ተጠራጣሪነት ለኛ ለኢትዮጵያዊያኖች አዲስ ነገር ነው እንዴ?

nega

(ሄኖክ የሺጥላ)

አርበኛ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ሰሞኑን በሲያትል ተገኝተው ያሰሙትን ቅንጭብ ( ወይም ጭላጭ) መልዕክት አደመጥኩ። የንግግራቸው አንኳር ሃሳብ ይሁን አይሁን ወደፊት የምገነዘበው ጉዳይ ቢሆንም ፥ ስለ ተጠራጣሪነት በጣም በግርድፉ እና በጨረፍታ « ከአንድ ኢኮኖሚስት የሚጠበቅ ነው » አንስተው ያልፋሉ ። በዚህ ንግግራቸው ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠራጣሪነት የገረማቸው ይመስላል ። በእውነት ተገርመው ከሆነ ፥ እኔ ደሞ መገረማቸው የምር ሊገርመኝ ይችላል ። ምክንያቴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ ።

ተጠራጣሪነት ለኛ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ግኝት አይደለም ። ቀደም ባሉት ዘመናት ለምሳሌ የዘመነ መሳፍንት ግብዓተ መሬት ከተፈጠመ ብኋላ ፥ በአፄ ቴዎድሮስ አማካኝነት ፥ ሃጋሪቱን ወደ ተማከለ እና ጠንካራ አስተዳደር ለማምጣት ሲባል ዘመናዊ ስልጣኔን ከ ኣውሮጳ ለማስገባት ንጉሱ ያደረጉትን ጥረት ፥ በንጉሱ አካባቢ ያሉ የቅርብ ረዳቶቻቸው እና ባለ ሟሎቻቸው ይኽን ጉዳይ ሃገርን ለባዕዳን የመክፈት ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ወስደውት ነበር ። የንጉስን አስተሳሰብ « ታሪክን እና በህልን የሚመርዝ ፥ ሃይማኖትን የሚቀይጥ ፥ እና የሚለውጥ ፥ ሃገሪቱን ለውጭ ሃይሎች ( ባዕዳን ) ክፍት የሚያደርግ አካሄድ ስለሆነ ፥ ይህን ከውጭ ሃገራት ጋ ሊደረግ የታሰበውን የዕውቀት ልውውጥ እንዳይፈጠም ለማድረግ የሞከሩ ጥቂቶች አልነበሩም ። ምንም የማያውቁትን እና ለአንድ ቀን እንኳን ያልሰሙትን አካል አጥፊ ብሎ መፈረጅ ከልክ ያለፈ የተጠራጣሪነት መንፈስ ውጭ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ?

በአጤ ሚኒሊክ ዘመንም ጊዜ ይሄው የጥርጣሬ ማዕበል ነገስታቱን እና መነኩሳቱን ያሰመጠ እና የዋጠ ታሪክ ስለመሆኑ ተጥፎ እናያለን ። በይበልጥ አጤ ምኒሊክ ከአድዋ ድል ማግስት ፥ ከውጭ መንግስታት ጋ በመገናኘት ሃገራቸውን በእድገት ጎዳና ለመምራት ማቀዳቸውን ለካህናቱ እና «መሳፍንቱ» ሲያስረዱ ፥ ካህናቱ « እንደነሱ የጠራ መሳሪያ ባይኖረንም ፥ ጠላቶቻችንን የኢትዮጵያ አምላክ ድል ስለሚያደርግልን ፥ ከነሱ ጋ ይየምናደርገው ትውውቅ እና ትስስር ቢቆም ይሻላል » እያሉ ይመክሯቸው ነበር ። ይህ የተጠራጣሪነታችን አንዱ ማሳያ ነው ።

«በመሳፍንቱ እና መኳንንቱ» ፥ ብሎም በካህናቱ ቁጥጥር ስር የነበረው ማህበረሰብ የሚያሳየው ወግን የማጥበቅ ስርዓት እና ነገሮቹን ሁሉ በጥርጣሬ አይን የማየት እውነታ ፥ ስልጣኔን ለመቀበል ፥ ወደፊት ለመራመድ እና ካደጉት ከተፈሩት እና ከተከበሩት ሃገሮች ተርታ ለመቆም የሚደረገውን ጉዞ እጅግ አዳጋች ብቻ ሳይሆን የማይቻል አድርጎት ነበር ። ዛሬም ከዚያ የተለየ ነገር ያለ አይመስለኝም። የስልክ መምጣት ፥ የባቡር መንገድ መዘርጋት እና መሰል ነገሮች በህዝቡ ዘንድ የፈጠረው ከፍተኛ ጥርጣሬ ወደር የሌለው እንደነበረ አሁንም የታሪክ መዘክሮች ይዘግባሉ ። ወመዘክሩ በኪሉ ባይሸጥ ኖሮ መጥሃፍ በጠቆምኳችሁ ።

ንጉስን የሾመው እግዚያብሄር ነው ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ ፥ እንደ አፈ ወርቅ ገብረየሱስ አይነት ተራማጅ አስተሳሰብ ፥ እንደ ነጋድራስ ገብርህይወት ባይከዳኝ አይነት ባለ ሰላ ብዕር ፥ እንደ አለቃ ታዬ ያሉትን ባለ ተራራ መስተሃልይ ግለሰቦች ያቀርቡት የነበረው የህብረተሰቡን ስር የሰደደ የተጠራጣሪነት መንፈስ ፥ የካህናቱን በአንድ አይነት አስተሳሰብ ላይ ተተክሎ መቆም እና አደጋውን መተቸት ራሱ በህብረተሰቡ ዘንድ መማሪያ ከመሆን ይልቅ እነዚህ ምሁራኖችንም ፈርጆ በተመሳሳይ የጥርጣሬ ኮሮጆ ውስጥ ከቶ የነጮች ( የባዕዳን ቅጥረኞች ) ፥ ሃገራቸውን ለማጥፋት የሚያሴሩ የውጭ ሃገራት ተላላኪዎች ተደርገው ይታዩ ነበር ። ምክንያቱ ደም ምንም አይደለም፥ ያው ጥርጣሬ እንጂ !

ጥርጣሬ እና ተጠራጣሪነት ለኛ ለኢትዮጵያዊያኖች በእርግጥ አዲስ ነገር አይደለም ። ድክመታችንን በተራ አሉባልታ ፥ ውድቀታችንን በማጥላላት ፥ ሽንፈታችንን በጥርጣሬ ፥ አለመቻላችንን በእምነታችን እያሳበብን የኖርን ህዝቦች ስለመሆናችን ከበቂ በላይ ማስረጃም መረጃም አለን ። በታሪካችን መስራት መቻል የሚያስቀቅስ ፥ አፈድፋጅነት የሚያስሞግስ እንደነበር የታወቀን ነው ። ብረት ሰሪውን ጠይብ ፥ጠሃፊውን ጠንቋይ ፥ ሸማ ሰርቶ እራቁት ከመሄድ ቢታደግ ሸማኔ እና ቡዳ ፥ ቤተክርስቲያን ቢያገለግል ደብተራ ፥ ብረት ቢያቀልጥ ባለ እጅ ፥ ሸክላ ቢጠፈጥፍ ሟርተኛ ፥ ሬሳ ገልባጭ እና ወዘተ እያልን እያንዳንዱን መልካም ነገር ስንጠራጠር የኖርን ስለመሆናችን ከማንም የተደበቀ አይደለም ።

ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ( ብላቴን ጌታ ) ፥ ዝክረ ነገር በተባለው ሁለተኛ መጥሃፋቸው ፥ አጤ ሚኒሊክ ራሳቸው በዚህ ህብረተሰብ ከልክ ያለፈ የመጠራጠር አባዜ ተቆጥተው በ ጥር 17 ቀን 1900 ዓ.ም የሚከተለውን አዋጅ አውጀው እንደነበር ከትበውልናል

” ሰራተኛውን በስራው የምትሰድብብኝ ተወኝ ። ከዚህ ቀደም ብረት ቢሰራ ጠይብ ፥ ሸማ ቢሰራ ሸማኔ ፥ ቢፅፍ ጠንቋይ ፥ ቤተስኪያን ቢያገለግል ደብተራ ፥ እያላችሁ አርሶ ነጩን ከጥቁር አምርቶ የሚያገባውን አራሽ ፥ ከዘውድ ይበልጣል የሚባለውን ገበሬ እያላችሁ ፥ ነጋዴ ነግዶ ወርቁን ግምጃውን ይዞ ሲገባ አንተ ነጋዴ ገጣባ ( ያህያ ፥ የበቅሎ የፈረስ አጣቢ )፥ እያላችሁ በየስራው ሁሉ ትሳደባላችሁ ። እጁ ምናምን ስራ የማያውቀው ሰነፉ ብልኹን እየሰደበ አስቸገረ ። ” እያሉ ይገልጡና ይህንን ሁሉ ለማስቆም ” ዳግመኛ ሲሳደብ የተገኘ መቀጫው አንድ አመት ይሆናል !” ። ይላሉ ።

ጥርጣሬ የማንነታችን አካል ነው ። እስከ አሁን ማሸነፍ ያቃተን ከነፃነት በላይ ለትግላችን ማነቆ ፥ ለመንገዳችን እሾህ የሆነ ።

ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ
ተፈሪ መኮንን ( ግርማዊ ንጉስ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ በወቅቱ ራስ ተፈሪ ) የሲኒማ ቤትን ሲያስተዋውቁ ፥ ህብረተሰቡ በጥርጣሬ ነበር የተቀበለው ። ለዚህም የሰይጣን ቤት የሚል ስም ሰጥቶታል ። የድሃ ልጆችን ሰብስበው ሲያስተምሩ ፥ ትምህርቱን በጥርጣሪ ያዩት መሳፍንቱ እና መኳንንቱ ንጉሱ ለድሃ ልጆች ደብተር እና እስክርቢቶ ገዝቶ ማስተማር በመወሰናቸው ተቃውመው ለንግስት ዘውዲቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር ። ምክንያታቸው ደሞ የባዕዳን ትምህርትን ልጆቻችን ሊማሩብን ነው የሚል መሰረት የሌለው ጥርጣሬ ነበር ። የ ዘውዴ ረታን ( የቀዳማዊ ሃይለስላሴ መንግስት) መጥሃፍ ማንበብ የተሻለ ነገሩን ለመረዳት ይጠቅማችኋል።

ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ ( እየሰማሁ ሳይሆን እያየሁ ካደግሁት )

እናቶቻችን ጠላ ከቀዱ በኋላ ካናቱ የሚቀምሱት ነገር ምንጩ ባህል ሳይሆን የተጠራጣሪ ካቲካለኛ መንፈስ ለማረጋጋት የሚደረግ ጥረት እንደሆነ በጥናትም ፥ በንባብም ፥ በመኖርም ያገኘኋቸው መረጃዎች ያስረዳሉ ። በቀደመው ዘመን ደብተራዎች ፥ አፈ ሹሞች ፥ ከፍ ሲልም የንጉሱ ባለ ሟሎች እና ካህናቶቹ የሚጠፋፉበት አንዱ መንገድ የተመረዘ መጠጥ እንደሆነ መዛግብት ይናገራሉ ። ይኽም ታሪክ የጥርጣሬ መንፈስን በተዋረድ የመንደር ካቲካላ መሸጫ ድረስ ይዞት ተመመ ። ዛሬም ድረስ ታዲያ ፥ አንድ ሰባራ ስልጣንም ይሁን ድንቡሉ ሳንቲም የሌለው ሰካራም ጠላ ቤት ገብቶ የሚያዘውን አንድ ጣሳ ጠላ አስቀምሶ ( ወይም እመነኝ መርዝ የለውም ) ተብሎ እንደሚጠጣ እናውቃለን ።

አክሱምን እና ፋሲልን የመገንባት ባህላችን ሳይሆን ጠላ አስቀምሶ የመጠጣት ባህላችን ዘመን የተሻገረበትም ዋናው ምክንያት ከእድገት እና ለውጥ ይልቅ ለተጠራጣሪነት የቀረብን ህዝቦች ስለሆነንን ይመስለኛል ። አዎ ተጠራጣሪነት ለኛ ለኢትዮጵያዊያኖች አዲስ ነገር አይደለም !

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s