ባህል የሚያስታውስ ነው” ይሉታል (ኢፖምጉሕት ገጽ 214)።

ይኹን እንጂ ዶክተር መረራ ኢሕአዴግ እነዚህን እና ሌሎች በርካታ አረመኔያዊ የአፈና ስልቶች የቀሰመው ከደርግ ነው የሚል እምነት አላቸው። ለዚህ እምነታቸው እንደ አንድ ዐቢይ ምክንያት የሚጠቅሱት ገዢው ፓርቲ የደርግ አማካሪዎችን እና ባለሥልጣናትን ወርሶ በታማኝነት እንዲያገለግሉት ማድረጉን ነው።  እንደ ዶክተር መረራ አስተሳሰብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማዳከም እና ማጥፋት፣ ሕዝብን አስፈራርቶ መግዛት፣ በፕሮፖጋንዳ ጋጋታ ሕዝብን ማደንዘዝ፣ በፖለቲካ እስረኞች ላይ አሰቃቂ ግፍ መፈጸም፣ እነዚህ ሁሉ ኢሕአዴግ ከደርግ የተማራቸው ናቸው። “ከሁሉም በላይ ኢሕአዴግ ከደርግ የተማረው እና ምናልባትም ከአንድ ትውልድ በላይ የአገራችንን የፖለቲካ ባህል አበላሽቶ ሊሄድ የቻለው፣ በሆዳቸው ለሆዳቸው ብቻ የሚያስቡትን መፍጠሩ ይመስለኛል” በማለት ምሬታቸውን ይገልጻሉ መረራ (ኢታፈሚሕ ገጽ 49)። መቸም እንደዚህ ዐይነቱ አመለካከት ከየትኛውም (ሐቀኛ) የፖለቲካ ፓርቲ ቢመጣ ግራ ማጋባቱ አይቀርም። ከጎምቱ ተቃዋሚ እና ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ሲመጣ ደግሞ ግራ ከማጋባትም የዘለለ ይኾናል።

እውነት ሕወሓት/ኢሕአዴግ አፈናና ጭካኔ መማር የሚያስፈልገው ድርጅት ነውን? የራሱን አባላት እየገደለ የመጣ፣ ነጻ አወጣዋለሁ የሚለው ሕዝብ በረኀብ በተጠቃበት ወቅት የተሰጠውን ርዳታ ነጥቆ የሸጠ እና ገንዘቡን ለራሱ ጥቅም ያዋለ ድርጅት፣ ለዘረፈው ንብረት ካሳ የሚጠይቅ እና የሚቀበል፣ ቁልፍ የአገሪቱን ተቋማት በአንድ ዘውግ አባላት ቁጥጥር ስር አድርጎ ዐይኑን በጨው አጥቦ ለ25 ዓመታት ሲመዘብር እና ሲያፍን የኖረ፣ ከጥንስሱ በዘውግ ጥላቻ አለት ላይ የተገነባ እና የዘውግ ጥላቻን ሲያመርትና ሲያሰራጭ የኖረ ድርጅት – እውነት ዶክተር መረራ የጠቀሷቸውን እኩይ ተግባራት ያስተምር እንደኾነ እንጂ መማር የሚያስፈልገው ነው? የሚገርመው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ድርግን የሚያስከነዳ “ጥበበኛ” መኾኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ አብነት ዶክተር መረራ ራሳቸው ይጠቅሳሉ፤ “የበለጠ እንቆቅልሽ የሚኾነው ደግሞ፣ አንዳንድ የኢሕአዴግ መሪዎች የተሳተፉበት ያ “መሬት ላራሹ” ትግል ተረስቶ ዛሬ በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት “መሬት ለኢንቨስተሮች” መኾኑን ነው” በማለት አሳዛኙን ምጸት ይገልጹታል (ኢታፈሚሕ ገጽ 49)። ገዢውን ፓርቲ አብጠርጥረው የሚያውቁት ዶክተር መረራ አፈናና ጭካኔን ከደርግ እንደተማረ ማመናቸው ማብራርያ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። እንደውም አንዳንድ የፓርቲው መሪዎች “እንዴት ከደርግ ያሳንሰናል?” ብለው ዶክተር መረራን በስም ማጥፋት እንዳይወነጅሏቸው ያሰጋል።

አንጋፋው ተቃዋሚ የሕወሓት/ኢሕአዴግን አምባገነንነት ምንጭም ይተነትናሉ። ትንተናው ግን መንታ-ልብነት የሚስተዋልበት ነው። በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ “አብዮታዊ ዲሞክራሲን አራምዳለሁ” የሚልበትን ምክንያንት ሲያብራሩ ርዕዮተ-ዓለሙ የተመረጠው ሥልጣን ጨምድዶ ለመያዝ እና ከሥልጣን የሚመነጩ ጥቅሞችን ለማግኘት የሚያስችል ሽፋን ስለሚሰጥ እንደኾነ ያሰምሩበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲው አምባገነን የኾነው አምባገነንነትን የሚሰብከውን እና የሚደነግገውን “አብዮታዊ ዲሞክራሲን” እንደ ሃይማኖት በመቀበሉ እንደኾነ ያስረዳሉ። የምክንያት እና የውጤት ቅደም ተከተሉ ግልጽ አይደለም። ገዢው ፓርቲ አምባገነን የኾነው ለርዕዮተ-ዓለሙ ታማኝ በመኾኑ ነው? ወይስ ፓርቲው አብዮታዊ ዲሞክራሲን የሚያቀነቅነው ለአምባገነንነቱ ሽፋን ለመስጠት ነው? ዶክተር መረራ ሁለቱንም የሚሉ ይመስላሉ። ኾኖም ከለጋስ አረዳድ (charitable interpretation) አንጻር ሲታይ እንደ ዶክተር መረራ እምነት ምንጩ የፓርቲው አምባገነንነት ሲኾን ርዕዮተ-ዓለሙ ለአምባገነንነቱ ሽፋን ለመስጠትና ቅቡልነት (legitimacy) ለማግኘት የሚደረገው ሙከራ አካል ነው ማለት ይቻላል። ለርዕዮተ-ዓለሙ ታማኝ መኾኑ ነው አምባገነን ያደረገው የሚለው አንደምታ ፈጽሞ የሚያስኬድ አይኾንም። በርዕዮተ-ዓለማዊ ሰብ-ነክነት (Ideological prostitution) የተካነውን ፓርቲ ዋና አጀንዳ መሳት ይኾናል። ዶክተር መረራም የኢሕአዴግን መርህ ዐልባነት እና የአንድ ጠባብ የልሂቃን ቡድን ጥቅም አስጠባቂነት በአጽንኦት እና በዝርዝር ያስረዳሉ።

ኢሕአዴግ እና የአሜሪካ የውጪ ፖሊሲ

በኢታፈሚሕ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው። “የአሜሪካንን ጥቅም እስከተጠበቀ ድረስ የአሜሪካ መንግሥት ከማንም መንግሥት ጋራ ይሠራል፣ ነገ ጠንካራ ኾነው የሚወጡ ኀይሎች ከእናት አሜሪካ እንዳይርቁ ለማድረግ ደግሞ በደረጃቸው ይስተናገዳሉ ማለት ነው። ይህንን የአሜሪካኖችን የሁለት ደረጃ ፖሊሲ አውቆ ጫዎታው ውስጥ መግባቱ የእያንዳንዱ ተጫዋች ፈንታ ነው” በማለት አሜሪካ የሌሎች አገሮች ዜጎች የፍትህ እና የዲሞክራሲ ጥያቄ እንደማይገዳት ዶክተር መረራ አበክረው ይገልጻሉ (ኢታፈሚሕ ገጽ 133)። ይህን ሐቅ ተገነዘብኩ የሚሉት በ1992 ዓ.ም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋባዥነት የልዕለ-ኀያሏን ተቋማት በጎበኙበት ወቅት እንደኾነ የሚገልጹት መረራ ሐቁን ለመገንዘብ ያን ያህል ጊዜ ለምን እንደፈጀባቸው ግን አይገልጹም። የጉብኝት ዕድሉን ባያገኙ ኖሮ ደግሞ የበለጠ ጊዜ ሊወስድባቸው እንደሚችል መጠርጠርም ይቻላል። በ1992 ዓ.ም ቢኾንም እንኳን ተጋበዙ።

የኾነው ኾኖ ዶክተር መረራ አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያላትን አመለካከት እና ፖሊሲዋን ለማስቀየር ዕድል አለ ብለው ያስባሉ። “የራሱን ሕዝብ የሚያሸብር መንግሥት፣ በዘላቂነት የጸረ-ሽብር ዘመቻ አጋር እንደማይኾን ያለመታከት ለአሜሪካኖቹ ማስረዳትም የእኛ ፈንታ ነው” ይላሉ (ኢፈታሚሕ ገጽ 112)። በሚቀጥለው ገጽ ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአሜሪካ ባንድ ወቅት ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ ሰማኹት የሚሉትን ቀልድ ይናገራሉ። የቀልዱ አንኳር ጭብጥ ኢትዮጵያ ስር የሰደደ የዘውግ ክፍፍል ወይም ጥላቻ ያለባት አገር መኾኗን ማሳየት ነው። “አሜሪካኖች ይህን ልዩነት አይረዱም ማለት የፖለቲካ የዋህነት ይመስለኛል” የሚሉት መረራ የተለያዩ ዘውግ አባላት የኾኑ ተቃዋሚዎች አንድ ላይ እንኳን ለተቃውሞ መሰለፍ አለመቻላቸው ለአሜሪካ ፈተና እንደሚኾንባት ያክላሉ። ታዲያ አሜሪካ የዶክተር መረራን ምክር እንዴት ትቀበል? እያሰረ፣ እያሰቃየና እየገደለ ዜጎችን ረግጦ ሥልጣኑን በማረጋገጥ የሚያገለግላትን አምባገነን ትምረጥ ወይስ ታማኝ አገልጋይዋን አስገልብጣ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ቁልፍ ብሔራዊ ጥቅም ለአደጋ ታጋልጥ? የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አሜሪካ እምነት ልትጥልባቸው የምትችልባቸው ዐይነት ናቸው?  ለኢትዮጵያውያን ቢዋጥም ባይዋጥም ለአሜሪካ ግን መልሱ በጣም ግልጽ ነው።

ዶከተር መረራ ለአሜሪካ ሌላም ምክር አላቸው። የኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አምባገነኖች ለሕክምና፣ የዘረፉትን ንብረት ለማከማቸት እና ከሥልጣን ሲባረሩ የሚሄዱት ወደ አሜሪካ በመኾኑ ከቻይና የሚመጣባትን የዲፕሎማሲ ፉክክር በቀላሉ ለመቋቋም የምትችልበት መንገድ አለ፣ እንደ አንጋፋው ተቃዋሚ። የኀይለሥላሴ እና የደርግ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ታምራት ላይኔ፣ አልማዝ መኮ፣ ሃሰን ዐሊ እና ጁነዲን ሳዶ ወደ አሜሪካ መሰደዳቸውን ይጠቅሳሉ። ከገዢው ፓርቲ ጋራ በጥቅም የተሳሰሩ እንደኾኑ የሚታመን እዚያው “የሚርመሰመሱ ነጋዴዎችም” እንዳሉ ያስታውሳሉ። ታዲያ አሜሪካ ከፈለገች የተሻለ በምትወዳደርበት በዲሞክራሲ ብትጠቀም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን በቀላሉ አጋር ማድረግ ስለምትችል በአምባገነንነት ልምዷ የምትተማመነውን ቻይናን ማሸነፍ ትችላለች፤ እንደ ዶክተር መረራ አስተሳሰብ። ይኼንንም ምክር አሜሪካ ለምን እንደምትቀበል የሚያውቁት መረራ ብቻ ናቸው። ዲሞክራሲ በሰፈነበት አገር መሪዎች የመጀመርያ ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው ሕዝብ ኾኖ እያለ፣ ተጠሪነቱ እና ተጠያቂነቱ ለመረጠው ሕዝብ የኾነ ድርጅት ወይም ግለሰብ በአሜሪካም ኾነ በሌላ ኀይል ሊሽከረከር እንደማይችል ግልጽ ኾኖ ሳለ፣ አሜሪካ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎችን አስገልብጣ ተላላኪ አምባገነኖችን የማስቀመጥ ረዢም ታሪክ ያላት አገር መኾኗ የአደባባይ ምሥጢር በኾነበት ኹኔታ ዶክተር መረራ አሜሪካ ዲሞክራሲን ከልቧ እንድትደግፍ መምከራቸው ቅንነታቸውን ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ ያለው አይመስልም።

ማጠቃለያ

ሁለቱ የዶክተር መረራ መጻሕፍት በዚህ አጭር ዳሰሳ ከተነሱት በተጨማሪ እጅግ በርካታ አስተማሪ፣ አወያይ እና አዝናኝ ጉዳዮችን የያዙ ናቸው። አንባቢ በፖለቲካ አመለካከታቸው ቢስማማም ባይስማማም ዶክተር መረራ ስር የሰደደውን እና ክፉኛ የተወሳሰበውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የበኩላቸውን ጥረት እና አስተዋጽዖ በቅንነት ሲያደርጉ እንደቆዩ እና እያደረጉም እንደኾነ ብዙዎችን ለማሳመን የቻሉ ይመስላል። በኢፖምጉሕት እና በኢታፈሚሕ በግልጽ እንደሚታየው መረራ ተቃውሞ እና ቁጣ የሚገጥማቸው ከኢትዮጵያ ብሔረተኞች ብቻ ሳይኾን፣ “ኦሮሞ ዘመዶቼ” ከሚሏቸው የኦሮሞ ብሔረተኞችም ጭምር ነው። እንደውም የሚከፋው የኦሮሞ ተቃዋሚዎቻቸው ተቃውሞ ሳይኾን አይቀርም። ኾኖም እርሳቸው እንደሚያምኑት አብዛኛው የኦሮሞ ብሔረተኛ ከእርሳቸው ጋራ የሚቀራረብ አቋም እየያዘ መጥቷል። የገመድ ላይ ጉዟቸውም ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግሮች የሚፈቱ ከኾነ እንደ መረራ “የመጣው ይምጣ” ብለው ድልድይ ለመሥራት የሚጥሩ ፖለቲከኞች ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው። ለማንኛውም ለሁለቱ መጻሕፍት ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል። የፖለቲካ ጉዟቸውም ከገመድ ወደ አርማታ እንዲሸጋገር መመኘቱ አይከፋም።

ምንጭ – ስባት ኪሎ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: