ከነዚህ ጋር አፍሪካዊ መባል አያሳፍርም? (ነፃነት ዘለቀ)

ነፃነት ዘለቀ

ይሄ አፍሪካዊነት አሁን አሁንስ አይክዱት ነገር ሆኖ እንጂ በእጅጉ እያሳፈረኝ ነው፡፡ ከደቂቃዎች በፊት በኢሳት አንድ ዜና ተከታተልኩ፡፡ በዚያ እየጨስኩና እየተከንኩ ወደ ሥራ ገባሁ፡፡ ከዚህ አስጠሊታ አምባገነንነት መቼ እንደምንላቀቅ እግዜር ይወቀው፡፡Uganda's President Yoweri Kaguta Museveni

ዜናው የዩጋንዳን “ምርጫ” ተከትሎ በተከናወነው የአፄ ሙሴቪኒ “የሥልጣን ሽግግር” ላይ ስለተከሰተ አንድ አጋጣሚ ነበር፡፡ እሱም የአሜሪካና አውሮፓ ዲፕሎማቶች ሥነ ሥርዓቱን ረግጠው መውጣታቸውን የሚያትተው ዜና ነው፡፡ ምክንያታቸው እርግጥ ነው ዴሞክራሲ ተጨቆነች ወይ ተረገጠች ብለው ሳይሆን ሙሴቪኒ አይሲስን ማነው አይሲሲን ተናገረብን ብለው በማኩረፋቸው ነው፡፡ እንጂ ለዴሞክራሲማ እነሱ አይጨነቁም – እነሱ የሚጨነቁት ለፖለቲካዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ብቻ ነው፤ የአፍሪካም ሆነ የላቲን አሜሪካና የእስያ ሕዝቦች ቢጠበሱም ሆነ ቢገነተሩ አይሸቷቸውም – እንደሕዝብ ካልሆነ በስተቀር እንደመንግሥት ከሆነ ምዕራባውያን በጥቅሉ አደገኞችና የዚህች ዓለም ዳግም ምፅዓት ዋና ሰበቦች ናቸው፡፡ እነአሜሪካ እኮ  ጥንት ያኔ በደጉ ዘመን በግሪኮች አብባ ያፈራች ዴሞክራሲን ዛሬ እጅግ ሠለጠነ በተባለው በትክክል ከታዘብነው ግን ክፉኛ በሰየጠነው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ገድለው የቀበሩ አስመሳዮች ናቸው፡፡ በዴምራሲ ስም አንዱን ሲገድሉ ሌላውን ያድናሉ፤ አንዱን በመርዝ ሌላውን በጨረር እስከወዲያኛው ያሰናብታሉ፡፡ ሲፈልጉ በልዩ የኮማንዶ ኃይል  ያገር መሪን ከቤተ መንግሥቱ ጠልፈው ይወስዳሉ፡፡ በምድር ጎስቋሎች ላይ የምድር ንጉሦች፡፡ የዴሞክራሲ ካርድ የዕቃቃ መጫወቻቸው ናት – ግብዞች!

ከብዙዎች ምሣሌዎች አንዱን ብቻ ወስደን ሳውዲ ዐረቢያን በጨረፍታ እንመልከት፡፡ በቅድመ ልደተ ነቢዩ ሙሀመድ ዘመን በነበረ የቅጣት ሥልት ሐሙስ ሐሙስ አንገት በሰላ ጎራዴ ሲቀነጠስ አጠገብ ሆነው እያዩ (ምናልባትም በድጋፍ እያጨበጨቡ)፣ ሴት አትመርጥም አትመረጥም ብቻ ሳይሆን መኪና እንኳን ማሽከርከር አትችልም ተብሎ በተግባር መገለጹን እያዩ፣ ሴት በፍርድ ቤት ከወንድ እኩል ለምሥክርነት አትበቃም መባልን እያወቁ፣ ሴት ከራስ ፀጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ካልተሸፋፈነች ከቤት ውጪ መሄድ እትችልም መባልን እየተረዱ፣ አንድ ፉኣድና ቤተሰቡ ሚሊዮኖችን ዝንታለሙን አንቀጥቅጦ እንደሚገዛ ባይናቸው በብረቱ እየተመለከቱ….ይህን ሁሉ ጉድ እያዩ አሜሪካኖች የዚህች ሀገር ጥብቅ ጓደኛና የጭንቅ ቀን ደራሽ ሆነው ስናይ በአሜሪካ እስፊንክሳዊ ተፈጥሮ ሳንገረም ሳንጨነቅም አንቀርም፤ ብቻ ትኑርልን፡፡ ትልቅ ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበት – በጭንቅ ቀናችን የብዙ ወገኖቻችን መጠጊያ ሆናለችና ብድራታችንን በዚሁ በምድር ባንከፍላትም ለማንኛውም የከዳችው እግዜር ከሁሉም የሚጠቅሟት ነገሮች ጨማምሮ ይስጣት፡፡ ክፉ ብቻ የሆኑ አገሮችስ አሉ አይደል? ይህንንስ ማን አይቶበት! በነፃነት ዘመን የሚጠቅሙንን ስንቱን ምሁር ነው አቅፋ የያዘችልን፡፡ የክፉ ቀን ማኩረፊያ አያሳጣ፡፡ ቅጣት አድራሻውን ሲለውጥ ኢትዮጵያ አምራና ተውባ ካሁኑ ትታየኛለች፡፡

ሙሴቪኒ ባለባት አህጉር አባል መሆን አስጠላኝ፡፡ ሀፍረትና አምባገነኖች አይተዋወቁም – ይሉኝታና ወያኔ እንደማይተዋወቁት ሁሉ፡፡ ይህ ሰው ዩጋንዳን ለ5ኛ ዙር ሊቀጠቅጥ በማጭበርበር የወሰደውን መዶሻ ትናንት ተቀበለ – ከማን ተቀበለ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው – ከራሱ፡፡ ራሱ ከ25 ዓመታት በላይ ጨብጧት የነበረችዋን መዶሻ ከግራ ወደቀኝ አዟዟራትና ራሱን በራሱ መርጦ ራሱ ያዛት፤ ምን ዓይነት ሞኝነት ነው? የምረቃው አጃቢስ ምን ዓይነት ነፈዝ ነው? በመሠረቱ ሰው ሳይቀየር ለምን የምረቃ ሥነ ሥርዓት እንዲደረግ መድረክ ይዘጋጃል? ለምን አላግባብ ወጪ ይወጣል? ኤርትራ ማሪኝ ያስብላል፡፡ ኢሴ እውነቱን ነው፡፡ “ምርጫ እንደኢትዮጵያ ከሆነ በየስድስት ወሩም ማድረግ እንችላለን” ያለው ታሪካዊና በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ መመዝገብ ያለበት ነው፡፡ በኛ ሀገር እንኳን ለዚህ ማፈሪያ ምርጫ የሚወጣውን ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ እስኪ አስቡት፡፡ በገንዘብ ዕጥረት ምክንያት ስንት ፕሮጀክት አፉን ከፍቶ ተቀምጦ ወዘና ለሌለው የቸከና የመነቸከ ሀገራዊ የፌዝ ቲያትር በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በሰበቡም ለተጓዳኝ ምዝበራ ሲከሰከስ የሚያናድደው አንድም ባለሥልጣን ሲጠፋ በርግጥም ሀገር ለይቶላት እንደጠፋች መረዳት ይቻላል – ሁሉም ተያይዞ ነሆለል ሲሆን ይገርማል፡፡ ምን ዓይነት ወረርሽኝ ገባብን በል? በርሀብና በበሽታ የሚያልቀው ሕዝብ ደንታ የማይሰጣቸው፣ በስደትና በአስተዳደራዊ በደል ወደውጪ የሚጎርፈውና ውስጠቃው በዘራፊዎች የሚቦጠቦጠው፣ የምድርና የባህር ዐውሬ ሲሳይ ሆኖ የሚቀረው  ሕዝብ የማይታያቸው፣ ሆዳቸው ከሞላ ሌላ ነገር ትውስ የማይላቸው ዓሣማና ጅብ ባለሥልጣን ይስጠን? ሆ! ወይ ዘመን፡፡

ያኛው ሙጋቤ የሚሉት አኞ ደግሞ ከሁሉም የባሰበት ነው፤ “ሞቼም ቢሆን ከሥልጣን እንዳታወርዱኝ” ብሎ እንደኛው ጉድ እንደመለስ በዐፅሙ ሳይገዛ አይቀርም፡፡ አፍሪካ ትገርማለች – እኔስ ሳስበው በአዋላጆች የህክምና ስህተት እውነተኛ ልጆቿ  እየተቀበሩ እንግዴ ልጆቿ የሚያድጉባት ክፍለ ዓለም ሣትሆን አትቀርም – አሁን እስኪ አስቡት – እንዲያው በፈጣሪ ይሁንባችሁና እነመለስና ሙሴቪኒ ሰው ናቸው ትላላችሁ? በተለይ በአፍሪካ ሁሉን ነገር ስታዩት የሚሠራው ሁላ ከጤናማ ሰው የሚጠበቅ አይመስልም – ከጥቂት ነገሮች በስተቀር፡፡ ኦማር አልበሽር የሚሉት ደንቆሮ ደግሞ እኔ ጥንት ከዩንቨርስቲ ተምረቄ በወጣሁ ማግሥት ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ያለ ይሄው እኔ በቀደም ለት የልጅ ልጄን ድል ባለ ድግስ ባለም እስከምድረበት ጊዜ ድረስም  ያው ሥልጣን ላይ ፊጥ እንዳለ አለ፤ ይሄ ሥልጣን የሚሉት ነገር ምን ዓይነት ሀሽሽ ነው – እርግጠኛ ነኝ የሥልጣንና የሀብት ሱስ ከማንኛውም የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ይበልጣል፤ በህልምም በውንም እየመጣ የሚያርዥ ኃይለኛ ንጥረ ነገር ሳይኖርበት አይቀርም፤ ሰው ሁሉ ሲባላ የማየው በሀብትና በሥልጣን ነው – በተለይ በአፍሪካማ ያለው የተለዬ ነው፡፡ የኞቹን በዋናነት ሳንረሳ በሥልጣን ፍቅር ያበዱ ብዙ ናቸው፡፡ ወይ ሰው መሆን! ወይ አንቺ አፍሪካ! ምን ይዋጥሽ ከቶ! ሥልጣን የሚሉት ደዌ ኅሊናን የሚያስትና በውሸት ካባ የሚያዘንጥ ሆኖ ይቅር?

አንድ ሰው ከአንድ ትውልድ በላይ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ድፍረቱን ከየት ያመጣዋል? አጨብጫቢውና አቸፍቻፊውስ እንዴት ያስችለዋል? አንድ ልጅ ከተወለደ ጀምሮ ዐርባና ሃምሳ ዓመት እስኪሆነውና ከዚያም በላይ ካለአንድ መሪ ሌላ እኮ ላያይ ነው፡፡ ያኔ ሀገርም ዜጋም ባለበት መሄድ እንጂ ማደግ ብሎ ነገር አይታሰብም፡፡ መሪው ባለጌና እንደልቡ ይሆናል፡፡ ማንም ከሥልጣን እንደማያወርደው ስለሚያውቅ ለይስሙላና በአሜሪካ የሚወከለውን የፈረደበት የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተብዬውን ለማጭበርበር በሚደረግ የምርጫ ድራማ ራሱን እየደጋገመ ይሾማል፡፡ ዙፋኑ ላይ እንዳለ ያረጃል፤ እዚያው እየሸና እዚያው…እየተጸዳዳ፡፡ ያኔ ሕዝቡም ሀገሪቱም እየለየላቸው ይሄዱና ሁሉም ሳያምርባቸው ያረጃሉ፤ያፈጃሉ፡፡ ልጓም የሌለው ሥልጣን ሕጻን ያደርጋልና መሪው ሕዝቡን እንደብረት ቀጥቅጦ እንደሰም አቅልጦ ይገዛዋል፡፡ ያኔም we all willy-nilly vegetate and in the mean time we all die; here I should say ‘thanks’ to Mr. Death who knows no border when commanding people to stop breathing, be it a king or General, a president or PM, all are his slaves in time of his calling; nobody has the right to defy his order; thanks again Your Excellency Mr. Death who make us all equal at the end of the day. ውይ ሞት ባይኖር ምን ይውጠን ነበር?በ ኧረ የሞትን ዘር ያለምልምልን!

….ይህ ነው የሁላችን አፍሪካውያን ዕጣ! Ciao.

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s