በእርስ በእርስ ጦርነት ድል ሀያ አምስት አመት ፉከራ፤ ይገረም አለሙ

በእርስ በርስ ጦርነት ከሁለቱም ወገን የሚሞተው የአንድ ሀገር ልጅ ነው፡፡ አባትና ልጅ፤ወንድምና ወንድም ከዛና ከዚህ ተሰልፈው የሚገዳደሉበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ ይህም  በ17 አመቱ የርስ በርስ ጦርነት በግልጽ ታይቷል፡፡  ወያኔዎች ለድል የበቁት የኢትዮጵያን ሰራዊት ብቻ ሳይሆን ደርግን ተቃውመው ብረት ያነሱ ነገር ግን ከዋሉ ካደሩ ለህውኃት ህልውና አስጊ ይሆናሉ ያሉዋቸውን ድርጅቶች ጭምር ( ለምሳሌም ኢህአፓ ኢዲዩ ) ተዋግተው፤ከዚህም አልፎ በህውኃትም ውስጥ የተለየ አስተሳሰብ ያራመዱ ወይንም ለሥልጣን ያሰጋሉ የተባሉትን እያሰቃዩና እየገደሉ በመሆኑ መገዳደሉ በአንድ ሀገር ልጆች መካከል ከመሆን አልፎ በቤተሰብ መካከል ጭምር እንደነበር አሌ አይባልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ በኢህአፓነቱ በወያኔ እንደተገደለ የሚነገረውን የአቶ በረከት ስምኦን ወንድም መጥቀስ ይቻላል፡፡

Eprdf

በጦርነቱ ተጠቂ የሚሆነው ከሁለቱም ወገን ታጥቆ ለውጊያ የተሰለፈው ብቻ አይደለም፤ በውጊያው መካከል ሰላማዊ ዜጎች ሴት ወንድ ሕጻን አዛውንት ሳያለይ ለጉዳት ይጋለጣሉ፤የሀገር ሀብት ይወድማልና  ይህ ሁሉ የሚያሳዝን እንጂ የሚያስፈነድቅ አይሆንም፡፡ ስለሆነም ሰዋዊ አስተሳሰብ የተላበሰ ሀይል በርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ  የነበረውን አገዛዝ ለመለወጥ ከጦርነት ውጪ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ  ወደንና ፈቅደን ሳይሆን ተገደን በገባንበት የርስ በርስ ጦርነት የገደልንም እኛ የሞትንም እኛ በመሆናችን ጦርነቱ ባደረሰው የሕይወትም ሆነ የንብረት ውድመት ከልብ እናዝናለን፡፡ይህ መሰል ሁኔታ ዳግም በሀገራችን አንዳይፈጠርም ለሰብአዊ መብቶች መከበር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆንና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ አጥብቀን በመስራት የጠፋውን እንክሳለን ማለት ነው የሚጠበቅበት፡፡

ወያኔዎች ግን  ግንቦት ሀያ ሲመጣ በየአመቱ ለቀናት አንዳንዴም ለሳምንታት  ሲተኩሱና ሲገሉ፤ ጋራ ሲቧጥጡና ሲማርኩ ወዘተ የሚያሳዩ ፊልሞቻቸውን እያሳዩን የሚያሰሙት  የጀብዱ ዲስኩር፤ የሚያወርዱት የድል አድራጊነት ቀረረቶና ፉከራ የርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ ሳይሆኑ ድንበር ተሻግሮ ሉዐላዊነት ደፍሮ የመጣን ወራሪ ድል ነስተው የመለሱ ነው የሚያስመስላቸው፡፡

ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው በአሸናፊነት ስሜት ሲታበዩና በጀግንነት ሲፎክሩ የምናይ የምንሰማቸው በአብዛኛው ከደደቢት እስከ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በነበረው ትግል ድንጋይ ተንተርሰው ወዲ አኪር በልተው የታገሉት ሳይሆኑ አንድ ቀን ጠብ-መንጃ ነክተው የማያውቁት መሆናቸው ነው፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ የድል አጥቢያ አርበኞች የወያኔን ዓላማ ተቀብለው ሳይሆን አያያዙን አይተህ ወደ ሚያደላው በማለት ከመጣው ተጠግቶ መኖርንና እያዘረፉ መዝረፍን የተካኑ አስመሳዮች ናቸው፡፡ እነዚህ ወያኔ ከሥልጣን ቢወርድ ሀጁን  እያወገዙ መጪውን በማወደስ መስሎ ለማደር የሚቀድማቸው የለም፡

ወያኔዎች ዛሬም ከሀያ ዓምስት ዓመታት በኋላ ራሳቸውን ከደርግ ጋር እያነጻጸሩ መሻላቸውን ለማሳየት መጣራቸውና በአሸናፊነት መፎከራቸው ሰራነው የሚሉት የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀልብ የሚማርክ ውጤት ስለሌላቸውም ነው፡፡

ይህም ሆኖ ለንጽጽር ከመረጡት ደርግ ጋር በህሊና ሚዛን በገለልተኛንት ስሜት ብናነጻጽራቸው የሚሻሉበት ጥሩ ነገር የመኖሩን ያህል የሚመሳሰሉበትም፣የሚበልጡበትም ከዚህ አልፎ የሚያንሱበትም  ብዙ መጥፎ ተግባር አለ፡፡

ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን በወረቀት በማስፈር ይበልጣሉ፡፡ በአፈናው ግን አይተናነሱም፡፡ ሰው በመግደሉም ቢሆን ከደርግ ጋር የቁጥር ሂሳብ ይገቡ ካልሆነ በስተቀር አይተናነሱም፡፡ እንደውም ደደቤቲ ጀምረው የገደሉት ከተቆጠር እንደሚበልጡ አያጠራጥርም፡፡ በአገዳደል ግን ይለያያሉ፣ ደርግ ገድሎ በፍየል ወጠጤ ቀረርቶ በታጀበ መግለጫ ይፋ ያደርጋል፡፡ወያኔዎች ገድለው ሌላ ሰብብ ይፈጥራሉ፤አስክሬን ይደብቃሉ፤ሲጋለጡም የቁጥር ክርክር ይገጥማሉ፡፡ተቃውሞ ከበረታባቸውም ይቅርታ በማለት ለማለዘብ ይጥራሉ፤

በቀደሙት ሥርዓቶች የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች እስር ቤት በነበረችው ኢትዮጵያ በግንቦት ሃያ ድል ብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት ተጎናጽፈዋል ነጻነታቸውን ተቀዳጅተዋል ብለው ይደሰኩራሉ፡፡ ነገር ግን  በየክልሉ አስተዳዳሪ የሆኑት ድርጅቶች የህውኃት ሞግዚቶች አንጂ የህዝብ ወካዮች አለመሆናቸው ይጠቀስና  በብዙ አካባቢዎች የተነሱና በኃይል ታፍናው የሚገኙ የራስ አስተዳደር መብት ጥያቄዎች በማስረጃት ይቀርቡና ዲስኩሩን ፍሬ ቢስ ያደርጉታል፡፡

በኢኮኖሚ እድገት ከደርግ መሻላቸውን ሲናገሩ ሕዝቡ የዛሬና የትናንት ኑሮውን እያነጻጻረ ፤በገጠመው የኑሮ ውድነት እየተማረረ አረ የት ጋር እነማን ዘንድ ነው ይሄ እድገት የምትሉት በማለት ይጠይቃል፡፡

ትምህርት ቤት ኮሌጅ  አስፋፋን ብለው ከደርግ ጋር ሲፎካከሩ የትምህርት ጥራቱ ይሳለቅባቸዋል፡፡

ደርግን የመናገር ነጻነት ጠር አድርገው ራሳቸውን ለመኮፈስ ሲዳዳቸው በየእስር ቤቱ በሚገኙት ጋዜጠኞች  ይሳጣሉ፤ በክልል ከተሞች ቀርቶ አዲስ አበባ ላይ  እንኳን የሚታዩት  የህትመት ውጤቶች ከቁጥር የማይገቡ በመሆናቸው ይጋለጣሉ፡፡ ራዲዮና ቴሌቭዥኑ አልበቃ ብሎአቸው የኢንተርኔት የግንኙነት መንገዶችን ለመቆጣጠር በሚያፈሱት ገንዘብ ይሞገታሉ፡፡

የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ በማራመድ መሻላቸውን ሲናገሩ ቴሌን የማይነጥፍ ጥገት ብለው ሙጥኝ ማለታቸው ይታሰብና፤የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ብዛትና የሚሰሩት ይጠቀስና የሰሞኑ የሜቴክ ዝርፊያም በማስረጃት ይቀርብና የት ጋር ነው ነጻ ገበያ ይባላሉ፡፡

ደርግን የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ብለው እያወግዙ ለቁጥር አንጂ ለተግባር አንዳይኖሩ ያደረጉዋቸውን ፓርቲዎች በማስረጃት በመጠቅሰ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንደሚያራምዱ ሲናገሩ  የአንድ ፓርቲ ገዢነታቸውን ፓርላማው ያጋልጣቸዋል፡፡ ምርጫ አጭበርባሪነታቸው በማስረጃ ይቀርብባቸዋል፡፡ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ወያኔዎች  ሀያ አምስት ኣመት ሙሉ ራሳቸውን ከደርግ ጋር እያነጻጸሩ መኮፈስን ፣ የበርሀ ፊልማቸውን እያሳዩ  ጉሮ ወሸባ ማለትን  ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ በሥልጣን ላይ እስካሉም ከዚህ ድርጊታቸው የሚላቀቁ አይመስልም፡፡

ወያኔዎችን ሀያ አምስት ዓመት ሙሉ የሚያስፎክራቸው አምስት ሆነው ኋላ ቀር መሳሪያ ታጥቀው በጀመሩት ትግል የገበሬ ታጋይ ይዘው የሰለጠነና ዘመናዊ  መሳሪያ የታጠቀውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ማሸነፋቸው ነው፡፡ ለአሸናፊነት ለመብቃታቸው በምክንያትነት የሚጠቀሱ( ለምሳሌ በቅርቡ የተጋለጠው የእንግሊዟ ንግስት ደብቅ ርዳታ) እንዳሉ ሆነው የተባለው እውነት ነው፡፡ ትንሽ የነበረው ትልቁን ለማሸነፍ በቅቶ እሱ በተራው ትልቅ ሲሆን ግን ትንሽ ሆኜ ትልቁን ያሸነፍኩ እኔ ጀግናው የሚለው አስተሳሰቡ ላይ ቸክሎ መቆም የለበትም፡፡ እንደዛ ካደረገ ባሸነፈበት መንገድ መሸነፍን  እየጠበቀ  ነው፡፡ ነገር ግን ትልቅ የነበረው  በእኔ ትንሽ በነበርኩት  ሊሸነፍ የቻለው ለምንድን  ነው ብሎ ማሰብ ግን ዛሬ ትንሽ ነው ተብለው በሚናቁት ላለመሸነፍ መፍትሄ ለመፈለግ ያስችላል፡፡ ወያኔዎች ግን የተያያዙት ደርግን በማሸነፋቸው መኩራት ፣በማንም የማይደፈሩ አድርገው በማሰብ መፎከርና የደደቢት ትልማችንን ተግባራዊ ከማድረግ የሚያቆመን አይኖርም በማለት የጀመሩትን መቀጠል ነው፡፡

የወያኔዎችን ድርጊት አሳሳቢ የሚያደርገው በአሸናፊነት መፎከራቸው በማን አለብኝነት መኩራራታቸውና ከደደቢት ህልማቸው ንቅንቅ  አለማለታቸው ብቻው ሳይሆን ፡ከውድቀታቸው በፊት በሚነገራቸው ተመክረው፣  ከሚያደርሱትና ከሚደርስባቸው ተምረው የማይመለሱ መሆናቸው ነው፡፡ እነርሱ ሥልጣናቸውን ከሚያጡ ኢትዮጵያ ብትፈራርስ የሚመርጡ በመሆናቸው ውድቀታቸው  ሀገርንና ሕዝብን ለጉዳት  ይዳርጋል፡፡ ለዚህም ነው ለለውጥ የሚታገሉ ኃይሎች ወያኔን ከሥልጣን ማውረዱን ብቻ ሳይሆን የእሱ መውረድ ሊያደርስ የሚችለው አደጋ አነስተኛ አንዲሆን ለማድረግ ማሰብና መስራት የሚኖርባቸው፡፡

በእያንዳንዱ ርምጃቸውም ገደልን ብለው የሚፎክሩ፤ ማረክን ብለው የሚያቅራሩ፤ ድል አደረግን ብለው የሚኩራሩ መሆን የለባቸውም፤ ይህን ካደረጉ  ከወያኔ አልተሻሉምና ድል ቢቀናቸው አዲስ ንጉሥ አንጂ ለውጥ መቼ መጣ የሚለው ዜማ ለእነርሱም የሚዘፈን ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: