ትውልድ የሚሻገር መፍትሔ: እንዴት? – ሰቦቃ ዋቅቶላ

የዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ የየትኛውም የ ፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለም:: ሃሳቡም የግሉ ነው::

imagesየ ዛሬዋ ኢትዮጵያ የህዝቦችዋን የፖለቲካ ጥያቄን ፈትቻለሁ ብላ ብትፎክርም: ያው የተለመደ መፈክር ብቻ ከመሆን የዘለለ አይደለም:: ተደጋግሞ አንደሚባለው አሁን ያለው ህገ መንግስት አናሳ በሆነው ነገር ግን በታሪክ አጋጣሚ የመሳሪያ የበላይነት ያገኘው ወገን የፖለቲካ ፍላጎቴን ያስጠብቅልኛል በሚል ያረቀቀው: የመሳሪያ የበላይነቱን ተጠቅሞ ያስፀደቀው ነው:: ህገ መንግስቱ የፈታው የፖለቲካ ጥያቄ ቢኖር: የመሳሪያ የበላይነት ያገኘውን የትግራይ ብሔር ጥያቄ ብቻ ነው:: የ አንድ ብሄር  የፖለቲካ ቡድን: ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ትርጉም ያለው ወይይት አና ድርድር ሳያደርግ: እንዲያውም ተቃዋሚዎቹን አጥፍቶ ለመጨረስ በዘመቻ ላይ ሆኖ:  ያቀረበው ‘እኔ አውቅልህ’ መፍትሄ: የኢትዮጵያን የብሔር ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የነበረውን ዕድል ገደል የከተተ: ለአንድ ወይም ለብዙ መቶ አመታት ሊቆይ የሚችል ህገ መንግስት የመቅረጽ ዕድል ያጨናገፈ ነው::

ትውልዶችን ሊሻገር የሚችል መፍትሄ ማቅረብ : የህዝቦችን የፖለቲካ ፍላጎቶች  ማወቅ ይጠይቃል:: የህዝቦች የፖለቲካ ፍላጎት ለማወቅ ደግሞ ዲሞክራሲ ቅድመ ሁኔታ ነው:: ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ዕድል አግኝተው  የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በቀጥታም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ወይም በሌላ መንገድ ሊወስኑ ይችላሉ: በዚህን ጊዜ የአንድ ህዝብ የፖለቲካ ፍላጎት ታውቆል ማለት ይቻላል:: ‘እኔ አውቅልህ’ የፖለቲካ አራማጆች ቅድመ ሁኔታ የሆነውን የህዝብን በ ነጻ የመደራጀት: የመሰብሰብ: ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ የመሳሰሉትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች አፍነው የህዝቦችን የፖለቲካ ፍላጎቶች ራሳቸው ይወስናሉ::

ትውልዶችን ሊሻገር የሚችል መፍትሄ ማቅረብ : ለሕዝቦች የፖለቲካ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት ይጠይቃል:: ለሕዝብ የ ፖለቲካ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት መሰረቱ የህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ እንጂ የመሳሪያ የበላይነት የያዘው ቡድን ፈቃድ አይደለም:: በመሳሪያ የበላይነት ስልጣን የያዙ የፖለቲካ ቡድኖች በእኔ አውቅልህ የህዝቦችን የፖለቲካ ፍላጎቶች እንደሚወስኑ ሁሉ ለሕዝቦች የፖለቲካ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡት ራሳቸው  በፈቀዱት ልክ ብቻ ነው::

ህወሀት/ ኢህአዲግ ያቀረበው መፍትሄ የህወሐትን የበላይነት ለዘለቄታው የሚያስጠብቅ ነው:: የዚህ ፅሁፍ አላማ መፍትሄዎቹን በዝርዝር የመቃኘት አይደለም:: ብዙዎችም ብዙ አንደፃፉ አገምታለሁ: ነገር ግን በጥቂቱ ላንሳው::  የ ህወሐት ታጋዮች የ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አሾሾም ና ስልጣን እንዲሁም : የፕሬዚደንቱን አሾሾምና ስልጣን ሲወስኑ: የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ከ ህወሐት ቁጥጥር አንዳይወጣ አድርገው ነው:: ኢህአድግ ያለ ህወሀት ስውር ሆነ ግልፅ መሪነት ህልውና አይኖረውም:: የኢሕአድግ መሪ  ደግሞ ሁልጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሆናል:; ታጋዮቹ የክልልና የፌደራል ግኑኝነቶችንና የሀብት ክፍፍል ሲወስኑ የክልሎች ጠቃሚ ሀብቶች በሙሉ በ ፌዴራልና በሕህወሐት ስር አንዲሆኑ በማድረግ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ ታዋቂውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በሕገ  መንግስቱ ሲያካትቱ “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” እንዲሉ ነው:: የፍንፍኔ/ አዲስ አበባ የፖለቲካ ስልጣን መነፈግ የህወሀት ታጋዮችን የፖለቲካ ፍላጎት የማሳካት አላማ ያለው እንጂ አንዳዶች እንደሚያስቡት የ ኦሮሞ ን ህዝብ ፍላጎት ለመጠበቅ አይመስለኝም::

ከዚህ ብዙ ልንማር ይገባናል:: ከአንድ ትውልድ የማይሻገር ህገ መንግስት ከእንግዲህ ሊኖረን አይገባም:: ከ እኔ አውቅልህ ፖለቲካ መላቀቅ ይኖርብናል:: የፖለቲካ ድርጅቶች ሊታገሉለት የሚገባ ነገር ቢኖር  የህዝቦች መሰረታዊ  መብቶች እንዲከበሩ ነው:: ህዝቦች የሚፈልጉትን እንደሚያውቁ ከልብ መቀበል ያስፈልጋል::

አንዳንድ ጊዜ በመንግስት ሚዲያ ላይ ተቃዋሚዎች ሲከራከሩ እሰማለሁ:: ዋናው ጉዳይ ሁልጊዜ ይድበሰበሳል:: እንደኔ አመለካከት ዋናው የ ፖለቲካ ጉዳይ አሁንም የብሔር ጥያቄ ነው:: የክልሎች አና የ ፌደራል ግኑኝነት ጥያቄ ነው:: ይህ ጥያቄ ሰፊ ነው:: የ ኦሮሞ ህዝብ አና የ ፖለቲካ ድርጅቶች ለረጅም ጊዜ ሲያነሱትና ሲታገሉለት የቆዩትን ጥያቄ የያዘ ነው:: ይህ ጥያቄ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ያሉትን ከኦሮሞ ዉጭ ያሉ ህዝቦችን ይመለከታል:: ይህ ጥያቄ በፍንፍኔ/አዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩትን የተለያዩ ህዝቦችን ይመለከታል:: የ ኦሮሞ ህዝብ በፌደራል መንግስት ላይ የሚያነሳው የ ይገባኛል ጥያቄ የአማራና የሶማሌ የትግራይ እንዲሁም የሁሉንም ሌሎች ህዝቦችን ይመለከታል:: ይህ ጥያቄ ከ ኦሮሞ ዉጭ ያሉ ሌሎች ህዝቦች ከፌዴራል መንግስት ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚያነሱትንና  የሚታገሉለትን  የስልጣን ክፍፍል ጥያቄዎች የያዘ ነው::

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ አይዶሎጅን መሰረት አድርገው የሚደራጁ መኖራቸው ይታወቃል:: ዋነኞቹ ሊበራል ዲሞክራሲን እንከተላለን ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ ሶሻል ዲሞክራሲን እንከተላለን ይላሉ:: ህወሀት/ ኢህአድግ ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ነኝ ይላል/ አንዳንዴም ነጭ ካፒታሊስት/ ነኝ ይላል::  እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች በላይኛው ፓራግራፍ በተመለከተው ጥያቄ ግልፅ ልዩነት አላቸው:: ከ አድዮሎጂ ልዩነት ይልቅ ዋናው ልዩነታቸው አሱ ይመሰለኛል:: በክልልና በፌደራል ግኑኝነት ላይ ያላቸውን ፕሮግራም በቅጡ ሳይፈተሽ ወደ ፖለቲካ ሰልጣን ቢመጡ የራሳቸውን ዲዛይን በህዝቦች ፍላጎቶች ላይ አንደማይጭኑ ምንም ዋስትና የለም::

የፖለቲካ ድርጅቶች በክልልና የፌደራል ግኑኝነት ላይ ግልፅ የሆነ ፕሮግራም ሊኖራቸው ይገባል:: እንደ አኔ አመለካከት  የክልሎችና የፌደራል ግኑኝነት በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ ይወሰናል የሚሉትም ወገኖች ሆኑ: ግልፅ አቆም የያዙት ወገኖች የሕዝብን መደናገር በመቀነስ በኩል ምስጋና የሚገባቸው ናቸው:: በ ዲሞክራሲያዊ መንገድ ይወሰናል የሚሉት በዲሞክራሲያዊ ባህል አመኔታን  መገንባት አለባቸው::

የፌደራልና የክልል ግኑኝነት ጥያቄ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ቁልፍ ጥያቄ ነው:: የፌደራል አና የክልል ግኑኝነት ምንም ማሻሻያ አያስፈልገውም  በሚለው በ ህወሀት ኢህአድግ ዘንድ: ጥያቄውን ማንሳት የሕገ መንግስቱን የበላይነት አለመቀበል ነው:: የፌደራል አና የክልል ግኑኝነት ጥያቄ በሌሎች  ወገኖች ደግሞ የ ኢትዮጵያን አንድነት አንደማዳከም ይወሰዳል:: የፌደራልና የክልል ጥያቄ የብሔር ጥያቄን በሚያነሱ ህዝቦች የህልውናቸው መሰረት: ጭቆናን የሚከላከሉበት: እኩልነታቸውን የሚያረጋግጡበት: ከሌሎች ህዝቦች ጋር የማይጋሩትን የራሳቸው የሆነውን ታሪካቸውን የሚያስተምሩበት:ባሕላቸውን የሚያሳድጉበት ዋስትና ሆኖ ይቀርባል::

የህወሀት ኢህአድግ የብሔር ጥያቄን በዋነኛነት ሲያቀንቅን አንዳልነበረ ሁሉ በአሁኑ ጊዜ የብሔር ጥያቄን የሚያነሱ ወገኖችን ሁሉ በዘረኝነትና በሽብርተኛነት በመክሰስ ላይ ነው:: ይኽም የሕገ መንግስቱ አላማ የ ኤርትራ ከ ኢትዮጵያ መገንጠል ሽፋን ለመስጠትና የትግራይን ህዝብ የብሔር ጥያቄ የመመለስ ውስን አላማ ብቻ አንዳለው ያረግግጣል:: የብሔር ጥያቄ የኢትዮጵያን አንድነት ያዳክማል የሚሉ ወገኖች “ኢትዮጵያ” ሲሉ ሚዛናውነት ሲለቁ ይታያል:: የራሳቸው ብሔር ታሪክና ባህል: ከኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ለይተው ማየት ይሳናቸዋል :: የነሱ ብሔር ታሪክና ባህል  ከሌሎች ብሔሮች  ባህልና ታሪክ እኩል ሲሆን ሊደሰቱ እንጂ ሊከፉ አይገባም ነበር:: የኢትዮጵያ ብሔሮች ጥሩም ሆነ መጥፎ: የጋራ ታሪክ አላቸው:: የጋራና የግል ታሪካቸው ላይ መግባባት ይኖርባቸዋል:: የጋራ ታሪኩም ብቻ የኢትዮጵያ ታርክ ተብሎ ሊገለፅ ይገባል::

ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች: የሀወሀት/ ኢህአዴግ የፖለቲካ ሀይል: የአማራ ብሔር: የኦሮሞና የሌሎች የብሔሮች የፖለቲካ ሀይሎች ለሰላማዊውም ሆነ ውጤታማ የሆነ የፖለቲካ ሰልጣን ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ እዱሉ አላቸው::

የህወሀት ኢህአድግ የፖለቲካ ሀይሎች ፀሐይ አየጠለቀች መሆኑን መቀበል አለባቸው:: የህወሀት ኢህአዲግ የፖለቲካ ስልጣን ለጅትማሲ የነበረው የብሔር በሄረሰቦች መብት መከበር ጥያቄ የኦሮሞ ተቃውሞን: የጋምቤላን: የወልቃይትን: በደቡብ ኢትዮጵያ የተነሱ ተገቢ ጥያቄዎችን: በሀይል ለመመለስ ሀወሀት/ ኢህአድግ በወሰደው እርምጃ እርቃኑን ቀርቶል:: የህወሀት ኢህአዲግ ለራሱ ልማታዊ መንግስት የሚል ለጅትማሲ ለመፍጠር ቢሞክርም: ይኽ ምክንያት የውጭ መንግስታትን ከሚያማልል በስተቀር በሀገር ውስጥ ከጅምሩም ተቀባይነት ያገኘ አይደለም::

የህወሀት ኢህአዴግ የፖለቲካ ሀይሎች በሰላማዊ መንገድ የሰልጣን ሽግግር አንዲያደርጉ የታሪክ ሀላፊነት አለባቸው:: ይኽንን በሁለት አይነት መንገድ ማድረግ ይችላሉ:: የመጀመሪያው መንገድ በሀገሪቱ በጠቅላላ ነፃ አና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ ማድረግ ነው::  ይኽም በአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በሀገር ውስጥ አንዳይንቀሳቀሱ የወጡ አዋጆችን መሰረዝና: ለነዚህ የፖለቲካ ሀይሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ዋስትና መስጠትን ይጠይቃል:: የምርጫውን ውድድር የሚመራው አካል በተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነትን ያገኘና ዋስትና ያለው መሆን ይኖርበታል:: ምርጫው በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የሚመራ ሆኖ ቢቻል የተባበሩት መንግሥታት በዋነኛት የታዛቢዎችን ቡድን አንዲመራ መደረግ አለበት:: ሀወሐት ኢህአድግ በፓርላማ አብላጫ ድምፅ ላገኘው የ ፖለቲካ ድርጅት ስልጣኑን በማሸጋገር ታሪክ መሰራት ይችላል:: በምርጫው ሂደት በአሁኑ ወቅት ያለው የፖሊስ ሰራዊትና የመከላከያ ሰራዊት ሚና የህገር ውስጥ ሰላምና የውጭ ጥቃትን በመከላከል መወሰን አለበት::

የህወሀት ኢህአድግ የፖለቲካ ኃይሎች ሌላ ሊያደርጉት የሚችሉት አሁንም  በአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በሀገር ውስጥ የመንቀሳቀስ ገደብ የሚጥሉትን አዋጆችና ዉሳኔዎች በመሻር: ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመወያየትና በመደራደር ትውልድ የሚሻገር መፍተሄ መፈለግ ነው::

የህወሀት ኢህአድግ የፖለቲካ ቡድን የአንድን ብሔር ጥያቄ ከመመለስ ውጭ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ትርጉም ያለው የፖለቲካ መፍትሄ ያለመጣ ቢሆንም: ከሌሎች ብሔሮች ቀላል የማይባል የፖለቲካ ሀይል አሰልፎል:: ይኽ አሰላለፍ ግን ዘላቂነት የሌለውና  በሌላ አማራጭ ማጣት የተፈጠረ አሰላለፍ በመሆኑ  በማናቸውም ጊዜ ሊፈርስ አንደሚችል ሁለት ታላላቅ የፖለቲካ ክስተቶች አመላክተዋል:: የመጀመሪያው የ ፩፱፱፯ ምርጫ ሲሆን ሌላው ደግሞ በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ያለው የኦሮሞ  ተቃውሞ ነው::

ሀወሀት ኢህአድግ በእድሉ ሳይጠቀም ከቀረ ሌሎቹ የፖለቲካ ሀይሎች ትውልድን የሚሻገር መፍትሄ  ለማምጣት መተባበር አለባቸው:: ህወሀት ኢህአድግ ማዕቀብ የጣለባቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ማዕቀብ ያንሳ ስንል በተመሳሳይ ለሌሎቹም የፖለቲካ ድርጅቶች መስራት አለበት:: የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ከትብብር ውጭ መሆን የለበትም:: በመካከላቸው አስፈላጊ ያልሆነ  ግጭት ሊያመጡ ከሚችሉ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው:: የትኛውንም የ ፖለቲካ ፕሮግራም ቢያራምዱ: በትብብሩ ሂደት ገና የህዝብ አዎንታ የሚፈልግ ፕሮግራም አንደያዙ አንጂ: በሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ዉሳኔ አዎንታ ያገኘ የፖለቲካ ፕሮግራም አንደያዙ መቁጠር የለባቸውም::  በአሁኑ ውቅት ባገኙት ድጋፍ አና አቅም ተኩራርተው ከትብብር ዉጭ መሆንም  የለባቸውም::

የአማራ የፖለቲካ ሀይሎች መሰረቱ የቀድሞ የፖለቲካ ስልጣን ነው:: ይኽ የፖለቲካ ሀይል በአብዛኛው ቀደም ስል በነበሩ ስርዓቶች ከ አማራው ተራማጅ አስተሳሰቦችን ሲያራምድ የነበረው ክፍል የፖለቲካ አስተሳሰብን የወረሰ ነው:: የዚህ የፖለቲካ ሀይል ደጋፊዎች ከብሄር ጭቆና ዉጭ ስለነበሩ ከሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች በተሻለ ያለፉ ስርዓቶች የፈጠሩት የኢኮኖሚና የባህል የታሪክ የበላይነት የነሱ ነበሩ: ህወሀት ኢህአድግ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ሆነ የኢኮኖሚ የባህልና የታሪክ የበላይነት ለመያዝ በሚሰነዝረው ጥቃት ሁሉ የመጀመሪያ ኢላማው ናቸው:: ይኽ የፖለቲካ ሀይል በአሁኑ ወቅት  የፖለቲካ ስልጣን የሚያስገኘውን ጥቅም ቢያጣም  የቀዱሙት ስርዓቶች በፈጠሩለት መልካም አጋጣሚ በሌሎች ዘርፎች  የያዘውን የበላይነት አሁንም ሙሉ በሙሉ  አላጣም::  የፖለቲካ ስልጣንም ትግል በማድረግ ላይ ነው:: ፍትህ ዲሞክራሲና አንድነት ማምጣት የፖለቲካ ትግሉ ግብ አድርጎ ይገልፃል:: በህወሓት ኢህአድግ  የፖለቲካ ሀይሎች የፖለቲካ ህይሉ የሚታገለው አማራን ወደ ፖለቲካ ስልጣን ለመመለስ አና የአማራ የፖለቲካ የኢኮኖሚ የባህል የታሪክ የበላይነትን ለማስመለስ የሚታገል የፖለቲካ ሀይል ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን  ነገር ግን አንድ ስንዝር አንዳይራመድ ጥበቃ የሚደረግበት ነው:: ይኽ የፖለቲካ ሀይል በብሄር ጥያቄ ላይ ከሚያራምደው አቆም አንፃር በኦሮሞ ና በሌሎች የብሔር ጥያቄ በሚያነሱ የፖለቲካ ሀይሎች በጥርጣሬ የሚታይ ነው:: የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች በሚመሩት አሰላለፍ ከሁሉም ብሔሮች የተሳተፉ ግለሰቦች ባይጠፉም በዋነኛነት በተለይ ከ አናሳ ብሄሮች በርከት ያሉ ደጋፊዎችን ማሰለፍ ችለዋል::  ይኽ አሰላለፍ አናሳ ብሄሮችም የብሔር ጥያቄ ያላቸው በመሆኑ: ዘለቄታው አስተማማኝ  አይመስለኝም::

የኦሮሞ የፖለቲካ ሀይሎች የብሔር ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል:: ይኽ የፖለቲካ ሀይል ከዚህ ቀደም በነበሩ ስርዓቶች በሀይል የተነጠቃቸውን: ያልተመለሱ የፖለቲካ ጥያቀዎችን ለማስመለስ አንደሚታገል ይገልፃል: ይኽ  የፖለቲካ ሀይል የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ ቀደም በነበሩ የፖለቲካ ስርዓቶች በሀይል የተነጠቀው: ተመልሶለታል/ይበቃዋል በሚለው ሀወሀት ኢህአድግ የመረረ ጠላት ተደርጎ ተወስዶል:; ይኽ የፖለቲካ ሀይል በራሱ የፖለቲካ ሀይሎች ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን ተመሳሳይ የብሔር ጥያቄ ያላቸው አጋሮች አሉት:: ይኽ የፖለቲካ ሀይል  በአማራ የፖለቲካ ኃይሎችና በሰልፉ ውስጥ በተካተቱት ሁሉ ወዳጅነትን ሲነፈግ ይታያል::

ትውልድ የሚሻገር መፍትሄ ለማምጣት በነዚህ የፖለቲካ ሀይሎች መካከል ወይይት: መተባበር; ድርድር ያሰፈልጋል:: ከትንሽ ወደ ትልቅ የሚያድግ ትብብር ቢሆን ይመረጣል:: ትብብር ማድረግ አስቸጋሪና ፈታኝ መሆኑን በቅድሚያ መቀበል ያስፈልጋል::  በ መሳሪያ ሀይል አንዱ የፖለቲካ ሀይል ሌላውን ለማንበርከክ የሚያደርጉት ጥረት ዉሀ ቢወቅጡት አንቦጭ እንዲሉ ከሚሆን ዉጭ ትውልድ የሚሻገር መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም:: ለብዙ መቶ አመታት የቆዩ የሌሎች ሀገሮችን ሕገ መንግስቶች እያየን አድናቂ ብቻ ሆነን: ሌሎች ግን አንደተደነቁብን አንቀራለን::

ቸር እንሰንበት::

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s