ጠቡ የሻእቢያ እና የሕወሃት እንጂ የሕዝብ አይደለም | ግርማ ካሳ

solders ethiopian
(በአዲስ ገጽ መጽሄት እትም 13 የተወሰደ)

ሰሞኑን በሰሜኑ የአገራችን ግዛት ጦርነት ተቀስቅሷል። አስመራም፣ አዲስ አበባም ያሉ ገዢዎች ጦርነት መደረጉን ማመን ብቻ ሳይሆን “ይሄን ደመሰስን፣ ይሄን ያህል ገደልን” እያሉ በመማጸደቅ ላይ ናቸው። አለም የትናየት ደርሳለች፣ ትላንናት እኛ እየረዳናቸው ነጻ የወጡ የአፍሪካ አገራት እንኳን የትናየት ደርሰዋል፣ እኛ አሁንም መግደልን እንደ ጀብዱ አድርገን እናወራለን።

አንዳንድ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ከሻእቢያ ጋር የሚደረግን ጦርነት ከአንድ የዉጭ አገር ወራሪ ጋር እንደሚደረግ ጦርነት አድርገው ነው የሚያዩት። በኔ እይታ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው። በሻእቢያ እና በኢሕአዴግ መካከል የሚደረገው ጦርነት ከኢትዮጵያ ህዝብ እና ከኤርትራ ህዝብ ጥቅም ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ጦርነቱ ፣ በዜጎች ደም የሰከሩ፣ የሁለት አምባገነን ቡድኖች ጦርነት ነው። የነርሱ ጣጣ ነው። ለጥቅማቸው፣ ለስልጣናቸው ሲሉ የሚያደርጉት።

ምንም እንኳን ላለፉት 25 አመታት ኤርትራ በፖለቲካ አስተዳደር፣ በሻእቢያ እና በሕወሃት ሴራ፣ ከኢትዮጵያ ብትለይም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኤርትራ ህዝብ ግን በመንፈስ የተለየ ህዝብ አይደለም። በታሪክ፣ በባህል፣ በስጋ፣ በሃይማኖት እርስ በርሱ የተሳሰረና የተዋለደ ወንድማማች ህዝብ ነው። እግዚአብሄር ፈቅዶና ህዝቡ በትግሉ በርትቶ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታት በአስመራና በአዲስ አበባ ቢመጡ እንደገና ተስማምቶ ሊዋሃድ የሚችል ህዝብ ነው።

ብዙዎቻችን ላለፉት 25 አመታት ከነበረው ፖለቲካ የተነሳ፣ ሻእቢያን ከህዝቡ መነጠል አቅቶን፣ ሻእቢያ ላይ ችግር ስላለብን፣ ኤርትራዉያን ላይ በጅምላ እንፈርዳለን። ይህ ሌላ ትልቅ ስህተት ነው። እስቲ ስለ ኤርትራ ህዝብ ትንሽ ላካፍላችሁ። የሰማሁትንና ያነበብኩትን ሳይሆን ያየሁትንና እና ያለፍኩበትን። የአስመራ ዮኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩኩኝ ጊዜ የማስታወሰዉን። (ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ሆና የመጨረሻዎቹ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ነበርን)

ኤርትራ፣ አስመራ ሲባል ብዙ ጊዜ ወደ አይምሯችን ከሚመጡት ነገሮች ጥቂቶቹ፣ ግፈኛው ሻእቢያ ሲሆን ሌላው ደግሞ ብዙ ጊዜ በፖስት ካርድ ላይ የምናየዉ፣ ዘንባባዎች በዳርና በዳር ያሉበት መንገድ በመሃከሉ የሚያልፈው፣ ፒያሳ ወይንም ኮምፖሽታቶ የሚባለዉን ሰፈር ነዉ። በዚያ መንገድ ብዙ ኬክ ቤቶችና ቡና ቤቶች ነበሩ። ትዝ ይለኛል በአምሳ ሳንቲም አንድ ኬክና ምን የመሰለ ካፑቺኖ እናዝ ነበር። በተለይም ሲመሽ ከመብራቶቿ ጋር ከተማዋ በጣም ታምር ነበር። (በነገራችን ላይ አሁን አስመራ ያኔ የነበራት ዉበት የላትም። የተንኮታኮተችና ያረጀች ከተማ ሆናለች። የቀድሞው የክፍለ ሃገር አወቃቀር ብንመለከት የትግራይ ክፍለ ሃገር ቢያንስ አራት ፣ ጎንደር ሁለት፣ ጎጃም ሁለት፣ ወሎ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች እያንዳንዳችው ሲኖራቸው፣ ኤርትራ የነበራት፣ እኛ የተማርንባት አንዱ ዩኒቨርሲቲ ተዘግቷል። ከከተማዉ ዉበት ባሻገር የማልረሳዉና በዉስጤ የተተከለ አንድ ሌላ ነገር ቢኖር የሕዝቡ ፈሪሃ እግዚአብሄርነትና ደግነት ነበር። እስቲ አንዳንድ ያጋጠሙኝን ላጫዉታቹህ።

አንድ ቀን በዮኒቨርሲቲ ዉስጥ ወዳለዉ ካፍቴሪያ እራቴን ለመብላት እየሄድክ ሳለ ጓደኞቼ አገኙኝና «አትሄድም እንዴ ? » አሉኝ። «የት ?» አልኳቸው። «ንግደት» አሉኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ያንን ቃል የሰማሁት። ጓደኞቼ ነገሩን ያውቁ ነበርና ምን እንደሆነ በኋላ አስረዱኝ። ያን ቀን በአስመራ በሰሜን ምዕራብ በኩል ቪላጆ የሚባል ሰፈር፣ የሚካኤል ይሁን የገብርዔል ቤተ ክርስቲያን አለ። (የቱ እንደሆነ አሁን አላስታወስም)። የዚያ ቤተ ክርስቲያን ታቦት የሚወጣበት ቀን ነበር። ታዲያ ቤተ ክርስቲያኗ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ታቦቱ በነገሰበት ቀን ግብዣ አድርገዉ በአካባባዉ ያሉትን ሁሉ ይጋብዙ ነበር። ይሄ ስርዓት ነዉ እንግዲህ ንግደት የሚባለዉ።

ያኔ መኪና የለንም። በእግራችን ከአንድ ሰላሳ ደቂቃ በኋላ በቪላጆ ደረሰን። አራት ተማሪዎች ነበርን። በሰፈሩ ስንሽከረከር «ኑ ግቡ» ብሎ የሚጠራን ሰዉ አጣን። ለካ ኑሮ በጣም ስለተወደደ እንደድሮ በየመንገዱ እየቆሙ «ብሉልን ጠጡልን» ማለት ቆሟል። «መቼም የዩኒቨርሲቲ ካፍቴሪያ ምግባችንን ትተን ባዶ ሆዳችንን አንመለስም» ብለን ወደ አንዱ ቤት አመራንና አንኳኳን። «እንኳን አደረሳቹህ ? » ስንል ፣ አንዲት ያኔ ወደ አርባ አመት የሚጠጋት እናት፣ በእጇ አንድ ሕጻን ልጅ ታቅፋ ወጣችና «ግቡ፣ ግቡ » አለችን በፈገግታ። የቤቱ በር ጠባብ ነበር። ጎንበስ ብለን ገባን። የነበረችዋን ጠረቤዛ ከበብናት። በትልቅ ትሪ እንጀራ ቀረበልን። ሴትየዋ ድስቱን አመጣችና ወጡን እንዳለ እንጀራዉ ላይ ደፋችዉ። ብዙ ጊዜም አልፈጀብንም ትሪዉን ጠረግነዉ። ከዚያም በትላልቅ ጣሳዎች ጠላ አመጣች። ለኔ ዉሃ ተሰጠኝ። ምን ልበላቹህ ምን የመሰለ መስተንግዶ ተደረገልን።

አሰመራን ሳስብ፣ የአስመራ ነዋሪዎችን ሳስብ፣ ያቺን ሴት አስባለሁ። ለእግዚአብሄር ፍቅር ስትል፣ እንግዳን በደስታ የምትቀበል ! ችግረኛ ናት፣ ነገር ግን ከፊቷ ውስጣዊ ሰላም ያላትና ሰዉን የምትወድ ትልቅ ሴት ነበረች!! ያኔ በትግሪኛ አልነበረም ያናገርናት። «የኔ ዘር ናቸዉ» ብላ አልነበረም ያስተናገደችን። ነገር ግን ትልቅ ሴት በመሆኗ እንጂ።

የማያልፍ ነገር የለምና የዪኒቨርሲቲ ትምህርታችንን አጠናቀን የምረቃችን ቀን ደረሰ። ባጽእ (ምጽዋ) በሕዝባዊ ሀርነት ኤርትራ ግንባር ሥር ከወደቀ በኋላ በምጽዋና በአስመራ መሃከል ከሚገኝ አንድ የከፍታ ቦታ፣ «ግራፒ» እንለዉ የነበረ ከሩቅ የሚተኮስ መድፍ በየጊዜው አስመራ ከተማ ላይ ያርፍ ነበር። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ መብረሩን አቁሞ ነበር። የጦር አይሮፕላን ግን ማረፉን አላቆመም። በወቅቱ ደግሞ ሕወሃት በትግራይ ጥቃቶች ያደረግ ስለነበረ ከአስመራ አዲስ አበባ ያለው መንገድ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ነበር። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለማይበርም ቤተሰቦቻችን ለምረቃችን ከአዲስ አበባ ሊመጡ አልቻሉም። ስለዚህ የምረቃ ስነ ሥርዓታችን ብዙ አልጓጓንለትም ነበር። የምረቃችን ስነስርዓት ቀን በወንዶች ሽንት ቤት ዉስጥ ትልቅ ፈንጂ ፈነዳ። ያን ሰዓት ትልቅ ድንጋጤ በዩኒቨርሲቲ ጊቢ ዉስጥ ለጥቂት ደቂቃዎች ተፈጠረ። ወዲያዉ ሻቢያ የደስታ መግለጫ መልዕክት ማስተላለፉ ነዉ ብለን ቀልደን አለፍን። ከሩቅ በሚተኮስ መድፍ በግራፒ ተምሮ በፈንጂ መመረቅ ይሉታል ይሄ ነዉ።

ያ ቀን ከፈንጂ ፍንዳታዉ ሌላ የማልረሳዉ፣ በጣም ልቤን የነካና ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ዘላቂ ፍቅር እንዲኖረኝ ያደረገ አስደናቂ ነገር ሆነ። ቤተሰቦቼ ከአዲስ አበባ ስላልመጡ የምረቃ ልብሴን አዉልቄ ወደ ዶርሚተሪ ለማምራት እየተዘጋጀሁ ሳለ ድንገት፣ አንዲት ሴትዮ አበባ ይዘዉ ብቅ አሉ። ትዬ ዘይዳ ነበሩ። ትንሽ እንደቆየዉ ደግሞ አንዲት አሮጊት ሴትዩ ሌላ እቅፍ አበባ ይዘዉ መጡ። አደይ ጸሃይቱ ነበሩ። ሁለቱም አይተዋወቁም። በአራት አመት የአስመራ ቆይታዬ የተወዳጀኋቸዉ እናቶች ናችዉ። ያኔ ብቻዬን የሆንኩኝ መስሎኝ ነበር። ግን ከአንድም ሁለት እናቶች እንደ እናቴ ሆነዉ አበባ ይዘዉ በምረቃዬ ተገኙ። እነዚህ ሁለት እናቶች ዶሮ አርደዉ ቤታቸዉ ድግስ አዘጋጅተዉ ነበር። ሁለቱም ወደ ቤታቸዉ እንድመጣ ፈለጉ። ግራ ገባኝ። በኋላ አንዳቸዉ ጋር ምሳ ሰዓት ፤ ሌላኛዋ ጋር ደግሞ ሲመሽ ለእራት ሂጄ ከጓደኞቼ ጋር የተዘጋጀልኝን ድግስ ተካፈልኩ።

አስመራን ሳስብ፣ የአስመራን ሕዝብ ሳስብ ትዬ ዘይዳና አደይ ጸሃይቱን አስባለሁ። እነዚህ እናቶች በስጋ እናቶቼ አይደሉም። እንደነርሱ ትግሬ አይደለሁም። እንደነርሱ የኤርትራ ተወላጅ አይደለሁም። ነገር ግን የእነዚህን እናቶች የዋህነት፣ ፍቅርና ያላቸዉን ፈሪሃ እግዚአብሄር የሞላባቸው ትልቅ ሴቶች ናቸው። ደጎችና ለዘር ቦታ የማይሰጡ። እግዚአብሄር ባሉበት ቦታ ይባርካቸው።

የመጨረሻ አመት ተማሪ እያለን በአንድ ሃይ ስኩል፣ ለሶስት ወር ማስተማር ነበረብን። ባርካ ተብሎ በሚታወቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደብኩኝ። የተመደብኩበት ክፍል አስተማሪ ክፍሉ በጣም ረባሽ ክፍል እንደሆነ አስጠነቀቀኝ። በጣም ፈራሁ። ነገር ግን ማስተማሩን ስጀምር አስተማሪው ከነገረኝ የተቃረነ ሁኔታ ነዉ ያየሁት። ተማሪዎቹ በጣም የሚያዳምጡ፣ በአክብሮት ከታያዙ ብዙ ሊሰሩ የሚችሉ ሆነዉ ነበር ያገኘኋቸዉ። አስተማሪያቸዉም ብሆን ጓደኞቼም ሆነዉ ነበር የተለያየነዉ። ያኔ ከተማዋ ችግር ላይ ነበረች። እንደዚያም ሆኖ ግን ከፊታቸዉ፣ ከሁኔታቸዉ ያየሁት ፍቅርንና ደስታን ነበር።

አሰመራን ሳስበ፣ የአስመራን ሕዝብ ሳስብ፣ ያኔ ወርቃማ ዩኒፎርም ለብሰዉ የማስተምራቸዉን፣ ያዳምጡኝና ሳስረዳቸዉ ፊቴን ያዩ የነበሩትን የባርካ ተማሪዎችን አስታወሳለሁ። እርግጥ ነዉ ብዙ የሚያሳዝኑ ነገሮች በአስመራ አይቻለሁ። እርግጥ ነዉ ከተማዋ ያኔ መለስተኛ ጦር ግንባር ነበረች። እርግጥ ነዉ በየጊዜዉ ሳይታሰብ በሻቢያ የሚተኮስ መድፍ ባልተጠበቀ ቦታ ያርፍ ስለነበረ ብዙ ሰዎች አልቀዋል። እርግጥ ነዉ በደርግ ወታደሮች የተሰሩ ብዙ ግፎች ነበሩ። ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ፣ የሕዝቡ ፍቅር አሸንፎኝ ነዉ የጦር መሳሪያ በተሸከመ የጦር አይሮፕላን፣ መሳሪያ ላይ ተቀምጬ ከተማዋን የለቀኩት።

አሁንም ለአስመራ ትልቅ ፍቅር አለኝ። አሁንም አሰመራን ከአዲስ አበባ ቀጥሎ እንደከተማዬ ነዉ የማያት። አሁንም ያንን ሕዝብ እንደ ሕዝቤ ነዉ የማየዉ። አሁንም ኤርትራዉያንን ከተቀረዉ ኢትዮጵያዊ እንደተለዩ ተደርጎ ሲታይ አያስደስተኝም። በዚህም ምክንያት ነዉ የኤርትራን መገንጠል አጥብቄ የተቃወምኩት። አሁንም የምቃወመዉ። ለዚህም ነዉ ከመረብ ደቡብ ይኖሩ የነበሩ ወደ ኤርትራ ፣ ከመረብ ሰሜን ይኖሩ የነበሩ ደግሞ ከኤርትራ በግፍ እንዲባረሩ መደረጉ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነዉ የምለዉ። ለዚህ ነዉ የባድመ ጦርነት የወንድማማቾች የርስ በርስ ጦርነት እንጂ ከዉጭ ኃይላት ጋር የሚደረግ ጦርነት አይደለም የምለዉ።

የኢትዮጵያ ህዝብ መንቃት አለበት። የኢሕአዴግ መንግስት በባድመ ጦርነት እንዳደረገው አሁንም ኢትዮጵያዉያንን ለመገበር እየተዘጋጀ ያለ ይመስላል። በኦሮሚያ፣ በጎንደር በመሳሰሉት ቦታዎች እንዳየነው፣ ህዝባችን በኢሕአዴግ ታጣቂዎች የሚታረደዉና የሚገደለው አንሶ፣ እንደገና ከሻእቢያ ጋር በሚደረግ ጦርነት የሚማገድበት ምንም ምክንያት የለም። በመሆኑም ለኢሕአዴግ የጦርነት ጡሩምባ ጆሮዉን ይደፍን ዘንድ እመክራለሁ። ሕወሃት/ኢሕአዴግ ለአገርና ለሕዝብ አስባለሁ፣ ለአገርና ለሕዝብ ደህንነት እቆማለሁ የሚል ከሆነ፣ አገር ማለት መሬቱ ሳይሆን ህዝቡ ነውና ህዝብን መጀመሪያ ያክብር።

በሌላ በኩል ለዴሞክራሲ ቆመናል እያሉ፣ አለም በወንጀለኛነት የሚፈለገው የአረመኔው የኢሳያስ አፈወርቂን አገዛዝ መደገፍና እድሜዉንም ለማራዘም ደፋ ቀና ለሚሉ ተቃዋሚ ነን ባይዮችም ፣ መልእክት አለኝ። የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን የሚቃወም፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚነቀፍና በሻእቢያ የተዘጋጀ ፔቲሽኖችን ኢትዮጵያዉያን እንዲፈርሙ እንዳንድ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ ደርጅቶች የቅስቀሳ ዘመቻ መጀመራቸው በጣም የሚያሳፍር ነው። የሻእቢያ መንፈስ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ህዝብ ጠላት ነው። የሻእቢያ መንፈስ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው። የሰብዓዊነት ጠላት ነው። ከሻእቢያ ጎን በቆምን ቁጥር በሻእቢያ እጅ ለሚፈሱ ደሞች ሁሉ ተጠያቂ ነው የምንሆነው። በመሆኑም ከሻእቢያ ጋር የምናደረገውን ዳንኪራ በአስቸኳይ ማቆም አለብን።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s