ከማን አንሼ!!! – አገሬ አዲስ

 

በልጅነቴ እንደተረት የተነገረኝ ምሳሌ አሁን ካረጀሁም በዃላ በቁም ነገር ጨዋታ በሚመስል መልኩ ቀርቦ ለማዳመጥ በቅቻለሁ።ዕድሜ ደጉ!!
ተረቱ እንዲህ ነው።እንስሳት ጉባኤ ላይ ተቀምጠው ውይይት ሲያደርጉ የመናገር ቅድሚያ የሚሰጠው በአካሉ ጎልቶና ፈርጥሞ ለሚታየው አውሬ ወይም እንስሳ ነበር። የሌሎቹ ደቃቃና ቀጫጫ፣እንስሳት ድምጽ የመስጠቱ ዕድል እየተነፈጋቸው ሁል ጊዜ የትላልቆቹ አድማጭ፣ጭፍራና አድናቂ ብቻ ሆነው እንዲኖሩ ይገደዱ ነበር።ታዲያ በዚህ አይነቱ አለእኩልነትና የመብት ጥሰት የተበሳጨችው አንድ እንቁራሪት ከሌሎቹ መካከል በድፍረት ወጥታ “እንዴ ሁል ጊዜ የእኛ ድምጽ አይሰማም፣ለመናገርም መብት የለንም፣ቅድሚያ የሚሰጠው ሁል ጊዜ ለዝሁኑ ነው፤ ለምን እንደዚያ ይሆናል?ማን ከማንስ ያንሳል?” ብላ በምሬት ተናገረች።እሷን መሳይ እንስሳቶች የእንቁራሪትን ሃሳብ በመደገፍ አጉረመረሙ። ስብሰባውን ይመራ የነበረው አንበሳ ጥያቄና ተቃውሞው ወደ እራሱ እንደሚመጣ በማወቅ በመዳፉ መሬቱን ደበደበና ዝምታ እንሲፍን በማግሳት ሁሉንም ጸት እንዲሉ ካደረገ በዃላ “አዎ በእኛ በእንስሳቱ መካከል መከባበር የተገባ ነው።ትንሹ ለትልቁ አክብሮት መስጠት ይጠበቅበታል፤ታላቅነት ደግሞ የተፈጥሮ ስጦታ ነው።ታዲያ ከዚያ የተፈጥሮ ስጦታ ውጭ እራሱን ትልቅ የሚያደርግ እንስሳ አለ?”ብሎ ዓይኑን እያፈጠጠ ወደ እንቁራሪቷና ወደሌሎቹ ደጋፊዎቿ በመመልከት እንደተለመደው ካለምንም ተቃውሞ አሰራሩንና ባህሉን ተቀብለው እንዲያድሩ አስጠነቀቀ።እጄን አልሰጥም ያለችው እንቁራሪት “ማን ከማን ያንሳል?ማበጡንም ቢሆን እናውቅበታለን” አለችና ያለ የሌለ ሃይሏን ሰብስባና ትንፋሿን ውጣ ለመወጣጠር ስትሞክር አቅም ተሳናትና በተሰብሳቢው እንስሳት መካከል ፈንድታ ሞተች።

ይህ ነበር በልጅነቴ እንደሌሎቹ የዕድሜ አጋሮቼ ሲነገረኝ የነበረው ታሪክ።አቅምን ያለማወቅ ፣ከማን አንሼ ታሪክ።
ሰሞኑንም ይህን መሳይ ተረት በኢትዮጵያኑ የትግል ጎራ ውስጥ ከተሰለፉት መካከል የአንዱ ድርጅት አመራር አባል የሆነው ግለሰብ ነጻነት ለኢትዮጵያ በሚባለው ራዲዮ ስርጭት ቀርቦ የተናገረው የእንቁራሪቷን ታሪክ እንዳስታውሰው አደረገኝ።ለሙሉ ግንዛቤ ከዚህ በታች ያለውን የቪዲዮ የድምጽ ቅጅ በማዳመጥ መረዳት ይቻላል።
Neamin-Zeleke-1https፡//youtu.be/erPWBdb_U3Q
ይህንን ኢንተርቪው ከሰማሁ በዃላ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፣

በ2001 ዓ.ም.እ.አ.አ.አሜሪካ በአሸባሪዎች በተጠቃችበት ወቅት የአገሪቱ ፕሬዚደንት የነበረው ጆርጅ ቡሽ በቀል ለመመለስ ለጦርነት በሚዘጋጅበት ወቅት አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች መንግሥታት ስለተቃወሙት፣ እነሱን ከጥፋት ሃይሎች ጋር ለማዳበል “iether you are with us or with them” በማለት በጠባብ የምርጫ ሳጥን ውስጥ ለማስቀመጥ እንደሞከረ የሚያሳየው አባባሉ ነው።በዚያን ጊዜ ቡሽ ለሚያደርገው ጭፍን ጦርነትና ዕቅድ አለመተባበር ማለት ከሽብርተኞች ጋር መወገን ማለት ነበር።ሽብርተኞችንና የቡሽን አደገኛ መንገድ የሚቃወሙት ወገኖች በዚህ የጆርጅ ቡሽ አመለካከት የነጻ አቋምና አመለካከት መብታቸው የተገፈፈ ነበር።የፈሩት አልቀረም ይኸው የቡሽ መዘዝ አሁን ዓለማችን ካለችበት ከነበረው ለበለጠ ቀውስና አደጋ ውስጥ ተነክራ ትገኛለች።
ታዲያ የቡሽ ነገር ምን አነሳው ይባል ይሆናል።

ከላይ በቀረበው የራዲዮ ቃለምልልስ ላይ ነአምን ዘለቀ የተባለው የግንቦት ሰባት አመራር አባል ድርጅቱ በአስመራ ውስጥ ተቀምጦ በሻእብያ እየተመራና እየተረዳ የሚያካሂደውን ጦርነት በመደገፍ ሂደቱን የሚቃወሙትን እንደጆርጅ ቡሽ በማውገዝ ከኢትዮጵያ አንዱ ጠላት ከሆነው ከወያኔ ጋር ማስተሳሰሩ ተመሳሳይ ሆኖ አገኝቼዋለሁ። እውነት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ አንድነት፣ለዲሞክራሲ ስርዓት የሚታገል ከሆነ ትግሉን ከአምባገነኖች መዳፍ ውስጥ አላቆ፣በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍና ተሳትፎ ፣በኢትዮጵያ ምድር ያድርገው ብለው የሚነቅፉትን ፣በትግል ስልት የሚለዩትን የአንድነት ሃይሎች በማውገዝ፣ ጆርጅ ቡሽ ”እኛን ያልደገፈ የጠላት ተባባሪ ነው እንዳለው ሁሉ “የሻእቢያን መንግሥትና የግንቦት ሰባትን ስልት መቃወም ጸረ ወያኔ ትግላችንን መቃወም ነው፤” “ከእኛ ጋር ወይም ከወያኔ ጋር የመሆን ጥያቄ ነው” በማለት ትችት ሰንዝሯል። የተለየ ስልት በሚከተሉትና ነቀፋ ባቀረቡት ላይ እንደጆርጅ ቡሽ የነጻ አመለካከትንና ተቃውሞን የማፈንና የማስፈራራት መልእክቱን አሰምቷል።እሱም ጆርጅ ቡሽን ለመሆን የጆርጅ ቡሽን አባባልና ዘዴ መጠቀሙ፣የቋንቋውና የአነጋገሩ ቃና ተመሳሳይ ከመሆኑም በላይ፣የወሮ በላውን የመንግሥቱ ሃ/ማርያምን ድንፋታ አስታወሰኝ።የሌለውን አለኝ ፣ያልሰራውን ሰራሁ ማለቱ ደግሞ ፈንድታ በሞተችው እንቁራሪት መልክ እንዳየው አደረገኝ።
ይህ ማለት ግን አቶ ነአምንም ሆነ ሌላው የየትኛውም አይነት ድርጅት አባል የመሆንና የሚከተለውን ስልት አላከብርለትም ማለት አይደለም።ባልቀበለውም አከብርለታለሁ።የእኔ አነሳስ በሰለጠነ የፖለቲካ ውይይት የምንለያይበትን ነጥብና መስመር በገሃድ ቁልጭ አድርጎ በማስቀመጥ አንዱ ከሌላው የሚማርበትን ዘዴና ከስህተቱ የሚወጣበትን፣የጋራ ትግሉ ስኬታማ የሚሆንበትን መንገድ መፈለግና ማሳየት ነው።በምጠረጥረው ሁኔታ በግንቦት ሰባት መሪዎች ላይ ተመሳሳይ ችግር ቢፈጠር ወይም አደጋ ቢደርስ ያንገበግበኛል፣ያሳዝነኛል።ለትግሉም ድርብ ክስረት ይሆናል።ያ ሳይደርስ ቀደም ብሎ አደጋው ሊከሰት የሚችልበትን መጠቆም ግን ሊከበር የሚገባው የወዳጅና የወገን ምክር ነው።በጭፍን እየጋለቡና እያጨበጨቡ ሰቅሎ ማውረድ አልወድም።ባለፉትም የትግል ታሪካችን የተፈጸመውና አሁንም በመፈጸም ላይ ያለው የዚሁ ካለመሰላል ሰቅሎ ካለመሰላል ጎትቶ የማውረድ ባህል ነው።ያ ደግሞ መቀየር አለበት።ፖለቲካችን

ከስሜት፣ከደምፍላት፣ከወገንተኝነት፣ከውሸት መላቀቅ አለበት።አገር የጋራ እንደመሆኑ የሁሉም ድምጽና ፍላጎት ሊደመጥ ይገባል።በጠላትነት ተመድቦ እውነትን በሃሰት መቀየር የጥፋት ጥፋት ከመሆኑም በላይ የሚጠፉበትን ጎዳና መቀየስ ይሆናል።

በጣም ያስገረመኝ ደግሞ ቃለምልልሱን ያዘጋጀውና ያስተላለፈው አቶ ዓለም ፈቃደ ያንጸባረቀው አቋም ነው።ዓለምን ለብዙ ዓመታት ከአቶ ነአምን ዘለቀ ጋር ካለው እውቅና ዘመንና በላቀ የትግል ተሳትፎ የማውቀው ጓዴና አሁንም ጋጓደኛ ነው።በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን፣ጸረ ሻእቢያና ወያኔ አቋም የነበረው፣እራሱን ጥሎ ለትግል የቆመ መሆኑን እመሰክራለሁ፤የገረመኝ ነገር ግን በ2004 ዓ.ም.ኮሎኔል ታደሰ ፣የአርበኞች መሪ ዋሽንግተን በመጣ ጊዜ፣ዓለምና እኔ በተናጠል አግኝተነው የጠየቅነውና የተቃወምነው ነገር ቢኖር እንዴት ኢሳያስ አፈወርቂን አምነህ ኤርትራ ውስጥ ጸረ ወያኔ ትግል ታካሂዳለህ? ሻእቢያና ወያኔ እኮ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ናቸው።የአሁኑ በጥቅም ዙሪያ፣ኢትዮጵያን በመዝረፍ ዙሪያ የተከሰተው ጊዜያዊ ጠባቸው ለነገው ትብብራቸው እንቅፋት አይሆንም፤የኢትዮጵያ አንድነትና አገር ወዳድ ሃይሉ ሲጎለብትና ሲጠናከር ተባብረው ከማጥፋት አይመለሱም፤ሻእቢያ አንተንም ድርጅትህንም ያጠፋችዃል የሚል ነበር።ያልነው አልቀረም፣ኮለኔል ታደሰም የት እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም፣ ሻእብያ ደብዛውን አጠፋው።ድርጅቱም ኢትዮጵያዊነታቸውንና ኢትዮጵያን የሚያስቀድሙት ታጋይ አባላቱ ተገለውና ተገልለው ተሽመድምዷል። ታዲያ ዓለም በዛ ጊዜና እስከቅርብም ጊዜ ድረስ ይገፋ የነበረው አቋምና አመለካከት አሁን እንዴትና ለምን ተቀየረ?የፕሮፌሶር አስራት አክባሪና ደጋፊ የነበረው፣ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምነው፣ተገንጣይ ሃይሎችን ይቃወምና ይኮንን የነበረው ጓዴ በግንቦት ሰባቶች ላይ እንደ ኮሌኔል ታደሰ ለመተቸት ምን አንደበቱን ያዘው?ምን ነካውና ድፍረቱን አጣ?የአቋምና የአመለካከት ለውጥም ካደረገ ቢናገር ጥሩ ነበር፤ያንን ደግሞ አክብርለታለሁ እንዲከበርለትም ከጎኑ እቆማለሁ።በተገናኘን ቁጥር ግን በውይይት የማውቀው ጸረ ሻእቢያነቱንና ለኢትዮጵያ አንድነት መቆሙን ነው።

በግንቦት ሰባትም ላይ ያለኝ ልዩነት በስልት ደረጃ እንጂ ወያኔ በመወገዱ አስፈላጊነት በተነሳ ጥያቄ አይደለም። ልዩነቴ ወያኔን ለማሶገድ በተነደፈው የትግል ስልት ዙሪያ ነው።ስልቱን ባልቀበልና ብቃወመውም ድርጅታዊ መብቱን አከብራለሁ።እነሱ በሻብያ ድጋፍ ፣ተገንጣዮችን አስተባብረን ወያኔን እናሶግዳለን ባዮች ናቸው።በኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄና ከወያኔ በዃላ ስለሚመጣው የስርዓት ለውጥ ግልጽ የሆነ ትንታኔ አይሰጡም።ብቻ በማንም ይሁን በማንም፣ ከጸሃይ በታች ባለ ሃይል ባገኘነው እርዳታ ወያኔን መጣል ነው ከሚል ባሻገር ለአገሪቱና ለሕዝቡ ቋሚ ችግር መፍትሔ የሚሆን መልስ አያቀርቡም።ከማንኛውም ጋር እንተባበራለን ሲሉ ግን ለኢትዮጵያ አንድነት ፣ለሕግ የበላይነት፣ለዲሞክራሲ ስርዓት መስፈን…ወዘተ ከሚታገሉት ኢትዮጵያኖች ጋር ግን አይደለም።የእነሱን የበላይነት፣አመራር፣ስልት የማይቀበል አይፈልጉም፣እንደጠላት ወይም እንደ ወያኔ አጋርና ደጋፊ አድርገው ይቆጥሩታል። ለዚህም ተደጋግሞ ለቀረበላቸው ጥሪ የሰጡት መልስና ዝምታ ማስረጃ ነው።ዝርዝሩ ካስፈለገ ወደፊት ሊቀርብ ይችላል። ወያኔ ብቻ ይውደቅ፣ከሱ የከፋ አይመጣም የሚለው ቅኝት ደግሞ ከሃያ አምስት ዓመት በፊት ወያኔ ጸረ ደርግ ትግል ሲያካሂድ፣በአገሪቱ ላይ አሁን የምንቃወመውን ስርዓት እንደሚያሰፍን ሳንመለከትና ሳናገናዝብ ብቻ ደርግ ይውደቅ ከሚል ጥላቻ በመነሳት ከተወሰደውና አሁን ከሚቆጨን አቋም አይለይም።በወቅቱ ነገሮች ተስተካክለው፣ጎባጣው ቀንቶ ካልተራመድን የዃላዃላ ተቀምጠን የሰቀልነው ቆመን ለማውረድ እንደሚያዳግተን አሁን እያየነው ነው።ወደፊትም እንዳይደገም ትምህርት ልንቀስም ይገባል።

ለግንቦት ሰባትም ሆነ ሌሎቹ ለሚያካሂዱት ትግል የሚያዋጣው ዋሻና ደጀኑ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ መሬት ነው።በዓለም አቀፍ ደረጃ፣በከባቢ ደረጃና በአገር ውስጥ የወገንና የጠላት ሃይልን አሰላለፍ ያላመዛዘነና ያላወቀ፣ወይም ከጠላቶቹ በአንዱ በጊዜያዊ ጥቅም የተታለለ ታጋይ የታሰረበትን ሰንሰለት ተሸክሞ እንደሚጓዝ እስረኛ ያህል ነው።እንደልቡ ሊንቀሳቀስና ካሰበበት የድል ጣቢያ ሊደርስ አይችልም።
ከሚጎዳ እሰጥ አገባ፣ውሸትና ትእቢት ተላቀን በጋራ ያገራችንን ችግር ለመፍታት ቅን፣ደፋር፣ ግልጽና እውነተኞች ሆነን እንነሳ፣ቅድሚያ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት እንስጥ!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s