ሳዑዲ አረቢያ የአባይን ወሃ በሱዳን ምድር መጠቀም መጀመሯን ተከትሎ ግብፅና ሱዳን መወዛገብ ጀመሩ

ሳዑዲ አረቢያ የአባይን ወሃ በሱዳን ምድር መጠቀም መጀመሯን ተከትሎ  በአባይ የውሃ ኮታ ላይ ግብፅና ሱዳን እየተወዛገቡ ነው። የውዝግቡ መነሻ ሳዑዲ አረቢያ የአባይን ውሃና የሱዳንን ሰፊ የእርሻ መሬት ተጠቅማ እህል በማምረት ህዝቧን ለመቀለብ ያደረገችውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የሱዳን ምክርቤት የ99 ዓመቱን ሊዝ በማፅደቁ ነው። ለረዥም ጊዜ ሲያወዛግብ የቆየውን ይሄንኑ የሊዝ ጉዳይ ሰኞ እለት የተሰበሰበው የሱዳን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል። ይሄው ሰፊ የእርሻ ልማት የአባይን ውሃና የሱዳንን ሰፊ መሬት የሚጠቀም ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋነኛ ማዕከልም ሰቲትና የላይኛው አትባራ የሚባሉ አካባቢዎች መሆናቸውን የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ ያመለክታል። ሁለቱ አገራት በቀጣይ የሚያከናውኗቸውን ሰፊ የግብርና ፕሮጀክቶች ዝርዝር ጉዳይ በተመለከተ ለሶስተኛ ወገን እንዳይገልፁ በስምምነታቸው ማዕቀፍ የተካተተ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። ረቂቅ ስምምነቱ ለፓርላማው በቀረበበት ወቅት አንዳንድ የፓርላማ አባላት የሊዝ ጊዜው ከመርዘሙ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ከማንሳት ባለፈ ተቃውሞ ያላሰሙ መሆናቸው ታውቋል። አንዳንድ የፓርላማ አባላት ሀሳባቸው ተቀባይነትን አያግኝ እንጂ የሊዝ ጊዜው ከ20 እስከ 25 ዓመት አጥሮ ከዚያ በኋላ ኮንትራቱ እንደየአስፈላጊነቱ እየተራዘመ የሚሄድበት ሁኔታ ጠይቀው ነበር።

ሱዳንና ግብፅ እ.ኤ.አ በ1959  ኢትዮጵያን ሳያካትቱ በተፈራረሙት የአባይን ውሃ በኮታ የመከፋፈል ስምምነት መሰረት ግብፅ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ የውሃ ኮታን የወሰደች ሲሆን ሱዳን በአንፃሩ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን የውሃ ኮታን እንድትጠቀም መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር። ሱዳን ከአቅም ጋር በተያያዘ በዚህ ስምምነት መሰረት የተመደበውን ኮታ ሙሉ በሙሉ ሳትጠቀም የቆየች ሲሆን የአሁኑ የሳዑዲ አረቢያ የ99 ዓመት የሊዝ የግብርና ልማት የሱዳንን ኮታ ከነበረው ስምምነት በላይ ከፍ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋትን በግብፆች በኩል ያሳደረ መሆኑን የአልሞኒተር ዘገባ አመልክቷል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ሙያዊ ትንታኔን ያቀረበው አልሞኒተር የቀድሞውን የግብፅ የውሃና የመስኖ ሚንስትር ሞሀመድ ናስር ኤልዲን አላምን ያነጋገረ ሲሆን፤ እንደባለሙያው ዘገባ በ1959ኙ ስምምነት መሰረት ሱዳን ወደ ተመደበላት18 ነጥብ 5 ቢሊዮን የውሀ ኮታ እየተጠጋች በመሆኑ ከዚያ በኋላ የሚኖረው የውሀ አጠቃቀም የግብፅን የውሀ ፍጆታ አልፎ የሚነካ መሆኑን ገልፀዋል። ይህም የ1959ኙን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል። የሱዳንን ውሃና ሰፊ መሬት በመጠቀሙ ረገድ ሳዑዲ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ሀብታም አረብ አገራትም ጭምር እያንዣበቡ ሲሆን ግብፅ ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተች መሆኑ ታውቋል። ሁለቱ አገራት እስከዛሬ ድረስ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ በትብብርና በስምምነት ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ግን ልዩነቶችና እርስ በእርስ መጠራጠር እየታየባቸው ነው።

በዚሁ ዙሪያ አስተያታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸውና በአባይ ዙሪያ ሰፊ ምርምርን ያደረጉት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ኢትዮጵያ፤ በአባይ ውሀው ኮታ ዙሪያ ኢትዮጵያ አስተያየት መስጠት ማለት የ1959ኙን ስምምነት እንደመቀበል የሚያስቆጥር መሆኑን ገልፀው፤ ይሁንና በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያ የራሷን የቅርብ ክትትል ማድረግ ያለባት መሆኑን ግን አመልክተዋል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s