የኛ ሐዋርያት …በቀራንዮ መንገድ ላይ! – ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ – አሜሪካ)

(በኢትዮጵያ በሚታተመው “አዲስ ገጽ” ቁጥር 10 ላይ ታትሞ የወጣ።)

ነብዩ መሃመድን ጨምሮ ሌሎች ነብያት ህዝባቸው ሃጥያት መስራት እንዲያቆም፣ መንግስት ግፍ መስራት እንዲተው ምክር ሰጥተዋል፤ ክርክር ገጥመዋል።  ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሃጢያት በደሙ ሊያስተሰርይ በመስቀሉ ላይ ደሙን አፍስሷል፤ ስሙን አንግሷል። የኛም ክርስቶሶች የእስር ዋጋ እየተቀበሉ፤ በደማቸው አክፋይ የመስዋዕትነትን ዋጋ እየከፈሉ… ትላንት በታሪክ ነበሩ፤ ዛሬም በኛ ዘመን አሉ። የኛ ጋዜጠኞች የመሰቀያቸውን ግማድ ተሸክመው፤ እንደክርስቶስ ጉዟቸውን በቀራንዮ መንገድ ላይ አድርገዋል። ከ’ነሱም ጋር በሺዎች የሚቆጠሩ ትውልድ ብጹዓን የሚላቸው፣ ኢትዮጵያዊ ሐዋርያት አሉን። እነሆ ወደቀራንዮ የሚደረገው ጉዞ ተጀመረ እንጂ፤ አልተገባደደም። አብረን እንጓዝ።

Tensaye አቶ መለስ ዜናዊ ከመሞታቸው በፊት፤ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም በፊት፤ በሽግግር መንግስቱ ሰሞን… ከሓዳስ ኤርትራ ጋዜጠኛ ጋር አንድ ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር። በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ ጋዜጠኛው እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “እርስዎ የኢትዮጵያ መሪ ባይሆኑ ኖሮ፤ ምን ይሆኑ ነበር?” አላቸው።

አቶ መለስም… “መሪ ባልሆን ኖሮ፤ ጋዜጠኛ እሆን ነበር” የሚል ፈጣን ምላሽ ሰጡ።

እንግዲህ ይህ የጋዜጠኝነት ሙያ፤ መሪዎች ጭምር ወደፊት ይሆኑ ዘንድ የሚመኙት የነበረና የተከበረ ሙያ ነው። የተከበረ የሚያደርገው ደግሞ፤ ጋዜጠኛው ለጥቂቶች ሳይሆን ለብዙሃኑ እና ለተገፉት አንደበት ሆኖ ድምጻቸውን ስለሚያሰማላቸው ነው። እንዲህ አንገታቸውን ቀና አድርገው እውነትን የተናገሩና የመሰከሩ ጋዜጠኞች፤ እንደሻማ እየቀለጡ እና እንደብረት እየተቀጠቀጡ፤ ከአላማቸው ፍንክች ሳይሉ ሞትን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ስናይ… ሰማዕትነታቸው ያስቀናናል፤ መስዋዕትነታቸው ያኮራናል። እነዚህ ኩሩ ኢትዮጵያውያን እንደክርስቶስ በሃሰት ተመስክሮባቸው፤ የክብር ጌጣቸውን ተሸክመው በቀራንዮ አቀበት ላይ ናቸው። እነሆ ከስቃያቸው ስቃይ ከፍለን ሸክማቸውን ባንሸከምም፤ ዛሬ እነሱን እናስታውሳለን፤ እንዘክራቸዋለንም።

በአንድ ወቅት ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወደ አውሮጳ የሚወጣበት አጋጣሚ ተፈጠረና ደውዬ እንዳናግረው ተደረኩ። ተመስገን ስለመልካሙ ሃሳባችን አመስግኖ፤ ነገር ግን ወደውጭ ወጥቶ የመቅረትም ሆነ ቀሪ ዘመኑን በስደት ለማሳለፍ ፍላጎት እንደሌለው በትህትና ገለጸልኝ። እስክንድር ነጋም ቢሆን በአሜሪካ የነዋሪነት ፈቃድ የነበረው፤ ቀሪ ኑሮውንም በአሜሪካ ማድረግ የሚችል ሰው ነበር። ነገር ግን በአገሩ ላይ መስዋዕት መክፈልን መረጠ። ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬም ቢሆን፤ በብዕሩ መንግስትን እንጂ ህዝብን እንዳላሸበረ ከሳሾቹ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሆኖም ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ ሆነና በክርስቶስ ስም ምለው የሚገዘቱት ጠቅላይ ሚንስትራችን ጭምር፤ “አሸባሪዎች!” ብለው የማይፈነክት ድንጋይ ወረወሩባቸው።

“እኔ የተሻልኩ ነኝ” የሚሉ ሰዎች መሻላቸውን ማሳየት ያለባቸው ፍርደ ገምድል በመሆን ሳይሆን፤ ተሽለው በመገኘት ነው። ንጹህ ዜጋን በጉልበት ወህኒ አስገብቶ መክሰሱና ፍርድ መስጠቱ፤ ለባለግዜዎች ቀላል የመሆኑን ያህል ወደፊት በታሪክ ፊት መዳኘት ራሱ ከባድ ፈተና ነው። ለነገሩ ቀዳሚው አለመታወቁ እንጂ፤ ሞትና ወህኒ ቤት ለታጋዮች መታፈሪያቸው እንጂ ማፈሪያቸው አይደለም። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ መሪ የተባሉ መሪዎች ግን ቢያንስ፤ ጋዜጠኞችን “አሸባሪዎች ናቸው” ብለው ባይዋሹ በመጨረሻው ሰአት ከመቀሰፍ ይተርፉ ነበር።

ነገሩ አንድ ቀልድ ያስታውሰናል። እንዲህ ነው። አንድ የአገር መሪ፣ ጋዜጠኛ እና ቄስ በአንድ አነስተኛ አውሮፕላን እየሄዱ ሳለ፤ የአውሮፕላኑ ሞተር እየሞተ መጣና ፓይለቱ ፓራሹቱን ታጥቆ እንዲህ አላቸው፤ “አውሮፕላኑ ሊከሰከስ ነው። ያለን ፓራሹት ግን ሁለት ነው። ተስማምታቹህ በመጠቀም፤ በሁለቱ ፓራሹቶች እራሳችሁን አድኑ” ብሎ ዘሎ ወረደ።

በመቀጠል  የአገር መሪው፤ “ይህ የአሸባሪዎች ድርጊት መሆኑን ደርሰንበታል።” ብሎ በችኮላ አነስተኛ ሻንጣውን በጀርባው አዘለ። ከዚያም “ለማንኛውም እኔ የአገር መሪ ስለሆንኩ፤ ከናንተ ይልቅ ለህዝቡ አስፈልገዋለሁ” አላቸውና ተንደርድሮ ወደ ታች ተምዘገዘገ።

ከዚያ ቄሱ ለጋዜጠኛው እንዲህ አሉት። “እኔ ብዙ አመት ኖሬያለሁ። አንተ ግን ገና ብዙ ስለምትኖር፤ አገርህንም ወደፊት ስለምታገለግል የቀረውን አንድ ፓራሹት ተጠቀምበት” አሉት።

ጋዜጠኛውም ለቄሱ መለሰላቸው፤ “አያስቡ አባ።” አለ… “አያስቡ አባታችን። ሰውየው ፓራሹቱን ሳይሆን፤ ሻንጣውን በጀርባው ተሸክሞ ነው የወረደው።” አለና አንዱን ለራሱ ወስዶ፤ ሁለተኛውን ፓራሹት ለቄሱ ሰጣቸው።

ዘር እና ጥላቻን መሰረት ያደረገው ፖለቲካ… አገራችን በአንድ ሞተር ብቻ እንደምትበር አውሮፕላን እያስመሰላት መጥቷል። ይህ የዘር እና የቂም ፖለቲካ እየጠነከረ ሲመጣ መሪዎች ያለ ፓራሹት ከላይ ወርደው ይፈጠፈጣሉ። በአደጋው ግዜ የዳኑት ድነው፤ “አውቀናል” በሚል የዘር እና የጥላቻ ፖለቲካ ልባቸውን ያደከሙ ሰዎች፤ እንደዱባ ቁልቁል ወርደው ሲፈጠፈጡ ለመታዘብ በቅተናል። እኛ ግን ከነሱ ይልቅ የጋዜጠኞቻችን ጉዳይ፤ ብሎም ከዚያ ጀርባ ያለው የሃሰት ፕሮፓጋንዳና የፍትህ ሽል ውርጃ ያሳስበናል።

ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፤ ስለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ስለመሰከሩ፤ ሃሳባቸውን በነጻነት ስለገለጹ ክብር እና ምስጋና ሲገባቸው፤ እስር እና እንግልት ኒሻናቸው ሆኖ ወህኒ ተወርውረዋል። ህዝቡ “ጀግና” በሚል ክብር ሲጠራቸው፤ ገዢዎች ደግሞ “አሸባሪ” የሚል ቅጽል ሰጥተዋቸዋል። ሌባ ፖሊስን እንደሚጠላ ሁሉ… እራሳቸውን ለገዢው አካል ተገዢ ያደረጉ ግለሰቦች ለጋዜጠኞቻችን ያላቸው ጥላቻ እና የጠላትነት መንፈስ መስመሩን የለቀቀ ነው። ይህ አስተሳሰብ ሊቀየር ይገባል። ለዚህ ደግሞ እንዲህ አይነት የተዛባ እና የተሳሳተ አመለካከት የሚፈጥረውን ግዙፍ አካል ማስተካከል የግድ ይላል።

እንደእውነቱ ከሆነ…  ከወንድሞቻችን መታሰር ባልተናነሰ ሁኔታ፤ ከዚህ ጀርባ ያለው ግዙፍ የቅጥፈት ፋብሪካ ያስፈራናል። ይህ የቅጥፈት ፋብሪካ ከግዜ ወደ ግዜ ራሱን እያሳደገና እየሰፋ በመምጣት ላይ ነው። ይህ ግዙፍ የመንግስት አካል ህግን እሱ በሚፈልገው መንገድ ወይም ለሱ በሚመቸው መንገድ አጣሞ ይጠቀምበታል። የራሱ የሆነ አፋኝ የደህንነት ቡድን፣ በህግ ስም አንቀጽ ጠቅሶ የሚከስ እና የሚዳኝ፣ በእስር ወቅት ተቃዋሚ የነበረ እስረኛን የሚያሰቃይ ልዩ ሃይል አለው። ጋዜጠኛ ውብሸት በጓደኞቹ እንዳይጠየቅ፤ ተመስገን ደሳለኝ ከነጀርባ ህመሙ እንዲሰቃይ፤ እስክንድር ነጋን ሰው እንዳያየው የሚያደርግ ጨካኝ የሰዎች ስብስብ አላቸው። የጋዜጠኛ እስክንድርን እናት ሃብት ወስደው፤ የሱን ንብረት እና ቤት በዳኛ ውሳኔ አስፈርደው ወርሰውበት፤ እስር ቤት ውስጥ ያለውን መጽሃፍት፣ በርጩማ እና ሌላ ቁሳቁስ… ጥርስ ብሩሽ እና ሳሙና ሳይቀር ቀምተው… ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሏቸው በእጁ ላይ የነበረውን የመጨረሻ ሃብት መጽሃፍ ቅዱሱን ወስደውበት… የ’ስር ቤቱ ንብረት የሆነ አንድ አሮጌ ባልዲ ትተውለት፤ ይቺኑ ባልዲ እንደወንበርም እንደጠረጴዛም እንደመተከዣም ሲጠቀምባት ሲያዩ ደስ የሚላቸው ጨካኝ ሰዎችን ነው በየወህኒ ቤቱ ጭምር እያፈሩልን ያሉት። ሌላው ቀርቶ እነዚህን በአሸባሪነት ስም የታሰሩ ሰዎች እስረኛው ሲያናግራቸው ከተገኘ ከፍተኛ ቅጣት ስለሚደርስበት፤ ደፍሮና ቀርቦ የሚያናግራቸው እንዳይኖር ጭምር አድርገዋቸዋል። ይሄ ሁሉ የሚሆነው ጨቋኙንና ጨካኙን ደርግ ጨርሼዋለሁ ብለው በሚፎክሩ እንደሰው በተፈጠሩ ‘ሰዎች’ መሆኑን ልብ በሉ።

ይሄም ሁሉ ሆኖ ከዚህ ጀርባ ሌላ የሚያናድድ አመል አላቸው። ይዋሻሉ። አሁን ከላይ የተዘረዘረው ነገር ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጭምር ቢነገራቸው፤ እውነት መሆኑን እያወቁት የህሊናቸውን አይን ጨፍነው ሽምጥጥ አድርገው ይክዳሉ። ይሄ ነገራቸው ደግሞ እንደጉንፋን ከአንዱ ወደአንዱ የሚጋባ በሽታ እየሆነ መጥቷል። ከ’ነሱ አልፎ ትውልድ ጭምር በውሸት በሽታ ተለክፎ፤ የማናውቀው የክህደት ባህል እንደአረም ሆኖ እየወረሰን ይገኛል። በየአመቱ ውሸት እና ክህደት እየጨመረ፤ ቅን ልቦና ንጹህ ህሊና ደግሞ እየመነመነ በመምጣት ላይ ነው። በየመንግስት መስሪያ ቤቱ በሃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች፤ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ እስከሚመስል ድረስ ብዙዎቹ ለሌላው ግድ የለሽና ጨካኝ እየሆኑ ናቸው። ይሄ ሁሉ ከአንዱ ትውልድ ወደሌላኛው እንደውርዴ በውርስ መተላለፍ ከጀመረ ሰነባበተ።

ባለፈው ሰሞን… እኛ ባለንበት አትላንታ ከተማ የትልቁ ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ፤ ፓስተር ቶሎሳ ጉዲና ምዕመናኑ ፊት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ አሉን። “ምነው?” ብንል…

“ኢትዮጵያ ውስጥ ቅንነት እየጠፋ ነው።” ብለው አዝነው አለቀሱ አሉ። እውነት ነው። ነገሩ ያስለቅሳል። ቅን መንግስት ቢኖረን እኮ ህዝቡም ያንን ቅንነት ለመውረስ ቅርብ ይሆን ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ከመሪዎች የሚወረሰው መልካም ነገር እየተሟጠጠ መጥቶ ሸር እና ተንኮላቸው እንደጀብዱ የሚወራበት ዘመን ላይ ደረስን… እውነትም ይሄ ያሳዝናል፤ ያስለቅሳልም።

“ህዝብ መሪውን ይመስላል” እንዲሉ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከነገሥታቱም ከፕሬዘዳንቱም… ወኔ እና ጭካኔን እየተማረ ዛሬም ድረስ አለ። ጨካኝ ንጉሥ ሲነሳ ህዝቡ ጭካኔን ይማራል፤ ደግ ንጉሥ ሲነግስ ህዝቡም ቅንነትን ይማራል። በዚያኑ ልክ ደግሞ ጥፉ እና ክፉ መንግስት ሲመጣ፤ ትውልድ አለቆቹን እየመሰለ – ሰው ሆኖ በአውሬ ልቦና ውስጥ ሲኖር እናያለን። ጋዜጠኛን “አሸባሪ” ብሎ ከሚከራከር ጠቅላይ ሚንስትር ወይም ሌላ ሚንስትር፤ ይህ ትውልድ ውሸት እንጂ ብዙም ሌላ የሚማረው ነገር አይኖረውም።

አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ቋንቋችን እንደባቢሎን ዘመን ተዘበራርቆ፤ እኛ የምንለውን እንዳይሰሙ… እነሱ የሚሉትን እንዳንሰማ ቢደረግም፤ ደግመን ደጋግመን ኢትዮጵያዊነትን ማስተማር ይገባል። ፍቅር በመስጠት መልካም ምሳሌ መሆን ካልቻልን ወደ ቀራንዮ የሚወስደውን አቀበት መንገድ ብቻችንን ችለን አንዘልቀውም። በመተባበር እንጂ በመነጣጠል አናሸንፍም። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ።

ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ እድሜያችን በሃያዎቹ ውስጥ የነበርን ልጅ እግር ጋዜጠኞች፤ ዛሬ የእርጅናን ሰፈር ከቅርብ ርቀት ላይ ሆነን በማየት ላይ ነን። በትዝታ ወደኋላ መለስ በማለት ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ያሳለፍነውን የልጅነት ዘመን ስመለከት፤ በወጣትነት እድሜ… ለወጣቱ መልካም አርአያ ለመሆን የደከምነው  ግዜ ይበልጥብኛል። ነጻው ፕሬስ ከመስፋፋቱ በፊት፤ ኢህአዴግ አዲስ አበባ እንደገባ… ስለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እና ስለህዝቧ  አንድነት መመስከር ያለህግ የሚያሳፍን ወይም የሚያሳስር ነገር ሆኖ ነበር። ሰንደቅ አላማችንና ጀግኖቻችን ተዋርደው አንድነታችን ጥያቄ ውስጥ በገባበት ወቅት እስክንድር ፒያሳ ላይ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አስጀመረ።

የአካባቢውን ወጣቶች በማሰባሰብ ለቡድኖቹ ስም ሰጣቸው። አንዱን ’ምኒልክ’፣ ሌላውን ‘ቴዎድሮስ’፤ አንደኛውን ሰንደቅ አላማ፣ ሌላኛውን ‘አንድነት’ ብሎ በመሰየም በፒያሳው ሜዳ ላይ የኳስ ግጥሚያ ያካሂድ ጀመር። የምኒልክ ቡድን ሲያሸንፍ ተጫዋቹና ቲፎዞው ወደ አጼ ምኒልክ አደባባይ ሄዶ፤ “ምኒልክ ህያው ነው” እያለ መፈክር ያሰማል። የአንድነት ቡድን ካሸነፈ… “አንድ ነን” እያለ ይዘፍናል። የሰንደቅ አላማ ቡድንም የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውለበልባል። በዚህ አይነት ዘዴ ወጣቱ ገና በጠዋቱ ስለኢትዮጵያ አንድነት እንዲነሳ የበኩሉን ያደርግ ነበር። እንዲህ አይነት መልካም ተግባር የሚፈጽመው ጓደኛችን አሁን በእስር ላይ ይገኛል። የእስክንድር እና ሌሎች ጋዜጠኞች መታሰር ሳያንስ፤ ከሌላው ወገን የምንሰማው የሃጢያት አንደበት ግን፤ ዛሬም ሳይታክት… ጋዜጠኞቻችንን “አሸባሪዎች ናቸው” ይለናል። ውሸቱን ከመለማመዳቸው ብዛት ይሄን ሁሉ ሲሉ… ህሊናቸውን አይቀፋቸውም፤ ምላሳቸውንም አያነቅፋቸውም።

“ህዝብ መንግስትን ይመስላል” ስንል ለጉዳዩ ማብራሪያ ሳያስፈልገው፤ እያንዳንዳችን በታሪክ ወደኋላ ተመልሰን የመንግስታት እና የህዝቡን ተወራራሽ ባህሪ ልናጤነው እንችላለን። መሪዎች ወደ አደባባይ ወጥተው የጥፋት ዘር ሲዘሩ፤ “የለም! ይሄ ለኢትዮጵያ አይበጅም” የሚል ወገን እና ፕሬስ ከሌለ፤ ሙሰኞች ህዝቡን እየዘረፉ፣ አምባገነኖች በጠመንጃ እየገዘፉ… ውሸታቸው እየተደጋገመ፤ ሲደጋገም ደሞ ውሸታቸው እውነት እየመሰለን ሊመጣ ይችላል። ከዚያም አልፎ የተሳሳተ እምነታቸው ጭምር በሌላው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም።

“ህዝብ መሪውን ይመስላል” ለሚለው ቃል ሌላ  ማጠናከሪያ ምሳሌ ላክል። በአጼ ምኒልክ ዘመን የሆነ ነገር ነው። አጼ ዮሃንስ ከሞቱ በኋላ… በ1880ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ክፉኛ በድርቅ ተጠቃች። የድርቁ ዋና መንስኤ ዝናብ ጠፍቶ ሳይሆን፤ ከብትበበሽታ በማለቁ ነበር። በዚያን ግዜ ህዝቡ ከበሬ በቀር ሌላ የማረሻ መንገድ የለውም። ከገሶ እና ዲጂኖ ውጪ እንደ ዶማ አይነት መኮትኮቻ እምብዛም አያውቅም። እናም ከብቱ ሲያልቅበት… ሞፈር እና ቀንበሩን ሰቅሎ፤ በረሃብ እሳት እየተቆላ አለቀ። በዚህን ግዜ አጼ ምኒልክ የውጭ አገር አማካሪዎችን ሰብስበው፤ “የአገሬ ሰው በሬው ቢያልቅበት፤ በእጁ አፈር እየጫረ መዝራት ጀመረ። እንደው ለመሆኑ እናንተ አገር በሬ ሳይኖር፤ መሬቱን እንዴት ነው የምታለሙት?” አሏቸው።

“ከብረት የሚሰራ መኮትኮቻ አለ” ይሏቸዋል።

አጼ ምኒልክ የተባለውን መኮትኮቻ ዶማ በብዛት ከውጭ አገር አስመጥተው፤ ገሚሱን እንጦጦ ጋራ ላይ እንዲቀመጥ ያስደርጋሉ። በንጋታው ወደ እንጦጦ ተራራ ሲወጡ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ፤ ይሄ ‘ከውጭ አገር መጣ’ የተባለውን መኮትኮቻ ለማየት በእግር እና በበቅሎ ግር ብሎ ይከተላቸዋል። አጼ ምኒልክ እንጦጦ ጋራ ላይ ዶማዎቹ ከተቀመጡበት መጋዘን ሲደርሱ፤ ከበቅሏቸው ወርደው አንዱን ዶማ አስመጡና መቆፈር ጀመሩ። በዚህን ግዜ ሌሎቹ ተከታይ መኳንንቶች… “ኧረ አይገባም ጃንሆይ! እናግዝዎ!” በማለት ዶማውን እንዲሰጧቸው ተሽቀዳደሙ።

በዚህን ግዜ አጼ ምኒልክ፤ “ይሄ እኔ የምሰራበት ዶማ ነው። ለናንተ የሚሆናችሁን ዶማ እያመጣቹህ እንደኔ ኮትኩቱ።” አሏቸው። ከዚያም እዚያ የተሰበሰበው መኳንንት በሙሉ እየተሽቀዳደመ አንዳንድ ዶማ እያነሳ እንጦጦ ጋራን በዶማ አረሱት። በመጨረሻም የባህርዛፍ ፍሬ ተከሉና ሁሉም አንዳንድ ዶማ ወስዶ እንዲያስተዋውቅ አስገደዱ።

ከእንጦጦ ጋራው የዛፍ ተከላ በኋላ ዶማ በመላው ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ተዋወቀ። በርግጥ ሰነፎች እና አሽሟጧጮች ዛሬም ድረስ፤ “ከእጅ አይሻል ዶማ።” ሲሉ ከሰማቹህ ከእንጦጦ የተረፈ ተረት መሆኑን ልብ ይበሉ። ይሆነ ሆነና አጼ ምኒልክ ዶማን በዚህ መልኩ አስተዋወቁ። እንግዲህ ከመቶ አመት በፊት… እንዲህ በመስራት ምሳሌ መሆን ከተቻለ፤ በሰለጠነው ዘመን ህዝብን በመልካም አስተዳደር እጦት ማመስ እና ማተራመስ እድገት ሳይሆን ውድቀት ነው ሊሆን የሚችል።

የእንጦጦ ጋራ ነገር ከተነሳ አይቀር… እንጦጦ ጋራን ይዘን እስከ ሱሉልታ የሚወስደውን መንገድ ይዞ የሚሄድ ሰው አንድ ነገር ይታዘባል። ከአዲስ አበባ ውጪ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የነበረው መሬት በሙሉ ታጥሯል። ገበሬው እና የአካባቢው ነዋሪ ተነስቶ ቦታው የተከለለው ለልማት ተፈልጎ አይደለም። ወይም ለህዝቡ ጥቅም አይደለም። ይህ በመኪና ሄደው ሄደው የማይጨርሱት ቦታ የታጠረው ለ”መለስ ዜናዊ መታሰቢያ” የምታስቢያ ድርጅቱ ወይም ማዕከሉ የበላይ ሃላፊ ደግሞ ማነው? የሙስና እመቤቷ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ናት። እሷና መሬት ሲገናኙ ምን ልታደርገው እንደምትችል፤ አንድ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ቢጠየቅ አብራርቶ የሚመልሰው ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም። እግረ መንገድዎን ግን ልጆች ጭምር ከዘመኑ መሪዎች ምን እየተማሩ እንደሆነ አስቡት። የመልካም ምሳሌነቱን ነገር እዚህ ላይ እናሳርፈውና ስለፍትህ መጓደል ትንሽ አውግተን እንለያይ።

እንደ እውነቱ ከሆነ… ኢህአዴግ የደርግን ወታደር እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ አላሸነፈም። ማሸነፍ ያልቻለበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ገና ከጅምሩ ከሰንደቅ አላማው ጀምሮ፤ ታሪክን ማዛባት እና የህዝብ እሴቶችን ማናጋት ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ በመንቀሳቀሱ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ሺህ አመታት ይዞት ከቆየው እሴቶቹ መካከል ደግሞ፤ አንደኛው የተስተካከለ ፍርድ ማግኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነበር።

ደሃው “ባይበላ ባይጠጣ ይቅር” ብሎ የተስተካከለ ፍርድ ለማግኘት፤ አገር አቋርጦ ንጉሡ ፊት መሬት ስሞ “አቤት” የሚልበትን ዘመን ባናየውም፤ አባቶች ለዚህ ምስክር ናቸው። የበላይ ሃላፊዎች ሲሾሙ፤ “ፍርድ እንዳታጓድል፤ ደሃ እንዳትበድል።” ተብለው ነው የመንግስት አደራ የሚቀበሉት። ይሄ የድሮ ታሪክ ሊሆን ይችላል። አሁን ያሉትን ባለስልጣናት ካየን በተቃራኒው፤ “ፍርድ አጓድል፣ ደሃን በድል” የተባሉ ይመስል ህዝቡን ሲያምሱት ይውላሉ። አንድ ሃላፊ ጋር ገብተው በአክብሮት መነጋገር አይቻልም፤ ባይጥልዎትም ሊዘረጥጥዎ ይችላል። እድገትን በፎቅ ብዛት ሳይሆን፤ በአተሳሰብ ጥልቀት ከመዘነው ብዙ ተበልጠናል።

በቅርቡ ትልቅ ድርጅት በመንገድ ሰበብ የፈረሰባቸው ዘመዶቻችን፤ “አቤት” ለማለት አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በብዙ ደጅ ጥናት ባለስልጣኗን ለማነጋገር ቢሮዋ ገቡ። የህወሃት አባል መሆኗ ላይገርምዎ ይችላል። ነገር ግን በችሎታዋ ቦታው ላይ ብትቀመጥ መልካም ነበር። ዘመዶቻችን ጉዳያቸውን ያስረዱ ጀመር። “ይሄን ቦታ ከጃንሆይ ዘመን ጀምሮ ሰርተንበታል። ደርግም አልወረሰብንም። አሁን ግን ካሳ እንንኳን ሳይሰጠን ፈረሰብን።” አሏት።

ባለስልጣኗ የተባለውና የፈረሰውን ቦታ የምታውቀው ትመስላለች። ግን ደግሞ ተናዳላች። “ስንት አመት ሰራችሁበት?” አለች።

“እኛ ሳንወለድ ጀምሮ የነበረ ነው። ከስልሳ አመት በላይ ሰርተንበታል።” አሏት። ከዚያ በኋላ ሴትዮዋ የጭቃ ጅራፏን አወረደችባቸው።

“ለስልሳ አመት የህዝቡን ስትመጡት ኖራችኋል ማለት ነው። እንደናንተ አይነት ፓራሳይቶች ናቸው ያስቸገሩን…” በማለት እዚህ ላይ መዘርዘር የማያስፈልጉ ስድቦች አክላበት፤ አዋርዳ ከቢሮዋ አባረረቻቸው። ሰው በአገሩ እንዲህ አይነት ግፍ እየተፈጸመበት ነው። ጉዳዩ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር። ጭራሽ ከፈረሰ አራት አመት ለሆነው ህንጻ የአንድ ሚሊዮን ብር የግብር እዳ እንዲከፍሉ፤ ካልከፈሉ ሌላ ንብረታቸው እንደሚወረስ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸው፤ ሳይወዱ በግድ ገንዘቡን ከፈሉ።

ይሄ እንደምሳሌ ያነሳሁት ታሪክ የተጋነነ አይደለም። እንዲያውም ቦታ ላለመጨረስ በአጭሩ ያቀረብኩት፤ በቅርብ የማውቀው ታሪክ ነው። እንዲህ አይነት ታሪክ ያላቸው፤ ፍትህ የተዛባባቸው፤ “ለማን አቤት ይባላል?” እያሉ ግራ ተጋብተው ዝም ያሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። አሁን ቅርብ ግዜ እንደሰማነው ከሆነ ደግሞ፤ ግምት ሳይሰጡ ለሚያፈርሷቸው ህንጻዎች፤ ባለጉዳዩን ካባረሩ በኋላ የካሳውን ገንዘብ ለራሳቸው ሰዎች እንደሚያስተላልፉ ሰምተን ተግርመን ዝም ብለናል።

በአሁኑ ወቅት ፍትህ አጥተው… ወዴት ‘አቤት’ እንደሚሉ ግራ በተጋቡ ህዝቦቻችን መሃል ነው ያለነው። ሰዎቹ እንደሆነ… እንኳንስ የተስተካከለ ፍርድ ሊሰጡ ቀርቶ፤ የመሃል አገሩን ህዝብ እንደጠላት በማየት፤ መንደሩን እየሸነሸኑ እና የህዝቡን የፍትህ እምነቱን እየሸረሸሩ ዛሬ ያለንበት… ይሉኝታ ቢስ ዘመን ላይ አድርሰውናል። ጠመንጃ ካነሱበት ግዜ ጀምሮ… ትምክህት መመሪያቸው፤ ጠመንጃ ሃይላቸው ሆኖ ዛሬም ድረስ አሉ። በሌላ በኩል ያለው… ሌላው ደግሞ “ኃይል የእግዚአብሔር ነው።” ብሎ መጭውን ግዜ በብርታት የሚጠብቅበትን ዘመን እንድናይ አድርገውናል።

ነገሩ ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል በአንድ ግጥማቸው ላይ እንደገለጹት መሆኑ ነው።

“መሬት የእግዚአብሔር ናት፣ ባለቤት የላትም፤
ኃይለኛ እየሄደ፣ ያስገብራል የትም።”

“ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው” እንደሚባለው ሆኖ ሆድ ከምናባብስ፤ ነገራችንን ወደ ማጠቃለሉ ብንሄድ ይሻለናል።

እናም ለማጠቃለል ያህል…  የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ገና በጠዋቱ ስለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ሲያስተምሩ ነበር። “በዘር እና በብሄር መለያየት የለብንም” በማለት፤ ስለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ተሟግተዋል። በገዢዎቻችን ዘንድ የጥላቻ መንፈስ ሲንሰራፋ፤ የብሄር ዘረኝነት ሲስፋፋ ጋዜጠኞቻችን… “ተው – ይሄ ለህዝብ አይበጅም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የመንግስት ምላሽ ግን ወንድሞቻችንን  በማሰር አርፈው እንዲቀመጡ ወይም ጋዜጠኞችን በማሸበር አገር ለቀው እንዲወጡ ማድረግ እንደዘመቻ ትኩረት ተሰጠበት።

እርግጥ ነው። ጋዜጠኞችን ማሰር እና ማሸበር ይቻል ይሆናል። የሚፈራም ከተገኘ ማስፈራራት ይቻላል። የህዝብን አንደበት ሙሉ ለሙሉ መዝጋት ግን እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው። ይህን አንደበት መዝጋት ማለት፤ የታፈነ የህዝብ ድምጽ ማፈን ማለት ይሆናል። የታፈነ ስሜት ሲገነፍል ደግሞ መመለሻ አይኖረውም።  ይህ ስሜት ገንፍሎ አገር ከመጥፋቱ በፊት፤ እንደተጣደ ሽሮ ‘እፍ እፍ’ እያለ ከመገነፍል የሚያድነው ፕሬሱ መሆኑን፤ በቅን ልቦና በንጹህ ህሊና መዝኖ ነጻውን ፕሬስ እንደእንቁላል መንከባከብ ብልህነት ነበር።

በድሮ ተረት እንሰነባበት። ሁለት ጓደኛሞች በርሃ አቋርጠው እየሄዱ ሳለ አለመግባባት ተፈጠረ። እናም ጉልበተኛው አቅመ ደካማውን በጥፊ መታው። በዚህን ግዜ አቅመ ደካማው ምንም አላለም። በበርሃው አቧራ አፈር ላይ”ዛሬ ጓደኛዬ በጥፊ መታኝ” ብሎ ጻፈ። ብዙ ከሄዱ በኋላ ደግሞ ወንዝ አጋጠማቸውና ከውሃው ጠጥተው መዋኘት ጀመሩ። ነገር ግን ደራሽ ጎርፍ መጣና አቅመ ደካማው በወንዙ ሊወሰድ ሆነ። በዚህን ግዜ ጉልበተኛ ጓደኛው በብዙ ጥረት የአቅመ ደካማ  ጓደኛውን  ህይወት አተረፈለት።

ከሞት የተረፈው ሰውም በትልቅ አለት ላይ፤ “ዛሬ ጓደኛዬ ከሞት አዳነኝ” ብሎ በአቧራ ላይ ሳይሆን በአለት ላይ ቀረጸው።

በዚህን ግዜ ጉልበተኛው በሁኔታው ተገርሞ “በጥፊ ስመታህ አቧራ አፈር ላይ የጻፍከውን ታውቃለህ። አሁን ደግሞ ከወንዝ ውሃ ሳተርፍህ ይህን በድንጋይ ላይ ጻፍከው። ምንድነው ሚሰጥሩ?” አለው። ጸሃፊውም እንዲህ ሲል መለሰ።

“ሃይለኛ ዝናብ ወይም ንፋስ በሚመጣ ግዜ በአፈር ላይ የጻፍኩት ነገር ይጠፋል። አንተ ያደረስክብኝ በደል ግዜያዊ ስለሆነ፤ ይቅርታ በተባባልን ግዜ እንደአቧራው ላይ ጽሁፍ ከልቤ ይጠፋል። ጸባችን ሳይሆን መልካም ተግባራችን በአለት ላይ ተጽፎ መቅረት አለበት። ይህም ውሽንፍር እና አውሎ ንፋስ ቢመጣ ጭምር አይጠፋም። እነሆ በአለት ላይ የተጻፈው ለዘላለም ይታወሳል።” አለው።

እኛ ጋዜጠኞች ፍጹም  አይደለንም። ልንሳሳት ወይም አንዳንድ ወገኖችን ልናስቀይም እንችል ይሆናል። ነገር ግን ካጠፋነው ይልቅ የሰራነውን መልካም ነገር በማየት፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለይ ለነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች በልቡ ውስጥ ልዩ ስፍራ ሊሰጥ ይገባል። ሙያውን እየሰሩ ላሉትንም ሆነ ላለመስራት ለተገደዱት፤ ለታሰሩትም ሆኑ ለተሰደዱት ጋዜጠኞች ክብር ልንሰጣቸው፤ መልካም ተግባራቸውን በልባችን ጽላት ልንጽፈው የግድ ነው። እነጋዜጠኛ… ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ እና እስክንድር ነጋ የጀመሩትን የቀራንዮ መንገድ እኛም ልናግዛቸው ይገባል – ጉዞው ተጀመረ እንጂ ገና አልተገባደደምና።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s