ከሃብታሙ አያሌው እስከ በቀለ ገርባ – በእስር ቤት የሚፈጸሙ ሰቆቃዎች | ከሙሉነህ ኢዩኤል

ባለፈው ሳምንት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ ፌዴራልስት ኮንግረስ መሪዎች ከታጎሩበት ጎረኖ “ፍርድ ቤት” ቀርበው ነበር። መቸም ስም አጥቼለት እንጂ “ፍርድ ቤት” ብዬ ስጠራው በጣም እየሰቀጠጠኝ እንደሆነ ይታወቅልኝ። ያለ ስሙ ስም ሰጥቼ “ፍርድ ቤት” ስለው አቶ በቀለና ሌሎች ብዙ ሺዎች የሚያዩትን ፍዳ ያራከስኩባቸው፣ ወያኔንም ስልጣኔ የሚባል ነገር እስከወዲያኛው የማይገባው እጅግ ኋላ ቀር ቡድን እንደሆነ እያወኩ ተቀናቃኞቹን ፍርድ ቤት አቅርቦ እንዲዳኙ እድል የሚሰጥ ስልጡን ቡድን እንዲመስል ያረኩ እየመሰለኝ በጣም እየተሳቀቅኩ ነው። ቢያንስ አቶ በቀለና በዚያ ማሰቃያ ቦታ የተገኙና ወደፊትም የሚገኙ ሁሉ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ብዬ እንደማላምን ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ። እነርሱም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና ወያኔ እስካለም ድረስ እንደማይቀርቡ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ትግላቸው ለምን ሆነና?

bekele gerba

እጅግ አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው ጉዳይ ግን የእነ አቶ በቀለና ጓዶቻቸው በቁምጣና በእጅጌ ካንቴራ ተገላልጠው መምጣታቸው ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያት የነበረው የሚለብሱትን የልብስ አይነትና ቀለም ወያኔዎች ካልመረጥንላችሁ በሚል ባነሱት የእብሪት እርምጃ አልበገር ያሉ ታሳሪዎች የሰው ልጆች መሆናቸውንና ለሰው ልጅነት ያላቸውን የተከበረ እይታ ለማሳየት አጋጣሚውን ለመጠቀም መወሰናቸው ነበር። የእነ አቶ በቀለ መልዕክት ከአሳሪዎቻቸው መልዕክት በእጅጉ ይቃረናል። እስቲ ሁለቱን መልዕክቶች ተራ በተራ እንያቸው፤

ታሳሪዎች የ”ፍርድ ቤት” ቀጠሮ እንዳላቸው ስለሚያውቁ አስቀድመው ተዘጋጅተዋል። እነ አቶ በቀለ “ፍርድ ቤት” ሊሄዱ የተነሱት በአጋዚ ጦር በኦሮሚያ ውስጥ ለተገደሉ ከ400 በላይ ለሚቆጠሩ ወንድሞቻቸው ሃዘን ሊቀመጡ እንጂ ፍትህ ፍለጋ አልነበረም። በሃገራችን ባህል ደግሞ ሰው ሀዘን ሲቀመጥ ጥቁር ይለብሳል። እንኳን በግፍ ለተጨፈጨፉ ወንድሞቻቸው ቀርቶ ሰው እድሜ ጠግቦ ለሞተ ዘመዱም ጥቁር ይለብሳል። ለቅሶ ደርሰው የሟች ቤተሰቦችን ማጽናናት ባይችሉ እንኳን ”በፍርድ ቤት” ደጃፍ ተገኝተው ሃዘናቸውን መግለጽ ይፈልጋሉ። ሰው መሆን ይሀው ነው ትርጉሙ።

አሳሪዎች ጥቁር የለበሱ ታሳሪዎችን ሲመለከቱ ደማቸው ፈላ። ወደየመኪኖቻቸው መውሰዱን ለጊዜው ገታ በማድረግ ወደዞኖቻቸው መልሰው ልብስ እንዲቀይሩ ያዛሉ። ወላጆች ለህጻናት አልያም በራሳቸው መምረጥ ለማይችሉ (mentally impaired) ለሆኑ ልጆቻቸው ልብስ ይመርጡላቸዋል። ጌቶች ለታሳሪዎች “ልብሳችሁን ቀይሩ” ሲሏቸው ምን እያሏቸው ነው? ህጻናት ወይም የአካል ጉዳተኛ ስለሆናችሁና መምረጥ ስለማትችሉ እኛ እንምረጥላችሁ እያሏቸው ነው። ለአቶ በቀለ ከራሱ ልብሶች ውስጥ አሳሪዎች መርጠው ቢሰጡት በራሱ ምርጫ የገዛቸውና ሌላ ጊዜ ሲለብሳቸው የነበሩት የራሱ ልብሶች በጣም አስጠሉት። እነርሱ የመረጡለትን ልብስ መልበስ ህጻን ነኝ አልያም የአካል ጉዳተኛ ነኝ ብሎ እንደማመን ሆነበት። “እናንተ የመረጣችሁልኝን የራሴን ልብስ ከምለብስ እራቁቴን ብሄድ ይሻለኛል” አለ። የራሱ ልጆች ያሉት የተከበረ ሰው (adult) መሆኑን አስመሰከረ። ሰው የመሆን ትርጉሙ ለራሱ የሚለብሰውን የሚጠጣውን የሚመራውን መምረጥ መሆኑን አስተማራቸው። እንዳለመታደል ሆኖ አሳሪዎቹ ይሄ ትምህርት ይገባቸዋል ወይ ብዬ እጠይቅና በአንድ ወቅት በእጃቸው ስለነበርኩና እነዚህን ሰዎች ስለማውቃቸው ድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰስ ስለሚሆንብኝ በጣም እተክዛለሁ።

በመጨረሻ በእስር ቤት ውስጥ ሰቆቃ ስሚፈጽሙና ስለሚያስፈጽሙ ሰዎች ማንነት ጥቂጥ ልበል። የእስር ቤቱ ዋና ዋና ሰዎች የአንድ አካባቢ ተዎላጆች ናቸው። ዋናው ሃላፊ አብርሃም ወ/አረጋይ ይባላል። ሰውነቱ ሞላ ያለ፤ ምቾት ያንገላታው ሰው መሆኑን ከቆዳው ወዝ በቀላሉ መገመት የሚያስችል አይነት ሰው ነው። ከድንጋይ ማምረቻ ድግሪ ጭኗል እይተባለ ይወራለታል። ድንጋይ የሚፈለጥበት እንጂ እውቀት የማይገበይበት ቦታ ለመሆኑ ከአብርሃም ወ/አረጋይ በላይ ምን ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል? አብርሃምን ያገኘ ሁሉ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ማድነቁ የማይቀር ነው። በምንም አይነት ጉዳይ ላይ ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ መግባባት የማይታሰብ ነው። ድንጋይ ታውቃላችሁ? የሰው ድንጋይ። ለፖለቲካ እስረኞች ያለው ጥላቻ ድግሞ የሚያስፈራ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ያለው ሰው አበበ ዘሚካኤል ይባላል። ቀይ አጭር፤ በአንድ በኩል ከጆሮው ከፍ ብሎ ጭንቅላቱ ላይ ትንሽ እብጠት ያለበት ሰው። እህቱ የቀበሌያችን ሊቀመንበር ነበረች። ከበደች ዘሚካኤል ትባላለች። አበበ በጣም የምትወዱት ክፉ ሰው ነው። እንዴት ክፉ ሰው ይወደዳል ትሉኝ ይሆናል። ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ የምትናገሩት ነገር የሚገባው ሰው ማግኘት መቻል እንዴት ብርቅ ነገር መሰላችሁ! እስር ቤት ውስጥ ያሉ ሃላፊዎች ሁሉ ድንጋይ በሆኑበት ቦታ የምትናገሩት ነገር የሚገባው ብቸኛ ሰው አበበ ይባላል። ርህራሄ የሚባል ነገር መኖሩን ያልሰማ ሰው ነው። አብርሃም በማይኖርበት ጊዜ የእስር ቤቱ ሃላፊ እርሱ ነው። በተጨማሪ ለእስረኞች የሚመጡ መጽሃፍትን አንብቦ እንዲገቡ አልያም እንዳይገቡ የሚወስነው እርሱ ነው።

በሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ሶስት ሰዎች ሲሆኑ፤ እነርሱም ሻለቃ አፈወርቅ፣ ጉኡሽና የማነህ ተክሉ ይባላሉ። የአፈወርቅንና የጉኡሽን የአባቶቻቸውን ስም አላውቅም። በዚህ አጋጣሚ የአባቶቻቸውን ስሞች ላስቀዳኝ ወሮታ እከፍላለሁ። ሻለቃ አፈወርቅ ገራ ገር ሰው ነው። በገራገርነቱ ካልሆነ በቀር በእውቀት ከሌሎቹ እምብዛም የሚለይ አይደለም። ምንም እንኳን በተወላጅነት የጌቶቹ አገር ሰው ቢሆንም የደርግ ሻለቃ ስለነበር ሌሎቹን ይፈራቸዋል። እኔ እንዳየሁት ሌሎቹን ስለሚፈራ ነው እንጂ በጎ ነገር ለማድረግ ፍላጎት ያለው ሰው ይመስላል። ከብዙ እስረኞች እንደሰማሁት የጥቅምት 21 1998 የጅምላ ጭፍጨፋ ያስቆመው እርሱ እንደሆነ የመሰክሩለታል፤ ራሱም የዚያን ጎደሎ ቀን የጅምላ ፍጅት ማስቆሙን ይናገራል። በዚህ ጭፍጨፋ የሞቱት 163 እስረኞች ሲሆኑ ስም ዝርዝራቸውን “የቃሊቲው መንግስት” በሚለው የሲሳይ አጌና መጽሃፍ ውስጥ መመልከት ይቻላል። ሻለቃው ለአጣሪ ኮሚሺን ሃላፊዎች በሰጠው ቃል በ30 ደቂዳ ውስጥ 1500 ጥይት መተኮሱን እየተጸጸተ መግለጹን ሰምቻለሁ። ከቃሊቲ የወጣን ቀን በእነ አቶ ሀይሉ ሻውል ዞን የነበሩትን የቅንጅት እስረኞች “አውቀን በድፍረት ሳናውቅ በስህተት የፈጸምነውን በደል ይቅር በሉን” አይነት ሰላምታ ሰጥቶ መሸኘቱን በዚያ ዞን ከነበሩ እስረኞች ሰምቻለሁ።

ጉኡሽ በእድሜ ተለቅ ያለ ሰው ነው። በቤትና በስራ ቦታው መካከል ልዩነት እንዳለው የሚያውቅ አይመስልም። ወይ አልነገሩትም፤ ወይም አልገባውም። ጋቢ ለብሶ እስር ቤት ውስጥ ሲንጎማለል ስታዩት እስረኛ እንጂ ከጌቶቹ ወገን በጭራሽ አይመስላችሁም። “ጌታዬ ይሄ እኮ የሥራ ቦታ ነው፤ ጋቢ ተለብሶ አይዞርም” ብሎ ማን ወንድ ይነግረዋል? አንዳንዴ ደርግ በእነዚህ መሸነፉ በጣም ያስገርማል። አልፎ አልፎ ሲስቅ እንዳየሁት ትዝ ይለኛል።

የማነህ ተክሉ ፊቱ ዝናብ አርግዞ እንድጠቆረ የሃምሌ ወር ዳመና ፊቱ የማይፈታ ሰው ነው። እንደሱ አይነት ጨካኝ ከሰው ያልተፈጠረ አይነት ሰው ነው። ስለዚህ ሰው ባሰብኩ ቁጥር የሚመጡብኝ አንድ ቀን ነው። የሄ ቀን “ፍርድ ቤት” ደጃፍ መኪና ውስጥ ተቀምጠን ወደአዳራሽ እስከሚያስገቡ እየተጠባበቅን ሳላ እኛን ካለንበት መኪና ማዶ ባለ ሌላ መኪና ውስጥ ያለችውን ባለቤቱን ሰላምታ ስለሰጣት እስክንድርን ሊቆጣው ወደ መኪናችን የመጣበት ቀን ነው። በጣም ተናዶ ለመማታት እየቃጣው ሰላምታ መስጠት እንደማይችል ገለጸለት። እስክንድርም የዘጠኝ ወር እርጉዝ የሆነች ባለቤቱን ሰላም በማለቱ እንዲያው ሊያዝንለት እንጂ ሊቆጣው እንደማይገባው በትህትና ሊያስረዳው ሞከረ። ይባስ ብሎ ሰርካለምና እስከንድር እንዳይተያዩ ሴት እስረኞችን የጫነው መኪና እኛ ካለንበት ዞር እንዲል ትዕዛዝ ሰጠ። እስረኞች ሰዎች መሆናቸውን የዘነጋ ሰው ነው። እነ አቶ በቀለና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በምን አይነት መከራ ውስጥ እንደሚያልፉ እንዲያስታውሰን የአቶ ሃብታሙ አያሊውን ሰቆቃ ልጋብዝዎ፦

Leave a comment