በሕግ አምላክ 5 ሳይባል 6 አይባልም!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

 

 

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ይሄንን ጽሑፍ ዕንቁ መጽሔት ላይ የጻፍኩት ከሦስት ዓመታት በፊት እየተኪያሔደ የነበረው የእርቅ ሒደቱ በወያኔ እንዲቋረጥ ተደርጎ በሙቱ አባ ጳውሎስ እግር አባማትያስን ለማስቀመጥ ሽር ጉድ ይባል በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ሰሞኑን እንደ አዲስ ጉዳዩ “ሲኖዶስ ይሰደዳል? የለም አይሰደድም!” በሚል በመነሣቱ ነው ያቀረብኩላቹህ መልካም ንባብ፡-

“የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል” እንዲሉ የ4ኪሎዎቹ ግራ ክንፍ አባቶች ቡድን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበረ ፕትርክናቸው እንደማይመልሱ ይፋ አደረጉ፡፡ ምክንያቱም አሉና “ከ20 ዓመታት በፊት በሕመም ምክንያት ሥራውን መሥራት አልችልም በሚል ደብዳቤ አስገብተው ትተውት ስለሄዱ በቦታቸው ሌላ ፓትርያርክ ተክተን ቆይተናል አሁን ለ20ዓመታት ምንም እንዳልተሠራ ቆጥረን ወደኋላ መመለስ አንችልም” በማለት የሚያውቁትን እውነት ሳይሆን የሚኖሩትን እብለት በይፋ ተናገሩ፡፡ ለዚህ ለዚህማ ታዲያ ድርድሩና እርቁስ ለምን አስፈለገ? ሰዎቹ በመግለጫቸው ብፁዕነታቸው ልሂድ ሲሉ አሉ “ቅዱስ አባታችን ለማን ትተውን ይሄዳሉ? ማንስ ይሰበስበናል?” ብለን ለምነናቸው ነበር፡፡ ከሔዱም በኋላ ለ10 ወራት ያህል ጠብቀን ሕመማቸውም ተሽሏቸው ከሆነ እንዲመለሱልን ጠይቀናቸው ነበር ብለዋል፡፡ ታዲያ መሄዳቸው ይህንን ያህል ያስጨነቃቸው ያስከፋቸውም ከሆነና እንዳሉትም መመለሳቸውን የሚፈልጉና የሚናፍቁ ከሆነ ምነዋ ታዲያ አሁን ልመለስ ሲሉ ምንሲደረግ! ዘራፍ! ማለታቸው? በቀል መሆኑ ነው ወይስ ውሸት?

እውነቱን ግን ማለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ማን እንዴት አድርጎ እንዲሰደዱ እንዳደረጋቸው አይደለም እነሱ ሕዝበ ክርስቲያኑም በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሚገባ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም እያወቁ ለአፍታ እንኳን እግዚአብሔርን ባለማሰብ፣ ባለመፍራትና ባለማፈር ማበላቸው ለገዛ ራሳቸው ያላቸውንና የሚሰጡትን ዝቅተኛና እርካሽ ዋጋ ሊያሳይ ቢችል እንጂ ሌላ የሚፈጥርላቸው እርባና እንደሌለ ኅሊናቸው ያውቀዋል፡፡

እንበልና ያሉት እንኳ ልክ ቢሆን ማለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ “በሕመም ምክንያት ሥራዬን መሥራት አልችልም” ቢሉ ኖሮም እንኳ እርሳቸው ስለታመሙ ሥራው ግን መሠራት ይኖርበታልና ፕትርክናቸው ሳይነካ ምክንያቱም እንደ ቀኖና ቤተክርስቲያን በሕይወት እያሉ ሊነካ አይችልምና እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራ ምስለኔ ወይም እንደራሴ ተሠይሞ ሥራው እንዲሠራ ይደረጋል እንጂ የትኛው ሕገቤተክርስቲያን ነው ፓትርያርክ ከታመመ፣ ካረጀ፣ ከተሰደደ ወዘተ. በቦታው በመንበሩ ሌላ ፓትርያርክ ይሾማል የሚለው?

አሁንም የ4 ኪሎዎቹ የግራ ክንፍ ቡድን አባቶች እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያፈቅሩ፣ እውነትን የሚናገሩ፣ ስለ ሃይማኖት የሚኖሩ፣ ምእመናንን የሚያከብሩ ከሆነ ይህንን ጥያቄ በትክክል ያስኬደናል የሚሉትን ሕገ ቤተክርስቲያን በመጥቀስ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን በይፋ ሊመልሱልን ይገባል፡፡ እንዲሁ ዝም ተብሎ በድፍኑ “ቀኖና ቤተክርስቲያን” የምትል ቃል በመጥቀስ በሌለ ቀኖና ተሸሽጎ ወይም አምታቶ ማምለጥ አይቻልም፡፡ ስለተሰቀለው መድኃኔዓለም ክርስቶስ ብላችሁ መልሱልን፡፡ ይህንን ጥያቄ ሳትመልሱ የምታደርጉት ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሕጋዊነት የለውም ክሕደት ነው፣ እብለት ነው የእግዚአብሔርን ጥሪ እንዳልሰማችሁት ረግጣችሁ እንዳለፋችሁት ቁጠሩት፡፡ ምክንያቱም እሱ በየዕለቱ ሊደረግ ሊፈጸም የሚገባውን ነገር ሁሉ በቤተክርስቲያኗ የሕግ የሥርዓት የቀኖና መጻሕፍት እየተናገራቹህ እየገሠጻቹህ እየመሰከረባቹህ ነውና፡፡

እውነት እንነጋገር ከተባለ እንደ ቤተክርስቲያኗ ሕግና ሥርዓት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን 5ኛ ፓትርያርክ ነበራትን? 5 ሳይባልስ 6 ሊባል ይቻላልን? ቢባል ካላበልን ካልቀጠፍን ካልተዳፈርን በስተቀር እውነቱን ከተናገርን በርግጠኝነት 5ኛፓትርያርክ እንዳልነበራትና 5 ሳይኖርም 6ኛ ብሎ መሾም እንደማይቻል እንናገራለን እንመሰክራለን፡፡ አባ ጳውሎስ እንደሚታሙት ሁሉ “ፓትርያርክ ለመሆን የሚያበቃቸውን መስፈርት ጨርሶ አያሟሉም” የሚለውን እንኳ ለፈጣሪ ትተን አባ ጳውሎስ 5ኛ ፓትርያርክ እንዳልነበሩ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ምክንያቱም የቤተክርስቲያኗ ሕግ (እግዚአብሔር) ቁልጭ አድርጎ በማያሻማ መልኩ መልሶታልና፡፡ በቀኖና ቤተክርስቲያን ላይ በግልጽ ከተቀመጡት ምክንያቶች በስተቀር ፓትርያርክ ሳይሞት በሕይወት እያለ በምንም ተአምር ፓትርያርክ ሊሾም እንደማይቻል ተናግሯልና፡፡ በመሆኑም ከዚህ ሕግ ውጪ በሆነ መንገድ የሆነ ቡድን ሾምን ቢሉ ያ ሹመት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም ድርጊቱም አመፃ ነው ያስኮንናል፡፡ በመሆኑም በግልጽ አማርኛ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን 5ኛ ፓትርያርክ አልነበራትም 6ኛም አይኖራትም ማለት ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ እንደ ቤተክርስቲያኗ ሕግና ሥርዓት ቤተክርስቲያን የምታውቀውና እየተገለገለችም ያለችው በ4ኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ነው፡፡ 5ኛ 6ኛ 7ኛ እያለ ሊቀጥል የሚችለው ልዑል እግዚአብሔር ብፁዕነታቸውን በሞት ከወሰደ በኋላ ብቻና ብቻ ነው፡፡

ታዲያ እውነቱ እንዲህ ከሆነ ይህንንም ፓትርያርክ ሾምን የሚሉቱ የ4ኪሎዎቹ የግራ ክንፍ ቡድን አባቶች የሚያውቁት ከሆነ ይሄንን ሁሉ ትርምስ ምን አመጣው? ከተባለ መልሱ ቀላልና ግልጽ ነው፡፡ የ4ኪሎዎቹ የግራ ክንፍ አባቶች ቡድን የሠሩትና ሊሠሩት ያሰቡት ነገር እግዚአብሔርን እንደሚያስቆጣና እንደሚያስቀይም ቢያውቁም፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ከንቱና ፋይዳ ቢስ መሆኑን ቢያውቁም፣ ያሳሰባቸውና እንዲሠራ የፈለጉት ሥራ ምድራዊው እንጂ ሰማያዊው ባለመሆኑ፣ የሌላውን እንጂ የቤተክርስቲያኗን ባለመሆኑ፣ የግለሰቦች እንጂ የእግዚአብሔር ባለመሆኑ እነሱን በምቾት እስካኖረ ጊዜ ድረስ የሠሩት ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለመኖሩና ፈጣሪን ማስቀየሙ አላሳሰባቸውም አላስጨነቃቸውም አያስጨንቃቸውምም፡፡ ለቤተክርስቲያን የማሰብ ዓይነት ሰብእና ለመያዝ ማመንና መንፈሳዊነትን ይጠይቃልና፡፡

ምንም እንኳ እናምነዋለን የሚሉት ቅዱስ መጽሐፍ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” ቢልባቸውም ቅሉ የሐ. ሥራ 5÷29 ቅዱስ ቃሉ “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ ይልቁንም ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” ቢልባቸውም ማቴ. 10÷28 ሰዎቹ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን በመፍራታቸው፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰው በመታዘዛቸው፣ እንደራሴነታቸው ለእግዚአብሔር መሆኑን ረስተው ወይም አሽቀንጥረው ለምድራዊያን በማድረጋቸው ይህ ችግር ሊፈጠር ቻለ፡፡

የ4 ኪሎዎቹ የግራ ክንፍ አባቶች ቡድን ምን ነበር ያሉት? “5 ብለን 6 እንላለን እንጅ እንደገና ተመልሰን 4 አንልም ለታሪክ አዘጋገብ አይመችም” አሉ፡፡ «ብፁዓን» አባቶች ሆይ! አሁንም እባካቹህ ስለ ወላዲተ አምላክ ብላቹህ ትመልሱልን ዘንድ እንማፀናለን፡፡ ይበላሻል የተባለው ታሪክ የትኛው ታሪክ ነው? የትኛውስ ቀኖና ነው የሚጣሰው? ከማንም በላይ በዚህ 20 ዓመታት ውስጥ በዚህች ቤተክርስቲያን ምን እንደተሠራ ልቡናቹህ ያውቀዋል ምስክሮችም ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ በሚገርም ሁኔታ ተለውጠው የግራ ክንፍ አባቶች ቡድን በመሆን ተሰልፈው መግለጫ ሰጪ ሁሉ የሆኑ ቢኖሩም ከመሀከላቹህ ቀደም ሲል ግን በአባ ጳውሎስ ላይ በቤተክርስቲያኗ ግፍ አበዙ፣ የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ተቆነጻጸለ ተፋለሰ ወዘተ በማለት በተለያየ ጊዜ ከባድና ጠንካራ አመፅ ቀመስ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ይሄ እንደምን ተዘነጋቸው? ሥራ የተባለው ምኑ ነው? ተደርጎ በማያውቅ አረማዊ ድፍረት የእግዚአብሔር መንፈስቅዱስ ቦታ በሰው መወረሱ? የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ከዶግማ እስከ ቀኖና መፍረሱ መጣሱ? የአስተዳደር መዋቅሯ በየጊዜው ለድርጅታዊ አሠራር ሲባል ያለ አግባብ እና ያለ ሥርዓት መናጥ መቃወሱ? ሀብት ንብረቷ ያለ ማሠለስ ያለ ሃይ ባይ መዘረፍ መከስከሱ? ዘረኝነት መንገሡ? የምዕመናን ኅብረትና አንድነት ሆኖ በማያውቅ ደረጃ መፈረካከሱ? የምእመናን ቁጥር በተኩላት እየተበላ መቀለሱ? ይሄነው ሥራ የተባለው? ታሪክ የተባለውስ የትኛው ታሪክ ነው? እርግጥ ነው ታሪክ ሲባል መልካም መልካሙ ብቻ አይደለም መጥፎ መጥፎውም እንደ መጥፎነቱ የታሪክ አካል መሆኑ አይቀርም፡፡ ነገር ግን መጥፎውን ታሪክ ያመለጠ ካልሆነና አሁንም የማረም የማስተካከል ዕድሉ ካለ ያለፈውን ምዕራፉን በማስተማሪያነት ይዞ ያላመለጠውንና ያላለፈውን የመጥፎን ታሪክ አካል ያርሙታል ያቀኑታል ያስተካክሉታል እንጂ ሊገልጹት በሚያሳፍር ምክንያት ዳግም እንደገና በመሳሳት በጥፋት ላይ ጥፋት በመጨመር በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ላይ መጫወት መቀለድ ይገባል?

ታሪክ ይበላሻል ቀኖና ይጣሳል አላቹህ? ታሪክንና ቀኖናንማ ምሳቹህ ቀበራችሁት እኮ! በዚህ አጋጣሚ ዳግመኛ ስሕተት በቤተክርስቲያን ላይ አንፈጽምም በማለት ተቃውሞ ላሰማችሁትና ላልተስማማቹህት ብፁዓን አባቶች በግል አድናቆቴና ምስጋናዬ? ይድረሳቹህ፡፡ ነገር ግን ሥራቹህ ገና ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም ያበርታቹህ፡፡ ተቃውሟቹህ በስማቹህ ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ ስም የወጣውን መግለጫና የታቀደውን ስሑት የጥፋት ሥራ ሕጋዊ እንዳልሆነና ሊተገበር እንዳይችል በመታገል ለሕዝበ ክርስቲያኑ እስከ ማስተጋባትና ካስፈለገም መከራ እስከመቀበል ድረስ ካልዘለቀ ተቃውሟችሁ የይስሙላ ይሆናል፡፡ ቤተክርስቲያንንም ለተኩላት አሳልፋችሁ እንደሰጣቹሃት ቁጠሩት፡፡ በዝምታ ራስን ማግለልም ከተባባሪነት ተለይቶ የሚታይ አይደለም ቤተክርስቲያንን ከአደጋ በጎችንም ከተኩላ ለመታደግ የሚያበቃ ሥራ አይደለም ዝምታቹህ ለአጥፊዎች እንጅ ለቤተክርስቲያን አይጠቅምም፡፡ በእግዚአብሔርም ዘንድ ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ ነገር ግን በተቃውሟቹህ ብትቀጥሉ እኛ ምእመናን ከጎናቹህ ነን የቤተክርስቲያን በዚህ ደረጃ መቀለጃና መጫወቻ መሆን አስቆጥቶናል፡፡

ተቃውሟችንን ማሰማት እንፈልጋለን ቤተክርስቲያናችንን ለማንም ከሀዲ ጥቅመኛና ምንደኛ መረካረኪያ አሳልፈን በመስጠት ባለዕዳ መሆን አንፈልግም፡፡ ተቃውሟችንን እንድትመሩልን እንፈልጋለን ይህንን ስታደርጉ ብቻ ነው ተጋድሏቹህ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ሊያሰጣቹህ የሚችለው ታማኝ እረኝነታቹህ የሚረጋገጠው አባትነታቹህ የሚታወቀው፡፡ ቤተክርስቲያን እስከዚህ ዘመን ድረስ መቆየት የቻለችውና ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተምህሮዋን ጠብቃ ለመሸጋገር የበቃችው የአላዊያን ነገሥታትንና የመናፍቃን ጳጳሳትን የጥፋትና የክሕደት ሥራ አባቶችና ምእመናን በመቃወማቸው፣ አይሆንም አይቻልም በማለታቸውና እነዚያን የጥፋት አካላትንም ከቤተክርስቲያናችን በማራቃቸው በማስወገዳቸው ሰማዕትነት እስከመቀበል ድረስ በመጽናታቸው ነው፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ ግዴታ እና ኃላፊነት በሁሉም ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ በስሙ ከተጠመቅንበትና ልጅነትን ካገኘንበት ቀን ጀምሮ የተጫነብን አምላካዊ አደራ እና ግዴታ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይህንን አምላካዊ አደራና ግዴታ መወጣት እንፈልጋለን ምሩን አሰማሩን፡፡

ሲኖዶስ ማለት በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ፣ የመንፈስቅዱስን ፈቃድ የሚፈጽሙ፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ጥቅም የሚያስቀድሙ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ ማለት እንጂ የመንፈስቅዱስን ፈቃድ የሚፃረሩ፣ ለቤተክርስቲያን መከራ የሚደግሱ፣ ሕግጋቷን የሚያፈርሱ የሚጥሱ ሰሐትያን ምንደኞች ሊቃነ ጳጳሳት ዱለታ ማለት አይደለም፡፡ ይሄ የድፍረት ድፍረት ነው፡፡ ሲኖዶስን ሲኖዶስ የሚያደርገው ስሙ ሳይሆን ግብሩ ነው፡፡ ሰዎቹ በመግለጫቸው “መንበረ ፓትርያርክና ቅዱስ ሲኖዶስ አይሰደዱም ይህ በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅ” በማለት የተሰደዱ የቤተክርስቲያን አባቶችን ጠቅሰው መንበሩና ሲኖዶሱ ግን እንዳልተሰደዱ ነባራዊ ሁኔታዎችን ባላገናዘበ መልኩ ምሳሌ ጠቅሰው ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ እንደዛ ከሆነማ መንበረ ማርቆስ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ማለት ነዋ? ምክንያቱም እንደነሱ አባባል የቅዱስ ማርቆስ መንበር ያለው እስክንድርያ (ግብጽ) በመሆኑ ከእስክንድርያ መውጣት ስለማይችል፡፡ ግብጾችም እንዲህ እያሉ “እኛስ እራሳችን ለዚህ ሥልጣን እንዴት የተገባን ሆን?” ሳይሉ፣ በከንቱ ያገኛችሁትን በከንቱ ስጡ የሚለውን አምላካዊ ቃል እረስተው፣ ኢትዮጵያዊያኑ እግዚአብሔርን በማምለክ ይቀድሙናል እኮ! ሳይሉ፣ ሥልጣነ ክህነትን ሲከለክሉ ለወንጌል ወይም ለክርስትና መስፋፋት እንቅፋት እየሆኑ እንደሆነ ሳይረዱ ለ1600 ዓመታት ያህል እነሱ ከሌላ ያገኙትን ጵጵስናንም ፕትርክናንም ከልክለውን ቆይተው ነበር፡፡ ድርዲቱም ጸረ ክርስትና ነው፡፡

በዚህ ዓይነት አሠራርማ ቢሆን ኖሮ ክርስትና ከኢየሩሳሌም ባልወጣም ነበር፡፡ ወንጌልም በመላው ዓለም ባልተስፋፋ ወይም እንዲስፋፋ ባልተፈልገም ነበር፡፡ ክርስትና የርሥትና የጉልት ወይም የዘር ጉዳይ አይደለም ያመነ ሁሉ የሚዋጅበት ክርስቶሳዊ ሕይወት እንጅ፡፡ ሲኖዶስ ማለት ቅድስት ቤተክርስቲያንን የሚመሩ ብቁ ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ ማለት ከሆነና ከመሬት ጋር የተጣበቀ ግዑዝ ነገር ማለት ካልሆነ እንዴት ሆኖ ነው ታዲያ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተሰደው ካሉበት የሚያደርጉት የቤተክርስቲያን ጉባኤ ሲኖዶስ ሊባል(ሊሆን) የማይችለው?

የቤተክርስቲያን ሦስቱ ዐበይት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች ማለትም ጉባኤ ኒቅያ፣ ጉባኤ ቁስጥንጥንያ፣ ጉባኤ ኤፌሶን (በኒቅያ፣ በቁስጥንጥንያ፣ በኤፌሶን የተደረጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች) ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም እስክንድርያ የተደረጉ ይመስላቸዋልን?፡፡ ጥያቄው እሱ አይደለም ጥያቄው እንደቃሉ ሁሉ በሰው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ ተጠያቂነቱ ለሰው ሳይሆን ለመንፈስ ቅዱስ የሆነው፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ዶግማ ቀኖናና ሥርዓት የሚጠብቀው ወይም እየጠበቀ ያለው የብቁአን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ የትኛው ነው? የሚለው ነው እንጂ ቦታ አይደለም፡፡ ይህ ነጥብ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የትኛው ነው የውጭው ነው ወይስ የሀገር ቤቱ የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ይመልሳል፡፡

ከሰዎቹ መግለጫ ላይ ሌላው ያስገረመኝ ነገር ስደተኞቹን አባቶች በድርድሩ ወቅት “ከቤተክርስቲያን ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ጉዳዮች በማንሣታቸው” ያሉት ነገር ነው፡፡ ጉዳዩን በግልጽ ቢናገሩት ምንኛ በተመቸ ነበር ይሁንና በሌሎች መድረኮችም ይህ “ተያያዥነት ይሌለው” ያሉትን ጉዳይ ምንነት ገልጸውታል፡፡ ስደተኞቹን አባቶች “ፖለቲከኞች ናቸው” ብለዋቸዋል፡፡ አሁንም ግን  ጉዳዩን ፖለቲካ ነው አሉ እንጅ ዝርዝር ጉዳዩን መናገር አልፈለጉም፡፡ ይሁንና እነኛ አባቶች የሀገርና የሕዝብ ጉዳይ በማንሣታቸው ከሆነ ፖለቲከኛ ያሏቸው እነሱን ብቻ ሳይሆን ከስንክሳር እስከ ገድላገድላት ያሉትንም እንደነ አቡነ ተክለሃይማኖት ያሉ ቅዱሳን አባቶቻችንንም እየዘለፉ ነው፡፡ “ድሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” ብሎ ማለት ከሐዋርያዊ ተልእኮ ውስጥ ዋነኛው ሥራ ነው፡፡ ሐዋርያት ያሁሉ መከራ የደረሰባቸው ምን ስላደረጉ ይመስላቸዋል? ክርስቶስን (ወንጌልን) መስበክ ማለት  እውነትን ፍትሕን መስበክ ስለ እነሱም መጋደል ማለት እንደሆነ አያውቁምን?  እነ ዮሐንስ አፈወርቅ መከራ የተቀበሉት ምን ስላደረጉ ይመስላቸዋል? ስለ እውነት ስለ ፍትሕ መጋፈጥ መከራ መቀበል ሐዋርያዊ ግዴታ ነው፡፡

አብሶ ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለዚህች ሀገር ባለአደራ ናትና ለዚህች ሀገር ህልውናና ነፃነት ታቦት ተሸክማ ለጦርነት እስከ መሰለፍና የማይተካ መሥዋዕትነት እስከመክፈል ድረስ ያላደረገችው ነገር የለምና ስንት የሆነችበትን የደከመችበትን ዋጋ የትም በትና እንደ እንግዳ ልትሆን ፈጽሞ አይገባትም በሚገባ ያገባታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ሀገሪቱንና ሃይማኖቷን ወይም አማኖቿን ነጣጥሎ የጠራበት አንድም ጊዜ እንኳን የለም፡፡ ባለ አደራ ናት፡፡ ምነው የአራት ኪሎዎቹ አባቶች የማን የፖለቲካ ቡድን አባል ሆናቹህ ያውም ቤተክርስቲያንን በሚጎዳ መልኩ የማንን ሥራ እንደምትሠሩ የማናውቅ ይመስላቹሀልን? ይሄን ካደረጋቹህ ላይቀር ይህችን ሀገረ እግዚአብሔር የቃልኪዳን ምድር በሚጠቅም መልኩ ለሀገሪቱ አንድነት፣ ለሕዝቡ ደኅንነት፣ ለታሪክ ሕያውነት በሚበጅ መልኩ በመሰማራት የአባቶቻችንን ፈለግ በመከተል አደራ ብትወጡ ምንኛ በታደላቹህ ነበር፡፡

ከ4ኪሎዎቹ ግራ ክንፍ የአባቶች ቡድን ውስጥ ከሞላ ጎደል በአባ ጳውሎስ የተሾሙ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት “አባ ጳውሎስ ፓትርያርክ አልነበሩም ከተባለ የእኛም በእሳቸው የተሰጠን ጵጵስናም አይኖርም ማለት ነው” በሚል ሥጋዊ ስሌት የተነሣ ነው፡፡ ነገር ግን ጵጵስናን በመመረጥ እንጂ በጉልበት ሊያገኙት እንደሚችሉ ያስባሉን? ከእግዚአብሔር ካልተሰጠ ከሰው ማግኘት ይቻላልን? ከእግዚአብሔር ያላገኙትን ያልተሰጣቸውን እንዳገኙ እንደያዙ መስለው ለሰው ቢታዩ ለነሱ ምን ይጠቅማቸዋል? እራስን ማታለል እራስን መሸንገል አይሆንባቸውምን? ባንፃሩ ግን ለጵጵስና የተገቡ ከሆኑ እንደ ቤተክርስቲያን መጻሕፍት ማለትም ገድላትንና ተአምራትን ጨምሮ ስለ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ሲናገሩ ባልተገባቸው ሰዎች የተደረጉ መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንደተደረገላቸው ሰዎች እምነትና ንጽሕና ምንም እንኳ ሹመቱ ባልተገባቸው ሰዎች ቢፈጸምም በእግዚአብሔር ዘንድም ግን እንደተፈጸመላቸውና እንደሚጸድቅላቸው መጻሕፍቱ ይናገራሉ ይመሰክራሉ፡፡ የእነኝህ ጳጳሳት ሹመትም በዚሁ መልኩ የሚታይና የማያሳስብ ነገር ነበር፡፡ ለነገሩ እንዲያው ነገሩን አልኩ እንጂ ለእነዚህ አባቶች ከስደተኛው ሲኖዶስ ዘንድ ጵጵስናቸውን እንደሚቀበሉ ተነግሯቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ ሰዎቹ ግን ባልታወቀ ምክንያት እንደልባቸውና ኅሊናቸው ማደር ሳይፈልጉ ቀርተዋል ፡፡

እንግዲህ እነኝህ ሰዎች ይህንን በማድረጋቸው ቅድስት ቤተክርስቲያን የሚጋረጥባትንና የሚደርስባትን አደጋ ከምንም ሳይቆጥሩ ይህንን አድርገዋልና ቤተክርስቲያን ለሚደርስባት ችግር ሁሉ ኃላፊነትን ይወስዳሉ በሥጋም በነፍስም ተጠያቂ ይሆኑበታል፡፡ ይህ ሁኔታ ቤተክርስቲያን በምኖች እጅ እንዳለች ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ስደተኛውም ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗ ሕግ እንደሚፈቅድላቸው ሁሉ እነሱም እንደተናገሩት የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የመመሥረትና የመምራት መብት ያለን የቤተክርስቲያኗን ሕግ ሥርዓትና ቀኖና ጠብቀን አክብረን ያለነው እኛ እንጂ ለሕገ ቤተክርስቲያን ደንታ የሌላቸው ሥርዓትና ቀኖና አፍራሾች የ4 ኪሎዎቹ የግራ ክንፍ አባቶች ቡድን አይደለም፡፡ በመሆኑም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሲያርፉ በቦታቸው ሥርዓቱን ጠብቀን ቀጣዩን ፓትርያርክ እንሾማለን ብለዋልና የ4ኪሎዎቹ የግራ ክንፍ አባቶች ቡድን በሠሩት እጂግ ብስለትና ኃላፊነት የጎደለው ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስሕተት ወይም ጥፋት ውጤቱ ቤተክርስቲያን ለሁለት መከፈሏ እርግጥ ሆኗል ማለት ነው፡፡

የዚህ መዘዝ ደግሞ ከዚህ ቀደም ቤተክርስቲያን በገጠማት ተመሳሳይ ችግር ከደረሰው ጉዳት የተለየ አይሆንም፡፡ ቅዱሳን አባቶችንም ያሳሰባቸው ይሄው ነው ይህ ዛሬ የገባው የክሕደትና የድፍረት መንፈስ ዛሬ ያላደረገውን ነገ የሚያደርገው መሆኑ፡፡ ማለትም ዛሬ ሥርዓትንና ቀኖናን እንዳስጣሰ እንዳስፈረሰ አለመቅረቱ ይህ ክፉ መንፈስ አንዴ ገብቶ ቦታ ይዟልና ነግሣôልና ነገ ደግሞ እሱ በፈለገ ጊዜ የቤተክርስቲያኗን ዶግማ በይፋ ማስጣሱ ማስፈረሱ የማይቀር መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ወይም መንገድ ነው ዛሬ ከ30ሽህ በላይ ዓይነት የክርስትና ሃይማኖት ነን የሚሉ ተቋማት ሊፈጠሩ የቻሉት፡፡

የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚያሳየን ይህንን ነው፡፡ በመሆኑም የቤተክርስቲያኗ ሐዋርያዊ አስተምህሮና ርትዕትነት ዘላቂ መሆኑ ከባድ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ድረስ የከፋና የከበደ ስሕተት ነው የተፈጸመው ለነገሩ እነዚህ የግራ ክንፎቹ “የአባቶች” ቡድን እንደ ግንዛቤአቸው እምነታቸውና ዓላማቸው የሚበልጥባቸው ስለበለጠባቸው እንጂ ይሄንን አደጋ አጥተውት አይመስለኝም «ላልምልን ሰርቄአለሁ?» ነበር ያለው ሰውዬው? ታዲያ እንግዲህ ይህ ሁሉ ሲሆን እጅና እግራችንን አጣምረን ዝም ብለን ነው የምናየው? ቀን የማይመሽብህ አምላክ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሆይ ለአንዲቷ ሃይማኖት ሲሉ በስምህ መከራን ሰማዕትነትን ለተቀበሉ ቅዱሳን የገባኸውን ቃልኪዳን አስበህ ድረስልን ታደገን አሜን!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: