ከሞኝ ገበሬ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል! – አገሬ አዲስ

 

ያገራችን ብዙሃኑ ደሃ ገበሬ ባለችው ጠባብም ትሁን ሰፊ መሬት በሬ እያጣመደ ለሚያርሰው እርሻ ከበሬ ቀጥሎ ከሚያስፈልጉት መሣሪያዎች መካከል ቀንበርና ሞፈር ዋናዎቹ ናቸው።እነዚህን አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎች በወፍ ዘራሽ ከበቀለ ጫካ ወይም በቅድሚያ ከመሬቱ ላይ ከተከለው ዛፍ ያገኛቸዋል።እነዚህ መሳሪያዎቹ ካልተሟሉለት እርሻ የሚባል ነገር አይታሰብም።ብዙሃኑ ያገራችን ገበሬ ቀናና ደግ፣ተንኮል የማያስብ ሲሆን ከመካከሉ አንዳንድ ብልጦች(አታላዮች) አሉበት።ብልጦቹ ከውጣ ውረድ ይልቅ በዘዴ የሚሹትን ለማግኘት የሚያስችል ተንኮልን ይጠቀማሉ።የደጉንና የየዋሁን  ገበሬ ማሳ ለመንጠቅ፣ድንበሩን ለመግፋት፣የማይሸርቡት ተንኮልና ዘዴ የለም።ገበሬ በመሆናቸው ለደሃ ገበሬው ጥቅም የሰጡ መስለው በአጥፊ ምክርና ድለላ ንብረቱን ይነጥቁታል።የሚያርስበትን መሬት፣በሬ፣ሞፈርና ቀንበር ወይም እነዚህን የሚያገኝበትን መንገድ ሁሉ ይዘጉበታል።ከርዕሱ ብንነሳ አንዱ መንገዳቸው ለወደፊት ይጠቅመኛል ብሎ ተክሎ ፣ተንከባክቦ ያሳደገውን ለሞፈርና ቀንበር ሊሆን የሚችል ዛፍ በዘዴ አታለውና አባብለው ቆርጠው ለራሳቸው እንደሚጠቀሙበት የሚያሳየውን ተግባራቸውን ነው።በዚህ መልክ የተነጠቀው ገበሬ ሞፈርና ቀንበሩ ቢሰበር ወይም ከጥቅም ውጭ ቢሆን በቀላሉ ከደጃፉ ቆርጦ የሚተካው አይሆንም፤የግድ ጫካ ገብቶ መፈለግና መቁረጥ ተሸክሞም ማምጣት ግዴታው ይሆናል።ለዚህም ነው ከሞኝ(ከየዋህ)ገበሬ ደጃፍ ሞፈርና ቀንበር ይቆረጣል የተባለው።

በተመሳሳይ ደረጃ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ አገሩን ይወዳል፤ አገሩ  ላይ ሰላም ወርዶ፣ቀና መንግሥትና ስርዓት ሰፍኖ፣ለማየት ትልቅ ፍላጎትና ጉጉት አለው።ሌሎች አገሮች ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ወይም ለመብለጥ የማይመኝ ዜጋ የለም።አገሩን ከመውደዱ የተነሳ በስደትም አገር ቢሆን የሠራውን ሠርቶ ፣አንጀቱን አስሮ በአገሩ ላይ ንብረትና ሃብት ይዞ ተመልሶ በአገሩ ላይ የመቀመጥ ፍላጎትና ምኞት አለው።በአንጻሩም እንደ አጭበርባሪው ገበሬ በአገር ፍቅር ስሜቱ እየገቡ ፣ለበጎ ነገር ያጠራቀማትን የሚነጥቁ ጮሌዎች በየጊዜው እንደሚነሱ በተግባር ታይቷል፣አሁንም እየታዬ ነው።የኢትዮጵያዊውን አገር ወዳድነት ፣አገር ወዳድ መስለው በመግባት እየቦረቦሩት፣ንቃቱን አጨልመው፣በተሳሳተ መንገድ እየነጎደ ፣በመከራ የያዛትን ገንዘብ እያራቆቱት ሲሄዱ በመመልከት አድራጎታቸውን የሚቃወመውን ዜጋ በጥላቻ መንፈስ ፣የአገር ጠላት፣የልማትና የዕድገት ጸር እንደሆነ እያወገዙና እያስፈራሩ ጸጥ ለማድረግ ይሞክራሉ።  የሚበዘብዙት ዜጋ እንዳይሰማና እምቢ እንዳይል በማይደርሰው ጥቅም ዓይኑንና አፉን፣ጆሮውንም በመድፈን ያራቁቱታል።አገር ወዳድና ለአገር ጥቅም የቆሙ መስለው ሌላው በነሱ ስር እንዲሰለፍ ማራኪ  የልማት ዕቅድ በመንደፍ  በሆነ ባልሆነው መንገድ ይዘርፉታል፣ያታልሉታል።የዋሁ አገር ወዳድ በቃላት ከመታለሉም በላይ ከአንዱ ወገኑ ተነጥቆ ለሚሰጠው ቁራሽ መሬት እራሱን ሲሸጥ ማየቱ ይዘገንናል።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ከድህነት ወጥታ ከሌሎች አገሮች በልጣ ለማየት ይሻል።ያ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድ፣ዴሞክራትና በሕግ ስር የሚያድር ፣በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው።ማንኛውም ቀና አሳቢ ኢትዮጵያዊ የልማት እቅዶች በተግባር እንዲገለጹ የማይሻ የለም።የዓባይም ወንዝ ተገድቦ ለአገር ጥቅም እንዳይውል የሚቃወም የለም።ካለ የኢትዮጵያ ጠላት ብቻ ነው።ግን ዓባይ እንዴትና በምን መልክ ለጥቅም ይዋል የሚለው ጥያቄ ተገቢ ሲሆን ያንን የሚጠይቅ እንደጠላት የሚያስቆጥር ጥፋት አይደለም።ተገቢ ጥያቄን ጥፋት አድርገው የሚቆጥሩ ከዓባይ ግድባ በስተጀርባ ለመጠቀምና የዓባይን ግድብ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚሽቀዳደሙ አጭበርባሪዎች ብቻ ናቸው።

የሕወሃት/ኢሕአዴግ ቡድን በዓባይ ግድብ ሳቢያ በውጭ አገርና በአገር ውስጥ በማስገደድና በማታለል ከኢትዮጵያውያን ብዙ ገንዘብ ሰብስቧል፤ቦንድ እየሸጠ፣በእርዳታ፣በብድር፣መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ሰብስቧል፣አሁንም እየሰበሰበ ነው።ለባለገንዘቡ ግን ምን ያህል እንደሰበሰበ፣ምን ያህል እንደወጣና እንደቀረ የሚገልጽ ወቅታዊ ሪፖርት አይሰጥም።በቦንድ ግዢ የተሳተፈውም ኢትዮጵያዊ ደፍሮ አይጠይቅም።በሚሰጡት የማታለይ ጥቅማ ጥቅም አፉን ሸብቦ፣አውጣ ሲሉት እያወጣ፣ደግፍ ሲሉት እየደገፈ፣የጥፋት ተባባሪ ሆኗል።አሁንም እየሆነ ነው።

በየጊዜውና በየቦታው እንደሚያደርጉት አሁንም በመጭው ቅዳሜ (june 25/2016) በኔዘርላንድ፣ ሮተርዳም ከተማ የሃያአምስተኛ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን ለማክበርና የፈረደበትን የዓባይ ግድብ ቦንድ ለመሸጥ ስብሰባ ጠርተዋል።በዚህ የሚሳተፉትን ወገኖቼን ፍላጎታቸውን ባከብርም፣የሚያዋጡት ገንዘብ የት እንደሚውል፣እስከዛሬስ የተዋጣው፣የተሰበሰበው የሕዝብ ገንዘብ ከምን እንደደረሰ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው እንዲጠይቁ ሲሆን በተጨማሪም የሚሰጡት ገንዘብ በውጭ አገር ባንክ ለባለሥልጣኖቹ ተከፋፍሎ እንደሚቀመጥ፣የነሱ በየቀኑ እያተመ በሚረጨው ዋጋ ቢስ የኢትዮጵያ ብር(ያግኙት አያግኙት ዋስትና የለም)የሚቀየር መሆኑን እንዲገነዘቡት ነው።በተጨማሪም በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን በቀውስና ውጥረት ላይ በመሆኑ  በአገሪቱ ላይ ለደረሰው ስብራትና ለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ የሆኑት ባለሥልጣኖቹን በሹመት ስም በያገሩ እያሶጣ ነው።በዓባይም ሆነ በቤት ግንባታና  በሌላ የልማት ዕቅድ ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ በነዚሁ ባለሥልጣኖች ካዝና ገብቶ  እንደሚቀር ሊያውቁት ይገባል።እንደ የዋሁ ገበሬ ከምትኖሩበት አገር ድረስ እየመጡ የሚበዘብዟችሁን ዘራፊዎች አትመኗቸው።ነቄ! በሏቸው።

ለማወናበድና ለማጭበርበር የሚጠቀሙበት ጥሪ ይህን ይመስላል

ተባብረን ዘራፊዎችን እናሶግድ!!!

አገሬ አዲስ

1E

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s