አቶ አሰፋ ጫቦ -ምነው እስካሁን? – ይገረም አለሙ

  •  

አቶ አሰፋ ጫቦ

ከአቶ አሰፋ ጫቦ ጋር ያስተዋወቀችን ተወዳጇ ጦቢያ መጽሄት ነበረች፡፡ በጽሁፋቸው አወኳቸውና በይበልጥ በሁለት ነገር ውዴታና አክብሮት በልቤ ታትሞ ቀረ፡፡ አንደኛው ጽሁፋቸው የሚነበብ ብቻ ሳይሆን የሚታይ መሆኑ ነው፡፡ ፊልም የማየት ያህል ነው፡፡ ማዕከላዊ የሚባለውን የግፍ ቦታ ለአጭር ግዜም ቢሆን ገብቼ ከማየቴ በፊት በአይነ ልቦናዬ የቃኘሁት ፤ጨንቻን በእግሬ ሳልረግጣት በፊት ያወቅኋት በአቶ አሰፋ ጽሁፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዛ አባላሽኝ ዘመን ለሆነው ሁሉ ተጠያቂነታችን ይበዛ ያንስ ካልሆነ በስተቀር ማናችንም ነጻ አይደለንምና የድርሻ ድርሻችንን እንውሰድ በማለት (ቃል በቃል አልጠቅሼ ይሆናል) በየጽሁፎቻቸው ይወተውቱ የነበረው ነው፡፡ ያን ማድረግ ተችሎ ቢሆን ዛሬ የደረስንበት የውድቀት ደረጃ ላይ ባልተገኘን ነበር፡፡

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ አልፎ አልፎ  በድረ-ገጾች ብቅ እያሉ ትውስታቸውን የሚያካፍሉን አቶ አሰፋ ሰሞኑን “ትቼው ረስቼው” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያን የተቃውሞ ፖለቲካ ጎራ ርስተ ጉልት ስላደረጉት ኢ/ር ኃይሉ ፕ/ር በየነና ፕ/ር መረራ በጥቅል ትንሽ ግን ጥልቅ መልእክት ያለው ነገር ነገሩን፡፡ ስለ ፕ/ር በየነ ደግሞ ትንሽ ሰፋ አድርገው ትውውቃቸውን፣ የፕ/ር የሥልጣን ጥም ፣ፓርቲ አፍራሽነት ብሎም በወያኔነት መጠርጠር ነገሩን፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ምነው አቶ አሰፋ እስከ ዛሬ ያሰኘኝ፡፡ ፕሮፌሰሩ ይህን ያህል ዓመት በየግል ፓርቲዎችን ሲያብጡ፣ ህብረት በተባለበት ቦታ ሁሉ ፊጢ እያሉ ሲያሽመደምዱ አቶ አሰፋ ነጋሪም ኮርኳሪም ሳያስፈልጋቸው ለውጥ አመጣም አላመጣም ስለ ፕ/ር በየነ የሚያውቁትን በመግለጽ ማንነታቸውን በማጋላጥ የበኩላቸውን ማድረግ ነበረባቸው ብዬ አሰብኩ፡፡ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ  እየባሰ እንጂ እየተሻለ አልሄደምና፣ ፕሮፌሰር በየነም የሁለትና ሶስት ፓርቲዎች ሊቀመንበር ከመሆን አልታቀቡምና፣መድረክን እግር ከወረች አስረውታልና ፤ ከሞት በመለስ ሥልጣን የሚለቁም አይመስሉምና ወዘተ አቶ አሰፋ የሚያውቁትን በተለመደው ግልጽነትዎና ድፍረትዎ ያካፍሉን፡፡

ስለ ፕ/ር በየነ ብዙ ተጽፏል፣የአቶ አሰፋ ግን ከሁሉ ሚዛን አንደሚደፋ እገምታለሁ፡፡በተጨባጭ ማስረጃ የሚገለጽ  የአይን እማኝነት ነውና፡፡ በፕ/ር በየነ ከተነገሩና ከተደረጉ አያሌ ነገሮች መካከል ሁለቱ ዘወትር ይገርሙኛል፡፡ አንደኛው  በአንድ ግዜ የብሔርም  የሕብረ ብሔርም ፓርቲ ሊቀመንበር መሆናቸውና የምርጫ ቦርድ ምሥክር ወረቀት ማግኘታቸው ነው፡፡ የብሄሩ የሀድያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሲሆን ሕብረ ብሔራዊዎቹ  ብዙ ናቸው፡፡ ሁለተኛው የቅንጅት አመራሮች ከእስር በተፈቱ ሰሞን ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል የጀመረው ደቡብ ህብረት ነው  ከዛ በኋላ ከበሮ በሰው አጅ ሲያዩት ያምር አንደሚባለው ብዙዎች እንገፍ እንገፍ ሲሉ አይተናል፣አንዳንዶችም እየሮጡ ወደ እስር ቤት ሲገቡ ተመልከተናል፡” ( ቃል በቃል አልጠቅሼ ይሆናል ) ያሉት ነው፡፡

አቶ አሰፋ የጠቀሱዋቸው የፕሮፌሰር መረራና የፕ/ር በየነ የአመታት ቁርኝትም የውስጥ አዋቂ ገለጻ የሚሻ ነው፡፡ ምክንያቱም ውጫዊ ሁኔታቸውን በቅርብ ለምናውቅ ሰዎች ሁለቱን እንዲህ ለአመታት በሊቀመንበርነት ቦታ እያፈራረቀ የሚያቆይ ሁኔታ የላቸውም፡፡ የውስጡን ግን አላወቅንም፣ ማወቅም አልቻልንም እናም አቶ አሰፋ የሚያውቁት ካለ ጀባ ቢሉን፡፡ ህብረት በተባለ ቁጥር ሰዉስ ርሳቸውን የሚመርጥበት ምክንያት ምን ይሆን?

ስለሁለቱ ካነሳሁ አይቀር አንድ ትውስታየን ላካፍል ምን አልባት አቶ አሰፋንም ለመኮርኮር ይረዳ ይሆናል፡፡ ትቼው ረስቼው ያሉትን ያካፋሉን የአቶ ግርማ ሰይፉ ጽሁፉ ኮርኩሮቸው እንደሆነ ነግረውን የለ፡፡

ግንቦት 1992 ዓም ነው፤ በኦብኮ አስተባባሪነት በኢተፖድኀ ድጋፍ ስምንት ፓርቲዎች ትብብር ለመፍጠር በኢየሩሳሌም ሆቴል ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ህብረቶችን ካለመራሁ የሚሉት ፕ/ር በየነ በዚህ ስብሰባ አልተጋዙም ነበርና ተሰብሳቢዎቹ ገና ከአዳራሽ ሳይወጡ የፖለቲካ ቁማር በማለት አውግዘው የተቃውሞ መግለጫ አወጡ፡፡ መድረኩን ያስተባበረው ኦብኮ (አሁን ኦህኮ ነው)  ሊቀመንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና በዚህ ጉዳይ ላይ ጦቢያ መጽሄት ጠይቋቸው (ቁጥር 12/1992) የሰጡት ምላሽ ከብዙ በጥቂቱ እንዲህ የሚል ነበር፡፡  “…በኢተፖድኀ አመራርና በዶ/ር በየነ መካከል፣ በዶ/ር በየነና በሌሎች የአማራጭ ኃይሎች መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በተከበረ ኢትዮጵያዊ የሽምግልና ባሕል እንዲፈታ ብዙ ጥረን ነበረ፡፡ በተለይ በምርጫ አካባቢ የተቀዋሚ ኃይሎች ኀብረት እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለነበር ዶ/ር በየነ እመራቸዋለሁ የሚሉዋቸውን ድርጅቶች  በሙሉ ጋብዘን ነበር፡፡ ኢህአዴግ በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች የለምንም ጥያቄ አቤት ብለው የሚሄዱት ዶ/ር በየነ እሳቸው የሚመሩት አማራጭ ኃይሎች በጋራ ስብሰባውን ካላዘጋጀ አልገኝም  ብለው የቅንጦት የሆነ የቴክኒክ ቅድመ ሁኔታ አቀረቡ፡፡ እሳቸው የሚመሩት አማራጭ ኃይሎች አዘጋጅ ከሆነ በዛ ያሉ ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ የማይገኙ ስለሆኑብንና አማራጭ ስላጣን ስብሰባውን ስንቀጥል ደግሞ ያለ እኔ እንዴት ተሰበሰቡ በማለት ሕዝባዊ ኃላፊነት ከሚሰማው ተቀዋሚ የማይጠበቅ መግለጫ አወጡ፡፡ የሚገርመው ደግሞ እሳቸው የሚመሩት አማራጭ ኃይሎች ጸሐፊ ከእኛ ጋር ተሰብስቦ እያለ ከማን ጋር እንደጻፉና ማኀተሙን ከየት እንዳመጡ ባናውቅም መግለጫቸው ስብሰባ ላይ እያለን ደረሰን፡፡ ዶ/ር በየነ ለደቡብና ለተቀሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ምን እንደሚፈልጉ አንድ ቀን እውነቷን እስኪነግሩን ድረስና ተቀዋሚው ኃይል ለእሳቸው ቁመት የሚሆን ኀብረት ፈጥሮ እሳቸው እስኪታረቁን ድረስ ዝርዝር ሁኔታ ውስጥ መግባት ባንፈልግም ዶ/ር በየነ ለማን የፖለቲካ ጠቀሜታና ለምን ተልእኮ ደጋግመው በእኛም ድርጅት ላይ ሆነ በሌሎች ተቀዋሚ ኃይሎች ላይ ድንጋይ እንደሚወረውሩ ግራ እንደገባን ከኢትዮጵያ ሕዝብ መሸሸግ አንፈልግም፡፡ ….የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ተቀዋሚ ኃይሎችን እየከፋፈለ ነው ለሚለው የዶ/ር በየነ በሬ ወለደ ተረት ሳንጨነቅና እላይ እናድስቀመጥነው ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ ነገ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተቃዋሚው ጎራ ማን የአምስተኛ ረድፍኛ ሚና እየተጫወተ እንዳለ በተግባር ሊታይ ስለሚችል ወደፊትም ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡”

የፕ/ር መረራ ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም አምሰተኛ ረድፈኛው ቢያንስ ለህዝብ በይፋ ባይታወቅም ይህ ከተባለ  ወዲህ ሁለቱ በኢዴኃህ ሊቀመንብረነት ወንበር ላይ ተፈራርቀዋል፤ መድረክንም እየተፈራረቁበት ነው፤ ምስጢሩ ምን ይሆን?

በኢትዮጵያ ውስጥ  አዲስ ፓርቲ ለመመስረትም ሆነ ህብረት ለመፍጠር እንቅስቅሴ ሲጀመር በውስጥ ለውስጥ መንገድ ከወያኔ ሰፈር የምትተላለፍ መልእክት አለች፡፡ እገሌን ሊቀመንበር ብታደርጉት ተግባብተን ልንሰራ እንችላልን የምትል፡፡ ወያኔን በቅጡ ለሚያውቅ ይህች ነገር በምክር ብቻ እንደማትቆም ይረዳል፡፡ የሚፈልጉት ሰው ሥልጣኑን እንዲይዝ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ተሳክቶላቸዋል ያልተሳካላቸውም አለ፡፡

ይህች ነገር አቶ አሰፋ በጽሁፋቸው ማጠቃለያ ላይ

“በየነ ጴጥሮስ እላይ በጨረፈታ ለማሳየት ለሞከርኩት ስራው መላውን አለም ደጋግሞ ዞሯልኮ! በዚህ 25 አመት ሙሉ የድርጅቶች መሪነቱ ምን ፈየደ? ምንስ ተናገረ? ምንስ ጻፈ ?የሚል ቢኖር ጉዱ ይፈላ ነበር። የሚል ሰው አለመኖሩ የበጀው መስለኝ። እንዳይኖሩ አድርጎ ይሆን?አሁን ግርማን ላከበት? አንዳንዴ ያኔ ከባንክ ገንዘብ ይዞ ጠፍቶ በኋላ የወያኔ አባል ሁኖ የገንዘብም ምክትል ሚንስቴር እንደሆነው ሰውዬ በየነ  ጴጥሮስም የወያኔ አባል ይሆን? እላለሁ  የኸው ለ25 አመት ያ ሁሉ ሰው ወህኒ ሲወርድ በየነ አለምን ይዞራል።” በማለት ከገለጹት ጋር ይዛመድ ይሆን! ረዥም እድሜ ከጤና ጋር ለአቶ አሰፋ ጫቦ ተመኘሁ፤ ከይር ያሰማን ፤ፍቅርና ሰላም ይስጠን

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s