የ2008 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ አገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና መሰረቁ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችና ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት እየተተቸና በሕብረተሰቡ ዘንድም ዋና አነጋገሪ ጉዳይ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ተማሪዎች ገንዘባችውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ሰውተው ለፈተናው ተዘጋጀተው በመጠባበቅ ላይ እያሉ የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የፈተና ጥያቄዎችና መልሶቻቸው ፈተናው ከሚሰጥበት ከግንቦት 22 ቀን 2008ዓ.ም በፊት ባሉት ቀናት በፌስ ቡክ ላይ ተለቆ ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል። ፈተናው መሰረቁና መልሶቹም በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተማሪዎች የጧቱን ፈተና በመፈተን ላይ እያሉ የወያኔ የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው አልተሰረቀም በማለት መግለጫ ሰጠ። መግለጫውን በሰጠበት የሰዓታት ልዩነት ውስጥ ፈተናው መሰረቁን አምኖ ፈተናውን ሰረዘ።
ወያኔና ቅጥፈት የማይለያዩ ሰውና ጥላ ናቸው፤ በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ይሏል ይኼ ነው። የፈተናው መሰረቅና መሰረዝ በተማሪዎች ፣ በመምህራን፣ በወላጆችና በአጠቃላይ በሕዝብ ላይ የፈጠረው ድንጋጤ፣ በአገርና በሕዝብ ሀብት ላይ ( 202 ሚሊዮን ብር በላይ)ያዳረሰው ኪሳራና የሞራል ስብራት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በተለይም ስንቅ ይዘው፣ ቤት ተከራይተውና ከሩቅ ቦታ መጥተው ትምህርታቸውን ሲማሩ በነበሩ ተማሪዎች ላይ የደረሰባቸው ኪሳራና የሚደርስባቸው ተጨማሪ ወጪ ፣ ፈተናው በድጋሚ ላለመሰረቁ ዋስትና አለመኖር፣ ተማሪዎችንና አስተማሪዎችን ጭንቀት ላይ ስለጣላቸው በሌላ ጊዜ የሚሰጠውን ፈተና በሙሉ እምነት ተረጋግተው ይሠራሉ ተብሎ አይገመትም።ይህን ጭንቀት ወላጆችም የሚጋሩት ነው የሚሆነው።