የስደት ፖለቲካ ትዝብቴ እፍታ | ከሶልያና ሽመልስ (ውይይት መጽሔት)

 

ከአዘጋጁ: ይህ ጽሁፍ በኢትዮጵያ ታትሞ በወጣው ‘ውይይት’ መጽሔት ላይ ታትሞ ወጥቷል:: በሃገር ቤት ያላችሁ አንባቢዎች መጽሔቷን ገዝተው እንዲያነቧት ትበረታታላችሁ::

ፎቶ ከአልጀዚራ ቲቪ ስክሪን

ከሶልያና ሽመልስ

ከተሰደድኩ ሁለት ዓመት ሊሆነኝ ነው። አቆጣጠሬ በሽብርተኝነት ከተከሰስኩበት ቀን ጀምሮ ሆነ እንጂ ከአገር ከወጣሁ ከተቆጠረ ደግሞ ሁለት ዓመት ከአንድ ወር አካባቢ ሆነኝ። የስደቴን ቀን የክሱ ቀን አድርጌ የምቆጥረው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው፣ ከወዳጆቼ እስር ጀምሮ ያልቆረጠልኝ ‹ላልመለስ እችላለሁ› የሚለው ሐሳብ የተረጋገጠው በክሱ በመሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ እንደፖለቲካ ስደተኛ ወደ ዋሽንግተን ያቀናሁበትና ፖለቲካውን ማጤን የጀመርኩት በይፋ ከተከሰስኩ በኋላ በመሆኑ ነው። ስደት የጀመርኩት እንደማንኛውም አገር ቤት ውስጥ ፖለቲካ በቅርበት እንደሚከታተል ሰው የዳያስፖራን ፖለቲካ በቅርቡ እንደማውቀው እየተሰማኝ ነበር።

በቅድመ ስደት ኑሮዬ ከአገር ውጪ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ትችቶች ቢኖሩኝም በአብዛኛው የተስፋ ምንጭ አድርገው ከሚወስዱት ሰዎች የምመደብ ነበርኩ። ‹የቦታ ልዩነት ለፖለቲካ ተሳትፎ ብዙም ለውጥ የማያመጣ፣ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከውጪም ያለው ኃይል ወሳኝ ሚና ያለውና ሚናውን አውቆ ለዚያ የተዘጋጀ ነው› የሚሉት እምነቶቼ ለተስፈኝነት ካበቁኝ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ነበሩ።

የስደት ፖለቲካ 101

ከቀናት በኋላ ስደት ‹አውቶማቲክ› በሆነ መልኩ በጣም ፖለቲካዊ እንደሆነ ተረዳሁ። በአንድ በኩል አገር ቤት የሚቸግረኝን ፖለቲካ የሚያዋራ የቀድሞ ወዳጅ ወይም የትምህርት ቤት ጓደኛ ማግኘት አለመቻል እዚህ ተቃራኒ ሆኖ አገኘሁት። አገር ቤት ሴት ጓደኞቼን ሳገኝ ሁለተኛ ደረጃ አብሬ የተማርኳቸውን ጓደኞቼን ሳዋራ ፖለቲካዊ ወሬ ጭራሽ አይታሰብም ነበር። ሌላ፣ ሌላ “ኖርማል ነገር” አውርተን

እንለያያለን። የፖለቲካ ወሬ፣ ከፖለቲካ ወዳጆች ጋር ብቻ የተወሰነ ነበር። በተቃራኒው ስደት ላይ ሁሉም ሰው ፖለቲካ ያወራል፣ ለዛውም በሙሉ መብት እና እርግጠኝት። የመጀመሪያ ሰሞን ቢገርመኝም በአንድ በኩል ደግሞ ደስ አለኝ። ብዙው ሰው የአገር ጉዳይ የሚሳስበውና የሚወያይ መሆኑ አሪፍ ነገር አይደል?! ሌላው የስደት ‹ሀሁ› ከጥቃቅን ነገሮች ይጀምራል። የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መንግሥትን ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ብሎ የሚጠራ ሰው ማግኘት አይታሰብም። እንደው የሕ.ወ.ሓ.ት. ደጋፊ የሆነ ሰው የማግኘት ዕድል አልገጠመኝም እንጂ ቢያጋጥመኝ እነሱም ቢሆን ሕ.ወ.ሓ.ት.ንም ሆነ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን በአደባባይ ሥሙ የሚጠሩት አይመስለኝም። (ማንኛውም መንግሥትና ከመንግሥት ጋር የተያያዘ ነገር ሥሙ “ወያኔ” ነው)። ባንዲራው ልዩ ነው፤ ንግግሩ ልዩ ነው። ስደት ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የሌለበት የአገር ቤት ‹ኮፒ› መስሎኝ እንዳልነበር፣ እኖርበት ስጀምር ግን ግር አለኝ። ምኑም አገር ቤት አይመስልም። መንገዱም፣ ሰዉም፣ ወሬውም፣ ፖለቲካውም፣ ሥራውም። እንደውም፣ ‹ስለስደት ፖለቲካ ሳስብ በስርዓት አላሰብኩም ነበር ማለት ነው?› ብዬ ተገረምኩ። ብዙ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ከዛም በተጨማሪ የፖለቲካ ውይይት ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን በማየት ብቻ አገር ቤት ከማውቀው የተቃውሞ የፖለቲካ ውይይት እና ምኅዳር ጋር ይመሳሰላል ብዬ ማሰቤ ስህተት ነበር። በእርግጥ በውጪ የሚኖሩ እና የፖለቲካ አመለካከታቸው (ቢያንስ በውይይት ባሕላቸው) ከእኔ ጋር የሚመሳሰሉ የአሜሪካን ነዋሪዎችንም ማወቄ ለስደት ፖለቲካ የቀድሞ አረዳዴ የዋሕነት አስተዋ ዖ እንዳደረገም ገባኝ።

ብዙው የፖለቲካ ስደተኛ አገር ቤት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና ጉልበቱን መስዋዕት ለማድረግ ወደኋላ የማይል ነው። ገንዘብ ያዋጣል። ሰልፍ ይሰለፋል። የተጠየቀውን ይሰጣል። ፍጹም ለአገራቸው ቀንአዊ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ድምጻቸው የተሰማ ሳይመስላቸው  ሲቀር ተስፋ ሳይቆርጡ፣ ዐሥርት ዓመታትን አሳልፈዋል። የሚያውቁኝ ወይም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ስለ ዞን9 የጦማሪዎች ስብስብ የሰሙ ሰዎች የሰጡኝ ማ ናኛና ማበረታቻ ብዙዎቹ በበጎ አስተዋ ዖ የሚያደርግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ እንደሚያበረታቱ በግል እንድረዳም አስችሎኛል። ይህ ሁሉ ቅንነት ባለበት ቦታ ግን ብዙ ‹የስትራቴጂ› መሠረታዊ መግባባት ማጣትና የፖለቲካ ውጥንቅጥም አብሮ ይታያል። በስደት ያለው ፖለቲካ አገር ቤት ካለው ፖለቲካ በተሻለ የመሆን ዕድሎች ቢኖሩትም እኔ ካየኋቸው መሠረታዊ ትምህርቶች በመነሳት ከስር ያሉት ሦስት ዋና ዋና ተግዳሮቶች የብዙ ከላይ የጠቀስኳቸውን ዜጎች አቅም በአግባቡ የፖለቲካ ሂደቱን ወደፊት እንዳይገፋ አድርገውታል እላለሁ። በእኔ ግምገማ መሠረት ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን እና ጭቆናውን ከስሌቱ አውጥተን ብናሰላው በንጽጽር አገር ቤት ያለው የተቃውሞ ፖለቲካ በሁሉም መልክ በስደት ካለው የተሻለ ውስጣዊ መርሕ (internal principle) ላይ የቆመም ይመስለኛል።

ተቋም መፍጠር ያለመቻል (Lack of institution)

የስደት ፖለቲካው ተቋማት የሉትም ማለት ይቻላል። እንዳለመታደል ሆኖ አገር ውስጥ ያጣነው ነጻ ተቋማትን ማቋቋም አለመቻል ስደት ላይም ተከትሎን ይታያል። አገር ውስጥ ቢሆን የሃብት ማጣት (lack of resource)፣ የነጻነት ማጣት (freedom of association) እና የዕውቀት ማጣት (lack of capacity and knowledge/skill) ዋና ዋናዎቹ ተቋም መመሥረት ያሉበት ችግሮች ናቸው። በውጪ አገር ግን የሀብት ችግር ሳይታይ (የኢትዮጵያውን እንዲሁም የሌሎች አጋዥ ሰዎችን ሀብት መጠቀም እየተቻለ)፣ የነጻነት ችግር ሳይኖር (የተመዘገበ ድርጅት እና የማኅበረሰብ ሚዲያ ማቋቋም ያለምንም ከባድ መሥፈርት ማድረግ እየተቻለ)፣ የዕውቀት ችግር ሳይኖር (ብዙ የተማሩ እና የመማር ፍላጎት ላላቸውም አቅም ማጎልበቻ ዕድሎች እያሉ)፣ ይህ ነው የሚባል ፖለቲካዊ ተቋም ማየት አይታሰብም። ይህ ነው የሚባል የኢትዮጵያውያንን መብት (በስደት) የሚያስጠብቅ ተቋም የለም። ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ማኅበረሰብ (ኮሚኒቲ) ቢፈለግ አይገኝም። ምናልባት ከነተግዳሮቶቻቸው የሰሜን አሜሪካው የስፖርት ፊስቲቫልና፣ የቅርቦቹ ሚዲያ ተቋማት አንደሙከራ ይጠቀሱ ይሆናል። የእነሱንም ቢሆን የተቋማዊነት መሥፈርቶችን በዝርዝር ብናስቀምጥና ብናይ ማሟላታቸው ላይ ብዙ አተካሮ እንደሚኖር ይሰማኛል።

ይህ ራስን አሰባስቦ ተቋማትን መፍጠር አለመቻል (ተቋማት ስል፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የፖለቲካ አቀንቃኝ ቡድን፣ የፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቡድን፣ የማኅበረሰብ እና የሞያ ድርጅቶች የመሳሰሉትን እያልኩ እንደሆነ ይታሰብልኝ) ከላይ ከላይ ብናየው እንኳን ብዙ ችግሮች አሉ። የመጀመሪያው ተቋም ከሌለ በግል የታሰበበት ራዕይ፣ ዓላማ እና ግብ አይኖርም። ምን ማድረግ ነው የምንፈልገው? ማን ላይ ተ ዕኖ ለማድረግ ነው የምንፈልገው? መቼ እና እንዴት አድርገውን ነው ያንን የሚፈለገውን ተ ዕኖ/ አስተዋ ዖ የምናደርገው? የሚሉት ጥያቄዎች በቂ መልስ አይኖራቸውም። ይሄ ደሞ ይደረጋል የሚባለውን የፖለቲካ/የመብት/ማኅበራዊ ትግል አስተዋ ዖ እጅግ በጣም ይጎዳዋል። ከዛም በላይ ትግሉ በግለሰቦች ዙሪያ እንዲንጠለጠል (አሁን እንዳለው) በር ከፍቶለታል። ግለሰቦች ምንም ያህል ቁርጠኛ ታጋይ ቢሆኑ የተቋማትን ቦታ መተካት አይችሉም። በዚህም የተነሳ ስደተኛው፣ በትንሹ ባለፉት 25 ዓመታት የአሜሪካን እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርጉ ሲጎተገትም ሆነ አገር ቤት ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ብርቱ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም። ይህ ችግር በቁጥር ከፍተኛ የሆነውን እና በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ ትልቅ ፖለቲካዊ ኃይል ሊሆን የሚችለውን ዳያስፖራ ሰልፍ ሜዳ ላይ ብቻ አስቀርቶታል።

ተቋማት አለመኖራቸው እና በግለሰቦች የሚመራ እንቅስቃሴ ሌላው ችግሩ ለፈጠራ፣ ለአዲስ ሐሳብ እና ከጊዜ ጋር ለሚፈጠር ለውጥ ክፍት አለመሆኑ ነው። ይህ ሁለተኛው ትልቁ ተግዳሮት ነው የምለውን የስደት የተቃውሞ ጎራ ውስጣዊ ልዩነትን እንደ አደጋ የመመልከት አባዜን ያስከትላል።

ውስጣዊ ልዩነትን እንደ አደጋ መመልከት

ይህንን በተቃውሞ ጎራ ያሉ የሐሳብ ልዩነቶችን እንደጠላትነት የመመልከት አባዜን ብዙዎች (አልፎ አልፎ እኔን ጨምሮ) ከገዥው መንግሥት ዕኩል በተቃዋሚው ጎራ ዘንድ ሐሳብን በነጻነት መግለ ትልቅ አደጋ አለበት ተብሎ ሲነገር ይታያል። ለዛሬ እዛ ድረስ ጎትቼ ሐሳብን በነጻነት የመግለ መብት በተቃውሞ (ለዚህ ሑፍ ሲባል ‹የስደት ተቃውሞ›) ጎራ ያለበት ሁኔታ መንግሥት ከሚጋርጥብን አደጋ ዕኩል ነው ብዬ መደምደም አልፈለኩም (ምክንያቱም ለመ ናናትም ይሁን ጠንካራ ክርክር ለማድረግ በቂ ማስረጃ የለም)። ነገር ግን ውስጣዊ የሐሳብም ሆነ የርዕዮተ-ዓለማዊ አመለካከት ልዩነት የሚስተናግድበት መንገድ በጣም ደካማ እና ሰዎች የማሰብ መብታቸው ጭምር ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። ይህ በአደባባይ ከማኅበረሰብ ሚዲያ ጀምሮ በግል የተለየ ሐሳብ ያቀረቡ ሰዎች ሁሉ የሚደርስባቸው መገለል፣ ወከባ እና ስድብ ዋና ማሳያ ነው። እየተደረገ ያለውን ነገር የጠየቀ/የሞገተ ሁሉ የመንግሥት ደጋፊ፣ ትግሉን አጣጣይ ከዛም አለፍ ሲል የግል ችግር ያለበት ተደርጎ ይቀርባል። ይሰደባል። ይህ ሒደት ሰው ርዕዮተ-ዓለምን ፣ የትግል ‹ስትራቴጂ›ን እና ስልትን ውጤታማነት፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ሳይጠይቅ በጅምላ እንዲደግፍ ያስገድደዋል። ከዚህ ወጣ ያለ ሐሳብ ያላቸውም ካሉ ወይ በስድብ እና ማሸማቀቅ ከፍ ካለም ደሞ በማግለል እና ሥም በማጥፋት ከመድረኩ ይገለላሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት በጻፍኩት (“በተቃዋሚ ሥም ተቃቅፎ መሳሳም፤ ለትልቁ ስዕል ሲባል” የሚል) ሑፍ ‹አገር ቤት ከነበረው የተቃውሞ ጎራ ያሉ ሰዎች ጋር ያለመርሕ መስማማት፣ ለተቃውሞ ሲባል ብቻ ኅብረት መፍጠር እና አጋርነት ማሳየት ላይ ግፊት ማድረግ ጉዳት አለው› የሚል ነገር አስፍሬ ነበር። በወቅቱ አገር ውስጥ ያለው የተቃውሞ ጎራ ውስጣዊ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ በመሠረታዊ ደረጃ በሚያስማማው ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲሠራ እና ለውስጣዊ ልዩነት ቦታ እንዲሰጥ መጠቆሜ ነበር። በወቅቱ ጫን ብዬ የወቀስኳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሚዲያዎችም ነበሩ። ያኔ የስደት ፖለቲካውን ሳላይ በመሆኑ አሁን ሳስበው የምጠብቀው ‹ስታንዳርድ›ን ከፍ አድርጌ ነው እንጂ “ይቅር በሉኝ” ለማለት ሁሉ አምሮኛል። ቢያንስ ከዚያ በኋላ ባለው ልምድ ከነችግሮቹ አገር ቤት ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከሚከፍለው መስዋዕትነት አንጻር ውስጣዊ ልዩነትን በመቀበል ረገድ በስደቱ ፖለቲካ በጣም በብዙ ይሻላል። በክፉ ቀንም ልዩነትን አቻችሎ በመደጋገፍ ረገድ የአገር ውስጡ ፖለቲካ የተሻለ ነው።

እነዚህን የስደት ፖለቲካ ተግዳሮቶች እያሰብኩ ሳለ አንደኛው ምክንያቱ ምናልባትም ለረጅም ዓመት የቆዩ የዕድሜ ባለጸጋዎች እና ፖለቲካው ላይ ረጅም ዓመት የቆዩ ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ ይሆናል የሚል ሐሳብ መጣብኝ፤ ይህ ወደ ሦስተኛው ተግዳሮት ይወስደኛል።

ለመታደስ ያልተዘጋጀ

ፖለቲካም ሆነ ርዕዮተ-ዓለም ይታደሳል፤ ይቀየራል፤ አዲስ ሰዎችን እና ሐሳቦችን እያካተተ መሄድ አለበት። ይህ በስደት ፖለቲካው ላይ የሚሠራ አይመስልም። ብዙ የፖለቲካው ፊቶችም ሆኑ ተሳታፊዎች ለዐሥርት ዓመታት ፖለቲካው ላይ የቆዩ ናቸው። ይህ አገር ቤትም እውነት ቢሆንም ልዩነቱ አገር ቤት ወጣት መሪዎች እና አባላት እየተቀላለቀሉት ከነባራዊው እውነታው ሳይርቁ (with context) የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ‹ኮንቴክስቱ› ለለውጥ ይገፋቸዋል። ስደት መረጃ እንጂ ‹ኮንቴክሰት› የለውም። ይህ ከ‹ኮንቴክስት› መራቅ የስደት ፖለቲካውን አስፈላጊ ለውጥ/መሻሽል የማድረግ ችሎታ ያሳንሰዋል። (ወይም መታደስ እንዳለበት አይገባውም)። የአባይን መሠራት እየደገፈ መንግሥትን የሚቃወም ወጣት እንዳለ መስማት ስደት ፖለቲካው ላይ ላሉ ጥቂት ለማይባሉ ሰዎች “ወያኔነት” ነው። ይህ ለመታደስ አለመዘጋጀቱን ለማሳየት በየፖለቲካ ስብሰባው የሚሄደውን ሰው የዕድሜ እርከን ማየቱ ብቻ ይበቃል። ከቁጥሩ ማነስና የተለመዱ ፊቶች መብዛት በተጨማሪ የወጣቶች ተሳትፎ በጣም ውስን ነው። ወጣቶች ፖለቲካዊ ውይይቱን ስለማይወዱት ወይም ስለማይፈልጉት አይመለስኝም ስብሰባዎቹ ላይ የማይገኙት። ከዚያ ይልቅ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ከነሱ አስተሳስብ ጋር የሚሄድ ስለማይመስላቸው ነው ብዬ ነው የምገምተው። እንደ አለመታደል ሆኖ የዳያስፖራ ፖለቲካ በነዚህ ጥቂት ፊቶች ነው የሚመሰለው። ይበልጥ የሚያሳስበው ደግሞ ችግሮችን የመገምገም እና የሥራ አቅጣጫን የመገምገም ባሕል እና ለክፍተቶች መፍትሔ የመስጠት ተቋማዊ አሠራር ስለሌለ ይህ ነው የሚባል መፍትሔ ወይም ውይይት ሲደረግበት አይታይም። ከዚህም በተጨማሪ በማኅበራዊ፣ በመዝናኛ እና በመሳሰሉት መልኩ የኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ዕድሎች ካለመኖራቸውም በተጨማሪ (ካሉም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በፓርቲ ፖለቲካ የተያዙ ወይም መጠጋጋት የሚጠበቅባቸው በመሆናቸው) ኢ-ፖለቲካዊ (apolitical) በሆነ ሥራ ብዙ ኢትዮጵያውያንን የመሳብ ዕድላቸው ደካማ ነው።

ይሄ እንግዲህ በጥቅሉ ለእኔ የታየኝ የውጪው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተግዳሮት ነው። የማውቀው አብዛኛው የሰሜን አሜሪካውን ስደተኛ እና ፖለቲካውን ቢሆንም የወል ከሆነው ማኅበረሰባዊ አመጣጣችን አንጻር ግን አውሮፓም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን እገምታለሁ። ይህ ሑፍ ሁሉንም ተግዳሮቶች በጥልቅ እና መፍትሔ አይዳስስም። ከትልቁ የተግዳሮት ተራራ በእፍኝ እንዳካፈልኳችሁ ቁጠሩልኝ። ችግሩን መናገር መጀመር ለመፍትሔ ፍለጋው አንድ አካል ነውና።

ወ/ሪት ሶልያና ሽመልስ የዞን ፱ ኢ-መደበኛ የጦማሪዎች ስብስብ መሥራች አባል እና የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት ሥራ አስፈፃሚ ኃላፊ በመሆን እያገለገለች ነው፡፡ በኢሜይል አድራሻዋ soliyesami@gmail.com ሊያገኟት ይችላሉ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s